ወዳጅነት ጥልቅ ነው፤ ወንድማማችነት ደግሞ የማይበጠስ ቋጠሮ፤ ኢትዮጵያውያንም ይሄው ወዳጅነታቸው ጥልቀቱ፤ የወንድማማችነታቸውም ቋጠሮው ጥብቀት በጉልህ የሚታይባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች በርከት ያሉ ናቸው። በደስታ ኀዘናቸው፣ በከፍታና ዝቅታቸው፣ በሰላምና በጦር ድሎቻቸው፣… በሁሉም ገጾቻቸው የአንድነትና የመተባበር ታሪካቸውን በማይደበዝዝ ቀለም ከትበው አልፈዋል።
እነዚህ የታሪክ ገጾቻቸው ደግሞ ሁሉም በኢትዮጵያ ልዕልና፣ በኢትዮጵያዊ ከፍታ ላይ ተመስርቶ የእንችላለን ሥነልቡናን በግልጽ ያሳየ፤ የአትችሉም እሳቤትን የሰበረና የእናውቅላችኋለን ቀንበርን የመሸከም ፍላጎትም ሥነልቡናም ያለመላበስን ሰብዕና ለዓለም ያሳዩባቸው ነበሩ። እነዚህ የአብሮነትና ትብብር ገጾች በጦርነትም፣ በወንድማማችነት መተጋገዝም የሚገለጹ ዘርፈ ብዙ ተባብሮ የማሸነፍና ፈተናዎችን የመሻገር ድሎች ናቸው።
ለአብነት፣ ከሦስት ሺህ የዘለለ ታሪክ ክምር ውስጥ ከቅርቡ የታሪክ ገጽ ለመጥቀስ ያህል እንኳን የኢትዮጵያውያን የከፍታና የእንችላለን ሰብዕና መገለጫ ከሆነው የአድዋ ተራሮች ገድል የጦር ግንባር ገጽ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚገጥሟትን ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ሰደድ እሳትና ሌሎችም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችንም ሆነ አደጋዎቹ ያስከተሉትን ጉዳት ተባብረውና ተጋግዘው ሲሻገሩ ያሳለፉባቸው በርከት ያሉ የታሪክ ገጾች አሏቸው።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያን የወንድማማችነት ትብብርና አብሮነት ጉዞ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ያህል ተፈትኖም፣ የብርታቱ ክል ተገልጦም የሚያውቅ አይመስለኝም። ይህ ለምን ሆነ የሚል ካለ ደግሞ ነገሩ እንዲህ ነው። በአንድ በኩል የውጭ ኃይሎች ተልዕኮን ተሸካሚዎችና የረዘሙ እጆቻቸው የፈጠረብን ብርቱ የአንድነትና የወንድማማችነት ቋጠሮን የመበጠስ የስልሳ ዓመታት የሴራ ዘር ፍሬ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በዓለማችን የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረብን የድርቅና ጎርፍ በርከት ብሎ የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ነው።
የመጀመሪያው ጉዳይ ተደጋጋሚ ሙከራቸውን አክሽፎ ምኞታቸውን ባዶ ያስቀረባቸው የኢትዮጵያ ሕብረትና አንድነት እንደ እሳት የገረፋቸው የምዕራቡ ዓለም የቅኝ ገዢነት ቅዠት ያሰከራቸውን አገራት ተልዕኮ ተቀብሎ በጫካ ተወልዶ ጫካ ያደገው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የፈጠረብን ችግር ነው። ይሄም የሽብር ቡድኑ በ17 ዓመታት የጫካ ኑሮው፤ እንዲሁም በጋላቢዎቹ አገራት ተሸካሚነት ወደ መሃል አገር ዘልቆ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ሰርቼባቸዋለሁ ብሎ በተማመነባቸው የከፋፋይነት የሴራ ተግባራት ምክንያት የፈጠረው ቀውስ ነው።
