
እንደ ሀገር ምንም እንኳን ለሥልጣኔ ቀደምት ብንሆንም የኃያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂ ማራገፊያ ከመሆን ያላለፍንበት ሚስጢርም ይኸው ነው። መንግሥት ይህንን የታሪክ ስብራት መቀየር ያስችል ዘንድ ከትምህርት ሥርዓቱ ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪው፤ ከቤተሰብ እስከ መንግሥታዊ ተቋማት ድረስ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ፖሊሲና የሕግ ማሕቀፎችን ቀርጾ እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ ለክህሎት ትልቅ ስፍራ በመስጠት እያንዳንዱ ዜጋ ሁለትና ከዚያ በላይ የሙያ ባለቤት የሚያደርግ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የተቀየሩት ክህሎታቸውን ማሳደግ በመቻላቸው ነው። እኛ ብዙውን ጊዜ ልምድ የምንወስድባቸው የአውሮፓ ሀገራት ጭምር የእድገታቸው ሚስጥር ክህሎት ነው። ግን ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደጉ የኤዢያ ሀገራት ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሀገራት ከልማታቸው ጀርባ ስላለው ሚስጢር ምንነት ብዙ ጽሑፎች ወጥተዋል። ሌሎች ነገሮች ቢኖሩም በዋናነት ግን የሰው ኃይላቸው ላይ የሠሩት ሥራ ነው። ለምሳሌ የኮሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር፤ የሲንጋፖር፣ የማሌዢያና መሰል በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገራት ከጀርባቸው ያለው ትልቁ ነገር ለሰው ልጅ ክህሎት የሰጡት ትኩረት ነው።
እነዚህ ሀገራት የዜጎቻቸውን ምርታማነት አሳድገው፤ (አንዳንዶቹ ሀገራት እንዲያውም በቂ የተፈጥሮ ሀብትም አልነበራቸውም)፤ የሰው ኃይላቸውን በማብቃታቸው ምክንያት ከሌሎች ሀገራት የተፈጥሮ ሀብት በማስገባት እሴት ጨምረው ትልቅ ላኪ ሀገራት የሆኑ አሉ። ለምሳሌ ብረት የሚያመርቱ ሀገራት ብረትን በጥሬው ከሌላ ሀገር በማስገባት እሴት ጨምረው መልሰው የሚልኩ አሉ። የግብርና ምርቶችም እንደዚሁ ለምሳሌ ቡናን የመሳሰሉት ጥሬ ምርቶችን የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ አንድን ሀገር ከሌላ ሀገር፤ አንድ አካባቢ ከሌላ አካባቢ ተወዳዳሪነት እንደ ትልቅ ማርሽ ቀያሪ ተደርጎ የሚወሰደው ክህሎት ነው። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ክህሎት ያለው ዜጋ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወጣኝነት የተጀመረው የትናንቱ “ሰመር ካምፕ” የዛሬው “ክህሎት ኢትዮጵያ”፤ ከሶስት ተቋማት ጋር በመሆን የተጀመረ ፕሮግራም ነው። የወጣቶችን ሥራ አጥነት መቅረፍ፤ የኢኮኖሚ እድገትን ማስመዝገብ፣ የሙያ ሥልጠናና ክህሎትን ውጤታማ ማድረግ እንዲሁም በሥራ ፈጣሪዎች የታቀዱ ህልሞችን እውን የማድረግ ተልዕኮም አለው።
ይህንኑ እውን ለማድረግም በሀገሪቱ ካሉ የቴክኒክና ሙያ (የቲ ቪ ቲ) ተቋማት ውስጥ በቴክኖሎጂ እውቀታቸው የተሻሉ ናቸው ተብለው የተለዩ ወደ ካምፑ በመግባት የሶፍት ስኪልና የሀርድ ስኪል ሥልጠናዎች እንዲወስዱም መንገድ ይከፍታል። ፕሮግራሙ ሰልጣኞች በውስጣቸው የያዙትን ሃሳብ ወደ መሬት አውርደው እንዲተገብሩ የሚያስችልም ነው።
ለክህሎት ኢትዮጵያ ስኬት ሲባልም ዜጎች ባሉበት ሆነው ማግኘት የሚፈልጉትን ክህሎት እንዲያገኙ የዲጂታል ስኪል ባንክ ተቋቁሞም ወደ ሥራ ገብቷል።
“ክህሎት ኢትዮጵያ ከክህሎት ልማት አንጻር ተደራሽነታችንን የምናሰፋበት መንገድ ነው። በኢትዮጵያ የርቀት ሥልጠናዎችን ጨምሮ ክህሎት ላይ ለምሳሌ ቴክኖሎጂን መሥራት ለሚፈልጉ አስፈላጊውን እውቀት የሚያገኙበትን እድልም የፈጠረ ነው” የሚሉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው።
እኛም በሥራና ክህሎት እሳቤ የክህሎት ልማት ማለት ምን ማለት ነው? አሁናዊ ቁመናውና የወደፊት እጣ ፋንታው ምን ይመስላል? ስንል ከክብርት ሚኒስትሯ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በአዲሱ የሥራና ክህሎት እሳቤ የክህሎት ልማት እንዴት ይገለፃል?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ አዲሱ እሳቤ ሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ከሚለው የኢትዮጵያ ህልም የሚቀዳ እሳቤ ነው። ምክንያቱም ይህንን ሩቅ ተጓዥና ዘመን ተሻጋሪ ህልም ለማሳካት የክህሎት ልማት ሥራው ትልቅ ትርጉምና ፋይዳ ያለው ነው። በመሆኑም በጣም ብዙ ሀገራዊ ችግሮችን የሚፈታ ብዙ እድሎችን የሚፈጥር ስለሆነ ለዚህ የሚመጥን አስተሳሰብ አደረጃጀት፤ የአሠራር ሥርዓትና የቴክኖሎጂ ግንባታ ጉዳዮችን መሠረት አድርጎም የተቀረጸ ነው።
በእኛ እሳቤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓቱ ሥልጠና ብቻ ሳይሆን አምራች የሆነ ዜጋ ማፍሪያ፣ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የመገንባት፣ ሀገር በቀል የሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥርዓትን እውን የማድረግ ትልቅ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ከሥልጠና በላይ በሚል ማሕቀፍ እንዲታይ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፦ ቴክኒክና ሙያ ከሥልጠናም በላይ ሲባል እሳቤው ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ በአራት ምሰሶዎች ላይ የተመሠረተ 38 የለውጥ አጀንዳዎች የተቀረጹለት ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ከ38ቱ 11ዱን ማሕቀፎች ይይዛል። ከሥልጠና በላይ የሚለውን እሳቤም እንዲያሟላ የሚያደርጉ መሠረታዊ የሆኑ ተቋሙ ዘረመል ብሎ የሚጠራቸው በእንግሊዘኛው አጠራር (DNA) የሚባሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።
የዜጎችን ሁለንተናዊ ችሎታና ብቃት በማሳደግ ውስጥ የሀገርን ተወዳዳሪነት ማጎልበት አለና ለዚህ የመጀመሪያ ጉዳይ አድርገን የወሰድነው ፍላጎት መር የሆነ የሥልጠና ሥርዓትን ነው። ኢንዱስትሪውም ሆነ ግብርናው ብሎም አገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚፈለጉ ባለሙያዎችን በማብቃት በኩል የነበረን እይታም ሆነ ዝግጅት ፍጹም መተላለፍ የነበረው ነበር። አሁን የምንቀርጸው ሥርዓት ይህንን አለመጣጣም የሚፈታ ፍላጎትና ገበያ መር እንዲሆን ሰፋፊ የትምህርት ሥርዓት (ካሪኩለም) ቀረጻዎችን ሠርተናል።
እነዚህ ካሪኩለሞችም እስከ አሁን የማናውቃቸውን የሥልጠና ዘርፎች አካቶ ነባሮቹንም ከዘመኑ ጋር እንዲራመዱ በሚያደርግ የተከለሰም ነው። የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናው በጣም ትልቅ አቅም ያለው ነው። ይህንን የሚመጥን ሥርዓት በውስጡ እንዲይዝ ይገባ ነበርና ለዚህ ደግሞ ሃሳብ ችሎታ ያላቸውን ዜጎች ለመሰብሰብ አሁን ላይ ተደራሽነታችንን እያሰፋን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ቀደምና አሁን ያለው የሰልጣኝ ቁጥር እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ይህ የሥልጠና ሂደት ሲጀመር የሰልጣኙ ቁጥር ከ 1 ሚሊየን በታች ነበር። ዛሬ ላይ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ሁለንተናዊ ብቃታቸው የተሟላ ሆኖ እንዲወጣ እየተሠራ ነው። ከዚህ አንጻር ጊዜውን የዋጀ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክህሎቶች ላይ አሰልጣኞችንም ሰልጣኞችንም የማብቃት ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው። ይህ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ሲሆን በተለይም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓቱ የኩባንያዎች መፈልፈያ እንዲሆን ማድረግ እንደ ትልቅ የሪፎርም ሃሳብ ተይዞ እየተሠራበት ነው።
የኢንኩቤሽን ማዕከላት አሉ። ዜጎች ወደ ኢንተርፕራይዝ ወደ ኩባንያ እያደጉ እንዲሄዱና ሥራንና የሥራ ባሕልን እዚያው ተለማምደው እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ጊዜው የሚጠይቀው ሀገር ወዳድነት እና አርበኝነት በመሆኑ በካሪኩለም ደረጃ ሀገር ወዳድነት የሚል የሥልጠና ዓይነት ተካቷል። ይህ ደግሞ በሥራና በትጋት ይተረጎማል በመሆኑም ከቴክኒክና ሙያው ጋር አስተሳስሮ ለማየት እየተሞከረ ነው።
ሥርዓቱን” አንተርፐሪነር” የማድረግ ወይም ሥነ ምህዳሩን በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓት ውስጥ መገንባት ትልቅ የለውጥ አጀንዳ ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል። በዚህም የመጀመሪያው ችግርን የመፍታት መፍትሔ የማምጣት አዳዲስ ነገሮችን የማመንጨት እሴት የማከል አስተሳሰብ ባሕልና ባሕሪን የመገንባት ሥራን ያጠቃልላል። ዘንድሮም በስፋት ተግባር ላይ አውለነዋል።
በዚህም ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ፖሊ ቴክኒኮች ትኩረት ሰጥተን ከመሥራታችንም በላይ ሥራውን ወደ ኮሌጆች ለማሳደግ እየተሠራ ነው። በኮሌጆች አካባቢ አሰልጣኞችም ሰልጣኞችም እንዲቃኙ ማድረግ በመቻሉ ከዚህ ቀደም ያልነበራቸውን አዳዲስ ሀብቶችን ማመንጨት ችለዋል።
ወደፊትም በራሳቸው የሚቆሙ በጀት የማይጠብቁ ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ የተቀመጠ ጊዜና ግብ አለ። ነገር ግን የሚያወጧቸው መፍትሔዎችና ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ችግር ፈቺ፣ የኢኮኖሚውን የመወዳደር አቅም የሚያጎለብቱ እንዲሆኑ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ የተሠራ ነው።
አሁን ላይ በኮሌጆቻችን አካባቢ የፋብሪካ ደረጃ ያላቸው ትልልቅ ማሽኖች ማምረት ማውጣት የተቻለበት በገበያ ግንባታው ላይ መሳተፍ የተቻለበት አቅም ተፈጥሯል። ያልነበረን የመፍጠር የነበረን ደግሞ የማሻሻል ሥራዎች ተሠርተዋል።
አዲስ ዘመን፦ የቴክኒክና ሙያ አሰለጣጠን ችግሮች ምን ነበሩ ?እንዴትስ ታለፉ ?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ከዚህ ቀደም የነበረው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የአሰለጣጠን ችግር ጎልቶ የታየው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በገባበት ጊዜ ነው። ወቅቱ ሁሉም ዜጋ ቤቱ የተቀመጠበት የማስተማር ዘዴውንም መቀየር ያስፈለገበት ቢሆንም ቴክኒክና ሙያ ሥልጠናው ግን ለዚህ ምቹ አልነበረም። ከዚህ ትምህርት በመውሰድም ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በመሥራት አሁን በተለይ ፖሊ ቴክኒኮች አካባቢ ለመድረስ በጣም ጥቂት ቢቀርም ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆን ዲጂታል ሥርዓት ለመዘርጋት ተችሏል።
