ከሶስት ዓመት በፊት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር የግማሽ ዓመቱን የበጀት አፈጻጸም በማስመልከት ማክሰኞ፣ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም ሰጥቶት በነበረው መግለጫ፣ ከ102 መሥሪያ ቤቶች የአንድ ሺህ ፕሮጀክቶችን ዝርዝር ሒደት የሚያሳይ መግለጫ ወይም ፕሮፋይል ተሰናድቶ ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የ43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን አስታውቆ ነበር። የዚህ ሁሉ ወጪና ክስረት ደግሞ ሌላ ሳይሆን በወቅቱ አገሪቱን ሲመራና ሙስናን የሥርዓቱ አካል አድርጎ የነበረው ቡድን ሥራ እንጂ ሌላ አይደለም።
በወቅቱ፣ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት ያደረገው 102 መሥሪያ ቤቶች አንድ ሺህ ፕሮጀክቶችን ፕሮፋይል ወይም የአፈጻጸም ወቅታዊ ሒደትን አመላካች ዝርዝር መግለጫዎችን ነበር። የፕሮጀክቶቹ ፕሮፋይል በተዘጋጀበት ወቅት ፕሮጀክቶቹ ምን ያህል በጀት እንደተመደበላቸው፣ መቼ ተጀምረው ማለቅ እንዳለባቸው ወይም እንደነበረባቸው፣ ከተጓተቱም ምን ያህል ወጪ እንዳስከተሉ በተደረገ ማጣራት፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመታት የዘገዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸው እንደተደረሰበት በመግለጫው ተካትቶ ነበር።
እነዚህ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችም በአገሪቱ ላይ 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውም ተነግሯል። በወቅቱ እንደተገለጸውም ይህ የገንዘብ መጠን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ተመድቦለት ከነበረ በጀት (46 ቢሊዮን ብር) ጋር የሚቀራረብ ነው። ይህንን ያህል ነበር በነበረው ብልሹ አሰራርና ቅጥ ባጣ ስግብግብነት ምክንያት አገሪቱ መቅኔዋን የተመጠጠችው። ለዚህ ደግሞ የስኳር ፋብሪካዎቹን ብቻ ወስዶ ማየት ይቻላል።
በዚህም ምክንያት የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው መርሃ ግብር፣ የጥራት ደረጃ እና በጀት ባለመከናወናቸው በኢኮኖሚ ውስጥ ያመጣሉ ተብሎ የሚጠበቀውን ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። ለሕብረተሰቡ የታለመውን አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አልተቻለም።
እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ሁሉ እጅግ ዝቅተኛ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከፍተኛ ለሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ ሆኖ መቆየቱን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሰነድ ያመለክታል። ከዚህ ሰነድ የምንረዳውም ያውና ተመሳሳይ ሲሆን፤ እሱም ከለውጡ በፊት በነበረው አስተዳደር የፕሮጀክቶች አፈፃፀም አዘቅት ውስጥ የነበረ መሆኑን ነው።
ከተለያዩ ተቋማትም ሆነ ከላይ ከገለጸው ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት ተችሎ የነበረው ከለውጡ በፊት የነበረው አስተዳደር የነበሩት ቁልፍ ችግሮች ፕሮጀክቶቹ መቼ ተጀምረው እንደሚያልቁ፣ በየዓመቱ ምን ያህል በጀት እንደተጠቀሙ፣ በአካል የሚታየውና በሪፖርት የሚቀርበው አፈጻጸም አለመጣጣም፣ የፕሮጀክት ክትትል ደካማነት፣ የፕሮጀክቶች ሒደት በማሕደር ተሰንዶ ክትትልና ወቅታዊ ግምገማ አለማድረግን የመሳሰሉት ነበሩ።
በቅድመ ለውጥ በነበረው አስተዳደር ወቅት የጥራት፣ የመጓተት፣ ያለ በቂ ጥናትና አንዳንዴም ያለምንም እቅድ ወደ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ሲገባ እንደ ነበር መረጃዎች ይናገራሉ። በጥናቶቹ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ከተቋራጮች ጋር የሚገባው ውል ደካማነትም ተጠያቂነት ሲያጓድል እንደቆየ የተመለከተ ሲሆን፤ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የተገቡ ውሎች በማሳያነት ቀርበው ነበር።
ባጭሩ ከለውጡ በፊት (ቅድመ ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር) የነበረው የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም (እየተነጋገርን ያለነው፣ የተወሰኑ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ስለ የሚያተኩረው፣ ስለ “የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት” ተብሎ ስለሚታወቀው አይደለም) ይህንን ይመስል ነበር።
በመሆኑም እነዚህን የመሳሰሉ የአሰራር ችግሮች የአፈጻጸም መጓተቶች የሚያስከትሏቸውን ኪሳራዎችና አላስፈላጊ ዕዳዎች ለመቀነስ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ሂደት፣ ትግበራቸውንና የተመደበላቸውን በጀት አጠቃቀምና ሌላውን ዝርዝር ጉዳይ የሚቆጣጠር ተቋም በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እየተቋቋመ እንደሚገኝ በወቅቱ ተገልጿል።
