ለሙሉ አካል ሕልውና ሲባል ከጣቶች መካከል አንዷ ጣት የማይድን ተዛማች በሽታ ሥር ከሰደደባት የሕመሟን ቦታ ቆርጦ ማስወገድ የሕክምናው አንድ ጥበብ ነው። ምክንያቱም ይህች ጣት ካልተወገደች በስተቀር ችግሯ የከፋ ይሆናልና ነው። በመሆኑም የበሰበሰ ጣት ለመቁረጥ መሳሳት አያሻም ያለበለዛ መላ አካልን እስከማፍረስ የደረሰ ጥፋትን እና ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። እናም ካንሰር የሚሉት በሽታ አንድጣት ላይ ከታየ ቶሎ መቁረጥ ይበጃል። ያለበለዚያ በመላ ሰውነት ተሰራጭቶ እየገዘገዘ ሰውነትን ያፈርሳል።
ኢትዮጵያም አሁን ላይ የገጠማት ይሄ መሰል ችግር ነው። በእርግጥ በተለምዶ ‹‹ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም፤ ምክንያቱም አካል ነው›› ይሉት ብሂል አለ። ነገር ግን የበሰበሰው ጣት በሽታውን ለመላው አካል አሰራጭቶ ሙሉ ሰውነት እንዲፈርስ የሚያስገድድ ከሆነ መቁረጥ ይበጃል። አጉል አካል አይቆረጥም በማለት ሙጭጭ ብሎ መንገታገት ጉዳቱ ራስን እስከ ማጣት ያደርሳል።
እስከ መቼ ምንም የማያውቁ ልጆች የመስዋት በግ ሆነው ይዘልቃሉ? እስከ መቼ ሕዝብ ይሸበራል? እስከ መቼ የበሰበሰ ጣት እድሜ ይረዝማል? የተወሰነ እድሜ ቢኖረውም በቆየ ቁጥር ሴራው የበለጠ ስለሚወሳሰብ መላ ሰውነት እንዲፈርስ መንስኤ መሆኑ አይቀርም። ለእዚህ መፍትሄው ቀድሞ ቆርጦ መጣል ነው። ስለዚህ የበሰበሰውን በማስወገድ ሌላ ጣትንም ሆነ አካልን ጤናማ ማድረግ ተገቢ ነው።
መልካም የሠራ መልካም ነገር ያገኛል። የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ ትረግጣለች እንደሚባለው ደግሞ ጠግቦ ማር የረገጠ ክፉም ዕጣ ፈንታው በመጨረሻ ውድቀት እንደሚሆን አያጠያይቅም። ክፉ ሲወድቅ ሌላውን ይዞ አዘቅት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ ‹‹ራስህን ቻል›› ማለት ያስፈልግ ነበር። ነገር ግን አንዳንዶች ‹‹የራሳችን አካል ነው›› በሚል ሰበብ ክፉ ሰሪ እጃቸውን ይዞ እየጎተተ ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ሊጨምራቸው ጫፍ ላይ ሲደርስ ይብቃህ እያሉት አይደለም።
የአሸባሪው ሕወሓት የጥፋት ቡድንም እንዲሁ ነው። ምናልባት ቀደም ሲል ለትግራይ ሕዝብ ተስፋ እየሰጠ ዘመናትን አስቆጥሯል። አሁንም ያንኑ የውሸት ተስፋ መስጠቱን ቀጥሎበታል። ሃምሳ ዳቦ ከመላስ አንዷን መጉረስ እንደሚባለው፤ ሲልስ የኖረውን ዳቦ ከአሁን በኋላ እንደሚያጎርስ ቃል ገብቶም ይሆናል። ነገር ግን ይህን አያደርግም። ምክንያቱም ይኸው ቡድን ‹‹ሰው ሊወድቅ ሲል ይኮራል፤ ይታበያል›› እንደሚባለው የተፈጠረበትን ሕዝብ ንቆ ሲኩራራ እና ሲታበይ ለመውደቅ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል።
