አንዳንድ ጊዜ እንደ ዘበት በአንድ አጋጣሚ በህይወታችን ገፅ ላይ የተፃፈ፣ የተከተበ፤ ሁነት፣ ገጠመኝ፣ ሀሳብ አልያም እውቀት በክፍል ከቀሰምነው ቀለም ይደምቃል። ግዘፍ ይነሳል። የዛሬ አጀንዳዬን ርዕስ የሰማሁበት አጋጣሚ ከ25 አመታት በኋላም ትላንት የሆነ ያህል ይታወሰኛል ።
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በሀገራችን የተፈጠረው ነባራዊ አገራዊ ሁኔታ ይሄን ትውስታዬን ከእንቅልፍ ቀስቅሶታል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ( አአዩ ) ቆይታዬንና በወቅቱ የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የንቅናቄውን መሪዎችና የዋናው ግቢ የ6 ኪሎ ድባብ እና ለዛሬ በአጀንዳነት የመረጥሁት ፅንሰ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበትን አውድ context አስታውሶኛል።
ስለ ተጨባጭ፣ ተግባራዊ፣ ነባራዊ ንድፈ ሀሳብ፣ ኀልዮ (Pragmatic Theory)፤ የሰማሁት ዛሬ ለምገኝበት ፖለቲካዊ ስብዕናዬ ትልቁን መዋጮ ካበረከተው የዛን ጊዜ የተማሪዎች ካውንስል መሪዎች ከአንደኛው ነው። ስሙን የማልጠቅሰው ፈቃደኝነቱ ስለአልጠየቅሁት ነው። ስምየለሹ የተማሪዎች መሪ ደግሞ ማነው !? ማለታችሁ ስለማይቀር ጥቂት ልበል፤ በ80ዎቹ አጋማሽ በአአዩ የተማሪዎች ንቅናቄ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ትንታግ፣ ደፋር፣ አንሰላሳይ፣ አንባቢ፣ አንደበተ ርዕቱ፣ ደማም charismatic መሪዎች መካከል፤ የሲቪል ምህንድስና ተማሪና መካሪዬ፣ አናጺዬ (mentor) ቀዳሚው ነው ።
በህይወቴ እንደ እሱ ያለ በአገር ፍቅር የነደደ ፤ ለነፃነት፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት ቀናዒ የሆነ እና የተሰጠ ወጣት ገጥሞኝ አያውቅም። በወቅቱ በአአዩ የተማሪዎች ዕንቅስቃሴ ስማቸው ገኖ ከነበሩት፤ ከእነ ጋሻው ካሴ፣ አበበ ገላው (“ የበጋው መብረቅ ! “ እለዋለሁ)፤ ለእኔ ስሙን ያልጠቀስሁት የተማሪዎች መሪ ቀዳሚ ነበር።
በወቅቱ ተማሪዎች ላይ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፖለቲካን ፣ ፖለቲካዊ ስብሰባን ሱስ እስከ ማድረግ ደርሶ ነበር። ብዙ ካልተዘመረላቸው፣ ካልተነገረላቸው ጀግኖችም አንዱ ነው። በተማሪዎች ንቅናቄ በነበረው ከፍተኛ ሚና ከዩኒቨርሲቲ ከተባረረ በኋላም በሚፈፀምበት ማዋከብና ማሳደድ ከሚወዳት አገሩ እስከተሰደደባት ዕለት በፖለቲካው በአደባባይም በህቡዕም ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበር።
በመስቀል አደባባይ በተካሄደ አንድ ሕዝባዊ ስብሰባም ካሰማው ዲስኩር፤ “ ኢትዮጵያዊነት ሲበርድን የምንደርበው፤ ሲሞቀን የምናወልቀው ጃኬት አይደለም ! “ ያለው ዛሬ ድረስ በእዝነ ህሊናዬ ህያው ነው ።
በደሙ ውስጥ ሳይቀር ፖለቲካ ዘልቆ የተዋኸደው፤ ከሰው ጋር በተዋወቀ በደቂቃዎች ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ የጦፈ የፖለቲካ ክርክር፣ ውይይት መጫር እና” ፖለቲካንና ኮረቲን በሩቁ “ የሚሉትን ሳይቀር ልብ መማረክ የሚችል ልዩ ተሰጥኦ ነበረው።
በወቅቱ አለም በቃኝ ብላ ከቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም የማትጠፋውን የአጎቴን ባለቤት፤ ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአንድ እጇ ቄጠማ ፣ በሌላ እጇ እነ ጦቢያን ፣ ጦማርን ፣ ኢትዮጵን ፣ ወዘተ . ይዛ እንድትገባ ያደረገ ፤ ጉደኛ ነበር ።
