አገር በግለሰቦች አስተሳሰብ የቆመች የብዙ አመለካከቶች ድምር ውጤት ናት። የአገራችን አሁናዊ መልክ በእኛ በልጆቿ አስተሳሰብ የተፈጠረ ነው። በመኖራችን ውስጥ የምንከውናቸው እያንዳንዱ ሕይወታዊ እንቅስቃሴ በአገራችን ነጋዊ መልክ ላይ የራሱን አሻራ ያሳድራል። እናም እንደአስተሳሰባችን ዓይነት የምንፈጥረውም ሆነ የምናጠፋው ሕዝባዊ ታሪክ አለ። አሁን ላይ በአገራችን እየሆነ ያለውም ትላንት ላይ በተሳለ አዳፋ ስዕል ነው።
በጊዜአዊ ጥቅም፣ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት የሳልናቸው እኩይ ምስሎች ዛሬ ላይ እያሰቃዩንና ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። ዛሬን ብቻ የምንኖር የሚመስለን ብዙዎች ነን። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ብለን ታሪክና ትስስር የምናበላሽም ሞልተናል። ዛሬ ላይ ሆነን ነገን አሻግረን ባለማየታችን ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ እየከፈልንም እንገኛለን። ከዛሬ ቀጥሎ የሚመጣ ሌላ ቀን አለ። ከእኛ ቀጥሎ በሚመጣው ቀን ላይ ለሚፈጠረው አዲስ ትውልድ ማሰብና መጨነቅ ነው ጀግንነት።
ጊዜው የእኛ ነው ብለን የምንሠራው እያንዳንዱ በደልና ግፍ ቀን ቆጥሮ ነገ ላይ ዋጋ ያስከፍለናል። የምንከፍለው ዋጋ ደግሞ ቀላል አይደለም።
የአገራችን መልክ የእኔና የእናንተ መልክ ነው። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን የሆነችው በእኔና በእናንተ ብዙ መልክ፣ ብዙ አስተሳሰብ ነው። ከዚህ አኳያ መልኳን የሚያሳድፍ አንዳች ነገር ማድረግ ነገ ላይ የበዛ ዋጋ ያስከፍላል።ዋጋ የሚያስከፍለውም የተደረገበትን ብቻ ሳይሆን አድራጊውንም ነው።
ከትምህርት ቤት ስንቀር፣ ከሥራ ገበታችን ስናረፍድ የአገራችንን ጸዐዳ መልክ እያጠየምን ነው። ጥቅም ለማግኘት እጅ መንሻ ስንሰጥና ስንቀበል አገር እያሳደፍን ነው። በሙያችሁ ኃላፊነት ሲጎድለን፣ የአገርና የሕዝብን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባራትን ስንፈጽም ያኔ አገራችንን እያዋረድን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።ለሕዝብ ግልጋሎት የተሠሩ መሠረተ ልማቶችን ስናወድም፣ በውሸት ትርክት በሕዝቦች መካከል ጥላቻና መለያየትን ስንፈጥር ያኔ አገራችንን እየገደልናት ነው።
ዛሬ ላይ አገራችን ላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ብዙ ነገር አድርገናል።የእኔና የእናንተ አስተሳሰብና አመለካከት በአገራችን ህልውና ውስጥ አለ።የምንሆነው እየሆንነው ያለነው ማንኛውም ነገር በለውጡ ኃይል ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ አለው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በዜጎቿ ትላንታዊ አስተሳሰብ ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ የምትፈጠረውም በዚሁ በእኛ በዜጎቿ አስተሳሰብ ነው።
ስለሆነም ምንድነው የምናስበው? ምንድነው እየሆንን ያለነው? አሁናዊ ሁኔታችን ምን ይመስላል? ቤተሰቦቻችን የሚያስተምሩን፣ ትምህርት ቤት መምህራኖቻችን የሚሰጡን ዕውቀት ምን ዓይነት ነው? የኢትዮጵያን ጥንታዊ መልክ በሚያውቅ ማህበረሰብ ውስጥ ነን? የምንኖርበት አካባቢ መልካሟን ኢትዮጵያ ለመፍጠር አስተዋጽኦ አለውን? ይሄን ሁሉ ጥያቄ መመለስ አለብን።