አሁን ደግሞ ክፋት እና ኩራቱ ጥሎታል። በሌላ መልኩ ስትራቴጂ ቀርፆ መንገድ ቢጀምርም አልሆነለትም። አሁንም የውሸት ፕሮፖጋንዳውን በመንዛት የጥፋት መንገዱን ቀጥሎበታል። የጥፋት መንገዱ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ትልቅ ዋጋ እያስከፈለ ነው። ነገር ግን አሁንም የትግራይ ሕዝብ ዝም ብሏል። ምክንያታቸው ፍራቻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ለትግራይ ሕዝብ መፍራት አያዋጣም።
በእርግጥ የትግራይ ህዝብ የሽብር ቡድኑ ጥቃት እና ጥፋት ከባድ ነው እና መናቅ የለበትም። ነገር ግን መናቅ ባይኖርበትም ፍራቻውን አቁሞ መድሃኒት ለማግኘት ፊቱን ካላዞረ፤ የሽብር ቡድኑ መዘዝ ተመዞ የሚያልቅ አይሆንም። አሁን ላይ አንዴ ጋብ ሌላ ጊዜ ሞቅ እያለ የሚቀጥለው የሽብር ቡድኑ በሽታ እውነተኛ መድሃኒት ካላገኘ መልሶ መነሳቱ አይቀርም።
የሽብር ቡድኑ አሁንም ለትግራይ ሕዝብ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ የጣት ቁስል ሆኗል። የጣት ቁስል ይዞ መተኛት ደግሞ አይቻልም። ልተኛስ ቢሉ እንዴት ይሆናል? ከነአባባሉ ‹‹የጣት ቁስል እና የጎረቤት ምቀኛ እየጠዘጠዘ እንቅልፍ አያስተኛ›› ይባል አይደል።
ቁስሉ በጠዘጠዘ ቁጥር አናት የሚሰነጥቅ ህመም ይሠማል። ከዚህ ህመም ደግሞ ሞት ይሻላል። የጥፋት ቡድኑ አሁን የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያውያንን እየጠዘጠዘ ነው። ‹‹ከሕዝብ አብራክ የወጣሁ ለሕዝብ የቆምኩ ነኝ›› ቢልም ሕዝብ እያስጨረሰ፤ የለመደበትን የሕዝብ ልጅነቱን በተግባር ክዶ በትግራይ ሳይቀር የሕዝብ አመኔታን ያጣበት ብዙ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል። ታዲያ ይህን መሳይ ከሃዲ ቡድን ‹‹ልጄ ነው›› እያሉ ማሽሞንሞን ስለምን ይሆን?
ድብቅ የሥልጣን ጥማትን ለማርካት ከስድስት አሥርት ዓመታት በፊት በጥፋት ተነስቶ እሳት እያነደደ ሕዝብ እየፈጀ ወደ ሥልጣን የመጣው የሽብር ቡድን፤ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ የዓድዋ ድል ማሳያ የሆነውን ‹‹የትውልድ ጉልበት ህብረት›› የሚባለውን ብሒል ለመበጣጠስ የሔደበትን መንገድ በእውነት ላስተዋለው በጣም ያሳዝናል። ኢትዮጵያውያን ከህብረት እና ከአንድነት ይልቅ ልዩነታቸውን ብቻ እያሰቡ በሆነ ጊዜ እንዲበተኑ የፈፀመው ሸፍጥ ታሪክ ይቅር የሚለው ዓይነት አይደለም።
የሕዝብ ሃብቱ በዋናነት አንድነቱ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በዘመነ ሕወሓት ይህ አንድነቱ በተለያየ መልኩ እንዲላላ ተደርጓል። አንድ ከሚያደርገው ጉዳይ ይልቅ በህገመንግሥቱ ሳይቀር ለሚበታትነው ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቷል። አንድ መሆን መልካም ቢሆንም ነፃነት በሚል ሽፋን ማንም ቢሆን መገንጠል እንደሚችል በሕገመንግሥቱ አስቀምጠዋል። የትግራይ ሕዝብ ይህንን ቡድን በብብቱ ይዞ ሲያሞቀው የኖረው ለእውነተኛ ነፃነት እንጂ ኢትዮጵያን እንዲበትን በመፈለጉ ነው ለማለት ያስቸግራል። ሕዝቡ ፍላጎቱ በትክክልም ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ከሆነ ቡድኑን ከዚህ በኋላ ይብቃህ ሊለው ይገባል።
የትኛውንም ችግርም ሆነ የትኛውንም ፈተና ማለፍ የሚቻለው በመፈረካከስ ሳይሆን በአንድነት ነው። መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ እንደሚባለው ቀድሞም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ከማንም በፊት በማስተዋል ቡድኑን ‹‹የወጣኸው እና በትግራይ ህዝብ የተፈጠርከው ለዚህ ዓላማ አይደለም፤ ለምን ይህን አደረግክ?›› ብለው ሊጠይቁት ይገባ ነበር። ነገር ግን ይህንን አላደረጉም፤ አልጠየቁም።
እሳቱን ሲያስነሳ ሳይቃጠል በቅጠል ማለት እና የሚያቀጣጥለውን እሳት ማጥፋት ሲገባ፤ አሁን እንኳን በቅጠል ሊጠፋ ኬሚካል የተጨመረበት የእሳት ማጥፊያ ውሃ በምድርና በአየር እየተረጨበት ላለመጥፋት እየተፍጨረጨረ ያለ ኃይል ሆኗል። እናም በትንሽ በትንሹ የለኮሰው እሳት በዓመታት ጉዞ ውስጥ ዛሬ ላይ አገርና ሕዝብ እየበላ ይገኛል።
ምናልባት አሁን ላይ ከብዙ ተረት በኋላ የከሰመ ሊመስል ይችላል፤ ይሁን እንጂ አሁንም የጠፋ ቢመስልም በአመድ የተዳፈነው እሳት ረመጥ ሆኖ ቀስ እያለ መቀጣጠሉን እየጀማመረው ነው። አፋር እና አማራን ወሮ በጥምር የኢትዮጵያ የጦር ሃይል ተሳድዶ ቢመለስም አሁንም አላረፈም። ሃይለኛ ነኝ ባይነት እና ጉልበተኛነት ጊዜ ያለፈባቸው የኋላ ቀርነት መገለጫ ቢሆኑም፤ የሽብር ቡድኑ አሁንም ውስጥ ውስጡን እምቢተኛነቱን ቀጥሏል። መንግሥት የመሆን ህልሙ አልተገታም፤ እየገፋበት ይገኛል። ለዚህ ማሳያው አሁንም አላርፍ ብሎ በአፋር አካባቢ እየጫረ ያለው እሳት ተጠቃሽ ነው።
‹‹የክፉ ልጅ እናት ሁልጊዜ ታዝናለች›› እንደሚባለው የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ምክንያት ለስድስት አሥርት ዓመታት ሲያዝን ኖሯል። ከጥቂቶች በቀር አጠቃላይ ሕዝቡ ደስታ ከራቀው ከራርሟል። ሕወሓት ከመፈጠሩ ጀምሮ በሚለኩሰው እሳት፤ የትግራይ ሕዝብ ጧሪ ልጅን፣ መከታ ወንድምን እና አባትን አንዳንዴም እህት እና ወንድምን እንዲሁም እናትን በጦርነት ማጣት ተለምዷል።
