ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኗ አስረጂ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ይታወቃል:፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለያዩ ጊዚያት የተገኙት የሉሲ፣አርዲና ሰላም ቅሪተ አካል በቂ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ ከሰሞኑ ስካይ ኒውስ የተሰኘው ድረገፅ ባወጣው ዘገባ መሰረት በ15ኛው ክፍለ ዘመን ተቀብሮ የነበረ የበርካታ ህፃናት ቅሪተ አካል መገኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ቅሪተ አካሉ የተገኘው ቀደም ባለው ጊዜ የመስዋእት ስነስርአት በሚደረግበት አካባቢ እንደሆነና ቅሪተ አካሎቹ በመስዋእት ስነስርአቱ ልባቸው የተወገደ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ቦታም የሶስት ጎልማሳ ሰዎች፣ የ200 እንስሳትና ከ141 በላይ የህፃናት ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል፡፡ ሳይንቲስቶች በአካባቢው ቁፈራ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ2011 መሆኑን ዘገባው ያመለከተ ሲሆን ፣ ከዘጠኝ አመት በኋላም ቅሪተ አካሎቹን ማግኘት ችለዋል፡፡
አብዘኛዎቹ ህፃናት በጊዜው ደረታቸው በስለት ተወግቶ እንደሞቱና ልባቸውም እንደተወሰደ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው ጥሩ ያልሆነ የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱን የሀገሪቱ ጠንካራ መንግስት ኢኮኖሚ፣ፖለቲካና ርዕዮታዊ መረጋጋት በመምታቱ ከዚህ መጥፎ ሁኔታ ለመላቀቅ ግብር ይሆን ዘንድ የተከፈለ መስዋትእነት እንደሆነ ማስረጃዎቹ ይጠቁማሉ ሲሉም ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል፡፡
የህፃናቱ ቅሪተ አካል ከዘጠኝ አመት በፊት ሁዋንቻኪቶ በተሰኘ ቦታ ቁፈራው የተጀመረው የአካባቢው ነዋሪዎች ከአፈር ውስጥ የወጣ አፅም ከተመለከቱ በኋላ እንደሆነም ታውቋል፡፡ 700 ስኬዬር ሜትር ስፋት ያለው ቁፋሮ ከተካሄደ በኋላ ሳይንቲስቶቹ የህፃናቱን ቅሪተ አካል ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ከቁፋሮ ቦታው ውጪ ሰዎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች የተገኙ ያልተሟሉ ቅሪተ አካላት የሟቾቹን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም ሳይንቲስቶቹ ፍንጭ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል በተሰሩ ጥናቶች መሰረት የህፃናቱ ቅሪተ አካል በጨርቅ የተጠቀለለና የጥቂቶቹ ደግሞ ፊታቸው ቀይ ቀለም የተቀባና ጭንቅላታቸው አካባቢም ልብስ እንዳለ ማረጋገጣቸውን ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የህፃናት ቅሪተ አካላት ከባህር ዳርቻ 350 ሜትር ራቅ ብለው የቀበሩ ሲሆን፣ እንስሳቶቹ ደግሞ ከተራራ አቅራቢያ ተቀብረው የተገኙ መሆናቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡ ፡ ህፃናቱ መስዋእት የተደረጉት ከባድ ዝናብ ጎርፍ አስከትሎ አካባቢውን በአሽዋ ስለሸፈነው ሳይሆን አይቀርም ሲሉም ሳይንቲስቶች ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ከባድ ዝናብ የሚጥልበትና በየጊዜውም ህፃናት በመስዋእትነት የሚቀርቡበት ቢሆንም፣ አሁን የተገኘው በርካታ አፅም በወቅቱ እጅግ ከፍተኛ የአየር ንብረት መለዋወጥ ተከስቶ ሳይሆን እንዳልቀረ ሳይንቲስቶቹ አክለው ገልፀዋል፡፡ አሁን በፔሩ የተገኘው በርካታ የህፃናት ቅሪተ አካል ቀደም ሲል በጅምላ ተገድለው በማእከላዊ ሜክሲኮ ከተገኙት የ42 ህፃናት ቅሪተ አካል ቁጥር ብልጫ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በአስናቀ ፀጋዬ