መቼም የክፉ ነጋዴ ነገር ለብዙ ጉዳይ ምሳሌ ይሆናል። ክፉ ነጋዴ በራሱ መክበር ሳይሆን በባልንጀራው መክሰር ይደሰታል አሉ ። እንደው እናንተዬ ባይልለት እንጂ ጉዳቱ እኮ በእሱ ይብስ ነበር። ክስረት ይሉትን ትልቅ ዕዳ ከትከሻው አዝሎ የሌላውን ውድቀት ባልተመኘ ፣ባረረው አንጀቱ ባልሳቀ ነበር።
አንዳንድ ልበ ክፉም እንዲሁ ነው። ከእጁ ፍሬ ይልቅ የሌላውን ገለባ ይሻል። ከራሱ ደስታ በላይ የሰው ሀዘንና ጉዳት ያረካዋል። ‹‹ያልታደልሽ›› አሉ እማማ ። አውነታቸውን ነው። እኔም፣ ደጋግሜ እንዲህ አይነቱን ውል አልባነት ‹‹አለመታደል ነው›› እለዋለሁ። አዎ! አለመታደል ።
የእነአያ እንቶኔም ጉዳይ እንዲሁ ነው። ልክ እንደ ክፉው ነጋዴ። በራሱ ደስታ ሳይሆን በሰው ሀዘን በሚረካው ፣ ውል አልባነት፣ ምቀኝነት መለያው በሆነው ልበ ጨካኝ ነጋዴ አይነት። እነሱ ቀድሞ ክፉ ታሪክ የሰሩ፣ ጓዶቻቸው ፍርድ ያገኙ ዘንድ በታሰሩ ጊዜ ስለምን ብለው ይጮሁ ነበር። የእነሱ ቀኝ ክንዶች ደግሞ በህዝብ ደም አሳፋሪ ታሪክ የጻፉ፣ በንጹሀን ማንነት ጥቀርሻ ታሪክን ያሰፈሩ ናቸው።
እነዚህ ቀኝ እጅ ተብዬዎች ዓመታትን ምቾት ካለው ማማ ሲፈናጠጡ ምህረት ይሉት አልነበራቸውም። ከጥቅማቸው ጥግ የደረሰ ሁሉ ህይወቱ ይነጠቃል፣ ታሪኩ ይጎድፋል፣ ዘር ማንዘሩ በመብራት እየተፈለገ ይሳደዳል።
እንዲህ ሲሆን ደግሞ ክፉ ድርጊታቸው በገሀድ ታይቶ አያውቅም። ለሊቱን ሲገድሉ አድረው ሲነጋ ጠፋ የተባለውን ያፋልጋሉ። ካለቀሰው ጋር አልቅሰው ደረት ይመታሉ፤ ይህ ድርጊታቸው መቼም ከጥርጣሬ ጥሏቸው አያውቅም። ሁሌም ደግነታቸው ገኖ ክፋታቸው ይቀበራል። ሴረኝነታቸው ተረስቶ መልካምነታቸው ይተረካል።
ወዳጆቼ! የክፉውን ነጋዴ ጉዳይ የዘነጋሁ አይምሰላችሁ። የእንዲህ አይነቱ ነጋዴ ማንነት በቀላሉ አይተውምና እኔም ፈጽሞ አልረሳውም። ይህ ነጋዴ ስለቅርብ ወዳጆቹ ዕድገት በእጅጉ የሚበሳጭ ጉደኛ ነው። እሱ የማንም ደስታና ስኬት ደስ ብሎት አያውቅም።
ሁሌም መሰሎቹን ሰብስቦ ለጥፋት ይሰማራል። መቼም ቢሆን ጥቅሙን አይረሳም። ‹‹ሌባ እናት…›› እንዲሉ ሆኖ ዙሪያ ገባውን፣ ፊትና ጀርባውን አምኖት አያውቅም። አስፈላጊ ከሆነ የራሴ የሚላቸውን ውዶቹን ሳይቀር ዕድሜያቸውን ይቀጫል። እነሱን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋቸው ባሰበ ጊዜም የተለመደ አፋላጊነቱ ቀርቶበት አያውቅም። ሁሌም ልቡ እያወቀ ለይምሰል በሚያወርደው የአዞ ዕንባው እሰከመቃብር ይሸኛቸዋል።
