
– ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች:: በተለይም ለምርታማነት ማነቆ የሆኑ የግብዓት አቅርቦትን ችግር ለመፍታት ባሳየው ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች:: ዘርፍን ለማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲመራ በማድረግ ረገድም የተገኘው እመርታ ቀላል የሚባል አይደለም:: በእነዚህ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ከግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል::
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ያከናወናቸው ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- እንደ ግብርና ሚኒስቴር የግብርናው ዘርፍ እንዲያድግ ካከናወናቸው በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም እንዲያድግ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል:: ይህም ሲባል የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን የምርጥ ዘር አቅርቦትም እንዲያድግ ሥራ እየተሠራ ነው:: የሜካናይዜሽንም በተመሳሳይ የአቅርቦትና ተደራሽነቱ ገና በጅምር ላይ ያለ ቢሆንም እሱም እየተሠራ ነው::
ከዚህ በፊት የተበጣጠሰ መሬት የነበረውን አርሶ አደር በክላስተር እንዲያርስ የማለማመድ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በተጨማሪም የመስኖ ልማትንም የማስፋት ሥራ ለአርሶ አደሮቻችንን የማለማመድ ሥራ እየተከናወነ ነው:: በዚህም በርካታ ውጤቶች እየመጡ ነው:: በተለይ ደግሞ ዋጋው አልቀነሰም ቢባልም፤ የምርት አቅርቦት በሀገር ደረጃ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሄድ የምርት አቅርቦቱ እንዲሻሻል ተደርጓል:: ይሄ ግብርና ሚኒስቴር ከተሰጠው ተልዕኮ፤ ኢትዮጵያም ካላት አቅም አኳያ በቂ ነው ወይ ቢባል በቂ አይደለም:: ግን ደግሞ ቀድሞ ከነበረበት አንፃር በርካታ መሻሻሎች አሉ ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- በተለይም የግብርና ሥርዓቱን በሜካናይዜሽን እንዲመራና አርሶ አደሩ በተጨባጭ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ አሁን ምን ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀማችን ገና ጅምር ሊባል የሚችል ነው:: ምክንያቱም የግብርና ሜካናይዜሽን ስንል በጣም ሰፋ ያለ ሃሳብ ያለውና ሰፋ ያለ ጉዳዮችን የሚይዝ ነው:: በተለምዶ አርሶ አደሩ ትራክተር ስለገዛ ‘ሜካናይዜሽን ተስፋፍቷል የሚል ነገር አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይስተዋላሉ:: ትራክተር ብቻውን ሜካናይዜሽን ተሟልቷል ማለት አይቻልም:: ኮምባይነርም በተወሰነ ደረጃ ተደራሽ ቢሆንም ከዚያ በላይ አርሶ አደራችን ስለሚገባው ከማሳ እስከ ጉርሻ ድረስ ያሉ ቴክኖሎጂዎችንም ማሟላት ይጠይቃል::
ለምሳሌ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ያለ ትራክተር አለ፤ ከዚህ በፊትም በስፋት ሲሠራ ቆይቷል:: ሌሎች ክልሎች ላይም አርሶ አደሩ በብድር ትራክተር እንዲያገኝና ኮምባይነር መግዛት እንዲችል እየተሠራ ነው:: አርሶ አደራችንም አሁን ላይ ግንዛቤው እያደገ ነው:: ከዚህ በፊት የነበረው ሰፊ ጉልበት አለ የሚል እሳቤ ስለነበረ ለግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ትኩረት ያለ መስጠት ሁኔታ ነበር:: አሁን ላይ ግን ጥቅሙም እየታወቀ ነው የመጣው:: ለምሳሌ የምርት ብክነትን ከመቀነስ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት የግብርና ሜካናይዜሽን ልምምዶቹ ጥሩ ናቸው:: ግን ይሄንን ማስፋት አለብን የሚለውን ነው መወሰድ ያለብን:: በአሁኑ ወቅት የኩታ ገጠም እርሻችን ወደ 12 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት:: ከዚህ ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው በትራክተር የታረሰ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ:: በቂ አይደለም የሚለው ቢወሰድልን ጥሩ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት ከዚህ አኳያ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይገለፃል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- የልህቀት ማዕከሉ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ይሠራል ብለን ነው የምናስበው:: በቅድሚያ ይህንን የልህቀት ማዕከል የኮሪያ መንግሥት በጀት ድጋፍ ነው የተሠራው:: በቴክኒክም ድጋፍ አድርገውልናል፤ በቀጣይ ይህንን ማዕከል ወደ ሥራ ከማስገባት አንፃር ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል አብረውን ነው የሚቆዩት:: ኢትዮጵያ ውስጥ ትራክተር፣ ኮምባይነርም ሆነ ሌሎች የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽኖች ይገባሉ:: ስናስገባ ግን አብዛኞቹ የሚገቡት በሰነድ ነው፤ የእኛ ባለሙያዎች በአካል አይተው ካረጋገጡ በኋላ ነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት::
ብዙ ጊዜ ግን በርካታ ማሽኖችን አስገብተን በትንሽ ብልሽት ሥራ የሚያቆሙበት ሁኔታ አለ:: በመሆኑም ማዕከሉ በዋናነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ማሽኖችን የጥራት ደረጃ የመለካትና ፍተሻ የማካሄድ ሥራ ይሠራል:: በተጨማሪም ጠጋኞችን ያሰለጥናል:: ሥልጠና ሲባል አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ማሰልጠን ሳይሆን የአሰልጣኞች ሥልጠና የሚሰጥበት እንዲሁም ደግሞ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ድጋፍና በሀገሪቱ ባሉ የህብረት ሥራ ማህበራት በኩል የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተቋቁመዋል:: እነዚህ ትክክለኛ ኦፕሬተር እንዲሆኑ ማድረግ ነው አንዱ ሥራው::
አሁን ላይ ከዩኒቨርሲቲ፣ ከምርምር እንዲሁም ከግብርና ለተውጣጡ ባለሙያዎች ነው እየተሰጠ ያለው:: በጥገና፣ በዲዛይን፣ በፍተሻ ላይም ሥልጠና እየተሰጠ ነው ያለው:: ይሄ እንግዲህ ሀገራችን ካላት አቅምና ከምንፈልገው አንፃር ማዕከሉ በጥቂቱም ቢሆን ያግዛል:: እንደዚህ ዓይነቶቹን በክልልም እያሰፋን ከሄድን የግብርና ሜካናይዜሽን እየሰፋ ይሄዳል:: ዲዛይንም እንሠራለን፤ ፕሮቶ ታይፕ የምንለው ለምሳሌ የቴክኖሎጂ መነሻ ለማምረት ጭምር ይረዳል:: ዩኒቨርሲቲዮቻችን ላይ የግብርና ምህንድስና የተማሩ ተማሪዎችና መምህራን አሉ:: በምርምርም ተቋማትም ሆነ ግብርና ላይ በተመሳሳይ ይሠራል:: እነዚያን ከግሉ ሴክተር ጋር አገናኝተን ምርምር እንዲሠራበት ማድረግ ነው::
የማዕከሉ መገንባት ለሀገራችን ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂ ለማመንጨትም እድል የሚፈጥር ነው:: በነገራችን ላይ ከዚህ ማዕከል ብዙ ነው የምንጠብቀው፤ በተለይ የእውቀት ሽግግር መኖር መቻል አለበት:: እንደሚታወሰው ከዚህ ቀደም የግብርና ሜካናይዜሽን ላይ የተሻለ ልምምድ ያላቸው ሀገራት ላይ ታይቶ ባለሙያዎች እንዲሁም የሥራ ኃላፊዎች ሄደው የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ይደረግ ነበር:: ግን 10ና 20 ሰው ውጭ ሀገር በመላክ ብቻ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም:: ስለዚህ ከኮሪያዎቹ ጋር ያደረግነው ስምምነት ብዙዎቹን እነሱ ባለሙያ አምጥተው እንዲያሰለጥኑልን ነው:: ከባለሙያ አልፎም አርሶ አደሮችንም እንዲያሰለጥኑልን ሃሳብ አቅርበናል:: በዚያ መሠረት ላለፉት ሁለት ዓመታት ከ100 በላይ ባለሙያዎች በሶስት ዘርፍ ሥልጠና ሰጥተውልናል::
ከሰለጠኑት ውስጥ የተወሰኑት ማዕከሉ ላይ ይቀላቀላሉ ብለን እናስባለን፤ ሌሎች ደግሞ በሚሠሩበት ቦታ ላይ ለማስተማርና ምርምርም ለመሥራት ይጠቀሙበታል:: ዋና አላማ እውቀትን ሀገራችን ላይ ማስቀረት መቻል አለብን የሚል ነው:: የሰለጠነው አካል የትም ሆኖ ሊሠራ ይችላል፤ ትልቁ ነገር ግን ሀገራችን ውስጥ እውቀቱ እንዲኖር ማድረግ ነው:: በተለይ ትራክተርን ፈታቶ መግጠም እንዲችል፣ ትንንሽ ብልሽት እንኳን ቢኖር በቀላሉ መጠገን የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው::
