ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ናቸው። አሸባሪው ሕወሓት የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በተለይም ከፍተኛ የተደራጀ የሰው ኃይል እና ዘመናዊ ተተኳሾችን የታጠቀው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት ባደረሰበት ጊዜ በቀጥታ የዕዛቸውን ሰራዊት ይዘው ጠላትን በመፋለም ጀብድ የፈፀሙ የጦር መሃንዲስ ናቸው።
አሸባሪው ሕወሓት ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በገባ ጊዜ በ15 ቀናት ውስጥ በመደምሰስ ተልዕኳቸውን በብቃት ተወጥተዋል። 150 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ በመግባት ጠላትን በመቁረጥ እጅግ ጀብድ የፈፀመው የደቡብ ዕዝን ሲመሩ ነበር። በእነዚህ ወቅቶች የፈጸሟቸው ጀብዶች በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም የሚፃፉ ናቸው።
በዛሬ ዕትማችን የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ አድርገናል። መልካም ንባብ። አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሚመሩት የደቡብ ዕዝ እውቅና እና ሽልማት ሲሰጠው ምን ተሰማዎት? ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- ይህን ሥራ ሲሠራ የቆየው በየደረጃው ያለው የሰራዊት አመራርና እስከ ታች ያለው ተዋጊ ዩኒት ይህ እውቅና እንዲያገኝ ሲደረግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል።
ደቡብ ዕዝ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በአገሪቱ ላይ የተቃጣውን በተለይ ደግሞ በተቋሙ ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት ጊዜ አልወሰደም። በፍጥነት ቆቦ አካባቢ በመገኘት ጠላትን የመከተ ዩኒት ነው።
ከዚያን ዕለት ጀምሮ በጣም ፈታኝ የሆኑ ማንም የማይደፍረውን ጀብድ እና ግዳጅ በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር እየወጣና እየወረደ ፈፅሟል። ዕዙ ግዳጁንና የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ፈፅሟል።
በመሆኑም ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ያለፉ አመራሮችና ተዋጊ ክፍሎችም እውቅና በመሰጠቱ በጣም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል።
አዲስ ዘመን፡- ተሸላሚዎች የተሸለሙበት መስፈርት ምንድን ነው?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- በእርግጥ ይህ በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ የለፉ ጀግኖች፣ የሰራዊት አባሎች እና ክፍሎች አሉ። ሆኖም እንደማሳያ የሚሆኑ ተምሳሌት የሚሆኑትን ወስደን ለማበረታታት ያክል ብቻ ያደረግነው ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም ጀግኖች ናቸው። ሁሉም የተሰጣቸውን ግዳጅ በአግባቡ እና በብቃት የፈፀሙ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ጦርነቱ ሲጀመር ከፍተኛ የጦር ክፍልና መካናይዝድ ኃይሉ በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ትግራይ ክልል እንደነበር ይታወቃል። ይህ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንዴት አሸባሪውን ሕወሓት መደምሰስ ተቻለ?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- ጦርነት በሚጀመርበት ወቅትም ሆነ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጋር በተያያዘ አብዛኛው የጦር ክፍሎቻችን በትግራይ ውስጥ ነበሩ። የተወሰኑትን የጦር ክፍሎች ለሕግ ማስከበር፣ ሠላምና ማረጋጋት ስንል ወደ ደቡብ፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ አካባቢ የወሰድናቸው ነበሩ። ከዚህ ውጪ አብዛኛው የነበሩት በትግራይ ሰሜን ዕዝ ውስጥ ነበር። ከ1990 ጀምሮ በዚያው ነበሩ።
