ንባብ በመዝገበ ቃላዊ ወይም በጥሬ ትርጉሙ ከአራቱ መሠረታዊ የቋንቋ ክህሎቶች አንዱ በሚል ሊገለጽ ይችላል። ነገር ግን ንባብ ክህሎት ብቻ አይደለም። ንባብ በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ዋነኛው የመማሪያ መሳያ ከመሆኑም በላይ ራስን ለማሻሻልና ህይዎትን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዕውቀቶችም የሚቀሰሙበት ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ ወሳኝ ሰብዓዊ ሐብትም ነው።
በመሆኑም ንባብ ተመራማሪና ችግር ፈች ዜጋ ለመፍጠር፣ በዕውቀትና በጥበብ ዋነኛው መሠረት ነው። የአገርን ባህልና ታሪክ የሚጻፈውና ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፈው በመጽሃፍትና በንባብ አማካኝነት ነው።
በተለያዩ መስኮች የዓለማችንን ሥልጣኔ ከፊት ሆነው በፊታውራሪነት የመሩ ሁሉም ታላላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብዕናዎች ለመጻህፍት ያላቸውን ልዩ ፍቅር የነበራቸው ናቸው፡፡
በአንድ ወቅት መላ አውሮፓን ጠቅሎ ከገዛው ታላቁ ንጉሥ ናፖሊን ቦናፖርቲ፣ ከአንድ ሺህ በላይ ፈጠራዎችን እስካበረከተው ቁንጮ ሳይንቲስት ቶማስ ኤዲሰን፤ ከባለቅኔው ሸክስፔር እስከ ፈላስፋው ሶረን ኪርክ ጋርድ ሁሉም ስለመጻህፍት ያልተቀኘ የለም። “የታላቅ አገር መሠረቱ የሕዝብ አንድነት ነው” በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁትና በግለኝነት አስተሳሰብ በዘቀጡ ዘመነ መሣፍንታውያን ተከፋፍላ የተዳከመችውን ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ አንድነቷ የመለሷት፤ ለታላቅነቷ ታላቅ ራዕይን ይዘው ሕይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ የታገሉላት፣ የጀግንነትና የታላቅ ስብዕና ምልክት የሆኑት ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሠት አፄ ቴዎድሮስም ለመጽሐፍ ልዩ ፍቅር ነበራቸው።
በዚህም ንጉሡ በሕይዎት ዘመናቸው ልዩ ልዩ ዕውቀትና ጥበብ የያዙ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ መጽሐፍትን በመቅደላ ጊዜያዊ ቤተ መንግሥታቸው ሰብሰበው እንደነበር የአገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል።
ይሁን እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ጨዋነታችንን፣ ሰው አክባሪነታችንን፣ ሃቀኝነታችን፣ እንግዳ ተቀባይነታችንና በአብሮነት ላይ የተመሠረተ ማህበራዊ ኑሯችን እንዲሁም ጀግንነታችንና ለነጻነት ያለንን ቀናኢነት ጨምሮ የሌሎችም በርካታ ጠቃሚ ባሀሎችን ባለቤቶች መሆናችን የሚያስከብረንና የሚያኮራን ቢሆንም ደካማ የንባብ ባህላችን ግን በተደጋጋሚ ከምንተችባቸውና ከምንታማባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል።
ሃሜት ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጥናቶች ሳይቀር በግኝታቸው የሚጠቅሱት መራራ ሐቅ ሆኖብናል። ለአብነት ያህል ከሦስት ዓመት በፊት በዚሁ ዙሪያ የተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት የንባብ ባህላችን እጅጉን ደካማ መሆኑን አመላክቷል።
ዋና ከተሞቻቸውን እንደ ማሳያ በመውሰድ የዓለም አገራትን የንባብ ባህል የገመገመው ይህ ጥናት እንደ ጃፓንና ጀርመን የመሳሰሉትን አገራት በማንበብ ባህላቸው ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን የጠቆመ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው የንባብ ባህል ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን አመላክቷል።
የዓለም አገራት ዋና ዋና ከተሞችን የንባብ ባህል “ከፍተኛ”፣ “መካከለኛ” እና “ዝቅተኛ” በሚል በሦስት ምድብ ውስጥ በቅደም ተከተል ስማቸውን በደረጃ ያስቀመጠው ጥናቱ የእኛዋን አዲስ አበባ ግን ዝቅተኛም ቢሆን ከነጭራሹ ደረጃ ውስጥ ሳያስገባት “የማታነብ ከተማ” በማለት ተሳልቆባት አልፏል። የንባብ ባህላችን በሚመለከት ሃቁ ቢመረንም ለእኛም ልካችንን ነግሮናል።
ለዚሁ ለደካማ የንባብ ባህላችን በምክንያትነት የሚጠቀሱ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ ግን የአቅርቦት እጥረትና የፍላጎት እጦት መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። የማያነብ ሕዝብ ደግሞ የብልጽግና ትንሳኤው ሩቅ ነውና ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን መሥራት የሚገባን ይሆናል። በዚህ
ረገድ በተለይም በአቅርቦት በኩል ያለውን ጉድለት መሙላት በዋነኝነት የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ የቅርቡን ትተን ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጀመረ ከሚባልበት ጊዜ ወዲህ ያሉትን ያለፉትን ሁለት ክፍለ ዘመናት ብቻ ብንመለከት ከዳግማዊ ቴዎድሮስ የመጽሐፍ ስብሰባና ቤተ መጻሕፍት የማቋቋም ሙከራ እስከ ደርጉ ዘመን መሃይምነትን የማጥፋት ዘመቻ የየራሳቸውን ጥረት አድርገዋል።
ድንቁርና መሩ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደሥልጣን መጥቶ አገሪቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ግን እንኳንስ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ሊሠራ ሆን ብሎ የወረቀትና የህትመት ዋጋዎችን በማናርና ጸሐፊያንና መጽሐፍትን በራሱ የተንሸዋረረ የጎጥ ፖለቲካ መነጽር እየተመለከተ በጠላትነት እየፈረጀ በማሳደድ በተቃራኒው ያለውን ጥቂት የንባብ ባህል ከነጭራሹ ሊያጠፋው ሞክሯል። ከሃያ ሰባት ዓመቱ የጨለማ ዘመን በኋላ በሕዝብ ትግል ሕወሓት ተወግዶ ወደሥልጣን የመጣውና አገር እየመራ የሚገኘው የለውጥ ኃይል በአንጻሩ የንባብ ዋጋ የገባው ይመስላል፡፡
የለውጡ መንግሥት ካከናወናቸውና ሊመሰገንባቸው ከሚገቡ በርካታ ተግባራት መካከልም የንባብ ባህላችን ደካማ ለመሆኑ በዋነኝነት ከሚጠቀሱ ችግሮች መንግሥትን የሚመለከተውን የአቅርቦት እጥረት ለማሻሻል በቅርቡ አስገንብቶ ያስመረቀው አብርሆት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስለት ነው።
ይህ የሚነበብ ግብዓትን በማቅረብና ለንባብ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍና የንባብ ባህልን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት አሁንም በመንግሥት በኩል መሠራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች የሚቀሩ ቢሆንም ጅምሩ ግን እንደ አንድ ትልቅ ርምጃ የሚወሰድና የሚያስመሰግንም ነው። ነገር ግን የሚነበብ ነገር መኖሩና የሚነበብበት ምቹ ቦታና ሁኔታ መኖሩ ብቻ የማንበብ ባህላችንን ያሻሽለዋል ወይንም ያሳድገዋል ወይ? በእርግጥ እንደ አብርሆት ዓይነት ምቹ የማንበቢያ ቦታና የሚነበቡ መጽሐፍት መኖራቸው ቢያንስ ማንበብ የሚወዱና ማንበብ የሚፈልጉ የንባብ ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ማንበብ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
