የካቲት ሲብት ልቤን እንደመሸበር የሚያደርገው የሆነ ስሜት መጥቶ ይሞላዋል። የሆነ ነገር ሊያሳጣኝ የመጣ የሚመስለኝ ነገር ያለ ይመስል ከእግር እስከ ራሴ ይወረኛል፤ ከአስራ ምናምን አመት በፊት ያጣሁትን እያሰብኩ የካቲት ሲብት ሆዴ ይሸበራል። የካቲት ለኔ ጭንቄ ነው። ምንም እንኳን የካቲት የከተተውን ያህል ታሪክ በእምዬ ኢትዮጵያ ባይሰራም፣ እኔ ልብ ውስጥ ግን ትንሽ ጫን የሚል ስሜት ይሰማኛል።
ለማናኝውም እኔን የጨናነቀኝን ጉዳይ ወደ ጎን ልተውና ይህ ወር ለእማማ ኢትዮጵያ ልዩ ወር ነው፡፡ ምክንያቱም የካቲት ወር እና ኢትዮጵያ የተሳሰሩባቸው በርካታ የታሪክ ክስተቶች አሉ፡፡ ምን ምን ናቸው ብላችሁ እንደምትጠይቁኝ በማሰብ፤ የታሪክ ክስተቶቹን እንዲህ በወፍ በረር በጥቂቱ ልጠቃቅስ ወደድኩ።
አንዳንድ ወራት ከአገራት ታሪክ ጋር ለመተሳሰራቸው ይህ ነው የምንለው ምክንያት ባናነሳም ግጥምጥሞሹን መዘከር የግድ ይለናል።
በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ደጋማ ክርስቲያኖች ከሙስሊም ሱልጣኔቶች ጋር ተደጋጋሚ የእርስ በርስ ጦርነት ያካሄዱበት፣ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት ወርኃ የካቲት መሆኑ ከታሪክ መዝገብ ውስጥ ያነሳነው አንደኛው ታሪክ ነው።
የየካቲት ታሪክ በዚህ አያበቃም በሌላም በኩል የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት በእማኝነት ከከተባቸው ታሪኮች መካከል አንዱ ነው።
የካቲት ሲነሳ የአፍሪካዊያን ኩራት የኢትዮጵያ ደግሞ የምንጊዜም ምልክት የሆነው የጥቁሮቹ መኩሪያ የአድዋ ድል የየካቲት ፍሬ ነው። በእምዬ ምኒልክ ‘ማሪያምን’ በሚል መሃላ ተደግፎ ለቀረበው ጥሪ ሰሜን የለ ደቡብ፣ ምስራቅ የለ ምዕራብ ሁሉም የሀበሻ ዘር ባንድ የከተተበት፤ ወራሪውን ሊያጠፋ የተመመው በዚህ ድንቅ ወር ነው።
የተሰጠን ሕይወት ዛሬ በነፃነት እንድንቆም ያደረገን ሰው የተከፈለበት መሆኑን እንዳንዘነጋ የሚያደርገን፤ ስንት ወገን የወደቀባት በነፃነት ምድር አፍ አውጥታ ብትናገር፤ አድዋ ዛሬ ላይ ብትመሰክር ዛሬ ቀና ብሎ ስለመሄዳችን ምክንያት የሆነ የቀኝ አገዛዝ በትር እንዳያርፍብን የሆነው፤ በትናንቱ የአድዋ ድል መሆኑን ለአፍታ መዘነጋት አይገባንም።
ዛሬ መከፋፈላችንን እየተመለከትን ዋጋ ያልተከፈለባት አገር ያለችን ለሚመስለን በደምና በአጥንት የተገዛን መሆናችንን እንዳንረሳ የሚያደርገን የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ አፍሪካ፣ የእምዬ ኢትዮጵያ አንፀበራቂው ድል የአንድነታችን ገመድ ሚስጥርን ለመዘከር ከዚህ ወር መባቻ የተሻለ ቀን መቼም አይኖርም።
እብሪት ልቡን የደፈነው የዝያድ ባሪ ጦር እምዬ ላይ የጭካኔ ጅራፉን ሊያሳርፍ በገሰገሰበት ወቅት ልማደኛው ጥቁር አንበሳ በድል አንገቱን አስደፍቶ የመለሰበት የካራ ማራው ገድል ሌለኛው የታሪክ ምዕራፋችንን ከትቦ ካስቀመጠው ደማቅ ታሪክ መካከል የየካቲት ወር ካበረከተለን የጉልሁ ታሪክ አካል አንዱ ነው።
ታሪካችን በሙሉ የጦርነት እስኪመሰል ብዙ የጦር ወሬዎችን ማንሳት ቢቻልም ለአሁኑ ይህ የድል ዜና ላይ አረፍ ብዬ ከታሪክ ውስጥ በመዘዝኩት ሰበዝ በሌላ በኩል በኪነ ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኃ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ልናገር።
ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ ዕረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 እንደ ነበር ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም ሆኖ ከታሪክ ድርሳናት መካከል ተመልክቻለሁ።
ከዜና ዕረፍቱም በሻገር ወርኃ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አጼ ሠርፀ ድንግልን፣ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው” የሚባሉትን አጼ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን ማንገሱ የሚታወሰው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ስልጣን የለቀቁት በየካቲት ወር ነበር፤ የቅርብ ጊዜ የታሪካችን አካል የሆነው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ወንበር በቃኝ ያሉት በየካቲት ወር መሆኑም አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በኢህአዴግ ሊቀ መንበርነት ብቅ ያሉት በዚሁ ታሪከኛ ወር በየካቲት ወር ነበር። ታሪክ መዛዡን ካገኘ መግተለተሉ አይቀርምና ገታ አድርጌ የዘንድሮው የካቲትስ ምን አስመዝግቦ ያልፍ ይሆን? ብዬ ልጠየቅ? ሌላ ጥያቄ የዘንድሮው የካቲት ምን ይዞ ቢመጣ ደስ ይላችኋል ልበል? ጭንቅ በሚል ስሜት ውስጥ ይሄን መጠየቅ ይከብዳል።
እኔ እናት ነኝ ልጆቼ የሚያድጉበት ንፁህ መስክ እሻለው፤ የአስክሬን ሽታ የማይሸትበት፤ የባሩድ ጭስ የማይተነፍግበት፤ ንፁህ የሰላም አየር የምተነፍስበት፤ በኩራት በድፍረት ልክ የአድዋ አባቶች እንዳጎናፀፉን ድል ቀና ብዬ በሰው ፊት የምቆምበት አይነት ድፍረት የሚያገናፅፈኝ ታሪክና ሀገር ያሻኛል። የካቲት ችግሩን ሰላም ማጣቱን ክፉ ክፉውን ከቶ ወደ ሰላም እንዲያሻግረን እመኛለሁ።
በህልሜ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ ለማየት የሚያስችለን ዘመን ያመጣልን ዘንድ አመኛለሁ። እርስ በእርስ መነቃቀፉ መነቋቆሩ አብቅቶ አዲስ ፀሃይ በእምዬ ላይ የሚታይበት ዘመን ያመጣልን ዘንድ አሁንም እመኛለሁ።
ይሄኛው የካቲት ታሪካችን አይቶት የማያውቀውን የመደማመጥ የመመካከር ልምምድ፤ የእርቅ የፍቅር የሰላም ልምምድ የምንለምድበት፤ የጦር ወሬ አብቅቶ በይቅርታ አዲስ ቀን አዲስ ተስፋ ለአዲሱ ትውልድ የምናቀብልበት፤ ተበተኑ ፈረሱ ካሁን በኋላ አልቆላቸዋል ለሚሉን እኛ እንዲህ ነን ብለን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ብሩሁ ነገ የምንሻገርበትን ታሪክ ይከትብልን ዘንድ እመኛለሁ።
የዘንድሮው የካቲት የበረከት ዝናብ የሚዘንብበት፤ የተትረፈረፈ ምርት የምናገኝበት እንዲሆንልን አመኛለሁ፤ በዚህኛው የካቲት ክፋት ችግራችን ታጥቦ፤ ያለ ደም ያለ እንባ የተቦካ አፈር የምንረገጥበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ ተመኘሁ። የአያቶቻችን፤ የአባቶቻችን፤ የኛም ሆነ የልጆቻችን አገርን በሰላም በተስፋ የሚያሻገር ድልድይ የሆነ ወር ይሰጠን ዘንድ ፈጣሪን እየተማፀንኩ የዛሬውን ጽሁፌን አበቃሁ።
ብስለት ዘ ኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014