ይህ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያውያንን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ለተጠጋ ጊዜ በከፋፋይነት ሃሳቡ ማዕቀፍ ውስጥ ለማስገባት ሰርቷል። ምኞቴ ግቡን መትቷል ባለባቸው ጊዜያትም ሙከራዎችን በማድረግ የትስስር ገመዱን የመላላት ልክ ለመፈተሽ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ ሙከራው የራሱ መጥፊያ ሆነበት። ምክንያቱም በዚህ ቡድን እንዲከፋፈሉ ሆነው ለተናጠል ጥቃት የተጋለጡ መስሎ የተሰማቸው ኢትዮጵያውያን ቡድኑን ለማጥፋት በአንድ ተሰልፈው በፈጠሩት ማዕበል ከስልጣኑ አውርደውና ከመሃል ገፍተው ወደተፈጠረበት ዋሻ መለሱት።
በዚህኛው ምዕራፍ የአባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውን የገለጡት የዛሬዎቹ ሕብረ ብሔራዊዎቹ ኢትዮጵያውያን፤ ሌላ የሕልውና ፈተና ገጠማቸው። ሆኖም መጀመሪያ፣ የሽብር ቡድኑ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን (የሰሜን ዕዝን) አጥቅቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያደረገውን ቅዠት በተባበረ ክንዳቸው አምክነዋል፤ ሁለተኛም ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ተሰጥቶ ከትግራይ ክልል መከላከያ ሰራዊቱ መውጣቱን ተከትሎ በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን የበቀል ወረራ ዳግም ቀልብሰው ወደ ጎሬው በመመለስ የማይዋዥቅ አንድነታቸውን አረጋግጠዋል። ይህ ተግባሩ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሊወርረው የመጣንም ሆነ ከውስጥ ሊወጋው የተነሳን ባንዳ አደብ ለማስያዝ በአንድ የመቆም የቆየ እሴቱን፤ ለጠላት ዝቅ ብሎ ያለመታየት ሰብእናውን፣ የመቻል አቅሙን ዳግም እንዲገለጥ አስችሎታል።
የአገርን ክብር ከማስቀጠል እና የራስን ልዕልና አስጠብቆ ከማኖር የትብብር ገድሉ ባለፈ፤ በፈታኝና መተጋገዝን በሚጠይቁት ክስተቶች ላይም ወንድማማችነትን ያረጋገጡበትን በርካታ ተግባራት አከናውነዋል። በእነዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት በጎርፍ፣ በድርቅ እና በጦርነት ጉዳት ምክንያት የተፈጠሩ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ከመጠገን አኳያ ኢትዮጵያውያን ሕያው የሆነ የፀና መተሳሰባቸውን አሳይተዋል።
ይህ ምናልባት እንደ ጦር ሜዳ ውሎ ወኔና ጀግንነትን ብቻ የሚጠይቅ አልነበረም። ከፍላጎትና መሻት ከፍ ያለ የማድረግ አቅምን ይፈልጋል። ለመስጠት የሚሰጡት ሊኖር ግድ ይላል። ይሄን የሚገነዘቡት ዓለምአቀፍ የረጂ ተቋማትና አገራት ደግሞ እነዚህን አጋጣሚዎች ተጠቅመው በሚያደርጓቸው የሰብዓዊ ድጋፎች ምክንያት በጦር ግንባር ያጧቸውን ድሎች በድጋፍ ስም እጅ ጠምዝዘው ለማግኘት እድል የሚሰጣቸው መሆኑን ያምናሉ።