ከእኔ አልፎ ቤተኛ ስለሆነው የትውውቃችን አጋጣሚ መግለፅ በራሱ ሰፋ ያለ ስለሆነ እዚህ ላይ ልተወውና የአጀንዳዬን ርዕስ ከአንደበቱ የሰማሁበትን አጋጣሚ ብቻ ላውጋችሁ ።
ከቀረቤታችን የተነሳ በተፈጠረ መተማመን የተነሳ ከእሱ አልፎ ከተለያዩ ታዋቂና የፖለቲካ ሰዎች ጋር ያስተዋውቀኝ ነበር ። ከአንድ ታዋቂና በወቅቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከነበሩ የሙያ ማህበር መሪ፣ የዩኒቨርሲቲው ሙህርና ፖለቲከኛ ጋር ሊያስተዋውቀኝ ከግቢው ውጭ ወደሚገኝ ቢሮአቸው እየሄደን ስለሰውየው አንዳንድ ነጥቦችን ያነሳሳልኝ ጀመር ።
ሰውየው እስከ ፒ ኤች ዲ የተማሩ የተመራመሩ ከመሆናቸው ባሻገር አንደበተ ርዕቱ ተናጋሪ ናቸው። ሆኖም ሰው ያለድክመት አይፈጠርምና ፁሑፍ ላይ ግን እምብዛም ናቸው። አይዋጣላቸውም።
አንድ ቀን ከውጭ መፅሔት ላይ ስለ Pragmatic Theory የሚተነትን አንድ ፁሁፍ አንብበው ሀሳቡን ለአንባቢ ለማጋራት ቢፈልጉም ለመፃፍ ስለተቸገሩ ፁሑፉን ከመፅሔቱ በመቀስ ቆርጠው በጋዜጣው ላይ እንዲያወጣው ወዳጃቸው ለሆነ ጋዜጠኛ መስጠታቸውን አጫወተኝ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፅንሰ ሀሳቡ በአእምሮዬ ጓዳ ሸልፍ ይኖራል ።
ከአለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በአገራችን የተከሰተው ለውጥ ፤ ይሄን ተከትሎ የተፈጠረው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ የሕወሓት፣ የሙህራን፣ የዲያስፖራው፣ ሚዲያው፣ የአለማቀፍ ማህበረሰቡና የምዕራባውያን አሰላለፍ ፅንሰ ሀሳቡን ማለትም ነባራዊ ኀልዮን በሚዛንነት፣ በማንጠሪያነት ተጠቅሜ፤ ማነው በተጨባጭ፣ በነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ አቋም የሚይዝ፣ ሀቲቱን የሚያዋቅር ብዬ እንድጠይቅ በተቃራኒው ደግሞ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ መሬት ላይ ከአለው ጥሬ ሀቅ ውጭ ከመፃኢ የሀገር፣ የሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም በተቃራኒው የቆመው ማነው የሚለውን፤ በመነፅርነት ልጠቀምበት ከአእምሮዬ ሼልፍ አቧራውን አራግፌ አውርጀዋለሁ ።
ኀልዮው ሰፊና ጥልቅ ፍልስፍና የተሸከመ ቢሆን ለመግባባት ያህል ብቻ እንደሚከተለው እበይነዋለሁ፤ ነባራዊ ኀልዮ የአሜሪካውያኑ ሲ ኤስ ፒርስ እና ዊሊያም ጀምስ የፍልስፍና ንቅናቄ ሲሆን፤ በአጭሩ ሲተረጎምም ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተጠይቃዊና አመክኖአዊ በሆነ አግባብ መከወን፣ መፍታት ነው።
ከፅንሰ፣ ከንድፈ ሀሳብ ይልቅ፤ በተጨባጭ፣ መሬት ላይ ባለ እውነታ፣ በነበራዊ አውድ መመራትን የሚለፍፍ ፍልስፍና ነው። ከዚህ አንፃር አብዛኛዎቹን የአገራችንን የፖለቲካ ልሂቃንን፣ ሙህራንን፣ አክቲቪስቶችን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ኢህአዴግን፣ መገናኛ ብዙኃንን፣ ወዘተ . ስንቃኛቸው ውስንነት ይታይባቸዋል።
ተግባራትን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የመከወን፤ ችግሮችን ከነባራዊ ሁኔታ አንፃር መርምሮ የመፍታት ክፍተት፣ ድክመት የሌለበት ተቋም፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ልሂቃን የለም ከድፍረት እንዳይቆጠርብኝ። በስሜታዊነት፣ በግዕብታዊነት፣ በመንጋ ግፊት፣ በግል ፍላጎት፤ ከምክንያት፣ ከእውቀት፣ ከአብርሆት enlightement ከማድረግ ይልቅ በዘውጉ፤ በተጨባጭ፣ በነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ከመወሰን፣ አቋም ከመያዝ ይልቅ በደመነፍስ በመነዳት ልምሻ ያልተጠቃ የለም። መጠኑ ይለያይ እንጅ አሸባሪውን ሕወሓት ጨምሮ አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ፣ ነባራዊ ሁኔታ በተጠየቅ ፣ በአመክንዮ መርምሮ ፣ ተንትኖ ከመፍታት ይልቅ በአፈተት፣ በአቦሰጥ፣ በግዕብታዊነት መፍታትን ይመርጡ ስለነበር አገራችን የገባችበትን ቅርቃር የምናስተውለው ነው። ትህነግ/ኢህአዴግ ቀደም ባሉት 27 አመታት በሀገሪቱ አንብሮት የነበረውን ኢፍትሐዊነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ ተቋማው ዘረፋ፣ ጎጠኝነት፤ ተጨባጭ፣ ነባራዊ ችግር መሆኑን አምኖ ከመቀበል ይልቅ መካድን ፣ ማስተባበልን በመምረጡ ሀገሪቱንም፣ እሱንም ከማይወጣው አዘቅት ከቶት ነበር።
አገራችንን ዛሬ ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ የዳረጋትም የአሸባሪው ሕወሓት ከነባራዊ ሁኔታ መናጠብ ቀዳሚው ምክንያት ነው ። በአንጻሩ በእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ ኃይል በተሟላ መልኩ ባይሆንም፤ ካለፉት ሶስት አመታት ወራት ወዲህ የአገሪቱን ፣ የፓርቲውን ነባራዊ ፣ ተጨባጭ ሁኔታ መርምሮ ፣ ተንትኖ መፍትሔ
መውሰድ በመቻሉ ዛሬ በተሻለ ተስፋና ዕድል ላይ እንድንገኝ አድርጓል። ይህ የለውጥ ኃይል በአገሪቱ የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የመፍትሔ ሀሳብ ፈለገ ካርታ ይዞ ባይመጣ ኖሩ ሊከተል የሚችለውን ቀውስ፣ እልቂት ባሰብሁ ቁጥር ያባባኛል። ሆኖም የለውጥ ኃይሉ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን አንጥሮ የለየውን ፣ መፍትሔ የሰጠውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አጢኖ እንደ ፓለቲካው የሚመጥን ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ የኑሮ ውድነቱ ፣ ስራ አጥነቱ ፣ የዋጋ ግሽበቱ የፈጠረው ችጋር ፣ እርዛት ፣ እርሀብ ለውጡን ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል ።
ፖለቲካው ላይ የታየው ተስፋ ሰጭ ለውጥ በኢኮኖሚው ቢደገም ኖሮ ለለውጡ የተሻለ ቅቡልነትን ከማስገኘት አልፎ በሕዝቡ ዘንድ የተሻለ መግባባት ፣ አንድነት ይፈጥር ነበር ። ባለፉት 27 አመታት ቀን ከሌት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ሲሰበክ በነበረ የዘውግ ፣ የማንነት ፖለቲካ የተነሳ በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን መጠራጠር ልዩነትም ለማጥበብ ያግዝ ነበር ።
ከፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን መዋቅራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ችግር መፍታት ለውጡን ለማስቀጠልም ሆነ አገራዊ አንድነትን ለመመለስ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተቀብሎ ነገ ዛሬ ሳይባል ተጨባጭ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ።
