ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተላብሰን አፍሪካዊ ማንነት አጉልተን ስለአፍሪካ ሊመክሩ የመጡ የአፍሪካ መሪዎች ለመቀበል መሰናዶ የጨረስንበት ወቅት ላይ ነን:: መዲናችን የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥን ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቃ የእንግዶቿን መምጣት እየተጠባበቀች ትገኛለች።
ኢትዮጵያውያን እንግዶቻቸውን በእቅፍ አበባ፣ በሞቀ ሰላምታ ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁት አድርገዋል። በአዲስ አበባ ከጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ለ35ኛው ጊዜ የሚካሄደው ጉባኤ አፍሪካዊያን ከሌላ ጊዜ በተሻለ ውሳኔ የሚያሳልፉበትና ስለ አህጉሪቱ የሚመክሩበት እንደሚሆን የተስፋይቱ አህጉር ህዝብ ተስፋ ሰንቋል።
አፍሪካዊያን በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተወያይተው የሚበጃቸውን ውሳኔ ያሳልፉ ዘንድ የመረጥዋት መዲናቸው አዲስ አበባ ለቆይታቸው መልካም ለመማከራቸው ምቹ ትሆን ዘንድ የእያንዳንዳችን አስተዋፅዖ ይበቃል::
ከነበርንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በዚህ ወቅት የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ልዩ ትርጉም አለው:: ቀድሞ የመሪዎች ጉባዔ ለማድረግ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ካደረገችው አስተዋፅኦና ሚና አንፃር ቀዳሚ ተመራጭ ነበረች::
የዘንድሮው ጉባኤ እዚህች ምድር ላይ እንዳይደረግ የብዙ ተፅዕኖና ተደራራቢ ጫና ተደርጓል:: ነገር ግን ኢትዮጵያ እንደቀድሞው ለተፅኖው ባለመበርከክ በያዘችው አቋምና በተሰራው ዲፕሎማሲ ወደ ዋናው ቤታቸው እና መዲናቸው አፍሪካዊያን መተው ስለ አህጉሪቱ ለመምከር ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል::
እርግጥ የፓንአፍሪካን መርህ አንግበው የኢትዮጵን ፅኑ አቋም አክብረው እዚህ ጉባኤው እንዲካሄድ ፍቃዳቸው የነበረው አፍሪካዊያን መሪዎችም ትልቅ ቦታ አላቸው:: የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መሪዎች ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው የኢትዮጵያ ውለታን ያልዘነጋ እና ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር የገለጠ ገጠመኝም ነው ።
ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ለመላ አፍሪካውያን ድምፅ በመሆን ፣ የአፍሪካ የነፃነት መስታወት ፣ የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ መወለድ እና ማደግ ትልቁን የመሪነት ሚና ስትጫወት ቆይታለች።
የአፍሪካ ሀገራትን ከቅኝ-ገዢዎች ቀንበር ነፃ መውጣት እንዲቻል ወኔ የሰነቀ እና ነጻነትን ያጎናጸፈ ንቅናቄ ፣ በአላማቸው ተበታትነው የነበሩ ጥቁር አፍሪካዊያን የዘር ግንድ ያላቸውን ህዝቦች አንድ ያደረገ እና ያዋሀደ፣ጥቁሮች የጋራ ፎረም አዘጋጅተው ስለ ችግሮቻቸው እንዲወያዩ ከሌሎች አፍሪካዊያን ጋር እድል ፈጥራለች::
ፓን አፍሪካኒዝም በአፍሪካ መሬት ላይ የኒዩክለር ሙከራ እንዳይደረግ የተቋቋመ፣ ጥቁሮች በአለም ላይ እንዲያብቡ ያደረገ እና ጥቁር ቀለም ከፍ ብሎ እንዲታይ ያስቻለ የአፍሪካዊያን የወንድማማችነት አድማስን ያሰፋ ድምቀት እና ድል እንደሆነ በርካታ ምሁራን ይገልፃሉ::
ኢትዮጵያ ዳግም የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት፤ ቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውታለች። በወቅቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ አድርጋ ነበር አህጉራዊ አንድነቱን ያቀጣጠለችው ።
ፓን አፍሪካኒዝም ለዛሬው የአፍሪካ ህብረት መመስረት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ እና አፍሪካዊያን ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን እንደሚችሉ አረጋግጧል።
እዚህ ጋር የጋናው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ኩዋሚ ንክሩማህ የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት፤ የዛን ጊዜው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግንቦት 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲመሰረ የተናገሩትን እናስታውስ ።
“ዛሬውኑ አንድ ካልሆን እንጠፋለን። የኢኮኖሚ ነጻነታችን የሚረጋገጠው በአንድነታች ነው” ነበር ያሉት። የኑክሩማ ንግግር አንጻር የአፍሪካዊያን በአንድ ላይ መቆም በተለየ መልኩ በጊዜው የቅኝ ግዛት ማዕበል ውስጥ ለነበሩት ሀገራት በእጅጉ አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር የህልውና ጉዳይ ጭምር መሆኑን ነው። ለኢትዮጵያም አስፈላጊነቱ ባይካድም ካላት ቁመና አንፃር የሌሎቹ ተጠቃሚነት ጎልቶ ሊታይ ይችላል።
‘የአፍሪካ ህብረትን‘ ለመመስረታቸው እርሾ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ትናንት በአውሮፓውያን የቀጥታ እና እጅ አዙር ቅኝ ግዛት ቀንበር ወድቆባቸው ለነበረው አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ዘንድ ተከፍሎ የማያልቅ ውለታና ክብር እንድትጎናጸፍ አድርጓታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ላይ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ፤ ‘’ኢትዮጵያ እናታችን ናት፤ እናት ከሌለች ቤተሰብ ይበተናል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት እናት ናት:: ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝምን መሰረት የጣለች፤ በቅኝ
ግዛት ስር ያልወደቀች ሀገር ናት ‘’ ሲሉ የኢትዮጵያን ሚና እና ውለታ በአደባባይ ሊመሰክሩ ችለዋል።
አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ትናንት ነጭ ጠላት ከፊት ለፊት እና ከጀርባ በገጠማቸው ሰአት፤ ኢትዮጵያ ከፊት በመቅደም ለመፍትሄ ባዝነዋል።
ዛሬ ደግሞ የአፍሪካውያን የአሸናፊነት ተምሳሌት ፣ ለህብረቱ መወለድ ሞተር የሆነችው ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ወንድሞቿን ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልጓታል። ምክንያቱም እነሆ። አገራችን ኢትዮጵያ ገጥሟት ከነበረው ውስጣዊና ውጫዊ የህልውና ትግል አንፃር ጉባኤው ለኢትዮጵያ የመልካምና የአሸናፊነት ማብሰሪያ ሊሆን ተቃርቧልና።
ምዕራባዊያን በሀሰተኛ ትርክቶቻቸው ግራ ላጋቡት አለም ሰላም መሆናችን ማሳያ ትልቅ መድረክ ተከፍቷልና በራሳችን የቆመን በአፍሪካዊነታችን የደመቅን ኩሩ መሆናችንን ያዩበታል:: የኢትዮጵያን አሸናፊነት ባይወዱም እንዲቀበሉ ባያምኑም እንዲያረጋግጡ ያደርጋቸዋል::
ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም፤ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ሊታደሙባት ቀርቶ ፤ ያሉትም የውጭ ዜጎች ከተማዋን ለቀው መውጣት አለባቸው በማለት በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄድብን የነበረውን የሚድያ ዘመቻ በማጋለጥ፤ እውነትም ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም በራሷ ማረጋገጥ የምትችል መሆኗን፤ ከተማችን አዲስ አበባም ከምንጊዜውም በላይ ሰላማዊና ውብ እንደወትሮውም የአፍሪካውያን መዲና ሆና መቀጠል የሚያስችል ብቃት ያላት መሆኑን የምናረጋግጥበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
በኢትዮጵያ ላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች አብረው በተነሱበት ፣ የአፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልግበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ፤ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መሪዎች ተስማምተው የሕብረቱ ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማድረግ መምጣታቸው ውለታን አለመርሳት ነው።
“ሰው ማለት፤ ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ቀን” እንደሚባለው አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ሰው በጠፋበት በዛ በጥቁሩ ጊዜ ሰው ሆነን እንዳሳየናቸው ሁሉ ፤ ለእኛም ዛሬ ሰው በመሆን በተጨባጭ አጋርነታቸውን አሳይተዋል::
አፍሪካዊ ወንድሞቻችን የተዋለላቸውን ሳይዘነጉ በታሪካዊው ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ በደህና መጥተዋል። አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ወደ ሁለተኛዋ ቤታችሁ ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጣችሁ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014