35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመቼውም በበለጠ ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት እንደሆነ ቅድመ ዝግጅቶቹ ይናገራሉ። እስካሁን ባለው ሂደትም ከመሪዎች ስብሰባ በፊት የሚካሄዱ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተከናወኑ የመቀጠላቸው ምስጢርም ይኸው የዝግጅቱ ጥንካሬ ማሳያ ነው። ምክንያቱም ይህ ጉባኤ ወሳኝ ነገሮች የሚፈጠሩበትና የሚተላለፉበት ነው።
እስከዛሬም ይህ ነገር የሚከናወን ቢሆንም የዘንድሮውን የሚለየው ግን ብዙ ነገር አለ። ከእነዚህም መካከል ኮቪድ 19 አንዱ ሲሆን፤ ስብሰባው በአካል እንዳይከናወን አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ሌላው ኢትዮጵያን ብሎም ፓን አፍሪካኒዝምን ለማዳከም የውጭ ጠላቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየሠሩ ባሉበት እና ዜጎቻቸውን ከአዲስ አበባ ውጡ በሚሉበት ወቅት መካሄዱ ታሪካዊ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ያላት የመሪነት ሚና በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን፤ ቀደምት የአፍሪካ ስልጣኔ ሲነሳም የኢትዮጵያ ስም አብሮ ይነሳል። የአፍሪካውያን የነፃነት ታሪክም እንዲሁ ሲወሳ የእርሷን ስም አለመጥራት አይታሰብም።
ምክንያቱም እርሷ የጥቁሮች የድል ተምሳሌት ናት። በቀጣይም አፍሪካውያን ከምዕራባውያን ጭቆና ለመላቀቅ ለሚያደርጉት ትግል መሠረት እንደምትሆንም እሙን ነው። ለዚህ ደግሞ አሁን ያሰናዳችው ጉባኤ አንዱ ምሰሶ ይሆናል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግንቦት 1955 ዓ.ም ሲመሠረት ራዕዩ የተባበረች፣ ነፃና በራሷ የምትመራ አፍሪካን እውን ማድረግ ነበር።
ይሁን እንጂ ሙሉ ራዕዩን ያሳካ ነው ለማለት አያስደፍርም። ዛሬም በእጅ አዙር ለመግዛት በርካታ ምዕራባውያን በተለያየ መንገድ እየሠሩበት ነውና። አፍሪካ ያለችበትን ኋላ ቀር የኢኮኖሚ ደረጃ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በእርዳታ ስም የሚያደርጉት ጣልቃገብነት ከፍ ያለ ነው።
ከዚህም አልፎ አሜሪካን ጨምሮ የተወሰኑ ምዕራባውያን በዴሞክራሲ ስም በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እጅ ለመጠምዘዝና የተፈጥሮ ሀብትን ለመመዝበር ዛሬም እንቅልፍ ሳይተኙ ያድራሉ። ይሁን እንጂ ይህንን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የነፃነት ተምሳሌት የሆኑ አገራት ላይ ማሳየት አልቻሉም። ጥቁሮች ኃያል እንደሆኑ ለማሳየት ኢትዮጵያ ዛሬም ተምሳሌትነቷን እያሳየችም ትገኛለች።
በፈተና ውስጥ ብትሆንም እንደ አህጉር ተወያይተው የጋራ ጉዳያቸውን በአንድነት እንዲሠሩ ለማድረግም ብዙ ሴራ ተሸርቦባት ሳለ ጉባኤውን ለማካሄድ አሳምና ቀን ቆርጣ ተግባሮቿን እየከወነች ነው። ነገር ግን ቀደም ብለው በኢትዮጵያ ሰላም የሌለ በማስመሰል በአንድ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ዜጎች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ዜጎች ወደኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ይሰብኩ ነበር። የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤም በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ብዙ ጥረዋል። ሆኖም በአሰቡት ልክ አልሆነላቸውም።
ቢሆንም አሁንም እንደማይተኙ ማወቅ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ማንነቷን ለማሳየት በ‹‹በቃ (#NoMore)›› እንቅስቃሴ ብቻ ብዙ ለውጦችን አምጥታለች። የገናና የጥምቀት በዓላትን በኢትዮጵያ እንዲያከብሩ ለአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አባላት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በዓላቱን ያለምንም ችግር አክብረውም ሁሉም ውሸቱን እንዲያጋልጥ አድርጋለች።
ከሁሉም በላይ በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች ከሚሳተፉባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች አንዱ ታላቁ ሩጫን አካሂዳ መላው ዓለም ኢትዮጵያ ሰላም እንደሆነች እንዲያውቅና እንዲናገሩላት ማድረግ ችላለች። ይህ ደግሞ ከጎኗ የሚሰለፈውን ሕዝብ አብዝቷል። አፍሪካዊ ብቻ ሳይሆን የሚቃረናት ሁሉ ከጎኗ እንዲቆም ያደረገችበት ነው። ዛሬም ጓዛቸውን ጠቅልለው የመምጣታቸው ምስጢር ይኸው ነው። የኅብረቱ ጉባኤ ለአፍሪካውያን ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይታወቃል።
መመካከሩ የቀጣይ ህልውና ጉዳይ ነው። የአህጉራዊ ብልጽግና መሠረትም ነው። ስለዚህም ይህንን ወሳኝ ምዕራፍ ለማስጀመር በአንድነት እንዲሰባሰቡ ሆነዋል። ይህ ደግሞ በተለይ ለኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም ያለው ነው። በመጀመሪያ ክብርና ልዕልናዋን የምታስከብርበት፣ የፖለቲካ ነፃነትና ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጥበትና በኢኮኖሚው ዘርፍ ራሷን የምታሳድግበት ነው።