ከዚያም አልፎ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የሥልጠና ጥራትን ለማሻሻል የስማርት ላብራቶሪ ዝግጅት (ስቱዲዮ) ማካሄድ ተችሏል። ይህም ማለት ወጥነት ያለው የሥልጠና ስታንዳርድ ከአንድ ማዕከል ወደሌላ ማዕከል እንዲደርስ ማድረግ ያስችላል። ይህ እንግዲህ ዘመኑን የዋጀ ሥርዓት ዜጎቻችንን ለማዘጋጀት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ቀደም ሥልጠናዎች በውል ያልተጠኑ ድግግሞሽ የሚበዛባቸው እንደነበሩ ይነገራል፤ ዛሬስ ምን መልክ አለው?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ የአካባቢዎችን የመልማት ጸጋ መሠረት በማድረግ የሥልጠና ሥርዓቱን ለመቅረጽ ተሞክሯል። የትምህርት ሥርዓት (ካሪኩለም) የተማሪ ቅበላ ሥርዓት በዚህ መልክ ሆኗል። ከዚህ ቀደም የነበሩት የሥልጠና ሥራዎች ድግግሞሽ የሚበዛባቸው ናቸው፤ ይህ ደግሞ የሀብትና የሰልጠነ ባለሙያ ብክነት አስከትሏል። ይህንን ለመቀነስም ያስችላል። የሥልጠናው ሂደት አካታችነት ባሕርይን እንዲይዝ የጾታ የእድሜ የአካል ጉዳት አይገድበውም፤ አሁን ላይ ደግሞ እነዚህን ጨምሮ ሌሎች የአካታችነት ፎርሞችን መሠረት አድርጎ ሥርዓቱን ከመቅረጽ አኳያ ባለፉት ዓመታት የሠራነው ሥራ አለ፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ፦ በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ እሳቤ እንግዲህ ስኪል ባንክ የሚል አዲስ ፕሮግራም ተጀምሯልና እስኪ ስለሱ ትንሽ ይበሉን?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ዜጎች ባሉበት ሆነው ማግኘት የሚፈልጉትን ክህሎት እንዲያገኙ የዲጂታል ስኪል ባንክ አቋቁመን ወደ ሥራ ገብተናል። ይህ ደግሞ ከክህሎት ልማት አንጻር ተደራሽነታችንን የምናሰፋበት መንገድ ሲሆን በኢትዮጵያ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካይነት የርቀት ሥልጠናዎችን ጨምሮ ክህሎት ላይ ለምሳሌ ቴክኖሎጂን መሥራት ለሚፈልጉ አስፈላጊውን እውቀት የሚያገኙበትን እድል የፈጠረ ነው።
ይህም ተደራሽና አካታች ለመሆን የራሱን እድል የፈጠረም መሆኑን አይተናል። በተመሳሳይ የሃሳብ ባንክን በመጠቀም ሃሳቡን ወደ ቢዝነስ መቀየር የሚፈልግም የት ጀምሬ ምን አድርጌ ምን ልሠራ እችላለሁ? የሚለውን የሚያሳይና ምን መሥራት እንደሚችል መነሻ ሃሳብ የሚሰጥ ነው።
ሌላው የአካታችነት መለያ ወይም የዘርፉን ተለማማጭነት ባሕሪይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው የሪፎርም አካል የሆነው መደበኛ ባልሆነ መንገድ (በልምድ) ያዳበሩትን ክህሎት እውቅና ሰጥቶ የመደበኛ ሥርዓቱ አካል ማድረግ፤ ይህንን በያዝነው በጀት ዓመት ወደ ሥራ አስገብተናል።
አሁን ላይ እንደ ጅምር ወደ 15 ሺ ዜጎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህ ደግሞ የዜጎችን የመደራደር አቅም ያሳድጋል፤ በኢኮኖሚው ውስጥም የበቃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ቁጥርን ይጨምራል።
የሥልጠና ሥርዓቶቻችን ከሀገራዊ የቅድሚያ ፍላጎቶች ጋር ተናበው እንዲሄዱ ሆኗል፤ በዚህም ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ እና ማዕድን ቀዳሚ አጀንዳዎች ናቸው።
በሌላ በኩልም አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲም ለዘርፉ የፈጠረው አዲስ እድል ያለ ሲሆን ይህም ደረጃ አምስት ላይ የቆመውን እስከ ደረጃ ስምንት ድረስ ለመውሰድ አስችሏል። በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ለማነቃቃት ብሎም ያደገ የሰው ኃይልን ለመፍጠርና የምርምር አቅማችንን ለማሳደግ ትልቅ እድልን የፈጠረም ሆኗል።
ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቴክኒክና ሙያ ከቴክኒክና ሙያ ወደ ዩኒቨርሲቲ በቅብብል መሄድ የሚቻልበትን ሥርዓት የዘረጋ ከመሆኑም በላይ ሂደቶቹን ተቋም በሚፈጥር መልኩ በመምራት ተቋማቱ ብቃታቸው የተረጋገጠ (የአይሶ) ተመዝጋቢና ሰርቲፋይድ መሆን ችለዋል ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮም 9 ተቋማት ይህንን የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ወስደዋል።
ከግል ዘርፉ ጋር ተሳስረን የምንሠራበት የስኪል ካውንስል የምንለውንም በግብርና ዘርፍ ጀምረናል፤ ወደ ሌሎች የሙያ ዘርፎች እያሰፋን እንሄዳለን። እዚህ ላይ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዓላማው የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው፤ ይህንን ሥራ ለማዘመን ምን መሥራት አለብን? የሚለውን በደንብ አድርገን በመለየት ወደ ተግባር ገብተናል። በዚህም ችግር ፈቺ የሆኑ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ሥራዎችን መሥራት አለብን፤ በማለት ተቀዳሚ ተልዕኳችን አድርገን እየሠራን ነው።
በመሆኑም ከትምህርት ቤት ጀምሮ “የክህሎት ውድድር”(ስኪል ኮምፒትሽን) ላይ እየተወዳደሩ እስከ ሀገር አቀፉ ድረስ የሚመጡ ወጣቶችን “ኢንኩቤት” የማድረግ ሃሳቦቻቸውን አበልጽጎ ወደ ምርት ወደ ገበያ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
አዲስ ዘመን፦ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የክህሎት ውድድር ዘንድሮ ለ4ተኛ ጊዜ ተደርጓል፤ ባለፉት ጊዜያት የነበሩት ከውጤት አንጻር እንዴት ይገመገማሉ?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ለውጤታማነት በጣም ውጤታማ ነው ከቅርቡ እንኳን ብንጀምር ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ላይ አሸናፊ የነበሩ ተሳታፊዎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በአንድ ዓመት ውስጥ 81 ቴክኖሎጂን ማውጣት ተችሏል። ሌላው በዘንድሮው ዓመትም ውድድሩን ሳንጠብቅ የተለያየ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች እርስ በርሳቸው ተወዳድረው እንዲያልፉ በማድረግ 99 የሚሆኑ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን ማውጣት ችለናል።
የ3ተኛው የክህሎት ወድድር ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች አንዳንዶቹ ትልልቅ ኩባንያ መሆን የሚያስችል መንገድ ጀምረዋል። ኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡም አሉ፤ በኢንስቲትዩቱ አካባቢም ቦታ ተዘጋጅቶላቸው በርከት ያለ የማሽነሪ ትዕዛዝ እየተቀበሉ መስራት የጀመሩ ወጣቶችም አሉ።
እነዚህ ደግሞ የነገ ባለሀብት ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ከመሆናቸውም በላይ የኩባንያዎች መፈልፈያ ሥርዓትን ማሳኪያ መንገድ የሚሆን ነው። የተሰጠንንም የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ ትልቅ መንገድም የሚሆን ነው።
ይህ የስኪል ኢትዮጵያ ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤትን ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ በየደረጃው ትልቅ ተነሳሽነት የሚፈጥር የማድረግ የመፍጠር አቅም ፍላጎትን የመጨመር አንዱ መገለጫ ነው። ከገንዘቡ በላይ ደግሞ የሀገርን ችግር የሚፈቱ እሴት የሚፈጥሩ ጥሩ አስተሳሰብ የሰርክ ተግባራቸው የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት የሚችል ፕሮግራም መሆኑን ደግሞ በአጭር ጊዜ አይተናል።
