ቅዳሜ ቀትር ላይ ነው፤ ሁለት እብዶችን በአንድነት ማየት ያልተለመደ ቢሆንም በአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ሶስት እብዶች ጉባኤ ተቀምጠዋል። የእነዚህ እብዶች ካለወትሯቸው በቁም ነገር ማውራታቸውና መደማመጣቸው ደግሞ የጉዳዩን አሳሳቢነትና ክብደት ይናገራል። በእብዶች ታሪክ ያለተፈፀመ እብደት በጤነኛ ነኝ ባዮች እየተፈፀመ በመሆኑ አንዳች የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ አለበት። ይላል ድምፁን ከፍ አድርጎ – ራሱን በጨርቅ የጠቀለለውና በጥቁረቱ ገላው ከልብሱ የተማሰለበት ወጣት ከወዲህ ወዲያ እየተራወጠና እጁን እያወናጨፈ ።
ንግግሩን ቀጥሎም አልበዛም እንዴ ? ከምር አሁንስ በጣም አበዙት? የኛም ማንንት መጠበቅ መከበር አለበት እንዴት አይረዱንም ከነሱ የተነጠልነው ስላልተስማማን አይደል እንዴ፤ በቃ! እኛም በነሱ እነሱም በኛ ማንነት፤ ምንነት ስራና እንቅስቃሴ መግባት የለባቸውም፤መግባት የለብንም፤ ድንበራችን መለየት አለበት። ከወደ ቀኝ ጥግ የተቀመጠው ሌላው ባለ አዳፋ ራቁታም ምላሸ መስጠት ጀመረ፤ በጊዜው እርምጃ ባለመውሰዳችን ነገሮች ከእጃችን እየወጡ ነው። በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ማንነታችንም ስራችንም በመጤዎች እየተወረሰ መጥቷል። ለኛ የተረፈን ስማችን ብቻ ነው።
በበኩሌ እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ የዚህ አይነት ወረራ ይፈፀምብናል ብዬ አልጠበኩም ነበር። ጀማሪው ተናጋሪ ጥያቄ አቀረበ ሰው ከሰው በምን ይለያል ? በብዙ ነገር በመልክ በፀባይ በሀብት በፆታ በቋንቋ በ….. ስንቱን ልግለፅልህ እኛስ ከሰው በምን እንለያለን ? በምግባር በባህሪ በፀባይ በስራችን ወዘተ… በኛስ መካከል ምን ልዩነት አለ ? በኛ በኩል በደረጃችን ነው እብድ፤ ቀውስ ፤ ወፈፌ፤ ሾጥ ያረገው ፤ ንክ፤ አውቆ አበድ …… ጀማሪ እብድ፤ የለየለት…….. ስንቱን ልንገርህ።
እኔ ግን የእኛን መለየት አልቀበለውም እስቲ እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር እንየው ራቁታችንን መሄዳችን ከሆነ ዛሬ ሴት ወንዱ የሚንቀሳቀሰው እርቃኑን ነው። ወንዱ ጭራሽ መቀመጫውን እያሳየ ነው የሚሄደው የሚሸጠው ልብስ ሁላ የተተለተለ የተቦጨቀ ሆኖ እያለ ለእኛ ሲሆን ለምን እንደሚኮነንአይገባኝም። ስማችንን ሲያጠፉ እብድ የፈለገውን ያወራል፤ ያሻውን ይናገራል ይላሉ። እውነቱ ግን ሌላ ነው ።
ዛሬ ከነሱ መሀል ብቻውን የማያወራ ማን አለ ? የስድቡንማ ነገር ተወው እድሜ ለፌስ ቡክ ይኸው በየቀኑ የስንቱ ዋልጌ ጉድ እየወጣ አይደል። ብታይ እኮ ስድቡ… ትችቱ…. ነቆራው… ዛቻው…. ድንፋታው…… ምን አለፋህ የስድብ ትምህርት ቤት የተከፈተ ነው የሚመስለው። ምን የተከፈተ ብቻ ፤የተስፋፋም ነው የሚመስለው፡፤ጥናት አልተሰራም እንጂ የእያንዳንዱ አበሻ ፌስ ቡክ ቢመረመር ጥራዝ ጥራዝ የስድብ መፅሀፍ የሚወጣው ይመስለኛል።
የድሮ እብድ መለያው ድንጋይ ድንጋይና ዱላ ይዞ መሮጡ ነበር። አስበው የዘንድሮ እብድ ምን ድንጋይ ይወረውራል። አላየህም ቡራዩ አላየህም….. የትኛው እብድ ያን ያህል ሰው ገሎ ያውቃል እነሱ ለውጥ መጣ ብጥብጥ፤ ሰላማዊ ሰለፍ ብጥብጥ፤ የድጋፍ ሰልፍ ብጥብጥ፤ ኳስ ጭዋታ ብጥብጥ … ለምሳሌ እኛ መንገድ ዘግተን አናውቅም ቢበዛ ህዝብ ፈርቶን መንገድ ይለቅልን ይሆናል እንጂ።
ዛሬ ወጣቱ ሽማግሌው አሮጊቱ ሳይቀር እየተነሳ መንገድ ይዘጋል። አንዳንዱ በድንጋይ ሌላው በእንጨት ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ብለው ብለው ምናምኑን ሁሉ ሰበስበው እያቃጠሉ በጭስ መንገድ መዝጋትም ጀምረዋል። አይገርምህም ወንድሜ !! ደግሞ ሲላቸው እብድ ከተማ ያቆሽሻል ይላሉ፡፡ እኛ እኮ ጤነኛ ተብዬዎቹ ያቆሸሹትን ከተማ እኛ እንቆሽሽ ይሆናል እንጂ ስናፀዳ ነው የኖርነው።
