1950ዎቹ ለአፍሪካውያን የተለየ ተስፋ ይዞ የመጣ ጊዜ ነበር። የአፍሪካ አገራት የነበሩበትን የቅኝ ግዛት፣ ጭቆናና የባርነት ቀንበር በመሰባበር ነፃነታቸውን ያወጁበት፤ በአህጉሪቷ የነፃነት ቀንዲል የፈነጠቀበት ጊዜም ነበር። ታዲያ በወቅቱ አፍሪካውያን ራሳቸውን ከቅኝ ገዢዎች ነፃ አድርገው ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር አንድ ሆነው መቆም ግድ ይላቸው ነበረ።
ትንታግ የሆኑ መሪዎቿም በአንድነት የመቆም እቅድን ወጠኑ። አፍሪካን አንድ የማድረጉ ጥረት ጅማሮ ላይ ሁለት ስለ አፍሪካ ነፃነትና ክብር የቆሙ፤ ነገር ግን የየራሳቸው ሀሳብና ግብ ያላቸው ቡድኖች ተመሠረቱ:: በአንድ ወገን ዋናና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አገራቱ በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤ አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድን ደግሞ በሌላኛው ወገን ተሰለፉ። ኢትዮጵያ ይህንን ክፍፍል እንዲቀር፤ ልዩነቶችም ወደ አንድ እንዲመጡና አፍሪካውያን አንድ ላይ ይቆሙ ዘንድ አስታራቂ ሆና መሃከለኛውን ቦታ ይዛ ተሰየመች። የአፍሪካን ጥቅም ለማረጋገጥ ብለው በተለያየ አቅጣጫ የቆሙት የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን አንድ በማድረግ ለአፍሪካ ነፃነትና ለሕዝቧ ኑሮ መሻሻል ይተጉ ዘንድ የእኛዋ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።
በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች በኢትዮጵያ ተገኝተው ስለአፍሪካ አንድነትና አብሮነት እንዲመክሩ ብዙ ማግባባቶችን አደረገች፤ ከብዙ ጥረት በኋላም ሃሳቧ ተሳክቶ አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበው ለነፃነታቸው በኅብረት የሚበጃቸውን ለመሥራት ተስማሙ።
በመጨረሻም ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች የአንድነት መተዳደሪያ ቻርተርን በአዲስ አበባ ተፈራረሙ:: በዚህም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ይፋ ሆነ:: ከዚህ በኋላ ድርጅቱ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ተሰብስቦ እየመከረ፣ ስለ አፍሪካውያን እያወጋና ጉዳዮችን መርምሮ ለውሳኔ እያቀረበ ለጥቁሮች መብት በብርቱ መታገሉን ተያያዘው:: በመላው ዓለም ስለ አፍሪካውያን መብት መከበር ብዙ ሠራ:: በሂደትም ለውጦች መጡ::
ነፃ ያልወጡ የቀሩ የአፍሪካ አገራት ነፃ እንዲወጡና ጠንካራ ሆነው እንዲቆሙ ብዙ ጣረ:: አባል አገራቱም ምንም ያህል የተፈለገውን ያህል ተፅዕኖ መፍጠርና አህጉሪቱን ሙሉ በሙሉ መለወጥ ባያስችላቸውም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጥንካሬ ብዙ ደከሙ:: በእርግጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት አንግቦት ከነበረው አባል አገራቱን ከቀኝ ገዥዎች ነፃ የማውጣት ተልዕኮ አንስቶ እስከ ወቅታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ድረስ አበጀህ የሚያስብሉትን ስኬቶች አስመዝግቧል። ያም ሆኖ መንገዱ አልጋ በአልጋ የሆነለት ወይም ሁሉን ተግዳሮቶች በስኬት ያጠናቀቀ ተቋም ለመሆን አልታደለም።
ይልቁንም አሁንም የኅብረቱን መሪዎች ትኩረት የሚሹ በርካታ ችግሮች አሉበት። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋነኛ ድክመት ሆነው ከሚወሰዱ ጉዳዮች መካከል ድርጅቱ በከፍተኛ ደረጃ ለውጭ ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ የተጋለጠ መሆኑ ዋነኛው ነው። ምንም እንኳን የድርጅቱ መርህ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የማይጋብዝ ቢሆንም በተግባር ሲተረጎም ግን አይስተዋልም።
ድርጅቱ የገለልተኝነት መርህ እንደሚከተል አስቀምጦም ነበር። ይሁን እንጂ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ጊዜ አብዛኞቹ አገራት የገለልተኛ አገሮች ማህበር አባል ቢሆኑም የአፍሪካ አገሮች እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው አፍሪካን የጦርነት አውድማ አድርገዋት ነበር። ቀዝቃዛው ጦርነት ቀዝቃዛ የተባለበት በሁለቱ አገሮች ካምፖች ከቃል ጦርነት በዘለለ መልኩ ቀጥተኛ ጦርነት ባለመካሄዱ ነበር። አፍሪካ ግን የሁለቱ ኃያላን ካምፖች የጦርነት አውድማ ነበረች።
አንዱ የአፍሪካ አገር የምዕራቡ ዓለም ደጋፊ ከሆነ ሌላኛው የምሥራቁ ደጋፊ ይሆን ነበር። በዚህም ሁለቱም ካምፖች ለርዕዮተ ዓለም ተከታዮቻቸው የጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ አፍሪካ እርስ በእርስ እንድትባላ አድርገዋል። አገሮች ብቻ ሳይሆኑ በአንድ አገር ያሉ ዜጎችም በምዕራቡና በምሥራቁ ጎራ ለይተው በመሰለፍና በመከፋፈል ከፍተኛ ደም ያፋሰሰ ጦርነት እንዲካሄድ አድርገዋል። መንግሥታት የሶሻሊስት ካምፕ ደጋፊ ከሆኑ መንግሥትን የሚቃወሙ አማጽያን የምዕራቡ ካምፕ ደጋፊ በመሆን እርስ በእርሳቸው ተፋልመዋል።
የሁለቱን ካምፕ ፍጥጫ አፍሪካ ብድርና እርዳታ ለማግኘት ልትጠቀምበት ሲገባ እውነተኛ የጦርነት ሜዳ ሆና አገልግላለች። በአጠቃላይ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ለአፍሪካ የባከነ ዘመን ሊባል የሚችል ነው። ሌላኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ከሚለው መርሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነው። ይህም ድርጅቱ በአንዳንድ አገራት ውስጥ የሚፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶችንና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን ጣልቃ እየገባ መፍትሔ እንዳይሰጥ በማድረጉ በአምባገነናዊ መንግሥታት በአህጉሪቱ ሕዝቦች ላይ በርካታ ግፎችና ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ሲካሄድ ጭምር ዝምታን እንዲመርጥ አድርጎታል። የዩጋንዳውን አምባገነን ኤዳሚን ዳዲን ድርጊት ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
በመሆኑም ድርጅቱ አፍሪካን ከነጮች አገዛዝ ነፃ ቢያወጣም ሕዝቦቿን ከገዛ ጉያዋ ከፈለቁ ጨቋኝ አምባገነን መሪዎች ግፍና ጭቆና ሊታደጋት አልቻለም። እናም የአህጉሪቱንና የሕዝቦችን እውነተኛ ነፃነት ማረጋገጥ ተስኖት ኖሯል።
ስለሆነም ከሃምሳ ዓመታት በላይ ስለ አፍሪካውያን የተሟገተውና የሠራው ተቋም ለአፍሪካውያን በሚፈልጉት መልኩ ድል ሊያስገኝላቸው አልቻለም:: ድርጅቱም ሲመሠረት ይዞት የተነሳውን ዓላማ ማሳካት ተስኖታል:: እንዲያውም እያደር የማስፈፀም አቅሙ እየተዳከመ ሄዷል:: መሪዎችና የአፍሪካ አገራት ድርጅቱን ከማጠንከር ይልቅ በለዘብተኝነት እየተመለከቱ መቀጠላቸውም ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ተደርጎ ይወሰዳል:: በተጨማሪም አህጉሪቱን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአባል አገራቱ መዋጮ እንደመተዳደሩ አባል አገራቱ የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ እንኳን በተገቢው መልኩ መክፈል አልቻሉም ነበር::
በዚህም አቅሙ ተዳከመ፤ ይህን አድርጉ ያን አታድርጉ የሚለው የመሪነት ትእዛዙን የሚያከብር አገር ቁጥር ቀነሰ:: በመሆኑም ይህንን የተገነዘቡት የአፍሪካ አገራት ለአፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት ድርጅቱን እንደ አዲስ ለማቋቋም ወሰኑ:: በመሆኑም ተዳክሞ የነበረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ መልክ ተጠናክሮና በጉዳዮች ላይ የመወሰን አቅሙን አሳድጎ በአዲስ ድርጅት ለመተካትና አፍሪካን እንደ አዲስ በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም አፍሪካውያን በደቡብ አፍሪካ ደርባን ተሰባሰቡ።
53 የአፍሪካ አገራትን በአባልነት በማካተትም የአፍሪካ ኅብረትን መሠረቱ። በዚህም ኅብረቱ ሰነዶቹን ፈትሾና ራሱን አጠንክሮ ግጭቶችን ለማስቀረት፣ ብሎም ግጭቶች ሲከሰቱ ለመፍታት አስፈላጊ ሲሆንም የራሱን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት የሚያስችለውን አቅም አጠናከረ።
በአህጉሪቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ግጭቶችን ለማብረድም ሰላም አስከባሪ ኃይሉን ማሰማራትም ችሏል። በተጨማሪም በአህጉሪቱ ውስጥ ስልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የሚቆናጠጡትን በማውገዝና እውቅና ባለመስጠት ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት የራሱን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛል::
ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን አሁንም በአንዳንድ አገራት ያሉ ግጭቶችን ማስቆም አልቻለም። ናይጄሪያ በአፍሪካ ትልቅ አገር ሆና ሳለች በየቀኑ በግጭት የምትታመስ አገር ሆናለች።
ኮንጎም ከተራ ዘራፊዎች እስከ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች በየቀኑ የሚፋለሙባት፤ በተፈጥሮ የታደለች ግን በዚያው ልክ የተረገመች አገር ሆናለች። በግብጽና በሊቢያ በተከሰተው የአረብ አብዮት ኅብረቱ አቋም በመያዝ ችግሩን ለመፍታት ቀዳሚ መሆን ሲገባው አሁንም የውጭ ኃይሎች እንደፈለጉ ሲሆኑ ተስተውሏል። ምንም እንኳን ዘግይቶም ቢሆን የተሳካ ሥራ መሥራት ቢችልም ከዚህ ቀደም በኬንያና በዚምባቡዌ ምርጫን ተከትሎ የተነሳውን የእርስ በእርስ ብጥብጥ በመግታት በኩልም ዳተኝነት ታይቶባታል።
በሊቢያ ምዕራባውያን ጣልቃ ገብተው በጎነጎኑት ሴራ ዜጎቿ በሁለት ጎራ ተቧድነው አገራቸውን እንዳልነበረች አድርገው ሲያወድሙ የአፍሪካ ኅብረት የት ነበር አስብሏል። ይህም የቀደሙ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ችግሮችን በሚፈታ መንገድ እንደ አዲስ ተጠናክሮ ተመስርቷል ቢባልም የአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን የማስፈፀም አቅሙ ያን ያህል የተጠናከረ አለመሆኑን ያመላክታል።
ሌላው ለኅብረቱ ድክመት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ትልቁ ጉዳይ ከ3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ ዛሬም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ መቀመጫ የሌላት መሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ ኅብረቱ አህጉሯ በተመድ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ከዚህ ግባ የሚባል ሥራ የሠራው የለም።
በዚህም ምዕራባውያን ሀይ ባይ አጥተው በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ እንዳሻቸው ሲፈተፍቱ ይስተዋላል። እንዲሁም ኅብረቱ በ2060 አንድም የመሣሪያ ድምጽ የማይሰማበት አፍሪካን የመፍጠር ዕቅድ አስቀምጧል።
ነገር ግን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ይህንን እቅዱን ለማሳካት የሚችልበት ቁመና ላይ ይገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከዚህ አኳያ ኅብረቱ ዛሬም ቢሆን ጠንክሮና አባል አገራቱን አስተባብሮ አህጉሪቱን በራሷ የቆመችና ዴሞክራሲ ያበበባት ለማድረግ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል:: በተለይ አህጉሪቱን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት ዛሬም በሞግዚት መልክ የሚያስተዳድሯት ምዕራባውያንን ጫና ቀንሳ በራሷ ለራሷ ጉዳይ ትቆም ዘንድ ኅብረቱም አባል አገራቱም በኅብረት ሊቆሙ ይገባል:: የአፍሪካ ኅብረት እነሆ ከስኬቱም ሆነ ከልምዱ ለመማር የሚያስችለው የግማሽ ክፍለ ዘመን የእድሜ ባለፀጋ ነው። እናም የወደፊት አቅጣጫውን ሲተልም ያለፈውን ጉዞ ዞር ብሎ ማየት፤ የቆመበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቆ መረዳትና መጪውን አቅርቦ ማሰብ ይጠበቅበታል።
ከዚህ አንፃር የኅብረቱ ቀጣይ ጉዞ ሰፊ ጥናትና ትንታኔ የሚጠይቅ ይሆናል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014