በአንድ ወቅት «ኢትዮጵያውያን ‛የመጀመሪያው’ ማለት ይወዳሉ» የሚል ሃሜት መሰል የአላዋቂ ቧልት በአንድ ታዋቂ ቧልተኛ ከተሠራጨ ወዲህ ብዙ የዘመን ተጋሪዎች እውነት መስሏቸው «ልካችንን ነገረን» እያሉ ቧልተኛውን በአድናቆት ሲያመሰግኑና የአባባሉን ትክክለኛነት ደጋግመው ሲያስተጋቡ ሰምቼ በመሳቅ ፈንታ በተቃራኒው ማዘኔን አስታውሳለሁ።
ምክንያቱም ታዋቂው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የምዕራባውያንን «እኛ ብቻ አንደኛ» የሴራ ስብከት መሣሪያ ሆኖ በመመልከቴ ነው። እውነቱን ስንመረምር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን «የመጀመሪያው» ማለት የምናበዛው በምክንያት ነው። በብዙ ነገሮች ቀዳሚ የሆንን የመጀመሪያ ሕዝቦች ነን።
እንደዚያ ከሆነ ደግሞ በሆነ ነገር ቀድሞ መገኘትና የመጀመሪያው ማለት የማይወድ አገርና ሕዝብ ያለ አይመስለኝም። ሲቀጥል የእኛ ስለሆነ እንጂ የመጀመሪያው ከማለትም አልፈው በሁሉም ነገር «አባት» ነን ማለት የሚወዱት ምዕራባውያንስ ምን ሊባሉ ነው? የባዮሎጂ አባት፣ የፊዚክስ አባት፣ የሕክምና አባት፣ የጂኦግራፊ አባት…ኧረ ምን አባት ያልሆኑበት ነገረ ዕውቀት አለ።
«ጀማሪም፣ አባትም እኛ ብቻ ነን» ለማለት ካልሆነ በቀር በሆኑበትም ባልሆኑበትም በሁሉም ነገር አባት ነን፣ አባት ነን የሚሉት እነርሱ እያሉ የሆንነውን ነን በማለታችን እኛ ላይ የሚቀለድብን በምን ምክንያት ነው? ለማንኛውም የመጀመሪያ ስለሆንን «የመጀመሪያው» በማለት ሃሳባችንን እንቀጥላለን። በዓለም ላይ የመጀመሪያው ስልጣኔ የተመሠረተው በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የዓባይ ሸለቆን ተከትሎ ነው።
ኧረ እንዲያውም የመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው መጀመሪያ የሆነው የሰው ዘርም የተገኘው ልዩ ስሙ ሓዳር በተባለ ሥፍራ አፋር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እዚሁ በአፍሪካ ምድር ነው።
አፍሪካ የሰው ዘር መገኛ አህጉር ናት። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከአመክንዮም በላይ በዚህ ሐቅ መሠረት አፍሪካ የስልጣኔም መገኛ ክፍለ ምድር ናት። ለምን ቢሉ ምድርና መላዋ የእግዚአብሔር ብትሆንም ምድርና መላ ምድራዊ ስልጣኔዋ ግን የሰው ልጆች ነው፤ የሰው ዘር የተገኘበት ምድር እርሱ የስልጣኔም መገኛ ነው። ከእነግሪክና ሮማ ስልጣኔ ሺ ዘመናት በፊት በምዕራብ አፍሪካ በእነ ጋናና ሶንጋይ፣ በመካከለኛው አፍሪካ በእነታላቋ ዚምባብዌ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያና ግብጽ ታላላቅ ስልጣኔዎች ያበቡባቸው የዓለም ክፍሎች ነበሩ።
በዚህም ከሂሳብ እስከ ምህንድስና፣ ከመድኃኒት ቅመማ እስከ ሕክምና፣ ከሥነ ፈለክ እስከ ሥነ ክዋክብት፣ ከፊደል እስከ ዘመን መቁጠሪያ፣ ከዜማ እስከ ፍልስፍና አፍሪካውያን «ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ» ቢሆንባቸውም ቅሉ ለዓለም ስልጣኔ የአንበሳውን ድርሻ አበርክተዋል።
የሩቁን ትተን የቅርቡን ብናስታውስ እንኳን ዛሬ «ያለእኔ ስልጡን የለም» በሚል እብሪት ዓለሙን በአንድ እግሩ ያስቆመው የምዕራባውያን ስልጣኔ አንቀላፍቶ መላ አውሮፓ በጨለማ ውስጥ በነበረበት ዘመን አፍሪካ ውስጥ ዛሬም ድረስ አሠራራቸው እንቆቅልሽ ሆነው የቀሩ እንደነላሊበላ ዓይነት ዕፁብ ድንቅ የኪነ ሕንፃ ጥበቦች እየተገነቡ ነበር።
