ዚምባቡዌ በቀድሞ መሪዋ ሮበርት ሙጋቤ ዘመነ መንግሥት «ዴሞክራሲን በአግባቡ መተግበር እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቀረት አልቻለችም» በሚል በአሜሪካ መንግሥት ይፋዊ ማዕቀብ የተጣለባት እኤአ በ2003 ነው። ይህ የዋሽንግተን ውሳኔና አቋምም እኤአ በ2005 እንዲሁም 2008 ዳግም ፀንቶ እንዲቆይ ተደርጎል። ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታትም ሮበርት ሙጋቤን ጨምሮ በ141 የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ዛኑ ፒ.ኤፍ. እና አመራሮች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል። ከሁለት ዓመት በፊት ለ37 ዓመታት የነገሱት ሮበርት ሙጋቤን ተክተው በትረ ስልጣኑን የተረከቡት የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የነጩ ቤተ መንግሥት ማዕቀብ ተፈፃሚ ከሆነባቸው የመንግሥት አመራሮች አንደኛው ናቸው።
ምናንጋግዋ አንጋፋውን ሙጋቤን ተክተው ስልጣን በተረከቡ ማግስት አገሪቱን ለመሰል ማዕቀብ የዳረጋት ከምዕራባውያን ጋር የመቃቃሯ ምክንያት መሆኑን በመረዳት፤ ይህ ለማደስና ሁለንተናዊ ለውጦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቃላቸውን ሰጥተዋል። በተለይ ዚምባቡዌ የገባችበት ከባድ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ይታደስ ዘንድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና የመፍጠር አቅሙ ገዝፎ የታየው የነጩ ቤተ መንግሥት ማዕቀብ ይነሳላቸው ዘንድ ከመጠየቅ ባለፈ እስከመማፀንም ተሻግረዋል።
ይህ ጥያቄያቸው የዋሽንግተንን ልብ የማራራት አቅሙ እንዲገዝፍም የአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምህዋር በማሻሻል ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ህፀፆችን ለማስውገድ ይረዳሉ የሚሏቸውን የተለያዩ ለውጦችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሥራ አጥነትንና ሙስናንን ለመቅረፍ እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ እንደሚሠሩም ቃላቸውን ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንቱ ቃል በገቡት መሰረት በአንዳንድ ጉዳዮችም ቃላቸውን በተግባራቸው ማስደገፍ ቢችሉም በዴሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ትግበራ ላይ ከጥንካሬ ይልቅ ድካማቸው ገፍዞ ታይቶባቸዋል።
በተለይ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር በአገሪቱ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት ከሁሉ በላይ አመድ አፋሽ አድርጎባቸዋል። ሰውየው በምርጫ ውጤት አሸናፊነታቸውን ማወጁም በተለይ በተቃዋሚው መሪ የዴሞክራሲያው ለውጥ ንቅናቄው መሪ ኔልሰን ቻሚሳና ተከታዮቻቸውን ብርቱ ወቀሳን ማስተናግድ ግድ ብሎታል። ከዚህም በላይ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡና የዜጎች ህይወት እንዲያልፍም ምክንያት ሆኗል። በኢኮኖሚውም ቢሆን ሰውየው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት የቻሉ አይመስልም። በአሁን ወቅት አገሪቱ ባለፈው አስር ዓመት ከነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ በከፋ ሁኔታ ውስጥም ትገኛለች፡፡