ነገር ግን የሚነበብ ነገር ሞልቶ ተትረፍርፎ ለማንበብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታም እንደልብ ተሟልቶ የሚያነቡት ጥቂቶች ብቻ ከሆኑ፣ ብዙኃኑ የማንበብ ፍቅርና ፍላጎት ከሌለው የሚያነብ ሕዝብ መፍጠር ይቻላል ወይ? ዛሬ በዋናነት ላየውና ላሳየው የፈለኩት አንኳር ሃሳብም በእነዚህ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች ይዘን እንደ ሕዝብ የጎደለንንና ለዘመናት የምንተችበትን ድክመታችን መንስኤ ለማወቅና ለችግራችን መፍትሔ ለማበጀት ጉዳዩን በጥልቀት ስንመረምር ደካማውን የንባብ ባህላችን ለማሻሻል መሬት ላይ ከምንገነባቸው የአብርሆት ማዕከላት በፊት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ቀድሞ መገንባት ያለበት ቀዳሚ አብርሆት መኖሩን እንገነዘባለን።
ከውጫዊው አብርሆት በፊት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ቀድሞ መገንባት ያለበት ዋነኛው የንባብ ባህል ማሻሻያ ውስጣዊ አብርሆት እርሱም ፍቅረ ንባብ(ፍቅረ ንዋይ አላልኩም) ነው። ምክንያቱም የትምህርትና የዕውቀት ብሎም የዕድገትና የብልጽግና መሠረት የሆነው ጠንካራ የንባብ ባህል ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም።
ከሁሉም ከሁሉም በፊት ፍቅር ይፈልጋል። ፍቅሩ ሲኖረን ፍላጎቱ ይመጣል፣ ፍላጎት ካለ ደግሞ ያንኑ የምንፈልገውን ነገር ከምኞት አልፈን በተግባር እናደርገዋለን፣ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ደግመን ደጋግመን እናደርገዋለን።
ቀጥሎም የተደጋገመው ድርጊታችን ልማዳችን መሆን ይጀምራል፣ ልምዱ ባህሪያችን፣ የእያንዳንዳችን ግለሰባዊ ባህሪይ ተደምሮ እንደሕዝብ የምንንከባከበውንና ቅድሚያ የምንሰጠውን መለያ ባህላችን ይሆናል። የማንበብ ባህልም በዚህ መንገድ ነው የሚገነባው።
ጀርመናውያን በአንድ ወቅት “በመጸዳጃ ቤቶቻችን የምናነበው ነገር ይቀመጥልን” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መንግሥታቸውን መጠየቃቸውን ታሪክ ይነግረናል።
ይህም ጀርመናውያኑ እንዲህ ዓይነቱን ድንቅ የንባብ ባህል እንዴት አዳበሩት፣ እኛስ የንባብ ባህላችንን ለማሻሻልና እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ያመላክተናል፡፡
ጀርመናውያኑ መጸዳጃ ቤት ውስጥም ሆነው ማንበብ ይፈልጋሉ ማለት እጅግ የሚደነቅ ከፍተኛ የሆነ የንባብ ባህል አላቸው ማለት ነው። ለመሆኑ ጀርመናውያኑን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳይቀር እንዲያነቡ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድነው? እንዲህ ዓይነቱን አንባቢነትስ “የንባብ ባህል” የሚለው ብቻ ይገልጸዋልን? ደካማውን የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመርመርና መመለስ ይገባናል።
የንባብ ባህላችን ለማሻሻል ትልቁ ሚስጥር ያለው በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ነውና። የዳበረ የንባብ ባህልን ለመፍጠር በቅድሚያ “የዳበረ(ለስሜት የጋለ ነው የሚባለው) የጋለ የንባብ ፍቅር” ሊኖረን ይገባል።
አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር፤ እንደ አገር የዳበረ የንባብ ባህል ባለቤት ለመሆን መፍትሄውም ይኸው ነው-መጽሐፍትን ማፍቀር፣ ንባብን ማፍቀር! ምክንያቱም አንድን ነገር ሳንፈልገው፣ ሳንወደው እንዴት እንዲኖረን እናደርገዋለን? እናም በምንፈልገው ነገር ላይ ጥሩ ችሎታ እንዲኖረን ከፈለግን ከሁሉም በፊት ለዚያ ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ከላይ የተገለጸው የጀርመናውያኑ ሁኔታም የሚያሳየን ይህንኑ ነው።
እነሱ አይደለምና በመደበኛው ጊዜያቸው በዚያች የመጸዳጃ ቤት የደቂቃ ቆይታቸውም የሚነበብ ነገር ማጣት አይፈልጉም። ለምን ቢሉ ንባብን ያፈቅሯታልና! ከማንበብ ፍቅር ይዟቸዋልና! ይህም የንባብ ፍቅራቸው በከፍተኛ ደረጃ የዳበረና የበለጸገ የንባብ ባህልን ፈጠረላቸው።