ለሌሎች አፍሪካውያንም እንዲሁ። አፍሪካውያን ከምዕራባውያን ተጽዕኖ ነፃ መውጣት የሚችሉት ራስን ለመቻል በአንድነት ሲሠሩ ብቻ ነው። ስለሆነም እንዲህ ዓይነት ጉባኤዎችን ተጠቅመው እንደ አንድ አህጉር ሆነው ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ የሆነውን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማስከበር አለባቸው። አፍሪካውያን ዛሬም ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነፃ ያልወጡት ይህንን ባለማድረጋቸው እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። መሪዎቻቸውን የሚመርጡላቸው ምዕራባውያን መሆን የለባቸውም።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎችን መደገፍ አለባቸው። ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ጥቅም መከበር የሚሠሩ መሪዎችን ምዕራባውያን በመፈንቅለ መንግሥት እንዳስወገዷቸው ወይም በማዕቀብ አሳስረው እንዳስቸገሯቸው ታሪክ መዝግቦታል። ይህን ስልታቸውን በኢትዮጵያ ላይ ሞክረውታል። እናም አፍሪካውያን አሁን ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆሙ ሁሉ ሌሎች አፍሪካውያን አገራትም እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ ሲገቡ መከታ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የዚያን ጊዜ ኃይላቸው ጋሻ ሆኖ ከጠላት ይታደጋቸዋል፤ወደ ኃያልነትም ይቀይራቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው አታውቅም።
ለአፍሪካ ነፃነት ያላት አቋም አንድም ቀን ቀንሶ አያውቅም። ለፓን አፍሪካዊነት የምትሰጠው ቦታ ሁሌም ጉልህ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ‹ኢትዮጵያ› ናት። በአፍሪካዊነት ላይ አታወላውልም›› እንዳሉት፤ ኢትዮጵያም ብትሆን በእንደዚህ ዓይነት ጉባኤያት ላይ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባት።
ምክንያቱም አሁን የአፍሪካን ጥቅም በአንድነት የሚያስከብር፤ ድምጹን የሚያሰማ ተቋምና መሪ እንዲሁም አጀንዳ ቀርጾ ወደፊት የሚያመጣ አመራር ያስፈልጋል። በዚህም የተቻላትን ማድረግ ይጠበቅባታል። ለዚህ ደግሞ የአሁን የእንሰባሰብና እንወያይ ጥሪዋ ያስመሰግናታልና ይህንን ማጠናከር አለባት።
ቀደም ሲል የነበረውን ሁኔታ በብዙ መልኩ እንደቀየረች ሁሉ ዛሬም የምዕራባውያንን ዋሾነት ማጋለጧን ልትቀጥልበት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካውያን፣ የጥቁር ሕዝቦችና የሰው ልጅ አጀንዳ መሆኑን ምዕራባውያን ጭምር እንዲረዱት አድርጋለች። ይህ ደግሞ አገራቱ አቋማቸውንና ሥራቸውን እንዲመረምሩ አስገድዷቸዋል። እናም ኢትዮጵያ ብቻዋን ይህን ያህል ርቀት መጓዝ ከቻለች እንደአፍሪካ መጓዝ ቢቻል ምን ያህል ለውጥና ብልጽግና ማምጣት እንደሚቻል መገመት አያዳግትም።
እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር ያስፈልገናል፡፡ ይህ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ እንዳይካሄድ የሚፈልጉት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን በመቆጣጠር በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነትና የአህጉሩን ፖለቲካ በበላይነት ይመራሉ። እናም ይህን ዲፕሎማሲያዊ ድል መቀበል አልፈለጉም።
ይህ እንዳይሳካም አገሪቱ ላይ ሕወሓት በሚባለው ባንዳና ተላላኪያቸው በኩል ሽብር ይፈጥራሉ፤ እየፈጠሩም ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ይህ መቼም አይሳካላቸውም። ኢትዮጵያ የነበራትን ክብርና የቆየ መልካም ስሟን አታስነካም። ለዚህም ብዙ ተግባራትን እየከወነች ትገኛለች።
የመጀመሪያው ወዳጆቿን ማብዛት ሲሆን፤ ኢትዮጵያን የሚደግፉ አስተሳሰቦችና ለኢትዮጵያ የሚታገሉ ዜጎች በተለያየ የዓለም ክፍል እየታዩ መጥተዋል። ይህ ደግሞ ለምዕራባውያኑ ሌላ ሽንፈት ነው። በአገራችን ተከስቶ የነበረው ግጭት የፖለቲካ ቅራኔ የፈጠረባቸው የውጭ ኃይሎች ሚዲያዎቻቸውን በመጠቀም ዘመቻ ሲያካሂዱ እንደነበርም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ይህንን ሁሉ ተንኮል ድባቅ መትቶ ዛሬ ላይ መድረሱም የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠ መሆኑን ሁሉም ይረዳዋል።
ስለሆነም ይህ 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ከፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል ባለፈ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለውና መጠቀሙ ላይ እናተኩር በማለት ሀሳቤን ቋጨሁ። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 28/2014