
አቶ መለሰ በየነ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ
ከጥቂት ዓመታት በፊት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላም እጦት ከሚታመሱት አካባቢዎች አንዱ ነበር። ጥቂት የማይባሉ የጥፋት የግጭትና የመፈናቀል ዜናዎችም በተደጋጋሚ የሚሰሙበት ነበር። በችግሩም ከሰው ሕይወት ማለፍ ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን ለጉዳትና ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ በኩል የወደመውም ንብረት ቀላል የሚባል አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ግን ክልሉ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ወደ መረጋጋት በመግባት የሰላምና የልማት ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል።
በየቦታው መሳሪያ ታጥቀው የነበሩት ተቃዋሚዎችም ከመንግሥት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ መግባታቸው የክልሉን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን መላውን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ ነው። ዛሬ በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ለመንቀሳቀስ ስጋት ያለበት አካል የለም። እንደ ሰላሙ ሁሉ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችም በኢኮኖሚው ረገድ የክልሉን የነገ መዳረሻ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ሆነዋል። ለመሆኑ ከዛ አስፈሪ ስጋት በመላቀቅ ዛሬ ለደተረሰበት ሰላምና የኢኮኖሚ መነቃቃት የተከናወኑ ተግባራት ምን ይመስሉ ነበር ስንል የክልሉን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነን አነጋገረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።
አዲስ ዘመን፤ የቤኒሻንጉል ክልል ሀገራዊ ለውጥ መካሄድ በጀመረበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር ?
አቶ መለሰ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በለውጡ ግዜና ከለውጡ በኋላ ያለበትን ሁኔታ ለመገምገም በቅድሚያ ከለውጡ በፊት የበሩ ሁኔታዎችን ማየት ይገባል። ክልሉ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት እጅግ በርካታና ውስብስብ ተግዳሮቶች የነበሩበት ነው። ከእነዚህም መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው ጉዳይ ክልሉ ከመሀል ፖለቲካ የተገለለ ሆኖ መቆየቱ ነው። በዚህ የተነሳ እንደ ክልል በሀገራዊ ጉዳዮች ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሲደረግ አልነበረም። ይህም በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ በርካታ ጥቅሞቹን ሳያገኝ ለዓመታት ለመቆየት ተገዷል። በተመሳሳይ በኢኮኖሚው ረገድም የነበረው አግላይነት ጫፍ የደረሰ ነበር። በእነዛ ዓመታት እንደ ሀገር እየተተገበረ ያለው ራስን በራስ የማስተዳደር የፌደራል ሥርአት ለቤኒሻንጉል ሕዝብ የይስሙላ አንጂ ሕዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እውነተኛ አልነበረም።
አጠቃለይ የነበረው አስተዳደር በከፍተኛ ደረጃ ጣልቃ ገብነት የነበረበትም ነበር። ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ እስከ ለውጡ ድረስ ድጋፍ ለማድረግ በሚል ሰበብ የሚመጡ ግለሰቦች ክልሉን በሞግዚትነት ሲያስተዳድሩት ቆይተዋል ለማለት ያስደፍራል። ከፌደራል መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ በሚልና በአማካሪነት የሚመጡ አካላት የራሳቸው ተልእኮና ዓላማ ያላቸው በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ከለውጡ በፊት በራሱ የሚወስንበት እድል እንዳይኖር አድርጎት ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በኢኮኖሚው ረገድም ክልሉ ሰፊና ሊለማ የሚችል የእርሻ መሬት እና ከፍተኛ የመአድን ሀብት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ቢሆንም፤ እነዚህ ሀብቶች የአካባቢውን ነዋሪና መንግሥትን ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚያስችል አኳኋን ሲተዳደሩና አገልግሎት ለይ ሲውሉ አልነበረም።