ጁንታው ከመነሻው ጀምሮ ህልሙ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልተቧጠጠው ተራራ፤ ያልሸረበው ሴራ፣ ያላጠመደው የተንኮል ወጥመድ እና ያልተከለው የሰላም እና የእድገት ተጻራሪ ጋሬጣ የለም።
ጁንታው ከፍጥረቱ ጀምሮ ያለማጋነን አንድም ቀን ትክክል የሆኑ ስራዎችን ሰርቶ አያውቅም። የስህተት ድሪቶዎችን በላዩ በላዩ መደረት መታወቂያው ነው።
ከስልጣን ሊወገድ ወንበሩ መነቃነቅ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ለስድስት ጊዜ ከባባድ ስህተቶችን ፈጽሟል። እነኚህ ስህተቶቹ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈሉት ብዙዎቻችን የምናውቀው ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። መቀጥቀጥን ቁርስ እና ምሳው ያደረገው ጁንታ ለሰባተኛ ጊዜ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ዳግመኛ ወረራ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ እና እየተነኮሰ ይገኛል።
ለሰባተኛ ጊዜ ስህተት ከፈጸመ የጁንታው ፍጻሜ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ማስጠንቀቃቸው ይታወቃል። አሁን ላይ ጁንታው ለሰባተኛ ጊዜ ስህተት ሊፈጽም እየተንደረደረ ነው።
ይህ ማለት ደግሞ ጁንታው ራሱን የሚያጠፋበትን የመጨረሻውን ሸምቀቆ እየሳበ ነው። ወይም ጁንታው ራሱን በደነበረ የፈረስ ገመድ ውስጥ አንገቱን እያስገባ ነው። አንዳንዴ የጁንታውን አካሄድ በጥሞና የተመለከተ ማንም ሰው ጁንታው ኢትዮጵያን ከማፍረስ ይልቅ የትግሬን ሕዝብ በዋና ጠላትነት ፈርጆ የትግሬን ሕዝብ ለማጥፋት የተነሳ ጉድ ፍጥረት ጋር ማመሳሰሉ የማይቀር ነው። ለዚህም ሁለት አመክንዮችን ማቅረብ ይቻላል።
አንደኛ በትግሬ ሕዝብ ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦችን ማለትም የኤርትራ፣ የአፋር እና የአማራ ሕዝቦችን ጁንታው ለትግሬ ሕዝብ ሆነ ብሎ የገዛለት ጠላቶች መሆናቸው ነው። አሸባሪው ሕወሓት ወደ ስልጣን ለመምጣት እና በስልጣን ለመቆየት ዋነኛ መቆሚያ ዋልታው እና ማገሩ በትግሬ ሕዝብ ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦችን በጠላትነት ፈርጆ የትግሬን ሕዝብ ማጋጨት ነው። የኤርትራን፣ አማራና እና አፋር ሕዝቦችን ጁንታው ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ እንደጠላትነት በመፈረጅ ለማጥፋት ወስኖ የተነሳ ነው። እነኚህን ሕዝቦች ለማጥፋት ደግሞ የትግሬ ሕዝብን በመሳሪያነት እየተጠቀመ ነው።
ይህን የተመለከተ ማንም ሰው ጁንታው የትግሬን ሕዝብ ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ የትግሬ ሕዝብ ዋና ጠላት መሆኑን በቀላሉ እንዲገነዘብ ያስችለዋል። አሁን ላይ የትግሬ ሕዝብ ነግጄ አተርፋለሁ፣ የውጭ ግንኙነት አደርጋለሁ ቢል ከየትኛውም አጎራባች ሕዝብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ዙሪያውን በሕወሓት ሰራሽ የክፋት ፈንጅ ታጥሯል።
አብዛኛው የትግሬ ሕዝብም ጁንታውን የተሰራበትን ደባ ተገንዘቦ ጁንታውን በቃህ ማለት ሲገባው «ሙሽራን ሊሞቀው ሚዜን ልብ ወደቀው» እንዲሉ የጁንታ አመራሮችን እንዲመቻው የትግሬ ሕዝብ ልጆች ለመሰዋዕትነት እያቀረበ ይገኛል።
እንዴት የጁንታውን የክፋት አካሄድ የሚያስተውሉ የትግሬ ተወላጆች የጁንታውን ክፋት በሚመከት ልክ መደራጀት ተሳናቸው? ሁለተኛ ጁንታው የትግሬን ሕዝብ ሊያጠቃ የተነሳ ጉድ ፍጥረት መሆኑን ለመመስከር ጁንታው ከምስረታው ጀምሮ እስከዛሬ በትግራይ ሕዝብ ደም እንዴት እየቀለደ እንደለ መመልከቱ በቂ ነው።
ከምስረታው ጀምሮ የነበረውን እንተውና በአሁኑ ወቅት በተለይም እኔ በጋሸና ግንባር በአይኔ ያየሁትን ብቻ ልጠቁም። በጋሸና ግንባር ጁንታው ያለ የሌለ ሃይሉን አሰልፎ ነበር። በጋሸና አጤ ውሃ በሰው ቁመት ልክ ምሽግ ሰራ። ከጫፍ ጫፍ በሚባል ሁኔታ በምሽጉ ላይ የባህር ዛፎችን ቆርጦ ደረደረ። በባህር ዛፎች ላይ አፈር፤ በአፈሩ ላይ ድንጋይ ደልድሎ ለመዋጋት ሞከረ።
እነኚህ ዝግጅቶች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደማያስጥሉት እያወቀ ኢትዮጵያን ወጋ። የኢትዮጵያ ሰራዊትም የአገርን ሕልውና ለማስቀጠል በእልህ እና በወኔ የሰው ኃይልን ኪሳራ በእጅጉ ባቃለለ መልኩ ተዋጋ። የጁንታው አዋጊዎች ግን ራሳቸውን ከተዋጊው በስተኋላ ደብቀው የድሃ ልጆችን ምንም ወታደራዊ ስልትን ባልተከተለ መልኩ ወደ እሳት ማገዷቸው። በከባድ መሳሪያዎች አረረም እንዳልሆኑ ሆነው ተበሉ።
ጋሸና ከተማ ለመግባት ሶስት ኪሎ ሜትር ሲቀር በነበረው ውጊያ በአስፋልት መንገድ ግራ እና ቀኝ በብዙ ኪሎ ሜትሮች «ራዲዬስ» የተደረደረውን የጁንታ አስከሬን ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም። በጋሸና ግንባር ጁንታው የተመታው ምት ከባድ እና ፋታ የማይሰጥ ስለነበር ከሞት የተረፈው ሃይሉ አስከሬኑን አዝረክርኮ ነፍሴን አውጭኝ ጥሎ ፈረጠጠ።
ይህን ተከትሎ የወገን ጦር ጋሸናን በተቆጣጠርን በበነጋው የጋሸና ዙሪያ አርሶ አደሮች ወንድ፣ ሴት፣ ህጻን አዛውንት ሳይል በነቂስ በመውጣት እና በቡድን በቡድን በመደራጀት በፈረስ ጋሪ የጁንታውን አስከሬን እየሰበሰቡ ሲቀብሩ ተመልክቻለሁ።
የጁንታውን አስከሬን የሚቀብሩ ሰዎች ከአስከሬኑ ብዛት በአንድ ቀን ቀብረው መጨረስ አለመቻላቸውንም ታዝቤአለሁ። ያየሁት አስከሬን ብዛት መቁጠር ባልችልም በብዙ ሺዎች እንደሚቆጠር ግን ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም።
የሚገርመው እና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የምፈልገው ነገር፤ ወደ ውጊያ ገብተው የሞቱት ተዋጊዎች ጁንታው በገፍ በሚሰጣቸው በሃሺሽ ራሳቸውን እንዲረሱ የተደረጉ ናቸው። የጁንታ ተዋጊዎች ተማርከው እጅ ስጥ ይላሉ። ቆስለው ወድቀው ቆስለው መውደቃቸውን ረስተው እጅህን ስጥ ይሉ ነበር። ጁንታው ተዋጊ ሃይሉን ሃሺሽ እያበላ በዚህ መልኩ ሲያሰልፍ ስመለከት ጁንታው የመጀመሪያ ግቡ የትግሬን ምድር ሰው አልባ ለማድረግ ነው ብዬ እንዳስብ አስገድዶኛል።
ጁንታውን የትግሬን ሕዝብ የሚያታልልበትን ቃላቶች ባስታወስኩ ቁጥር «አንድ ወቂት ተግባር ከአንድ ቶን ንድፈ ሃሳብ የበለጠ ዋጋ አለው።» የሚለውን ፍሬድሬክ ኤንግልስ ንግግር ያስታውሰኛል።
ወያኔ ለትግሬ ሕዝብ አደርግልሃለሁ ብሎ የገባው ቃል ሺህ ነበር። ነገር ግን ለትግሬ ሕዝብ ከጥፋት፣ መከራ፣ ርሃብ እና ከእልቂት ውጭ አንድም መሬት ላይ የሚታይ ነገር አላደረገለትም። በዙሪያው ያሉ ሕዝቦችን በጅምላ በጠላትነት ከመሸመት ውጭ ምንም አልፈየደለትም። አሁንም በትግሬ ሕዝብ ይምላል፤ ይገዘታል።
አይጥ እንደበላው ማግ በትግሬ እና በአጠቃላይ በኢትዮጰያ ሕዝቦች ላይ የሚፈጥረው ችግር ተጎትቶ አልልቅ ብሎ እያያን ነው። የወያኔ ግቦች ከመጀመሪያውም ጥፋቶች ናቸው። ቀጥሎም የጥፋት ግቦችን ከጫፍ ለማድረስ የተጠቀማቸው ስልቶች በስህተት የታጨቁ መሆናቸው ናቸው። ከስህተት የማይጸዳው ወያኔ ከዚህ በፊት ስድስት ከባባድ ችግሮችን መፍጠሩ ይታወቃል።
አሁን ሰባተኛ ለመድገም እየተጣጣረ ነው። ከዚህ በኋላ ጁንታው በሚፈጥራቸው ስህተቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ እና ጁንታውን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ ወደነበርነት ለመቀየር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ቀደሙ እጅ ለእጅ ተያይዞ መቆም አለበት መልዕክቴ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014