ትውልዳቸው በወሎ ክፍለ አገር ቦረና አውራጃ መካነ ሰላም ከተማ ነው። በ1968 ዓ.ም በለውጡ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተደጋጋሚ ይዘጉ ስለነበር የትውልድ መንደራቸውን ጥለው ወደ ደሴ ከተማ ተዘዋወሩ። በዛው ዓመት በግንቦት ወር ደሴ ከተማ የሐረር ሶስተኛ ክፍለ ጦር የወታደሮች ምልመላ ሲያደርግ ከጦሩ ጋር ተቀላቅለው ሰለጠኑ።
በሐረር ሐማሬሳ ማሰልጠኛ ገብተው የአገር ፍቀርና የውትድርና ስሜት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ተገነዘቡ። የእግረኛ ወታደራዊ ትምህርት እንደተማሩ፤ አስገንጣይ ሃይሎች በተለይ በኤርትራ አካባቢ ተጽእኖ ፈጥረው ስለነበር ለመመከት ስልጠናቸውን ሳይጨርሱ ወደ ኤርትራ ክፍለ አገር ተሰማሩ። ከ1969 አብዮቱ 10ኛ ዓመቱን እስካከበረበት 1977 ዓ.ም ድረስ በኤርትራ እግረኛ ወታደር ሆነው ቆዩ።
ምጽዋ ላይ 42ኛ ኮርስ ተመልምለው በሐረር ጦር አካዳሚ ለአንድ ዓመት ተከታትለው በ1973ዓ.ም የመኮንንነት ስልጠና ወስደው ተመርቀዋል። ወደ ኤርትራ በመመለስ በተለያዩ ውጊያዎች ተሳትፈዋል። በውትድርና ዘመናቸውም አራት ጊዜ ቆስለዋል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኤርትራ ባርካ ትምህርት ቤት በማታ ትምህርት ተከታትለዋል። የከፍተኛ ትምህርት እድል አግኝተው ወደ ሞስኮ ሌኒን ጦር አካዳሚ የተጓዙት የዛሬ እንግዳችን ሻምበል ዘለቀ አንዳርጌ ባገኙት የትምህርት ዕድል እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ተምረው ለመመለስ የሚያስችላቸው ነበር። ሆኖም ለሶስት አመታት እንደተማሩ 1983 ዓ.ም ወያኔ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ ያመጸበት ጊዜ ስለነበር በአገር ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
በወቅቱም በኮረምና አላማጣ ውጊያ 140ኛ ብርጌድ አዛዥነት እየመሩ ግራካሶና አሸንጌ ለማስለቀቅ በቅተዋል። ወደ አሰብ ለስራ እንደተጓዙ ነገሮች እየተበላሹ በመሄዳቸው፤ ጦሩም በመፍረሱ በርካታ የሰራዊቱ አባላት ወደጎረቤት አገራት ሲሰደዱ እርሳቸው ደሴ ገቡ። ወያኔ ደሴን እንደተቆጣጠረ የቀድሞ ሰራዊት አባላት እጅ ሲሰጡ እርሳቸው ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ።
ዘመድ ጋር ተጠግተው ወደ ደሴ ቤተሰብ ጋር ሲመለሱ ተይዘው ለሶስት ወራት ታስረዋል። ከተፈቱ በኋላ የተሰማሩት በሹፍርና ሙያና በተለያዩ የግል ስራዎች ነው። ከዛሬው እንግዳ ሻምበል ዘለቀ ከህይወት ልምድና ተሞክሯቸው እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
አዲስ ዘመን :- የኤርትራ ቆይታዎን እንዴት ያስታውሱታል?
ሻምበል ዘለቀ:- ኤርትራን ጠንቅቄ አውቃታለሁ። ፍጹም ኢትዮጵያን የሚሸት አገር ቢኖር ኤርትራ ነው። ሕዝቡ ኢትዮጵያን የሚወድ ነው። አስመራ ከተማ ትምህርት ስለጨረስኩ እዛው ለመኖርም ፍላጎት ነበረኝ። ከሱዳን ጠረፍ እስከ ጂቡቲ ጠረፍ በእግር ተጉዤም አይቼዋለሁ። ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ስትቀላቀል፤ በወቅቱ የተወለዱ ኢትዮጵያ ገብረእግዚአብሄር፣ ኢትዮጵያ ገብረመድህን በሚል የሚጠሩ በርካቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ የሚጠሩ በርካታ ሰዎች ያሉት ኤርትራ ነው።
ድሮም እንደጠላት የማየው ሕወሓትን ነው። የኤርትራን ህዝብ ጣሊያን በርዞታል የሚባለውም የተሳሳተ ነው። ባህሉ አልተበረዘም። ኤርትራ ውስጥ ሠርግ ሲኖር ገበታ የሚቀርበው በትሪ ነበር። ሕዝቡ ሻእቢያም ሲያሸንፍ ያጨበጭባሉ፣ እኛም ስናሸንፍ ያጨበጭባሉ። እኛ ብዙም በእዛ አንከፋም። 1970ዎቹ ነጻ ያልወጡበት ምክንያት ያኔ ጦሩ ጠንካራ ስለነበር፣ ሕወሓትም ብዙም ድጋፍ ስላልነበረው ነበር። አስመራ፣ ምጽዋ፣ ባሬንቱ ተከብበው ያላሸነፉት ቆይተው መንግሥት ሲዘናጋ አሸነፉ። ለኤርትራ መገንጠል የሕወሓት እጅ ወሳኝ ነበር።
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በባድመ ላይ በውጊያ እንድሳተፍ ተጠይቄ ነበር። በመሰረቱ ወሳኝ የሚባሉ አካባቢዎች ተወስደው ለባድመ ጦርነት ውጣ ሲሉኝ ‹‹ምኗን ሰዳ ምኗን ጨበጠች›› እንደሚባለው አልዘምትም ብዬ እምቢ አልኩኝ። ባድመ ላይ መዝመት አላስፈለገኝም። ምክንያቱም ቦታው አሸዋማ ነው። የእርስ በእርስ ጦርነትም ስለሆነ ምክንያታቸውም አይገባኝም፤ አልተሳተፍኩም። ግን የኢትዮጵያን ጉዳይ በአንክሮ ስከታተል ቆይቻለሁ። ዶክተር ዐቢይ ሁለቱን አገራት ለማግባባት የሄዱበት መንገድ በጣም የሚደነቅ ነው።
አዲስ ዘመን :- ለደርግ መንግሥት መሸነፍ እርስዎ በምክንያትነት የሚጠቅሱት ምንድን ነው?