የሜጋ ፕሮጀክቶች ዋና ዋና አገራዊ ፋይዳዎች፤ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻን የያዙ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንግዲህ አንዱ ፕሮጀክት ሲሆን ሁሉም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ቢጠናቀቁ ኖሮ ምን ያህል ጠቀሜታን ሊያስገኙ እንደሚችሉ መገመት ለማንም አያዳግትም።
ከስራ እድል ባለፈም ከሕብረተሰቡ የእለት ተእለት ተጠቃሚነት አኳያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያላቸው ፋይዳ ቀላል አይደለም። ይህንንም በአንድ ተቋም ምሳሌነት ማየት ይቻላል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ታሕሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና አገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ ‘የብርሃን ለሁሉ’ መርሀ- ግብር ተግባራዊ ተደርጎ እ.ኤ.አ በ2025 ዓ.ም 65 በመቶ የሚሆነው ሕብረተሰብ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲሁም 35 በመቶው ደግሞ ከብሔራዊ ግሪድ ውጪ ወይም በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
የፌዴራል መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅን በማዘጋጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሰነድ እንደሚያመለክተው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ ለማድረስ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ያከናውናል። በተጨማሪም አገራችን ከምትከተለው የልማት አቅጣጫ አንፃር በግሉ ዘርፍ ሊሞሉ የማይችሉ ዘርፎች ላይ መንግሥት በልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ኢንቨስትመንቶችን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ፕሮጀክቶች ለሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ሲሆን ይህንን ኃላፊነት ለመወጣትም መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው። የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት የሚወጠኑና የሚተገበሩ ከመሆናቸው አንፃር ከአገራት የረዥም ጊዜ ወይም የመካከለኛ ዘመን እቅዶች የሚመነጩ መሆን እንዳለባቸውም ነው የሚያስረዱት።
ከዚህ ባለፈም መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን የልማት ግቦችና ዓላማዎች ለማሳካት በፕሮጀክቶች አማካኝነት የሚተገበሩ በመሆኑ የፕሮጀክቶች መነሻዎች እና ልየታ እነዚህን ግቦች የሚያሳኩ መሆናቸው በግልጽ በሚያመላክቱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ሊረጋገጥ የሚገባው መሆኑን አስምረው ማስረዳታቸው የፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው መርሃ ግብርና ደረጃ መጠናቀቃቸው የሚኖራቸውን ከፍ ያለ አገራዊ ፋይዳ የሚያሳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት የፓርላማ ማብራሪያቸው “ቢሮዎቻችን ሲፀዱ ተንጫጩ፣ አንድነት ፓርክ ሲጠናቀቅም አሽሟጠጡ፣ በሸገርና እንጦጦ ፓርክ ልማትም ተበሳጩ፤ ዳቦ የሚሻ በርካታ ድሃ እያለ የምን ፓርክ እያሉ ተንጫጩ። በአዲስ አበባ የተመዘገበው አስደናቂ ልማት በገበታ ለአገር በክልሎችም ለመድገም ሲሠራ ጩኸቱ ይጨምራል። የብልጽግና ጉዞም ተጠናክሮ ይቀጥላል” እንዳሉት በመሰረተ ልማቱ ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
መንግሥት ለሚቀጥለው 10 ዓመት የያዛቸውን እቅዶች ለመተግበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መሰረተ ልማት ቁልፉ ጉዳይ ከመሆኑ አኳያ፣ ይህ አሁን በዐቢይ አስተዳደር እየታየ ያለው ጥረትና ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ የማጠናቀቅ አቅም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል የሚለው የብዙዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው ፍላጎት ነውና ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ምን እየተሰራ እንደሆነ በማሳየነት ወስደን እንመልከት።
የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የአንድ አገር ሁለንተናዊ ጤናማነት ከሚለካባቸው ጉዳዮች አንዱ በዛች አገር የሚከናወኑት የመሰረተ ልማት ተግባራት ናቸው። በመሆኑም በአገሪቱ መሰረተ ልማቶች አሉ ወይስ የሉም፤ ካሉስ በምን አይነት የእንቅስቃሴ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየሄዱ ነው ወይስ አይደለም? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው የግድ ነው።
እነዚህን ጥያቄዎች ታሳቢ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፤ በተለይ “አዲስ አበባ በሽብርተኛው ቡድን ተከባለች” ከሚለው የበሬ ወለደ የጠላት ወሬ አኳያ አንስተን ከአዲስ አበባ ከተማ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤትን መረጃ መሰረት በማድረግ አጠቃላይ የሜጋ ፕሮጀክቶችን ይዞታና ያሉበትን ሁኔታ እንመልከት።
ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እድሳት ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በዘመናዊ እና ለስራ ምቹ በሆነ መልኩ ታድሷል። 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ያለው የአድዋ ዜሮ ፕሮጀክት የዓድዋን ታሪክ ለመዘከር በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው። 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት 19 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ የዲጂታል መጻሕፍት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት ለምርቃት በቅቷል።
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለልዩ ልዩ ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሆኖ እየተሰራ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ 1 ሺህ 400 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ተሽከርካሪ ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት በሚያስችል መልኩ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የቤተ መንግሥት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ ክንውኑ 79 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ለ 1 ሺህ ተሽከርካሪዎች የፓርኪንግ አገልግሎት ይሰጣል። እንዲሁም ሌሎች፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸው በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶችና የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል እና ተፈጥሯዊ መስህቦች በጠበቀ መልኩ ነው እየተከናወኑ የሚገኙት። አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ መሆኗንም ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች ናቸው እየተሰሩ ያሉት።
የሜጋ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ ሂደት በተመለከተ የሁሉም ሥራ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው እየሄደ ያለው። አልፎ አልፎ ችግር አጋጠመ ከተባለም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በኮቪድ-19 ምክንያት የሰው ኃይል እንደተፈለገ ማንቀሳቀስ አለመቻሉ ነው። ሜጋ ፕሮጀክቶቹ እንዳይቋረጡ፣ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲከናወኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅርብ ክትትልና የምክር አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበረው ፕሮጀክቶችን የማጓተት ተግባር፣ እንደ አዲስ አበባ ካየነው በአሁኑ ሰአት የለም። በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ አለ። እሳቸው ከመጡ ወዲህ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡ በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። አሁን በመጠናቀቅ ላይ ያሉና ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ አሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግዙፍ ሕንጻም የዚህ ዋናው ማሳያ ነው። በመሆኑም የዐቢይ አስተዳደር በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያመጣው።
ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባ ተከባለች፣ የሽብር ቡድኑ እዚህ ደርሷል ወዘተ የመሳሰሉ የሀሰት ትርክቶች ከበሬ ወለደ ወሬነት አልፈው ስራችን ላይ ያደረሱት ችግር የለም። አብዛኞቹ ሜጋ ፕሮጀክቶቹን እየገነቡ ያሉት የውጭ ዜጎች ናቸው። እንደማንኛውም ሰው በግለሰብ ደረጃ ስጋት የተፈጠረባቸው ሊኖሩ ቢችሉም እውነቱን እንዲረሱት በመደረጉ ስጋታቸው ተወግዷል። ወሬው በሬ ወለደ መሆኑን በሚገባ አውቀውታል። እዚሁ እየኖሩ ስለሆነም እውነቱ ከእነሱ የተሰወረ አይደለም።
እዚህ ላይ ማሳሰብ የሚያስፈልገው በሚነዛው የሀሰት ትርክት የከተማው ነዋሪ ምንም ሳይረበሽ ስራውን እንደተለመደው በተረጋጋ መንገድ ሲያከናውን መቆየቱን፤ በቀጣይም በዚሁ አግባብ ሊያከናውን የሚገባው መሆኑን ነው። የሽብር ቡድኑ የከፈተብንን ጦርነት በድል አጠናቅቀን ወደ ተለደመደው መደበኛ ሰላምና ስራችን እስክንመለስ ድረስ ሕዝቡ ከመንግሥትና ከመከላከያ ጎን በመቆም ከልማታችን ሊያደናቅፈን፣ አገራችንን ሊያፈርስ የተነሳን አሸባሪ ሃይል ማጋለጥ፤ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ይገባዋል::
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014