ከዚህ በቀደመው መጣጥፌ ዴስቲኒ ኢትዮጵያዎች ወይም ” ቲም ንጉሡ ” የተገለጠላቸው ራእይ በ50ዎቹ ደቀ መዛሙርት ተተርጉሞ” ብሩህ ተስፋ ከፊታችን ነው ! እርሱን ዕውን ለማድረግ እንነሳ! “በሚል ርዕስ ከወካይ ዜጎች ለመላው ኢትዮጵያውያን ከቀረቡ ራዕዮች አራቱን ያቀረብሁ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ቀሪዎችንና የመጣጥፌን መቋጫ እንዲህ አቅርቤያለሁ ፡፡
5 . ለዚህ ራእያችን መሳካት ሁላችንም ተግተን መፈጸም ያሉብን ዓበይት ጉዳዮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው ፡- 5.1. በየጊዜው እያየነው ያለነው አላስፈላጊ ግጭትና እርሱን ተከትሎ የሚከሰተው እልቂትና የሀብት ውድመት ተመልሶ እንዳይመጣ ፣ በሃሳብ አለመግባባቱም ፈጥኖ ወደ ጥቃትና ግጭት እንዳያመራ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ለዚህም እንደፖለቲካ መሪነታችን ወይም ኃላፊነት እንደሚሰማው ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሃሳቦች ወደ ሕዝብ ከመውረዳቸው በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት እልባት እንዲያገኙ ሁላችንም አጥብቀን እንድንሰራ እንጠይቃለን፡፡
5.2. በሀገራችን ሲንከባለሉ የቆዩ አወዛጋቢ ጉዳዮች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በህዝብ ተመርጦ የሚመጣ መንግሥት እንዲፈታቸው የሚጠበቁ ቢሆኑም አንዳንድ ጉዳዮች ግን ጊዜ የማይሰጣቸውና በቅድሚያ መከወን የሚገባቸው ናቸው ። ለምሳሌ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ፤ የወጣቶች ሥራ አጥነት እንዲቀንስ ጥረት ማድረግ ፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ሊጠቀሱ ይችላሉ ።
እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት እነዚህና መሰል አጣዳፊና ፈታኝ ጉዳዮች የግጭት መንስኤዎች እንዳይሆኑና በነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች እንዲካሄዱ እንመክራለን።
5.3. እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ለሀገራዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ሲባል በጊዜ ሂደት የሚፈቱና ከምርጫ በኋላ ሊሻገሩ የሚችሉትን ማናቸውንም ጉዳዮች ግለሰቦች ፣ ቡድኖችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርቡ እንመክራለን ። እኛም ብንሆን እነዚህን ጉዳዮች በምንም አይነት አመክንዮ ቢሆን ለግጭት መጫሪያነትና መቀስቀሻነት ላለመጠቀም ተስማምተናል።
5.4. እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ሀገራዊ ውሳኔ የሚያሻቸው ማናቸውም ጉዳዮች ሁሉም በአንድ ጊዜ ሊተገበሩ እንደማይችሉና በሂደት እንደሚፈቱ አውቀን ሁላችንም ለጉዳዮቹ የመፍትሔ አካል በመሆን ጉዳዮቹ ቅደም ተከተል በሚይዙበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ጥሪ እናቀርባለን ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባለፉት ዘመናት በሀገራችን ታሪክ ላይ የሚታየውን አለመግባባት ጊዜ ወስዶ ለማየትና ከሁሉም የአተያይ ጎራዎች የተወጣጡ ምሑራንን በማሳተፍ እስክንግባባ ድረስ ለግጭት በማይዳርግና የቆየውን ህብረ ብሄራዊ ትስስራችንን በማያላላ መንገድ እንድንጠቀምበት እናሳስባለን።
6 . እኛ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት በዚህ የሴናሪዮ ቀረፃ ሂደት እንደተረዳነው ከሆነ የተለያየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸው ወገኖች የውይይት መድረክ ቢያገኙ ወዳጅነትን መፍጠርና ወንድማማችነትን ማጎልበት እንደሚቻል ፣ በሰከነ መንፈስ በመወያየት ከባድና አይነኬ የሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ሊዳሰሱ እንደሚችሉና ከዚህ መሠል ሂደት መግባባት ፣ መተማመንና መፍትሔ ሊመጣ እንደሚችል ተምረናል።
ስለሆነም የፖለቲካ መሪዎች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች ዜጎች ከመደበኛ መድረኮች ባሻገር በሌሎች መንገዶች እየተገናኙ ቢወያዩና የጋራ መፍትሔዎችን ቢያፈላልጉ የተራራቁ አቋሞቻቸውን ለማቀራረብና ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል እንደሚያግዛቸው ከልባችን የምናምን መሆኑን ከወዲሁ እየገለጽን በሀገራችን የጋራ ጉዳዮች ላይ በመደበኛና ሌሎች መንገዶች ውይይቶች እንዲስፋፉ ጥሪ እናስተላልፋለን ፡፡
7 . እነሆ እኛ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ የሴናሪዮ ቡድን አባላት አሁን የፈጠርነውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት እንደ መልካም ስንቅ በመውሰድና ደግሞም ለሀገራችን መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ በማመን የእርስበርስ ግንኙነታችንን ይበልጥ አጠናክረን ለመቀጠል የወሰንን መሆናችንን እየገለጽን አንዲት ውድ ሀገራችንን ለማዳንና ወደ’ንጋት’ እንድንደርስ በፍጹምመሰጠት እንደምናግዝ ቃል እንገባለን። …” የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ዘጠኝ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ፎረም ፎር ፌደሬሽን ለበርካታ አመታት በመመካከር እና የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር ሀገራችንን ከገባችበት ቅርቃራ ያወጣል ያሉትን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እና ኢትዮጵያን ይወክላሉ ተብሎ የታመነባቸውን 50 የሴናሪዎ / የዕድል ፈንታ / ቡድን አባላት ለስድስት ወራት በተከታታይ ሶስት ዙሮች ተገናኝተው በኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ላይ በዝግ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን ሲመክሩ ቆይተዋል።
በውይይቶቹ መጨረሻ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊገጥሟት የሚችሉትን አራት ሴናሪዮዎች ለይተው አመላክተዋል። እነዚህ አራት ሴናሪዮዎች የተዘጋጁት አገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በመተንተን፣ የባለሙያ ምክር በማድመጥና አስፈላጊ ነጥቦችን ለውይይት ማዳበሪያነት በመውሰድ ነው።
የሴናሪዎች ቡድን አባላት እነዚህን እድል ፈንታዎችን / ሴናሪዎችን / መለየት የቻሉት በብዙ ምክክር ፣ ሙግት እና ማንሰላሰል መሆኑን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ወደፊት የምትደርስበትን ሁኔታ የሚወስኑ የተለያዩ መንገዶች አሉ። የሴናርዮ ቡድኑ ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ መጪውን ዘመን በሚገባ ያመላክታሉ ብሎ ያመነባቸውን አራት ሴናሪዮዎች ቀርጿል።
ስለወደፊት በእርግጠኝነት መተንበይ ባይቻልም ስለተወሰኑ ጉዳዮችን ግን አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ፣ ከተሞች እንደሚስፋፉ ፣ የወጣቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድና ይህም ብዙ የሥራ ዕድል ፍላጎት ጥያቄን እንደሚያስነሳ ፣ እንዲሁም የፌደራሊዝም ሥርዓት የተወሰኑ ይዘቶች ወደፊት እንደሚቀጥሉ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በመነሳት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።
በሌላ በኩል አሁን እርግጠኛ መሆን የማይቻልባቸው ጉዳዮች አሉ። የዴሞክራሲ ባህርይ ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ፣ የኢኮኖሚ ዕድገታችን እና ሁሉን አቃፊነቱ ፣ የግጭትና ብጥብጥ አዝማሚያ ፣ ለአካባቢ መጎሳቆል የምንሰጠው ምላሽ ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻላችን ፣ ዓለምአቀፋዊና ከአገር ውጭ የሚፈጠሩ ክስተቶች በአገር ላይ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ፣ እንደ አገር የመቀጠላችን ነገር እና መሰል ጉዳዮች ናቸው።
የቀረቡት አራት የወደፊት ሴናሪዮዎች እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን ከምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች እንደምንሰጣቸው ምላሾች የተለያዩ አራት መዳረሻዎችን ያመላክቱናል ።
እነዚህ መዳረሻዎች በ2032 ዓ.ም ሊከሰት የሚችሉ ሴናሪዮኖች ናቸው ።እነሱም ፦ 1.ሰባራ ወንበር
2. አፄ በጉልበቱ
3.የፉክክር ቤት እና 4.ንጋት ናቸው ፡፡
- ሰባራ ወንበር
የመጀመሪያው ሴናሪዮ ሠባራ ወንበር ሲሆን ለችግሮቻችን የምንሰጠው ምላሽ ጥንቃቄ የተሞላበት እና አሁን ባሉብን የአቅም ውስንነቶች ልክ የተገደበ መሆኑን ያሳያል ። የሰባራ ወንበር ሴናርዮ ጠንካራ በሚመስል ፣ ነገር ግና ገና ሲነኩት እንደሚሽመደመድ ፣ ቀላል ክብደትን እንኳን የማይሸከም ወንበር የተመሰለ ነው ፡፡
2. አፄ በጉልበቱ
አጼ በጉልበቱ የሚባለው ሁለተኛው ሴናሪዮ ግዙፍ የሆኑት የአገራችን ችግሮች ቆራጥ አመራር ያስፈልጋቸዋል ከሚል እሳቤ በመነሳት ለችግሮቻችን ፈላጭ ቆራጭ የሆነ እና በጥብቅ ቁጥጥር የተሞላ ምላሽ የሚሰጥ ነው ።
በዚህ የማንአለብኝነት ሴናሪዮ የችግሮቻችን ምላሽ ብለን ያመንነው ፈላጭ ቆራጭ የሆነ እና ጥብቅ ቁጥጥርን ያማከለ ሥርዓት ነው ።
3 የፉክክር ቤት፦
ሶስተኛው አማራጭ ሴናሪዮ የፉክክር ቤት የሚባለው ነው ። የተለያዩ ቡድኖች በነጻነትእና ባልተማከለ መልኩ የመሰሏቸውን ምላሾች በተናጠል በመሰንዘራቸው ሳቢያ የሚፈጠረውን የተሸራረፈና የቡድን ፉክክር የሞላበትን ምላሽ መልክ የሚያሳይ ነው።ይህ ሴናሪዮ ልክ አበው እማው የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚሉት የተለያዩ ቡድኖች እና ክልሎች ያገኙትን አዲስ ነጻነት እነርሱ እንደፈለጉትና እንደመሰላቸው መጠቀማቸውን የሚያሳይ ሲሆን ከመንግሥት አንስቶ እስከ ቤተሰብ ደረጃ በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚመጡ ክፍተቶችንና ክፍፍሎችን የሚያሳይ ነው።
4 . ንጋት
ንጋት አራተኛው ሴናሪዮ ሲሆን ቀስ በቀስ በሚደረግ የተቋማት ግንባታ ልንደርስበት የምንችለውን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያሳይ ነው ።የንጋት ሴናሪዮ የኢትዮጵያ እድገት ደረጃ በደረጃ ዕውን የሚሆንበትን ተስፋ ያዘለ ነው።
የሙሉ ቀን ብርሃን አልሆነም ። ነገር ግን የአዲሱ ቀን ወገግታ ጀምሯል ። ኢትዮጵያውያን ሕጋዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እና የዕርቅ ሂደቶችን አጠናክረው በመተግበር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እያስቀጠሉ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሥር የሰደዱ ማሕበረሰባዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እልባት ማግኘት ጀምረዋል ። ከቅራኔ እና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታና እርቅ አስተሳሰቦች በማሕበረሰቡ ዘንድ እንዲሁም በመደበኛ እና ማሕበራዊ መገናኛዎች በየዕለቱ ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቶአል ።
የዲሞክራሲ ተቋማትና ኢኮኖሚው ደረጃ በደረጃ እየተገነቡ ፣ በጋራ ርእይ ላይ የተመሠረተ አንድነት በመፍጠር ላይ ይገኛል። እንደ ማጠቃለያ “…የኢትዮጵያ ሰላም እና ብልፅግና በምትሀት በአስማት እውን ሊሆን ስለማይችል ዝም ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንጠብቀውም። የምንገነባው እና ሰርተን የምናገኘው ነው። ተሸንፈን የምናሸንፍበት ነው።
አሸንፈን የምንሸነፍበት ነው ።ሰጥተን የምንቀበልበት ፣ ተቀብለን የምንሰጥበት ነው ።የምንተባበርበት ነው። ልክ እንደ ጋብቻ የሚቆጠር ነው ።ጋብቻ ውስጥ አሸናፊ ተሸናፊ የሚባል ነገር የለም ።
ሁለቱም አሸናፊ ናቸው ።ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም እንደ ጋብቻ አይነት ግንኙነት ላይ ነው ያለነው ።ሰዎች የተሻለ የተባለ ሲናሪዮዎን ላይ ለመድረስ የትኛው መንገድ ነው የሚያስከደኝ የሚል ጠቢብ የሆነ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል፡፡
” የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ሀሳብ አመንጪ እና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ከፍ ብለው እንዳስገነዘቡት ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት መስቀለኛ መንገድ ወደ ብሩህ ተስፋ የማሸጋገር ጉዳይ ቁጭ ብሎ እጅን አጣጥፎ በመጠበቅ ወይም በፍላጎት ብቻ ሊሳካ አይችልም።
ስለሆነም የሁሉንም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል። ይህ ተሳትፎ ግን በግዕብታዊነት እና በአቦሰጥ ዘው ተብሎ የሚገባበት አይደለም ።
በሰከነ አእምሮ በጥሞና የተተለመውን መንገድ መከተል እንጂ። ይህን መንገድ 50ዎቹ የዴስቲኒ ቡድን አባላት ለስድስት ወራት የሀገራችንን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ እና መጻኢ እድል ወይም አደጋ በጥልቅ ተጠየቃዊ እና አመክኖአዊ በሆነ አግባብ ተንትነው ከላይ የተዘረዘሩትን እድል ፈንታዎች ተንትነው አስቀምጠዋል ።” የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓም ” ከላይ በተዘረዘሩት እድል ፈንታዎች / ቢሆኖች / ሊሆን ይችላሎች/ scenarios በአንዱ ይወሰናል ።
በሰባራ ወንበር ወይም በአፄ በጉልበቱ አልያም በፉክክር ቤት ወይም በንጋት። የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ቢሆኖች ሀገራችንን ከገባችበት የቀውስ አዙሪት ፣ የግጭት አረንቋ ፣ ልዩነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት ፣ ኢፍትሐዊነት ፣ ኋላቀርነት ፣ ወዘተ . ሊታደጓት የሕዝቧንም ተስፋ ሊያለመልሙት አይችሉም ።ሶስቱም ሴናሪዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በንጉሳዊው ፣ በወታደራዊው ወይም በኢህአዴግ ተገልጠው ዛሬ ለደረስንበት ውስብስብ ችግር የዳረጉን ናቸው ።
ዛሬ ላይ ከሶስቱ አንዱን አልያም ሶስቱን ሴናሪዎች በአንድነት ብንመርጥ ወዳለፍናቸው አገዛዞች እና መከራዎች የሚመልሱ ናቸው። በአንጻሩ 50ዎቹ የዴስቲኒ አባላት በአንድ ድምፅ ሀገርን እና ሕዝብን በማስቀደም የመረጡትን እድል ፈንታ ” ንጋትን ” ብንመርጥ መፃኢው ዘመን እንደ ጎህ የሚቀድ እንደ ንጋት ወገግ እያለ የሚሄድ ይሆናል።
ዴሞክራሲያዊ ፣ ፍትሐዊ ፣ እኩልአዊ ፣ ሀገር መመስረት እንችላለን ።ከልዩነት ይልቅ በሚያጋምዱን በረከቶች ላይ የሚያተኩር ዜጋ ለማነፅ እና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት ያስችላል። በአጠቃላይ በ2032 ዓ.ም የተሳካ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ይሆናል።ይነጋል።
ይሄን ተስፋ ሰንቀን ነው ሀገራዊ ምክክሩን የምንቀበለው ። ዴስቲኒ ኢትዮጵያም ሆነ ማይንድ ኢትዮጵያ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ ይጫወታሉ ተብሎ የሚጠበቀው ይሄን እርሾና ወረት ታሳቢ በማድረግ ነው።
ለሀገራዊ ምክክሩም መደላድል በመሆን ያገለግላል። ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !!! አሜን ፡፡
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 28/2014