ከታችኛው እርከን ጀምሮ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እድል ሰጥቶ የመጣ ፕሮግራም ስለሆነ የተደራሽነት ጉዳዩም ላይ በጣም ትልቅ አቅም አለው። እስከ አሁን ያወጣናቸው ቴክኖሎጂዎች እንኳን ወደ ማስፕሮዳክሽን እያስገባናቸው ከሄድን የሚፈጥሩት እድል በጣም ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የዓለም የክህሎት ማህበረሰብ አባል ሆናለች፤ ይህ እድል ለዘርፉ ምን ዓይነት አበርክቶዎችን ይዞ መጥቷል?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ይህ መድረክ በርከት ያሉ የውድድር ዓይነቶች የሚካሄዱበት በመሆኑ በቂ ዝግጅት አድርገን ተወዳዳሪዎቻችንን ስንልክ ሀገራችን በትልቁ ትነሳለች። ሥርዓቱ የኦሎምፒክ ዓይነት ሲሆን በየሁለት ዓመቱም የሚካሄድ ነው፤ እኛም በክህሎት ዘርፉ በዘመኑ የደረስንበትን ደረጃ እናሳይበታለን፤ ከሌሎች ምን መውሰድ አለብን የሚለውን እንቀስምበታለን። ዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮችን በመፍጠር ረገድም የራሱን አበርክቶ ይወጣል።
በሌላ በኩልም ዘርፉ ዓለም አቀፋዊነቱ እያደገ እንደመጣ የሚያሳይ በመሆኑም እኛም ህልም ያላቸውን ዜጎቻችንን ከግብ ለማድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የክህሎት ልማት ሥራ ለመሥራት የሚያስችል በርከት ያሉ አማራጮች ያሉት ወጣቶቻችን ስለ ክህሎት ያላቸውን አመለካከት የሚያሳድግ ልምዳቸውን የምናጎለብትበት ሃሳቦቻቸውን ማበልጸግ የሚችሉበት አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማካሄድ የሚያስችል “የክህሎት ፓርክ” ግንባታ ጀምረናል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የክህሎት ማህበረሰብ አባልነቷ ክህሎትን ከፍ ባለና በአዲስ እይታ ሀገራዊ ጥያቄን በሚመልስ መንገድ የዜጎችን የተወዳዳሪነት አቅም በሚያሳደግ ቅኝት እየመራች ውጤት እንድታመጣ ያግዛታል። በቀጣይም የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ብዙ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ የክህሎት ልማቱ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ሚና እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ የፈለገውን ሥራ በፈለገው ቦታና ሁኔታ መሥራት የሚችል ዜጋ ስንፈጥር የመደራደር አቅሙንም እያሳደግንለት ነው። በልምድ የተገኘ እውቀትን እውቅና የምንሰጥበት ፕሮግራም ዜጎች የሚወዳደሩበት ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍ የሚልበት በዛው ልክ ደግሞ ለሀገራቸው አበርክቷቸው የሚጎላበት ነው።
ዘመኑን ለዋጀ የሥልጠና ሥርዓት ስናዘጋጃቸው ሀገራዊም ዓለም አቀፋዊም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረግናቸው ነው። የተቋማትን ሥርዓት ዓለም አቀፋዊ እያደረግን ስንሄድ ውድድራችን ድንበር የተሻገረ ይሆናል።
በጠቅላላው ግን በራሳቸው የሚተማመኑ ምን? መቼ? የት? መሥራት እንደሚችሉ የሚያውቁ ልባቸውን አዕምሯቸውንና እጃቸውን ያገናኙ ሰዎች የመፍጠር ጉዳይ ስለሆነ ኢኮኖሚው ብቁ በሆነ፣ የኢንዱስትሪ ዲስፒሊን ባወቀ የሰው ኃይል ሲመራ ተወዳዳሪ ይሆናል፤ ዜጎችም በአስተዋጽኦቸው ልክ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም