አሸባሪው ሕወሓት እንደ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ የመከራና የሰቆቃ ምክንያት ከሆነ ሰነባብቷል። ድርጅቱ በባህርይው ሰጥቶ በመቀበል በመቻቻል በመነጋገር መርህ የማያምን ሁልጊዜ በበላይነት ሌሎችን በመግዛትና በመጨቆን በዘረፋ መኖር የሚፈልግ ነው።
አገርንና ሕዝብን ማስቀደም የአገር ሉዓላዊነት የዜጎች ክብር አንድነት በቡድኑ መዝገበ-ቃላት የማይታወቁ ናቸው። እንደ ድርጅት ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስካለበት የውድቀት አፋፍ ድረስ የሚታወቀው በክህደትና በሴራ፤ በእኔነት የአገርንና ሕዝብን ታሪክ በማንቋሸሽ ነው። ለቡድኑ ቀዳሚው አጀንዳ ኢትዮጵያዊነት አገራዊ ክብርና ነጻነት ሳይሆኑ በብሔር ብሔረሰቦች መብት ሽፋን እርሱ ሲፈልግ የሚሰበስባቸው ሳይፈልግ የሚበታትናቸው ሕዝቦች ያሉባትን አገር መግዛት ነው።
አገርን ለማፍረስ የማያመነታ ለዚህም እስከ ጥግ ድረስ ለመሔድ የተዘጋጀ ቡድን ነው። በእኔ እምነት የአሸባሪው ሕወሓት የክህደት ጉዞ የሚጀምረው ገና ከምስረታው ነው። በዚህ ጽሑፍ የማነሳቸው በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች የፈጸማቸውንና የታዘብኳቸውን አምስት የክህደት ተግባራቱን ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት የደደቢት የክህደት ጅማሮ
በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደታየው አንድ ድርጅት ርዕዮተ-ዓለማዊም ሆነ ብሔራዊ መሰረት ይዞ አሳካዋለሁ ለሚለው ዓላማና እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ወይም በትጥቅ ትግል ለመታገል ሊመሰረት ይችላል።
በአሁኑ ዓለማዊ ሁኔታ የትጥቅ ትግል በአብዛኛው ጊዜ ያለፈበት ሲሆን አሸባሪው ሕወሓት ትግል በጀመረበት ወቅት የጊዜው መዝሙር ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ በዱር በገደሉ ትግሉን እንድትመራ የሚል ስለነበር በትጥቅ ትግል ለመታገል በረሀ መግባቱ ብዙም ክፋት አልነበረውም።
ይሁን እንጂ በጥቂቱ በምንገነዘበው ለትግል ይዞት የተነሳው ዓላማ ግን ጤነኛ አልነበረም። አሸባሪው ሕወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረው ከኢትዮጵያ አንድነት እና ዘላቂ ጥቅም በተቃራኒ በመቆም ነበር። ወደ በረሀ የገባው በትክክልም ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና ጥቅም በመቆርቆር ጭቆናን አፈናንና አድልዎን በመቃወም ቢሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር።
ሆኖም ይህ ቡድን ከመነሻው የበላይነት እና የጎጠኝነት የከፋፋይ አስተሳሰብ የተጠናወተው ስለነበር ይዞ የተነሳው ዓላማ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ትልቅ ስፍራ ያላትን ትግራይን ገንጥሎ ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት ጨቋኝ በሚል ትርክት በጠላትነት የፈረጀውን የአማራውን ሕዝብ ማህበራዊ እረፍት መንሳት እንደነበረ ከተለያዩ ድርሳናት መረዳት ይቻላል።
በ1968 ዓ.ም ላይ ከባላባታዊ ስርዓትና ከኢምፔሪያሊዝም ነጻ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ማቋቋም የሚል ገንጣይ ዓላማ የያዘ ፕሮግራም እንደተቀረጸ በኋላ ላይ በአባሉ ተቃውሞ ሲገጥመው እንደተሰረዘ አቶ ገብሩ አስራት ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ አሸባሪው ሕወሓት ይዞት የተነሳው ዓላማ የትግራይን ሪፐብሊክ መመስረት ብቻ ሳይሆን የትግራይ ትግሪኝ ግዛትን ማቋቋምም እንደሆነ እነ አቶ አብራሃም ያየህን የመሳሰሉ የድርጅቱ አመራሮች የነበሩ በወቅቱ የገለጹት ጉዳይ ነው።