የሰለጠኑትን እንደ ሀብት ነው የምንወስዳቸው፤ እነሱ ደግሞ በቀጣይ አገልግሎት በሚሰጡ ማዕከላት ላይ ሄደው ድጋፍ መስጠት እንዲችሉ፤ አርሶ አደራችን በቀላል ብልሽት ሲያጋጥመው እነሱን ማገዝ እንዲችል በማለም ብዙዎቹን እንዲያሰለጥኑ አድርገናል:: ሌላው ሥልጠናውን ሲወስዱ በውጤታቸው ተለይተው 12 የሚሆኑትን ኮሪያ ሄደው ለ15 ቀን እንዲሰለጥኑ ተልከዋል:: በጥቅሉ ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ደግሞ በደንብ አገልግሎቱን እያሰፋ ይሄዳል::
ክልሎች ላይም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ በተለይ ጥገና መስጠት የሚያስችል፤ የኦፕሬተር ሥልጠናዎችን መስጠት አቅም እንድንፈጥር ለማድረግ ፍቃዳቸውን አሳውቀውናል:: ግን ሙሉ ለሙሉ እኛ በውጭ ሀገር መንግሥት ላይ ጥገኛ እንድንሆን ሳይሆን አሁን ላይ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትም ሆነ በሌሎችም አካላት የተሠሩ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን እያቋቋምን የምንሄድበትን ሥርዓት መፍጠር ነው የምንፈልገው:: ያሉትንም የማጠናከር ሥራ እየሠራን ነው:: ሜካናይዜሽኑ እያደገ ሲሄድ አብሮ እያደገ የሚሄድ ነው የሚሆነው::
አዲስ ዘመን፡- ማዕከሉ የምርምር ሥራም እንደሚሠራ ተጠቅሷል፤ ይህ ሌሎች ማዕከላት ከሚሠሩት የምርምር ሥራ በምን ይለያል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- ምርምሩ በዋናነት ከዲዛይን ይጀምራል፤ ይህም ሲባል ለኢትዮጵያ እንደ የሥነ-ምህዳሩ ሁኔታ ምን ዓይነት ትራክተር፣ ኮምባይነር መሆን አለበት? የሚለውን ከዲዛይን ጭምር ነው የሚሠሩት:: አሁን ገና ሥራ አልጀመረም፤ ምርምር ይሠራል ሲባል ሌላ ተቋማት የሚሠሩትን ደርቦ ይሠራል ማለት አይደለም:: ለምሳሌ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ የሜካናይዜሽን ዘርፍ አለ፤ ክልሎችም ላይ በተለይ ኦሮሚያ ላይ በጣም ሰፋፊ የምርምር ሥራዎች ይሠራሉ:: እነዚህን አብረን ነው የምናስተሳስራቸው:: ድግግሞሽ እንዲኖር ሳይሆን ተደጋጋፊ የሆነ ሥራ ነው የሚሠራው::
አዲስ ዘመን፡- የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የነበሩ አሻጥሮችን በማስቀረትና በትክክል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተሠራው ሥራ ምን ያህል አመርቂ ነው?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– እንደ ሀገር ሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር 2014 እና 2015 ዓ.ም ላይ የገጠመ ተግዳሮት ነበር:: ያጋጠመን ችግር እንደ ግብርና ሚኒስቴር ሊፈጠር የማይገባው ነበር፤ ግን ደግሞ አጠቃላይ ሁሉም አርሶ አደር በሕገ ወጥ መንገድ ነው ማዳበሪያውን ያገኘው የሚለውም ስህተት ነው:: ሕገ ወጥ የማዳበሪያ ዝውውር ነበር ሲባል የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ፤ መፈጠር አልነበረባቸውም፤ ከተፈጠረ በኋላ ግን መፍትሔ ወደማፈላለግ ነው የሄድነው:: አንደኛው በሁሉም አካባቢ በቂ የሆነ ማዳበሪያ ማቅረብ ነው:: ሁለተኛው በአፈር ማዳበሪያ ግዢ ሥርዓት ውስጥ ያልነበሩ ክልሎችን አስገብተናል:: በነገራችን ላይ በአፈር ማዳበሪያ ግዢ ሥርዓት ውስጥ አንዱ የተማርንበት ለምሳሌ የጋምቤላ ክልል፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩት እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸውም አርሶ አደሮች በአፋር ክልልም ማዳበሪያን በተመለከተ ቅሬታዎች ነበሩ:: እነዚህን ቅሬታዎች ማዕከል በማድረግ ክልሎቹ ባሉበት ማዳበሪያ ማቅረብ ጀመርን::
