ወይዘሮ አያል አብዩ በጎንደር ከተማ በምዕራብ በለሳ አርባያ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከ50 አመት በላይ እድሜ ባለው አርባያ ወረዳ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር አባል ሆነውም ቆይተዋል። ማህበራቸው አቅም እንዳልነበረውና መደራጀታቸውም ጥቅማቸውን ሳያስጠብቅላቸው መቆየቱን የሚያስታውሱት ወይዘሮ አያል፣ የማህበሩ ቆይታቸው ምንም እንዳልገጠማቸው ሲገልጹ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል” ብለውታል። በዚህ የተነሳም የምርታቸውን ተገቢውን ዋጋ ሳያገኙ፤ ከጤናቸውም ሳይሆኑ ቆይተዋል።
ይህ ህይወታቸው ግን ከአመታት በፊት ማህበራቸው የጸሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን አባል ከሆነ በኋላ ይቀየራል። ‹‹እስከ ዛሬ ገበያ በወጣ በወረደ ቁጥር ስንጎዳ ኖረናል›› የሚሉት ወይዘሮ አያል፣ ማህበራቸው ከጸሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ጋር ከተቀላቀለ በኋላ ግን ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ይገልጻሉ። ሰሊጥ፣ ሽንብራ፣ ጤፍ እያመረቱ ለዩኒየኑ እንደሚያቀርቡ፣ በዚህም ምርታቸውን ለነጋዴ ሲያቀርቡ ይደርስባቸው የነበረው የዋጋ መውደቅ መቅረቱን ያብራራሉ። አሁን ምርታቸውን በተመጣጣኝና ቋሚ ዋጋ ለማህበሩ ያቀርባሉ። ክፍያውም በወቅቱ ይደርሳቸዋል፤ በዚህም ጥሪታቸው እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ፣ ዩኒየኑ ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበላቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
‹‹አሁን ደግሞ የማህበራችን ድርሻ ባለበት ፋብሪካ የሚመረተውን ዘይት በመቀበል ለተጠቃሚ እንድንሸጥ እድል ተፈጥሮልናል።›› የሚሉት ወይዘሮ አያል፤ ፋብሪካው ከውጪ የሚመጣውን ዘይት ሊያስቀር እንደሚችል እና በዚህም ከማህበሩ አባላት አልፎ ሌሎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ። ዘይቱም ከሚያውቁት ግብአት እንደሚመረትና ጥራቱ የተጠበቀና ለጤናም ተስማሚ መሆኑን ይናገራሉ። የወገራ ወረዳ ዳሞት ልደታ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ቢራራ አየለ በ2000 ዓ.ም የተመሰረተው የሚጋ ዘር ብዜት ሊቀመንበር ናቸው። “ሊቀመንበሩ እንዲህ አይነት ትልቅ ፋብሪካ በአርሶ አደሩ መገንባቱ አንድ ተስፋ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።
ማህበሩ የፀሀይ ዩኒየን አባል ከሆነ አንስቶ ተጠቃሚ መሆኑን ይገልጻሉ። አካባቢው ደጋ በመሆኑ የቢራ ገብስን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን እንደሚያመርት ፣ቀደም ሲል ምርቱን በወረደ ዋጋ ለገበያ ያቀርብ እንደነበር አስታውሰው፣ የግብርና ወቅት ሲያልፍ በርካታ ሰዎች ስራ ፈት ይሆኑ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬ ብዙ ሰው ውሎ መግቢያ ማግኘቱንና አጠቃላይ የአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴም እየተነቃቃ መምጣቱን ይመሰክራሉ። የጎንደር ከተማ ቀበሌ 11 ነዋሪው ወጣት ብርሃን ገብረ ማርያም ላለፉት አስራ አምስት አመታት በቀን ስራተኛነት በተለያዩ ቦታዎች ሰርቷል።
አሁን የጸሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን የዘይት ፋብሪካ ሰራተኛ ነው። ‹‹ቀደም ሲል ዘወትር ማለዳ ተነስተን እንደ አዲስ ስራ እንፈልግ ነበር፤ ለስራው ዋጋ የሚያወጡልን አሰሪዎቻችን ናቸው፤ የሰራንበትም ክፍያም በወቅቱ የማይከፈለበት ጊዜ ነበር።››የሚለው ወጣት ብርሃን፣አሁን ሁሉም ነገር እየተስተካከለ መምጣቱን ይገልጻል። ‹‹ምን ያህል እንደሚከፈለን፣ መቼ እንደሚከፈለን እናውቃለን ፤አሁን በየአስራ አምስት ቀኑ ይከፈለናል፤ ይህ መሆኑም ተረጋግተን እንድንኖር አስችሎናል። ገቢውም ራሴንና ቤተሰቤን› ይላል። የፀሀይ ሁለ-ገብ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒዬን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ እንዳሉት፤ ዩኒየኑ የተመሰረተው መጋቢት 1992 ዓ.ም በሁለት ወረዳዎች በአምስት መሰረታዊ ማህበራት አለፋ ጣቁሳ ሁለገብ የገበሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየን በሚል ነበር። በወቅቱም 2500 አባወራዎች ፣ሁለት ቅጥር ሰራተኞ ነበሩት፤ካፒታሉም 360 ሺ ብር ነበር።