እናም ከድጋፍ ጋር ጥቅምን አስተሳስረው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። ይኸኔ የመጡበትን ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጎን ብለው ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት፤ ጥቅም አስጠባቂ ባንዳዎቻቸውን አቅም ለማጎልበት ይተጋሉ። ይሄን ያዩና የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከቀድሞው በተለየ መልኩ በእነዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት “እርዳታ ለሰብዓዊነት እንጂ ለእጅ መጠምዘዣ ከሆነ በአፍንጫችን ይውጣ” በሚል ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅን ዓላማ ያደረገ ሥራ ውስጥ ገቡ።
በዚህም በምግብ ራስን መቻል ቅድሚያ ተሰጠው፤ እናም በቆላማ አካባቢዎች ጭምር በመስኖ ስንዴ ማምረት ተጀመረ። ይሄም ኢትዮጵያ ከውጭ ጥገኝነት ራሷን ማላቀቅ እንደምትችል ያመላከተ ውጤት ተገኘበት። አሸባሪው ቡድን በቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን 70 በመቶ ድጋፍ በመንግሥት አቅም ለማቅረብ አስቻለ፤ በሌሎችም ድርቅና ጎርፍ በጎዳቸው አካባቢዎች ላይም የውጭ ድጋፍን ሳይጠብቁ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አግዟል።
ይሁን እንጂ ይሄ በራስ አቅም ሁሉን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አሁንም ለጠላቶቻችን እረፍት አልሰጣቸውም፤ እናም ቀደም ብለው በፈጠሩት ሰንሰለት ታግዘው የሽብር ቡድኖችን በማጠናከር እና የተራዘመ የዜጎች ችግርና መከራ እንዲፈጠር በማድረግ የውስጥ አቅምን ማዳከም ዋና ስራቸው ሆነ። መንግሥት በትግራይ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው የሚል የፈጠራ ወሬን በማሰራጨት ጭምር ለሌላው ሕዝብ ትኩረት እንዲነፈግና ቅሬታ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግም ያላሰለሰ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ጀመሩ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ለሽብር ቡድኑ የጥፋት አቅም የሚፈጥር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረስ የታገሉት እነዚህ የውጭ ረጂ ተቋማትና አገራት፤ በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝና ሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች በድርቅና በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉና ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን መመልከት አልፈለጉም ነበር። ይልቁንም አፋር በግፍ ተፈናቅሎ የሚበላውም የሚጠለልበትም ሳይኖረው በአፋር ምድር ለሽብርተኛው ቡድን አቅም መፍጠሪያ የሆኑ በእርዳታ ስም የሚገቡ በርካታ ተሽከርካሪዎች ነበሩ። አማራው በግፍ ተፈናቅሎ የድጋፍ ያለህ እያለ ድምጹን ሲያሰማ፣ አማራው እየተራበና እየታረዘ መመልከት ያልቻሉት እነዚህ ኃይሎች በአማራ በኩል ከሽብር ቡድኑ አጋዥ የሆኑ የድጋፍ ዳቦ ስም የተሰጣቸውን እርዳታዎች ማድረስ አልቻልንም የሚል ክስ ያቀርባሉ።