አሁን በራቸው ላይ ስላቀረብን ወደ አዲስ አበባ ወይም አዳማ መጥቶ ከማዕከላዊ መጋዝን የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ በሕገ ወጥ መንገድ የመሸጥ እድሉ የለም:: እሱን ዘግተናል:: ትልቅ ለውጥ ያመጣንበት አንዱ ይሄ ነው:: ሌላው ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር አለ:: ቁጥጥሩ ቢኖርም እጥረት ስላለ ከየትም መጥቶ አርሶ አደሩ ጋር ይድረስ እንጂ እኔ አልቆጣጠርም የሚሉም ነበሩ:: ይሄ ትክክል እንዳልሆነ በደንብ ተገማግመናል፤ አሁን ላይ ማንም ሰው እንደ ፈለገ የአፈር ማዳበሪያ ከሕግ ውጭ ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም:: ለሁሉም በሚያለማበት ቦታ አቅርበናል::
በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሀብቶችም ከዚህ በፊት በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚቀርበው ከማዕከላዊ መጋዘን ነበር የሚወስዱት፤ እሱንም አሁን አስቀርተናል:: እያንዳንዱ ባለሀብት ከሚያለማበት ክልል ነው የሚወስደው:: ይህንን በማድረጋችን ባለፈው ዓመት የሰማነው ጩኸት የለም:: በዚህ ዓመት አጋጥሞ የነበረው አንድ ጉዳይ ነው፤ ከደቡብ ክልል መጥቶ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ተያዘ የሚል ነው፤ እሱም ተወርሷል:: አልፎ አልፎ እኛ ያልደረስንበት ችግር ሊኖር ይችላል:: በጥቅሉ ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የሚሠሩ አሻጥሮች ተቀርፏል ማለት ይቻላል:: እንዲያውም አንዳንድ ክልሎች ለምርት ዘመኑ በቂ አግኝተናል፤ ከዚህ በኋላ አንፈልግም እያሉ ደብዳቤ እየፃፉ ነው::
ከዚያ ባሻገር ዲጂታላይዝ ማድረግ አለብን ብለን ጀምረናል፤ በመላው ሀገሪቱ ዲጂታላይዝድ አሠራር መዘርጋት ሰፋ ያለ ጊዜ፣ ሀብት፣ የሰው ኃይል ይፈልጋል፤ እሱን እናሳካለን ብለን እናስባለን:: ይህ ሲሆን ሁሉም ሰው በጠየቀው ልክ የአፈር ማዳበሪያ ማግኘት እንዲችል እድሉን ይፈጥራል:: ግን ደግሞ ማዳበሪያ አትስረቁ ስላልን ስርቆት ይቆማል ማለት አይደለም፤ ትልቁ ነገር ሥርዓት መዘርጋት ነው:: የምንዘረጋው ሥርዓት ግን የተፈለገውን ግብ መድረስ እንችላለን ወይ? የእኛ ግብ አንዱ አርሶ አደራችን ማዳበሪያው በሚፈልገው ጊዜ እንዲደርስለት ማድረግ ነው:: ይህንን ደግሞ ዲጂታላይዝ ስናደርገው ግዢ ወቅቱንም በትክክለኛ መረጃ መሠረት ለመወሰን ያስችለናል:: ሁለተኛው ገንዘብ ተሸጦ ወደ ባንክ የማይገባበትና ስርቆትም ጭምር ነበር:: አሁን ሽያጩ በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን በሞባይል የሚከፍልበትን ሥርዓት ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ስለሆነ ዲጂታላይዜሽኑን በትክክል ወደ መሬት ስናወርደው አንዳንድ ችግሮችንም ጭምር ለመቅረፍ ያግዘናል::
አዲስ ዘመን፡- የምርጥ ዘርን ምርታማነትንና ጥራቱን ማሳደግ ላይ እንደ ሀገር ያለው አቅም ምን ደረጃ ደርሷል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- በሁሉም አካባቢዎች የግብርና መዋቅሩ የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል፤ ግን ባስተዋወቅነው ልክ ተደራሽ አድርገናል? ሲባል እዚያ ላይ ውስንነቶች አሉ:: እሱን ለማሳደግ ምርጥ ዘር ማባዛትን በመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍም ገብቶ መሰማራት አለበት:: በዚህ ረገድ አነስተኛ ልምምድ አለን፤ ለምሳሌ ኮርቲቫ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆሎን ማባዛት ሥራ ከጀመረ ረጅም ዓመት ሆኖታል፤ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ይሠራል:: በቅርቡ ደግሞ የውል እርሻ አዋጅን ካፀደቅን በኋላ የተወሰኑ የግል ኩባንያዎች አዳዲስ ዝርያዎችን እያስገቡ ነው:: በተለይ የበቆሎ ዘርን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሠራ ነው ያለው:: ነገር ግን ከውጭ ሀገር በሚመጣ ወይም ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች አባዝተው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጡት ዘር ላይ ብቻ አርሶ አደራችን ጥገኛ እንዲሆን ሳይሆን በእኛ በምርምር መዋቅራችን የተሻሻሉ ዝርያዎች በስፋት ስለሚወጡ እነሱን የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት አለብን::
