ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ አስደንጋጭ ፣ አሳዛኝ ፣ ልብ ሰባሪ፣ ተስፋ አጨላሚ የሆነ በርካታ መከራዎችን አልፋ እዚህ ደርሳለች።
ከእንግዲህስ አገር ሆና መቆም አትችልም የሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ያደረጉንን ብዙ ቀውሶችም ተሻግራለች። ኢትዮጵያን እራሳቸው ጭቃ አቡክተው የሰሯት ይመስል በዚህ ምክንያት ትፈራርሳለች፤ እንደዚያ ትሆናለች ብለው የሟርት መንፈሳቸውን ሲዘሩ ከወደቀችበት እየተነሳች እነሱ እንዲቀበሩ ያደረገችበት አጋጣሚ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ከሩቁ ብንጀምር የአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ አገረ መንግስትነት ያከተመ እንዲመስል አድርጎ ነበር። ፋሺስት ኢጣሊያን ለዳግም ወረራ ሲመጣ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከዓለም ካርታ ትጠፋለች የሚል ድምዳሜም የበላይነትን አግኝቶ ቆይቷል። ኋላም በዘመነ መሳፍንት የኢትዮጵያ ተስፋ ጨልሞ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
የ1966ቱ አብዮት፣ የቀይ ሽብር ክስተት፣ የሕወሓት ወደ ስልጣን መምጣት፣ ሳያስበው ከስልጣን መፈናቀልና አሸባሪ ሆኖ በአገርና ህዝብ ላይ መከራን ማዝነብ ሁሉ ሲታዩ የኢትዮጵያ አገር ሆኖ የመቀጠልን ተስፋ ያጨለሙ መስለው ነበር ።ነገር ግን ሁሉም በጊዜና በሰዓቱ ከማለፉም በላይ እኛም ዜጎቿ አገራችንን ቀብረን ያለአገር የምንኖር መስሎን ከነበረው ሁኔታ እንድንወጣ ሆኗል።
በእርግጥ አሁንም አሸባሪው ሕወሓት አፈር ልሶ አገራችንን ደግም መከራ ውስጥ ለማስገባት ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ የተለያዩ ሁኔታዎች ያመለክታሉ።
በተለይም አሁን ላይ በአማራ ክልልና በአፋር በኩል ተቀጥቅጦ የሸሸው አሸባሪ ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ በአፋር ትንኮሳ ጀምሮ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሰለው ነው ።ነገር ግን ዛሬም እንደትላንቱ አገሬ የተሳፈረችበት መርከብ እንኳን በአሸባራ ሕወሓት በማንም የማይናወጥ በመሆኑ ጊዜያዊው የቡድኑ ስራ ከሽፎ ዳግም ድል ለእኛ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እዚህም እዚያም ወዳጅ መስለው ጠላት እየሆኑ ሟርታቸውንና ሴራቸውን ሲዶልቱ ዘመናትን እንደተሻገሩት እንደነ ሕወሓትና ጀሌዎቻቸው ሳይሆን ኢትዮጵያ የማትናወጥ ጠንካራ መርከብ በመሆኗ ሁሉን በድል ትወጣዋለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተለይም “ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” የሚል ስያሜ ለተሰጠው ዘመቻ አበርክቷቸውን ላኖሩ የመገናኛ ብዙሀንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ምስጋና ባቀረቡበት ወቅት፤” ኢትዮጵያ በየዘመኑ ያላላፈችው ፈተና የለም አሁንም እያለፈች ያለችው ጊዜ የዘመኑን ፈተና ነው፤ ነገር ግን አገሪቱ የገጠማት ችግር መርከቧን አፍርሶ በጀልባ እንድትሔድ የሚያደርጋት ሊሆን አይገባም “ ነው ያሉት። አዎ እስከ አሁን ያየናቸው ሁነቶች በሙሉ የሚያሳዩን አገራችን በጠንካራ በየትኛውም ወጀብ በማይናወጥ መርከብ ላይ የተሳፈረች መሆኑን ነው።