እብድ እንዴት አድርጎ ቆሻሻ ይፈጥራል ? ስለዚህ ስንት ዘመን አስከብረን የኖርነውን እብደት ማንም ወንዝ አመጣሽ ማንም ጊዜ አመጣሽ እንዲነጥቀን መፍቀድ የለብንም። እኛ እኮ ማንም ይመን አይመን አብዛኞቻችን ያበድንበት በቂ ምክንያት አለን ፡፡ ካስፈለገም ከሆስፒታል ፣ ከፀበል ብሎም ከጎረቤት ጭምር መረጃና ማስረጃ ማቅረበ እንችላለን። ተናጋሪው እልህ እየተናነቀው ንግግሩን አቆመ። የጉባኤው ሰብሳቢ ንግግሯን ቀጠለች በርግጥ አለች በርግጥ የሀገሪቱ መሪ የእኛን የእብዶች መብት ማስጠበቅ አለባቸው፤ የመንደር እብዶች ፤ ምሁር ተብዬ የቢሮ እብዶች፤፤የፌስ ቡክ እብዶች ፤ ባጠቃላይ አውቆ እብዶች ከእኛ እንዲለዩ ብሎም በእኛ ስራና ተግባር እንዳይገቡ ማድረግ አለባቸው። ነገር ግን አሁን የተናገርኩት እንዳለና እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገሪቱ መሪ ቦታ ሆነን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል።
በመጀመሪያ ደረጃ ከሞቀ ቤቱ በጠዋት በሰላም ወጥቶ በየመንገዱ በየቢሮው በተለይ በፌስ ቡከ የሚያብደውን መለየት እጅግ አስቸጋሪ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ያለባቸውን የጤነኛ እብድ ብዛትም ከግንዛቤ ማስገባት አለብን። በነገራችን ላይ እሳቸው ማለቴ የሀገሪቱ መሪ ስለሙስና፤ ሌቦችና ዘራፊዎች ሲያወሩ ”እንሰራቸው ብንል አንድ ከተማ አይበቃንም” ብለው ነበር አሉ። እንግዲህ ልብ በሉ እሳቸውንም እኛንም ጤና እየነሳ ያለውን በስሜት የሚነዳ እብድ ህዝብ ልሰር ቢሉ ደግሞ ራሷ ሀገሪቱ እምትበቃቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም እዚህ ካለው ባልተናነሰ ከውጪ የሚመጣ በሚሊዮን የሚቆጠር ዳያስፖራ እብድም አለባቸውና ነው። ስለዚህ ጥያቄውን መመለስ ያለበት ሌላ ወገን ነው። ሌላ ወገን ስል መጀመሪያ እያንዳንዱ በየቤቱ የራሱን ወፈፌ መያዝ ማስታገስ አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እያንዳንዱ አካባቢ ከወፈፌነት ወደ ቀውስነት የተሸጋገሩና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙትን የመቆጣጠር ብሎም በቤተሰብ ደረጃ የሚደረገውን ክትትል መደገፍ ይጠበቅበታል። ሲሰልስ እያንዳንዱ ክልል በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የየራሱን ወፈፌ፣ ቀውስ፣ ንክ፣ ባለ ዛርና ባለ ውቃቢ ጭምሮ መያዝ፣ ሀይ ማለት አለበት ። ለዚህ ደግሞ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ያዘው፣ በለው የሚሉ ምሁራንና አክቲቭስቶች የራሳቸውን ንግግር የሚያዳምጡበት፤ በድረ ገፅ የፃፉትን ራሳቸው የሚያነቡበት በቴክኖሎጂ የታገዘ አዳራሽ መገንባት ያስፈልጋል። ለወጣቶቹም ድንጋይ የሚወረውሩበት ሰፋፊ ሜዳ፤ የሚያቃጥሉት ጎማና መንገድ መዘጊያ ትልልቅ ድንጋይ እንዲሁም የሚዘጋ መንገድም ጨምሮ ማዘጋጀት አለባቸው። ለዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄንን የሚያሳልጥ ኮሚሽን መቋቋም አለበት።
ኮሚሸኑ ደግሞ ከባለስልጣን ወፈፌ፤ ከአክቲቪስት ቀውስ፤ ከወጣት እብድ፤ ከሃይማኖት አባት ንክ፤ ከዳያስፖራ ሾጥ ያረገው፣ ከጋዜጠኛ ጨለፌ ማካተት አለበት። ብላ ንግግሯን አጠናቀቀች። ሶስቱ ሀገር ወዳድ እብዶች የውሳኔና የመፍትሄ ሃሳባቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፅሁፍ ለማቅረብ ተስማምተው ብእርና ወረቀት ሲያገናኙ “አንተ !!! አትበተንም” የሚል ጠንካራ ድምፅ ሰሙ። የጉባኤው አባላት ድምፁን ተከትለው ከመንገዱ በስተግራ ጥግ አይናቸውን ሲወረውሩ በቆመጥ፣ በክላሽና ካቴና የተደራጁ የክልል ፖሊሶችን ተመለከቱ። በዚች ቅፅበት ሶስቱም የረሱትን የሀገሪቱን መሪ ትልቅ እዳ ለማስታወስ እድል አገኙ፤ ለካስ በሀገሪቱ “የታጣቂ እብዶችም” ነበሩ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