አሹ ኢትዮጵያ! አፍሪካውያን ገዢዎቻችን የሰላሣ አምስተኛውን ዙር አህጉራዊ ስብሰባ በስኬት አጠናቀው በሰላም ወደየቄያቸው ተመልሰዋል። የስብሰባው በድል መጠናቀቅ እኛን ዜጎች በደስታ፣ አገራችንን በኩራት፣ መሪዎቻችንን በእፎይታ ማረስረሱን ጮክ ብለን ባንመሰክር በመንግሥታችን ዓይን ፊት ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ፊት አደራ በል ተብለን መወቀሳችን አይቀርም።
በተለይም ጉባዔው በእኛ አፈር ላይ እንዳይካሄድ የሟርት ጠጠር ሲበትኑ የነበሩት ጨለምተኛ ባህር ማዶኞች ስብሰባው በስኬት በመጠናቀቁ ተሸማቀው “ደብቁን” እንደሚሉ እንገምታለን።
ይህ አህጉራዊ ስብሰባ በተጠበቀው ልክና ባልተጠበቀው ከፍታ እንዲጠናቀቅ የየራሳቸውን አቅምና እውቀት አሟጠው ኃላፊነታቸውን ለተወጡት የመንግሥት ቁንጮ ሹመኞች፣ እስከ ታች ላሉት ዜጎችና ከፊትና ከበስተጀርባ ሆነው ላገለገሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ በዚህ አምደኛ ብዕር ቢመሰገኑ “ማን ሆነህ” አሰኝቶ “ውሻን ምን አገባው ከእርሻን” ብሂል እንደማያስተርት ይታመናል።
ምክክር ባለበት ድል፤ መደማመጥ በሰፈነበት ስምምነት ስለመኖሩ ተሞክሯችን ብቻም ሳይሆን ቅዱሳት መጻሕፍትም አስረግጠው ያስተምሩናል፡- ቅዱስ መጽሐፍ “ምክር ባለበት በዚያ ሰላም አለ” እንዲል።
አፍሪካውያኑ አለቆቻችን በዚህ መሠረታዊ መርህ መሠረት ልብ ተቀልብ ሆነውም ይሁን ወይንም “በንግግር እየተሻኮቱ” ተሸነጋግለው ከሆነም እኛ ተራ ዜጎች ባልታደምንበት ጉባዔ ላይ “እንዲህና እንዲያ ሆነ” እያልን አቃቂር ለማውጣት ስለምንቸር ትችታችንን አናጎላም።
ከዚህ ሁሉ ይልቅ ግን ተመራጩ መንገድ መሪዎቹ ሲገናኙና ሲለያዩ በፈገግታ እየተፍለቀለቁ ሲተቃቀፉ ስላስተዋልን ሳይግባቡና ሳይተማመኑ እንዳልቀሩ ቀልብያችን የነገረንን ብንመሰክር ይበጃል። የዲፕሎማሲ ባህርይ ነው ከተባለም ምን ገዶን።
ለማንኛውም፤ የአስተናጋጇ አገራችን ልባዊ ፍቅርና አክብሮት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የታዳሚዎችን ክብር የሚመጥን መስተንግዶና አቀባበልም ሳይጓደልባቸው ስቀው እንደተቀበልናቸው ስቀው እንዲሄዱ ማድረግ መቻል ትልቅና ተጠቃሽ ተግባር ነው። በሰው ሠራሽ ብርሃናት በፈካው የአደባባይ ማዕድ ዙሪያ ተሰባስበው “ዋንጫ ኖር! Cheers!” እየተባባሉ ሲደናነቁ ትዕይንቱ በቴሌቪዥን መስኮታችን ቤታችን ድረስ ደርሶ ተመልክተናልና ለዚህም ታላቅ ተግባር ኢትዮጵያ ሆይ አበጀሽ! ማዕድሽ ሙሉ ይሁን ብለን መርቀናታል።
ታዳሚዎቹ ጎምቱ የአፍሪካ መሪዎች ተወያይተው የደረሱባቸው ውሳኔዎች እየተቆነጣጠሩም ቢሆን በየሚዲያው ሲዘገቡ አድምጠን የገባን ገብቶን ባልገቡን ጉዳዮች ላይም “ይሁን!” በማለት ውጤቱን በአሜንታ ተቀብለናል።
በተለይም “አፍሪካውያን የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ ተባብረው ለማስወገድና የተሻለ አህጉር ለመፍጠር ከልብ ሆነው ሊሠሩ እንደሚገባ የተላለፈው መልእክት በተግባር ላይ የሚውል ከሆነ መልካምነቱ አያጠራጥርም።
ጤና፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የኢኮኖሚ ትስስርና የአየር ንብረት የሚሉት የተግባር ምላሽ የናፈቅንባቸው የጋራ አጀንዳዎች በአስቸኳይ እንዲተገበሩ ለመሪዎቹ በጋራ የተሰጡ የቤት ሥራዎች መሆናቸው ሲገለጽ ስለሰማን ለተፈጻሚነቱ ይቅናችሁ ብለን መርቀናቸዋል።
ኢትዮጵያ በመሪዋ ፍልቅልቅ ፈገግታ ታጅባ መሪዎቹን በደስታ ተቀብላ በሰላም መሸኘቷን እንደ ቀላል ጉዳይ ሳንቆጥር እኛ ልጆቿ “አርሜ ኬኛ! ‹እናት ሀገርን!›” በታላቅ ምስጋና፤ “አቢቹ” የሚል የፍቅር ቅጽል በስማቸው ላይ ያከልነው መሪያችንንም ከፍ ባለ አክብሮት ከወንበራችን ላይ ተነስተንና ባርኔጣችንን አውልቀን “ጎፍታ ኬኛ ባዬ ገለቶማ” እንላቸዋለን። መሪዎቹን ጋቢ አልብሰው በማሞቃቸውም ፀጋ ያልብስዎት ብለን መርቀናቸዋል። ክብሩ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ስለሆነ መመራረቁ ክፋት እንደማይኖርው እናምናለን።
ዳሩ ከመረጋገም ምን ትርፍ ይገኛል? “የኢትዮጵያ አምላክም” የጠላቶቻችንን ሴራና ተንኮል በጣጥሶ ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ስለረዳን እንደየእምነታችን የተትረፈረፈ ምሥጋና ብናቀርብለት ተገቢም አግባብም ነው።
ጓዳችን ሲፈተሽ፤
ለስብሰባው ስኬት ከኋላ ሆነው ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩትና፣ በጭንቀት ተወጥረው የሰነበቱት የአገራችን ጎምቱ ሹማምንትና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በሙሉ ድካሙ ገና እንዳልለቀቃቸው በሚገባ እንረዳለን።
የጉባዔውን ስኬትና ጉድለት ለመገምገምና ለመፈተሽም ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አልጠፋንም። ቢሆንም ግን ከአደባባዩ ቱማታ ወደ ጓዳችን ዘልቀን አገራዊ ህፀጾቻችንን ማረሙ ጊዜ የሚሰጠው ስላልሆነ እንደለመድነው “መንግሥታችን ሆይ!” በማለት ጆሮ እንዲያውሰን የምንማጸንባቸውን “አሳሮች” ከዚህ በታች እንዘረዝራለን።
አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት የተዋቀሩበት ቢሮክራሲ እንዲፈተሽ ደጋግመን ብንጮኽም ዛሬም “አባ ከና” ብሎ የሚያደምጠን ስላጣን ችግሮቻችን እየባሰባቸው እንጂ ሲሻሻሉ መመልከት ብርቅ ሆኖብናል። የሕዝብ እምባ ከከረጢቱ ውስጥ ተንጠፍጥፎ ያለቀ፤ የብሶት መገለጫ ምሬቱም የተሟጠጠ ይመስላል።
ግራ የምንጋባባቸው ጉዳዮች ከዕለት ወደ ዕለት እየበረከቱ እንጂ ሲሻሻሉ እያስተዋልን አይደለም። በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ትብታብ በመንግሥት የቁጥጥር ስልትም ሆነ በጾምና በጸሎት ሊፈታ የቻለ እስከማይመስል ድረስ ወደ ማን አቤት እንደሚባል ሕዝቡ ግራ ተጋብቷል።
ጉቦና እጅ መንሻ እንደ ቀደምት ዘመናት አዩኝ አላዩኝ እየተባለ በድብቅና በሽሽግ መከወኑ ቀርቶ በይፋና በግልጽ ከሆነ ውሎ ማደር ብቻም ሳይሆን ከፍታውን ጨምሮ ወደ ባህል ደረጃ ስለተሸጋገረ ቁመት እየጨመረ በመመዘዝ ላይ ነው። ይህ መከራችን ለመንግሥትና ለመዋቅር አስፈጻሚዎቹ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም።
ጉዳዩ በይሁንታ እንዲጸድቅ ተፈልጎም ከሆነ እንደ አንዳንድ አገራት “ነባር ባህል” ጉዳይ ለሚፈጽሙ የመንግሥት ተቀጣሪዎችና የፖለቲካ ተመራጭ ሠራተኞች በሙሉ ሙዳዬ ምጽዋት የሚሰበስቡበት ከረጢት ከወንበራቸው ቢሮ ፊት ለፊት እንዲቀመጥ ቢደረግ ይመረጣል። በአዋጅ የሚደነገግ ከሆነም ተገልጋዩ ቁርጡ ይነገረውና ትዕዛዙን እየተገበርን የሞታችንን ቀን እያነባን እንጠባበቃለን።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ (ወጣ ሲባልማ ይብስበታል) በየትኞቹም መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የዘግነቴ ክብር ተጠብቆልኝና ታክስ ከፋይነቴ ከግምት ውስጥ ገብቶ ሳልጉላላ ጉዳዬን በሕጉ መሠረት አስፈጽሜ መውጣት እችላለሁ የሚል ዜጋ አለሁ የሚል ከሆነ እርሱ ዕድል የቀናው ወይንም “ሃሎ!” የሚባል ዘመድ ወይንም ጓደኛ ያለው ሊሆን ግድ ነው።
ከዚህ ውጭ የብዙኃን ዜጎች ድምጽ ይደመጥ የሚባል ከሆነ ጀማው ከጸሐፊው ሃሳብ ጋር እንደሚስማማ መቶ በመቶ ማረጋገጥ አይሳንም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ላለፉት ሰላሣ ሰባት ዓመታት ያህል ባለመታከት ይሄንን መሰል “የቁራ ጩኸት” ብዕሩን እያስጮኸ መኖሩ የትዕግሥቱን ስፋት ብቻም ሳይሆን ሥር የሰደደው አገራዊ ፈተና ምን ያህል ከብረት አሎሎ እንደጠነከረ የሚያሳይ ጠቃሚ ማስረጃ ነው።
በአገራችን ጓዳ ውስጥ የተፈለፈለው ዘርፈ ብዙ ችግር ኢትዮጵያን ወዴት አድርሶ የት እንደሚያሳርፋት ማሰቡ በራሱ እግዚኦ አያድርስ አሰኝቶ እንድናማትብ ያስገድደናል።
ዕድሜያችንን በሙሉ እያነባን ከመኖር ጎን ለጎን የተስፋችን ቡቃያ የሚያቆጠቁጠው በእንክርዳዶች መካከል አልፎ አልፎ በመልካም ፍሬዎች የሚመሰሉ የሕዝብ አገልጋዮችና ሹመኞችን ስለምናስተውል ነው።
እንጂማ ዕለት በዕለት እንደምናስተውላቸው ጥልፍልፍ ፈተናዎች ቢሆን ኖሮማ ይሄኔ እስትንፋሳችንም ሆነ ብዕራችን ተቃቅፈው ለዘለዓለሙ ባሸለቡ ነበር። እንኳንም በብስጭታችን ምክንያት ለደም ብዛት እንጂ ለሞት አልፈን አልተሰጠን። እንኳንም በጨለማ መካከል ተስፋ የሚፈነጥቁልን የሕዝብ አገልጋይ ጥቂት ቅሬቶች ኖሩልን። ሰሞኑን የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ በርካታ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ብቅ የማለት ክፉ እድል ገጥሞኝ ነበር።
ያለ ምንም ማጋነን የሄድኩባቸው መንግሥታዊ ተቋማት በሙሉ የተወረሩት በተሰላቹ፣ እጅ እጅ ለማየት በፈጠኑ፣ ተገልጋዩን ከማክበር ይልቅ አዋርዱ የሚል ትዕዛዝ የተሰጣቸው የሚመስሉ “ደመወዝተኞች” መበርከታቸውን ነው። የከተማውን የውልና ማስረጃ ጽ/ቤቶች፣ የመንገድ ትራንስፖርት ተቋምን፣ የግብር ሰብሳቢ መ/ቤቶችን (ይህንን መንግሥታዊ ተቋም እንኳን መሥሪያ ቤት ከማለት ይልቅ ማስለቀሻ ቤት ማለቱ ይቀላል)፣ የወረዳና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶችን … ላልዘልቅበት ዝርዝሩን ጀመርኩ እንጂ በአካል እየሄዱ የችግሩን ግዝፈት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
ጸሐፊው በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ “አገሬን አገለግላለሁ” በሚል ተስፋ ትምህርቱን እንደጨረሰ ከተመቻቸ የባዕድ ምድር ሳይውል ሳያድር ስለመመለሱ የተጸጸተበት ጊዜ ቢኖር ይህ ወቅት ነው። ከትናንት ይልቅ ዛሬ ይሻላል ብለን የደሰኮርነው ተስፋችን ሁሉ እንደ ጉም በንኖ ከማስተዋል ምን የከፋ ነገር ይኖራል? በተደጋጋሚ ለማስተዋል እንደሚቻለው ትልቁ አገራዊ በሽታ በኃላፊነት ተዋረድ መሠረት አንድ የበታች ሠራተኛ ለአለቃው መታዘዝ ያለመፈለጉ አንዱ ሙልጭ ብሎ የጠፋ ባህል ነው።
“ተገልጋይ ንጉሥ ነው!” የሚለው ያረጀውና ያፈጀው አባባል ከእነ ሉሲ ጋር ቅሪተቢሮክራሲ ሆኖ ሙዚዬም ከገባ ሰነባብቷል። በምትኩም “ተገልጋይ ማልቀስ ግዴታው ነው!” ወደሚል “እድገት” ተሸጋግሮ ልቅሶና እዬዬ የባለጉዳዮች መታወቂያ ሆኗል።
በዚሁ ድምጸትና ስሜት ከአንድ ቀን በፊት ለማከብራቸው ለወጣቱ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ስልክ ደውዬ “የተገልጋዩን ለቅሶና ድምጽ በስልክ ውስጥ” እንዲሰሙ ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ግብረ መልሳቸውንም በጉጉት እጠብቃለሁ።
ግን እስከ መቼ?
እርግጥ ነው አገራችን በብዙ ውጥረቶች ተከባ የምታቃስትባቸው ጉዳዮች በርካታ እንደሆኑ ይገባናል። የጦርነቱ ዳፋ ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ ነገሮች ወደ ቀድሞ መልካቸው እንዳልተመለሱም አይጠፋንም።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሸሽግው ሕዝብና ሥርዓቱን ለማላተም ሰይጣናዊ ተልዕኮ የተላበሱ የሕዝብ ቅንቅኖች ተጠራርገው እንዳልጸዱም ይገባናል።
ወሳኞች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ተረጋግተው በመደበኛ ተልዕኳቸው ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ ቀልባቸውን የሚሰልቡ ብዙ ውስብስብ ወቅታዊ ችግሮች እንደሚኖርባቸው ሳንገምት አልቀረንም።
ቢሆንም ግን “ባለቤት አልባ” እስከ መሆን የደረሰው መንግሥታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ በአግባቡ ተፈትሾ እልባት እስካልተሰጠው ድረስ “ቆይ ብቻ” የሚያሰኘው ፉከራ ሌላ አገራዊ መከራ እንዳያስከትል በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል።
ለመሆኑ በካርዳችን አሸናፊነት ምሩን ብለን የመረጥናቸው የሕዝብ እንደራሴዎች ውሎ አምሽቷቸው ምን ይመስላል? ቢያንስ በተመረጡባቸው አካባቢዎች እየተገኙ የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄ ለማዳመጥ ምን ሰነካላቸው? “ከበሮ በሰው እጅ ያምር . . .” እንዲሉ ሥልጣን በእነርሱ እጅ ሲወድቅ ምን ፈየዱልን ወይንስ ጭርሱኑ ነገረ ዓለሙን ሁሉ ዘንግተው በምክር ቤታቸው ወንበሮች ላይ አሸለቡ? ምረጡን ብለው ሲቀሰቅሱን በገቡት ቃል መሠረት እኛ ዜጎች የከፈልንላቸው ብዙ ክቡር ዋጋ ስላለ ቢስሙም ባይሰሙም ወደ ቀልባቸው እስኪመለሱ ድረስ እንሞግታቸዋለን።
ጮኸን ጮኸን አልሰማ ብለው ድምጻችን የሚሰልል ከሆነም ወንበራቸውን እንዲለቁ እንታገላቸዋለን። መንግሥትም ቢሆን “ይጯጯኹ ምን እንዳይመጣ ነው?” ከሚለው ደርጋዊና ኢህአዴጋዊ ደዌ ቢፈወስ ይበጀዋል።
በተለይ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚመራቸውን ተቋማት ገመናቸውን እየገላለጠ የወረሩትን ተባዮች እንዲያራግፍ በሕዝብ ድምጽ እንጠይቃለን።
ይህ መልዕክት ለሌሎቹ የአገራችን ክፍሎችም ስለሚሰራ “የሕዝብ አቤቱታ ወደ ኡኡታ” ከመለወጡ አስቀድሞ መንግሥት ሆይ! ጆሮህን ከፍተህ ስማን! አይንህን ገልጠህ ቢሮክራሲህን ፈትሽ!? ሰላም ይሁን!::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014