ይህም በጥቅሉ ሲታይ ከጊዜ በኋላ ይህ ፕሮግራም ተሰረዘ ቢባልም ድርጅቱ ኢትዮጵያን መግዛት ባቃተው ጊዜ የሚያንቀሳቅሰው አጀንዳ እንደሆነ እየተገለጸ የመጣ እውነት ነው። በዚህ ሁኔታ የቡድኑ የአገር ክህደት ጉዞ አንድ ብሎ የተጀመረው እዚህ ጋር ይመስለኛል።
የአሸባሪው ሕወሓት ወደ ስልጣን መምጣትና የሽግግሩ ውድቀት
አሸባሪው ሕወሓት ኢሕአዴግ በሚል ግንባር በተለያዩ ውስጣዊና ውጭያዊ አስቻይ ሁኔታዎች በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የማእከላዊ መንግስት ስልጣንን ከጨበጠ ብዙም ሳይቆይ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ታሪክ የረጅም ጊዜ አሉታዊ ውጤት ያስከተሉ የክህደት ተግባራትን ፈጽሟል።
የሀገረ-መንግስቱ አንድ አካል የነበረውንና በዓመታት የተገነባውን የመከላከያ ሰራዊት አፍርሶ መበተኑ እነዚህ ሁሉ ተግባራቱ ታሪክ ይቅር የማይለው የክህደት ስራው መገለጫዎች አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ። አሸባሪው ሕወሓት የመንግስትነትን ስልጣን ከጨበጠ ከአንድ ወር በኋላ የሰላምና የዲሞክራሲ የሽግግር ኮንፈረንስ አዘጋጀ።
ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕወሓት ላይ የነበረው የገንጣይ አስገንጣይ የጥርጣሪ ሀሳብ እንዳለ ሆኖ ደርግ ይፈጽማቸው በነበሩ ተግባራት በእጅጉ የተማረረበት ወቅት ስለነበር ከደርግ ይሻላል በሚል እሳቤ የተወሰነ ተስፋን ይዞ ድርጅቱን የተቀበለበት ሁኔታ ነበር።
ሕወሓትም አጋጣሚውን በመጠቀም ሥልጣኑን ለማደላደልና በይበልጥም ምዕራባውያንን ለማስደሰት የዲሞክራሲ ጠበቃ ሆኖ ብቅ አለ። በወቅቱም አስቀድሞ በኤርትራ ሰንዐፈ ከተማ ከኦነግ ጋር የተፈራረመውን የሽግግር ወቅት ቻርተር በኮንፈረንሱ አቅርቦ ሊያጸድቅ ችሏል።
ቻርተሩ በክፍል አንድ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 10/1948 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀውን ሁሉ-አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ሰነድን በመቀበል ሀሳብን የመግለጽ የመቃወም የመደራጀት መሰረታዊ የግለሰብ መብቶች እንደሚከበሩ ይደነግጋል።
ይህን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ፓርቲዎች የተደራጁበት የግል ፕሬሶች በብዛት መታተም የጀመሩበት ወቅት ነበር። በኮንፈረንሱ ኢሕአፓና መኢሶንን የመሳሰሉትን በማግለል በአብዛኛው የብሔር ድርጅቶች እንዲሳተፉ አድርጓል። በቻርተሩ መሰረት የተቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ቢመስልም የጠቅላይነት አስተሳሰብ ባህርይው የሆነው ሕወሓት ቀስ በቀስ በፈጠረው ጫና ለስልጣኔ ያሰጉኛል ያላቸውን ኦነግንና የደቡብ ሕብረት የመሳሰሉ ድርጅቶች ተወካዮችን በሰበብ አስባቡ ከሽግግሩ መድረክ እንዲገለሉ አድርጓል።
በአማራ ሕዝብ ዘንድ በፍጥነት ተቀባይነት እያገኘ የነበረውን የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅትን በማዳከም ታይቶ የነበረውን የመድበለ-ፓርቲ ዲሞክራሲ ጭላንጭል እንዲጠፋ አደረገ። በሕዝቡ ዘንድ ተስፋ ተደርጎ የነበረው የለውጥና የአዲስ ምዕራፍ የዲሞክራሲ ጅማሮ በሕወሓት ሁሉን የመጠቅለል አባዜ ሊጨነግፍ ችሏል። ሕወሓት አዲስ ታሪክ ሊሰራበት ይችል የነበረውን እድል አመከነው።
ሽግግሩ ተጠናቅቆና ሕገ-መንግስት ጸድቆ ቋሚ መንግስት ሲመሰረት ድራማ መሰል ነገር ተከናወነ። የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩት መለስ ዜናዊ ለተመረጠው ቋሚ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስተር ለመለስ ዜናዊ ስልጣን አስረከቡ። የደርጉ ሊቀመንበር ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ለኢሕዴሪ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማሪያም ስልጣን አስረከቡ እንደተባለው ሁሉ ታሪክ እራሱን ደገመ።
የ1997 ታሪካዊ ምርጫና አሳዛኙ ፍጻሜው
አሸባሪው ሕወሓት በሽግግሩ ሒደት ዋና ዋና ተቀናቃኝ የሚላቸውን ከመድረኩ አሰናብቶ ሕገ-መንግስት ከጸደቀና ቋሚ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ የሥልጣን መንበሩን አረጋግቶ አገሪቱን መግዛት ቢቀጥልም በ1993 ዓ.ም በውስጡ የተፈጠረው ክፍፍል በሕልውናውና በስልጣኑ ላይ አደጋ የደቀነበት ሁኔታ ነበር።
የክፍፍሉን አደጋ በወቅቱ የድርጅቱ ቋንቋ ተንበርካኪ የተባለው የእነ አቶ መለስ ቡድን አንጃ የተባለውን የእነ አቶ ስዬ ቡድን በማስወገድ በአሸናፊነት ካለፈ በኋላ ሕወሓት የበለጠ ስልጣኑን እያጠናከረ ሔዶ የ1997 ምርጫ ደረሰ። በዚህ ወቅት የተወሰነ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም ሕወሓት መራሹ መንግስት ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ለውጥ አያመጡም በሚል እሳቤ የተዘጋውን የፖለቲካ በር ገርበብ በማድረግ አንጻራዊ ነጻ የፓርቲዎች ፉክክር የግሉ ፕሬስ እንቅስቃሴ ሊታይ ችሏል።
በዚህ ሁኔታ ምርጫው ተካሒዶ ውጤቱ ወደ መታወቅ ሲመጣ ወንበሩን ሊያሳጣው እንደሚችል ሲገምት በደም ያገኘሁትን ስልጣን “ለነፍጠኞችና ትምክህተኞች” አልሰጥም በማለት የግድያና የጭካኔ በትሩን ማንቀሳቀስ ጀመረ። በብዙ የተጠበቀው ምርጫ በአሳዛኝ የግድያና የእስር ትራጀዲ ሲደመደም ሕወሓት ሕዝብን ከኋላቸው ያሰለፉ የተቃዋሚ መሪዎችን ወደ ቃሊቲ ወርውሮ የተንገዳገደ ወንበሩን በደም አበላ በማጠናከር አገዛዙን ቀጠለ።
የፈሪ በትር እንደሚባለው ከዚህ በኋላ በእነ አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ አጋፋሪነት አፋኝ የተባሉ የጸረ-ሽብር፣ የሚዲያ፣ የሲቪል ማህበራት የመሳሰሉ አዋጆችን በማውጣት በሕዝብ ድምጽ ላይ ክህደት ፈጽሞ የአፈና ስርዓቱን አጠናክሮ ቀጠለ።
የ2010 ዓ.ም ለውጥና የአሸባሪው ሕወሓት ክህደት
ይህ ወቅት ለሃያ ሰባት ዓመታት የዘለቀው የሕወሓት ኢሕአዴግ የአፈና የግድያ የዝርፊያና የአድልዎ አገዛዝ በቃ በማለት ሕዝባዊ ተቃውሞው ጫፍ የደረሰበት ጊዜ ነበር። በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው የለውጥ ኃይል የሕዝቡን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት በመከተል ውስጣዊ የፖለቲካ ትግሉን እያጠናከረ ሔዶ በድርጅቱ ውስጥ በተደረገው የአመራር ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሊመጡ ችለዋል።
የለውጡ መንግስት ያልተጠበቁ አስገራሚና አዳዲስ እርምጃዎችን መውሰድ ሲጀምር ሕወሓትም ወደ መቀሌ በማፈግፈግ ለውጡን መገዳደርና የለመደውን የክህደት ሴራ መጎንጎን ጀመረ።
በየክልሉ ያሉ በብሔረሰብ ተወካይነት ስም የሚወራጩ አሉኝ የሚላቸውን የግጭት ነጋዴዎችና የጥፋት ተባባሪዎች በፋይናንስ በመሳሪያ በስልጠና በመደገፍ በአገሪቱ በአራቱም ማእዘናት የግድያና የብጥብጥ እሳት አቀጣጥሎ መቀሌ ላይ ሆኖ እሳቱን ይሞቅ ነበር። ዓላማውም ለውጡን ቀልብሶ ቢችል ወደ ስልጣኑ መመለስ ካልሆነም አገሪቱን አዳክሞና በታትኖ ደደቢት ላይ የሰነቀውን ዓላማ ለማሳካት ነበር ብሎ ማሰብ ይቻላል።
የ2012 ዓ.ም ምርጫ መራዘምና የአሸባሪው ሕወሓት አመጸኝነት
የአሸባሪው ሕወሓት ለሕገ-መንግስት ያለመገዛት የክህደት ተግባር ግልጽ ሆኖ የወጣው በ2012 ዓ.ም መደረግ የነበረበትና በኮቪድ ወረርሽኝ መሰራጨት ምክንያት ያልተደረገው አገራዊ ምርጫ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሲደረግ ነው።
በወቅቱ ከምርጫው አለመደረግ ጋር ተያይዞ በመንግስት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ከቀረቡ አማራጮች መካከል የሕገ-መንግስት ትርጉም መስጠት የሚለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ ጉዳዩን ለሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በመላኩ ጉባኤውም የውሳኔ ሀሳቡን በሕገመንግስቱ መሰረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበበት ሁኔታ ነበር።
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሕገ-መንግስቱ የተሰጠውን ሕገ-መንግስቱን የመተርጎምና የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን መሰረት በማድረግ ምርጫው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች በስልጣናቸው እንዲቆዩ ወስኗል። በዚህ ወቅት ሕወሓት ግራ ቀኙን ማየት ባለመፈለግ የሕገ-መንግስቱን አንድ አንቀጽ ብቻ መዝዞ በመጮህ ሃያ ሰባት ዓመት ሳያከብረው የኖረውን ሕገ-መንግስት ተጣሰ በሚል ጩኸት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ እንደማይቀበል በመግለጽ ሒደቱን ማጣጣል ጀመረ።
ማንም ሰው ወይም ቡድን በምክር ቤቱ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደትና ውሳኔ ላይስማማ ይችላል። ሆኖም የሕገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ሚና ያለውን የምክር ቤቱን ውሳኔ ግን አልቀበልም ማለት አይችልም።
ይህ የሕገ-መንግስታዊነትን ሀሁ የሚያውቅ ሊረዳው የሚገባ ነው። ሕወሓት ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገ ከሕጋዊነት ጽንሰ-ሀሳብ ጋር የተፋታ ድርጅት በመሆኑ በእራሱ ግምባር ቀደም ሚና በጸደቀው ሕገ-መንግስት የተቋቋመውንና የትግራይን ሕዝብ በመወከል ሲሳተፍበት የኖረውን ምክር ቤት ውሳኔ ያለመቀበሉና በአመጽ መቀጠሉ ለሕገ-መንግስቱ እሞታለሁ ሲል የነበረው እርሱ ስልጣን ላይ እስካለና ለእርሱ እስከተመቸው ድረስ ብቻ መሆኑ በግልጽ የታየበት ሁኔታ ነበር።
በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት የፌዴራሉ መንግስትና የክልል አስተዳደሮች በስልጣናቸው እንዲቆዩ በመደረጉ እነዚህን አካላት ሕጋዊ አይደሉም የሚለውን ጩኸት ለእራሱና ቢጤዎቹ ተናግሮ እራሱ አድምጦ በክልሌ የእራሴን ምርጫ አደርጋለሁ የሚል ዘመቻ በመጀመር እንዳለውም አደረገ።