እዚህ ጋ አንድ ታሪክ ላንሳ፤ ልጁ እናቱ እንቁላል ግዛ በዛውም በሚተርፈው ለአንተም ከረሜላ ግዛ ተብሏል። ነገር ግን ወደ ሱቅ ሲላክ ከረሜላ ከሚለው ውጪ ልብ ብሎ አልሰማም፤ እርሱ ልቡ ያለው ከረሜላው ላይ ብቻ ነው። ቲማቲም እና ከረሜላውን ገዝቶ መጣ። የላኩት እናቱ ተበሳጩ ያልኩህን ትተህ ያላልኩህን ገዝተህ ትመጣለህ? ሂድና የተላከውን ነግረህ ይዘህ ና አሉት። ልጁ ተመልሶ ወደ ሱቁ ሮጠ፡ ‹‹ይሔን አይደለም›› አለ። እናቱ የመለሱለትን በኪስ ወረቀት የተሰጠውን ቲማቲም ለባለ ሱቁ ሰጠ። ‹‹ታዲያ ምንድን ነው?›› አለ። ባለሱቁ፤ ልጁም መልሶ ‹‹ቲማቲም›› አለ። ‹‹የሰጠሁህ እኮ ቲማቲም ነው›› ሲለው፤ ‹‹አይ እናቴ ይሄ አይሆንም ብላኛለች›› ብሎ መልስ ሰጠ። ባለሱቁም ለልጁ ‹‹በትክክል ሔደህ የተባልከውን ጠይቀህ ና›› አላለውም። የሰጠውን ቲማቲም ከኪስ ወረቀቱ አውጥቶ መልሶ ጠንካራ ቲማቲሞች መርጦ ለልጁ ሰጠው።
ልጁ በድጋሚ ወደ እናቱ ሮጠ። የገዛውን ለእናት አሳየ፤ አሁንም ልጁ ይዞ የመጣውን እናት ሲያዩ እጅግ ተበሳጩ፤ ደማቸው ተንተከተከ፤ ብስጭቱ አዙሮ ሊደፋቸው ደረሰ። ለምን ይህን ገዛህ ብለው አልጠየቁም፤ ልጁ የሰጣቸውን ጥለው እንደ ዕብድ እየተወራጩ ወደ ሱቁ ሄዱ፤ ባለሱቁ ላይ አፈጠጡ። ‹‹አንተ ደንቆሮ የማትረባ መቼም አትሻሻልም›› እያሉ ደነፉ። ባለሱቁ ግራ ተጋባ ‹‹አሁን እንቁላሉን አምጣ›› አሉ። ‹‹ይክፈሉና›› አለ። አሁንም የበለጠ ተበሳጩ። ‹‹ገንዘብ ትጠይቀኛለህ?›› ብለው ለድብድብ ተነሱ፤ ሴትየዋ ባለሱቁን ካልገደልኩ ብለው ለያዥ ለገናዥ አስቸገሩ። ባለሱቁ ያጠፋው ምንም ዓይነት ጥፋት አልነበረም። የትግራይ ነገርም እንዲህ ሆኗል።
ገና ከመጀመሪያው ልጆቿን በትክክል ነግራ አስጠንቅቆ መላክ ነበረባት። የተላኩት ልጆች ትኩረታቸው ከረሜላው ላይ ነበር። ስለዚህ እናታቸው የላከቻቸውን ረሱ። ከረሜላውን ሲልሱ ከርመው፤ በመጨረሻ ስህተት ቢሠሩም በትክክል ተነጋግሮ መክሮ እንደመመለስ በተቃራኒው ጥፋትን ምንም ባላጠፋው ላይ አላኮ አጉል ብሶት ውስጥ ገብቶ ትውልድ ሲጠፋ መመልከት እንደትክክለኛነት ተወሰደ።
ልጆች ከሁሉም ጋር በግልፅ ተነጋግረው ችግራቸውን ፈትተው ከሁሉም ጋር አብረው መኖር ሲገባቸው በአጉል ትዕቢት ተወጥረው ‹‹የበላይ ነን›› አይነት አካሄድን ተከተሉ። እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ አንድ ቡድን ቀርቶ በቀጣይ ለአሜሪካንም ቢሆን የዓለም የበላይ ነን አካሄድ እንደማይበጅ እያየነው ያለነው ሃቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በፍፁም ማንም የበላይ ሆኖ መቀጠል አይችልም። ማንም ያለፈቃድ እና ያለ ሕዝብ ምርጫ አገር መምራት አይፈቀድለትም። ማንም የትኛውም የጦር መሳሪያ እና የሰለጠነ ሃይል ቢኖረውም ሕዝብ ካልፈቀደ የሚሆን ነገር የለም። የመጨረሻው ውጤት ዕልቂት ነው። ስለዚህ የሚበጀው መነጋገር፣ መተማመን ሃይልን አሰባስቦ የኢትዮጵያ ጠላት በሆነው በድህነት ላይ ክንድን አበርትቶ ማለፍ ነው። ይህንን ማንም ቢሆን ሊረዳ ይገባል።
