(ክፍል አንድ)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት በህዝብ ከተጠቆሙ 632 እጩዎች መካከል 42ቱን መለየቱን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርገዋል ።
በአዋጁ በተቀመጡት መስፈርቶች አማካኝነት ከተጠቆሙት 632 እጩዎች ውስጥ የተለዩት 42 ዕጩዎች ላይ ከአማካሪዎች ጋር ምክክር እየተደረገበት ሲሆን በያዝነው ሳምንትም በተለዩት 42 እጩ ተጠቋሚዎች የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ላይ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፤ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አካላት በሚገኙበት ምክክር ተደርጎ ግብአት እንደሚሰበሰብ አብራርተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረ-ገጽና በማህበራዊ ሚዲያ የተለዩት 42 እጩዎች ማንነት ይፋ እንደሚደረግና ከህዝብ የሚሰበሰበው ግብአት ተገምግሞ የመጨረሻዎቹ 11 ዕጩ ኮሚሽነሮች ተለይተው በምክር ቤቱ እንዲሾሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሮቹ ከተሾሙ በኋላ በሚጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ አገራዊ የፖለቲካ ሀሳቦች የሚነሱ በመሆኑ ሁሉም አካል የሰከነ ውይይት በማድረግና መግባባት ላይ በመድረስ የአገሪቱን ቀጣይ ጉዞ ስኬታማነት ማረጋገጥ ይገባል በማለት ማሳሰባቸው ተዘግቧል ።
ሀገራዊ ምክክሩን ተከትሎ የጸደቀው አዋጅ እና የአፈ ጉባኤው መግለጫ ሁለት ትክክለኛና ታሪካዊ መታጠፊያዎችን አስታውሰውኛል። ብዙዎቻችን ልብ አላልነው ይሆናል እንጂ የሀገራዊ ምክክሩ መሠረት የተጣለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት በኢፌዴሪ ፓርላማ ቀርበው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት ታሪካዊ የመጀመሪያ ንግግር ነው ።
ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ከፍ ባደረገው በዚህ ንግግራቸው ፍቅርን ፣ ይቅርታን ፣ መነጋገርን፣ መደማመጥን ፣ መቀባበልን ፣ ወዘተረፈ አውጀዋል። የሀገራዊ ምክክሩ ዕርሾ ይህ ንግግራቸው ነው ። ይሄን ተከትሎ የሀገሪቱ ድባብ መቀየር ጀመረ ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታትዎ በላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩና በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ተቃዋሚዎች እንዲሁም በስደት ላይ የነበሩ ተፎካካሪዎች እና አክቲቪስቶች ሀገራቸው ገብተው እንዲታገሉ አድርገዋል።
አፋኝ ሕጎች እንዲሻሻሉ ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። ተዘግተው የነበሩ 260 ብሎጎችና ድረ ገፆች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተከፍተዋል። በአሸባሪነት ተወንጅለው ተዘግተው የነበሩ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎችን እግድ በማንሳት ፤ ጋዜጠኛ በመሆናቸው የተለያየ ታርጋ ተለጥፎባቸው በእስር ሲማቅቁ የነበሩ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያን በመፍታት ፤ ሀቀኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ተቋማዊ ለማድረግ ሕጎችን ማሻሻል ፤ ገለልተኛ ተቋማትን ገለልተኛ በሆኑ ግለሰቦች እንዲመሩ ማድረጉ ፤ ትህነግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ሻእቢያን እንደማስፈራሪያ ይጠቀምት የነበረ ስሁት ፖሊሲ በለውጡ ማግስት ተቀይሮ እርቅ መውረዱ ፤ ወደ ሀላፊነት በመጡበት አንድ አመት ብቻ 23 የተለያዩ ሚዲያ ባለቤቶች ያለምንም መሸማቀቅ ፣ ግራ ቀኝ መገላመጥ ፣ ስጋት ፣ ውጣ ውረድና እንግልት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የብሔራዊ እርቅና የመግባባት ጥርጊያ መንገዱን ማቅናት የተጀመረው በለውጡ ማግስት ነው ማለት ይቻላል ።
ይሄን መነቃቃትና አዲስ መንፈስ ተከትሎ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ እንደ ደመኛ ይተያዩ የነበሩ ፖለቲከኞችን ፣ ልሒቃንን ፣ አክቲቪስቶችንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ጠረጴዛ አቅርቦ በማነጋገር አሁን እየታሰበ ያለው ሀገራዊ ምክክር እውን ሊሆን እንደሚችል በተግባር አሳየ ። ፍንጭ ሰጠ ።
ነጮች እንደሚሉት litmus paper ሆኖ አገልግሏል ። ከያኒው ቴዲ አፍሮ ፣”የኋላው ከሌለ፣የፊቱ አይኖርም፤” እንዳለው ፤ እንዲሁም ያለፈውን ወዲያው ወዲያው የመርሳት የዝንጉነት አባዜ ስላለብን ለሀገራዊ ምክክሩ እርሾ የነበረውን ዴስቲኒ ኢትዮጵያን መለስ ብሎ የማስታወስ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ስለሆነ በወፍ በረር እንቃኝ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ” …ኢትዮጵያ መሀፀነ ለምለም ናት። … ” በማለት ሀገራችን በታሪኳ ከገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በክብር አቅፈው ደግፈው የሚታደጓት የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳሏት መናገራቸው ይታወሳል። ዛሬም ልጆቿ በማንነት እና በሴራ ኀልዮት የተነሳ ተቃቅረው አይንህን ለአፈር በተባባሉበት ፤ አይንና ናጫ በሆኑበት ፤ ሀገር ፅንፍ በወጡ ሀሳቦች እየተላጋች መንታ መንገድ ላይ ቆማ እያለ የሚያሻግር ሀሳብ ያላቸው ልጆቿ ደርሰውላታል።
ድፎ ባልቆርስም እነዚህን ልጆቿን እኔ ” ቲም ንጉሱ ” ብያቸዋለሁ። በአስተባባሪያቸው አቶ ንጉሱ አክሊሉ ስም። አቶ ንጉሱ የኢኒሽየቲቩ ጠንሳሽና ዋና አስተባባሪ፤ በሙያቸውም ታዋቂ ማህበራዊ ተሟጋችና የግሎባል ገቨርናንስ ባለሙያ ናቸው። ዛሬ በሀገራችን የተፈጠረውን ንቃቃት በመጠቀም የፖለቲካ ነጋዴዎች ሌት ተቀን ግጭት ፣ ቀውስና ሴራ እየቀፈቀፉ እስፖንሰር እያደረጉ በድሀ ልጅ ደም ሸቅጦ ለማትረፍ ደፋ ቀና በሚሉበት ቀውጢ ሰዓት” ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቮች ” ደግሞ ሀገራችንን ከጥፋት ለመታደግ ሀሳብ በማፍለቅ ተስፋችንን እንደገና አለምልመዋል። የተሰበረውን ቅስማችን ሊጠግኑ አሐዱ ብለዋል።
ጠቢቡ ሰለሞን ቤተክርስቲያንን እና ፈጣሪን በለሆሳስ በሚሰማ መዝሙር እንዳመሰገነው እኔም እነ ” ቲም ንጉሱ “ን ፣ 50ዎቹን ንጋቶች እና የሰላም ሚኒስቴርን ለማመስገንና እገረ መንገዴን ዛሬ ለፍሬ የበቃውን ጥረታቸውን ከአንባቢያን ጋር ለማስተዋወቅ የመጣጥፌን ርዕስ ” የኋላው ከሌለ፣…፤” ብየዋለሁ። ከፍ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለሀገራዊ ምክክሩ በፋና ወጊነት አንስቻለሁ ። ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሽየቲቭ አገራችን ለምትገኝበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መፍትሄ ለማቅረብ የተጠነሰሰ አገር በቀል እንቅስቃሴ ነው።
የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች (Core Team) ዘጠኝ ያገባኛል ብለው የተነሱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እነዚህም ልዩ ልዩ ብሔሮችን፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን፣ እምነትንና የሙያ ስብጥርን ይወክላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በመስራት ላይ የሚገኘው ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ የተሰኘውና መቀመጫውን በካናዳ ያደረገው ዓለምአቀፍ ተቋም በገዢውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ እንደገለልተኛ አካል ስለሚቆጠር ተቋሙ ኢኒሽየቲቩን በፕሮጀክትነት እንዲይዘው ተመርጧል። የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ቡድን የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመፈተሽ አገራችን ካለችበት ቅርቃር ልትወጣ የምትችልባቸውን አማራጮች ሲያፈላልግ ቆይቷል።
ፈተናውን ከወደቁ አገራት ተሞክሮ ማግኘት እንደሚቻል የማይካድ ቢሆንም፣ መሠል የፖለቲካ አጣብቂኝን በስኬት ጠርምሰው ካለፉ አገራት ግን የተሻለ ገንቢ ትምህርት ማግኘት እንደሚቻል የቡድኑ ጽኑ አቋም ሆኖ ቆይቷል።
የደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያና መሠል አገራት ልምድ እንደሚያሳየው መጪው ዘመን ላይ ልዩ ትኩረት ያደረጉ ወሳኝ አካላት ተቀራርበው በመጪው ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲመክሩ የሚያግዙ አሰራሮች አገሮቹን ከአጣብቂኙ ለማሾለክ ከማስቻላቸውም በላይ ለሌሎች የሠላም እና ዕርቅ ጥረቶች ዕገዛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደቻሉ ታሪክ ይመሰክራል። ከዚህ አንጻር ሲታይ እ.ኤ.አ. በ1991 ደቡብ አፍሪካ ረዥም ዘመን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቀውሷን ለመፍታት በተቸገረችበት ወቅት እንደ አንድ የብሔራዊ ሠላም ግንባታ መሳሪያ ተደርጎ ተግባራዊ የተደረገው የትራንስፎርሜሽን ሴናሪዮ ዕቅድ ነበር ።
በጊዜው በሁለት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ጠንሳሽነት በቁጥር ወደ 30 የሚጠጉ ተጽዕኖ አምጪ እና ገዢ አመለካከትን የሚወክሉ ሰዎች ከመላው የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ መስኮች በጥንቃቄ ተመርጠው በደቡብ አፍሪካ ሊከሰቱ የሚችሉ መጻኢ ዕድሎችን (scenarios) እንዲቀርጹ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ተደረገ ።
ከገዢው ፓርቲ፣ ከተፎካካሪዎች (ለምሳሌ – የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ወይም ኤ.ኤን.ሲ. ፓርቲ፣ ፓን አፍሪካን ኮንግረስ እና መሰል ፓርቲዎች) እና ከሌሎች መስኮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተቀራርበው በሂደቱ ተሳታፊ በመሆን ሴናሪዮዎቹን በጋራ ቀረፁ።
ሂደቱም በተሳታፊዎች መካከል ወዳጅነትን፣ ቅብብሎሽንና መተማመንን እንዲፈጥሩ አዲስ መንገድን ጠርጎላቸው ነበር። በተጨማሪም ይህ ሂደት እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በአቋሙ ላይ ክለሳ እንዲያደርግና አገሪቱ የምትገኝበትን የከፋ የፖለቲካ ቀውስ አስተውሎ በሰላም የምታልፍበትን የጋራ ውሳኔ እንዲያሳልፍ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ይህንን ሂደት አስመልክቶ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ይህ ሂደት ተሳታፊዎቹ በግላቸው ከፍ ሲልም በአገር ደረጃ የነበራቸውን አልሸነፍ ባይነት እና ግትርነት እንዲተውና ሽግግር እንዲያደርጉ በማገዝ ደቡብ አፍሪካ ደጃፍ ላይ ቆመው የነበሩ ብጥብጦችና የመበታተን አደጋዎች በመጡበት እግራቸው እንዲመለሱ በማድረግ አገሪቱ ወደቀጣዩ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።ይህ ተሞክሮ ላይ በመመርኮዝ ይህ ልምድ እንደ ኮሎምቢያ፣ ጓቲማላ፣ ታይላንድ፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች አገሮች ተወስዶ ጥቅም ላይ ውሏል።
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ የዚህ ዘዴ ጠንሳሽ እና በደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች አገሮች ሂደቱን በማስተባበር የተሳተፈውን ሪዮስ ፓርትነርስ የተባለውን ድርጅት ዋነኛ መስራች አዳም ካህንን በማግኘት፣ በተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ በመምከር ለበርካታ ዓመታት ዕቅድ ሲያቅድ እና የሌሎች ሃገራትን ልምድ ሲያሰባስብ ቆይቷል። ከዚያም ከሌሎች የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች ጋር በመመካከር ሃሳቡን በኢትዮጵያ የመተግበር ዕቅድ ተያዘ ።
አስተባባሪ ቡድኑ አስቀድሞ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የፖለቲካ አመለካከቶችን እና ክልሎችን የሚወክሉ ቁልፍ ተጽዕኖ አምጪ ሰዎች ለመለየት እንዲቻል ሁሉን አካታች የሆነ የመመዘኛ ማዕቀፍ (multi-criteria assessment framework) ቀርጿል። ይህ ቡድን የሚመለምላቸውን የሴናሪዮ ቡድን አባላት አመራረጥ ተዓማኒነት ለማጉላት ደግሞ የጾታ፣ የዕድሜ፣ የብሔር፣ የሐይማኖት፣ እና የሙያ ስብጥርን የመሳሰሉ ሚዛን ማስጠበቂያዎችን (sensitivity markers) ተጠቅሟል።
በእነዚህ መሥፈርቶች በመጠቀም በአመለካከት ደረጃ የአሁኗ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ይወክላሉ ብሎ ያሰባቸውን ወደ 50 ገደማ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን (ሁለት የዳያስፖራ አባላትን ጨምሮ) መልምሏል።
ኢኒሽየቲቩን ለመጀመር የመንግስት እውቅና ያስፈልግ ስለነበር ከሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው አካላት ዘንድ ቀርቦ በመወያየት ይሁንታንና ድጋፍን አግኝቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን ፣ የገዥው ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የአባል ፓርቲዎች ኃላፊዎች ጋር ቀርቦ ስለ ሂደቱ በማስረዳት ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን አረጋግጧል ።
በዚሁ መንፈስ የሂደቱ አስተባባሪዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችን በማነጋገር ድጋፍ አሰባስበዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉም አድርገዋል ። ከዚህ በተጨማሪ ታዋቂ የመገናኛ ብዙኃን ፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና የሲቪክ ማሕበረሰብ ወኪሎችንና ምሑራንን ቀርቦ በማነጋገር በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓል ።
ለዛሬ በዚህ ላብቃ በክፍል ሁለት መጣጥፌ በስፋት እመለስበታለሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014