አዲስ አበባ፡- የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ተጠቅመው በአገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀረበ።
«ኪነጥበብ ለሠላም» በሚል መሪ ሐሳብ በቀድሞ የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ትናንት ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በተደረገው ውይይት የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑ፤ ልዩነቶችን በጥበብና ብልሀት የሚያልፉና ችግሮችን በማህበራዊ ትስስራቸው የሚፈቱ ናቸው። ይህ ባህል ደግሞ በይበልጥ የሚገለጠው በኪነጥበብ ባለሙያዎች በመሆኑ ሙያተኞቹ የበኩላቸውን ሚና ሊያበረክቱ ይገባል።
እንደ ወይዘሮ ሙፈሪያት ገለፃ፤ የኪነጥበብባለሙያዎች አገር ለመገንባትም ሆነ ለማፍረስ አቅሙ አላቸው። አሁን ደግሞ አገሪቱ የሚያስፈልጋት ሠላምና መረጋጋት በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ሠላምን ማስፈኑ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአገሪቱ እየታዩ ያሉ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ለመፍታት መፍትሄ አመንጭ መሆን እንዳላበቸው የገለፁት ሚኒስትሯ የሠላም ገፆችን እየገለጡም ያልተዳሰሱ በጎ እሳቤዎችንና ተግባራትን ማሳየትና ማስተማር ላይ አተኩረው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
‹‹ ዛሬ አገሪቱ በጥበብ ችግሮችን የሚፈታ ዜጋ ትፈልጋለች›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ የምትገኘውን አገር በሠላም ገጽታ ግንባታ የሚያግዝ፣ ችግሮችን የሚጠቁም፣ የተሳሳቱ አቅጣጫዎችን የሚያርም የኪነ ጥበብ ባለሙያ ትሻለች ሲሉ ተናግረዋል።
አስቸጋሪ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች የመቀየሩ ብልሀት በኪነጥበብ ባለሙያው ዘንድ የተለመደ በመሆኑ የጠቆሙት ወይዘሮ ሙፈርያት ይህንን ስልት ተጠቅሞ ሠላም ዋጋ በማስገንዘቡ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
«ሠላም በእያንዳንዱ ዜጋ ልቦናና እጅ ላይ ይገኛል» ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሠላም የሚሠራ እንጂ የሚሸመት ባለመሆኑ ባለሙያዎቹ የሰውን ልቦና ስለ ሠላም ዋጋ በማስተማር ጭምር አቅማቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ብለዋል። አገሪቱ ያጋጠማት ችግር ወቅታዊና በቀላሉ የሚፈታ በመሆኑም ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ከትካዜያቸው ለማንቃት ከምንጊዜውም በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ትኩረት ያሻል ብለዋል።
ሰዓሊ ዳንኤል አስፋው በበኩላቸው፤ ስለ ሠላም መስፈን ኪነጥበብ በተለያየ መልኩ ልትናገር ትችላለች ብለዋል። እንደሳቸው አገላለጽ ይህን የማድረጉ ኃላፊነት የባለሙያዎቹ በመሆኑ የጥበብ ኃይልን ማሳየት አለባቸው። የዜግነትና የሞራል ግዴታንም በዚያው ልክ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሰዓሊው ኪነጥበብ የመንፈስ ብቻ ሳይሆን የነፍስም ጭምር በመሆኗ ባለሙያዎቹ ስብራትን የመጠገን፣ ቁስልን የማከም ችሎታን ተጠቅመው በእያንዳንዱ ላይ ሠላም የሚያስገኘውን ስፋር ቁጥር የሌለው ጥቅም በኪነ ጥበብ ሙያቸው ታግዘው ማስተማር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሠላም ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በሠላም ግንባታ ዙሪያ የውይይት መድረኮችን እያካሄደ ሲሆን፤ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል። የውይይት መድረኩ በሠላም ሚኒስቴርና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው