“እንቆቅልሽ/ህ ?
” እንቆቅልሽ/ህ ከአገራዊ የሥነ ቃል እሴቶቻችን መካከል አንዱና ተወዳጅ ጨዋታ ነው። ዕድሜና የፆታ ልዩነት ሳይገድበው በተወሰኑ ሰዎች መካከል የሚከወነው ይህ የፉክክር ጨዋታ ከጊዜ ማሳለፊያነቱ ይልቅ አመራማሪነቱና አስተማሪነቱ ይበልጥ የጎላ ነው።
እንደ ኢመደበኛ የትምህርት ዓይነት ለአጠቃላይ እውቀት መፈታተሻና መማማሪያ ሊቆጠር የሚገባው ይህ ድንቅ የጨዋታ ቅርስ እየደበዘዘ መጥቶ ለዛሬውና ለመጻኢው ትውልድ ባዕድ እስከመሆን ለመድረሱ ተጠያቂዎቹ “ቅርሱን በአደራ አቀባይ መሆን የሚገባው ይህ ትውልድ” እና የትምህርት ሥርዓታችን እንደሆኑ መገመት አይከብድም።
የፎክሎር ተመራማሪዎች፣ ደራስያን፣ የልዩ ልዩ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራንና የባህል ተመራማሪዎች ወዘተ. የዛሬውን ትውልድ ወክለው ተቀዳሚ ተጠቃሽና ተወቃሾች ናቸው።
የትምህርት ሥርዓቱን የሚመራው ተቋምም “ዝም አይነቅዝም” ቢልም ከወቀሳው ስለማያመልጥ ግዙፉን የኃላፊነት ድርሻ ለመሸከም ግድ ይለዋል።ጣታችንን በመጠቆም የፈረድንባቸው እነዚህ ሁለት አካላት “አይመለከተንም!” ብለው በማገንገን “ክሱን” ማጣጣል ከፈለጉም በዚህ “የነፃ ሃሳብ” መድረክ ላይ መሟገቻቸውን ማቅረብ መብታቸው ነው።
“የትዝብቱ ፋይል በጭራሽ እኛን አይመለከትም” በማለት አክርረው በይግባኝ መከራከር ከፈለጉም “ምን ተእዳችን” ብለን ፍርዱን ለታሪክ እማኝነት እናስተላልፋለን። ለማንኛውም፡- “እንቆቅልሽ/ህ?” በሚል ጥያቄ የሚጀምረው ጨዋታ “ምን አውቅልሽ/ህ!?” የሚለውን የተጠያቂውን ምላሽ ሲያገኝ የእውቀቱን ብስለት የሚፈታተኑ ጥያቄዎች መዥጎድጎድ ይጀምራሉ።
ለምሳሌ፡ – “ሲሄድ ውሎ ሲሄድ የሚያድር?” የሚል የእንቆቅልሽ ጥያቄ ቢጠየቅ “ወንዝ ነው!” የሚል መልስ ካልተሰጠ፤ ጠያቂው አገር እንዲሰጠው የግድ ይላል። ጠያቂው የአገር ስጦታ ሲቀርብለትም የተሸለመውን አገር በማወዳደስ “እከሌ የሚሰኘውን አገር አግኝቼ ምን አጥቼ፤ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ፤ እንዳልሰድብህ/ሽ ወዳጄ ነህ/ሽ፤ እንዳልተውህ ጠላቴ ነህ/ሽ!” እየተባባሉ ጨዋታው ተጋግሎ ይቀጥላል።
በአይ እና አዎ (አያዎ – Paradox) ታጅቦ በጠያቂው የሚፎከርበት “ወዳጅነቱም ሆነ ጠላትነቱ” እንዲያው ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር “በእንካ ሰላንትያው” ላይ ቅይማት ስለማይፈጥር ተጠያቂው በሁለተኛና በሦስተኛ ዙር ለሚጠየቀው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ከመለሰ ስለሚጨበጨብለት “የጠላትነቱ” ውግዘት ተነስቶለት በወዳጅነት ይደናነቃሉ።
“ኢትዮጵያዬ ሆይ እንቆቅልሽ ?”
