ቅርብ ወራጆች ዋና ዋና ፌርማታ ላይ የሉም። ረዣዥሙን የተሳፋሪ ሰልፍ የመቋቋም ትዕግስት የላቸውም።ቅርብ ዓላሚዎችና ቅብጥብጦች ናቸው። ትዕግስተኞች ያለሙበት ቦታ ለመድረስ ረዥም ሰዓት ተሰልፈው ባቡሩን ሲሞሉት ቅርብ ወራጆች የመጓዝ ዕቅድ ባይኖራቸውም ዘው ብሎ ይሳፈራሉ።ሆኖም ባቡር ውስጥ ያለውን መጣበብና መጨናነቅ የመቋቋም ጽናትም የላቸውም።
እናም ተሳፋሪ መስለው ይገቡና በአጭሯ ጉዟቸው የሚመነተፍ ካገኙ መንትፈው በቀጣዩ ፌርማታ ይወርዳሉ።ቀድመው “ወራጅ አለ” የሚሉትም እነሱ ናቸው።የሚመነተፍ ካላገኙም የባቡሩን መጨናነቅ፣ የሕዝቡን ብዛትና መንግሥትንም እያማረሩ በሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ፌርማታ ላይ ይወርዳሉ።በዚህም አይቆሙም።ከነጥቆ ሯጭ ባህሪያቸው ጋር ወደሚስማማ ሌላ ባቡር ያማትራሉ።በዚያም ተሳፍረው ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማሉ።ወደ የትኛውም ባቡር ለመሳፈርም ሆነ ከባቡሩ ለመውረድ ምክንያታቸው ቁሳዊና ስሜታዊ ፍላጎታቸው ብቻ ነው።
ደግነቱ የቅርብ ወራጆች መሳፈር በባቡሩ የመጫን አቅም ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የለም።በመውረዳቸውም የጉዞውን አቅጣጫና መዳረሻ አይቀይሩትም።በእርግጥ ሲሳፈሩ በተሳፋሪው ላይ መጨናነቅና መጣበብን፤ ሲወርዱም ባቡሩ እንደሞላ ስለሚወርዱ መገፋፋትና መገፈታተርን ይፈጥራሉ።
ምናልባት የመመንተፍ ፍላጎታቸው ካልተሳካላቸው አብዝተው ይበሳጫሉ።መሬቱን ይደበድባሉ፤ በየምክንያቱ ድምጻቸውን ከፍ ከፍ አድርገው በብስጭት ይጮሃሉ።በዚህም አቧራ ያስነሳሉ፤ አየሩን ይበክላሉ።በጩኸታቸውም ጸጥታውን ያደፈርሳሉ።የተሳፋሪውንም የነዋሪውንም ሠላማዊ ህይወት ያውካሉ።
የአገራችን ፖለቲካ ውስጥ የቅርብ ወራጅ ፖለቲከኞች ሚና አስገራሚ ነው።በአገራችን በተካሔደው ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት ውስጥ ቅርብ ወራጆች የዳር ተመልካቾች ነበሩ።ትግሉ ፍሬ ማፍራት ሲጀምር ብሎም የለውጥ ኃይሎች አሸንፈው የመንግሥት ሥልጣን ሲረከቡ የቅርብ ወራጆች የትግሉ አካል ነን ብለው ተቀላቀሉ።ከዚያ በኋላ “መደመር የሕይወት መርሐችን ነው” ብለው ተነሱ።ያልተደመረ ወይም አልደመርም ያለ ጠላት ነው፤ ከመደመር ውጪ ፖለቲካ የለም አሉ።የመደመር ጠበቃና አቀንቃኞች ሆኑ።ስለመደመር የገባቸው ግን አይመስሉም።መደመር ማለት የጠሉትን መቀነስ ይመስላቸዋል።መደመር ማለት የመንጋ ፍላጎትን ማስፈጸም ይመስላቸዋል።
ቅርብ ወራጆች ቶሎ ተሳፍረው ቶሎ ስለሚወርዱ የጉዞውን ርቀት፣ አቅጣጫ፣ ፍጥነት፣ ፈተናና መዳረሻ አያውቁትም።መውረጃቸውም፣ ስሜታቸውም፣ ድጋፋቸውም፣ ሀሳባቸውም ቅርብ ነው።የሩቅ ዓላማ፣ የሩቅ ጉዞ፣ የሩቅ ሐሳብ፣ የሩቅ ህልም የሚል ነገር አይመቻቸውም።ሁሉንም ነገር ከራሳቸውና ከዙሪያቸው ብቻ ነው የሚመለከቱት።በትግል ሂደት ውስጥ እናገኛለን ብለው የገመቱትን የቅርብ የስሜት እርካታ ወይም ጥቅም ካላገኙ ወዲያው ይወርዳሉ።