ሻምበል ዘለቀ:- በርካቶች እንደሚያወሩትና እንደሚጽፉት አይደለም። መንግስቱ ኃይለማርያም የጻፈውንም አንብቤያለሁ። እኔ ለደርግ ሰራዊት ሽንፈት ነው የምለው ሰራዊቱን በብቃትና በጥራት የማደራጀት ችግር ነው። እነርሱ ሽምቅ ተዋጊዎች ነበሩ። እነርሱን የሚመጥን ትግል እናድርግ ብለን ነበር። እኛ መኮንኖች አንድ ወቅት ላይ ‹‹ተገድዶ አለፍላጎቱ ታፍሶ የሚቀላቀል ጦር ታመጣላችሁ፤ ብሄራዊ ምልምል ታስገባላችሁ፤ ጦር ታበዛላችሁ መብቱና ግዴታውን የሚያውቅ ወታደር ይዘጋጅ። ለዚህም እኛ እንበቃለን የወታደር ጋጋታ አያስፈልግም።›› እንላቸው ነበር።
በወቅቱ ያኮረፉ ጀኔራሎችም ነበሩ። ለምሳሌ መንግሥቱ ኃይለማርያም ኮሎኔል በነበረበት ወቅት ከኮሎኔል በላይ የነበሩ ሰዎች ለጊዜው እንጂ እንደማይደግፉት ይነግሩናል። የኤርትራን ጉዳይ ፈትተን ወደዚህ መንግሥት እንዞራለን የሚሉ ከፍተኛ መኮንኖች ነበሩ። ምንም እንኳን አንዳንድ ኮሎኔሎች ከመንግሥቱ ኃይለማርያም የማይሻሉ ቢሆኑም መፈንቅለ መንግሥት እስከማድረግ ተደርሷል። ዞሮ ዞሮ ብቃትና ጥራት ያለው ወታደር አለመቋቋሙ፣ ፖለቲካውን በተገቢው መንገድ የሚሰራ ሰው አለመኖሩ ለውድቀቱ እንደምክንያት ማንሳት ይቻላል። እነርሱ በሚዳከሙበት ወቅትም ለድርድር የሚቀርቡበት አማራጭም ነበር። የሚያነሱት ከመገንጠል ጋር የተያያዘ ጥያቄ ስለነበር መንግሥትም አልተቀበለውም።
በነገራችን ላይ የኤርትራ ጉዳይ እስከነጻነት የሚደርስ ነገርም አይደለም። የተቀሙት በፌዴሬሽን ነው፤ ስለዚህ ሊመለስ የሚገባውም በፌዴሬሽን ነው። እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ግዳጅ ጥሎ ውሰደው ከዚህ በኋላ ያለውን ተብሎ የሚወረወር ወደብ አልነበረም። በርግጥ ያለቀ ጉዳይ ነው። ወደ ወያኔ ስንመለስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የዶክተር ዐቢይ መምጣት ሰላም ለስምምነቱ ጥሩ ነገር አድርገዋል። እርሳቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ የተናገሩት በፍቅር፣ በሰላምና በመደመር ነገሮች በሰላም ሊፈቱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ነበር ። ነገር ግን ሕወሓት ወደ ጦርነት እንደሚገባ ውስጤ ይነግረኝ ነበር።
ነፍሳቸውን ይማርና ፕሮፌሰር መስፍን ባንድ ወቅት የዶክተር ዐቢይ ነገር ለክርስቶስም አልበጀም። ግራህን ሲመቱህ ቀኝህን ስጥ የሚለው ይህች አገር መፍረሷ ነው የሚል መልክት አስተላልፈው ነበር። ወደ ሰላም እንደማይመጡ፣ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነና ለጦርነት እንደሚመጡ ሁሉ ግምት ነበር። በሚዲያቸው የሃሰት መረጃንና የጦር ቅስቀሳ ያዘሉ መልእክቶችን ያስተላልፉ ነበር። በረሃ በነበሩበት ጊዜም የሚያስተላልፉት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ነበር። በድምጸ ወያኔ በአማራ ላይ ቅስቀሳ አካሂደዋል። ‹‹የተከበርከው የትግራይ ሕዝብ ሆይ ትግሬ ገዳይ የሚለው አማራ እየፎከረ ነው›› ይሉ ነበር። በመንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን ስለብሄርና ብሄረሰብ የሚነሳበት ሁኔታ አልነበረም። ከዛን ጊዜ አንስቶ የሃሰት መረጃ በማስተላለፍ ሕዝቡን ይቀሰቅሱ ነበር።
በደርግ ጊዜ ይካሄድ የነበረው የመደብ ጦርነት ነበር። ይህ ማለት ወቅቱ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ነበር። ሞስኮ በነበርኩበት ጊዜም ሌኒን ያካሄደውን አብዮት በቦታው ተመልክቻለሁ። የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ መርህ ነው። ሃይማኖት የአዳም ዘሮች ወንማማቾች ናቸው ይላል። በፈረንሳይ አብዮትም ሁሉም ሰዎች ወንድማማቾች ናቸው ተብሏል። የፊውዳል መደብ፣ የገዢ መደብ፣ የከበርቴ መደብና የሃብት ክፍፍሉን ፍትሃዊ ለማድረግ ሶሻሊዝምን ብሎም ካፒታሊዝምን እንገነባለን ብለን ነበር። በሶቪየት ሕብረት ውስጥ ኮምኒዝም በአንድ ወቅት ተገነባ ተብሎ ነበር። አሁን በኢትዮጵያ ያለው የብሄርተኝነት ፖለቲካ እጅግ ኃላ ቀር ነው። የዘር ፖለቲካ ከ150 ዓመታት በፊት የተወገደ ነው። ሕወሓቶች አሁን ወደዚህ ተመልሰው ኢትዮጵያን ለምን እንደሚያዋርዱ አይገባኝም። ሁሉም የፖለቲካ ደንቆሮዎች ናቸው። የማስተዳደር ብቃትና እውቀት የላቸውም።
አዲስ ዘመን :- በወረራው ጊዜ የደሴ ከተማ ምን አይነት ገጽታ ነበረው?
ሻምበል ዘለቀ:- ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ማእበል እየተመራ የሕወሓት ሃይል እየገሰገሰ በነበረበት ወቅት የቀድሞ ጦር አባላት ቆቦ ላይ ሄደን እንመክት ብለን ነበር። ጌታቸው ረዳ ‹‹ሂሳብ እናወራርዳለን›› ብሏል። ሂሳብ ከነርሱ ጋር አወራረድን ከተባለ 30 ዓመታት አልፎናል። አሁን ሂሳብ ይወራረድ ካሉ ስልጣን በያዙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእኛም ላይ ነው። አመጣጣቸው አደገኛ ነው፣ ተቆጥተዋል፣ ከነበራቸው ባህሪ የበለጠ ወደ አውሬነት ተቀይረዋል፤ ማንንም ሰው አይምሩም፤ ስለዚህ መነሳት አለብን ብለን ተናግረን ነበር። አልተሳካም እንጂ የሚቆስል ወታደር መሳሪያ እንኳን አስታጥቁን ብለን ጠይቀን ነበር።
እነዚህ ሰዎች ለኢትዮጵያ ክፉ የሰሩ ናቸው። እየገፉ ሄዱ። ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጦሩ ለቀቀላቸው፤ ግን ቀድመው ገብተውም ነበር። ብዙዎችም አካባቢውን ለቅቀው ሸሽተዋል። ከኤርትራ ይሸሻል፣ ከትግራይ ይሸሻል፤ ሰው ከንብረቱ፣ ከሚስቱ ወዴት ይሸሻል የመጣውን እጋፈጣለሁ ብዬ ደሴ ቀረሁ።
ጦሩ ሙልጭ ብሎ ከደሴ መሸሹን ያቆመው 6፡30 አካባቢ ነው። እነርሱ የሚገቡት ዘግይተው ነው። ከጦሩ ጋር የተራራቁ መሆናቸውን በተኩሱ አረጋግጫለሁ። ቆይተው ይገባሉ ብዬ ሳስብ ደሴ የገቡት ከሰዓት 9፡00 አካባቢ ነበር።
በየቤታችን ተቀምጠን ነበር።
መጀመሪያ ሲቲ ፓርክ ገቡ። መጀመሪያ የሚያስሱት አልኮል መጠጥ ያለበትን ቤት ነው። ቢራ እየጠጡ ከበሮ እየደለቁ ‹‹አንተ ማነህ ? አማራ አሁን የታለህ ? ሸሽቻለሁ!›› በማለት ሲያሾፉ ይደመጡ ነበር። በጣም ያሳዝን ነበር። ከቤት ውስጥ ሆኜ የከተማው እንቅስቃሴ ይታየኛል። የእዛኑ ዕለት ምሽት በየቤቱ እያንኳኩ ያልተከፈተላቸውን በመስበር ማውደም ጀመሩ። አብዛኛው የአካባቢው ሕዝብ ጥሎ ወጥቷል ቤቶችን መፈንቀል ቀጠሉ። ውሾች እየተከተሉ ይጮሁ ነበር፤ የዛን ሌሊት ቁጭ ብዬ አደርኩኝ። በማግስቱ ወደ ኮምቦልቻ ግስጋሴያቸውን ቀጠሉ። እሁድም ሰኞንም ከቤት ሳልወጣ ዋልኩ። ማክሰኞ ጓደኛዬ ቤት መጥቶ ይዞኝ ወጣ። በየመንገዱ ይፈትሹ ነበር። ግብራቸው ሞባይልና ብር ነበር። ሰውን እያሰለፉ በርብረው ይዘርፋሉ።
ወራሪ ሃይሉ ያበሳጨውም ሆነ ዘርፎኛል የሚለው ሻዕቢያን ነው። ወሎ መጥተው የህዝቡን ንብረት ለምን ያወድማሉ? እኔ የምለው መንግስት አላዳነኝም፣ በተአምር ተርፌያለሁ። ወደፊት ደግሞ ደብረጺዩን አያድናቸውም ሲያበቃለት ያልቃል። ሕዝቡ ሲረጋጋ ራሱን በራሱ የሚጠብቅበትን ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን:- በወቅቱ የሕዝቡንስ ስነ ልቦና እንዴት ይገልጹታል ?
ሻምበል ዘለቀ:- በቆይታቸው የሰነበቱት ነዋሪውን ሲያስጨንቁ ነበር። ለወረራ የሚገባው የመጀመሪያው ተዋጊ ሃይል ነው። በዋና ዋና መንገዶች ያገኟቸውን ባንኮች፣ ሱቆች እየዘረፈ ይዞ ይጓዛል። የምንጓዘው አገር ለመግዛት አይደለም፤ ኢትዮጵያን ነጻ አውጥተን የሽግግር መንግሥት አቋቁመን እንመለሳለን። ይልቅስ አሁን እኛ አልፈናችሁ ብንሔድም ቀጣይ የሚመጣ ዘራፊ ቡድን አለላችሁ እያሉ ነግረውናል።
የሚቀጥለው የተደራጀ የሚመስል ቡድን ነው። ራሱ ታጣቂ ነው። የዘረፋ ስራም ያከናውናል። የሚገርመው ነገር እርስ በርሳቸውም ቅራኔ አላቸው። ለምሳሌ ደሴ ላይ ሜርሻ ኤሌክትሮኒክስ ሲዘረፍ በወቅቱ ዘራፊውና ሌላው ቡድን እርስ በርሳቸው ተጣልተው በተኩስ ልውውጥ በመካከላቸው ተገዳድለዋል። በዚህ አጋጣሚ ወደፊት ለኢትዮጵያ ትልቁ ስጋት የትግራይ ወራሪ ሃይልና በየከተሞች የቦዘኔ መደብ የሚባሉት ናቸው። ንብረት የት እንደሚገኝ የሚጠቁማቸው አካል አለ።
እነርሱ ከአላማጣ፣ ከማይጨው ትራንስፖርት የሚሰሩ ሚኒባሶቻቸውን ይዘው መጡ እንጂ አንድም ተሽከርካሪ አልነበረም። ዕጥፍ እያስከፈሉ ይጭኑ ነበር። ከባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ጀምሮ የሚሰሩት የወራሪ ቡድኑ አባላት ነበሩ። ሲኖትራክና የሕዝብ ማመላለሻ በተለምዶ ታታ የሚባለው መኪና በእነርሱ እጅ ተይዟል።
የመንግሥት ንብረት ተበርብሯል፤ የመንግሥት መስሪያ ቤት ተሸከርካሪዎች ተዘርፈዋል። የግለሰብ ሃብት ተወስዷል፤ የቀረውም ወድሟል። ንጹሐን ተገድለዋል፣ በርካቶች ተደፍረዋል። በልዩ ተሽከርካሪዎች እየተዘዋወሩ የቆመ መኪና ያለበትን ቦታ በመጠየቅና አነፍንፈውም ያገኟቸውን ሞተር ሳይክልና የቆመ ተሽከርካሪ አንዳንዶቹን ጋቢናቸውን እየፈቱ በኤሌክትሪክ እያገናኙ እያስነሱ ይዘዋቸው ይሄዱ ነበር። በዚህ መንገድ አንድ እሁድ ቀን ጠጥተው በስካር መንፈስ ሲኖ ትራክ አስነስተው ሲጓዙ ሰው ገድለዋል። በነጻ የሚገኝ ስለሆነ የማሽከርከር ችሎታም የሌለው ከመሃላቸው የተሻለ የተባለው ይዞ ይሄዳል።
ወሩን ሙሉ በቦቴ መኪና እየጫኑ ነዳጁን አግዘዋል። የት ቦታ እንደሚያከማቹት እግዚአብሄር ይወቀው። ከሁሉም በላይ ከኮምቦልቻ ወጣ ብሎ ከሚጢቆ ብሄራዊ ዲፖ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ አግዘዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተሸከርካሪ ሎጎውን አጥፍተውት በርሱ ነበር የሚጭኑት።
ሕዝቡን የማሸበር ስራ ይሰሩ ነበር። ‹‹ወደ አራት ኪሎ የሚደረገው ጉዞ ይቀጥላል›› የሚል መፈክር አንግበው ነበር። የደሴ ሕዝብ ያሳለፈው አንገት ደፍቶ፣ ጸጥ ብሎ ነበር። የቦዘኔው መደብ አግዟቸዋል። በገቡ ማግስት ደሴ ከተማ ፒያሳ ላይ የሚውለበለበውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አወረዱት። ባንዲራ ተቀብለው በመቀየር ተባባሪ የነበረው፤ ሲወርድም የቀየረው ይሄው መደብ ነው።
ከመውጣታቸው ከሳምንት በፊት ጎረቤቴ የነበረ ትግረኛ ተናጋሪ ጋር የሚመጡ ሰዎች ነበሩ። ቋንቋውን የማልሰማ መስሎት በትግርኛ ቋንቋ ወንድሞቻችን በሙሉ አለቁ ይለው ነበር። ጠጋ ብዬ ጠየቅኩት ለመሆኑ የሚያጠቁት በምንድን ነው? አልኩት፤ ጦሩን እንኳን እናልፋለን ነገር ግን ድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላን) አላቸው አለኝ።
መኖሪያ ቤቴ ከፍታ ቦታ ላይ በመሆኑ ደጃፌ ላይ ተቀምጬ በእርዳታ ተሳቢ ተሽከርካሪ ከስር አስከሬን ከላይ ደግሞ ቁስለኛ ያመላልሱ ነበር። ከአንዱ ጠርዝ እስከሌላኛው ጠርዝ በአንደኛው ጠርዝ 10 በሌላው ጠርዝ ላይ 20 ጉልኮስ ተንጠልጥሎ ሰው ላይ ተሰክቶ ከአንዱ ወደሌላው እየተወዛወዙ ሲያልፉ ተመልክቻለሁ።
እኔ ቆስዬ ተመልክቻለሁ። ጉልኮስ ይዞ ወደ ሽንት ቤት ለመንቀሳቀስ እንኳን ያስቸግራል። በዚህ ትእይንት የጦርነት ሚዛኑ መቀየሩን ታዝቤ ነበር። ከሳምንት በፊት የቡድኑ አባላት ይረበሹ ነበር። ቁስለኛ በየት መስመር እንደሚጓዝ እንኳን ለይቻለሁ። ከባቲ መስመር የሚመጡት የደደሆ ቅጠል መኪና ላይ ጎዝጉዘው አይቻለሁ። የድድሆ ቅጠል የሚበቅለው ከባቲ በታች ነው። ቡርቃ፣ ካሳ ጊታና በረሃው ላይ ነው። በከሚሴ መስመር አልፎ የሚመጣው ደግሞ የባህር ዛፍ ቅጠል ሰክተው ሲመጡ አይቻለሁ። ከየት መስመር እንደሚመጡ የምለየው በዚህ ነበር። ጥቅምት 20 ገቡ ሕዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ወጡ። ደሴ የቆዩት 37 ቀናት ነው።
ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደፈለጉት ይንቀሳቀሱ ነበር። ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ከጦርነቱ በፊትም ትግራይ ተገንጥላ ራሷን ችላ ትኖራለች ይሉ ነበር። ትግራይ የታሪክ አገር ናት። ጥንታዊ አገር ናት የሚሉም አሉ።
ደሴ በወረራው ጊዜ ከደረሰባት ተጽእኖ በመነሳት እንዲህ በአጭር ጊዜ ወዘናዋ ይመለሳል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ወዟ ፈጥኖ ተመልሷል። የገበያው የዋጋ ሁኔታ የተወሰኑ ለውጦች አሳይቷል። ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገውን አጠንክሮ መስራት አሸባሪው ሕወሓት አንሰራርቶ ተመልሶ ስጋት እንዳይሆን ነው። ኑሮ ውድነት እንኳን ቢኖር አላማርርም። ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት ችለናል።
የኢትዮጵያን ታሪክ ከመሰረቱ አበላሽተዋል። መርጦ ለማርያም ሄጃለሁ። መርጦ ለማርያምንም አብርሃምና ኢዛና እንደመሰረቱት ይናገራሉ። የአክሱም ስርዓት ሲቋቋም ቋንቋው ትግርኛ ስለመሆኑ ማስረጃ የለም። የዛን ጊዜም ሰዎች ትግርኛ ተናጋሪ እንደሆኑ ያስባሉ። እኔ ግን የምወስደው ትግርኛ ከአማርኛና ከግእዝ ቋንቋ የመጣ የቅርብ ጊዜ ቋንቋ እንደሆነ ነው። ይህንን እንኳን የሚያስተምራቸው የለም። አክሱማውያን ነን፣ የአክሱም ሃውልትም የእኛ ነው ባዮች ናቸው።
በነገራችን ላይ በሕወሓት ዘመን የኢትዮጵያ ትንሳኤ መምጣቱን ያረጋገጥኩት ሻእቢያና ወያኔ ባድመ ላይ ሲጣሉ ነው። ወያኔን ሽኮኮ ብሎ ቤተ መንግሥት ያስገባው ሻዕቢያ ነው። ሽኮኮ ብሎ ያስወጣውም ሻዕቢያ ነው። እነዚህ ሰዎች እኛ የበላይ ነን የሚል አመለካከት አላቸው። ይሄ የተበላ እቁብ ነው። ይሄንን የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቀበለውም። ስቃያችን ሊበዛ ይችል ይሆናል እንጂ፤ ሕወሓት 360 ዲግሪ ቢሽከረከርም ኢትዮጵያን አያሸንፍም። ዓላማ የሌለው ሃይል በመሆኑ የሕወሓት መንገድ የቁልቁለት ጉዞ ነው። አዲስ አበባ ቢገባ እንኳን ጣርና እልቂቱ በዝቶ፤ ትግሉ ቢራዘምም ምንም ነገር አይሳካለትም ነበር። የሕወሓት ፖለቲካ እርባና ቢስ ነው።
አዲስ ዘመን:- የደሴ ሕዝብ ከወረራው ያገኘው ትምህርት ምን ይሆን ?
ሻምበል ዘለቀ:- ወረራው ለወሎ ሕዝብ ነጻነት ምን እንደሆነ አስተምሯል። ነጻነት አጥቶ፣ አንገት ደፍቶ መቀመጥ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ትምህርት አግኝቶበታል። ለእኔ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በወረራው ዘመን ሲራከስ ማየት የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ቀደም ሲልም ታዝቤያለሁ። የወሎ ሕዝብ ከዚህ በኋላ ነጻነቱን አያስደፍርም። ነጻነት አጥቶ መኖር ምን ማለት እንደሆነ ተምሯል።
አሁን ነጻነትንና ባንዲራን አፍቃሪ በዝቷል። ሕዝቡ የሽብር ቡድኑ አባላት ሰክረው በአደባባይ ሲንገላወዱ ተመልክቷል። ስርዓት የሌላቸው መሆናቸውንም ታዝቧል። ሕዝቡን አዋርደዋል፤ አስፈራርተዋል፤ ቀምተዋል፤ ገድለዋል፤ በእምነቱ እንዲያፍር አድርገዋል። ‹‹ጅቡ ሲወጣ አንበሳው ገባ…›› እያለ ሕዝቡ ከቤቱ ወጥቶ በጋለ ስሜት ለመከላከያ ሰራዊት አቀባበል ሲያደርግ ነበረ። የደሴ ሕብረተሰብን ለኢትዮጵያ ነጻነትና ባንዲራ ቀናኢ እንዲሆን አድርጓል።
ከተማውን ወደ ኋላ መልሰዋታል። የወጡት አፋራርሰው እና ዘርፈው ነው። በወረራው ጸጉሬ አድጎ ለመቆረጥ ስወጣ፤ ጸጉር ቤቶች በሙሉ ዝግ ነበሩ። በከተማው መብራት ተቋርጦ ምንም እንቅስቃሴ አልነበረም። በጀነሬተር የሚሰሩ ጸጉር ቤቶች ይቆርጡ የነበረው 200 ብር እያስከፈሉ ነበር። ይገርማል ይህንን ትቼ ከ50 ዓመታት በኋላ በ10 ብር ምላጭ ጸጉሬን ተላጭቻለሁ።
የሕወሃት የዘረፋ ቡድኑ አባላት ማታ ማታ በየቤቱ እየዞሩ ዘርፉ ይፈጽሙ ነበር። የሚነጋልንመጡ አልመጡ በሚል ሰቀቀን ነበር። የውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ ትንሽ ትልቁ ጀሪካን ተሸክሞ መመልከት የየዕለት ተግባር ነበር። ከኢትዮ ቴሌኮም የዘረፉትና አምስት ሺህ ብር የሚሸጠውን የስልክ ካርድ በአንድ መቶ ብር ሲሸጡ ተመልክቻለሁ። ነገር ግን ጥቅም ላይ ሳይውል ታግዶባቸዋል።
ዝርፊያ የሕወሓት ባህል የሆነ ይመስላል። ጠጋ ብለን ስናዋራቸው። ገበሬውን፣ ሚሊሻውን ጠርተው ሲያዘምቱን ‹‹ንብረታችንን እንዳይዘረፍ እንዴት እናድርግ?›› ብለን ጠይቀናል። ቦዘኔውን በሙሉ አፍሰን ወደ ውጊያ እናስገባላችኋላን ብለው ቃል በመግባት አሰልፈዋቸዋል። የከተማውን ሌባ አፍሰው አሰልጥነው ዘርፈህ ብላ፣ ያገኘኸውን ውሰድ ብለው አሰማርተዋል።
እንደውም የሚነገረው አብዛኞቹ ሃይቅ ግንባር ላይ ሞተዋል። የሕወሓት ቡድን አባላት ሌብነት እና ክህደት ያለባቸው ሰዎች ናቸው። የግል ንብረት አንነካም ይላሉ፤ ግን የግል ንግድ ድርጅቶችን ሰብረዋል። የወጥ ቤት ዕቃ፣ የፈርኒቸር መሸጫ ሱቅ በተሽከርካሪ ጭነዋል።
የወሎ ሕዝብ ንብረቱን የሚያጣው፣ ልጁና ባለቤቱ የሚደፈርበት፣ ቤቱ የሚዘረፈው በምን አበሳው ነው? ያኔ አመራሩ ሲፍረከረክ ሕዝቡ የሚያንቀሳቅሰው አጣ እንጂ ለመዋጋት ፍላጎት ነበረው። አሁንም ሕዝቡ በራሱ ግዜ መንቀሳቀስ አለበት። መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን:- የሕወሓት ሽብር ቡድን የደሴ የመጨረሻ ሰሞን ሁኔታቸውስ ምን ይመስላል?
ሻምበል ዘለቀ:- አርብ ዕለት ከሕዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም አንስተው የመሸሽ እንቅስቃሴ ይታይባቸው ነበር። በመጣደፍ የዘረፉትን ንብረት በተሽከርካሪ እየጫኑ ይሸሹ ነበር። ከቅዳሜ ሌሊት እስከ እሁድ ዕለት በተሳቢ ተሽከርካሪ ጦር ተጭኖ በማንቀሳቀስ ሽሽት ላይ ነበሩ። እሁድ ሕዳር 26 ቀን እግረኛ ማለፍ ጀመረ። ለማስመሰል ደግሞ በርካታ ተሽከርካሪዎች ባዷቸውን እያለፉ እንዲሄዱ ያደርጉ ነበር። ጦርነቱ ቀጥሏል ሽሽት አይደለም በማለት ሕዝቡን ለማወናበድ ይመስላል።
ከኮምቦልቻ ወደ ደሴ መግቢያ ሁለት በር አለ። በአንደኛው መገንጠያ በመንበረ ጸሃይ መግቢያ ሲሆን፤ ሌላው መግቢያ ደግሞ በሸዋ በር ነው። ተሸከርካሪዎቹ ርቀው አይሄዱም፤ በአንደኛው መገንጠያ አስወጥተው በሁለተኛው መግቢያ ይመልሷቸዋል። ሕዝቡ ወደ ታች ወረዱ እንዲል ነበር። የሽብር ቡድኑ ጦር ከኮምቦልቻ ያለማቋረጥ ያልፋል። በርካታ ተሽከርካሪዎች ባዷቸውን ያልፋሉ። ተሽከርካሪዎቹ ባብዛኛው አይጭኗቸውም። የሚጓዙት በእግራቸው ነው ። ነገር ግን ክፍት በሆኑ ተሽከርካሪዎች አንዳንዶች እየተንጠላጠሉ የሚወጡም ነበሩ። በእግር የሚጓዙት ድሮን ፍራቻ መሆኑ የገባን ቆይቶ ነው። የመጨረሻ አዳራቸው በነበረው ዕሁድ ለሰኞ አጥቢያ ያልዘረፏቸውን መፈንቀልና መዝረፍ ቀጥለዋል።
ሰኞ ጠዋት ከዘረፏቸው መካከል አነስተኛ ጀኔሬተሮችን በትከሻቸው ለሁለት ለሁለት ተሸክመው የትርሃስን ኮበሌ… የሚለውን ሙዚቃ እያዘፈኑ ወደ አገራቸው ይገሰግሱ ነበር። ሰኞ ቀን ሰባት ሰዓት ላይ ደሴ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ለቀቁ። ወዲያው ሰንደቅ ዓላማው ደሴ ከተማ ላይ የእነርሱ ወርዶ የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር መውለብለብ ጀመረ።
አዲስ ዘመን:- ወሎ ገራገሩ የሚለው አገላለጽ የአካባቢው ሕዝብ ምን አይነት ባህሪ እንዳለው ነው የሚያሳየው ?
ሻምበል ዘለቀ:- በየሄድንበት ቦታ ሁሉ የወሎ ተወላጅ ነን ስንል ወሎ ገብሱ ወሎ ገራገሩ ይለናል። ሙስሊምና ክርስቲያኑ እርስ በእርስ በመግባባትና በመከባበር የሚኖርበት ነው። በጥምቀት በዓልም የጊዮርጊስ ታቦት ሲገባ የሙስሊም ፈረሰኛ የሚታየው ጥምጣም ጠምጥሞ ነው። ወየአካባቢው ሰው ደግ ነው። ብሉ፣ ጠጡ የሚያውቅ፣ አቀባበሉና መስተንግዶ ፍቅር ነው።
በሕወሓት ዘመንም የተበደለ አካባቢ ነው። ወሎ መሃል በመሆኑ የተለዩበት አውራጃዎች አሉ። ኦሮምኛም ቢናገሩ ድባቡን ይዘው የኖሩት የሚቀራረቡት ከሚሴና ባቲ የኦሮሚያ ክልል ናቸው በማለት በአካባቢው ሰው አይተዳደሩም። የሰቆጣው ኒምራ የሚባለውን ደግሞ ልዩ ዞን ብለውታል። ራያና ቆቦ፤ ራያና አዘቦ የሚባሉ አሉ። ራያና ቆቦ ማለት ሳውቀው ዋና ከተማው አላማጣ ነው። ድንበሩ አሸንጌን አለፍ ብሎ ኮረምን ወርዶ ጉምቡርዳ ነው። አንድ አውራጃ ራያ ተወስዶበታል።
የቆቦ ሕዝብ በ1984 ዓ.ም አመጽ አንስቶ እምቢ ብሎ እንጂ አለውሃ ምላሽ ተብሎ ነበር። አብዛኞቹ የአካባቢ ስያሜዎችም ኦሮምኛ ናቸው። መካነ ሰላም ላይ የምትገኝ ለገማራ ወንዝ አለች። የአማራ ወንዝ ማለት ነው። ለጋ ሌንጫ፣ ለጋ ዳባ የሚባሉ ወንዞች ይገኙበታል። ለጋ ማለት በኦሮምኛ ወንዝ ማለት ነው። ደሴ፣ ጢጣ፣ ኡርጌሳ፣ መርሳ አማርኛ ስያሜዎች አይደሉም፤ ትርጉም አላቸው። ሕዝቡን መለያየት አይቻልም።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያዊነት ለእርስዎ ምንድን ነው?
ሻምበል ዘለቀ:- እኔ የእዚህ ብሔረሰብ አካል ነኝ ለማለት አልችልም። ኢትዮጵያዊ እንጂ። ኢትዮጵያዊነት አራት ጊዜ ደሜን ያፈሰስኩበት ነው። ኢትዮጵያዊነት ምን ጊዜም የማልፍቀው ነው። በዘሮች፣ በትውድ ደማቸውን ያፈሰሱ ዜጎች ዋጋ የከፈሉበት ነው። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት አሁንም ዘብ እቆማለሁ። እኔ ለባድመ አልዘምትም እንዳልኩት የአድዋ ዘመቻን ለአድዋ ተራሮች የተዘመተ አድርጌ አልመለከትም። ለመላው ኢትዮጵያ ወሰን ተብሎ ስለሆነ። ኢትዮጵያዊነት ሲካድ በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ነጻነትና ዳር ድንበርን ለማስከበር ደማቸውን ያፈሰሱ ቅን ሰዎች እንደተካዱ አስባለሁ። ምን ጊዜም በኢትዮጵያዊነት ላይ አልደራደርም።
አዲስ ዘመን:- በ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” እና አጠቃላይ በነበረው ሂደት ዙሪያ ምን አስተያየት አልዎት?
ሻምበል ዘለቀ:- የተገኘው ድል በአግባቡ መያዝ አለበት። የትግራይ ወራሪ ሃይል ትጥቅ እንዲፈታ መደረግ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ሕዝቡን ማስተባበር ይጠበቅበታል። ፍተሻ መካሄድ አለበት። ከደርግ መውደቅ ዋዜማ አንስቶ በርካታ የጦር መሳሪያ በአካባቢው ሊኖር ይችላል የሚል ግምት አለኝ። በአካባቢው በብዛት የደርግ ሰራዊት ሳንጃና ኮዳ ሳይቀር ሊገኝ ይችላል። እነዚህን የጦር ትጥቆች በሙሉ መረከብ ያስፈልጋል።
ድሮም ቢሆን ሚዲያቸውን እከታተል ነበር። መቼም የሚታመን ዜና ሲያቀርቡ አላጋጠመኝም። በቅስቀሳቸው የሚያሳፍሩ ቃላቶችን ይጠቀሙ ነበር። ላለፉት 30 ዓመታት ያደረጉት ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ሕዝብን የሚያሳውሩ የቅስቀሳ መንገዶችን መጠቀም ላይ እንደነበር ያስታውቃል። ከዜና ዘገባዎቻቸው እስከ ሙዚቃዎቻቸው ድረስ ጭፍን ጥላቻን የሚሰብክ፣ አውሬ ባህሪ የሚያላብስ ሥራ ሠርተዋል። ሕወሓቶች የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሱስ የሆነባቸው ናቸው።
አሁን ደግሞ እኔ እንደወታደር መከላከያ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን አልደግፍም። የትግራይ ሕዝብ አሁን ባለበት ሁኔታ እንደ ወሎ ሕዝብ መከላከያ ሲገባ እየጨፈረ አይቀበልም። እኛ ሕወሃት ሲገባ በር ዘግተን ፊታችንን እንዳዞርን ሁሉ ያ እንዳይገጥም ማሰብ ያስፈልጋል። ይሄ ለሰራዊቱ ጥሩ አይደለም። ወታደራዊ ባለሙያዎችና የጦር መሪዎች የሚመሩት ቢሆንም፤ መከላከያ ሰራዊት አንድ ቦታ ምሽግ ቆፍሮ፣ ፈንጂ አጥሮ መቀመጥና እነሱ ሲንቀሳቀሱ በተመረጠ ምሽግ ላይ መዋጋት ይቻላል።
መከላከያ ሰራዊት በጥሩ አቋም ላይ መሆኑን ተመልክተናል። የሰራዊት ብቃት ላይ የበለጠ መሰራት አለበት። የቀድሞውን ጦር ከአየር ሃይልም ሆነ ከባህር ሃይል እርሾ አድርገው መጠቀም፣ የፖለቲካ ሥራም ሊሠራ ይገባል። የቅስቀሳው ሥራም በተሻለ መንገድ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- የሽብር ቡድኑ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ሻምበል ዘለቀ:- ተወናብዶና በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የተንቀሳቀሰው ማዕበል ወደ አራት ኪሎ በሃይል የሚደረግ ግስጋሴ ውድቀት እንዳለው ተመልክቷል። በመሪዎቹ መታለሉንም ተገንዝቧል። ምናልባት የጥይት አፈሙዙን ወደ አመራሩ ሊያዞር ይችላል። አልያም ሕዝቡ ግፍ ሲበዛበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊጀምርም ይችል ይሆናል። ወደ ከተማው የተመለሰው ሌባ መቀሌና የአካባቢው ከተሞች ሊያስተናግዱት ስለማይችሉ ቀውስ ይፈጠራል። መቀሌ ወደ መሃል አገር የገባውን ጦር አትቀልብም። የዘረፉትም ያልቃል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ መቀሌ ላይ ለውጥ እናያለን ብዬ አስባለሁ። እጅ ከመስጠት፣ እርስ በእርስ ከመወጋገዝ ወይንም ለመንግሥትና ለሕዝብ የሚወግን፤ እነርሱን ግዳጅ ጥሎ ታሪክ የሚሰራ ሊኖርም ይችላል።
ምናልባትም መሪዎቹ በዚህ የተነሳ ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ያጠፋሉ፣ በርግጠኝነት በጀመሩት አካሄድ ግን አይቀጥሉም። በሰራዊታቸውም ሊመቱ ይችላሉ። ሾልከውም ሊወጡ ይችላሉ ብዬም እሰጋለሁ። መንግሥትም በጀመረው “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” አሸንፎ የሽብር ቡድን አባላትን አድኖ ለሕግ ሊያቀርባቸው ይችል ይሆናል።
የሽብር ቡድኑ አመራሮች በለመዱት የማወናበድ ዘዴ አዲስ አበባ እንገባለን በማለት እንጂ፤ አዲስ አበባን መቆጣጠር እንደማይቻል፣ ያን ያህልም ቅርብ እንዳልሆነ አጥተውት አይደለም። ዘመናዊ ውጊያ ገጥመው ሰራዊቱን ለመገዳደር እንዳልቻሉት ተረድተዋል። ይሄንን የሚሞክሩት አይመስለኝም። ነገር ግን አሁንም ማዕበል በማንቀሳቀስ ሌላ ሙከራ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ሻምበል ዘለቀ:- እኔም ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዘላለም ግዛው