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን መሰረታዊ ለውጥ ተከስቷል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሪዎች በክልሉ የሚኖረውን ሕዝብ ከማስተዳደር ባለፈ በፌደራል መንግሥት ውክልና በማግኘት በሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ የሚወያዩበትና ሊወስኑ የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል። እንደ ክልል ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ድጋፍና ትብብር ቢያስፈልግ ያንን ማግኘት የሚቻልበትም አካታች የፖለቲካ ሥርአት ተዘርግቷል። ዛሬ ላይ እንደ ክልል ነጻነት ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን ትክክለኛና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ሥርአት ተግባራዊ እየደረግን ነው ለማለት ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት እንደ ከዚህ ቀደሙ በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ሊገባ የሚችል አካል የለም። እንደ ሀገር የመጣው ለውጥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ከዚህ ቀደም በፖለቲካው ከሀገራዊ ተሳትፎ ተገለው የነበሩ ክልሎች በሀገራዊ ጉዳዮች የሚሳተፉበት እድል ተፈጥሯል። በዚህም ከተለያዩ ክልሎች ከሚንስትርነት ጀምሮ በሀገሪቱ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ለይ በመቀመጥ እያገለገሉ መሆናቸው ለዚህ ማሳያ ነው። በጥቅሉ የለውጡ መምጣት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብን ጥቅም ለማረጋጋጥ ያስቻለ ነው ለማለት ይቻላል። የተገኘው ተጠቃሚነትም ሕዝቡ በክልሉ ከሚያደርገው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በር የከፈተም ነው።
በተመሳሳይ ክልሉ ከለውጡ በኋላ በኢኮኖሚውም መስክ ከይስሙላ ባለፈ ሊተገበር የሚችል መብት አግኝቷል። ከለውጡ በፊት በክልሉ የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አግላይ ከመሆኑ ባለፈ ሙስናን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት የሚስተዋሉበት ነበር። በተለይም ከልማት ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለልማት በሚል በብድር መልክ ይመዘበር ስለነበር ከክልሉ በርካታ መሬቶች በልማት ባንክ በእዳ ተይዘው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት እነዚህ መሬቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ በመደረጉ በቂ ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ለባለሀብቶች ዝግጁ ለማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም የክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ባደረገው ጥሪ መሰረት በርካታ በዘርፉ መሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንቅስቀሴ በማድረግ ለይ ይገኛሉ። በጥቅሉ ለውጡ ክልሉን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማስጓዝ አስችሏል።
አዲስ ዘመን፤ ከዓመታት በፊት ክልሉ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብበት ነበር በአሁኑ ወቅት ደግሞ ክልሉ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር የክልሉ መንግሥት ምን ምን ሥራዎች አከናውኗል።
አቶ መለሰ፤ ከዓመታት በፊት የቤኒሻንነጉል ጉሙዝ ክልል ገጥሞት በነበረው ግጭትና መፈናቀል ዛሬ ለይ የተፈጠረው ሰላም እንደ ሕልም የሚታይበት ወቅት ነበር። ክልሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው አካላት በድብቅ የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ሆኖ ቆይቷል። በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ወደ ስልጣን መጥተው አዳዲስ እሳቤዎች መንጸባረቅና መተግበር ሲጀምሩ በክልሉ በተቃራኒው የተለየ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። የተለያዩ የፖለቲካ አሻጥሮችን በመፍጠር ስውር አካሄዶችን በመጠቀም በየቦታው ግጭቶች እንዲፈጠሩ በስፋት የሚሠሩ አካላት ነበሩ። የዚህ እንቅስቃሴ ዋነኛ መነሻ ዓላማ ክልሉን ሰላም በማሳጣት ሁከት በመፍጠር ማፍረስ ሲሆን ፤ እንደ መዳረሻ የያዙት ደግሞ እንደ ሀገር በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በመቀልበስ የእነሱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሥርአት እንዲቀጥል ማድረግ ነበር። በመጨረሻ ውጤቱ ባይሳካላቸውም እነዚህ አካላት የክልሉን የመሬት እና የማዕድን ሀብት በበላይነት ከመቆጣጠር ላለመውረድ ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። እነዚህ የፖለቲካ አሻጥረኞችና ልማታዊ ያልሆኑ ኪራይ ሰብሳቢ ጥገኛ ባለሀብቶች በኢሕአዴግ ድርጅት ስም ለረዥም ዓመታት በክልሉ ከፍተኛ ዘረፋ ሲያካሂዱ የነበሩት ናቸው።
በወቅቱ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ላይ በተለይም እንደ አሶሳ፤ ካማሺ፤ መተከል ባሉ አካባቢዎች ለውጡን አደጋ ያለው በማስመሰል ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። የሠሩት ሥራ ስር የሰደደና ትልቅ ችግር ሊያደርስ እንዲችል ደግሞ ትኩረታቸውን አድርገው የነበረው ወጣቱ ላይ ነው። ከዚህ ውስጥ በለውጡ ሰሞን በመቀሌ ፌደራሊስት ኃይል በሚል ሀገራዊ ጥሪ በማድረግ የጀመሩት እንቅስቃሴ ትልቅ ወጥመድ ያጠመዱበት ነበር። በዚህ ሂደት እንደ አንድ ተዋናይ ከተመረጡት መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩና በተለያዩ ሁኔታዎች ሳይሳካለቸው ቀርቶ አኩርፈው የነበሩት ተቃዋሚዎች ይገኙበታል።
እነዚህ አካላት የመቀሌውን ስብሰባ ከተሳተፉ በኋላ የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘው ወደ ክልሉ የተመለሱ ሲሆን ያንንም ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። መፈናቀሎችና የንብረት ውድመት እንዲሁም የተቋማት መፈራረስ ሊከሰትም በቅቷል። በክልሉ በሚኖረው ሕዝብ መካከልም ቅራኔ እንዲፈጠር በመደረጉ ከፍተኛ ማኅበረሰባዊ ቀውስና አለመተማመን ተከስቶ ነበር። ችግሩ በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ አካላት የሚተገበር ቢሆንም ከእያንዳንዱ ሴራና እንቅስቃሴ ጀርባ ከመሀል ሀገር ፖለቲካ ተገለናል ብለው ያሰቡት አካላት ትብብርና ድጋፍ ነበረበት። ይህ አጋጣሚ ዛሬ ነገሮች ተረጋግተው ሲታዩ ቀላል ቢመስልም ሕዝቡም ሆነ የክልሉ መንግሥት ብዙ ዋጋ የከፈለበት ነበር። በወቅቱ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን የከፋ ጉዳት እንዳይደርስና ነገሮች መስመር እንዳይስቱ ዋናውን ኃላፊነት በመውሰድ የሰሩት ሥራ ዛሬ ላይ ለመድረስ ያበቃና አንድ ውጤታማ የታሪክ አካልም ነው።
በዚያን ግዜ የነበሩትን ግጭቶችና ውጥረቶች ለማርገብ የመጀመሪያ ሥራ የተደረገው የሀሳብ ልዩነት እንዳለን በማመን ልዩነቶችን ከግጭት ባለፈ በመነጋጋር ብቻ ለመፍታት መንቀሳቀስ ነበር። ይህ ሀሳብ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ቢሆንም እንደየቦታው ለመተግበር የራሱ ጥበብና አካሄድ የሚጠይቅ ነው። በወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት በወሰኑት ውሳኔ በእሳቸው መሪነት ሁኔታዎችን በማመቻቸት እያንዳንዱን ቡድን ከሚመሩ አካላት ጋር ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ለማካሄድ ጥሪ አቀረቡ። ድርድሩ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን በማሰብም የተካሄደው በትጥቅ ትግል ውስጥ ካሉት ጋር ብቻ ሳይሆን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩትንም ባካተተ መልኩ ነበር። በውጤቱም በክልሉ ውስጥና በሌሎች አካባቢዎች «በሱዳን ታጥቆ ይንቀሳቀስ የነበረውን የቤኒን ሀይል ጨምሮ» ሁሉም ትጥቅ በመፍታት እና ስምምነት በመፈራረም በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ተቻለ። ዛሬ እነዚህ ተቃዋሚዎች ከነልዩነታቸው በፖለቲካውና አስተደደር ዘርፍ በክልሉ ከካቤኒ ጀምሮ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ተቀምጠዋል። በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመግባትም ክልሉን በጋራ በማስተደዳር ለሕዝብ ጥቅም በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ፤ የክልሉ መንግሥት የወጣቶች ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ምን ምን ተግባራትን አከናውኗል ።
አቶ መለሰ ፤ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና የተጀመሩ የልማትና የማኅበራዊ ግንኙነት የማጠናከር እንቅስቃሴዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ወጣቶች ለይ መሥራት አስገዳጅ መሆኑ እንደ መንግሥት አቋም ተይዟል። ከለውጡ በኋላ እንደ ክልል ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸውም ጉዳዮች መካከል በሰው ሀብት ልማት ረገድ ራሱን የቻለ፤ ብቃት ያለውና ለሕዝብ የሚቆም ትውልድ መፍጠር አንዱ መዳረሻ ነው። በዚህ መነሻነት በሥራ ፈጠራው ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በርከት ያሉ ወጣቶችን ሰርተው በላባቸው ባለሀብት ለማድረግ ተችሏል። ከዚህ ውስጥ በክልሉ ፕሬዚዳንት ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ ያለው ኢኒሼቲቭ ብዙዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አስችሏል።
ኢኒሼቲቩ የተጀመረው በክልሉ ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ ሀብቶችን በመለየትና በመገምገም ነበር። በዚህም በመአድን ዘርፍ ወርቅና ሌሎች የከርሰ ምድር ሀብቶች ፤ የቀርክሃ የሸክላና ሌሎች ሌሎች ለሥራ እድል ፈጠራ የሚሆኑ ሀብቶች ተለይተዋል። ወርቅ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተገኘ ሲሆን በብዙ ቦታዎች የድንጋይ ከሰልና ሌሎች መአድናት መኖራቸውም ታውቋል። ይህንን መነሻ በማድረግም መንግሥት በሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ማለትም የግብአት፤ የስልጠና፤ የቦታ፤ የመሳሪያ የብድር አቅርቦት ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።
ከእነዚህ መካከል በግጭት ውስጥ ለነበሩት የተፈጠሩ አጋጣሚዎችን ስንመለከት የክልሉ መንግሥት በካማሺ፤ በአሶሳና በመተከል ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት በመመደብ እና በባምባሲ ማሰልጠኛ ስልጠና በመስጠት ወጣቶችን ከጥፋት ወደ ልማት የማዛወር ሥራ አከናውኗል። እነዚህ ወጣቶች በወርቅ ማውጣት፤ በመአድን ልማትና በእርሻ በመሰማራት ዛሬ ለይ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ እድል በመፍጠር የሰላሙም የኢኮኖሚውም ዘብ ለመሆን በቅተዋል። በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት ከሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመሆን በቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች የተለያዩ ስልጠናና ድጋፎችንም አድርጓል። የተሰጠው ስልጠናና የተፈጠረው የሥራ እድል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ ትናንት በበርካታ ወጣቶች ውስጥ የተዘራውን አጥፊ ትርክት ከአስተሳሰባቸው ለማውጣት ያስቻለም ነው። ዛሬ በክልሉ ያለው የወጣቶች በሰላምና በልማት የመሳተፍ እንቅስቃሴ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጽንፍ በመያዝ ለሚንቀሳቀሱ አርአያ ሊሆን የሚችልም ነው።
ወጣቶችን የማብቃት እንቅስቃሴው በኢኮኖሚው ብቻ የተገደበ አይደለም። በአሁኑ ወቅት የወጣት ሴትና አዳዲስ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በአመራር ደረጃም የሚገኙት በርካቶች ናቸው። ከቀበሌ ጀምሮ መንግሥትን በሰላማዊ መንገድ የሚሞግት የሕዝብና የሀገር ፍቅር ያለው ትውልድ የመቅረጽ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። እንደ ክልል ከትምህርት ሥርአት ዝግጅት ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶት አየተሠራ ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራትን መሰረት በማድረግ ነው። ወጣቶች እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ማዘጋጀት እድሜያቸው ለሥራ ሲደርስ በሥራ ፈጠራ በግለሰብና በመንግሥት በመቀጠር የሥራ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ በስፋት እየተሠራ ይገኛል። ይህም ወጣቶች በሥራ ፈትነት ወደተለያዩ ጥሩ ያልሆኑ ባኅሪያትና ተግባራት እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ አንደ ከዚህ ቀደሙ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉበትንም እድል ያጠፋል።
አዲስ ዘመን፤ በክልሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ ይታወቃል። የክልሉ መንግሥት ይህንን ብዝሃነትን ባማከለ መንገድ ክልሉን ለማስተዳደር እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች እንዴት ይገለጻሉ።