ይባስ ብለው በረሃብ የሚሞተው፣ በመጠለያ እጦት የሚሰቃየው በሽብር ቡድኑ የተፈናቀለው የአማራም ሆነ የአፋር ሕዝብ (በሰብዓዊ መብት ስም የሚቆምሩባቸው ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ) ድምጽ ሳይሰማቸው፤ እየተራቡና እየታረዙ ችግራቸውን ችለው የሚሄደው እርዳታ ለወንድም ሕዝብ ነው ብለው ሲያዩት ረሃባቸው እየተቀሰቀሰም ቢሆን በአይናቸው እየተከተሉ የሚሸኙትን እርዳታ የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ምክንያት መኪኖች እንዳያልፉ ባደረገ፤ በአውሮፕላን ድጋፍ እናድርስ ብለው ላንቃቸውን ከፈቱ።
በሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ላይ በድርቅ ምክንያት አያሌ ሰዎች ሲፈናቀሉ፤ በየቦታው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳ ሲሞቱ፤ ሕጻናትና ሴቶች በረሃብ ሲጠበሱ፣ ልጆች ወተት አልባ የእናታቸው ጡት ላይ ተጣብቀው ጠብ የሚል አጥተው በደከሙ አይኖቻቸው ረሃባቸውን የሚያስታግስ ነገር ሲፈልጉ፤ … መመልከትና ችግሮቻቸውን ማድመጥ ያልቻሉ የሰብዓዊነትን ካባ የደረቡ አካላት፤ ለሽብር ቡድኑ ሕልውና መቆየት ቀን ከሌት ሲታትሩ ታዩ።
ይሄንና ሌሎች መሰል ጥቃቶችን መሸከም ያቃተው ኢትዮጵያዊ ታዲያ፤ ይሄን መሰል ግፍና መገፋት የተፈጠረው ሕዝቡ ለእነሱ አልንበረከክም፣ ሆዴን ለሚሞላ ስንዴ ስል ክብሬን ለመንጠቅ ለሚታገሉኝ ኃይሎች እጄን አላስጠመዘዝም ባለው ሕዝብ ላይ መሆኑን ተገነዘበ። ችግሩን ተገንዝቦም ዝም አላለም። እናም ለወገኔ መድረስ የሚችል ከእኔ በላይ የለም ብሎ ተነሳ። ሁሉም ከሌለው ላይ ቀንሶ ለወንድም እህቱ ለማጋራት የሚያስችለውን ሥራ ጀመረ።
አዲስ አበቤው በአማራ እና አፋር በአሸባሪው ቡድን በግፍ ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖቹ የሚችለውን ይዞ ቦታው ድረስ ሄዶ ጠየቃቸው፤ አጋርነትና ወንድማዊ በሆነ ልብ አጽናንቶ፣ አጉርሶና አልብሶ ተመለሰ። ወደ ሶማሌ እና ሌሎች በድርቅ ወደተጎዱ አካባቢዎች በማቅናትም ችግሩ ተፈጥሮ ያመጣው ነውና በትጋታችን መሻገር እስክንችል ለጊዜው በእጃችን ያለው ይሄ ነውና ተቀበሉን ብለው የችግር መሻገሪያ አንድ ደረጃ የሚሆን ድጋፋቸውን አስረከቡ።
ደቡቡ ወደ ሰሜኑም ወደ ምስራቁም በማቅናት ከልብሱም፣ ከጉርሱም፣ ከገንዘቡም የሚችለውን ለወደኖቹ በማጋራት የማይላላ የትስስር ቋጠሮውን አጥብቆ ተመለሰ። አማራው ምንም እንኳን እኔም በችግር ላይ ያለው ቢሆንም ከእኔም የባሰ ችግር ላይ የወደቀ ወንድሜ በመኖሩ ካገኘሁት ላይ ላካፍለው ወንድማዊ ደሜ ያስገድደኛል፤ ዛሬን ተጋግዘን ማለፋችን የነገው ብሩህ ጉዟችን ከዳር መድረስ መሰረት ነው ብሎ፤ ወደ ምዕራቡም ወደ ምስራቁም ወንድሞቹ በማቅናት ልባዊ ፍቅሩንና አለኝታነቱን አረጋገጠ።
ኦሮሞው የተወሰኑ አካባቢዎቹ በድርቅ ተጎድተው ሰዎች ችግር ላይ ቢወድቁም፤ እንስሳት በብዛት ቢሞቱም፤ ከእኔ የባሰ ችግር ላይ ለወደቁ ወንድም እህቶቼ መድረስ አለብኝ ብሎ መሃረቡን በመፍታት ወደ ሰሜኑም፣ ወደ ምስራቁም በማቅናት ካለው ላይ አካፍሎ ለወገን ደራሽነቱን አሳይቷል። ሐረሪው፣ ሲዳማውና ሌላውም ሁሉ ለወገኔ ከእኔ የተሻለ ሊደርስለት የሚችል ማንም ኃይል የለም በሚል ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ የወንድማማችነት መንፈስ የችግር ጊዜ ደራሽነቱን አሳይቷል።