ሀገራችን ውስጥ የተሻለ ዝርያ ካለ፤ የተሻለ ሥራ መሥራት ከተቻለ በውጭ ላይ ብቻ መደገፍ የለብንም:: ያንንም ቢሆን ግን አንዘጋም፤ ምክንያቱም ለግሉ ዘርፍም እድል መስጠት እንደሚገባ ፖሊሲው ስለሚደነግግ ነው:: ግን ደግሞ በራስ አቅም ማደግ ላይ ትልቅ ርብርብ ስለሚፈልግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግብርናው ግልፅ አቅጣጫ እያስቀመጠ ያለው በምርምር የወጡ ምርታማነታቸው የተረጋገጠ፤ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ ዝርያዎች በስፋት ለአርሶ አደሩ መተዋወቅና መድረስ መቻል አለባቸው የሚል ነው:: እነዚህን ለማባዛት አሁንም በተመሳሳይ በመንግሥት ባለው የክልሎች የዘር ኢንተርፕራይዞች ብቻ ሳይሆን የግሉም ዘርፍ ይህንን ዝርያ በሕጉ መሠረት ወስዶ፤ አባዝቶ ተደራሽ ማድረግ እንዲችል አሁን የሕግ ማሕቀፎች ተዘጋጅተዋል::
ከግብርናውና ከምንፈልገው እድገት አንፃር የዘር አቅርቦትና አጠቃቀማችን ገና አላደገም:: እያንዳንዱ አርሶ አደር ምርጥ ዘር መጠቀም መቻል ብቻ ሳይሆን ተደራሽ መሆን አለበት:: ዋጋውም ደግሞ ተመጣጣኝ መሆን ይገባዋል:: ለዚህ ደግሞ የዘር አቅርቦቱ ተመጣጣኝ ማድረግ ያስፈልጋል:: እዚህ ላይ ግብርና ከማዳበሪያው ጎን ለጎን ምርጥ ዘር ላይ በስፋት መሥራት አለበት:: ምክንያቱም በሀገራችን ውስጥ መሥራት እየቻልን መቸገር የለብንም:: ግን ቁርጠኝነትና ትልቅ ሥራ ይፈልጋል:: በተመሳሳይ ዘር ላይ የዲጂታል ሥርዓት አስጀምረናል:: አንዱ ይገጥመን የነበረው ችግር ዘር አንድ ቦታ ላይ ያድራል፤ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ እጥረት ይከሰታል:: ስለዚህ የሁሉንም ክልል የዘር ፍላጎት፤ አቅርቦትና ሥርጭት የመከታተያ ሥርዓት ዘርግተናል:: አሁን በፓይለት ደረጃ ነው ያለው፤ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ግን ሁሉም ክልል በዚህ ሥርዓት የምናስተናግድ ነው የሚሆነው::
ምርጥ ዘር እስከ 30 በመቶ የምርት ጭማሬ እንዳለው ይታወቃል፤ ይህንን ማሳደግና የዘር አቅርቦቱን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል:: በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ ዘር ከውጭ ነው የሚገባው:: ስለዚህ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ ይገባል:: ይህም ብዙ ሥራ ይጠይቃል፤ በሂደት እየተማርንበትም፤ ባለን አቅም መሥራት ያስፈልጋል:: በጥቅሉ የዘር አቅርቦቱ ተሻሽሏል፤ ግን ደግሞ በቂ አይደለም:: ጥራትንም በሚመለከት የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን አንዱ የተቋቋመበት ዓላማ የዘር ጥራትን የማስጠበቅና የመቆጣጠር ሥራ እንዲሠራ ነው::
ዘር ማምረት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ ይህንን የመቆጣጠር ሥልጣን አለው:: እየተሠራ ነው፤ ግን ደግሞ የእሱም አቅም ማደግ መቻል አለበት:: የዘር ጥራት አንዳንድ ጊዜ አርሶ አደራችን ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ:: ዘርተን አልበቀለንም የሚሉ አሉ:: አንድ ጊዜ ነጋዴዎች ቀለም ቀብተው ለአርሶ አደሩ የሚሸጡበት ሁኔታ አለ፤ ይህንን መቆጣጠር ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጉዳይ የምርምር ተቋማት፤ ከሚያባዙ አካላት ጋር ተናቦ ያለ መሥራት ችግር ነው፤ ብዙ ጊዜ የምርምር ተቋማቱ ያወጧቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች የሼልፍ ላይ ጌጥ ሲሆን ይስተዋላል:: ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ ሚኒስቴሩ ምን እየሠራ ነው?