ከሰሞኑ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በ158 ሀገራት ላይ ባደረገው ጥናት መሠረት ዚምባቡዌ ከዓለም ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ከኦሊቪያ ቀጥላ በ2ኛነት ደረጃ ላይ መቀመጧን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ዘገባዎችና አስተያየቶችን የሚሰጡ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ምሁራንም ምንም እንኳን የፕሬዚዳንቱ የለውጥ ሂደት ሙሉ በሙሉ በስኬት እየቀጠለ ነው ብሎ ለመናገገር ባይደፍሩም፤ ለለውጥ የሚከፈለውን ድካም አንጸራዊ ለውጥ ከግምት እንዲገባ ሲወተውቱ ቆይተዋል። የፕሬዚዳንቱ ጥረት የዋሽንግተንን የማዕቀብ አቋም የማስለወጥ አቅም ሊኖረው እንደሚችል ተንብይዋል።
ከቀናት በፊት የሆነው ግን እንዳታሰበው ሳይሆን ቀርቷል። ለአስራ ስድስት ዓመታት የዘለቀው የዚምባቡዌ ለውጥና የአሜሪካ ማዕቀብ ያልተማመነ ጉዞም ቀጣይነት ተረጋግጧል። ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ እንዲራዘም ወስነዋል። የነጩ ቤተ መንግሥት አለቃ፤ አዲሱ የዚምባብዌ መንግሥት የሚከተላቸው ፖሊሲዎች ከአገራችው ፖሊሲ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው ማዕቀቡ ለተጨማሪ ጊዜ ለመራዘሙ በዋና ምክንያትነት አቅርበዋል። የዚምባብዌ መንግሥት እየተከተለው ያለው ፖሊሲ ያልተለመደና ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስጋት የሚደቅን መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኤመርሰን ምናንጋግዋ ወቅታዊና አስፈላጊ የሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን መተግበር እንዳልቻሉና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ከዋሽንግተን መንግሥት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና መገለጫ መቀየር እንዳልሆነላቸውም የነጩ ቤተ መንግሥት አስተዳዳር አመላክቷል። ፕሬዚዳንቱ ፤ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትንና ተቃውሞዎችን የሚገድቡ ህጎችን ካልለወጡና ለመብታቸው መከበር አደባባይ የወጡ ዜጎችን ደህንንት ማስጠበቅ እስካልቻሉም ማዕቀቡ ፀንቶ እንደሚቆይ በነጩ ቤተ መንግሥት አለቃ ቃል የታጀበው መግለጫ አፅእኖት ሰጥቶታል።
የሃራሬው አስተዳደር በአንፃሩ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ትግበራ በተከናወኑ ተግባራት የምርጫን ሂደት ነፃ፣ ታማኝና ግልፅ ማድረግን ጨምሮ የህዝብና ለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በማስጠበቅ ረገድ አስደናቂ የሚባሉ ለውጦች መታየታቸውን በመጠቆም፤ የትራምፕ ያልተጠበቀ ውሳኔ በአንፃሩ ወቅታዊው የአገሪቱን ጥረት የማኮሰስ ነው ብሎታል። በዚህ ረገድ የዚምባቡዌ ኒውስ ዘጋቢዋ ታንያ ሙጋቤ ባሰፈረችው ሀታታም፤ የዛኑ ፒ.ኤፍ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ጄሴፍ ሹማ የትራምፕን ተግባር ምንም ትርጉም የማይሰጥ ማለታቸውን አስንብባለች። በእርግጥም ይህን እሳቤ የሚጋሩት አልታጡም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን የኢኮኖሚ አማካሪውና ፕሮፌሰር ስቲቭ ሄንክ የቀድሞው የዚምባቡዌው የተቃውሞ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ አማካሪ ኤዲ ክስንም የትራምፕን ውሳኔ ከኮነኑት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆነዋል። ባለሙያዎቹ የሃራሬ መንግሥት የለውጥ ትግብራ አፈፃፃም በማድነቅና ይህም በተጨባጭ የሚታይና በአንዳንድ አገራት እውቅና ሳይቀር የተሰጠው መሆኑን በመጠቆም የእንደ አውሮፓ ህብረት ሁሉ ከዋሽንገተን መንግሥት ማዕቀቡን የሚያሻሻልበትን ሂደት እንደሚጠበቁም አስረድተዋል።
በዚህ መልኩ የአገሪቱ መንግሥት አመራሮችና ስመጥር ባለሙያዎች፤ መሰል ማዕቀብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በሚያደረጉት ጥረት ሁነኛ ማነቆ እንደሚሆን ሲናገሩ ቢደመጡም እንደ ዶናልድ ትራምፕ ሁሉ ምናንጋጋዋ የገቡትን ቃል ፈጽመው አለመገኘታቸው የሚመሰክሩም በርካቶች ሆነዋል። በተለይ በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሲቪል ማህበረሰብ፤ የምናንጋጋዋ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ቀደም ሲል የተረከበውን ከማስቀጠል ባለፈ ይህ ነው የተባለ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ሲገልጹ ተሰምተዋል። በተለይ የተቃዋሚው መሪ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄው መሪ ኔልሰን ቻሚሳን ምናንጋግዋን ከቀድሞው ሮበርት ሙጋቤ የማይሻሉና ደካማ ብለው ወርፈዋቸዋል።
ኘሬዚዳንቶቹ ልዩነታቸውን ለማጥበብ ይመካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል እንደ ቻሚሳን ሁሉ ሌሎችም አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚሉ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች ቁጥርም በርካታ ነው። ፕሬዚዳንቱንም የለውጥ ጅምር ያላንኳሰሱ የአሜሪካንን ውሳኔም ያለተቃወሙም አሉ። በዚህ አቋም የተለዩት ባለሙያዎችና መገናኛ በዙሃንም የትራምፕ አስተዳዳር በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑ ቀይ መብራት በማሳያት ፕሬዚዳንቱም ሆኑ ጋሻጃገሬዎቻቸው ይበልጥ ለለውጥ እንዲነሱ የማድረግ አቅሙን ተመልክተውታል።
አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎችም በአንፃሩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም የማዕቀብ መነሳት ግድ ስለመሆኑ ተሟግተዋል። በተለይ የደቡብ አፍሪካውን መሪ ሲሪል ራማፎሳን አገሪቱ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ደፋ ቀና እያለችና የደቀቀውን ኢኮኖሚያዋን ለማዳስ በምትፍጨረጨርበት በዚህ ወቅት ማዕቀቡን ማፅናት ተገቢ እንዳልሆነና መነሳት እንዳለባት መግለጻቸው የደቡብ አፍሪካው ቢዝነስ ዴይ ጋዜጣ አስነብቧል። ላላፉት አስራ ስድስት ዓመታት የዚምባቡዌ ለውጥና የአሜሪካ ማዕቀብ ባለመተማመን ጉዞ በድጋፍና በተቃውሞ መካከል መቀጠሉ ያልጣመው የሃራሬ መንግሥት ግን ጉዳዩን በሰከነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው ተመላክቷል።
የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ጄምስ ማንዙን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ እንደዘገበውም፤ ሃራሬ የትራምፕ ውሳኔ ይቅርታ እንደማትነፍግና ማዕቀቡ እንዲሰረዝላት በቀጣይም ከዋሽንግተንም ሆነ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ውይይት ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች። እንደ ዘገባው ከሆነም፤ ዋና ጸሐፊው አገራቸው በወቅታዊው ማዕቀብ ተስፋ ሳትቆርጥ መጪውን እንደምትጠብቅና ከምዕራባውያኑ ጋር በቅርበት እንድምትሠራ ጠቁመው፤ ምንም እንኳን ይፋዊ ባይሆንም ባለፈው ወርም በአገሪቱ ቀጣይ የበጀት ድጎማ ቅበላ ላይ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመዲናዋ ሃራሬ ውይይት መካሄዱን አብራርተዋል።
ከዚህም ጥረት በላይ ምናንጋግዋ መንግሥት ማዕቀቡን ለማስነሳትና ከዋሽንገተን ጋር መልካም የሚባል ግንኙነትን ለመፍጠር ይረዳው ዘንድ የቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሀብት አፈላላጊና የህዝብ ግንኙነት አጋር 500 ሺ ዶላር ዓመታዊ ክፍያ መቅጠሩ ታውቋል። ይህን ያደመጡና የተመለከቱም ለአስራ ስድስት ዓመታት የዘለቀው የዚምባቡዌ ለውጥና የአሜሪካ ማዕቀብ ያልተማመነ ጉዞ በዚህ መንገድ ብቻ መፍትሔ ስለማግኘቱ ተጠራጥረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በታምራት ተስፋዬ