ሕዝብን ማገልገል እና የጋራ ተጠቃሚ መሆን እንጂ ለብቻዬን ማለት አያስኬድም። መንፈሰ ጠንካራ እና ጦረኛ መሆን መንግሥት ለመሆን በቂ አይደለም። መንግሥት ለመሆን የሕዝብ ፈቃድ ያስፈልጋል። ይህንን የትግራይ ሕዝብም ማወቅ አለበት። እንደተላከው ልጅ እናት ገንዘቡን መስጠት ብቻ ሳይሆን ገንዘቡ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለበት። መጠየቅ እና ረጋ ብሎ እያነጋገሩ መምከር ይገባል። በአግባቡ ሳያነጋግሩ ባለሱቁን ከመኮነን ይልቅ ልጁን መጠየቅ ይገባል። ልጁን ‹‹ግዛ የተባልከው እንቁላል ነው፤ ለምን እንቁላል ገዝተህ አልመጣህም?›› ማለት ያስፈልጋል።
አሁን ላይ ከምን ጊዜውም በላይ የትግራይ ሕዝብ ጠያቂ ሊሆን ይገባል። የሽብር ቡድኑ የጀግና ዘር ነን ብሎ ወጣቱን ከእናቱ ጉያ ነጥቆ ወደ ጦርነት አስገብቶ ሲማግደው ከርሞ፤ የወጣው ወጣት ብቻ ሳይሆን ዕድሜው ካልደረሰ የ12 ዓመት ልጅ ጀምሮ ዕድሜው እስገፋ የ60 ዓመት ሽማግሌ አዛውንት ድረስ የዘመተው የት ደረሰ? ብሎ መጠየቅ የግድ ነው። የሽብር ቡድኑ ሴት ወንድ ሳይል አቅም ያለውን ሁሉ አግዟል። ‹‹ይህ ሁሉ ከተላከ በኋላ የት ደረሰ? ምን ውጤት መጣ?›› ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። አሁን ግን ቡድኑን የጠፉ የቤተሰብ አባል የት እንዳለ መጠየቅ አለባቸው።
‹‹ለምን ቃል እንደገባኸው ተመልሰህ የኢትዮጵያ መሪ አልሆንክም?´´ ንገረን ሊሉት ይገባል። አሁን የትግራይ ሕዝብ የመጨረሻ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜው ነው። ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቅ ከዛም መልስ ማግኘት ይኖርበታል። ነገሩ ጥያቄ ሲቀርብ ቡድኑ የሚሰጠው መልስ የለውም። ምክንያቱም የሆነው በተላከው መሠረት ሳይሆን በተገላቢጦሽ ነው።
መጀመሪያ ከሠላሳ ዓመት በፊት ቃል የገባውን የትግራይ ሕዝብ በሚፈልገው መሠረት አልፈፀመም። አሁንም ባለው ሃይል ተማምኖ መንግሥት እንደሚሆን ቢገልፅም እንደተናገረው አልሆነም። እንደውም ‹‹የትግራይ አካል ነኝ›› በሚል ማታለያ ሁለንተናው በስብሶ ሕዝቡን በበሽታ እየበከለ ነው። የበሰበሰ ደግሞ ሁሉንም ይዞ እንዳያፈርስ ቀንጥሶ መበጠስ እና ከራስ አካል መለየት ያስፈልጋል። የትግራይ ሕዝብም ይሄን የሽብር ቡድን የሚጠይቅበት፤ ምላሽ ካጣም የማይድን በሽታው ተዛምቶበት ይዞት እንዳይጠፋ በቃሕ ሊለው፤ በካንሰር እንደተያዘችው ጣት ለሕልውናው ሲል ቆርጦ ሊያስወጣው ይገባል። ለዛም ጊዜው አሁን ነው።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014