ዩኒየኑ በመካከለኛው ጎንደር ዞን እያገጠመ የነበረውን የግብርና ግብአት አቅርቦትና ስርጭት እና የግብርናና ሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ግብይት ችግርን ለመፍታት ሲባል የተቋቋመ ሲሆን፣ ከዚያም አድማሱን እያሰፋ መጥቷል። በ1997 በአስር ወረዳዎች በአርባ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት የፀሀይ ሁለ-ገብ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒዬን በሚል እንደገና ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት ዩኒየኑ በ12 ወረዳዎች 143 መሰረታዊ ማህበራት 120 ሺ450 አባዎራዎችና ከግማሽ ሚሊየን በላይ ቤተሰብ አቅፏል።
ከ100 ለሚበልጡ ሰራተኞችም የስራ እድል ፈጥሯል።ካፒታሉንም በቅርቡ ያስመረቀውን የዘይት ፋብሪካ ሳይጨምር ከ75 ሚሊይን ብር በላይ አድርሶታል። አላማውም ገበያ በማረጋጋት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ፣ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ ሲሆን፣ ለዚህም ምርጥ ዘርና የእርሻ ግብአት በማቅረብ ሲያገለግል ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም 100 ሚሊየን ብር በማውጣት በ7 ሺ 834 ካሬ ሜትር ላይ ያስገነባው የምግብ ዘይት ማምረቻ ወደ ስራ ገብቷል። ፋብሪካው በአመት 80,000 ኩንታል የቅባት እህል በግብአትነት የሚጠቀም ሲሆን ፣በቀን ከ10,000 ሊትር በላይ የምግብ ዘይት የማምረት አቅም አለው። የኑግ፡ ለውዝ፡ ሱፍና ሰሊጥን ጨምሮ ሰባት አይነት የቅባት እህሎችን አበጥሮ ፈጭቶና አጣርቶ ነው ዘይት የሚያመርተው።
ምርቱንም ከግማሽ ሌትር እስከ ሀያ ሌትር በሚይዙ የፕላስቲክ መያዣዎች አሽጎ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ያቀርባል። በሀገሪቱ የሰሊጥ ዘይት በማምረት የመጀመሪያው ሲሆን፣ ለ52 ቋሚና 24 ጊዚያዊ ሰራተኞች የስራ እድል ከፍቷል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ በዘይት ምርቶች ግብይት ረገድ የሚታየውን ያልተመጣጠነ አቅርቦትና የተጋነነ ዋጋ እንደሚያስተካከልም ታሞኖበታል። አብዛኛውን ግብአት በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች የሚገኘውን ምርት የሚጠቀም ሲሆን፣ በአካባቢው ላሉ የቅባት እህል አምራቾችም የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሕብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይለልኡል ተስፋዩ እንደሚሉት፤በክልሉ የሕብረት ስራ ማሕበራት መስፋፋት ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።
ከ1991 ዓ.ም በፊት በክልሉ በአይነት ሁለት በቁጥር 962 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ነበሩ። ካፒታላቸውም 46 ሚሊየን ብር ሲሆን አባላቱም አንድ ሚሊየን አይሞሉም ነበር። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በ22 ዘርፎች ከ15 ሺ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 70 ዩኒየኖች አሉ። ከነዚህ ውስጥ 3 ሺ 424ቱ የገንዘብና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ሲሆኑ ካፒታላቸውም በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር በላይ በዩኒየን ደረጃ ደግሞ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ደርሷል። የቁጠባ መጠናቸውም ከ3 ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር በላይ ሲሆን ከ 3 ነጥብ ሰባት ሚሊየን ብር በላይ ለአርሶ አደሩ ብድር እየሰጡም ይገኛሉ።
