ከዓመት በፊት ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ከተማ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ለምስክርነት የተጠራ አንድ ግለሰብ ፍርድ ቤት ሲደርስ ከሰጠው የምስክርነት ቃል በመነሳት በዚያው ቅጽበት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖር ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ለምስክርነት የተጠራበት ጉዳይ ግን ተጠራቶ ወር ባልሞላ ጊዜ ውሳኔ ያገኛል፡፡ ይሁንና ለምስክርነት የተጠራው እና በዚሁ ምክንያት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ የሚያስታውሰው ይጠፋል፡፡ ይህ ሰው አንዳችም ጥፋት ሳይገኝበት ለአንድ ዓመት ማረሚያ ቤት ይቆያል፡፡ በየጊዜው ለማረሚያ ቤቱ ‹‹ያለአግባብ ታስርኩ›› እያለ አቤት ቢልም ሰሚ ጆሮ ያጣል፡፡
በሂደት ይህ መረጃ ጋዜጠኛ ብዙዓለም ቤኛ ዘንድ ይደርሳል፡፡ ብዙዓለም ጉዳዩን ይዞ ወደ ማረሚያ ቤቱ በመሄድ መረጃውን አጣርቶ በዜና ለህዝብ ተደራሽ አደረገ፡፡ ጉዳዩ መገናኛ ብዙሃን ጆሮመድረሱን የሰሙት የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ሌሎችም በቅፅበት ለታራሚው ትራንስፖርት በመስጠት ከአካባቢው እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ ብዙዓለም በሌላ ጊዜ ጉዳዩን ከምን ላይ እንደደረሰ ለመከታተል ወደማረሚያ ቤቱ ሲሄድ ሰውየው የለም፣ ምን ፍርድ ተሰጠው የሚለውን መረጃ ለማግኘት ቢሞክርም መልስ አላገኘም፡፡ በዚህ ሁኔታ ጋዜጠኞች መረጃ ለማድረስ በሚተጉበት ጊዜ መረጃ የመከልከል አሊያም ደግሞ የፍርድ ሂደቶች በግልፅ ያለመናገር እንዲሁም ጋዜጠኞች የችሎትና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመዘገብ ፈተና እንደሚሆንባቸው ይናገራል፡፡
ላለፉት ሰባት ዓመታት የችሎት ዘገባን በተከታታይ ሲሠራ የነበረው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ገመቺስ ታሪኩ በኢትዮጵያ ውስጥ የፍርድ ቤት ውሎና የችሎት ዘገባዎች ማስተላለፍ ፈታኝ መሆኑን ይናገራል፡፡ ችሎቶች ለጋዜጠኞች ምቹ ካለመሆናቸው በተጨማሪ በተቋማቱ አካባቢ መረጃ የመስጠት ባህሉ ደካማ ነው፡፡ መረጃዎችን በሬዲዮ ወይንም በቴሌቬዥን በቀጥታ ማስተላለፍም ከባድ ፈተና ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በችሎት ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንኳንስ ጋዜጠኞች በሥርዓት መረጃ የሚያገኙበት ቀርቶ ለችሎት ታዳሚም በቂ የመቀመጫ ቦታ የለም፡፡ ችሎቶቹ ሲገነቡም ይህን ታሳቢ ያደረጉ ባለመሆናቸው መረጃ ለማስተላለፍ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
ጋዜጠኛ ገመቺስ እንደሚለው፤ በአንዳንድ ጋዜጠኞችም ረገድ የችሎት ውሎን ሚዛናዊ ዘገባዎችን ከመስራት አኳያ ዳተኝነት ይስተዋላል፡፡ የፍርድ ቤት ዘገባን ሲዘግቡ ዳኞችን እንደ ምንጭ መጠቀም ይገባል፡፡ ከፍርድ ውሳኔዎች ህብረተሰቡ እንዲማርበት እና ከጥፋት እራሱን እንዲያቅብ ከጥቂት ዳኞች በስተቀር በርካታ ዳኞች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆንና መገናኛ ብዙሃን አውታርን መሸሽ የተለመደ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃን አንዳንድ ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ ወንጀለኛ አስመስሎ በማቅረብ የጋዜጠኞችን ክህሎት ጥያቄ ውስጥ ያስገባሉ፡፡ በርካታ አገራት የፍርድ ቤት ዘገባዎችን ለማሳየት ‹‹ካርቱን›› እና ሌሎች ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ በመሆኑ በበርካቶች ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ ነው፡፡ በአጠቃላይ የዳኞች ለመረጃ ቅርብ አለመሆን፣ ችሎቶች ለመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ምቹ አለመሆንና ከዘመኑ ጋር አለመዘመን ጋዜጠኛውን የሚፈትኑ እንደሆኑ ይገልፃል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ዶክተር ንጉሴ ጌታቸው፤ ፍርድ ቤት ውሳኔን ለመስማት ወደ ችሎት ሁሉም ዜጋ ስለማይገባ ትክክለኛ መረጃ በጋዜጠኞች በኩል ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችም መረጃዎችን በተደራጀ እና አስተማሪ በሆነ መንገድ ከአድሎ ነፃ በመሆን ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሁንና የጋዜጠኝነት ሙያ አለመዳበር፤ የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት እና አሰራር ከመገናኛ ብዙሃን ጋር አለመናበብ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት አለመዳበር እና ሌሎች ምክንያቶች ችሎት ዘገባ እና ጋዜጠኝነት በቀላሉ እንዳይናበቡ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞች የችሎት አዘጋገብ ላይ ያላቸው ክህሎት ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከተቋማት እና ግለሰቦች ክብር ጋር የተቆራኙ ተግባራትን በጥንቃቄ ከመዘገብ አኳያ ግድፈቶች በተደገጋሚ ይከሰታሉ፡፡
የችሎት አዘጋገብ እና ሙያዊ ቃላትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድም ሰፊ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችም ሆኑ ፍርድ ቤቶች የተናበበ አሰራር መከተል እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ ኑሬ በበኩላቸው፤ የህግ በላይነት እንዲከበር ጋዜጠኞች፣ ፍርድ ቤቶችና እና ሌሎች ተቋማት በመናበብ መስራት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ፡፡ በአንድ አገር ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት እንዲኖርና ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሚዲያ በችሎት ዘገባ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሚዲያው የለውጥ አካል ካልሆነ ለውጡ የተፈለገውን ግብ በታሰበው መጠን እንደማያሳካ የሚናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ረገድ ጋዜጠኞችም ሆኑ ፍርድ ቤቶች ከባድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ፍርድ ቤትም ሆኑ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የህዝብ ተቋማት እስከሆኑ ድረስ ለህዝብ ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ ሁለቱም ተቋማት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣትም የድርሻቸውን እንዲወጡ ያሳስባሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር