በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰፊው መሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያዎቹ ረድፍ ላይ ከተቀመጡት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል ዕድል በተሰጠ አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄ ለመጠየቅም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድም ዕድል እየሰጡ፣ የሚነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን በፍፁም ትህትና ያዳምጣሉ፡፡ የዕለቱ ዋና አጀንዳ ውይይቱ ምን መልክ ኖሮት ይቀጥል? የሚል እንጂ ለሚነሱ ጥያቄዎች እንደ ገዥ ፓርቲ ሆኖ ምላሽ ለመስጠት እንዳልሆነ ለማስረዳትም ይጥራሉ፡፡
ትናንት የተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ዓላማ ለቀጣይ ተግባብቶ ለመሄድ እንዲያስችል፣ ምን ላይ ትኩረት ቢደረግ እንደሚሻል እንዲሁም ውይይቶች መቼ፣ ማን፣ እንዴት ይምራ በሚል ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡
ሁሉም ፓርቲ አለኝ የሚለውን ሐሳብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዝርዝር በማቅረብ እንደየ ርዕሰ ጉዳዩ ጥልቀትና ስፋት ተደራጅቶ ውይይት የሚደረግበት እንደሚሆንም ዶክተር አብይ ይገልፃሉ፡፡ ለውይይቱ እንደ መንደርደሪያ ካቀረቡት ሐሳብ መካከል አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መምከርና ለአገር መሥራት ቀዳሚው ሲሆን፣ በውይይቱም የማያግባቡ ጉዳዮች የሚፈተሹበት፣ አጣዳፊ የሆኑት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ውይይት የሚደረግበት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር አብይ እንደተናገሩት፤ የዕለቱ ውይይት ደረጃ አንድ የሚባል አይነት ነው፤ ደረጃ ሁለት የዴሞክራሲያዊ ተቋማትና ባህል ግንባታ ሲሆን፣ ደረጃ ሦስት ደግሞ ዘላቂና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት የሚፈጠርበት ነው፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ዓላማናጭብጥ ስላላቸው በየደረጃቸው የሚካሄዱ ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አንድ ህፃን ልጅ ሲወለድ ብዙ አጥንቶች ይኖሩታል፤ እያደረገ ሲሄድ ደግሞ እነዛ በርካታ አጥንቶች በመሰባሰብ ቁጥራቸው አነስተኛ ይሆናል፡፡ ህፃን ሆኖ ሳለ የነበሩት በርካታ አጥንቶች ጠንክሮ እንዲቆም ግን ጉልበት አይሆኑትም፡፡ ሰበሰብ ብለው ሲዋሃዱ ግን ጥንካሬን ስለሚሰጡት በሁለት እግር መቆም ብሎም መራመድ ያስችሉታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሁ ናቸው፤ መብዛታቸው በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ብርታት አይሆናቸውም፡፡ አንድነት ሲፈጥሩ ግን ጠንካራ፣ መንግሥትን ሞጋች፣ ህዝብንም አሳማኝ ይሆናሉና በቀጣይ ወደ 70 የሚጠጋው ፓርቲ ወደ አራትና አምስት ዝቅ ብሎ እንደሚመጣ ተስፋ ይደረጋል፡፡
የዕለቱ ውይይት የደረጃ አንድ ቢሆንም ከፓርቲዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ በርካታዎቹ አስተያየቶች የፓርቲዎች ቁጥር ዝቅ እንዲል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሐሳብ ቅቡል መሆኑን የሚገልፁ ናቸው፡፡ ለውይይት መጠራታቸውና በነፃነት ሐሳብ ማቅረብ መቻላቸውም ይበል የሚያሰኝ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ከእነዚህም መካከል ከወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ የተነሳው አስተያየት እንደሚያመለክተው፤ በቁጥር የበዛው ፓርቲ ሁሉ በአብዛኛው ሥልጣን ፈላጊ ሳይሆን መብት ጠያቂ ነው፤ መብቱ ሲመለስ ፓርቲውም የሚከስም ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ይኸው የወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፡፡
ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ የቀረበው አስተያየትም፤ ሁሉም ፓርቲ እንደየ ርዕዮተ ዓለሙ በጋራ መሰብሰብ ቢችል ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መሆን እንደሚቻል የሚገልጽ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው ለውጥ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ይህ እንዲቀጥል ደግሞ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነ ያመላክታል፡፡
የግንቦት ሰባት ፓርቲ ተወካይ ያቀረቡት አስተያየትም፣ እስካሁን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ችግር የነበረው መንግሥት ነበር፤ አሁን ግን ችግሩን በመቅረፍ ላይ የሚገኘው መንግሥት ነውና የሚበረታታ መሆኑን ነው፡፡ውይይቱም ገለልተኛ በሆነው በምርጫ ቦርድ እንዲሆን መደረጉና ኢህአዴግም እንደ አንድ ፓርቲ መሳተፉ መልካም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወካይ የቀረበው ጥያቄ ደግሞ ከምርጫ በፊት እንደ አገር መተማመንና መደማመጥ ስለሚያስፈልግ ለዚህ ምቹ እንዲሆን ዜግነትን የሚክደው ሕገ መንግሥት ሊስተካከል ይገባልና ምን ታስቧል? የሚል ነው፡፡ ተወካዩ አክለውም፤ ከምርጫው በፊት ይቅርታና እርቅ እንዲሁም የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ አለበትና በዚህም ላይ ምላሽ እንደሚሻ አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለተነሱት አስተያየቶች ማጠናከሪያና ለጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ እንዳብራሩት፤ በቁጥር ከ70 ለሚልቁ ሁሉም ፓርቲ ቢሮ እና መሰል ጉዳዮችን መስጠት በራሱ ችግር መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ጠንክሮ ለመቆም አብሮነትን ፈጥሮ መጣመሩ ጠንካራ ያደርጋል፡፡
በፓርቲዎች መካከል መተማመን የሚፈጠረው በአንድ ጀምበር ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ዋናው ነገር ዛሬ ይጀመር፡፡ ሕገ መንግሥትም ቢሆን አይሻሻል የሚል አመለካከት የለም፡፡ ሐሳብ ካለ ለውይይት ይቅረብ፡፡ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ የምርጫ ሕጉን ለማሻሻልም ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በአገር ደረጃ እርቀ ሠላም እንደሚያስፈልግ ታምኖ ኮሚቴም እየተዋቀረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመጀመሪያ ግን ሁሉም ከራሱ ጋር መታረቅ እንዳለበት ገልፀው፣ የህዝብና ቤቶች ቆጠራም ከምርጫው በፊት ይካሄዳል፡፡
ከተለያዩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሲነሳ የነበረው ሐሳብ እንደሚያመለክተው፤ ገዥው ፓርቲ ዘንድ የነበሩ በርካታ ችግሮች ተቀርፈዋል፡፡ የፓርቲ ቁጥር አነስ ማለቱ ተፎካካሪዎችን እንደሚጠቅምም ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ተፎካካሪዎች ግን ገና አንድ ለመሆን ዝግጁነት ያላቸው አይመስልምና እዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡ መንግሥት አንድ እንዲያደርጋቸው መጠበቅም የለበትም፡፡
ቀጣይ ውይይቶች ደረጃቸውን ጠብቀው የሚካሄዱ መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ትንንሽ መሆን መታፈን ማለት ነው፤ በሁለት እግርም እንዳንቆም የሚያደርግ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ጉልበትና ጥንካሬን ለማግኘት ብሎም ህዝብንም ለማሳመን ቅንጅትን በመፍጠር ለምርጫ ራስን ማዘጋጀት ብልህነት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ተረኛ አሸናፊም ለመሆን በቁጥር አንሶ መገኘት ወሣኝ መሆኑን መክረዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