የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች በ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት፣ ጉዳያቸውን በጋራ ለማየት፣ ለመምከርና የጋራ ግንዛቤን ለመያዝ ወደ ምድረ ቀደምትዋ አገር፣ ኢትዮጵያ ለመምጣት የዝግጅታቸው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። የአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባም ለእንኳን ደህና መጣችሁ ሥነሥርዓት መሰናዶዋን ጨርሳ ለአቀባበሉ ሽር ጉድ እያለች ነው።
የምስራቅ አፍሪካዋ ፈርጥ ኢትዮጵያ ስለ አፍሪካ አፍሪካውያንን አስተባብራ ለመቆም ስለ አፍሪካ በአፍሪካውያን ለመምከር እንደወትሮው ዘንድሮም ሽር ጉድ ላይ ናት። ኢትዮጵያ እንግዶችዋን እንዲህ ብላ ትቀብላለች። “ውድ አፍሪካውያን እንኳን በደህና ወደ መዲናችሁ መጣችሁ።
ዛሬ ድረስ ነፃ አገር ሆኜ፤ የአፍሪካውያን ተምሳሌት፣ የአትንኩኝ ባይነት ዓርማ ተላብሼ ቆሜያለሁ። ሉዓላዊነት ላይ ፀንቼ ክብሬንና ማንነቴን ሳላስነጥቅ ለጥቁሮች ተምሳሌት ሆኜ ቆይቻለሁ። ክንዳችንን አስተባብረን በአንድነት ለአንድነታችን እንድንቆምም በእኔ በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ላደርግ ተዘጋጅቻለሁ።
” ለአፍሪካ መሪዎች እዚህ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ ላይ መሰብሰብ ትርጓሜው ከሁሉም ይልቃል። ኢትዮጵያ ላይ ሆኖ ስለራሳቸው መምከር ከየትም በተሻለ ጥልቅ አንድምታ አለው። ምክንያቱም አፍሪካውያን በባርነት ቀንበር ስር ሲወድቁ የነፃነት ችቦ ያበራች፤ ክብራቸው ሲነካ፣ ነፃነታቸውን ሲያጡ በአትንኩኝ ባይነት መንፈስ ለጥቁሮች የነፃነት ጀምበር የፈነጠቀች አገር መሆኗ ነው።
ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትዋን የሚዳፈሩ የውጪ ጣልቃ ገብነቶች በመቃወም በዓለም አደባባይ ከጥቂት ወዳጅ አገራት ጋር በመሆን ስትሞግት ሙገታዋ ስለራስዋ ነፃነት ብቻ አልነበረም፤ ስለ መላው አፍሪካም ጭምር እንጂ። ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ኃያላን ሌላው ላይ እንደለመዱት ሁሉ በውስጥ ጉዳይዋ ገብተው ይህን አድርጊ፣ ፈቅደናል፤ ያን አታድርጊ፣ ኮንነናል ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑ በሚገባቸው ቋንቋ ነግራቸዋለች።
አገሪቱ ኢትዮጵያ መሆኗንም እንደዛው። ልክ እንደ አድዋው ሉዓላዊነትዋን ድጋሚ ሊንዱ የፈለጉትን ኃያላን በመሞገት በአገራዊ ጉዳይዋ እራስዋ ብቻ የመወሰን መብት ያላት መሆንዋን አስመስክራለች።
በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ እጃቸውን እንዳሻቸው ለሚሰነዝሩት ምዕራባውያን ትምህርት መሆን የሚችል ፅናትና አንድነት በሕዝቧ ውስጥ የሰረፀ በመሆኑ ችግሮቿን ሁሉ በድል ተወጥታቸዋለች። “አለቀላቸው” ያሉት አንድነታችን፤ መች በእናንተ ተጀመረና ነው በእናንተ የሚያልቅልን በማለት ጉዞዋን ቀጥላለች።
እጅጉን የበረከተ ጫና ከውጪም ከውስጥ ተቀነባብሮባት በጠንካራ ልጆችዋ መስዋዕትነት ዳግም ሕልውናዋን በማይናወጥ መሠረት ላይ የጣለች አገር መሆንዋን ያረጋገጠችው ኢትዮጵያ ስለራስዋ ብቻ ሳይሆን ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን ነፃነት ስለመታገሏ ታሪክ ምስክር ነው። ይህንን ደግሞ ሁሉም አፍሪካዊ በሚገባ ያውቀዋል።
ስለ አፍሪካ ነፃነትና ነፃ መሆን ፊት ቆማ የመራች፣ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት በቀዳሚነት የታገለች ወዘተ የነፃነት ቀንዲል መሆንዋን አፍሪካውያን፤ መላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ያውቀዋል።
በዚህች የነፃነት ምድር ስለራሳቸው ለመምከር መሰባሰባቸው ልዩ ትርጉም የሚያሰጠውም ለዚሁ ነው። እርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የራስዋን ጉዳይ በራስዋ ብቻ መፍታት እንደምትችል፤ የሌላው አገር ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በሉዓላዊነትዋ ላይ ሳትደራደር በፅናት እየታገለች ባለችበት ወቅት ወንድም የአፍሪካ አገራት መሪዎች በዓመታዊ ጉባኤያቸው ላይ ለመታደም መምጣታቸው ታላቅ ድል ነው። የማይናወጥ ወንድማማችነት መገለጫም ነው።
አፍራሽ/አንጋሽ ቀጥረው በተዘዋዋሪ የሚዘውሯት ምድር አፍሪካ “በቃ!!” ማለትን ከጀማሪዋ ኢትዮጵያ አይታለችና “በቃ!!” ልትል መሰናዶ ላይ ናት። እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት የታደለች፣ ከቢሊዮን የሚልቅ የሕዝብ ብዛት ያላት ድንቅ አህጉር አፍሪካ ዛሬም ድረስ በራስዋ አልቆመችም። ከሁሉ በላቀ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና ከራስዋ ተርፎ ለሌሎች የመመገብ አቅም ያላት አፍሪካ ዛሬም እጅዋን ወደ ሌሎች ዘርግታ “እርዳታችሁን እሻለሁ” ከማለት አልተቆጠበችም።
የአፍሪካ ጉዳይ የሚሽከረከረው በሌሎች፤ ስለስዋ እቅድ የሚነደፈው በባዕዳን ነው። የሚበጃትን መርጣ፣ የሚሆናትን ሾማ በሰላም ውላ እንዳታድር በራሳቸው ጥቅም በታወሩ ጣልቃ ገቦች እጅና እግሯን ታስራ ኖራለች። የዳበረ ባህላዊ፣ የራስዋ የሆነ ጎምቱ አስተዳደራዊ ሥርዓት ያላት አህጉር የፖለቲካ ትርምስ መቀስቀሻ፣ የችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርገው ሲጠቅሷት፤ ሁሌም፣ ከገጠማት ችግር ለመውጣት ስትፍጨረጨር ሌላ ችግር ጨምረው ወደ ኋላ ሲመልሷት ነው የኖሩት።
ዛሬ ግን ይህ ሁሉ በቃ!! እየተባለ ነውና “በቃ!!!” (ኖሞር!!!)። ሆን ተብሎ በሚሠራ ሴራ እራስዋን እንዳትችልና የተፈጥሮ ሀብትዋን ተጠቅማ ከችግሯ እንዳትላቀቅ ከሚያደርጓት ባዕዳን ነፃ ወጥታ በምድርዋ ብርሃን እንዲፈነጥቅ፤ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ማድረግ ከመሪዎቿ ጀምሮ የሕዝቦችዋ ዋንኛ ትኩረት መሆን ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ ከ”በቃ!!!”የተሻለ መርህ የለም።
አፍሪካውያን መሪዎች ስለአፍሪካ፣ ስለጋራ ጉዳዮቻቸው፣ ስለጠንካራ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ተቋማት መገንባት፣ ስለለውጣቸው በነፃዋ ምድር ነፃ ሆነው ይመክራሉ። የጥቁር ሕዝቦች መናኸሪያ የሆነችው ውቧ ምድር አፍሪካ ዛሬ ላይ ነፃነትዋን ብታውጅም፤ ሙሉ ነፃነትዋን በእውን አልተቀዳጀችም።
አሁንም በጥንት ገዢዎችዋ ግፍ የሚዋልባት አህጉር ናት። በዚህም ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ላይ ላዩን ነፃ ናችሁ የተባሉት በርካታ የአፍሪካ አገራት ዛሬም በእጅ አዙር ግዞት ውስጥ ናቸው። ፖለቲካና አገራዊ ሁኔታቸው የሚዘወረው በምዕራባውያኑ ነው። ለዚህ ነው አፍሪካ “በቃ!!!”ን ይዛ መነሳት ያለባት መሆኑ በከፍተኛ ደረጃ አፍሪካዊ ስምምነትን ያገኘው። ለዚህ ነው በራሷ ወስና ስለራሷ መቀመር ያለባት መሆኑ በደማቁ የተሰመረበት።
አፍሪካ በስዋ ልኬት ስለራሷ የተሰፉ መገለጫዎች ስለ እሷ ቁመና በትክክል የሚያንፀባርቁ ማንነቶችና ነፃነቶችን መጎናፀፍ አለባት። ከሩቅ ጣልቃ ገቦች ተጠብቃ በራስዋ መራመድ እንድትችል የልጆችዋ ኅብረት ያስፈልጋልና የጀመሩት የአብሮነት ድክድክ ወደ ሶምሶማ መቀየር፤ ከዚያም ወደ ታላቁ ሩጫ .…. የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለባት በራስዋ የቆመች ጠንካራ አፍሪካ በመፍጠሩ ሂደት የዛሬዎቹ መሪዎች ታላቅ ኃላፊነት አለባቸው። ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ እያላት በዓለም አቀፍ መድረኮች ድምፅዋን ከፍ አድርጋ የምታሰማበት መድረክ ስለምን ተነፈገች? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊፈልጉለት ይገባል።
አህጉሪቱ ከውጪ ጣልቃ ገብነት የምትላቀቀው እንዴትና በምን መንገድ ነው? አፍሪካውያን አንድ ሆነው ጠንክረው እንዳይቆሙ ያደረጋቸው ዋናው ጉዳይ ምንድነው? ብለው መወያየት ይገባቸዋል። ስለ አፍሪካ እሩቅ ያለው ዓረብ ሊግ ሲወስን ስለምን እኛ ዝም አልን? ብለው እራሳቸውን መጠየቅ ይጠበቅባቸዋል።
መሪዎቹ ከምንግዜውም በላይ ስለ አህጉሪቱና ሕዝቦችዋ በጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር ይገባቸዋል።
የመሰረቱዋቸው፣ የአፍሪካ ኅብረትን የመሳሰሉ ተቋማት በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ለማድረግ ምን ሊደረግ ይገባል? ብለው መምከር ያሻቸዋል። አንዲት ጠንካራ አህጉር እንደሌሎቹ ከፊት ተሰልፋ የምትቆም፣ ዓለም “አፍሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አለች?” የሚልላት አህጉር ልትፈጠር ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው። ይህ ታላቅ ሕዝብና አህጉር የፀጥታው ምክር ቤት ላይ ስለምን ቋሚ መቀመጫ ተነፈገ? ስለምን የዚህች አህጉር ሕዝብ ከሌላው ውሳኔና ፍቃድ ነፃ ሳይሆን 20ኛው ክፍለ ዘመን ያበቃል? ብለው መጠየቅ፤ የማንቂያ ደወልንም መደወል ከዚህ ጉባኤ ይጠበቃል። እርግጥ በአህጉሪቱ አንዳንድ ብርቱ መሪዎች አህጉሪቱ የሚገባትን ለማድረግ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል።