ከዚያ በኋላ ሁሉንም ነገር መቃወም ይጀምራሉ።ይቅርታን፣ ምሕረትን፣ አካታችነትን፣ ሰላምን ከረዢሙ የአገርና የጋራ ጥቅም አንጻር መመዘን አይችሉም።በእኩልነትና ፍትሃዊነት ላይ ወደተመሠረተ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከሚወስደው ዘላቂ የትግል ጉዞ በስሜት ተሽቀንጥረው ይወርዳሉ።ስሜታቸውም ቅርብ በመሆኑ በቶሎ ይቆጣሉ፤ በፍጥነትም ከድጋፍና ከትግል መሪነት ጫፍ ወደ ተቃውሞ ጫፍ ይሄዳሉ።በስሜትና በአገር፤ በጊዜያዊ የግል ጥቅምና በዘላቂ የአገር ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት አያስተውሉም።ልጆች ይወልዳሉ እንጂ ስለልጆቻቸው የነገ እጣፋንታ ደንታ የላቸውም።
ቅርብ ወራጅ ፖለቲከኞች ይገርማሉ! ለአገርና ለትውልድ ዘለቄታዊ ጥቅም ሲባል ከጦርነት ለመውጣትና በሠላማዊ ንግግር አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተወሰዱ እርምጃዎችን በስሜታዊነት በመቃወም ዘለው ለመውረድ ሴኮንዶች አልፈጀባቸውም።እግረ መንገዳቸውንም አቧራ በማስነሳትና ከፍ አድርገው በመጮህ ሠላማዊ መስተጋብሩን ለማወክ መቅበዝበዝ ጀመረዋል።ፈጥነውም ለየራሳቸው ቁሳዊና ስሜታዊ እርካታ ሲሉ የብሔርና ሐይማኖትን ባቡር ለመሳፈር እየተሯሯጡ ነው።እዚህም ውስጥ በቅርብ ወራጅ ፖለቲከኛ ባህሪያቸው የቅርብ ዒላማቸውን ለማሳካት እንጂ ለሚምሉለትና ለሚገዘቱለት ሃይማኖት ዘለቄታዊ ክብርና ጥቅም በማሰብ አይደለም።
ቅርብ ወራጅ ፖለቲከኞች ግብታዊ ስሜታቸውን እና ስግብግብ ቁሳዊ ፍላጎታቸው ለማርካት ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።ህይወት ቢጠፋ፣ አካል ቢጎድል፣ ንብረት ቢወድም ደንታቸው አይደለም።ከአገር ህልውናና ጥቅም በተቃርኖ የሚቆሙ ናቸው።ቅርብ ወራጅ ፖለቲከኞች ከራሳቸው ውጪ ለማንም አይጠቅሙም!!
ቅርብ ወራጆች ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ።ደግነቱ እነርሱ የባቡሩን መሙላትና መጉደል፣ የጉዞውን አቅጣጫና መዳረሻ አይቀይሩትም።ጥቅምና ጉዳታቸውም እንደ ጉዟቸው አጭርና ጊዜያዊ ነውና ቅርብ ወራጆች እንዲህ ናቸው።
እኛ ግን ለምንወዳት አገራችን የረጅም ጊዜ የሰላምና የዕድገት ዓላማ አለንና ቅርብ ወራጆችን በወጉ እንወቃቸውና ከሴራቸውና እኩይ ቅስቀሳቸው መጠንቀቅን አንርሳ።ለእነርሱ ግብታዊ የስሜት እርካታና ቁሳዊ ትርፍ ሰለባ እንዳንሆን በንቃት ልንከታተላቸውና ልናወግዛቸው ይገባል።ይልቁንም ለአገራችንና ህዝቦቿ እንዲሁም ለትውልዱ ዘላቂ ክብርና ጥቅም መከበር ሲባል ጸንተን መቆም ይገባል።ዛሬን ለነገ ግብዓት አድርገን ከመጠቀምም መደናቀፍ የለብንም!
አባቡሌ ከጉለሌ
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2022