አንዲቱ ብዙነሽ፤ “ምልክቴ” የምትለው ማዘጋጃ ቤቷ የታደሰላትን መዲናችንን እንኳን ደስ ያለሽ በማለት ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንዘልቃለን። አዲስ አበባን የእኔ የሚሏትና የእኛ የሚሏት ብዙዎች ናቸው። የዕድሜ በረከቷ የ135 ዓመታት ጣሪያ የነካውን ይህቺን ከተማችንን በአንቱታ ከሚጠሯት ይልቅ አንቺ ባዮቿ እንደሚበዙ ማስታወሱ አይከፋም። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው።
ዕለት በዕለት የምናስተውላት እንደ ታሪክ ጠገብ ከተማነቷ በቅርሶቿ ገዝፋና ደምቃ ሳይሆን በየዕለቱ እየፈረሰች ስለምትገነባ፣ እየተቆፈረች ስለምትደማ ነው። ከእነ አሻራቸው የተነቀሉትን ዝነኞቹን ነባር ሠፈሮቿንና ተጠቃሽ ምልክቶቿን (Landmarks) ዛሬ ዛሬ ከቦታቸው ብንፈልጋቸው እንኳን እንደነበሩ ለማግኘት ደብዛቸው ራሱ ስለመገኘቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ስለዚህም ነው የዕድሜዋን ፀጋ በማክበር እንደ ባህላችን “እርስዎ” በማለት ፋንታ ሁሉም ታዳጊ መሆኗ እየታወሰን “አንቺ” በማለት የምናንቆለጳጵሳት፤ ሲከፋንም የምንከፋባት። ብዙ የዓለማችን መሰል አንጋፋ ከተሞች ቅርሳቸውንና ነባር ባህላቸውን ከዘመናዊው ፈጣን የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ጋር አስማምተው ያስጠብቃሉ እንጂ እንደኛይቱ አዲስ አባባ በወረት ነፋስ እየተወዛወዙ ነጋ ጠባ አቅላቸውን አያጡም።
ይህ ጸሐፊ የአዲስ አበባ ቤተኛነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ዓመታት ከተማዋ ባከበረቻቸው ክብረ በዓሎቿ ላይ የአንድ ብዙ ከተማነቷን አስመልክቶ የተለያዩ የጥናት ጽሑፎችን በማቅረብ የነዋሪነቱን መዋጮ ለማበርከት ሞክሯል።
በተለየ ሁኔታ ግን ሁለቱን ብቻ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። የመጀመሪያው የመቶኛ ዓመቷ በዓል በ1979 ዓ.ም ሲከበር ስለ ሠፈሮቿ አመሠራረት ዘርዘር ያለ ጥናት ለማቅረብ ጊዜው ዕድል ሰጥቶት ነበር።
ጥናቱ ለአንድ የመድረክ ፍጆታ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በማሰብም የዚህ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተወዳጅ እህት በነበረችውና የተነባቢነቷ እስትንፋስ እንዲጨልም በተወሰነባት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተወዳጅ ጋዜጣ ላይ “የመቶ ዓመት ሻማ ሲቀጣጠል” በሚል ርዕስ በተከታታይ ሙሉ የጥናት ጽሑፍ ለንባብ እንዲቀርብ ተደርጓል።
ሁለተኛው ጥናት የተደረገው ደግሞ የ125ኛ ዓመቷ ሲከበር ከነፍሰ ሄር ብቃለ ስዩም (ዶ/ር) ጋር በመሆን “የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ አመሠራረትና የአካባቢዎቿና የሠፈሮቿ አሰያየም” በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ ጥናት በጋራ በማቅረብ በዓሏን አድምቀንላታል።
“ትዝታ አያራጅም” እንዲሉ ይህንን የግል አስተዋጽኦ ለማስታወስ ምክንያት የሆነኝ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም 2.2 ቢሊዮን ብር ሆጨጭ ተደርጎ የታደሰውን የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ዜና ባዳመጥኩበት ወቅት ነው።
ከታሪክ ምስክሮች ይልቅ “ዘመኑ የእኔ ብቻ ነው” የሚሉ ፊትአውራሪዎች ተሽቀዳድመው የሚጋፉበት የሀገራችን የግብዣ መድረኮች ባህል እጅጉኑ ሥር የሰደደ በመሆኑ እንጂ በዚህ “የእድሳት ምረቃ መርሃ ግብር” ላይ የታሪክ ጉዳይ የሚታወስበት መለስተኛ ውይይት ወይንም ጠንከር ያለ ሲምፖዚዬም ቢካሄድ ፋይዳው ከፍ ባለ ነበር።
በጸሐፊው የግል አስተሳሰብ የእድሳቱ ሪፖርት ሲቀርብ ውብ ቢሮዎች፣ ጊዜያዊ የሕጻናት ማቆያ ክፍል፣ የቴያትር አዳራሽ፣ ቤተመጻሕፍት የመሳሰሉት የሕንጻው ይዘቶች ተዘርዝረው “ለታሪካዊ መዘክሮች” ማስታወሻ እንዲሆን አንድ ክፍል እንኳ ያለመመደቡ ወይንም ተመድቦም ከሆነ ያለመገለጹ ግርታ ፈጥሮብኛል።
እስከ መቼስ ዛሬን ብቻ እየተመለከትን ትናንትን “ፊት እንደምንነሳው” በግሌ ሊገባኝ አልቻለም።
ጥቂቱን እናስታውስ፤
“የጣይቱ የመሬት አጠቃቀም ፕላን” በመባል የሚታወቀውና ጥንታዊቷ አዲስ አበባ ተሸንሽናበት የነበረው የሦስቱ ቀጣናዎች ታሪካዊ ዳራ “በታደሰው ውብ ሕንጻ ውስጥ” ቢካተት ኖሮ “ታሪክ ከወንበሩ ከፍ ብሎ ባርኔጣውን በማንሳት” ባከበረን ነበር።
በቀጣና አንድ ውስጥ በተካተተው የቤተ መንግሥቱ (ግቢ) ዙሪያ ለፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲያመች ተብሎ ለ34 ያህል የወቅቱ የሲቪል፣ የጦር ባለሥልጣኖች፣ መኳንንትና ሹማምንት፣ ለአቡነ ማቴዎስ፣ ለእጨጌውና ለአድባራቱ ካህናትና ሠራተኞች እየተደለደሉ የተሰጡት ታሪካዊ ሠፈሮችና አካባቢዎች ለዛሬው ትውልድ ቢተዋወቁ ዛሬ የታነጸበት የትናንት ገጽታ ምን እንደሚመስል ትልቅ ማስተማሪያ በሆነ ነበር።
ለማሕበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ማዕከልነት በተመረጠውና በቀጣና ሁለት ሥር የተከፈለው የአራዳ ጊዮርጊስ ታሪካዊ አካባቢ በዝርዝር ቢዘከርና ቢታወስ ፋይዳው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም።
ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዝቅ ብሎ ያለውና የታደሰውን ማዘጋጃ ቤት አካቶ ቁልቁል የተዘረጋው የቀጣና ሦስቱ የአራዳ ገበያ ኢኮኖሚውንና ንግዱን በማሳለጡ ረገድ የነበረው ሚና ቀላል እንዳልነበር ትውልዱ በሚገባ ቢገነዘብ አይከፋም ነበር። “ለካስ ነበር እንዲህ ቅርብ ነበር” አሰኝቶም በአግራሞት እጅን በአፍ ላይ ማስጫኑ እንደማይቀር መገመት አይከብድም።
ለምሳሌ፤ ከቀጣና አንድ አካባቢዎች መካከል ራስ ካሳ ሠፈር ወይንም ራስ ተሰማ በመባል የሚታወቁት አካባቢዎች የትኞቹ ነበሩ? ጠብመንጃ ያዥ ሠፈርተኞች “የከተሙት” የት አካባቢ ነበር? የግብር መብራት ያዦችስ? ወዘተ. እያልን ብንጠየቅ ለመልሱ አፋችን መያዝ አይገባውም።
ከቀጣና ሁለት መካከልም ለምሳሌ የጥንቱ ካህን ሠፈር በዛሬው አጠራር በየትኛው ክፍለ ከተማ ውስጥ ይገኛል? የሚል ታሪክ የተጠማ ጠያቂ ቢያፋጥጠን መልሱን በቀላሉ መስጠት ይቻል ነበር።
የእጣኑ፣ የሉባንጃው፣ የከርቤውና የአሪቲ መዓዛማ ጭሳጭስ መቸርቸሪያዎቹ የቀጣና ሦስቶቹ ደማቅ የመገበያያ ማዕከላት የት አካባቢ ነበሩ? የዘይት፣ የላምባ፣ የሽቶ ወዘተ. መገኛቸው የት ነበር? የወቅቱ ገንዘብ መንዛሪዎች አላዱን፣ ሩቡን፣ መሐለቁን በዓይነት በዓይነቱ ጨርቅ አንጥፈው ይመነዝሩ የነበረበት ሁነኛ ቦታ ዛሬ እድሳት ተደርጎለት የማዘጋጃ ቤቱ ሕንጻ ያረፈበት ቦታ ላይ የነበሩ ስለመሆኑስ ስንቶች ያውቁታል።
ለዛሬው ትውልድ ይህ ደማቅ የታሪክ አሻራ በታደሰው ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ውስጥ ቢተዋወቅ አይጠቅምም ይሆን?