እንደ አቶ ሀይለልኡል ማብራሪያ፤በግብይት ረገድም ባለፉት አምስት ተከታታይ አመታት ሰሊጥ፤ ቦለቄ፤ ኑግ፤ ቡና፤ ማሾ ወደ ውጪ በመላክ ለአባላቱ የገበያ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ 139 ሺ 920 ኩንታል ምርት ወደ ተለያዩ የእስያና አውሮፓ ሀገራት በመላክ 27 ሚሊየን 596 ሺ 494 የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ ተገኘቷል። ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግርም በክልሉ የሚገኙ ሀያ ዩኒየኖችና ሶስት መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት በዱቄት፣ በዘይት፣ በመኖ ማምረት፣ በማርና ወተት ማቀነባባርና ማጣራት እንዲሁም በማዳረበሪያና ሳሙና ማምረት ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ግብርናውን ለማዘመንም አስራ አንድ ዩኒየኖችና 26 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት 34 ትራክተሮች፣ ሶስት ዘመናዊ ኮምባይነሮችና 39 መውቂያ ማሽኖችን ወደ ስራ በማስገባት በክልሉ መካናይዜሽን እርሻ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ዋና ስራ አስኪያጁ ያመለክታሉ። በፋብሪካ ግንባታ ረገድም በጸሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከተገነባው የምግብ ዘይት ፋብሪካ በተጨማሪ የምግብ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ በወደራ ዩንየን፡ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ በአድማስ ዩኒየን እየተገነቡ እንደሚገኙም ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኡስማን ሱሩር ፋብሪካው በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ፈጣራ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀው፣ የአባላቱን ገቢ ከማሳደጉ ባሻገር ለአካባቢው የመሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።ሌሎች የሃገራችን ኅብረት ስራ ማህበራትም ይህንን በጎ ልምድ ወስደው ሃገራዊ እድገትንና ገቢን በሚያሳደጉ የልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዋና ስራ አስኪያጁ እንዳብራሩት ፤ እንደዚህ አይነት ወደ አግሮ ፕሮሰሲንጉ በፍጥነት የሚቀላቀሉ ኅብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሣደግ የሚያግዙ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ፣ግብዓቶችና አሠራሮችን ወደ ሁሉም አባል በጊዜ ፤ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው። አቶ ኡስማን እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ85 ሺ በላይ የመሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት እና ከ388 በላይ ዩኒዬኖች ይገኛሉ። የተጠቃሚ አባላት ቁጥርም ከ20 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። የማህበራቱ ካፒታል እያደገ ሲሆን፣ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ የጋራ ሃብት አፍርተዋል። የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ረገድም ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ ችለዋል። ፀሃይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒዬን በግንባር ቀደም ተዋናይነት ከሚንቀሳቀሱ 388 ኅብረት ስራ ዩኒዬኖች መካከል አንዱ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