መላ አውሮፓ በድቅድቅ ጨለማ በነበረበት በዚያው ዘመን ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በስልጣኔ ጫፍ ላይ የደረሱ ሦስት ታላላቅ ግዛት አጼዎች ነበሩ። ሃይማኖትንና ሃይማኖታዊነትን እንደመግዣ መሣሪያ አድርጎ ለሰው ልጆች አዕምሯዊና ማህበራዊ ዕድገት ነፃነት የሚያገለግሉ ሌሎች ሰዋዊና ዓለማዊ ዕውቀቶችን ሁሉ በኃጢአትነት በማውገዝና እንዲዳፈኑ በማድረግ ቄሳራውያን አምባገነኖች በአውሮፓ ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል የጭቆና፣ የመከራና የድንቁርና ዘመን አስፍነው ነበር።
ሆኖም ከአምስት መቶ የጨለማ ዘመን በኋላ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ኋላቀርነትና ድንቁርና በማስወገድ ለጥቂት ፈላጭ ቆራጭ ቄሳራውያን አምባገነኖች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ ሕዝባዊ ስልጣኔ ለመመሥረት ያለመ እንቅስቃሴ ተጀመረ።
ማዕከሉን በጣሊያኗ የፍሎረንስ ከተማ አድርጎ እነሚካኤል አንጀሎ፣ ዳንቴ፣ ሊዮናርዶ ዳቪንችና ጋሊሊዮ ጋሊሊን በመሰሉ ማህበራዊ መሃንዲሶች የተመሠረተው አዲሱ የስልጣኔ እንቅስቃሴም ይዞት የተነሳውን ዓላማ ለማሳካት የጥንት አያት ቅድመ አያቶቹን ጥበብ መለስ ብሎ መመርመርና ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለበት ወሰነ።
ለዚህም ወደጥንቱ የምዕራባውያን የግሪኮ-ሮማን ታላቅ ስልጣኔ ተመልሶ ማዕከሉን እዚያ ላይ አድርጎ መሥራት ጀመረ። በዚያም ላይ ተመርኩዞ የጥንቱን ጥበብና ዕውቀት በመጠቀም በፍልስፍና፣ በዕውቀት፣ በሳይንስ፣ በፍትሕ፣ በነፃነትና በዴሞክራሲ ላይ የተመሠረተ አዲስ የለውጥ ስልጣኔ ፈጠረ።
ሃይማኖትን እንደሽፋን በሚጠቀሙ ራስ ወዳድ አምባገነኖች ክፋትና ስንፍና በግፍ ታፍነው እንደደበቁ ተደርገው የነበሩት የግሪኮ ሮማን ትልልቅ ጥንታውያን ጥበቦችና ዕውቀቶች እንደጥንቱ ታላቅ መሆንን በሚሹ የአውሮፓውያን አዲስ ትውልድ ከተቀበሩበት ወጥተው ዳግም ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋልና ስሙንም ዳግም ትንሳኤ ወይንም ሕዳሴ ብለው ጠሩት።
«እንደጥንቱ በጥበብና በዕውቀት እንሰልጥን፣ እንደ አባቶቻችን ታላቅም እንሁን» በሚል ዋና እሳቤ የሚመራው አዲሱ ዳግም ትንሳኤ የስልጣኔ እንቅስቃሴም እጅግ በፍጥነት ይስፋፋ ጀመር። ከጣሊያን ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምዕራብና መካከለኛውን አውሮፓ አዳርሶ መላ አውሮፓን አጥለቀለቀ። በዚህም አዲሱ የዳግም ልደት እሳቤ አምባገነኖች ያጨለሙትን ዘመን በፍጥነት በብርሃን እየገለጠ ፈረንሳይ ደረሰ።
በዚያም «አብርሆት» የሚባለውን የዳግም ትንሳኤ ቀጣይ የስልጣኔ ደረጃ ወልዶ ለአውሮፓውያንና ለምዕራባውያን እንካችሁ አለ። ይህም የጥንቱ የግሪኮ ሮማን ስልጣኔ በዳግም ልደት ፍሬ አፍርቶ በሥነ ጽሑፍ፣ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በጥበብ አውሮፓ እንደገና ማበብ የጀመረችበት ጊዜ ነበር።
በቀጣይም የዳግም ልደት የስልጣኔ እሳቤ ከፍተኛ ዕድገትና ተከታታይ ድል እያስመዘገበ ገስግሶ እንግሊዝ ሲደርስ «የኢንዱስትሪ አብዮት»ን በመፍጠርና ለብዙ ሺ ዘመናት የሰው ልጆች ይጠቀሙበት የነበረውን አሠራር ከመሠረቱ በመቀየርና ሥር ነቀል የአስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ ለውጥ በማምጣት ለአውሮፓ ብቻ ሳይሆን ለዓለማችን የዘመናዊ ስልጣኔ መሠረትን ጣለ።
ዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት የምንመለከታቸው የሰው ልጆች የዘመናዊው ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ ማናቸውም ዓይነት ምጡቅ ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች ሁሉ የዚሁ የዳግም ትንሳኤ የስልጣኔ አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ ዕውቀት ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ከአውሮፓውያኑ የዳግም ትንሳኤ የስልጣኔ እሳቤ አፍሪካም ሆነ ሌላው ዓለም የተጠቀመ ቢሆንም የዕውቀት ጠቃሚነት ደግሞ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነውና ይበልጥ የጠቀመው ግን ራሳቸውን አውሮፓውያኑንና ምዕራባውያኑን መሆኑ ግልጽ ነው።
እንዲያውም ዳግም ትንሳኤያቸው ከፍሬው ይበልጥ እንዲጠቀሙ ብቻ ሳይሆን በሌላው ላይ የኃይል የበላይነትን እንዲያገኙና የማይገባቸውን እንዲጠቀሙ፣ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሌላው ሀብትና ጉልበትም እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል።
በዚህም ከእነርሱ ሺ ዘመናት በፊት ቀድማ በስልጣኔ አብባና ደምቃ ትኖር የነበረችው ታላቋ አፍሪካ ከረጅም የጨለማ ዘመናት በኋላ እነርሱ በዳግም ትንሳኤ ዓለምን ሲገዙ እርሷ በተቃራኒው ለድንቁርናና ለኋላቀርነት ተዳርጋ ጭራሽ የእነርሱ መጠቀሚያ ሆና እየማቀቀች ትገኛለች።
የአፍሪካ ድንግል ሀብትና የሕዝቦቿ ጉልበት ለዘመናት የተበዘበዘው፣ ሕዝቦቿ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ለዓመታት በባርነት የማቀቁበትም ከዚሁ ከአውሮፓውያኑ ዳግም ትንሳኤ፣ ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ መሆኑም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ያም ሆኖ ለዳግም ልደታቸው መፈጠርና በዚያ ምክንያት ላገኙት ጥቅም ሁሉ ባለቤቱ ራሳቸው ናቸውና እነርሱ ብቻ ለምን ተጠቀሙ? በሌላው ላይስ ለምን የበላይነትን አገኙ? ማለት አይቻልም።
ስለሆነም የእኛን ትክክለኛ ተጠቃሚነት ለመፍጠርና የእነርሱን የበላይነትም ለማስቀረት ብቸኛው መፍትሔ በእነርሱ ዳግም ትንሳኤ እኛ ለምን አልተጠቀምንም ሳይሆን እኛም የራሳችንን ትንሳኤ ማምጣት ነው። ስለአውሮፓውያኑ ዳግም ትንሳኤ ሰፋ አድርገን መመልከታችንም ለዚሁ ነው፤ የእኛም መዳኛ ዳግም ልደታችን ማረጋገጥ መሆኑን ለማጠየቅ! እናም አፍሪካውያን የጥንቱን ስልጣኔያችንና ታላቅነታችን ለመመለስ እጅግ የዘገየን ቢሆንም አሁንም አልረፈደም።
ዳግም ትንሳኤያችን ለማምጣትና የጥንቱን ስልጣኔያችንና ታላቅነታችን በመመለስ ዳግም በሀብታችን ለመጠቀም፣ የምዕራባውንን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትና የበላይነትና የብቻ ተጠቃሚነት ለማስቀረትና ዳግም ፍትሕና እኩልነትን ለማረጋገጥና ዳግም የበለጸገች፣ ስልጡንና ታላቅ አፍሪካን ለመፍጠር ጊዜው አሁን ነው።
ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን ከምንጊዜውም በላይ የነቁበትና እንደ ሕዝብ አንድ ሆነው የቆሙበት ጊዜ በመሆኑ የአፍሪካን ትንሳኤ ለማረጋገጥ ትልቅ እድልን ይፈጥራል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ቀናት በኋላ አፍሪካውያን ነፃነታቸውን የተቀዳጁበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዙፋን ወራሽ የአፍሪካ ኅብረት 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ በዚሁ በተመሠረተበት በዚሁ በአፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበት ቀን በአፍሪካውያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ታላቅ የድል ቀን መሆኑ ይታወቃል። በተባበረ ክንድ እናት አፍሪካን ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የሚያግዝ መተባበሪያ መድረክ ለመፍጠር የአፍሪካ መሪዎች ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ያፈራበት እና መላ አፍሪካውያንን የሚያስተባብር አንድ አህጉራዊ ድርጅት፤ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ዕውን መሆን ችሏል። ያች ቀን በሁሉም አፍሪካውያን ልብ ውስጥ በልዩ ፍቅር ተጽፋ ሁሌም በክብር ስትዘከር የምትኖርበት ምክንያትም ይኸው ነው።
የአህጉሪቱን ሕዝቦች በማስተባበር ቅኝ ግዛትን በማስወገድና ነፃነትን በማቀዳጀት ለአፍሪካውያን ትልቅ ድልና ስኬት ያስመዘገበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዙፋን ወራሽ የሆነው የአፍሪካ ኅብረትም ከነፃነት በኋላም ለዓመታት የቀጠለውን የአውሮፓውያን የእጅ ቅኝ ግዛት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ በማድረግና የእርስ በእርስ ትብብርን በማሳደግ ከዘመናዊ ቅኝ ግዛትና ከድህነት ነፃ የሆነች የበለጸገች አፍሪካን ዕውን በማድረግ የዙፋን አውራሹን ስኬት መድገም ይጠበቅበታል።
ለዚህ ደግሞ እንደጥንቱ ሁሉ ዛሬም አፍሪካውያንንና መላ የጥቁር ሰው ዘሮችን ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት «በቃ» ብላ ከተነሳችው የጥቁር ሕዝብ ነፃነት ፋና ወጊዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ ላይ አብሮ መቆም አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።
አፍሪካውያን ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ የሕዝቡን አንድነት እንደ ኃይል በመጠቀምና የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ሕዝባዊ ትግል በቁርጠኝነት በመደገፍ እንደ ቀደምቶቹ ፓን አፍሪካ አባቶቻቸውና የአፍሪካ አንድነት መሥራች አፍሪካዊ የነፃነት መሪዎቻቸው ዛሬም የአፍሪካ መሪዎች እንደ መንግሥት አንድ ላይ አብረው መቆምና መተባበር ሲችሉ ነው።
ሲቪል ተቆርቋሪዎችና የአፍሪካ ተሟጋቾች በተናጠል በሚያደርጉት ኢመደበኛ ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ 1949ኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንዳደረጉት ዛሬም የአፍሪካ መሪዎች በፖሊሲና በመንግሥታዊ ተቋሞቻቸው የእጅ አዙር ቅኝ ቅዛትን «በቃ» በማለት ከሕዝባቸው ጎን መቆም ሲችሉ ነው።
ያኔ ነው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፍሪካ ከምዕራባውያን የዘመናት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ነፃ የምትወጣው! አፍሪካ ዳግም ትንሳኤዋን ስታረጋግጥ ነው፤ በሁሉም ዘርፍ ከተፅዕኖ ተላቅቃ በነፃነትና በአሸናፊነት መቆም የምትችለው! እግዚአብሔር ከእኛ ከልጆቿ ጎን ሆኖ የአፍሪካን ዳግም ትንሳኤ ዕውን ያድርግ!::
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014