አቶ መለሰ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አንድ ወጥ ብሔር፤ ሀይማኖትና ማንነት ያለው ማኅበረሰብ ያለበት አይደለም። ሁሉም አካባቢ የቋንቋ የእምነትና የማንነት ብዝሀነትን ያቀፈ ነው። በሁሉም ቦታ ከአምስቱ የክልሉ ብሔረሰቦች ባለፈ ኦሮሞ፤ አማራ፤ አገው፤ ደቡብ ሕዝቦችና ሌሎችም በስፋት የሚገኙበት ነው። ዛሬም ድረስ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሕብረተሰብ መስተጋብበር አለ። ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ በመሻገር ዛሬ ያለውን ሰላም ለመፍጠር ይህ ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስርም የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው። ዛሬም የፖለቲካ ተሳትፎው አካታችነት የሌሎችን ውክልና በማስተናገድ ረገድ ጥሩ የሚባል ተሞክሮ ያለበት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች ከወረዳ አስከ ክልል ድረስ በምክር ቤትና በኃላፊነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማስመዝገብ ብሎም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ሁነኛ መንገድ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ይረዳል።
አዲስ ዘመን ፤– በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የኦኮኖሚ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ መለሰ፤ በክልሉ ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ልዩነት ያለበት ነው። ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ቢሆንም በሚጠበቅበት ደረጃ ጥቅም ለይ ሳይውል ቆይቷል። ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ግን የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ተደራሽ መሆን፤ ዘመናዊ የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ መደረግ ጀምረዋል። ክልሉ በግብርና ብዙ ሊሰራበት የሚችል ከክልሉ አልፎ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ፌደራል መንግሥት በልዩ ትኩረት ድጋፍ እየደረገለት ይገኛል። ለዚህም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብትም ይገኛል። በተለይም በቅርቡ በሰላም ተመላሾችና ሌሎች ወጣቶች እንቅስቃሴ የተጀመረበት የአሳ እርባታ እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት ነው። አሁን የተጀመሩት ሥራዎች እነዚህን አቅሞች በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችሉ ናቸው። ይህም ሆኖ ካለው እምቅ ሀብትና አቅም አኳያ የተጀመሩት ሥራዎች በቂ የሚባሉ አይደሉም። በመሆኑም ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን በማመን ራሳችንን ለትልልቅ ፕሮጀክቶች እያዘጋጀን እንገኛለን።
በሌላ በኩል እንደ አንድ የኢኮኖሚ ትሩፋት የሚታያው በስፋት እየተከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ ነው። እነዚህ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የነዋሪዎችንም ሕይወት የቀየሩና ጠንካራ የሕዝብ ትስስር እንዲኖር ያስቻሉም ናቸው። በከተማዋ እየተካሄዱ ላሉት የኮሪዶር ልማትና ሌሎች መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች ሕብረተሰቡ በራስ ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ድጋፍ የእኔነት ስሜት ለመፈጠሩ አመላካች ነው። ለመንገድ ግንባታ ብቻ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ብሮችን በግለሰብ ደረጃ ያዋጡ ግለሰቦች ተገኝተዋል። ምንም እንኳን ምትክ ቦታና ካሳ የሚሰጥ ቢሆንም ለልማት ቤታቸው የሚፈርስባቸውና ቦታቸው የሚነካባቸው ግለሰቦችም ትብብር የሚያስደንቅ ነበር። በተለይም በተያዘው በጀት ዓመት ከአስራ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር በላይ ደረጃውን የጠበቀ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ለአሶሳ ከተማ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ያስቻለ ሆኗል። በሁሉም አካባቢዎች የኮብል ስቶን መንገድ ግንባታም እየተገነባ ይገኛል።’ ይህ ግንባታ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለሌሎች ሕዝባዊ የልማት ሥራዎች ትልቅ መነሳሳትንም የፈጠረ ሆኗል።
በተጨማሪ በለውጡ ወቅት ወድመው የነበሩ የጤና ተቋማት፤ ትምህርት ቤቶችን ሌሎችንም መልሶ የመጠገንና ሙሉ ለሙሉ ወደነበሩበት ተመልሰው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ ይገኛል። ነገር ግን በዚህ ረገድ በወቅቱ የነበረው ውድመት ከፍተኛ ስለነበር ሁሉንም መሸፈን አልተቻለም። ሁሉንም ወደነበሩበት ለመመለስ ደግሞ በትክክል የደረሰውን ጉዳት መለየት ስለሚያስፈልግ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በኩል ጥናት እየተደረገ ይገኛል። ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ በማግኘት ሕብረተሰቡንም በሙሉ አቅም በማሳተፍ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚሠሩ ሥራዎችም ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን ፤ በክልሉ የተጀመሩ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ለውጦችን ለማስቀጠል ምን አቅድ ተይዟል።
አቶ መለሰ በየነ፤ ለውጥም ሆነ ብልጽግና ሲታሰብ የሕዝብ ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ የመሪዎች ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በዚህ ረገድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከትናንት ችግር ያወጡት መሪዎች በአሁኑ ወቅት እያሳዩት ያለውን ብልጽግና ለማስቀጠል ብቃቱ ያላቸውና ቁርጠኞችም ናቸው። በየደረጃው ያለነውም አመራሮች እንደ ክልል ትናንት ነገ እንዳይሆን ለመሥራት በስፋት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ይህም ማለት በክልሉ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ሁሉን አቀፍ አካታች ሥርአት ዘላቂነት ባለው መልኩ በኢኮኖሚውም በፖለቲካውም የሁሉንም ተሳትፎ እንዳቀፈ እንዲቀጥል ማስቻል ማለት ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተገኘው ምቹ ሁኔታ በትምህርት በጤና በማኅበራዊ ዘርፍ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል። ከዚህ በኋላም ክልሉ ለፖለቲካ ፍጆታ ብሎ ሳይሆን በእውነት ሕዝቡንም ክልሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ። በዚህ ረገድ ከስምምነት ለይ የተደረሰበት አንድ አካሄድ አለ። እሱም «ምንም ነገር ተጀምሮ መቆም የለበትም» የሚል ነው። ትውልዱም መጀመርን ወይንም የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥን መዳረሻው እንዳያደርግ ሰርተን በማሳየት ለማስተማር የምንቀሳቀስ ይሆናል።
ይህም ሆኖ እንደ ክልል መሠራት ያለባቸው ግዜ የማይሰጡ የቤት ሥራዎችም አሉብን። ለምሳሌ በገቢ አሰባሰብ ረገድ ከግዜ ወደ ግዜ ከፍተኛ መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም ከሚጠበቀው እና ሕብረተሰቡ ከሚፈልገው የልማት መዳረሻ አኳያ ብዙ ይቀረናል። በመሆኑም ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ግብር የመሰብሰብ ሥርአት መዘርጋት ይጠበቃል’። ይህንንም መሰረት በማድረግ ምን ያህል የገቢ ሀብት አለ የሚለውን ለመለየት ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆኑ የክልሉን አጠቃለይ የገቢ አቅም ማጥናት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመናል። ጥናቱ የተጀመረ ሲሆን ተጠናቆ ወደሥራ ሲገባ የክልሉ ገቢ የመሰብሰብን አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል ይሆናል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በመልካም አስተዳደርና በሙስና ረገድም የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሠራው ሥራ አስደናቂ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል። ይህም ሆኖ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ሲቪል ሰርቫንቱ ለይ አንደ ሀገር የተገኘው አፈጻጻም የቤኒሻንጉል ክልልንም የሚወክል ነው። በጥሩ ሁኔታ በሥርአት የሚሠሩ አገልግሎት የሚሰጡ የመኖራቸው ያህል ሰዓት ከመስረቅ ጀምሮ አገልግሎት በመስጫ ሰዓት የግል ጉዳያቸውን የሚከውኑም አሉ። ለዚህ በሀገር ደረጃ የተዘጋጀ ፖሊሲ አለ። እንደ ክልልም የሰው ሀብት አጠቃቀማችን ውጤታማ ነው ? ወይንስ አይደለም ? የሚለውን በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል። በዚህ ሂደት ሙስናን ለመከላከል ቴክኖሎጂ መጠቀም፤ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውን አገልግሎት ሰጪዎች የማበረታታት ሥራ የሚከናወን ይሆናል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው የሥነ ምግባር ጉድለት የሚገኝባቸውን በመረጃ በተደገፈ መልኩ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፤ ለነበረን ግዜ አናመሰግናለን
አቶ መለሰ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም