አዲስ አበባ፡- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባለፉት ዓመታት የሕግና የአሠራር ክፍተቶች ታይቶባቸዋል በተባሉ አንድ ሺህ 582 ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታወቀ።
ተቋሙ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ባካሄደው አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ እንዳስታወቀው እነዚህ ተቋማት ባለፉት ዓመታት ከተገልጋዩ ቅሬታ የቀረበባቸውና የአሠራር ክፍተቶች የታየባቸው ናቸው።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በምክክሩ ላይ እንደገለፁት ቁጥጥሩ ከተካሄደባቸው ተቋማት መካከል የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ዘጠኙ ክልሎች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት ተቋማትና ሌሎች የልማት ድርጅቶች ይገኙበታል።
የቁጥጥር ሥራዎቹ የሚካሄዱት ጥብቅ የአሠራር መመሪያ በማዘጋጀት እንደሆነ የገለፁት ዋና ዕንባ ጠባቂው በሚሰጠው ግብረ መልስ መሰረትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማካሄድ የጋራ መግባባትና መፍትሄ ላይ ለመድረስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል። እንደ ዶክተር እንዳለ አገላለፅ በቅርቡ ቁጥጥር ከተካሄደባቸው መካከል ጤና ተቋማትና የመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት፣ የቤቶች ኤጀንሲ፣ የኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያና ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች የታየባቸው 16 ተቋማት ይጠቀሳሉ።
ዶክተር እንዳለ አክለውም በተቋሙ የቁጥጥር ሥራው ከተካሄደ ወዲህ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ወጥ የሆነ የመታወቂያ አወጣጥ እንዲኖር በመጠቆም፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ አደረጃጀቱን ወደ ኮርፖሬሽን እንዲለውጥና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲያሻሽል ተጽዕኖ ለመፍጠር ተችሏል። በትራንስፖርት ሚኒስቴር ላይ በተደረገ ቁጥጥርና በተሰጠ ግብአትም አገራዊ ፖሊሲ እንዲወጣ፣ አማራጭ የከተማ ታክሲዎች እንዲበራከቱና በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት እንዲገኝ ጭምር ተደርጓል።
ተቋሙ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና ውሣኔ ላይ እንደማተኮሩ አስተዳደራዊ በደሎችን በመለየት ጥፋቶች እንዲታረሙ ለማድረግ ይሠራል ያሉት ዋና ዕንባ ጠባቂው ቀዳሚ ምርመራው ከተካሄደ በኋላ በተሰጠው ግብአት መሰረት በአግባቡ ስለመከናወኑ የድጋሚ ቁጥጥር ተግባራት በጥልቀት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር እንዳለ አገላለፅ አብዛኞቹ ተቋማት ስለተገኘው የለውጥ ውጤት ሪፖርት ለማድረግ ተባባሪዎች ቢሆኑም የዛኑ ያህልም ጥቂት የማይባሉት ለአሠራሩ ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም። ለአብነትም የሸቀጦች ዋጋ መናርና አሉታዊ ተጽዕኖ አስመልክቶ ለመፍትሄው ባለመተ ባበር ንግድ ሚኒስቴር ክፍተት ከተስተዋለበት መሥሪያቤቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል ብለዋል።
በመንግሥት ተቋማት አገልግሎትና ውሣኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደል ለመለየት በተደረገው ጥረትም 85 የሚሆኑ አገር አቀፍ ጥናቶች ተካሂደዋል። ተቋሙ ከውጭ አገራት ባገኘው ተሞክሮ አስራአንድ ሞዴል የህፃናት ፓርላማዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ ህፃናት ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ዕድል መፍጠሩንም ዋና ዕንባ ጠባቂው ተናግረዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንኡስ አንቀጽ 15 የህዝብ ዕንባ ጠባቂ እንዲቋቋም በተደነገገው መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 211/92 ተቋቁሞ በይፋ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