ነገር ግን ከዚህ መርከብ አውርደው በጀልባ ሊያስኬዷት በማዕበል ሊያስበሏት የሚፈልጉ ሀይሎች በርካታ ናቸው። እስከ ዛሬ በመጣንበት አንድነታችንና ህብረታችን ታግዘን ኢትዮጵያን ዛሬም እንደትላንቱ ልናሻግራት ይገባል።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ኢትዮጵያ እንዳሰቧት ሳይሆን ባላሰቡት መንገድ እየመጣች ቀበርናት ሲሉ ቀድማ እየቀበረቻቸው ፣ መቃብሯን ለተመኙላት መከራ እየሆነችባቸው ዛሬ ደርሳለች። ወደፊትም፣ እስከዘላለሙም በዚሁ መንገድ ለሟርተኞች፣ ለእናት ጡት ነካሾች እጅ ሳትሰጥ ትኖራለች። በክስተቶች የምትጠፋ፣ በየአጋጣሚ በሚፈጠሩ ቀውሶች የምትፈርስ አገር አለመሆኗንና የተሳፈረችበትም መርከብ የማይበገር መሆኑን ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ያስመሰከረች ተአምረኛ አገር ስለመሆኗ ደግሞ ምስክሮች ነን ።
በሚከሰቱ ጊዜያዊ ጉዳዮች እያዘንን አገራችንን ጠበቅ አድርገን ከመያዝ ከቦዘንን (ከተዘናጋን ) ግን እነዚህ ከመርከብ አውርደው በጀልባ ሊያስዋኟት ለሚፈልጉ ሀይሎች አሳልፈን እንሰጣታለን፤ ይህንን ማድረግ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት ማነስ መሸነፍ ነው። ማነስ መሸነፍ ደግሞ ለጠላቶቻችን በር መክፈቻ ትልቅ መንገድ ይሆናል።በመሆኑም ከፊታችን እየመጣ ያለው ነገር በጣም ከባድ በመሆኑ እነዚህን የጀልባ ቀዛፊዎች ወዲያ ብለን መርከባችንን ማጽናት ማጠንከር የሁላችንም ሀላፊነት ነው ባይ ነኝ።
እንደ ህዝብና እንደ አገር አላማችን በመርከቧ መጓዝ ከሆነ ከፊታችን ያለውን ፈተና ኮርተን እናልፈዋለን፤ አይ ጀልባ ነው ምርጫችን ካልን ግን እውነት ለመናገር ማዕበሉን አልፈን ነገን የምናይበት አጋጣሚው እጅግ የጠበበ ነው፤ በመሆኑም የነገዋን ጸሀይ ለማየት ዛሬ ላይ መክፈል ያለብንን ሁሉ መክፈል ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ ለአሉባልታና ለጊዜያዊ ቀውሶች ጆሮ አለመስጠትና በእነሱ ያለመወሰድ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።
ዛሬ ላይ ሆነን የምንሰራት እያንዳንዷ ነገር በተለይም ነገ በልጆቻችን ላይ የሚኖረው ጥሩም መጥፎም ጎን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ በመሆኑም ዛሬ የጸናች መርከብ በመገንባት የልጆቻችንን አልፎም የልጅ ልጆቻችንን ማጻኢ እድል ማሳመር የሁላችንም የቤት ስራ ነው። የአገር ጉዳይ ለመንግስት አልያም ለጥቂት ሰዎች የሚተው አይደለም ።
አገር የሁላችንም እናት መጠጊያ መከለያ መኖሪያ አለፍም ሲል መኩሪያ ናትና ዛሬ ላይ የሚገጥማትን እያንዳንዱን ችግር በጥበብና በትዕግስት ታልፈው ዘንድ የሁላችንንም ድጋፍ ትፈልጋለች። መንግስት ሊሳሳት መንግስት የዜጎቹን ድምጽ ያልሰማ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ይህንን ማረም ደጋግሞ ድምጽ ማሰማት ከስህተትም መመለስ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገም ስንቃችን መሆኑን መገንዘብ የግድ ነው።
ይህንን ባደረግን መጠን ደግሞ አገራችንን ከመርከቧ አውርደው ጀልባ ላይ ሊያስቀምጡልን የሚፈልጉትን ሀይሎች ከማሳፈራችንም በላይ አገራችን በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትቆም በማንም በምንም እንዳትናወጥ ለልጆቻችንም ምቹ እንድትሆን ማድረግ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።አበቃሁ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014