የሸር ስራው የማይገባቸው ብዙኃን ለአድናቆት ከእሱው ጋር መሆናቸውን ይቀጥላሉ። በየጊዜው ስለሚፈጽመው የትህትና አስመሳይነት የተለየ አክብሮትን ከደመቀ ጭብጨባ ጋር ይቸሩታል። እሱ ታዋቂው ሚዲያ ወርቅና ብሩ በእጁ ነበር። በፈለገ ጊዜ የልቡን ለማድረስ ዘገን ቦጨቅ ማድረጉ አይቀርበትም።
አንዳንዴ የነጋዴው ድርጊት ከዓዕምሮ በላይ ይሆናል። ለራስ ጥቅም እስካስፈለገው ድረሰ አያደርገው አይኖርም። ለያዘው ዓላማ ሰው መግደል፣ ህይወት መጥፋት ካለበት ውሳኔው የፈጠነ ነው። በስውር መፈጸም ያለባቸው ደባዎች ሁሉ በቀጭን ትዕዛዝ ተግባራዊ ይሆናሉ።
የስግብግቡ ነጋዴ ጉዳይ በዚህ ብቻ አይገደብም። ስልጣኑን እስከፈለገው ጥግ ሲያራምደው ኖሯል። ለእሱ እሰካዋጣና አስካተረፈው ድረስ አገርን እሰከመሸጥ መለወጥ ይደርሳል። የህዝብ ሀብትና ንብረትን በጥቅም ይለውጣል። ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት አስይዞ በነፍሳቸው ይደራደራል።
ነጋዴው ይህን አሳፋሪ ተግባር ሲፈጽም በውስጡ ያለው ምቀኝነት ፈጽሞ አይጠፋም። በእጁ ካፈሰው ወርቅ ይልቅ ከሌሎች ደጅ ያለ ኩበት ያስቀናዋል። ኪሱን ከወጠረው ብርና ዶላር ይልቅ በሌሎች መሀረብ የተቋጠረች ሳንቲም ያምረዋል። ማንም ከእሱ ቀድሞ እንዲያልፍና እንዲሻገር አይሻም።
ሁሌም ከራሱ መክበር በላይ በሌሎች ኪሳራ መደሰትና መርካቱ መገለጫው ነው። አገር እየዘረፈ፣ ህዝብ እየበዘበዘ የሚያገኘውን ውድ ሀብትና ንብረት በዙሪያው ላሉት ማጋራትን አይሻም። ምርቱን እየደበቀ፣ ዕብቁን ፣ወርቁን እየሸሸገ አርቴፊሻሉን፣ ማሳየት መገለጫው ነው።
በስልትና በጥበብ በሚዘርፈው የአገር ሀብት ከሚገኘው ትርፍ ጠበኝነት ለሚሻው ማንነቱ አውዳሚ መሳሪያ መግዛት፤ ለክፉ ቀኑ ስንቅ ይሆነው ዘንድም በድብቅ ስፍራዎች በመቅበር ሲያከማች ቆይቷል።
ይህ ልበ ክፉ ሁልጊዜ ከሚቦጠቡጠው ትኩስና ትልቅ ዳቦ ለሌሎች ቆርሶ አያውቅም። በእጁ የገባውን ሲሳይ በየመልኩ ከፋፍሎ ላሰበው ዓለማ ያውላል፤ አንዳንዴ በዙሪያው ለሚገኙ ጥቂቶች ፍርፋሪ ቢጤ ይጥልላቸዋል።
እነሱ የተሰጣቸውን አብቃቅተው በስራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ብዙኃን ያካፍላሉ። በራሱ የስልጣን ዛቢያ የሚዞረው ልበ ክፉው ነጋዴ ለሌሎች በጣለው ምንዱባን እየኮራ ስሙን ከከፍታው ይሰቅለል። በርካቶች ቢቸገሩ፣ ቢራቡ ደንታው አይደለም። ከአገር ቢሠደዱ፣ ቢፈናቀሉ ጉዳዩ አይሆንም።