ይህ ግን የሁሉም አፍሪካውያን መሪዎች መርህና የማይናወጥ አቋም ሊሆን ይገባል። ጉዳዩን ወደ ሕዝቡ ማጋባትና እውናዊ ነፃነትና መብት የተረጋገጠበት ፍትሐዊ ዓለም የመመሥረቱ ሂደት የጋራ ጉዳይ፤ የሕዝብ ጉዳይ፤ የመላው አፍሪካውያን ጉዳይ ማድረግ ይገባል። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው እጅግ ገዝፎ የመጣን ኃይል በተለያየ ዘመናት ተጋፍጠው አገራቸውን ጠብቀው እዚህ አድርሰዋል። አሁንም እየሆነ ያለው ይሄው ነው።
ሌሎች አፍሪካውያንም ልክ አድዋ ላይ ኢትዮጵያ ነፃነትዋን በወራሪዎች እንዳታጣ ያደረገችው ፍልሚያና ድል መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ሁሉ፤ ዛሬም የኢትዮጵያን እንቢታና አልደፈር ባይነት መላበስ ይገባቸዋል። አፍሪካውያን በጋራ ከቆሙ የሚያስቆማቸው ኃይል እንደሌለ ማመን ይኖርባቸዋል።
ታቅፈውት ያለውን የተፈጥሮ ሀብታቸውን እንዳይጠቀሙ ያደረጋቸው የእርስ በርስ መጠላለፍ፣ ኋላ ቀር አስተሳሰብና የእርስ በርስ ግጭት ዛሬ ሊቆሙ እንደሚገባ ሊወስኑ፣ ወስነውም ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል። የዘለዓለም ዓለም እሺታ ማንንም አልጠቀመምና የአሁኑ ዘመን መሪዎች ታሪክ ሊሰሩ ይገባል።
በጋራ ምክራቸው የዲሞክራሲ ተቋማቶቻቸውን ማጠንከር የጋራ መግባቢያ ስምምነቶቻቸውን መተግበር፣ አንድ ሊያደርጋቸው የሚችል ጥምረታቸውን ማጠንከር የዛሬዎቹ የመሪዎች ድርሻ መሆን ይገባዋል።
መቀበልን በመስጠት የሚለውጥ፣ ባርነትን በእውነተኛ ነፃነት የሚቀይር አዲስ ትውልድ አፍሪካ ውስጥ መፈጠር አለበት። ለዚህ ደግሞ ምቹው ጊዜ ዛሬ ነው። ምቹው ስፍራ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ነው። ውድ ኢትዮጵያውያን! አፍሪካውያን ወንድሞቻችን “አገራችን” ወደ’ሚልዋት የነፃነት ምድሯ ኢትዮጵያ እየመጡ ነውና በክብር ተቀበሏቸው።
በነጠረ ሰው አክባሪ ባህላችሁ፤ በዳበረ የአንድነት ስሜታችሁ፤ የአፍሪካን ጉዳይ በራሳቸው አፍሪካውያን ሊያዩ አህጉራችሁ የሚበጃትን የሚመክሩ ድንቅ አፍሪካውያን ወደ መዲናችሁና መዲናቸው እየመጡ ነውና ድንቅ እሴታችሁን አሳዩ። እነዚያ ሰላም የላትም ብለው በሩቅ የሚያወሩባት አገራችሁ ፍፁም ሰላም የተላበሰች ምድር መሆንዋን ሰላምዋን ይበልጥ በመጠበቅ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችሁ አሳዩ።
አፍሪካ የማንንም ጣልቃ ገብነት የማትፈልግ ነፃ ምድር መሆንዋን አፍሪካውያን እንዲያውጁ፤ ለዚህም ተግተው እንዲሰሩ ሀሳባችሁን አካፍሉ።
እናንተም ኢትዮጵያ ብላችሁ ፀንታችሁ እንደቆማችሁ ሁሉ፤ ነፃነታችሁ ለመላዋ አፍሪካ ይሆን ዘንድ ትጉ። አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014