የምርጫ አዋጆችን እራሱ በማውጣት ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የጨረቃ ምርጫ አካሒዶ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሲቀልድ እንደነበረው ዘጠና ዘጠኝ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ አወጀ። ይህ አካሔድ በግልጽ ሕገ-መንግስቱን የተቃረነ እና በሕገ-መንግስቱና የፌዴራላዊ ስርዓቱ መርሆዎች ላይ የፈጸመው ክህደትና ለሕግ አልገዛም ባይነት ነበር።
በሕገ-መንግስቱ በተደነገገው የፌዴራል መንግስትና ክልሎች የስልጣን ክፍፍል መሰረት የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከቱ ሕጎች የማውጣት ስልጣን በግልጽ ለፌዴራሉ መንግስት የተሰጠ ነው። በመላ አገሪቱ ማንኛውንም አይነት ምርጫ ለማካሔድ በሕገ-መንግስቱ ስልጣን የተሰጠው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው።
ይህ ሆኖ እያለ ሕወሓት ከሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች በሚቃረን መልኩ የእራሱን ምርጫ ለማካሔድ የሰጠው ምክንያት በሕገ-መንግስቱ እራስን በእራስ የማስተዳደር መብት አለኝ የሚል ነው። ይሁን እንጂ ሕወሓትና አጫፋሪዎቹ በወቅቱ ማየት ያልፈለጉት ጉዳይ የፌዴራላዊ የመንግስት ስርዓት መገለጫው የእራስ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የጋራ አስተዳደርም መሆኑን ነው።
ፌዴራሊዝም ኪዳን /Covenant/ ስምምነት ነው ሲባል ለፌዴራል መንግስት በስምምነት በጋራ አስተዳደር ሀሳብ በሕገመንግስት የተሰጠውን ስልጣን ክልሎች መውሰድ አይችሉም ማለት ነው።
በሕገ-መንግስታችንም የፌዴራሉ መንግስት የክልሎችን ክልሎች የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ተደንግጓል። ስለሆነም ሕወሓት ለቀጣይ ችግሮችና ቀውሶች ምክንያት ያደረገው ይህ የምርጫ ውዝግብ ቀድሞውንም ነገር የመፈለግ እንጂ አቋሙ ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ኖሮት አልነበረም።
የሕወሓት የመጨረሻው የክህደት ጥግ
አሸባሪው ሕወሓት ይህ ሁሉ ፖለቲካዊና ሕገመንግስታዊ ክህደት አልበቃ ብሎት የአገር ሉዓላዊነት የመጨረሻ መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ በየትኛውም ዓለም ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ እራሱ ያደራጀውንና ሲመራው የነበረውን ሰራዊት እንደ ጠላት ሀገር ኃይል የጭካኔ ተግባር ፈጸመበት።
አገሪቱንም ለውጭ ጠላቶች ጥቃት በማጋለጥ ሲዘጋጅበት የቆየውን በኢትዮጵያ ኪሳራ ትግራይን የመገንባት ዓላማ ለማሳካት እጅግ አሳፋሪ የሆነ የክህደት እና የወንጀል ተግባር ፈጸመ። ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እሔዳለሁ በሚል የእብደት ጉዞ የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር በንጹሐን ዜጎች ላይ አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊት የፈጸመ ድርጅት መሆኑን አሳይቷል።
አሸባሪው ሕወሓት ጅማሬው የሴራና የክህደት እንደሆነ ሁሉ መጨረሻውም በክህደት የተደመደመ ሆኗል። እኩይ ዓላማ ይዞ የተነሳ ኃይል በየትኛውም ዘመን ሲሳካለት በታሪክ አልታየምና የአሸባሪው ሕወሓትም ጉዞ መታሰቢያ እስከማይኖረው ድረስ በውድቀት እንደሚደመደም አያጠራጥርም። ኢትዮጵያና ሕዝቦቿም ከዚህ ጦረኛ ቡድን ተገላግለው የሰላምና ልማት ጎዟቸውን ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች
በወልዱ መርኔ
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014