የእኛም አገር ችግር የንባብ ባህል አለማደግ ሳይሆን የንባብ ፍቅር አለማደግ ነው። ለመሆኑ ማንበብ እንወዳለን? ስንቶቻችን ነን ለመደበኛ ትምህርት ወይም የሆነ አስገዳጅ ነገር ተፈጥሮብን ካልሆነ በስተቀር ለንባብ ፍላጎት ኖሮን፣ ፍቅሩ ኖሮን የምናነበው? ማንበብን የምንስለውስ እንዴት ነው? እንደ አንድ አስጨናቂ ሥራ ወይስ እንደ አዝናኝ የአዕምሮ ምግብ? መልሱን ለእያንዳንዳችን ልተወው። ከዚሁ ከንባብ ፍቅር ጋር በተያያዘ አንድ ወዳጄ ያወራኝን ቀልድ የምትመስል ዕውነት ነግሬያችሁ ወደ ቀጣዩ ክፍል ልለፍ።
“ልጆች ያስቀመጥከውን ብር እያነሱ ካስቸገሩህ መጽሃፍ ውስጥ ደብቀው፣ ሌባ ይወስድብኛል የሚል ስጋት ካለህም ይህ ዘዴ ግሩም መፍትሄ ይሆንልሃል”። አይገርምም!? በእኛ አገር መጽሃፍት የሚፈለጉና የሚፈቀሩ ሳይሆኑ የሚያስፈሩና የሚያስጠሉ ናቸው ማለት ነው? ታዲያ እውነት መጽሃፍትን እየፈራናቸውና እየጠላናቸው፤ እንዲህ እየሰለቸናቸው ከሆነ እንዴት ነው የንባብ ባህላችን የሚያድገው? እናም ከዚህ አመለካከታችን ተላቀን እንደ ሌሎቹ የዳበረ የንባብ ባህል ለመገንባት ያግዘን ዘንድ የዳበረ የንባብ ባህል ምንጭ የሆነው የንባብና የመጽሃፍት ፍቅር ሊኖረን የግድ ይላል።
አለበለዚያ እንኳን አንድ አብርሆት ሌሎች ሺህ አብርሆቶችን ብንገነባ ትርጉም የለውም፡፡ የንባብ ፍቅር ከሌለ፣ የንባብ ፍላጎት ከሌለ፣ የሚያነብ ከሌለ መጽሐፍትና መጽሐፍቱ የሚነበቡበት ቦታ ዋጋ የላቸውምና! እናም መሬት ላይ የተገነባው አብርሖት የመጻሕፍት ማዕከል የታለመለትን ዓላማውን ማሳካት ይችል ዘንድ ንባብን የምናፈቅርበት አብርሆት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሊገነባ ይገባል።
መንግሥት ውጫዊውን አብርሆት ገንብቷል፤ የውጫዊውን አብርሆት ዓላማ ከግብ ለማድረስ ውስጣዊውን አብርሆት መገንባት ግን የዜጎች ኃላፊነት ነው! ውሃን ከጥሩ ቢጠጡት፣ ነገርን ከሥሩ ቢሰሙት መልካም ነውና፤ እስኪ በተሰማሩባቸው ዘርፎች አብዝቶ ተሳካላቸው የዓለማችን ታላላቅ ሰዎች የስኬታቸውና ታላቅነታቸው መሠረት የሆነውን የንባብ ባህላቸውን ስለፈጠረላቸው የንባብ ፍቅር ያሉትን በራሳቸው አንደበት ከተናገሩት የሁለቱን ብቻ ላካፍላችሁና ጽሑፌን ላብቃ።
ዶክተር ጀምስ ስኖውደን የተባሉ እውቅ ደራሲና መምህር ስለንባብ ፍቅር እንዲህ አሉ፡- “መጽሃፍት ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶችንና የዓለማችን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሃብቶች-የሃሳብ ጭነቶችን የተሸከሙ ጀልባዎች ናቸው።
ከሚኖሩህ ነገሮች ሁሉ የተወሰኑ ጥሩ መጽሃፍት ይኑሩህ። አንብባቸው፣ አሰላስልባቸው፣ ያላቸውን ወደ ነፍስህ እስኪያንጠበጥቡልህና ጠቢብ፣ ባለፀጋና ብርቱ እስኪያደርጉህ ድረስ ወደ ልብህ አስጠግተህ እቀፋቸው”፡፡
ሎርድ ማክዋሌ የተባለ ብሪታኒያዊ የታሪክ ጸሃፊ፣ ዕውቅ ሃያሲና ዝነኛ ፖለቲከኛ ደግሞ ስለንባብ ፍቅር የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡ “ሁልጊዜም ትንሿን ልጄ ስለማስደሰቴ ሐሴት ይሰማኛል-እርሷ መጽሃፍትን የመውደዷን ያህል ደግሞ የሚያስደስተኝ ምንም ነገር የለም። ምክንያቱም እንደ እኔ እድሜዋ ሲገፋ መጽሐፍት ከየትኛውም ኬክ፣ አሻንጉሊትና ከማንኛውም ጨዋታና ትዕይንት ሁሉ የተሻሉ መሆናቸውን ትገነዘባለች።
ማንም እስከ ዛሬ ከኖሩት ነገሥታት ሁሉ ታላቁ እንዲሁም ባለ ቤተ መንግሥትና ባለ አትክልት ሥፍራ ቢያደርገኝ፣ የተመረጠ የእራት ግብዣ ከወይን መጠጥ ጋር የሚቀርብልኝ ንጉሥ ሊያደርገኝ ቢፈልግ እንኳ መጽሐፍትን የማንበብ ዕድል ከሌለኝ ንጉሥ መሆንን ነፍሴ አትቀበለውም። ማንበብን የማያፈቅር ንጉሥ ከመሆን ከበርካታ መጽሐፍቴ ጋር በአንዲት ትንሽ ክፍል ብታጎር እመርጣለሁ፡፡”
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥር 17/2014