ነገ እንድትኖረን የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ነው ያለችው።ፍቅር በማያውቅ ቤተሰብ ውስጥ ከሆን፣ መምህራኖቻችን ነገ ጥሩ ዜጋ ሆነን እንድንበቅል የሚያደርግ ዕውቀት እየሰጡን ካልሆነ፣ ሰፈራችንና አካባቢያችን ለነጋችን ማማር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ካልሆነ ነገ ላይ ችግር ፈጣሪዎች ሆነን ስለማደጋችን ጥርጥር የለኝም።ዛሬ ላይ የምንሆነውና እየሆንን ያለነው ነገር ሁሉ የእኛንም ሆነ የአገራችንን መጻኢ እድል የሚወስን ነው።
አገራችንን እንደፈለግን አድርገን የምንስላት እኛ ነን። እጃችን ላይ ያለው ብሩሽ ምን ዓይነት ነው? ቀለማችን፣ ሀሳባችን ምን ዓይነት ነው? መልካም አገር ለመፍጠር መልካም ቀለምና መልካም ሀሳብ ያስፈልገናል።
ከሁሉ በፊት አስተሳሰባችንና አመለካከታችንን እንፈትሽ፣ እናጥራ። ለአገራችን የሚሆን ብዙ እውነትን ከልባችን ውስጥ እናፍልቅ። የእኔና የእናንተ ለውጥ የአገራችን ለውጥ ነው። የእኔና የእናንተ አዲስነት የአገራችን አዲስነት ነው።
እኔና እናንተ ሳንዘምን የምትዘምን አገር አትኖረንም። እኔና እናንተ ሳንሻሻል የሚሻሻል ማህበረሰብ አይኖረንም። ከሁሉ በፊት እኛ መለወጥ አለብን። የአገራችን ለውጥ በእኛ ለውጥ ውስጥ ነው የሚፈጠረው።
እስካሁን ድረስ ባልተለወጠ አስተሳሰብ ያልተለወጠች አገር ታቅፈን ኖረናል። የሚበጀን እያለ በማይበጀን ነገር ላይ እየተባላን ብዙ የስኬትና የለውጥ ዓመታትን በከንቱ አሳልፈናል። የሚጠቅመን እያለ በማይጠቅመን ነገር ስንጋፋ አስቀያሚ ዛሬን ፈጥረናል።
ነገ የእኛ እንዲሆን እሻለሁ። ነገ እውነት የምንጽፍበት፣ የአገራችንን ውብ ስዕል የምንስልበት የኢትዮጵያና የሕዝቧ የከፍታ ዘመን እንዲሆን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። አሁን እጃችን ላይ ባለው አሁናዊ ወርቃማ ዕድል የነገዋን መልካሟን ኢትዮጵያ እንፍጠራት።እጃችን ላይ ባለው ብርሃናማ ዕድል ነገን የሚረከብ ብርሃናማ ትውልድ እንፍጠር።
እጃችን ላይ ባለው ዥንጉርጉር ቀለም የጥቁርና የነጻነት ምድር ለሆነችው ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ውብ ምስል እንፍጠር። ያቺን ምኒሊካዊቷን የነጻነት ተምሳሌት የጥቁር ዕንቁ፣ አብዲሳ አጋይቷን እመቤት፣ የዘርዐይ ደረስን ምድር፣ የበላይ ዘለቀን እርስት እውነተኛይቱንና ታላቋን ኢትዮጵያ እንፍጠር።ያንን ስልጡን ባለታሪክ ሕዝብ በዳግም ልደት እናስነሳው።
ሁላችንም እንደምናውቀው የአገራችን አሁናዊ መልክ ደብዛዛ ነው።ትላንትናዊ ውብ መልኳ የለም።ወደ ከፍታ እየሄደች መሆኗን የተመለከቱና ይህንን ከፍታዋን የማይፈልጉ አንዳንዶች ወደኋላ ሊመልሷት እየጠመዘዟት ነው።የአድዋን አይነት ህብረ ብሔራዊ ጀግንነትን ልትሠራ ባንሰራራችበት ወቅት ወደኋላ እየጎተቷት ነው። የኢትዮጵያ መነሳት የአፍሪካ መነሳት መሆኑ የገባቸውና ያስደገገጣቸው ምዕራባውያን እየሄድንበት ባለው የብልጽግና ጎዳና ላይ እኩይ ማሰናከያቸውን እያስቀመጡብን ነው።
የአንድነታችን ነጸብራቅ፣ የትንሳኤአችንን አብሳሪ፣ የተስፋችን ምልክት ሁሉም ነገራችን የሆነውን ሕዳሴ ግድባችንን እንዳንገነባ የነገር ሸር የሚሸርቡብን ብዙ ናቸው። አገራችን ከውስጥና ከውጭ ብዙ መከራና ችግሮች ከብበው ውብ መልኳን አጠይመውታል።እናስ ምን እያደረጋችሁ ነው? እናንተስ በምን ሕይወታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ናችሁ? ለአገራችን መልካሙን ሁሉ ለማድረግ ትክክለኛው ሰዓት ላይ ነን።
አገራችንም ሆነ ሕዝባችን ከችግር ለማውጣት ከዚህ የተሻለ ምቹ ጊዜ አናገኝም። ጠላቶቿን በመታገል የጀመረችውን የተስፋ ጎዳና እንድታይ ሁላችንም አለንልሽ ልንላት ይገባል። በአንድነት በመቆም ጠላትን ማሳፈር እንችላለን። የትላንቷ ትልቅ አገር በአንድነት በቆሙ ቅን ነፍሶች የተፈጠረች ናት። እርግጥ ነው በግራና በቀኝ ብዙ ጠላቶች ተነስተውብናል።
ሆኖም ጠላትን በማሳፈር ዳግማዊ ዓድዋን የምንሠራበት፣ የጥንቷን ታላቅ ኢትዮጵያ የምንገነባበት ዕድልም በእጃችን ላይ ይገኛል። ይህም አንድነታችንና ሕብረታችን ነወ። እናም በአንድነትና በሕብረት ለጋራ ጥቅም መቆም ግድ ይለናል። የሕዳሴ ግድባችንን ጨርሰን ሌላም ለመገንባትና የአገራችንን ታላቅነት ዳግም ለማረጋገጥ አንድነታችንና ሕብረታችን ዛሬም አማራጭ የሌለው ኃይላችን ነው።
አገራችን የምትለወጠው በአሜሪካና በቻይና ወይም ደግሞ በሌላ ጎረቤት አገር እርዳታ ሳይሆን በእኔና በእናንተ አንድነትና ሕብረት ነው። አንድነት ምን ያክል ኃይል እንዳለው ከእኛ ሌላ ምስክር አለ ብዬ አላምንም። ከየትኛውም አገርና ሕዝብ በላይ ስለአንድነት በኩራት መናገር የምንችለውም እኛው ነን ብዬ አስባለሁ።ለዚህ ደግሞ በአንድነታችንና በተባበረ ክንዳችን ያስመዘገብነውንና መላው የጥቁር ሕዝብ ቀና ያለበት፣ የበላይ ነን ብሎ ያስብ የነበረው መላው ነጭ ደግሞ የተዋረደበት፣ የጥቁሮች የይቻላል መንፈስ ያበበበትና የተጀመረበት ታሪካዊ የዓድዋ በማሳያነት ማቅረብ እንችላለን።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ጣሊያንን የማሸነፏን ሚስጢር ለማወቅ ነጮቹ ዛሬም ድረስ ምርምር ላይ ናቸው። ከመቶ ዓመታት በኋላም የኢትዮጵያን የታላቅነት ምስጢር ለማወቅ ጣሊያኖች እንቅልፍ አልተኙም።ሆኖም በመጨረሻ የኢትዮጵያን የአሸናፊነት መሠረት አንድነት መሆኑን ሁሉም ገብቷቸዋል።ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆን ባይችሉ ኖሮ ዛሬ ላይ የዓድዋ ታሪክ የጣሊያኖች ታሪክ ይሆን ነበር የሚሉም ብዙዎች ናቸው።አንድነት ምን ያክል ኃይል እንዳለው ከዚህ የበለጠ ማሳያ የለም።
ይሄ ሁሉ የሆነው በአንድነታችንና በሕብረታችን ነው። ይሄ ሁሉ ታሪካዊ ድል የተመዘገበው በአንድነት በቆሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ነው።አሁንም ከፊታችን የተጋረጠውን አሁናዊ የጠላት በትር በለመድነው አንድነታችን በመመከት ዳግማዊ ዓድዋን መጻፍ እንችላለን። መገንባት ለምንፈልጋት የነገዋ ታላቅ አገራችንም የመጨረሻው አማራጫችን አንድነታችን ነው።
ኢትዮጵያ ያልተለወጠችው እኛ ስላልተለወጥን ነው። የአገራችን መለወጥ ከእኛ መለወጥ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። አገር አይደለችም እኛን የምትለውጠን እኛ ነን በለውጣችን አገርን የምንለውጠው። ይህንን የምናሳካው ደግሞ አስተሳሰባችን፣ አመለካከታችንና የኑሮ ዘይቤአችንም በመለወጥ ነው። ለዚህም ከአካላዊ ለውጥ በመውጣት ወደ አእምሯዊ ለውጥ መሸጋገር ይጠበቅብናል።ምክንያቱም ብዙዎቻችን ለውጥ ሲባል የአካል ለውጥ ስለሚመስለን ነው። በአካል ስላደግንና ስለጎለመስን የተለወጥን የሚመስለን ብዙዎች ነን። ቁመት እያየን፣ አካላዊ ለውጣችን እየተመለከትን አደገ፣ አደገች ማለት የማህበረሰባችን አንዱ ባህሪ ነው። ለዚህም ነው ከነበርንበት መንቀሳቀስ ያልቻልነው።
ይሁን እንጂ አካላዊ ለውጥ ተፈጥሯዊ ለውጥ ነው።ምክንያቱም ስንፈጠር በራሱ ተወልደን እንድናድግ፤ አድገንም እንድንሞት ነው የተፈጠርነው። እውነተኛ ለውጥ ግን በአካል ውስጥ ሳይሆን በአእምሮ ውስጥ የተደበቀ ነው። እርግጥ ነው በአካል ስናድግ በአእምሮም፤ ይሄ ግን ብዙ ጊዜ አይሰራም።ለምን ቢሉ በአካል አድገውና ሁለት መልክ ጸጉር አብቅለው ያላደጉና ሁሌም እንደ ህጻን የሚያስቡ ሰዎች ሞልተዋልና ነው። በዛው ልክ በትንሽ እድሜአቸው እንደ ትልቅ ሰው የሚያስቡ የልጅ አዋቂዎች መኖራቸውም ሐቅ ነው።
በመሆኑም የአካል ለውጥ ስልጣኔን አያመጣም።ዕድገትና ስልጣኔ ያለው አእምሮ ውስጥ ነው። ለአካላዊ ዕድገትማ በተዘጋ ቤት ውስጥ፣ ያለ እናት ተኑሮም ማደግ ይኖራልና። ዋነኛው የለውጥ ኃይል ያለው ልብ ውስጥ ነው። በአእምሯችን እንደግ፣ በልባችን እንለወጥ። በሕይወታችን ውስጥ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች አስፈላጊዎች የምንሆነው አእምሯዊ ልህቀት ሲኖረን ነው። ይህ ባለመሆኑ ለችግሯ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በአገራችን አሁናዊ ሁኔታ የምንዘባበት ብዙዎች ነን።ይሄ የአእምሮ ዕድገት ባለመኖሩ የተፈጠረ ነው።በአካል ስለጎለመስን፣ ከአንተነት ወደ አቶነት ስለተሸጋገርን ወይም ደግሞ አንቱታን ስላገኘን ትልቅ ነን ማለት አይደለም።
ትልቅነታችን የሚመዘነው በትልቅ አስተሳሰባችን ነው።ትልቅ የምንባለው ለአገራችሁና ለሕዝባችን የሚሆን በጎ አሻራ ሲኖረን ነው። በአካል ስለተለቅን በአእምሮም ትልቅ ነን ማለት አይደለም። ዛሬ ላይ ሸብተውና ጎልምሰው አንቱ በተባሉ ሰዎች ነው መከራችንን እያየን ያለንው። አገራችን በአብዛኛው አበሳዋን እያየች ያለችው አንቱታን ባገኙ የትልቅ ትንሾች ነው። በጎ የሚያስብ ሰው ነው ትልቅ የሚባለው። በጎ በማሰብና በጎ በመሥራት በመልካም አስተሳሰብና በጎ ሥራ እጥረት አበሳዋ ለበዛው አገራችን አለኝታ እንሁናት።
እኛ ለአገራችን ሁሉ ነገሯ ነን።መከራና ደስታዋ በእኛ በኩል የሚመጣ ነው። እኛ ለአገራችን ቅርንጫፎች ነን።እኛ ለትውልዱ ብዙ ፍሬ ብዙ አበባዎች ነን።እኛ ብዙ ተስፋ ብዙ እውነት ነን።ግንዱ ጸንቶ ይቆም ዘንድ እናስፈልጋለን።አገራችን ግንዳችን ናት። የቆምንው በእሷ ላይ ነው።ወጥተን የምንገባው፣ አግብተን የወለድነው፣ ብዙ ራዕይ ሰንቀን በተስፋ የምንጓዘው እሷ ስላለች ነው። እናም አላዋቂነት የወለደው የክፋት ምሳራችንን እንጣል። አገር መገዝገዛችንን እንተው።
ዋርካ ሆና ለብዙዎቻችን ታጠላ ዘንድ እንባርካት። አንድ ዛፍ ያለ ስር፣ ያለ ቅርንጫፍ፣ ያለ አበባና ፍሬ ብቻውን ዛፍ መሆን አይችልም። አገራችን ዛፍ ናት።እኔና እናንተ ደግሞ ስርና ቅርንጫፎቿ፣ ፍሬና አበባዎቿ ነን። በዚህ እውነት ውስጥ ነን። በዚህ ስርዓት ውስጥ ነን። ከአካል ስልጣኔ ወጥተን አእምሯዊ ስልጣኔን ተላብሰን፤ ለሌሎች አስፈላጊዎች ሆነን እንቁም። በአካል ሳይሆን በአእምሮ መሰልጠንን ባህል እናድርግ። የእኔና የእናንተ ለውጥ የአገራችን ለውጥ ነው። የእኔና የእናንተ ትልቅ መሆን የአገራችንና የሕዝባችን ትልቅ መሆን ነው። አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014