ምናልባት የሚደረገው ድጋፍ በመጠን ደረጃ የአንዱ ከአንዱ ሊያንስና ሊበልጥ ይችል ይሆናል፤ ይህ ሁሉም ባለው ልክ ሊያደርግ ይገባዋልና ከዚሁ አግባብ ሊታይ የሚችል ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ከተደረገው ነገር መጠን በላይ የተደረገበት መንፈስና ሁኔታ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ኖሯቸው ሳይሆን ከሌላቸው ላይ ቀንሰው፤ አንዳንዶቹም ለችግራቸው መሻገሪያ ከተሰጣቸው ላይ ቀንሰው ብቻዬን በልቼ ወንድሜ ተቸግሮ ሲሞት ማየትን አልሻም ብለው ያደረጉት ነው።
ይህ፣ ኢትዮጵያዊ እሴት የፈጠረው የወንድማማቾች ጥልቅ ፍቅር እና በችግር የማይፈታ የመተሳሰሪያ ቋጠሮው ጥብቀት መገለጫ ነው። እኔ የምኖረው በወንድሜ መኖር ውስጥ፤ ወንድሜም የሚኖረው በእኔ መኖር ውስጥ ነው፤ የአንዳችን መኖር ለሌላችን ዋስትና፤ የአንዳችን አለመኖር ለሌላችንም ውድቀት ነው ብሎ የማሰብ የአንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ ተባብሎ የመኖር ታላቅ እሴት ውቅር ነው። ለሰብዓዊ ክብሩና ልዕልናው ሲል በባእዳን ስንዴ ሆድ ለመሙላት ስል እጄን አስጠምዝዤ ክብሬን አሳልፌ አልሰጥም ብሎ በሰብዓዊነት ስም የሚራወጡ ዓለምአቀፍ ረጂዎችን ድጋፍ የተነፈገ ወንድም ክብርን ለመጠበቅና ከሚደርስበት ሁለንተናዊ ስብራት ለመታደግ ሲባል የሚከፈል ዋጋ ነው።
ዓለምአቀፍ ረጂ ተቋማትና አገራት ሟቾችን ትተው ለገዳዮች በሚያላዝኑበት፤ ሟች እየራበው ለገዳዩ የሚላክን እርዳታ በመሬትህ ላይ ጠብታ ሳትነካ አሳልፍ በሚሉበት፤ ስለ ሰብአዊነት ሳይሆን ስለ ፖለቲካዊ ግባቸው የድጋፍ ስንዴን ይዘው በሚሽከረከሩበት፤… በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን ዋጥ አድርገው ስለ ተጎዱ ወንድም እህቶቻቸው ከራስ በላይ ለወገናቸው ያላቸውን የማይናወጥ ፍቅር የገለጡበት ነው።
ይህ ነው እንግዲህ ትናንት በጀግንነት ሜዳው የተጎናጸፉትን የመቻል ልዕልና፤ ዛሬም በጠላት ላለመደፈር ከሚደረግ የጦር ሜዳ ጀብድ በዘለለ፤ በስንዴ ክብርን አሳልፎ ላለመስጠት በወሰነ ሰብዕና በጋራ ቆመው አዲስ የእንችላለን ገጽ የገለጡት። እኛ ካላገዝናቸው፣ እኛ ቀለብ ካልሰፈርንላቸው፣ እኛ የድጎማ ገንዘብ ካልሰጠናቸው በረሃብና ችግር ስለሚቆሉ ተመልሰው ወደእኛው ማንጋጠጣቸው አይቀርም ብለው ለሚያሴሩ ኃይሎች ምላሽ የሰጡበትን የእርስ በእርስ ትግግዝና መረዳዳት አሻጋሪነት በተግባር ማሳየት የጀመሩት።
በዚህ መልኩ ነው ዛሬ ኢትዮጵያ በበዙ ችግሮችና ጫናዎች ውስጥ ሆና የነገ ብሩህ ተስፋዋን በትጉህ ዜጎቿ አቅም ለመወጣት በምትጥርበት ወቅት በስንዴ ስም ጉዞዋ እንዳይደናቀፍ የማስቻል ተደጋፍፎ የመሻገርን ጥበብ ያሳዩት። እናም ይህ ሁነት ኢትዮጵያውያን በችግር የሚፈቱ ሳይሆን፤ ችግርን ለመሻገር የጠነከረ ሕብረትና መተባበርን ሁነኛ መሳሪያቸው አድርገው እንደሚጠቀሙበት ሌላኛው የታሪክ ገጽ ማረጋገጫቸው ሆኗል።
ይህ መልካም ጅምር፤ የኢትዮጵያዊነት ሰብዕናም ነው። ሆኖም ዛሬ ታይቶ የሚከስም ላይሆን የትብብር መሸጋገሪያ ድልድዩ በፀና መሰረት ላይ ሊገነባ፤ የመከፋፈል ግድግዳውም ዳግም ላይጠገን ከነፈጣሪው ፈጽሞ ሊጠፋ ይገባል። ይኸኔ እንደ አድዋውና አሁንም በ“በቃ” ዘመቻው ዘመን እንደታየው ሁሉ የኢትዮጵያውያን የይቻላል ሌላው ገጽ ከፍ ብሎ ሌላ የተምሳሌትነት ክብርን ለኢትዮጵያም፣ ለኢትዮጵያውያንም ያጎናጽፋል። አበቃሁ! ቸር ሰንብቱ!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2022