የዲፕሎማቲክ ከተማነቷ ጅማሬ፤
ለእኛ ለባለ ሀገሮቹ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ ለአፍሪካዊያን ወንድም እህቶቻችን የፖለቲካ መዲና፣ ለመላው ዓለም ሕዝቦች ደግሞ ሦስተኛዋ የዲፕሎማቶች መናኃሪያ በመሆን የምትታወቀው አዲስ አበባ ለዚህ ሁሉ የአንድ ብዙነት ክብር ያበቃት አፈጣጠሯና አስተዳደጓ ምን ይመስላል? ብሎ መጠየቁ አግባብ እንደሆነ ይታመናል።
ጥቂት ታሪካዊ መደላድሎችን እናስታውስ። የከተሞች የአመሠራረት ታሪካዊ ዳራ የተለያየ ነው። በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሕዝብ ተሰባስቦ እርስ በእርሱ በሚያካሂደው መስተጋብር ሰፊ የሕዝብ ክምችት ስለሚፈጠር በትንሽ ሰፈርነት የተቆረቆሩ ቦታዎች በጊዜ ሂደት ወደቅድመ ከተማነት (Town) ከዚያም ቀስ በቀስ ወደከተማነትና (City) ብሎም ወደዘመናዊ ልዕለ ከተማነት (Metropolis) ያድጋሉ።
እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች የሚመሰረቱ ከተሞች እያደር ሰፊ የሕዝብ ክምችት በመያዝ አንዳንዶቹ የፖለቲካ፣ ሌሎች የንግድ፣ አንዳንዶችም የዲፕሎማሲ ወይም የጥበብ ወዘተ. ማእከላት ወደ መሆን ይሸጋገራሉ። አንዳንድ ከተሞች ልክ እንደ አዲስ አበባ በትንሽ ሰፈርነት ተቆርቁረው በውስጣቸው በሚካሄድ ፈጣን እንቅስቃሴ ምክንያት በዘፈቀደ ሲያድጉና ሲስፋፉ ተስተውለዋል።
አንዳንዶችም ውስጣዊ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከመ በመሄዱ እየከሰሙና እየፈረሱ መሄዳቸውን ከታሪክ መገንዘብ ይቻላል።
አንዳንድ ከተሞች ደግሞ ከምንም በመነሳት በፈጣን ሁኔታ ሲያድጉ ይስተዋላል። በዘመናዊ እቅድ የሚመሩና እድገታቸው በተገቢው አካሄድና ፍጥነት በመመራቱ ምክንያትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ ያለ እመርታ ያሳዩ የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
ለጊዜው ስለ አዲስ አበባ ከተማ የዲፕሎማሲ ማእከልነት ጥቂት እንበል። ከተማዋ ለታላላቅ መንግሥታት የዲፕሎማቶች መቀመጫነት ዐይን ውስጥ መግባት የጀመረችው ከአድዋ ድል ማግስት በጥቅምት ወር 1889 ዓ.ም. ነበር። የሀገሪቱ ሉዓላዊነት በአድዋው ታላቅ የጀግንነት ክብር ከተረጋገጠ በኋላ አዲስ አበባ ላይ የእርቅ ስምምነት ፊርማ ተከናወነ። ከዚያም ተከትሎ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሌጋሲዮኖቻቸውን በአዲስ አበባ በመክፈት ለከተማዋ ዕድገትና መስፋፋት ከፍተኛ የሆነ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ጀመሩ።
አሰፋፈራቸውም በጊዜው ከከተማዋ ዳርቻዎች ላይ ነበር። በተከታዮቹ ዐሥር ዓመታት ውስጥም ሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የወዳጅነትና የንግድ ውል ከኢትዮጵያ ጋር ተፈራርመው በአዲስ አበባ ውስጥ ሌጋሲዮኖቻቸውን አቋቋሙ። በ1906 ዓ.ም አጼ ምኒልክ ካረፉ በኋላም እስከ 1928 ዓ.ም. የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ድረስ ቱርክ፣ ግብጽ፣ ግሪክ፣ ቤልጅግ፣ ሳዑዲና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገሮች በቆንስላና በሌጋሲዮን ደረጃ ጽ/ቤታቸውን መክፈት ጀመሩ።
የዲፕሎማሲው ታሪክ የነጎደው እንዲህና እንዲህ እያለ ነበር። አንዳንድ አካባቢዎችና ሠፈሮች ዛሬም ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የባዕድ ሀገሮችን ስሞች እንደያዙ ይገኛሉ። ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ፣ ሩዋንዳ፣ አሜሪካን ግቢ፣ ጣሊያን ምሽግ፣ ጣሊያን ኤምባሲ፣ እንግሊዝ በር፣ ኮሪያ ሠፈር፣ ታይዋን፣ ዱባይ ተራ ወዘተ. እነዚህ ስሞች በአንድ አህጉር ውስጥ የሚገኙትን ሀገሮች ስሞች ብቻ ሳይሆን የዓለማችንን አህጉራት ማለትም፤ አፍሪካዊ፣ አውሮፓዊ፣ አሜሪካዊ፣ እስያዊ፣ አረባዊ ወዘተ. ስሞችን ይወክላሉ።
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት አዲስ አበባ በርግጥም የዲፕሎማሲ ከተማ ነች ቢባል አያሳፍርም። አዲስ አበባ ከተማ ከአንዳንድ ሀገራት ከተሞች ጋር “የእህት ከተማነት” ዝምድና ለመፍጠር ስትፈራረምም እነዚህን ታሪካዊ የሠፈሮቿን ግጥምጥሞሽ እያሰበች ብትጠቀምበት አትራፊ ትሆናለች።
ያለፈውን ታሪኩን የማያስታውስና የዛሬውን ተጨባጭ እውነታ በትናንት ውጤቶች የማይመዝን ትውልድ ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንና መልካም እድሎችን በጥሩ አኳኋን ሊተነብይ ወይንም ሊያቅድ አይችልም። ስለዚህም፤ ትክክለኛውን ታሪክ በሚገባ ማወቅና መገንዘብ ለነዋሪው ኅብረተሰብም ሆነ ለአስተዳደሩ ኃላፊዎች ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ሊሆን ይገባል።
ወደ ሁለተኛው የክፍለ ዘመን ዕድሜ እየተንደረደረች ያለችው አዲስ አበባ የዕድሜዋን ያህል አድጋለች ብሎ በሙሉ አፍ ለመናገር ያዳግታል። የመንግሥት ሥርዓት በፈጣን ሁኔታ መለዋወጥና ለውጡን ተከትለው የተከሰቱ በጎ ያልነበሩ ውጤቶች፣ የውጭ ወራሪ ኃይላት የፈጠሯቸው ተፅዕኖዎችና የነዋሪዎቿ የተዥጎረጎረ አመለካከትና የመሬት አጠቃቀም ሥርዓቱ ለከተማዋ ዕድገት መጓተት እንደ ምክንያት ሊወሰዱ ይችላሉ።
ክብርት ከንቲባ አዳነች አበቤ በሕንጻው እድሳት ምረቃ መርሃ ግብር ላይ፤ “የአሁኑንና የወደፊቱን ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ” በማለት በገለጹት ንግግራቸው ውስጥ የትናንቱን ታሪክ የዘለሉ ይመስላል። ዛሬና ነገ ያለ ትናንትና ፋይዳቸው እጅግም ስለሆነ አጽንኦት በመስጠት ትናንትን አክብረው ቢያስታውሱ ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። በተረፈ የማዘጋጃ ቤቱ መታደስን በማመስገን ማድነቁ አግባብ ሆኖ አንዳንድ ሁኔታዎችን ማስታወሱ ደግሞ ይበልጥ ጥረቱን ሙሉ ያደርገዋል።
አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ የሚገለገለው ከዋናው የማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎቶች ይልቅ በከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች፣ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው እንደሆነ በሚገባ ይታወቃል። እግርና ተገልጋይ የሚበዛውም በእነዚሁ ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ ነው። እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ እነዚህ የከተማው አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በሕንጻና በቢሮ አያያዛቸው ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መጠቆሙ “ለቀባሪው እንደማርዳት ያስቆጥርብናል።
የአንዳንዶቹ አያያዝማ ባይነሳ ይመረጣል። በግቢያቸው ላይ ያለው ውድቅዳቂ ኮተት፣ የቆሻሻ ዓይነትና ብዛት፣ የቢሮዎቹ መዝረክረክና በየግርግዳዎቹ ላይ የተለጣጠፉትን ማስታወቂያዎችን በማየት ብቻ ፍርዱን መስጠት ይቻላል።
እንኳን ለተገልጋዩ ሊመቹ ቀርቶ ለአገልጋዮቹ ለራሳቸው ምን ስሜት እንደሚሰጣቸው ቢጠና አይከፋም። በተዝረከረከ ቢሮ ውስጥ የሚያረካ አገልግሎት መጠበቅ የሚቻል አይሆንም። ስለዚህም “በነካ እጅ!” እንዲሉ በዚሁ የእድሳት የሞቀ ስሜት ታሪካዊ ፋይዳቸው በቸልታ ሳይታለፍ ለታችኞቹም የከተማው መዋቅሮች ትኩረት ይሰጥ የማጠቃለያ መልእክታችን ነው። ሰላም ይሁን!::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014