የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደ መጀመሪያው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ይቆጠራል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመው አፍሪካውያን ብዙ የቅኝ ገዥዎችን ብዝበዛና ጭቆና መከራ ካሳለፉ በኋላ ነው።
ምዕራባውያን የአፍሪካን ጥሬ ሀብትና የሰው ጉልበት ለመበዝበዝና ራሳቸውን ለማበልጸግ በርሊን ላይ ከዶለቱ በኋላ መቀራመት ጀመሩ። ይህ የምዕራባውያን እኔ ብቻ ልብላ ሴራ ግን ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ከሸፈ! ለመላው የዓለም ጥቁር አዲስ ወኔ ፈጠረ። የነጮቹ ሴራ ክሽፈቱ ኢትዮጵያን ቅኝ አለመግዛታቸው ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ሲገዟቸው የነበሩ ሌሎች የአፍሪካ አገራትንም መነጠቃቸው ነው። ቅኝ ይገዙ የነበሩ አፍሪካውያን አገራት ‹‹ለካ ቅኝ አለመግዛት ይቻላል!›› የሚል ጥያቄ ተፈጠረባቸው፡፡ እነሆ ከዚያ በኋላ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ።
በቅኝ ሲገዙ የነበሩ የአፍሪካ አገራት ራሳቸውን ነፃ አወጡ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፤ በኋላም የአፍሪካ ኅብረት ተባለ። የኅብረቱ ዋና መቀመጫም ቅኝ አለመገዛትን ለዓለም ባስተዋወቀችው ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ሆነ። እነሆ ዘንድሮው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሊደረግ ኢትዮጵያ ዝግጅቷን አጠናቃለች። ይህ የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመጀመሪያው(እንዲያውም ከምሥረታው) ጋር ይመሳሰላል። ልክ እንደመጀመሪያው ከብዙ ፈተና በኋላ የተደረገ ነው።
ከምዕራባውያን ያልተቋረጠ ሴራ እና ከኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ቆራጥነትና ብልህነት ትግል በኋላ የተደረገ ነው። ምናልባትም ለብዙዎቻችን በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የምዕራባውያን ሴራ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከፈተው ጦርነት ያለው ይሆናል።
ዳሩ ግን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲሰሩ የነበሩ ሴራዎችም የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው። በእነዚህ ምክንያቶች የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ልዩ ይሆናል። እነዚያን ሴራዎች ሲጠነስሱና ሲበጠብጡ የነበሩት አገራት አሁን የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ መካሄዱን ሲያዩ ዳግም ዓድዋ እንደተፈጸመ ይቆጥሩታል።
ይቺን አገር ማሸነፍ እንደማይቻል ያረጋግጡበታል። የአፍሪካ ኅብረት እኛ ኢትዮጵያውያን ልንኮራበት የሚገባ ትልቅ ዕድል ነው። ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ…›› ይሉት ተረት ሆኖብን ተገቢውን ክብርና ቦታ አልሰጠነውም። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን ቀላል ዕድል አይደለም። ይሄኔ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለች አፍሪካዊት አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ ምን ይሰማን ነበር? ኢትዮጵያ ውስጥ
በሌሉ ስንትና ስንት ነገሮች መንፈሳዊ ቅናት አላደረብንም ወይ? ቅኝ ገዥ አገራትን እንዴት ነው በኃያልነትና በክብር የምናያቸው? ኢትዮጵያ ደግሞ ቅኝ ባትገዛም ቅኝ አለመገዛቷ አያስቀናንም ነበር ወይ? በነገራችን ላይ በአንዳንድ የአገራችን ሰዎች የአፍሪካ ኅብረት ተገቢውን ክብርና ዝና እየተሰጠው አልነበረም።
የመሪዎች ጉባኤ ሲደረግ ብዙ ቀልዶች ይቀለዳሉ። ቀልዶቹ አይኑሩ ማለት ባይቻልም በቁም ነገር በየጋዜጣውና መጽሔቱ ማጣጣል ግን በተዘዋዋሪ አገርን ማጣጣል ነው። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ምን ስሜት እንደሚሰጥ የሚያውቁት ምናልባትም ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ።
የአፍሪካ ኅብረት ለኢትዮጵያ ትልቅ ኩራት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለመላው የአፍሪካ ሕዝብ ኩራት ነው። የአፍሪካ መሪዎች በተለያየ አጋጣሚ ስለኢትዮጵያ የነገሩን በቂ ነው። በአጭሩ ኢትዮጵያ እናታችን ናት፤ እናት ከሌለች ልጆች ይበተናሉ ነው ያሉት።