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– ምርምርን በአዲስ በተከለሰው ፖሊሲ ላይ ኮሜርሻላይዝድ ወይም ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ይፈቅዳል:: ይህም የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች በግሉ ዘርፍ በኩል ተባዝተው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እንዲሠራ ለማስቻል ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ግን ለሥራችን ድንበር አበጅተንለት የቤት ሥራዬን ጨርሻለሁ የምንልበት ሳይሆን በትብብር የመሥራት ባሕላችን ማሳደግ ይኖርብናል:: የወጡ ቴክኖሎጂዎችን የግብርና መዋቅሩ በአግባቡ ካላደረሰ ምርምር ደግሞ አንድ ደረጃ ገፋ አድርጎ አብሮ ማስተዋወቅ መቻል አለበት:: አሁን ላይ የሕግ ማሕቀፎቹ ብዙዎቹ እየተስተካከሉ ነው ያሉት:: የግሉ ዘርፍም ገብቶ ተደራሽ ለማድረግ እያስተካከልን ነው ያለነው:: ዋናው ነገር ግን ምርምሩ ያወጣቸው ቴክኖሎጂዎች ባለቤት እንደ መሆኑ ተጠቃሚው ጋር እንዲደርስ መሥራት ያለበት:: የበጋ መስኖ ስንዴ አንዱ ማሳያ ነው:: በፌዴራልም፤ በክልልም ያሉ ማዕከላት ከግብርና መዋቅሩ ጋር በጋራ ስለሠራ ነው እዚህ ደረጃ መድረስ የተቻለው::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ይፋ የተደረገው የእንስሳት ኢንቨስትመንት ሰነድ የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብ አንፃር ምን ዓይነት ፋይዳ ይኖረዋል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በእንስሳት ቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ ነች፤ ትልቁ ነገር የእንስሳት ሀብት በቁጥር ደረጃ መኖር ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ለእንስሳት ምቹ ሁኔታ አላት:: ይህንን ስናይ በአርብቶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደሩ በስፋት ይሠራል:: የእንስሳቱን ዘርፍ ለማሳደግ በቅርብ ዓመታት የተጀመረው የሌማት ቱሩፋት አንዱ ማሳያ ነው:: የመንግሥት ቁርጠኝነት ሲኖርና ትኩረት ሲሰጠው ያድጋል:: ዋናው ነገር ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ማድረግና ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ መጠቀም መቻል አለባት:: ይህንን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ መግባት አለበት:: የግሉ ዘርፍ ሲገባ ደግሞ ምን ምን ነገሮችን ነው ማየት ያለበት? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል::
በዚህ ረገድ የሌማት ቱሩፋት ኢንሼቲፉ ሲጀመር በብዛት ከተማና ከተማ ዙሪያ ላይ ነው:: በተለይ የዶሮና የከብት ርባታ በስፋት ነው ያለው:: የንብ ማነብ ሥራም ተጀምሯል፤ እንዲያውም የማይናደፉ ንቦችም ጭምር እየመጡና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉ ስለሆነ እዚህ ላይ እድገቶች እናያለን:: ትንሽ ወጣ ብለን ስናይ ግን ስታንዳርድ ይጎላቸዋል:: ለምሳሌ ውሃ ሳይኖር የወተት እርባታ ውስጥ መግባት አይገባም:: ውሃ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች አስቀድሞ ማጤን ያስፈልጋል:: ከመኖሪያ ቤት መራቅም ይኖርበታል:: እነዚህን መሰል ጉዳዮችን የያዘ፤ የኢትዮጵያንም አቅም ያሳየ ሰነድ ነው:: በተጨማሪም ማንኛውም ሰው እንስሳት ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ ቢፈልግ ምን ምን ነገሮችን ነው ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለብኝ ብሎ እንዲረዳ የሚያደርግ ነው:: ሰነዱ አሁን የተዘጋጀው በእንግሊዘኛ ነው፤ በቀጣይ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተተርጎም ተደራሽ መሆን ይጠበቅበታል::
አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ባለሀብቶችን እንዳይስብ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ሰፊ የፋይናንስ የቦታና መሰል አቅርቦት እጥረት እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንፃር ምን ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጥዋል?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– በነገራችን ላይ ሰነዱ ቴክኒካል ነገሮችን ነው እንጂ የውሳኔ ሃሳቦችን አያስቀምጥም:: እኛ የእንስሳት ስንል አስቀድሜ እንዳነሳሁት ከመሬት አቅርቦት አንፃር ምን መሆን እንዳለበት፤ የቱ ጋርስ ሊከናወን ይገባል? የሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው:: እስከ ዛሬ በነበረው ሂደት በሰብል ነው አብዛኛው ትኩረታችን የነበረው፤ ለእንስሳት የሚሰጠው ቦታ በጣም ትንሽ ነው፤ ከከተማ እንዲወጣም ደግሞ አይፈለግም:: የእንስሳት ኢንቨስትመንትን ማሳደግና የግሉን ዘርፍ መሳብ የምንፈልግ ከሆነ እንደ ሀገር ሆነ በክልል ምን ዓይነት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን? ሀብት ስላለን ብቻ የምንኩራራበት መሆን የለበትም:: ይህ ሀብት ወደ ገንዘብ መቀየር አለበት:: ወደ ገንዘብ ለመቀየር ደግሞ ምን ምን ነገሮች መስተካከል እንዳለባቸው የሚያመላክት ሰነድ ነው::
ፋይናንሱን በሚመለከት ለምሳሌ የእንስሳቱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ግብርና ትልቅ ፋይናንስ የሚፈልግ ቢሆንም በቂ ፋይናንስ ግን አልቀረበለትም:: ፋይናንስ ለማቅረብ በመጀመሪያ ዘርፉን እይታ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል:: ለምሳሌ የንግድ ባንኮችን ብንወስድ ግብርና ስጋት ያለበት ቢዝነስ ነው የሚሉ ያልተገባ እሳቤዎች አሉ:: መጀመሪያ ይሄ አስተሳሰብ መቀረፍ አለበት:: ትልቁ ነገር የሚበደረውን ሰው በአግባቡ ማወቅ፤ ቢዝነስ ፕላኑን መረዳትና ካበደሩ በኋላ ድጋፍ ማድረግ ነው የሚገባው:: የፋይናንስ ተቋማቱ ሁልጊዜ ሕንፃና ሆቴል ለሚሠሩ ብቻ በማደር ሀገር አታድግም:: ሆቴል የሠራው ሰው የግብርና ምርት ይፈልጋል፤ ስለዚህ የተመጋገበ ሥርዓት መኖር መቻል አለበት::
የብድር አቅርቦቱም ሆነ ሌሎቹም ነገሮች ግብርናውን ጭምር ያማከለ ሊሆን ይገባል:: በቅርቡ የግብርና ኢንሹራንስ እንዲኖር ለማድረግ የግብርናውን መዋቅር እያስተካከልን መሄድ አለብን:: በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ የገጠር ፋይናንስ ብለን አቋቁመናል:: ይህም ያስፈለገው ምክረ ሃሳብ ጭምር እንዲያቀርቡ ነው:: ፋይናንስ ተቋማት የግብርና ኢንቨስትመንት ህንፃ ከሚሠራው ጋር እኩል ሊያዩት አይገባም:: የግብርናውን ባሕሪ መረዳት ያስፈልጋል:: የሚሰጡ ማበረታቻዎችና የብድር እፎይታ ጊዜዎች ቢኖሩም በቂ አይደለም:: ልማት ባንክና ንግድ ባንክ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች አሉ፤ ይህም አንድ ለውጥ ቢሆንም ግን ግብርናው የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው፤ ለኢንዱስትሪ ሽግግሩም ወሳኝ ነው፤ የሥራ እድል ፈጠራው ላይም ግብርናው ትልቁን ድርሻ ይይዛል ካልን ፋይናንሱ ደግሞ በዚያው ልክ መኖር መቻል አለበት::
የሚጠየቀው ከሀገር አቅም በላይ አይደለም፤ ግን ባለው ልክ ግብርናው ላይ ፋይናንስ መኖር አለበት:: ባንኮቻችን የግብርናውን ባሕሪ ሊረዱ ይገባል:: ስታበድሪ ደግሞ በቴክኒክ ድጋፍ ማድረግና መከታተል ያስፈልጋል:: በመንግሥት በኩል ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል:: በጥቅሉ የፋይናንስ አቅርቦቱ ለእንስሳት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርት ወደ ውጭ መላክ አለባት ከተባለ ጥራት ያለው ምርት ማምረት ይጠበቅባታል፤ ጥራት ያለው ምርት እንዲመረት ደግሞ ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ባሻገር ባለሀብቶች መግባትና ለዚህም የብድር አቅርቦቱ ሊሰፋላቸው ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- ክልሎች ላይ ያለው የተንዛዛ አሠራር ባለሀብቱ ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት እንዳይገባ እንቅፋት እንደሆነበት በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፤ ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ ምን እየተሠራ ነው?