የአፍሪካ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባችን እንደስሟ አብባና አሸብርቃ 35ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ታዳሚዎችን ጠብ እርግፍ ብላ እያስተናገደች ትገኛለች።በተለይም ኮረና እና ጦርነት አጥልቶበት ከነበረው ክፉ መንፈስ ወጥታ እንዲህ በአማረና በደመቀ ድባብ መታየቷ ለሦስት ዓመታት ርቀው የቆዩትን አፍሪካውያን ወገኖቻችንን ብቻ ሳይሆንም ለእኛም ለመዲናዋ ነዋሪዎች ልዩ ተስፋን አጭሮብናል።
እንግዶቿም በመዲናይቱ ጨዋና አክባሪ ነዋሪዎች እየታገዙ የሞቀውን መስተንግዶ እየኮሞኮሙና እያጣጣሙ ስለመሆኑ ታዝበናል።ብዙዎቹም ባይተዋርነታቸውን ርግፍ አድርገው በመተው በከተማይቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ጉብኝታቸውን ቀጥለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የጉባዔው ታዳሚዎች አህጉሪቱ ባጋጠማት የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዙሪያ ከመምከር ባለፈ መሬት ላይ የሚወርድና ሕዝቡ ከገባበት ማጥ ውስጥ የሚያወጣ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ከጉባዔው ታዳሚዎች ተጠባቂ ሆኗል።
በተለይም ደግሞ አህጉራችን አፍሪካ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት በታሪኳ አይታው በማታውቀው መጠን መፈንቅለ መንግሥቶችን ያስተናገደች እንደመሆኑ ይህንን አይነቱን ፀረ- ሰላም እና እድገት ከሆነው የትግል ስልት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፖለቲካው ተዋናዮች ስነልቦና መንቀል የሚያስችል የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨትም ሆነ ውሳኔ ማስተላለፍ ከእነዚሁ መሪዎቻችን ይጠበቃል።
እንደሚታወቀው ባሳለፍነው ዓመት ብቻ ቻድ፣ ማሊ፣ ጊኒ ፤ መካከለኛው አፍሪካ እና ጎረቤት አገር ሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ካስተናገዱ የአፍሪካ አገራት መካከል ይገኙበታል።
በእነዚህ አገራት በፈጠረው የፖለቲካ ስርዓት ሳቢያ ዜጎቻቸው ፀረ ዲሞክራሲ በሆኑ የጦር ኃይሎቻቸው በትር ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ይገኛል።ይህም ደግሞ የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ እና ኮረና ቫይረስ ያደቀቀውን የአገራቱን ዜጎች ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።
በተለይም የዚሁ ችግር ሰለባ የሆነችው መንግሥት ያስተናገደችው ጊኒ የአሁኑ መፈንቅለ መንግሥት ለዘጠነኛ ጊዜ የተደረገባት ሲሆን ይህም በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ውጤት እንደሆነ ይነሳል።
በዓለም ላይ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላት እና የፖርቹጋል ቀኝ ግዛት የነበረችው ይህቺው አገር በከፍተኛ የብድር እና የውጭ እርዳታ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ ያላት የዕፅ አዘዋዋሪዎች መፈንጫ ሆናለች፡፡ ጊኒን ለአብነት አነሳን እንጂ የዚሁ መፈንቅለ መንግሥት ትኩሳት እንደወረርሽን እየተስፋፋ በርካታ የአፍሪካ አገራትን በማዳረስ ላይ ይገኛል።
እርግጥ ነው፤ አሁን ላይ በተለያዩ የአህጉሪቷ አካባቢዎች ያጋጠመው መፈንቅለ መንግሥት በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ዓ,ም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የተለየ አንድምታ አለው።ይኸውም አሁን ላይ ኅብረቱም ሆነ መላው አፍሪካዊ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹን ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው።
ለዚህም ነው ሌላው ቀርቶ ሱዳን ውስጥ የጦርኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት በማድረጉ ጠንካራ የተቃውሞ ሰልፍ እየተመለከትን የምንገኘው።ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ህብረቱ ራሱ መፈንቅለ መንግሥትን በተመለከተ ጠንካራ አቋም እያሳየ መሆኑ ይህንን ጊዜ ያለፈበት የስርዓት ለውጥ የሚያስተናግድ ነባራዊ ሁኔታ አለመኖሩን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችም የአህጉሪቱ ድርጅት ቀጣይነት የታየበት ርምጃዎችን መውሰዱ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ለአብነት ያህልም በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ አባልነቷን ለጊዜው ማገዱ ይህንን አይነቱን ተግባር ከአህጉሪቱ ለመንቀል በር ከፋች እንደሆነም ነው የሚያነሱት። እንዲህ ሆኖ በሱዳንም በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ሕዝቡ አምባገነኖችን በመቃወም በአደባባይ ድምጹን ማሰማቱን መቀጠሉ አሁንም ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ያለውን ጥማት ያሳያል።
በዚህ ረገድ ኅብረቱ በመፈንቅለ መንግሥቱና ይህንን በሚያራምዱ የፖለቲካ ኃይሎች ዙሪያ አቋሙን ግልፅ ባደረገ መልኩ ጠንካራ ውሳኔ መስጠት ላይ እምብዛም እንደሆነ እነዚሁ የፖለቲካ ተንታኞች አሰረግጠው ይናገራሉ። በአህጉሪቱ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በማድረግ ረገድም ህብረቱ ሚናውን እየተወጣ ነው ለማለት እንደማይደፍር ያመለክታሉ።
ለዚህ ደግሞ ማሳያ አድርገው የሚያነሱት የዩጋንዳው የረዥም ዓመታት መሪ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለስድስተኛ ጊዜ ሥልጣናቸውን ሲያራዝሙ ሕብረቱ ዝምታን መምረጡን ነው።
ዋነኛ ተቀናቃኛቸውቦብ ዋይን በምርጫው ወቅት በዩጋንዳ ታሪክ የማይዘነጋ ማጭበርበር ተፈጽሟል ባይ ናቸው። ከምርጫው መጀመሪያ ዝግጅት ጀምሮ በዩጋንዳ ታሪክ ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት እንደነበር፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ እኔ የምመራው የሕዝቦች ኃይል ንቅናቄ ፓርቲ ደጋፊ ወጣቶች በመንግሥት ታግተዋል፡፡
አሁንም ቢሆን የችግሩ ሰለባ የሆኑ በእነዚሁ የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ ሕዝቦች መፈንቅለ ስርዓት የሚመጡ መንግሥታት መቃወማቸውን ቀጥለዋል።የመፈንቅለ መንግሠቱ እንቅስቃሴ በሱዳን ብቻ ሳይሆን በማሊ፣ በሴኔጋል እና በስዋዚላንድም ጠንካራ ህዝባዊ ተቃውሞ ታይቷል።
ይሁንና አሁንም ኅብረቱ ጥርስ ኖሮት የነውጡን መሪዎች በማገድም ሆነ በዜጎች ላይ ያደረሱትን ጉዳት በመግታት ረገድ ረብ ያለው ስራ ሲሰራ አይታይም።ሌላው ይቅርና ትርምሱ እንዲቀጥል አልመው ለአማፂዮቹ የተለያዩ ስውርና ገሃድ የወጣ ድጋፍ የሚያደርጉ የቀድሞው ቀኝ ገዢ አገራትን ‹‹አርፋችሁ ተቀመጡ›› ብሎ የመገሰፅ አቅም ማጣቱ ጉዳይ ብዙዎች ላይ ቁጭት ፈጥሯል።
አፍሪካ ቀኝ ገዢዎቿ ከሰጧት ጨለማ ስያሜ እንድትወጣ፤ ለዜጎቿ የምትመች አህጉር ትሆን ዘንድ የመሪዎቿ ሚና ወሳኝ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም።በተለይም እየተካሄደ ባለው በዚህ አህጉር አቀፍ ጉባዔ የሚታደሙ መሪዎች እንደወትሮው መሬት ላይ የማይወርዱ አጀንዳዎች ላይ ጉንጭ አልፋ ውይይታቸው ወጥተው ጉልበታም የሆነ ውሳኔ ማስተላለፍ ከእያንዳንዳቸው ይጠበቃል።
ከሁሉ በላይ ወክለው የመጡት ሕዝባቸውን ህይወት የመታደግ ኃላፊነት በጫንቃቸው ላይ መሆኑን ተገንዝበው መፈንቅለ መንግሥትን ላይደገም ከስራቸው መንቀል ትልቁ የቤት ስራቸው ነው የሚሆነው።
ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ቁርጠኛ የሆነ እና ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እለት እለት የሚተጋ መሪ ያሻታል ባይ ነኝ።ከሁሉ በላይ ደግሞ ለውጭ ኃይሎች ጫና የማይንበረከክ ጣልቃ ገብነት ከእንግዲህ በቃ ብሎ የወደፊቷንና የበለፀገችውን አፍሪካ ለትውልድ የሚያኖር እንደራሴ ሊበዛልን ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።ለዛሬ አበቃሁ! ቸር እንሰንብት!፡፡
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014