ይህ ቀላል መልዕክት አይደለም። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ በተካሄደ ቁጥር የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። የሁሉም አገራት ሕዝቦች መሪያቸው የት እንደሄዱ ይነጋገራሉ ማለት ነው። የየአገራቱ መገናኛ ብዙኃን መሪዎች ወዴት እንደሄዱ ይናገራሉ። በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ስም ይነሳል። የየአገራቱን መገናኛ ብዙኃን የተከታተለ ሁሉ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ ያያል፣ ይሰማል፣ ያነባል ማለት ነው። በዚያ ላይ የአብዛኞቹ አፍሪካ አገራት መገናኛ ብዙኃን የሚጠቀሙት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚል መርህ እንዳለው ይታወቃል። በዚህ መርሁ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተለያዩ ውይይቶች ተካሂደዋል፣ የተለያዩ ስምምነቶችም አሉ። የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት በዋናነት በምን በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ገና አልታወቀም፤ ከዚህ በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥጋት ሆኖ ነበር። ከዚያ በፊትም በፀጥታና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዋና ትኩረት አድርጎ እንደነበር አይተናል።
የዘንድሮውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሌላው ለየት የሚያደርገው ነገር፤ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አገራቸውን ማየታቸውና ሰላምነቷን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቃቸው ነው። ዓለም ይህንን ተረድቷል። የኅብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በተመለከተም ዝም አላሉም። በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በፓን አፍሪካኒዝም ዙሪያ የውይይት መድረክ ማዘጋጀታቸው ይታወሳል።
በመድረኩም፤ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ አዲሱን የዳግም ቅኝ ግዛት ፍላጎት ለማክሸፍ አፍሪካዊ ዲያስፖራዎች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው፣ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም ከአፍሪካውያን ጋር በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መንፈስ በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ‹‹ኢትዮጵያ ፣የአፍሪካ ኅብረት እና የዲያስፖራው ሚና›› በሚል ጽሑፍ አቅርበዋል።
በጽሑፋቸው አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የጎላ ሚና እንዳላት ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁን አፍሪካ ኅብረት አመሠራረት ጀምሮ ያደረገችውን ጥረት ለዲያስፖራው አባላት አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍም፤ አፍሪካውያን ዲያስፖራዎች አህጉሪቱ በመሠረተ ልማት ፣በኢነርጂ እና በቴክኖሎጂ ያለባትን ክፍተት ለመሙላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል ። በመድረኩ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ፣ከካሪቢያን አካባቢ የመጡ ዲያስፖራዎች በፓን አፍሪካኒዝም ዙሪያ ያሏቸውን አስተያየቶች አቅርበዋል።
እንግዲህ ዝርዝር ጉዳዩን እንተወውና፤ ከዚህ ሁሉ ውስጥ የምንረዳው የአፍሪካ ኅብረት ምንነት በተለያዩ የዓለም አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየተዋወቀ መሆኑን ነው።
የዘንድሮውንም ለየት የሚያደርገው ከእነዚህ ዲያስፖራዎች ጋር ውይይት የተደረገበት መሆኑ እና ኢትዮጵያ ዳግም ክብር አስጠባቂነቷን ያስመሰከረችበት መሆኑ ነው። የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ነው። ዲፕሎማሲ ነው፣ ኢኮኖሚ ነው። ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን የነፃነት አስጀማሪና አርዓያነት የሚያጎላ፣ በዚህም ምክንያት የኅብረቱ መቀመጫ መሆኗ ነው።
ኢኮኖሚው ደግሞ የመሪዎች ጉባኤ በሚካሄድበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም በሚደረገው እንቅስቃሴ ሆቴሎችና ሌሎች የእንግዳ መዳረሻዎች ዓለም አቀፍ ግብይት ስለሚያገኙ ነው፡፡
በአጠቃላይ የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ዳግም ገናናነቷን ያስመሰከረችበት ነው። ዳግም ለኢትዮጵያውያን አሸናፊነትን ያጎናጸፈ ነው ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014