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡- በዋናነት እዚህ ላይ የግብርናው ሚና ማስረዳትና መግባባት ላይ መድረስ ነው:: እንደተባለው የግሉ ዘርፍ ሲመጣ ፍርሃት ጭምር አለበት፤ ለምሳሌ መሬት ለመስጠት ትልቅ ስጋት አለ:: ባለሀብቱ መሬቱን ይዞት የትም አይሄድም፤ ትልቁ ነገር ግን የግል ሀብቱ ሲመጣ የሚፈጥረውን የሥራ እድል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግሩንና የገበያ ማረጋጋትን ማሰብ ያስፈልጋል:: እንዳነሳሽው ችግሩ አለ፤ በተለያየ ጊዜ ሪፖርት ይደረግልናል:: ይህንን በውይይት በማስረዳት ነው ለመፍታት ጥረት እያደረግን ያለ ነው:: አንዳንድ ጊዜ የአመራር ለውጥ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጉዳዮች የሚራዘሙበት ሁኔታ አለ:: ጀማሪ ሲሆኑ ብዙ መሰናክሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ ግን ደግሞ የግድ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ ገብቶ ግብርናው ላይ ካልተሠራ ትራንሰፎርም መሆን አይችልም::
በነገራችን ላይ ይህ በአቅጣጫ የሚፈታ አይደለም፤ አስፈላጊነቱ ላይ በደንብ መነጋገርና መንግሥት ደግሞ ፌዴራልም ሆነ በክልል ላይ ያለው የቁጥጥር ሥርዓቱን ማሳደግ አለበት:: በመሠረቱ በባለሀብቱም ዘንድ ትልቅ ክፍተት አለ:: ለምሳሌ በቢዝነስ ፕላናቸው መሠረት የማይሠሩ አሉ:: በጣም የሚያማልል ቢዝነስ ፕላን ሊሠሩ ይችላሉ፤ እሱ ታይቶ መሬት ከተሰጣቸው በኋላ ምንም የማይሠሩ፤ አልያም በፕላናቸው መሠረት የማያከናውኑ አሉ:: ይህንንም እያረምን መሄድ መቻል አለብን:: አንዳንዶቹ ባለሙያ የማይቀጥሩ አሉ፤ ግብርና ሳይንስ የሚፈልግ የማይመስላቸው አሉ:: እውቀት ካልገዛ በተለምዶ ውጤታማ መሆን አይቻልም:: አሁን ያለው ዓለም የደረሰችበት ደረጃ ለዚያ የሚፈቅድ አይደለም:: ስለዚህ የግል ዘርፍን ሆነ ክልሎች ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- የሆርቲካልቸር አምራቾች ግብዓቶችን ለማስመጣት ተደራራቢ ግብር እንደሚጠየቁ ሲነገሩ ይደመጣሉ፤ ሚኒስቴሩ ለምርታማነት መጎልበት ተግዳሮት የሆኑ መሰል ችግሮችን በመፍታት ረገድ ምን እየሠራ ነው?
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– ከሆርቲካልቸር አምራቾች ጋር በተያያዘ የተነሳው እንደሚታወቀው አብዛኛው አርሶ አደር የሚጠቀመው ዩሪያና ዳብ ከቀረጥ ነፃ ነው የሚገባው:: ሌሎቹ ግን አንድ የግል ዘርፍ አትራፊ እንደ መሆኑ ሁሉንም ነገር ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን መጠበቅ የለበትም:: ሀገሪቱም ለማደግ የግድ ቀረጥና ግብር መሰብሰብ አለባት፤ ይህንን በሕጉ መሠረት ነው የሚስተናገዱት ብዬ አምናለሁ::
ሆኖም የውጭ ባለሀብቶችም ቢሆኑ ለፅድቅ ብለው ኢንቨስት አያደርጉም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አምርቶ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ነው የሚሠራው:: ሁሉም ነገር ነፃ ይደረግልን የሚለው ትክክል አይደለም:: ሀገራቸው ብንሄድ የሚሠሩት በሕጉ መሠረት ነው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም ሀገሪቱ ባላት ሕግ መገዛትና መዳኘት አለባቸው:: በመሆኑም በእነሱም ዘንድ እርማት እንዲያደርጉ የምንመክራቸው የሀገሪቱን ሕግ እንዲያከብሩ ነው::
ከፍጥነትና ቀልጣፋ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ ያ ደግሞ ኢትዮጵያ ገና እያደገች ያለች ሀገር ስለሆነች ፤ ከግሉ ዘርፍ ጋር አብሮ የመሥራት ልምዳችንም ገና እያደገ ስለሆነ አንዳንዱን መታገስ ያስፈልጋል:: አንድ ግለሰብ የፈጠረው ችግር ሀገራዊ መልክ መስጠት ትክክል አይሆንም:: እንደ ሥርዓት ግን ለየትኛውም አገልግሎት ፈላጊ የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ፍላጎት ነው ያለው::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጀት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
ሶፊያ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም