ሰዎች! እንዴት ነን? ሁሉ ሰላም ነው? ሰላም ያድርግልን። አሁን አሁን እግራችንን ደንቀፍ ላደረገን ድንጋይ ተቃውሞ መንገድ ዘግተን፤ ጎማ አቃጥለን፤ እርስ በርስ ተዘላልፈን ስናበቃ የፖለቲካውን ስርዓት የምንተነትን ሆነናል። ኧረ ማስተዋል ወዴት አለሽ? በዜማም ብትጠራ አልሰማ አለችን’ኮ! ወይ ቀድሞውኑ ስንራመድ መጠንቀቅ ነው። እንደውም ከግዑዝ ነገር ጋር መጣላት ያስጠረጥራል፤ ለምርመራም ያስጋብዛል ባይ ነኝ። አሃ! ድንጋይ ፖለቲካ አይደለማ!?
ሰው የአገራችን ችግር በእጥረት የተሞላ እንደሆነ ያስባል። የግንዛቤ እጥረት፣ የገንዘብ እጥረት፣ የምግብ እጥረት፣ የአቅም እጥረት፣ የመብራት ኃይል እጥረት፣ የእውቀት እጥረት ወዘተ እንደ ችግር ይጠቀሳሉ። ፖለቲካ የገባን እየመሰለንም የምንፈጥረው ችግር ብዙ ነው። አዎን! ይህ ሁሉ ችግር ነው። እኔ ግን ሰው እነዚህን ችግር ብሎ ሲጨነቅባቸው ይገርመኛል። አይደለማ! የእኛ ችግር ይህ ሁሉ አይደለም። አታምኑኝም!?
እንደው አናምንሽም ካላችሁ እነዚህ የተጠቀሱትና ሌሎችም ያልተጠቀሱት፤ የሚያው ቁንና የማናውቃቸው ተጨማሪ ችግሮቻ ችንም፤ እያንዳንዳቸው እንደ አንድ ነጠላ ፍሬ ቢታሰቡ፤ የችግሩን ዘንቢል አግኝ ቼዋለሁ ነው የምላችሁ። ይህ ዘንቢል ምን ይባላል? የምንፈልገውን ነገር አለማወቅ።
አበቃ! የሚፈልጉትን እንዳለማወቅ ያለ ችግር ግን የት አለ? እኔ በበኩሌ ከዚህኛው የባሰ ችግር ሊታየኝ አልቻለም። እኛ’ኮ እንኳን «ምን ትፈልጋላችሁ?» ተብለን ይቅርና «ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?» ስንባል፤ ያውም ዶክተርና ኢንጅነር ከማለት ውጪ ብዙ አማራጭ ያለ በማይመስለን ጊዜ፤ «ሥራ መያዝ» የምንል ሰዎች ነበርን።
ምን እንደምንፈለግ አናውቅማ። አስቡት! ስንት ዓይነት ሥራ እንዳለ? ተምረን የምንጨርሰው በ«ሥራ እናገኛለን» ግምት እንጂ የምንፈ ልገውን ለመሆን በማመን አይደለም። የሚፈልገውን የማያውቅ ምን አማራጭ አለው? ብትሉ፤ ሁለት አማራጭ አለው። አንደኛ የሚፈልገውን ለሚያውቅ ለሌላ አካል ግብዓት ይሆናል። ሁለተኛ የማያውቀውን የሚፈልግ እየመሰለው ለሁሉም ይነፍሳል። ሁሉም ጋር ይሄዳል፤ ሁሉም ጋር ይገባል። እንዲህ ዓይነት ሰው እንደው ተሳስቶ የሚፈልገውን ያወቀ ከሆነ፤ ያም እንከን ሆኖ ይገኛል፤ «እንከን ፈላጊ» ይሏል ይህን ነው። ስለመፈለግ ሲነሳ ግርም የሚለኝን ላካፍላችሁ።
የኑሮ ነገር መቼም የማይወስደን ቦታ የለም። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከመጠጥ ቤቶችና ካፌዎች በር እስከ ቤተመንግሥት አልያም በቀድሞው ስርዓት እስከ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ድረስ የፈታሾች እጅ አርፎብኛል። ይህ ማለት ከ«ኬፍ! ሰላም ነው?» ዓይነት ንክኪ እስከ «ኧረ ነዳጅ አልተቀበረብኝም!» የሚያሰኝ ዓይነት ፍተሻ ድረስ አይቻለሁ ነው። ፈታሾቹ አንዳች ነገር ፈልገው እንደሚ በረብሩ ይታወቃል፤ ግዴታ ሥራቸውም ነው። የሚገርመኝ ታድያ ልዩነቱ ነው።
በእርግጥ ኬክ ቤት ስትገቡና ማረሚያ ቤት ወይም ቤተ መንግሥት ስትገቡ የምታገኙት ነገር ስለማይመጣጠን የአፈታተሽ ልዩነቱን ነገር ልናልፈው እንችላለን። እንዲህ ግን የወጋችን ግብዓት ከመሆን አይድንም። ለምሳሌ በመሥሪያ ቤቴ ከበር ላይ ሰላምታ ሰጥተው የሚያስገቡኝ ፈታሾች አሉ። ወይም አንዳንዴ ጎራ በምልባቸው ህንጻዎች ላይ «እሺ!» ብያቸው የቦርሳዬን ቀለም አይተውና ልስላሴውን አረጋግጠው የሚያሳልፉ ይገጥሙኛል። መቅረጸ ድምጽ አይገባም ብለው ሲያበቁ ተንቀሳቃሽ ስልክ ግን ትዝ የማይላ ቸውም ጭምር ታዝበናል።
ታድያ እነዚሁ ፈታሾች አንዳንዴ «ፈትሹ ፈትሹ» ሲላቸው መሰለኝ «እስቲ!» ብለው ቦርሳችንን ከፈት ያደርጋሉ። ያገላብጣሉ፤ ያራግፋሉ። በእርግጥ ከጥቂት ወረቀቶችና ተለቅ ያለ የምሳ ዕቃ በቀር የሚያገኙት ነገር የለም፤ እኔ ቦርሳ ውስጥ። ግን መጀመሪያውኑ ምን እንደሚፈልጉ የሚያውቁ ስለማይመስለኝና ምን ቢያገኙ «አገኘን» እንደሚሉ ስለማይገባኝ እንደ እንግዳ ነገር በግርምት ነው የማያቸው። «ተቀጣጣይና የሚፈነዳ ነገር ነው የሚፈልጉት ‘ኮ!» አለችኝ አንዲት ጓደኛዬ። እንደዛ ነው? ምን ዓይነት ተቀጣጣይና የሚፈነዳ ነገር? መልኩንስ ያውቁታል? ይህን ሁሉ አስባለሁ።
መቼም የኢትዮጵያ አምላክ እንደ ቸርነቱ፤ «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉት እንዳይሆንብን ሲል ይጠብቀናል እንጂ፤ ዘቦችና ፈታሾቻችን የሚፈልጉትን ያውቃሉ ብላችሁ ነው? ለዛ ነው ይሄ የምንፈልገውን አለማወቅ ችግር ነው የምለው። ያው እንዲህ ቀለል ያሉትን አነሳን እንጂ የሚፈልጉትን በሚገባና በደንብ አስረግጠው የሚያውቁ ፈታሾችም አሉ። እነርሱ ደግሞ «ክፈች…ከፍ አድርግ… ፍታ…አውልቅ…አስቀምጪ…» ወዘተ እያሉ ረስተን የያዝነውን ዕቃ ሳይቀር ያስታውሱናል። የብረት ጌጣጌጦቻችንን ሳይቀር «ኧረ ጠዋት ከቤት ስወጣ ያደረኩት አልመሰለኝም ነበር» ያስብሉናል።
የሚፈልገውን የሚያውቅ የሚያገኘው የሚፈልገውን ነው። አለበለዚያ ግን ለማንም ለምንም ሳይጠቅም እንደተቅበዘበዙ መቅረት ነው። ከዛ አለፍ ካለ ደግሞ «መቅበጥ» የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ መነሻው ከዚህ ከሚፈልጉትን አለማወቅ ሆኖት እርፍ ይላል። እንዴት? የምንፈልገውን ሳናውቅ ስንቀር «ሁሉ አማረሽ»ን ሆነን ስለምናስቸግር።
ስንቀብጥ ጥያቄአችን «ለምናከብረው ሰው ለምን ሀውልት አልቆመላቸውም?» ከማለት «ለምን ሀውልቱ ደመቅ ያለ ቀለም አልተቀባም?» ወደ ማለት ይወርዳል። አነጋገራችን «ለምን ስለ አንድነት አናወራም?» ከሚለው «ማን ነው አንድ አድራጊ? ማነው አንድ ተደራጊ?» ወደሚለው ይዘቅጣል። ያየው ነገር ሁሉ ጣፋጭ እየመሰለው፤ «ግዢልኝ እናቴ!» እያለ እንደሚያስቸግር ህጻን መቅበጥ አንድ ነገር ነው፤ የሚፈልገውን የማያውቅ ሲቀብጥ ግን፤ አገር አይመልሰውም።
እና አሁን ባልኩት አትስማሙም? ችግራችን የምንፈልገውን አለማወቃችን አይደ ለምን? እንደችግር የሚነሱ እጥረቶቻችን ምክንያታቸው ይኸው ነው ማለቴስ ውሸት ነው? ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤት ወይም የፌዴራሊዝምና የመልካም አስተዳደር ስልጠና ምላሽ ይሰጣሉ ብዬ አላስብም። ልጆች እንኳ «ማንን ትፈልጋላችሁ ዛሬ በማለዳ…» እየተባባሉ ተቃቅፈው ሲጫወቱ፤ ጠያቂው ቡድን እገሌን እንፈልጋለን ብሎ ከጠየቀ በኋላ ነው ተጓተው አሸናፊው የሚለየው።
በዚህ መሰረት ለመጓተትና ለመገፋፋት ራሱ መጀመሪያ የሚፈልጉትን ማወቅ ያስፈልጋል ማለት ነው። ዳይ በቃ! ሁላችንም ምን እንደምንፈልግ መጠየቅ ነው። እዚህ ጋር ግን ያዙልኝ፤ «ምን ትፈልጋለህ?» ሲባል፤ «እገሌ ስለማይወክለኝ አልፈልገውም!» የሚል ደግሞ ይገጥማችኋል። ፍላጎቱን ካለማወቁ የተነሳ ቀድሞ ትዝ የሚለው የማይፈልገው ነው። የሚፈልገውን ለማያውቅ ምን ሊቀረብልት ይችላል? ተመልከቱ! «ሰላም! እንኳን ደኅና መጡ፤ የሚፈልጉትን አዝዘዋል?» ከአንገቱ ጎንበስ ከወገቡ ቀንጠስ ብሎ…አስተናጋጅ፤
«አላዘዝኩም! ምን ምን አለ?» «በየዓይነት፣ ማኅበራዊ፣ የፆም አገልግል፣ የፍስክ አገልግል፣ ኮርኒስ…» /አስተናጋጅ ዝርዝሩን ይቀጥላል/
«ምስርና ሽሮ አልፈልግም፤ እንቁላልም አልፈልግም፤ አይብም አልፈልግም…»/ ተስተናጋጅ ይቀጥላል/
ግራ የገባው አስተናጋጅ፤ ሥራው አስገ ድዶት ትዝብቱን ዋጥ አድርጎ፤ «እሺ ምን ላቅርብልዎ?»
«አንዱን አምጣውና ከበላሁ በኋላ እናያለን?»
«???»
አያቴ ብትሆን ይህን ሰው፤ «ምን ልሥራልህ ብዬ ጠይቄ እንቢ ብለሃል። በኋላ አልጣፈጠኝም፤ መረረኝ፤ ጨው ያንሰዋል… እያልክ ስታለቃቅስ እንዳልሰማ። እንደሙያዬ ነው ሠርቼ የማበላህ…ሰምተሃል!» ትለው ነበር። ያ አስተናጋጅ ግን እዛው ቆሞ እንግዳው የሚፈልገውን እስኪያውቅ ድረስ ይጠብቃል። «ማኅበራዊ ይሁንልዎ ይሆን?» የሚፈልገውን የማያውቅ ሰው ለአስተናጋጅ እንኳ አይመችም። እና…ምን ትፈልጋላችሁ? ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
ሊድያ ተስፋዬ