“ምን አውቅልህ!?” ካልሽኝ እነሆ የመጀመሪያው ሞጋቹ ጥያቄዬ። “እንቅፋት አይፈራ፣ ስንቅ አያሻው፣ ተመውጣቱ ዓለምን ዞሮ መምጣቱ?” መልሱን ፈጥነሽ እንድትሰጭኝ በትእግሥት ብጠብቅሽም ዝምታን በመምረጥ እድሜዬን ስላባከንሽ ከዚህ በላይ ልታገስሽ ስለማልችል ሌላ አገር ሳልፈልግ ራስሽን ስጭኝና መልሱን እኔው ራሴ ልጠቁምሽ። እናት ዓለሜ! ከተስማማን ልቀጥል? “ መልካም! ኢትዮጵያን አግኝቼ ምን አጥቼ፤ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ፡- ረሃቡም ጥጋቡም፣ ድርቁም ልምላሜውም፣ ጦርነቱም ድሉም፣ ዝማሬውም ኃዘኑም፣ ስደቱም ከስደት መመለሱም፣ ፍቅሩም ጠቡም፣ ኢትዮጵያዊነቱም ዘረኝነቱም፣ ክፋቱም ደግነቱም፣ ዲሞክራሲውም ጀብደኝነቱም፣ የኑሮ ትግሉም መንደላቀቁም፣ ጉበኝነቱም ንጽህናውም፣ መበደሉም ፍትሐዊነቱም፣ ጩኸቱም ዝምታውም፣ ሰላሙም ጭንቀቱም፣ እልሁም ይቅር ባይነቱም፣ እንባውም እልልታውም፣ ተስፋውም ተግዳሮቱም፣ ቢሮክራሲውም አሻጥሩም . . . አቤት የመከራሽ ብዛቱ ! ።
እንዳልሰድብሽ እምዬ ነሽ፤ እንዳልርቅሽ ቤት አልባ ነኝ። አልሰደድ የት ልገባ። እንዳልፀናም ሆዴ ባባ። ሁሉ ነገር እንቆቅልሽ፤ ግራ አጋብቶ የሚያዞርሽ። መልሱ እናት ሀገሬ ሆይ “ሃሳብ” ነው። በሃሳብ እየተላጉ መኖሩ የእኔ የጠያቂው ብቻ ሳይሆን የሕዝብሽም የጋራ እጣ ፈንታ ከሆነ ሰነባብቷል። የሚያሳስቡን ጉዳዮች ተቆጥረውም ይሁን ተሰፍረው የሚጠናቀቁ አይደሉም። ወዲህ ሲቋጠር እዚያ ይፈታል። ማዶ ሲተረተር እዚህ ይቋጫል።
የወደድነውን ስንጠራ ያልፈለግነው ይመጣል። የማዶውን ስንረታ የቅርባችን ያገነግናል። ልንስቅ ፈገግ ስንል ኅዘን ፈጥኖ ከተፍ ይላል። ተግተን ስናለማ ተግተው የሚያፈርሱ ሞልተዋል። ቢቸግረን አስቸገርንሽ። እኛ ልንመልሰው በማንችለው የሃሳብ አዙሪት በመክተት አንቺንም አዋከብንሽ። እኛም አንቺም በጋራ ልንመልሰው በማንችለው እንቆቅልሾች ተገዳደርንሽ። እምዬ ሆይ! ግራ ገብቶን ግራ አጋባንሽ። ግራ ካጋቡሽ ጋር በማበርም አዙሪቱን አከረርንብሽ።
“አዬ ምነው [ፈጣሪያችን]፤ ኢትዮጵያን ጨከንክባት? ምነው ቀኝህን ረሳሃት? እስከ መቼ ድረስስ መከራዋን ታከርባት? ልቦናህን ታዞርባት? ፈተናዋን ሰቀቀንዋን ጣሯን ይበቃል ሳትላት? አላንተ እኮ ማንም የላት . . . አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን በቅርሻት ግፍ አጨማልቃ፣ ታርሳ፣ ተምሳ በስብሳ . . . [አሜሪካም] እንደዚያው ነች በእብሪት ገዝፋ ተኮፍሳ፣ መስሎን እንጂ መቼ ገባን፤ ሥልጡን ብኩን መፃጉ ናት። (ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፤ እሳት ወይ አበባ፤ “ከሰቆቃወ ጴጥሮስ” ግጥም ይዘቱን ሳይለቅ ለዚህ ጽሑፍ ማጎልበቻነት ተሻሽሎ የተወሰደ።) የንግሥት ሳባና የንጉሥ ሰሎሞን የእንቆቅልህ/ ሽ ወግ፤ እየተማርን ያደግነው ንግሥተ ሳባ ኢትዮጵያዊት ገናና መሪ እንደሆነች ነው። መታወቂያ ስሟም አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ያህል እንደነበር በሦስተኛ ክፍል መጽሐፋችን ላይ ዛሬም ድረስ እንደተሰነደ በክብር ተቀምጧል።
ንግሥተ ሳባ፣ ንግሥተ አዜብ፣ ንግሥተ ማክዳ፤ ሦስቱም የሚያማምሩ ስሞች ናቸው፤ ይገባታል። ቅዱስ መጽሐፍ ይህቺን ክብርት ንግሥት የገለጻት እንዲህ በማለት ነበር። “የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች።
ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ ነገረችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን እንቆቅልሽ ሁሉ ፈታላት። ያልተረጎመላትና ከንጉሡ የተሰወረ እንቆቅልሽ አልነበረም።” (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ 10) የሚቀጥለው የታሪኩ ክፍል የቅዱስ መጽሐፍ ዋቢ የሚጠቀስለት ሳይሆን “በቃል” የተተረከ ጭማሪ ነው። በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥም አይገኝም። ተረኩን እናስታውስ፡- ንግስተ ሳባ ወደ ሰሎሞን ዘንድ እንደቀረበች የጥበቡን ልህቀት ልትገመግም በመጀመሪያ ያቀረበችለት የእንቆቅልሽ ፈተና በእርግጥም ተደርጎ ከሆነ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር።
ከንጉሥ ዘንድ በሰባት ርምጃ ርቀት ላይ ፊት ለፊቱ ቆማ ሁለት የተዋቡ የጽጌሬዳ እምቡጦች እያሳየችው “ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ! ከእነዚህ ሁለት ጽጌሬዳዎች መካከል የትኛው የተፈጥሮ የትኛውስ አርቴፊሻል ነው?” እጅግ ሞጋች እንቆቅልህ! ንጉሡም ጥቂት እንደማሰላሰል ካለ በኋላ “የተከበርሽ ንግሥት ሆይ! አንቺንም ለሺህ ዓመት ንግሥና ያብቃሽ።
በእጅሽ የያዝሻቸውን ሁለቱን የጽጌሬዳ እምቡጦች እባክሽ እዚያ መስኮት ላይ አስቀምጫቸው?” ንግሥቲቱም ለቀጥተኛ ጥያቄዋ ፍጹም ያልጠበቀችውን መልስ አከል ትዕዛዝ ስለሰጣት እንደታዘዘችው ሄዳ በተባለው የመስኮት ደፍ ላይ ሁለቱንም አበቦቹ ጎን ለጎን አስቀመጠቻቸው።
ልክ አስቀምጣ ዞር ስትል አንዲት ንብ ጥዝዝዝ እያለች ሄዳ በተፈጥሮው ጽጌሬዳ ላይ አረፈች። ንጉሡም ይህንን እንዳስተዋለ የትኛው አበባ የተፈጥሮ፤ የትኛው ደግሞ አርቴፊሻል እንደሆነ በመለየት “የተወራረዱበትን አገር እንድትሰጠው ግድ አላት!” ይላል አፈ ታሪኩ ወይንም ጥበበ ቃላቱ። ምናልባትም “የቀዳማዊ ምኒልክ” ታሪክ ከዚህ ጋር ይጎዳኝ ይሆን? እንጃ! ይሄ የጸሐፊው ግምት ነው። በተረቱ መደምደሚያ ላይ የምኒልክን ታሪክ የሚያጣቅስ ምንም ፍንጭ ግን አልተቀመጠም።
“ነው? አይደለም?” እየተባባሉ ከመሟገት ይልቅስ “ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ” ብሎ መገላገሉ ይቀላል። ስለዚህም ምክንያት ይሆን በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ፡- “ንጉሡንም አለችው፡- ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔ መጥቼ በዐይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር። እነሆ እኩሌታውን እንኳን አልነገሩኝም ነበር።
ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።” ብላ የመሰከረችለት በዚህን መሰሉ እንቆቅልሽ ስለተረታች ይሆን?” የዚህ ዐምደኛ መልስ አሁንም እንጃ! የሚል መሆኑን ልብ ይሏል።
እናት ዓለም አንቺስ ?
እኛ ልጆችሽ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን እንቆቅልሽን በቀላሉ ሊፈታ በሚችል አቅመ ጥበብ አልተባረክንም። እውነቱን ንገሩኝ ካልሽ ለተፈጥሯዊውም ሆነ ለአርቴፊሻሉ እውነታችንና የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ዛሬም እንቆቅልሾቻችን ሊፈቱልን አልቻሉም። እንቆቅልሾቻችንን መፍታት ስለተሳነንም “አገር ስጡን” የሚሉ ባእዳን እብሪተኞች ሳይቀሩ በከበባ ቀለበት ውስጥ ሊያስገቡን እየሞከሩ ነው።
“እንዳንተዋችሁ ወዳጆች ናችሁ፤ እንዳንረዳችሁ አገነገናችሁ” እያሉም በመዘባበት ሲሳለቁብን እያደመጥናቸው ነው። እናት ዓለም እንቆቅልሻችንን ፈትተሽ፤ ከውስብስብ ወጥመዳቸው ታደጊን። እንቆቅልሽ ሁለት፡- “ለምለም ምድር” እያለን ድርቅና ረሃብ የተፈራረቁብን ለዘመናት ነው።
” ረሃባችንን ለማስታገስ አቅም ስላነሰንም ዛሬም እንደ ቀዳሚ ዘመናቱ ሁሉ የስንዴ እርዳታና የተረጂዎችን ዓይን ዓይን እየተመለከት ነው። አሁን ይሄ ፈተናችን “ተፈጥሯዊ ነው ወይንስ አርቴፊሻል?” መልሱን ካወቅሽ ንገሪን፤ እኛ ለራሳችን ግራ ተጋብተን በምን አቅማችን መልሱን ለማግኘት እንመራመራለን? እንቆቅልሽ ሦስት፡- “ወንድም በወንድሙ ላይ ጨክኖ ጦር ሲሰብቅ፣ ነፍሱን በጭካኔ ሲነጥቅና ሀብትና ንብረቱን ሲያወድም በየት አገር ተሰምቷል? በሥልጣን ላይ ተቀምጦ ሲመራ የኖረውን አገር ከዳር ዳር ለማፈራርስ “አካፋና ዶማ” እያደለ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያፋጅ የሌላ አገር ታሪክስ ሰምተሽ ታውቂያለሽ? ይህ ታሪክ በራስ ምድር ሲፈጸም እያስተዋልሽ የእንቆቅልሹን መልስ ምን በማለት መለስሽ? እንቆቅልሽ አራት፡- እርስ በእርስ እየተደጋገፍን ከመረዳዳት ይልቅ ስንፋተግና ስንጠላለፍ ውለን ማደራችን ምን የሚሉት ደዌ ቢለክፈን ነው? የእኛን ያህል ቁጥር ያላቸው ፖለቲከኞች በየት አገራት አሉ? ካሉስ እንዴት ተኗኗሩ ወይንስ ልክ እንደኛው አገር ግማሹ ለጠላት እያደረ “ገሌ” ሲገባ፣ ከፊሉ ግራ ገብቶት ግራ ሲያጋባ እንደሚኖር ታሪኩን የሰማሽለት ሌላ አገር ይኖር ይሆን? እንዲህ መሰሉ የፖለቲካ ጥሎ ማለፍ ተፈጥሯዊ ነው ወይንስ አርቴፊሻል? እንቆቅልሽ አምስት፡- የመንግሥት መ/ቤት አገልጋዮች የመንግሥት አስለቃሾች የሆኑበት አገር ስለመኖሩስ ወዳጆችሽ አጫውተውሽ ያውቃሉ? ሹመት ለአገልጋይነት እንጂ ለገዢነት ሲሆን በዝምታ የምታስተውይውስ እስከ መቼ ነው? ሲመረጡ አጎንብሰው፤ ሲሾሙ ገዝፈው ለሚያመሳቅሉንስ የእናትነት መልስሽ ምንድን ነው? መልሱን ካላወቅሽ “አገር ስጭን ?” የነፍሳችንን ጩኸት ከሰማሽም ዜጎችሽ ነንና እየገሰጽሻቸውና እየመከርሻቸው አኑሪን። ቃልሽን ለሚንቀው፣ ክብርሽን ለሚዳፈረው፣ ብዝበዛን መኖሪያው ላደረገው፣ ፖለቲካውን ማትረፊያ አድርጎ ለሚሸቅጠው፣ በሥልጣኑ እየተመካ ልቡ ለደነደነው፣ ኢኮኖሚውን እያናጋ ለሚያጯጩኸን፣ እያጉላላ ለሚያስለቅሰን፣ እየነጠቀ ለሚዘርፈን. . . ወይ በትር ወይም ሰይፍ አንስተሽ እንቆቅልሻችንን ፍቺልን። ካልሆነልሽም አገር ስጭን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014