ለአብነት እኔ የምመራው የደቡብ ዕዝ ሰራዊት አባላት ከፊሉ ሰሜን ውስጥ የነበሩ ናቸው። በቦረና፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ አካባቢ የነበሩት አለመረጋጋቶችንና አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታትም ከሰሜኑ ክፍል መሳብና መወሰድ ስላለበት ኃይሉን ወደዚያ ወስደናል።
ይህ 21 ጉና ክፍለ ጦር የምንለው በትግራይ ክልል አዲግራት አካባቢ የነበረ ኃይል ነው። ከዚህ ውጪ ግን ወደ አምስት እግረኛ ክፍለ ጦር እና አምስት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ትግራይ ውስጥ ነበሩ። ከዚህ ውስጥ ሜካናይዝዶቹ በጣም ከፍተኛ የተኩስ አቅም ያላቸው ናቸው።
አገሪቱ የታጠቀቻቸው ከባድ መሣሪያዎች ያላቸው ክፍሎች ናቸው። አለን የምንለው በጣም የተደራጀ ባይሆንም በትጥቁም በሰው ኃይሉም አንድ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ቡሬ ላይ ነበረን።
ከዚያ ውጪ ከፍተኛ የተኩስ አቅም ያላቸው 4ኛ፣ 5ኛ፣ 7ኛ፣ 8ኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች እዚያው ትግራይ ውስጥ ነበሩ። ጠላትም በወቅቱ ያሰበው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮቹ ታንክ፣ መድፍ፣ ፒቲ አር፣ ቢ ኤም እና የመሳሰሉትን የታጠቁ ናቸው። ይህን ካፈረስኩ ኢትዮጵያን መቆጣጠር እችላለሁ የሚል ፅኑ ዕምነት በመያዙ ጥቃቱን አድርሷል።
ከዚህ ውስጥ ወደ ደቡብ እዝ የመጣው በእርግጥ በወቅቱም ተመድቦ የነበረው አልመጣም እንጂ 8ኛ ሜካናይዝድ ነበር።ይህ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት በሚፈፀምበት ጊዜ በውስጥ ጁንታው ያደራጃቸው ኃይሎች፤ በውጭ ደግሞ የተደራጀ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ጥቃት ተፈፅሞበት ነበር።
ይህ ኃይል የተኩስ ኃይሎችን ይዞ የወጣው እነዚህን ጥቃቶች በመስበር ነበር። የእዚህ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አመራሮችም ለሽልማት ቀርበዋል። የተኩስ አቅምንና የሰው ኃይልን አስተባብሮ ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ የተወጣበት ሁኔታ ነበር።
ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች ነበሩ። የወገን ኃይል አገርን መታደግ የቻለው ይህን በመስበር እና ጠላትን በመደምሰስ ነው።
በአጠቃላይ ግን ሁለት ሦስተኛው (2/3ኛው) የሰራዊት ክፍል ትግራይ ውስጥ ነበር ማለት ይቻላል። አዲስ ዘመን፡- ጠላትን ልዩ ኃይል እና ኮማንዶ እያለ ለዓመታት ከማሰልጠኑም በላይ በሰሜን ያለውን ሜካናይዝድ በማጥቃት በብዛት ተቆጣጥሮ እንደነበር ይታወቃል።
ታዲያ ጠላት የተሸነፈበት ታላቁ ምስጢር ምንድን ነው? ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- እውነት ለመናገር ከሆነ ሁልጊዜ ሀቅ የያዘ እና በትክክለኛ መስመር የሚጓዝ አሸናፊ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙውን ጊዜ ሌላውን አንነካም።
ነገር ግን የሚነኩንን፣ በእኛ ማንነት እና ሉዓላዊነት ላይ የሚመጡብን፣ የአገራችን ሕዝቦች ኩራት ለመስበር ለሚመጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ቀን እጁን ሰጥቶ አያውቅም። ይህን የውጭ ጠላቶቻችንም ይመሰክራሉ። በጣሊያን ወረራ ጊዜ ማንሳት ይቻላል። ጣሊያን ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን ብትወርም አልተሳካላትም።
ደርቡሾን ማንሳት ይቻላል እነርሱም አልተሳካላቸውም። እንግሊዞችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ብንመለከት የየመን ጦር በዚያን በእነርሱ ሞግዚት ስር ስለነበር በሱዳን በኩል መጥተው መቅደላ ላይ ያደረጉት ጦርነት ድባቅ መትተን አሸንፈናል።
ከታሪክ ስንነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን አገር እና ሕዝብ የመንካት ሃሳብና ፍላጎት የለንም። ከተነካን ግን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተንቀሳቅሰንና ተጠራርተን ጠላትን ለመምታት ጥረት እናደርጋለን። ይህ ሆኖ ጠላት የተደራጀ እና የታጠቀ ነው።
በሁለት እና ሦስት ዓመታት ዝግጅት ሳይሆን የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር ነኝ የሚለው ሕወሓት ለ27 ዓመታት አስቦበት ሲሠራ ቆይቷል። ጠላት 27 ዓመታት በሙሉ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር ነኝ በማለት ሲዘጋጅ፤ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሄደበት መንገድም የተጠና እና ትልቅ ዝግጅት የተደረገበት ነበር።
ይህ ቡድን መጀመሪያ ሲነሳ ትግራይን ነፃ አወጣለሁ ብሎ ነው። ነገር ግን በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ። በወቅቱ የደርግ ሥርዓት ላይ ያልተስተካከሉ አንዳንድ ነገሮች በመኖራቸው የቡድኑ አመራር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና ለመበዝበዝ የረጅም ርቀት ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ አገሪቱን ለመቆጣጠር ዕድሉን አግኝቷል።
አሸባሪው ሕወሓት የአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲፈረካከስም በሰራዊቱ ውስጥ እርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር ሲሠራ ነበር። ይህም ኢትዮጵያን የማዳከም አንዱ ዕኩይ ተግባር ነበር። ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በኋላ በ1993 ዓ.ም በተካሄደ ግምገማ በሰራዊቱ ውስጥ የሕወሓት ቡድን የበላይነት እየነገሰ ነው በሚል በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ።
በሌላው ላይ ጫና እያደረ ነው በሚል ቅሬታ ይነሳ ነበር። በ1997 ዓ.ም፣ በ2000 ዓ.ም መሰል ችግሮችና ቅሬታዎች በሰራዊቱ ውስጥ ይነሱ ነበር። በኋላ ይህ ፈንቅሎ ወጣ። ወጣቱ ይህን እየተረዳ በመጣ ጊዜ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝብና በአገሪቱ ውስጥ ማዕበል ተቀጣጠለ።
ማዕበሉ ሕወሓት የሚባለውን ቡድን አንፈልግም የሚል ነበር። በእውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብም ያደረገው ጥሩ ነገር ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ይህ ቡድን ይቅርታ ጠይቆ መኖር አለበት ብሎ ዕድል ቢሰጠውም መቐሌ ሄደው ሌላ ስትራቴጂ ነደፉ። የሕወሓትን ተግባር ሰራዊቱ በደንብ ይገነዛባል።
ይህን ስለሚረዳ ጥቃት በሚፈፀምበት ጊዜ የፈለገውን ያክል ቢታጠቅ የፈለገው ያክል ቢደራጅ በእልክ እና በወኔ አንድ ሰው እንደ አስር ሰው ሆኖ ተዋግቶ ድባቅ መትቶ ጠላት መቐሌን ለቆ ወደ ዋሻ እና ጫካ እንዲገባ አድርጎታል። ይህ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን በጣም እልክ አስጨራሽ ነበር። ምን ያክል ግፍ ሲፈፀምበት እንደነበር ይታወቃል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ወጣት ጀነራል መኮንኖችንና አመራሮች ወደ ሰራዊቱ እየተመለሱ ነው። እነዚህም በእልህና በወኔ ሲዋጉና ሲያዋጉ ነበር። ሕወሓት ሰበብ በመፍጠር ወጣት ጀኔራል መኮንኖችን ያለፍላጎታቸው ከአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲገፉ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።
ለአብነት ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ ጀኔራል ባጫ ደበሌ፣ አለምሸት ደግፌ ያለዕድሜያቸው ተገፍተው የወጡ ናቸው። ይህን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረድ። ከእነዚህ ውጪ ሌሎችም ተገፍተው የወጡ አሉ።
ጀኔራል ጌታቸው ሽፈራው፣ ጀኔራል አሎ አብዲ፣ ጀኔራል ኤፍሬም ባንጌ እና ሌሎች በርካታ ጀኔራል መኮንኖችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ለኢትዮጵያ ማገልገል የሚችሉ ወጣት ጀኔራሎች ናቸው። ተገፍተው የወጡት በርካቶች ናቸው።
እነዚህ ወደ ጦሩ ሲቀላቀሉ የፈጠረው ስሜትና ቁጭት ቀላል አይደለም። እነዚህን ነገሮች ሲሠሩ ሆን ብለው አስልተው ነበር። ሰራዊቱን ለማዳከም፣ ለመበታተን፣ የሰራዊቱን የማድረግ አቅም ለማሳጣት ሲሠራ ነበር። በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩ ጀኔራል አመራሮችን ይህን ይገነዛበሉ።
ስለሚገነዘቡም ጦርነቱ ሲጀመር ግዙፍ የሆነ የሰው ኃይልና የጦር መሣሪያ ቢኖራቸውም በነበረው እልህ፣ ወኔና ቁጭት ያንን ኃይል ደምስሰን ጫካ እና ዋሻ እንዲገባ ተደርጓል። ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ለመበዝበዝ እና ለማፈራረስ ጊዜ ወስዶ ሲሠራ የኖረ ቢሆንም ህልሙን ሙሉ ለሙሉ ማጨናገፍ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪ ሕወሓት የጽሞና ጊዜ ሲሰጠው ዳግም አማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ሲፈፅም ሰሜን ሸዋ ድረስ ለመድረስ አምስት ወራት ወስዶበታል። የአገር መከላከያ ሰራዊት መልሶ ሲያጠቃ ደግሞ በ15 ቀናት ተመልሶ ወደ ትግራይ የፈረጠጠበት ኦፕሬሽንና ድል እንዴት ተገኘ?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- ሥምሪቶችን አድርገን ግዳጅ ስንፈጽም በጠላት ላይ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራን ስናደርስ ነበር። መንግሥት ካለው ፍላጎት በመነሳት እንዲሁም በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት የሚያበቃ ነገር ስለሌለ ባለፈው ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም የጥሞና ጊዜም ሰጥቷል። እኛም ወቅቱን የያዝነውን ኃይላችንን ለማጠናከር፣ ለማሟላት ስልጠና ለመስጠትና ለማጀገን ጊዜውን እየተጠቀምንበት ባለንበት ወቅት ይህንን ሁኔታ እንደ ሽንፈት የቆጠረው የሕወሓት ኃይል የተለያዩ ቀዳዳዎችን በመፈለግ ሰርጎ ሊገባ ችሏል። ይህም ቢሆን ግን ሰርጎ የገባውን የጠላት ኃይል የመከላከያ ሰራዊታችን በሁሉም ግንባሮች ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ልክ አስገብቶታል።
የጠላት እሳቤ የነበረው እኛ ከትግራይ ስንወጣ ተሸንፈው ነው ብሎ በማሰብና ይህንንም ሕዝብ በተለይም ወጣቱን መቀስቀሻ ስላደረገው ኃይል ማግኘት ችሏል። እያንዳንዱ በክልሉ ያለ ገበሬ የታጠቀ ነው። ሚሊሻ እና ፖሊስ አለ፤ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይ ድረስ ያሉ የመንግሥት መስተዳድር አካላት አሉ፤ እነዚህን በጠቅላላ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ከጎኑ እንዲሰለፉ አድርጓል።
ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ጭምር የጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህንንም ኃይል በመያዝ በአማራ እንዲሁም በአፋር ክልሎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወረራን አድርጓል።
በዚህ ምክንያት ደግሞ ሁሉንም ቦታዎች የመከላከያ ሰራዊቱ ሊሸፍን ስለማይችል እነሱ አጋጣሚውን በመጠቀም ሰርገው ገብተዋል። ነገር ግን ይህንን ሰርጎ የገባን የጠላት ኃይል በብልሃት በጥበብ መደምሰስ እንደምንችል ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እናውቃለን፤ ይህንንም አድርገነዋል። በዚህም ደብረታቦር እና ባህርዳር ሊገባ የነበረን የጠላት ኃይል ጋሸና ላይ ወገቡን ቆርጠን ሳይወድ በግድ ወደመጣበት እንዲመለስ አድርገነዋል። ጠላት ያሰበውን ነገር ሳይፈጽም እንዴት አድርገን እንደምንቆርጠው እንደምንመታው እናውቃለን። ለምሳሌ ሰሜን ሸዋ መድረስ ችሎ ነበር፤ አዎ ደርሷል።
ነገር ግን ሃርቡ ላይ ያደረግነው ጦርነት ደግሞ ነገሮች እንዲዛቡበት አድርጓል። እዛ ስንቆርጠው ደግሞ በጠቅላላ እጅ ሰጠ ማለት ነው። ሕዝባችን ያስታውሳል ብዬ እገምታለሁ። በወቅቱ በአገር ውስጥ ያሉ ዲፕሎማቶች እንዲወጡ በማድረግ ሕዝቡን ብዥታ ውስጥ ለማስገባት ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን ሃርቡ ላይ ገብተን ስንቆርጠው የሚበላው የሚዋጋበት መሣሪያ ስናሳጣው ጠላት ሳይወድ በግድ እጁን ለእኛ ለመስጠት ተገዷል።
አዲስ ዘመን፦ የደቡብ ዕዝ እስከ 150 ኪሎ ሜትር ድረስ ሲቆረጥ የጦርነት ስትራቴጂ ነው ተብሎ ነበር እና እርስዎ የሚያስታውሱት እንደ ደቡብ ዕዝ ጠላት ከፍተኛ ምት የደረሰበትን ይንገሩኝ?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- በጣም የማስታው ሰውና የማልረሳው የጋሸና ነው። ጋሸና በጣም አስቸጋሪ መልከዓ ምድር ያለው ነው። በዚያ የክረምት ወቅት መሬቱ ጭቃና ዝናብ በበዛበት ጊዜ ጦሩ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉ ትልቅ ስኬት ነው።
ደብረ ታቦር እና ባህር ዳር ቢገባ ከዚያም አልፎ ደብረታቦርን ይዞ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ቢያቀና ኖሮ አደጋው ከባድ ነበር። በመሆኑም ደቡብ ዕዝ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሳያቅማማ ተቀብሎ ግዳጁን በአስደናቂ ጀብዱ ፈጽሟል። በጣም የማልረሳው ነገር በዚህ ውጊያ ላይ የመሬቱ አቀማመጥ ያለመመቸት ክረምቱ ተደማምሮ መኪና ለማንቀሳቀስ እጅግ በጣም ፈታኝ ስለነበር ቁስለኛ እንኳን የምናንቀሳቅሰው በቃሬዛ ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም፤ የወታደሩ ሬሽን ተተኳሽ የምናንቀሳቅሰው በሰው ኃይል በሸክም ነበር። ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ በእልህ በቁርጠኝነት አሳልፈነዋል። ከሁሉም በላይ ግን ካሳጊታ ላይ ጠላትን ተዋግተን ሚሌን መቆጣጠር እንደማይችል አሳይተንና በብዙ መስዋዕትነት አካባቢውን አስለቅቀን ስንጨርስ፤ ተጨማሪ ግዳጅ ተሰጠን።
እሱንም ያለምንም ማቅማማት ወስደን ከካሳጊታ በአፋር ዞን አምስት በሚባለው በኩል ረጅም ርቀትን በእግራችን ተጉዘን አርጎባ ደርሰን። ከዚያም ድሬ ቃሉ ወደሚባል አካባቢ ደርሰን ሃርቡ ለመግባት የነበረው ፈተና ቀላል አልነበረም። በተለይም አርጎባ ዞን አምስት በሚባለው የአፋር ክልል መካከል ላይ ምንም መንገድ አልነበረውም። ከዚህ የተነሳ ግማሹ በእግር የተቀረውን ደግሞ መንገድ እየጠረግን ኃይላችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማድረሳችን ቀላል አይደለም።
እዚህ ላይ መልክዓ ምድሩ እንዳለ ሆኖ ጠላት ከመጣ ደግሞ የተለያዩ ማነቆዎችን ስለሚፈጥር ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሥራው ተሠርቶ የሃርቡን ከተማ ግራ እና ቀኝ አስፋልት መንገዱ ተቆርጧል። እዚህ ደርሰን እስክንቆርጥ ድረስም ጠላት መረጃ አልነበረውም።
ይህ በጣም ከፍተኛ ድል የተጎናፀፍንበት ነው። ለሽልማት የበቁ ይህንን የሠሩ አዛዦች፣ አመራሮች እንዲሁም የሰራዊቱ አንዳንድ አባላት ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ የአሸባሪ ሕወሓት ቡድን ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በተጠጉ ጊዜ በሰራዊቱ ላይ ሐሜቶች ነበሩ። ይህንን እርስዎ ይሰሙ ነበር?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- እውነት ለመናገር ከሆነ ጀኔራል ሰለሞን እንዲህ ነበር የሚል ሀሜት አልሰማሁም።
የነገረኝም የለም፤ እታማለሁም ብዬ አላስብም። ጠላት ግን ከትግራይም ሳንወጣ ጀምሮ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ይሠራ ነበር። የዘመኑ ሌላው ጦርነትም የሥነ-ልቦና ጫና መፍጠር እና የጦር አመራሮች ያላደረጉትን አደረጉ እያሉ በሕዝቡና በሰራዊቱ ውስጥ አመኔታን እንዲያጡ ማድረግ ነው።
ጠላት ደግሞ በዚህ ስልት የተካነ ነው። አንድ ጊዜ ግን ልጆች እንደነገሩኝ በወልዲያ ጦርነት ወቅት ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ እና ጀኔራል እከሌ እያለ ጌታቸው ረዳ ተናግሯል ብለውኛል። ይህ ምን ማለት ነው ብዬ ትርጓሜው ላይ ብዙ አልተጨነኩበትም። ነገሩንም ላለው ሰው ትቼዋለሁ። በግሌ ግን ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለኢትዮጵያ አገሬ አንድነት እያንዳንዷን ቀንና ሰዓት ከሰራዊቴ ተለይቼ አላውቅም።
ከእነሱ ጋር በእያንዳንዱ ቦታ ወይም ግንባር ላይ እገኛለሁ። ጦሬን እመራለሁ፣ የጠላት የሥነ -ልቦና ጫናም እኔ ላይ ምንም ነው። እኔ የቆምኩት ለአገሬ ክብር ነው። አገሬ በልጆቿ አጥንትና ደም ተከብራ እንድትኖር የምጥር አንድነትና ሠላሟ ተከብሮ እንዲኖር የምሠራ ጀኔራል ነኝ። በኅብረተሰባችን ዘንድ በማወቅም ባለማወቅም የሚነገሩ ነገሮች ይኖራሉ።
በወቅቱ ግን በተለይም ከሰኔ ወር እስከ ታኅሣሥ ድረስ የመገናኛ ብዙኃንንም የመከታተል ዕድሉ ስላልነበረኝ የማውቀውም የምሰማውም ነገር የለም። እዚህ ላይ እውነት ለመናገር ሃርቡ፣ ካሳጊታ፣ ጭፍራ፣ ኮረት በር እና ሌሎች አውደ ውጊያዎች ላይ የእኔ አሻራ አለበት። በሕግ ማስከበር ውጊያውም ከሰራዊቱ ጋር ነበርኩ። ያደረግነው ውጊያ እጅግ ከባድ ነው። እኔ ግን እዚያው ነበርኩ። በዚህ ሰራዊቱም ያውቀኛል፤ ሕዝቡም ያውቀኛል። እንዳልከው ሐሜትም ቢያሙ እኔ ውስጤ ጤነኛ ስለሆነ ምንም አይመስለኝ።
አዲስ ዘመን፦ ጦርነቱ ሰሜን ሸዋ እየደረሰ በነበረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ወደጦር ሜዳ ክተት ብለው ነበር። ሁኔታው በእናንተ ላይ የፈጠረው ስሜት ምን ነበር? በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥስ እንዲህ ዓይነት መሪዎች እንዴት ይታያሉ?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- እውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክተት አዋጁን አውጀው እራሳቸውም ወደጦር ግንባር መጥተዋል። ይህንን ግን እኛ በፍጹም አላሰብንም ነበር። ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ግን ማዘዣ ጣቢያችን ላይ ሆነን ውጊያ ስንመራ እኔ ወዳለሁበት ካሳጊታ ግንባር መጥተዋል። በዚህ ጊዜ አብረዋቸው የነበሩ ሰዎችን ለምን ይዛችሁ መጣችሁ በማለት ተቆጥተን ነበር። ምክንያቱም የነበርንበት ቦታ በጣም ተኩስ የነበረበት ስለነበር እና አደጋ ያለው ቦታ ስለሆነ መስዋዕትነትም እየከፈለን ስለነበር የእሳቸው መምጣት ጥሩ አይደለም ብለን ነበር። ነገር ግን መምጣታቸው ደግሞ ለሰራዊቱ ትልቅ ሞራል የሰጠ ሆኖ አግኝተነዋል።
እኔ በነበርኩበት አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ቀን ሙሉ በመቆየትና ሰራዊቱ ምን እየሠራ እንዳለ በማየት አብረው ሆነው አመራር በመስጠት በማበረታታት ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጥንካሬን ሰጥተውናል።
ከዚያም ተመልሰው ጭፍራ ላይ ሲሄዱም ከፍተኛ የሆነ ሞራል ነበር። እሳቸው በዚህ ሁኔታ መታየታቸው በሰጡት አመራርነት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ስንወያይም ትልቅ አመራር ሰጥተዋል። ይህ አመራር ደግሞ ለዛሬው ድላችን ትልቅ አቅም ሆኖናል።
ይህ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ስንወስደው ደግሞ መሪዎቻችን ጀግኖች እንደነበሩ ከማስታወሱም በላይ ዛሬም አገራችን ሌሎች ተጨማሪ ጀግኖች እንዳሏት ያመላከተም ሆኗል። በዓድዋ ጦርነት አፄ ምኒልክ ከሰራዊታቸው ጋር ዘመተው ድል አድርገዋል።
አፄ ኃይለሥላሴም ይህን ታሪክ ደግመዋል፤ ወደ ግንባር ዘምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአባቶቻችንንና የአያቶቻችንን ታሪክ እንዲደገም አድርገዋል። ሕዝቡን፣ ሚሊሻውን ገበሬውን አነሳስተዋል፤ ይህ ሁኔታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ተመሳሳይ የሽብር አደጋ እየጣሉ ላሉት ኦነግ ሸኔና ሌሎች ቡድኖች ያልዎት መልዕክት ምንድን ነው?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- በአገራችን ውስጥ ሕወሓት የሚባለው ኃይል እዚህም እዚያም የሚፈጥራቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ይህንን እንደ አንድ ስትራቴጂ ይጠቀማል። ሕወሓት በአፈጣጠሩና በባህሪው ሠላም አይፈልግም። በጦርነት መሃል ለመጠቀም ይፈልጋል። ተመልክተህ ከሆነ ኦነግ ሸኔ እና ሕወሓት ጋብቻ የፈፀሙት ብዙም ሳይቆዩ ነው። እዚህም እዚያም ኦነግ ሸኔን ጨምሮ ፀረ ሠላም ኃይሎች አሉ። የእነዚህ መሪ እና አዝማች አሸባሪው ሕወሓት ነው። ሆነም ቀረ ይህንን ኃይልም የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም ሕዝቡም ጭምር በመተባበር እየተመከተ ነው።
ወደፊትም ቢሆን አገራችን ሠላም እንድትሆን ከተፈለገ በጫካ ውስጥ የሚኖር እና የታጠቀ ኃይል አያስፈልግም። ለምን በጫካ ውስጥ መኖር አስፈለገ? አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየትና በመደራደር ፍላጎትና ርዕዮተ ዓለም ያለው ለማራመድ መድረኩ ሰፊ ነው፤ ክፍትም ነው።
ጫካ ውስጥ ጠመንጃ ይዞ መቀመጥ አያስፈልግም። ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ይመልሳታል እንጂ አይጠቅማትም። ጫካ ውስጥ የሚገባው አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት የማስተዋለው ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ የሚገፋፋ ነገር የለም። ምህዳሩ የተመቻቸ ይመስለኛል።
ድሮ በአገራችን ምርጫ የለም። አሁን ግን ሕዝቡ የሚፈልገውን ይመርጣል የማይበጀውን ይጥላል። የሚጠቅመው በዚህ መንገድ መሄድ ነው። ሁሉም የየራሱ ሐሳብ አለው። ይህ ባህል ጥሩ ነው። ከዚህ ውጪ የእኔ ሐሳብ ብቻ መሆን አለበት ማለት አይጠቅምም፤ አይሆንም። ሌላውም ሐሳብ አለው። የሚበጀውን ደግሞ ሕዝቡ ያውቃል።
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመቻቸ ይመስለኛል። ጠመንጃ ይዞ ጫካ ውስጥ መንከራተት በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። እኛ ከአደጉት አገራት ለምን አንማርም? ያደጉት አገራት እንዴት እዚህ ስልጣኔ ላይ ደረሱ? መደማመጥና መተባበር መኖር አለበት። በዚህ ላይ ሕዝባችን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና መንግሥት በጥልቀት ሊሠሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በፈፀሙት ጀብድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል። ምን ተሰማዎት?
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን አተፋ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠ ሽልማት ነው። በግሌ ለእኔ የተሰጠው ሽልማት የእኔ ብቻ ሳይሆን የደቡብ ዕዝ ሽልማት ነው። እኔ ለብቻዬ የሠራሁት ሳይሆን ከልጆቹ ጋር በሠራሁት ሥራ ነው።
ይህ በመሆኑ ደግሞ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። ሽልማቱን የግሌ አድርጌ ሳይሆን የዕዜ አድርጌ ወስጀዋለሁ። ይህም ለቀጣይ ሥራ እኔንም የደቡብ ዕዝንም የበለጠ የሚያነቃቃ እና የሚያበረታታ ስለሆነ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንግዳ ስለሆኑ በተቋማችን ሥም አመሰግናለሁ።
ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር እና ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014