ይህን ባደረገ ቁጥር ስለመልካምነቱ እንዲወራ፣ ስለፈጸመው በጎነት እንዲወሳ የሚሮጡለት አይጠፉም። በሰጠው ፍርፋሪ ነፍሶች እንደለመለሙ፣ አገር እንደለማ፣ ህዝብ እንደተለወጠ ይነገርለታል። ይህ ከንቱ ውዳሴ መልካም ስም ችሮትም ዝናው ይካብለታል። ስለእሱ ማንነት ድንቅ ስያሜን የሚሰጡ አራጋቢዎች ዕድሜው እንዲራዘም፣ የስልጣን መንበሩ እንዲቀጥል ሲዘምሩለት ቆይተዋል።
ነጋዴው ሁሌም የውስጥ ምቀኝነቱ ከራሱ ጋር ነው። በበላይነት በተቆናጠጠው ወንበር ተቀምጦ የሚያስተዳድራቸውን አካላት እርምጃ በጥንቃቄ ይቃኛል። እነሱ በራሳቸው ጥረውና ለፍተው፣ ታሪካቸውን እንዲለውጡ፣ በዕድገት ጎዳና እንዲራመዱ አይሻም።
ለነጋዴው ይህ አይነቱ ዕድገትና ለውጥ ፈጽሞ አይመቸውም። እንዲህ መሆኑን ከተረዳ ለውሳኔው ይፈጥናል። ምክንያት ፈጥሮ ህብረታቸውን ያፈርሳል፣ አንድነታቸውን ይንዳል፣ እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋቸውን ለያይቶ ክፍተታቸውን ያሰፋል።
ሁሌም ከፍ ብሎ የተሰቀለው ስሙ ከስልጣኑ ጋር ተዳምሮ ልዩነታችሁን ልፍታ ባለ ጊዜ አንደበቱ ይደመጣል። ክብሪቱን እሱ እንዳልጫረው ሁሉ ችግር ተፈጥሯል በተባለበት አካባቢ ፈጥኖ ለመድረስ የሚቀድመው አይገኝም።
ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታን ያልጠረጠሩ በርካቶች ሁሌም ዳኛ ለሚሆንላቸው አስመሳይ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። አመኔታቸውን ክብራቸውን ያስረክባሉ። ክፉው ነጋዴ የጫረውን እሳት አጥፍቶ ፣ በዋሾ አንደበቱ ወሽክቶ ዓለማቸውን ሲነጥቅ ደግሞ ማናቸውም አይጠረጥሩትም። በረከታቸውን አስረክበው፣ ፍቅራቸውን አስነጥቀው ልዩነትን ሲሸለሙ የገደላቸውን ጠላት በክብር ተቀብለውና ሸኝተው ነው።
አደገኛው ነጋዴ አገሪቱን በመልክ ከፋፍሎ ከቁንጮነቱ ማማ ሲሰቀል የስልጣን ክንዱን በወጉ ይጠቀማል። ታላቅ ሀብትና ንብረት በሚታፈስባቸው ድንቅ ስፍራዎች ለሚኖሩ ታላቅ ህዝቦች የሚሸልመው ስጦታም ሙሉ ሆኖ አያውቅም። ከሚገባቸው አውርዶ፣ ከሚሰጣቸው ክብር ቀንሶ ‹‹አጋር›› ናችሁ ይላቸዋል።
ዓመታትን በጉልበት ሲገዛ በድፍረት ለቸረው ስያሜና ችሮታ ስለምን ብሎ የጠየቀው አልነበረም። ጥርሱን እያሳየ ሆዱን ሲያጎሽ፣ መዳፉን ዘርግቶ ጀርባውን ሲሰጥ የውስጡን ጥልቅ ደባ ያወቀ የጠረጠረ አልተገኘም።
አገር ቸርቻሪው ነጋዴ ሁሌም እጆቹ ረጃጅም ናቸው። ለራሱ ጥቅምና ህልውና ከሆነ ባህር መሻገሩን፣ ያውቅበታል። ይህ አይነቱ መንገድ ሁሌም የእሱና የእሱ ብቻ ሆኖ ቆይቷል። ሚስጥሩን የማያውቁ የዋሆች ምልልሱ ለብዙኃን ጠቀሜታ ሲመስላቸው ኖሯል። የራሱን ሥልጣን ለማደላደል የተራመደውን እርምጃ ግን ጊዜ ቆጥሮ ተግብሮታል።
ግፍ እየበዛ የስልጣን አርግጫው እየከፋ ሲሄድ አገዛዙ ‹‹ይብቃን›› ያሉ ቆራጦች ለዓላማቸው ተነሱ። የአገር ቸርቻሪውን፣ የነፍስ ነጣቂውን፣ የከፋፋይ ሴረኛውን ጉዞ ሊቆርጡ ከፊቱ ቆሙ። ድንገቴው ለውጥ ያስደነበረው ግፈኛ ነጋዴ እውነታው እየመረረው፣ ከእጁ ያመለጠው ክብሩ እየቆጨው ስልጣኑን አስረከበ።
ለብዙኃን ጥቅምና ክብር ሲባል የተጀመረው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ታሪክ መቀየሩን ያዘ። ይህ እውነታ ያልተዋጠለት ነጋዴ ጀሌዎቹን ሰብስቦ የራሴ ባለው ስፍራ ከተመ። ለዓመታት በዘረፈው፣ እልፍ ሀብትና ንብረት አሁንም ‹‹ይብቃኝ›› አላለም። ለዘመናት ባፈሰሰው የንጹሀን ደም አልረካም። መስረቅ የለመደ እጁ ጦር ለመስበቅ ተነሳ። ክፉ ልቦናው ጦርነት ማወጅ፣ አገር ማፍረሰ አማረው ።
አሁን የቀናተኛው ነጋዴ ልቦና በምቀኝነት ነዷል፤ ትናንት ሲያፈርሰው የነበረው አንድነት፣ ሲያደፈርሰው የኖረው ሰላም ተመልሶ ማየቱ እያንገበገበው ነው። ከራሱ ስልጣን ማጣት ይበልጥ አምሮ ተውቦ ያየው መግባባት ዕንቅልፍ ነስቶታል። ቁንጮነቱን ከመነጠቁ በላይ ዓለም በለውጡ ውጤታማነት ማጨብጨቡ አብግኖታል።
የቀናተኛው ክፉ ነጋዴ ማንነት በዚህ አይነቱ በጎ መንገድ አልፎ አያውቅም። አገርን ሲሸጥ፣ በርካቶችን ሲያሰቃይ ኖሯል። አንድነትን ሲያፈርሰ፣ ልዩነትን ሲያሰፋ ቆይቷል። የሆነውን መቀበል የተፈጸመውን ማመን ከብዶታል። ነጋዴው ውሎ አድሮ በከተመበት ስፍራ ከጀሌዎቹ መከረ። መማክርቱም ከእውነታው ፈጽሞ አላፈነገጡም። አሁን የትናንትናው ታሪክ ተቀይሯል። ልዩነት፣ ተወግዶ አንድነት ከብሯል። ፍቅርና ሰላም፣ መከባበርና መደማመጥ ነግሷል።
ነጋዴው የደረሰበትን ኪሳራ ደጋግሞ አሰላው። ኪሳራው እያየው ካለው እውነታ የሚበልጥበት አልሆነም። በእርግጥ ታላቁን የስልጣን መንበር ሳያስበው አስረክቧል። አብሮት የቆየው ክብርና ሞገስ ዛሬ የእሱ አልሆነም። ካጣው ይልቅ የሚመለከተው ድንቅ እውነታ ቢያበሽቅ፣ ቢያበግነው ሌላ ጥፋት ወጠነ። ዕቅዱን አንድ በአንድ ነድፎም ትናንት መከታ ሆኖ በጠበቀው ደጀን ላይ ኃይሉን አሳረፈ።
የትናንቱ አገር ሸቃጭ ነጋዴ ዛሬ ማንነቱ ተገልጧል። ሽንፈቱን ላለመቀበል አያደርገው አይፈጽመው የለም። ባህር ተሻግሮ የሚጠይቃቸው የቀድሞ ወዳጆቹ ለእኩይ ተግባሩ አጋር ሆነው ከጎኑ ቆመዋል። ተወልዶ ያደገባትን፣ በስልጣን ነግሶ የከበረባትን አገር ለማፍረሰ እያገዙት ነው። ጨኸቱን ተቀብለው ለማስተጋባት የገደል ማሚቶ የሆኑለት ከሀዲዎች የሚላቸውን ሁሉ ለመፈጸም ‹‹አለንህ›› እያሉት ነው። እነሱ የትናንቱን ውለታ የዘነጉት አይመስልም። ቀድሞ ኃይል ሳለው ያሻቸውን ሁሉ አድርጓል። ዛሬ እነሱም ስለጥንቱ ወዳጅነት ሲባል አይሆኑለት የለም።
በተባበረ ክንድ ክፋት፣ ሌብነቱ የተራገፈው እርጉም ነጋዴ ዛሬ ህሊናውን በገሀድ ሸቅጧል። የትናንት ክብሩ ወድቆ ሲንኮታኮት ሀቁን መቀበል አልሆነለትም። ዙሪያ ገባውን ‹‹ክተት›› ሲል ጦር ባዘመተባቸው ስፍራዎች ያሰበውን ሂሳብ ማወራረዱን አልረሳም።
ጀሌዎቹ ትዕዛዙን አንድ በአንድ እየፈጸሙለት ነው። መግደል፣ መዝረፍ፣ ማውደም፣ መድፈር ይሉትን ክፋት ተግብረውታል። በየደረሰበት ሽንፈቱን ሲከናነብ፣ ውድቀቱን ሲታቀፍ ሌላ መንገድ መቀየስ ይዟል። ወዳጆቹም ተማጽኖውን እየሰሙለት ነው።
የባህር ማዶዎቹ ባለውለታዎች ትንፋሹን እያዳመጡ የፍላጎቱን ያደርጋሉ። አገሪቱን ይኮንኑለታል፣ ድምጹን ያጮሁለታል፣ ሲገድል መገደሉን፣ ሲዘርፍ መዘረፉን፣ ሲያወድም መውደሙን ገልብጠው ያወሩለታል። ለእሱ የታሰበው ሁሉ በዕቅዱ መስመር አልተጓዘም። የኃይል ሚዛኑ በሽንፈት ተቀብሯል። የክፋት ታሪኩ በዓለም ተመስክሯል። ክፉው ነጋዴ ድል ተነስቶ ወደ ጎሬው ሲመለስ አንገቱን አልቀበረም። ከጉድጓዱ በላይ የዋለ ጭንቅላቱን አስግጎ ሌላውን ጉድጓድ መማስ ያዘ። ለዚህ ሴራው አሁንም ወዳጆቹ ‹‹አለንህ›› ሲሉ አበረቱት።
ሽንፈት የተላበሰባትን ምድር ስም ለማጉደፍ ሌት ተቀን ባዘነ። ግፍ እንደተዋለበት አየሰበከ፣ የበደል ሸክሙን፣ ዓለም ይይልኝ ሲል አለቀሰ። አራጋቢዎቹ ‹‹እውነት አለው›› ሲሉ ቃሉን አባዙለት ። ታላቂቱ አገር ኢትዮጵያ በጽኑ ታፈነች።
በመላው ዓለም ዕልፍ የሆኑ ልጆቿ፤ የክፋት እጆች ሁሉ ይነሱላት ዘንድ ‹‹ይበቃል›› ሲሉ ዘመሩ። ድምጻቸው ህብር ሆኖ በዓለም ቢስተጋባ የታሰበው ከሸፈ። የተደወረው ተበጠሰ። ይሄኔ የክፉው ነጋዴ ሽረባ ስር ግንዱ ተቆራረጠ።
ዓለም እንዲጠላት በታደመባት አገር ሚሊዮኖች በሯን ሊያገኙ ተጋፉ። ነጋዴው አንጀቱ አረረ። ያጠለሻት አገር በዓለም ደምቃ መታየቷ አበገነው። ወዳጆቹ አሁም አብረውት ቆመዋል። ጦርነትን ባሟረቱባት ድንቅ ምድር ዜጎቻቸው ለቀው ይወጡ ዘንድ እየወተወቱ ነው። ሁሉም ሴራ በታሰበው ልክ አልሆነም። ውሸት አግጥጦ ሲወጣ በታላቅ እውነት ቦታው ተሸፈነ።
ዕንቅልፍ አልባዎቹ ሴረኞች እረፍት ይሉትን አጥተዋል፤ ሽንፈታቸውን፣ ድል መነሳታቸውን ለመደበቅ አያደርጉት የለም። ልበ ክፉው ነጋዴ አገሩን ዘመድ አልባ ለማድርግ ባሴረው ሁሉ አልተሳካለትም። እያደናቀፈው መውደቁ ቢበዛ ታላቁን መረብ ለመዘርጋት ዳግመኛ መከረ። ይህች ድንቅ አገር በየዓመቱ አፍሪካውያን ወንድሞቿ በቤቷ ታድመው ይመክሩባታል። ለችግሮች መፍትሄ የሆነችው ምድርም ጥንሰስሱን ለመጀመር ቀዳሚዋ ነች።
የክፉዎቹ ልቦና ይህን ታላቅ ዕሴት ማደናቀፍ ቢችል አይታሰቤ ድል ይኖረዋል። የነበረን ታሪክ በስም ማጥፋት አብሰው ክፋትን ቢዘሩ፣ በአሸናፊነት የሞላ ፅዋቸውን ያነሳሉ። ይህን ለማሳካት ዋቢ የሚሆኗቸው ደግሞ በምርኮ የተያዙ፣ በህግ ጥላ ስር የዋሉ ጓዶቻቸው ናቸው። ጉባኤው እንዳይሰምር፣ በሮች እንዲዘጉ፣ ተቀባይነት እንዳይኖር የእነሱ ማንነት መነሻ ይሆናል።
የክፉው ነጋዴ ክንፎች በተሰበሩ ማግስት እጆቻቸው በካቴና የታሰሩ አጋሮቹ በህግ ጥላ ውለው ፍርድን ሲጠብቁ ቆይተዋል። እስከዛሬ በነጋዴውና በወዳጆቹ እሳቤ ይህ እውነታ ተቀባይነት የለውም። አሁንም የፍርደኞቹ መያዝ ለሴራቸው አመቺ ሆኗል። ጉባኤው እንዳይኖር፣ በሮች እንዲዘጉ፣ በዓላት እንዳይደምቁ፣ ታሳሪዎቹ ዋስትና ይሆናሉ። ድምጽን ለማወፈር፣ ጩኸትን ለማድመቅ ያግዛሉ።
የክፉው ነጋዴና የወዳጆቹ ውጥን አልሰመረም። ለጭዳነት የታሰቡት ዋቢዎቻቸው እጆቻቸው ከሰንሰለት ተፈቶ በድንገት ከእስር ተለቀቁ። ድንገቴው ውሳኔ የክፉውን ነጋዴ ህልም አጨለመው። ትናንት ታስረውብኛል ሲል ዓለምን የወተወተባቸው ጓዶቹ መፈታታቸው አበሳጨው። የእነሱ እውነታ ኪሳራውን አጎላው። ይሄኔ ልማደኛ ልቡ በቅናት ነፈረ። በተፈቱት እጆች፣ ነጻ በወጡት ነፍሶች ማንነት ተንጨረጨረ።
አገር ሸቃጩ ነጋዴ ለጓዶቹ በሆነላቸው መልካምነት በእጅጉ ተከፋ። እንዲህ መሆኑ የእሱና የወዳጆቹ ዕቅድ አልነበረም። የቀድሞ ውጥኑ የእነሱን ሰንሰለት በማጥበቅ የራሱን ህልውና ማስቀጠል ነበር። አሁን የታሰበው አልተሳካም። መፈታታቸው ከደስታ ይልቅ መርዶ ሆኗል። ዓመታዊው ጉባኤ እንደቀድሞው ሰምሮ ይቀጥላል።
አሁን እንግዶች በሰላም ይሸኛሉ። እውነተኞቹ የኢትዮጵያ ልጆች በገዛ አገራቸው ክብራቸውን ይለብሳሉ። ባንዲራችን ከፍ ብሎ ይሰቀላል። ልዩነት ተወግዶ ዓለም ለድንቂቷ ውድ አገር ቆሞ ያጨበጭባል። የክፉው ነጋዴ ኪሳራ ከቁጥር በላይ ሆኖ ቁስለቱን ማስታመም ይዟል።
ኢትዮጵያ ግን ትርፍ ኪሳራዋን ለይታለች። ይጠቅማትን አኝካ ውጣ የማይበጃትን መርዝ አንቅራ ተፍታለች። ትናንት የታሰበው ጉዞ ዛሬ ባልታሰበው መንገድ ተቆርጧል። አዲዮስ! ነጋዴ ።
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ጥር 19/2014