ፖለቲካው ላይ የሚታዩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለይቶ የተወሰደው በኢኮኖሚው ላይ መድገም ካልተቻለ ለውጡን ሊቀለብሰው ፤ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስደው ስለሚችል በጊዜ የለም ስሜት መረባረብን ይጠይቃል ። ማሻሻያዎች ሁሉን አቀፍ እና መሳ ለመሳ የሚሄዱ ሆነው እንደገና መቃኘት አለባቸው ። ሌላው በብልጽግና አባል ድርጅቶችም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ረገድ ተመሳሳይ ቁመና አለመኖሩ ለውጡን እያገራገጨው ነው ።
የአገሪቱን ነባራዊ ፣ ተጨባጭ ሁኔታ የመገንዘብ ሁኔታው ሆን ተብሎም ይሁን የጠራ ግንዛቤ ካለመጨበጥ የተነሳ ወጥ ባለመሆኑ ለውጡ የተሟላ እንዳይሆን አድርጎታል ። በተለይ አሸባሪው ሕወሓት የአገሪቱን ነባራዊ ፣ ተጨባጭ ሁኔታ ባለመቀበል እራሱ በፈጠረው አለም መኖር በመምረጡ የትግራይ ሕዝብ የለውጡ ትሩፋት እንዳይደርሰው ከማድረጉ ባሻገር ፤ ታጋች አድርጎታል ።
ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይ ዛሬም በትግራይ ፖለቲካዊ ምህዳሩ በትህነግ ልክ እንደተሰፋ ነው ። ዛሬ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ፣ የመሰብሰብ ፣ የመደራጀት መብት እንደተገደበ መሆኑ በአንድ ባንዲራ ፣ ባንድ ሕገ መንግስት ሁለት አገራት ሆነናል። ከፌደራል መንግስት ጋር ያለው ልዩነት ከመጥበብ ይልቅ ይብስ እየሰፋ ሄዶ ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ ለጦርነት ዳርጎናል ።
ይህ የትህነግ የዕብሪት የተስፋፊነትና የማንአህሎኝነት ስሜት ፤ የኢትዮጵያን የማፍረስ እና ለውጡን የማሰናከል አባዜ የአገሪቱን ፣ የቀጠናውን ፣ የአህጉሩን ፣ የአለማቀፉን ነባራዊ ሁኔታ አምኖ ካለመቀበል ፤ ከቁሞ ቀርነት አባዜ የመነጨ ነው ።
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራት ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፣ አክቲቪስቶች ፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ ልሒቃን ፣ የሀይማኖት መሪዎች ፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ ባለሀብቶች ፣ ወዘተ. እያንዳንዱ ውሳኔአቸው ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ያስገባ ተጠየቃዊና ምክንያታዊ ሊሆን ይገባል።
የሚወስዱት አቋም ከአገር ህልውናና ቀጣይነት አንጻር ፤ ከማንነትና ከሀይማኖት ይልቅ ነባራዊ ሁኔታውን በመተንተን ላይ የተመሰረተና አመክኖአዊ ሊሆን ግድ ይላል። እያንዳንዱ ውሳኔአችን በነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የሚተላለፍ ተጠየቃዊ ካልሆነ፤ ስሜታዊና ግዕብታዊ ይሆንና ከሰውነት ተራ ሊያስወጣን፤ ውሎ አድሮም ለጸጸት ሊዳርገን ስለሚችል ብርቱ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
አሸባሪው ሸኔ የአገሪቱን፣ የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ ችላ በማለት በምዕራብ ወለጋና በሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች የፈፀመው ጥፋት፤ ምን ያህል ፖለቲካዊ ዋጋ እንዳስከፈለው ነገ ሒሳቡን ሲሰራ፣ ሲያወራርደው የሚያውቀው ይሆናል።
አሸባሪው ትህነግም ከአገሪቱ ተጨባጭ፣ ነባራዊ ሁኔታ ባፈነገጠ መልኩ እየተከተለው ያለው ፖለቲካዊ አጥፍቶ መጥፋት ትከሻው ሊሸከመው የማይችል ቋጥኝ እንደጣለበት ባያምንም ልቡ ያውቀዋል። አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞችና ልሂቃን እና ሌሎች ሳይቀሩ፤ በለውጡ ማግስት የሽግግር መንግስት ይቋቋም እስከ ማለት ደርሰው ነበር።
ይህ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ ተንትኖ ካለመረዳት የመነጨ ነው። ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ ሰሌዳ ይካሄድ ወይስ ይራዘም የሚለው ጉንጭ አልፋ ሙግትም የዚሁ ቅርሻ ነበር። እውነት ለመናገር ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ኢዜማና አብን፤ ከልሂቃን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ኦቦ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ አይተ አረጋዊ በርሔ፣ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ሌሎች፤ ከማንም በተሻለ ሁኔታ የአገሪቱን ነባራዊ፣ ተጨባጭ ሁኔታ አንጥረው፣ ቁልጭ አርገው ለይተው፤ ይሄንኑ የሚመጥን አቋም የያዙ በመሆናቸው እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። ሁሉም በተለያየ ቋንቋና አበባል ይግለፁት እንጂ ያስቀደሙት ለውጡን ማስቀጠል፤ አገርን ማዳን ነው።
በሂደትም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታዊ እውን እንዲሆን ተቋማት መገንባት እንዳለባቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በማንነት ላይ ከተመሰረተ ፖለቲካ ይልቅ በዜግነትና በሀሳብ ልዕልና ላይ ወደተመሰረተ አደረጃጀት እንዲያዘነብሉ፤ አሁን ያሉት ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ አራትና አምስት ዝቅ ቢሉ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው መነሻ ሀሳብ ማቅረባቸው፤ እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ልሂቃን ምን ያህል በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ተጠየቃዊና አመክኖአዊ መፍትሔ እንዳመጡ መገንዘብ ይቻላል።
እንደ መውጫ በአገራች ዴሞክራሲና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ከማንነት፣ ከዘውግ ፈለፈል (shell) እንዲሁም ከስሜታዊነትና ግዕብታዊነት ተላቀን፤ በአብርሆት፣ በነባራዊ ኀልዮ ላይ ተመስርተን፤ ተጨባጭ ሁኔታውን አንጥረን ለይተን፤ ተጠየቃዊና አመክኖአዊ ውሳኔ ላይ የምንደርስ ከሆነ የሰውነትን እርካብ ተቆናጠን አገራዊ፣ ኢትዮጵያዊ መንበር ላይ እንደርሳለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ነባራዊ ሁኔታውን ሸምጥጠን ክደን ወደ ማንነት ጥፍራችን ገብተን፤ ከተጠየቃዊነት ይልቅ ስሜታዊነትንና ግዕብታዊነትን የመረጥን ለታ እንደ አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ሰው የመሆን ፀጋችን ከመገፈፉ ባሻገር አገራችንን፣ እናታችንን እናሳዝናለን።
ማቅ እናስለብሳለን፣ ትቢያ እናስነሰንሳለን፤ በልጆቻችንም እንደተወቀስን እንኖራለን። አዎ ! ቢዘገይም አልረፈደምና የእስከዛሬው የጥፋት መንገድ በቅቶን፤ ማንነት፣ ዜግነት ወደሌለው ተጠየቃዊነት፣ አመክኖአዊነትና ተግባራዊነት እንመለስ፤ በአምሳሉ የተፈጠርን ሰው ብቻ እንሁን።
የዛን ጊዜ ከራሳችን፣ ከተፈጥሮ፣ ከጎረቤታችን፣ ከአገራችን ጋር እንታረቃለን። በፌስ ቡክ፣ በዩቲውብና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች የበሬ ወለደና የሴራ ፖለቲካ መቅበዝበዝን ትተን መሬት ላይ ባለ ተጨባጭ ሁኔታ በስክነት እንመላለስ ። አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014