አካዳሚያዊ – ፖለቲካዊ ምክረ ሀሳብ
1. መግቢያ
በቶማስ ኪልማን የግጭት ሞዴል ኢንስትሩመንት መሠረት በዓለም 5 የግጭት ማስወገጃ (conflict management) ዘዴዎች አሉ፡፡ እነሱም፡- ትብብር (collaborating)፣ ውድድር (competing)፣ አካታችነት (accommodating)፣ ይቅርታ አድራጊነት ወይም አውቆ መተው (compromising) ናቸው፡፡
ግጭቱ ከቆመ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ወደ ሥራ የሚገባው ተከስቶ የነበረው ግልፅ ጦርነት ወይም ግጭት ሲጠናቀቅ ወይም ሲቆም ብቻ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የግጭት ሁኔታ ለዓመታት ወይም አስርተ ዓመታትን የወሰደ ሊሆን ስለሚችል ግጭቱ በቀላሉ እንደገና የሚያገርሽበት ዕድሉ ከፍ ያለና ወደ ከፋ ቀውስ ሊወስድ ስለሚችል የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራን አስፈላጊ አድርጎታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እ.ኤ.አ በሚያዝያ 1 2014 ይፋ በሆነው የሰላም እና ደህንነት ትርጉም መሠረት ሰላም መፍጠር (peacemaking) ማለት ገደብ የማይደረግበት ሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሕጋዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ግጭትን ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡
በሌላ በኩል ሰላም ግንባታ (Peacebuilding) ማለት ከሂደት ያለፈ እና ሰፊ የድህረ ግጭት አጀንዳ ያለው እና ኢንስትሩሜንታዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ማለት ነው፡፡
ሰላም ግንባታ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እና ግጭቶች ተመልሰው እንዳይከሰቱ ለማድረግ የግጭቶችን ምንጭ በመለየት ከስሩ ለመፍታት ዕርቅ፣ ተቋም ግንባታ፣ እና መዋቅራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሽግግር(Transformaion) ማምጣትን የሚያካትት ነው፡፡ በማለት ይገልፃቸዋል፡፡
ሰላም ግንባታ (Peacebuilding) ፈርጀ ብዙ አተያዮች እና ግቦችን በማካተት በማደግ እና ጥልቀት እያገኘ በመሄድ ላይ የሚገኝ ከድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የመጣ ንድፈ ሀሳብ እና ተግባር ነው፡፡
ፅንሰ ሀሳቡ የሰላም እና ደህንነት ጥናት ቀሲስ በሚባለው እንግሊዛዊው ጆን ጋልተንግ አማካኝነት ከተዋወቀበት እ.ኤ.አ ከ1976 ጀምሮ በጦርነት በሚታመሱ አገራት ሰላምን የሚያሰፍኑ የድህረ ግጭት ተግባራትን በማከናወን ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ተደርጎ የተወሰደ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የድህረ ጦርነት ዘላቂ ሰላም እና መልሶ ግንባታ ፅንሰ ሀሳብ የጎላ ግምት እና እውቅና እያገኘ መጥቷል፡፡ የቀድሞዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ሴክሬታሪ ጄኔራል የነበሩት ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊና ጋናዊው ኮፊ አናን የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ከፅንሰ ሀሳብነት ወደ ተግባርነት እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ የመጀመሪያውን የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ጽሕፈት ቤት በላይቤርያ በመክፈት የሰላም ግንባታ ተግባራት ከሞላ ጎደል ውጤት እንዲመጣ ጥረት ተደርጓል፡፡
በዚህ መሠረትም ድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ዋንኛው የሰላም ግንባታ ተግባር ሆኖ እንዲቀጥል በር ከፍቷል፡፡ የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ተግባራት ቅደም ተከተል (Priority) ሊዘጋጅለት እንደሚገባ እና በጥናት ላይ ተመስርቶ በቁልፍ የግጭቱ መንስኤዎች አተኩሮ እንደሚፈፀም ይገለፃል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጀመሪያው የሰላም ግንባታ ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በ 2005 ተቋቁሞ ድህረ ጦርነት ተግባራትን በመስራት ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከንድፈ ሀሳብነት አልፎ ሥራ ላይ መዋል ተጀምሯል፡፡
ድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ማለት ሰላምን ለማስፋት እና ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችሉ መዋቅሮችን ለይቶ በመደገፍ እና በማጠናከር ግጭት እንደገና እንዳያገረሽ የሚወሰድ እርምጃ ነው፡፡
ሰላም ግንባታ በሕዝብ ውይይት ይጀምርና የጋራ መግባባት በመፍጠር የተከሰተው ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያበረታታ፣ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የተቃርኖ ግንኙነት ወደነበረበት የሚመልስ እና የተቋማት ማሻሻያ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚከናወን ውስብስብ የረጅም ጊዜ ሂደት ነው፡፡
ድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ (Post-conflict reconstruction (PCR) የተሳሰሩ የአጭር፣ የመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ውስብስብ ሂደቶችን አልፎ ግጭት እንዳይባባስ እና እንዳያገረሽ ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚከናወን የመልሶ ግንባታ ተግባር ነው፡፡
2. ሰላም የመፍጠር እና መልሶ ግንባታ ግብ ሰላም የመፍጠር እና መልሶ ግንባታ ግብ በጦርነት በተጎዱ አገራት የነበረው ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ የመልሶ ግንባታ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡
3. ሰላም የመፍጠር እና መልሶ ግንባታ ዓላማዎች
1. ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ
2. ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሠረት የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ማምጣት
3. በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ኃይሎች ድርድር እና ዕርቅ እንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት 4. ፍትህ እና ርትዕ በማስፈን ጦርነቱ የፈጠራቸው የተለያዩ ጠባሳዎችን እና ጉዳቶችን ማከም
4. የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ የሚያካትታቸው ዋና ዋና ተግባራት
1. የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ( humanitarian assistance)
2. መልሶ ማቋቋም(Rehabilitation)
3. የፀጥታ እና ደህንነት ሴክተር ሪፎረም ማድረግና አፈፃፀሙን ማዘመን (Reform and Modernization)
4. የተፈጠረውን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል (Sustainability)
5. ቅድመ ጥንቃቄ እና ምላሽ (early warning and response efforts)
6. ግጭት እና ጥቃትን መከላከል( violence prevention)
7. ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ( military intervention)
8. ሰላም ማስከበር ( peacekeeping )
9. የተኩስ አቁም ስምምነት (ceasefire agreements)
10. የሰላም ዞኖችን ማቋቋም ( establishment of peace zones)
11. ግጭቱን የቀሰቀሱ ተዋናዮችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ከታጣቂነት መቀነስ እና እንደገና ማዋሀድ (Disarmament,Demobilization and Reintegration)፡፡
12. ፈንጅዎችን ማምከን (Mine Action) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ (Post conflict Peace Building) በተለያዩ ደረጃዎች (ፌዞች) ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ነጥቦች
ሀ) ደህንነትን ማረጋገጥ
ለ) ኢኮኖሚያዊ መልሶ ግንባታ ማከናወን
ሐ) የማህበራዊ መልሶ ግንባታ ሥራዎች እና
መ) ፖለቲካዊ መልሶ ግንባታ ተግባራትን በቀጣይነት፣ በጥራት እና ብቃት መፈፀም ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም በአጭር እና ረጅም ጊዜ ታቅደው የሚከናወኑ የመልሶ ግንባታ ፕሮግራሞች መረጋጋትን የሚያመጡ እና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ስለመሆን አለመሆናቸው የተለያዩ መለኪያዎችን በመጠቀም እየፈተሹ መቀጠልን ይጠይቃል፡፡
በአንፃሩ የአሻጋሪ መልሶ ግንባታ (Peace Transformation) ግብ በተራዘመ ጊዜ የሕዝብን አስተሳሰብ የመለወጥ፣ አለመግባባትን ከሚፈጥሩ የተዛቡ የሀብት አጠቃቀም እና ግንኙነቶች እንዳይኖር ማድረግ፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስተዋፅኦ ያላቸውን እንዲሁም ሀብትን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ አካባቢያዊ ተቋማትን መገንባት ነው፡፡
ግጭትን የማሻገር ተግባር ሦስት ገፅታዎች አሉት፡፡
1) ከግጭቱ ተዋንያን ጋር የተያያዙ
2) ተዛማጅ የሆኑ ጉዳዮች
3) መዋቅራዊ እና ባህላዊ የሆኑ ናቸው፡፡
5. የድህረ ጦርነት ሰላም ግንባታ ዋና ዋና ገፅታዎች (Components)
ሰላም የመፍጠርና መልሶ ግንባታ ተግባራት መዋቅራዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም እና ብቃት ለመገንባት የሚረዳ ፈርጀ ብዙ የፖሊሲ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ የሚያውል ነው፡፡
የድህረ ግጭት ሥራ በሦስት ደረጃዎች በመከፋፈል የሚሠራ ነው፡፡ ይሄውም
1) የደህንነት
2) የአስተዳደር
3) ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ብለን ልንመድባቸው እንችላለን፡፡ በድህረ ግጭት ጊዜያት መሠረተ ሰፊ ጥረት በማድረግ ሰላማዊ ሁኔታን ለማንገስ እና የተቀናጀ የፀጥታ እና ደህንነት ሥርዓት እንዲኖር የሚያደርግ ሰላምን የማረጋገጥ እና መልሶ ግንባታ ተግባራት ይኖራሉ፡፡
በዚህ መሠረት በዋና ዋና የሰላም እና ደህንነት ሥራዎች ማዕቀፍ ውስጥ የተመሠረቱ የድህረ ግጭት በርካታ ተግባራት ታቅደው የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሰላም ለመደፍረሱ ምክንያት የሆኑ የግጭት ተዋንያኑን ትጥቅ ማስፈታት (disarmament)፣ የግጭቱ መንስዔ እና ተዋናይ የሆኑ ታጣቂ አካላትን መበተን ወይም ለሰላሙ ጠንቅ እንዳይሆኑ ማድረግ(Demobilization)፣ የግጭት ተዋናይ የሆኑ አካላትን መልሶ ማዋሀድ (Reintegration)፣ የደህንነት ኣካላት እና ሥርዓቱ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያ ሥራዎች (Security Sector Reform-SSR) እና ፈንጅዎችን ማምከን (Mine Action) ይሆናል፡፡
ከግጭት አዙሪት የወጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ደካማ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የበዛ የፍትህ እጦት ስሜት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም መልካም አስተዳደር ለመፍጠር የሚያገለግል ሙያዊ አቅምና ብቃት ክፍተትን በግጭቱ ሂደት አስተናግደውት አልፈዋል ወይም አጥተውታል፡፡
ይህን የተወሳሰበ ማህበራዊ ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት እና የተረጋጋ አስተዳደር ለመፍጠር የሚያስችለው ደግሞ ሥራዎችን ተቋማዊ በማድረግ ማሻሻያ ሠርቶ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የግጭት በራሱ በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ መሪዎቹን እንዲመርጥ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ምንጩን በመለየት ግጭቱን ለማስወገድ የሚረዳ እና ብቃት ያለው አስተዳደራዊ ሥርዓት ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ ቀጣይነት ያለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቁልፍ ተግባር ይሆናል፡፡
6. የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራ
ተዋናዮች በተለያዩ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ሊያከናውኑ የሚችሉ በርካታ ተዋናዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተዋናዮች ከክልል መስተዳድር፣ ከማዕከላዊ መንግሥት፣ ከብዙኃን ማህበራት፣ መያድ እና ከግሉ ሴክተር የተውጣጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተዋናዮች የሥራው ዕቅድ ሲዘጋጅ፣ በገቢ ማሰባሰብ ተግባር፣ ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ እና በክትትል እና ቁጥጥር ሂደት ሊሳተፉ የሚችሉ ናቸው፡፡
በድህረ ጦርነት ሰላም ግንባታ ሂደት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግጭት አፈታት እና ድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ተግባራት የሚከናወኑበት በርካታ መሣሪያዎች (ዘዴዎች) ያሉት እና አብሮ የመሥራት ልምዱ ያለው በመሆኑ ለዚህ ሥራ ቁልፍ ተዋናይ መሆኑ አይቀርም፡፡
በተጨማሪም ያደጉ አገራት፣ እምነት የሚጣልባቸው ወይም ተቀባይነት ያላቸው የአካባቢ አገራት፣ የነበሩ ወይም ወዳጅ አገራት፣ እምነት የሚጣልባቸው የጎረቤት አገራት በሰላም ግንባታው ሂደት ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች የግጭቱን መዋቅራዊ ዳይናሚክስ እና ባህላዊ መንስኤ የሚገነዘቡ በመሆናቸው ለሰላም ግንባታው ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡
የግሉ ሴክተር ተዋናዮች ደግሞ በመልሶ ግንባታው ሂደት የፋይናንስ አቅም እና ጉልበቱ ስላላቸው የሰላም ግንባታ ዕድልና አጋጣሚዎችን በመፍጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡
7. በድህረ ጦርነት ሰላም ግንባታ አፈፃፀም ሂደት ወቅት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አስቸኳይ የሰላም ግንባታ ሥራዎች ስናከናውን ፍጥነት (Sense of urgency)፣ ገንዘብ እና አቅም ውስንነት በሚያጋጥመን ወቅት ለሰላም ግንባታ ሥራው ቅደም ተከተል አውጥቶ መንቀሳቀስ የሚያስቸግር ይሆናል፡፡
ሆኖም የምናከናውነው ተግባር የሚያመጣው ውጤት ተመዝኖ ያስቀመጥነውን ቅደም ተከተል ሳንከተል ልንፈፅመው እንችላለን፡፡
መሠረታዊ የሰላም ግንባታ ቅደም ተከተል መለኪያዎችን ስናስቀምጥ ሰላምን ለማጠናክር የሚያበረታቱ፣ ግጭቱ ተመልሶ የሚከሰትበትን ዕድል የሚቀንሱ እና የጦርነቱን መንስዔ ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን መርጦ በቅደም ተከተል መተግበር ተገቢ ይሆናል፡፡
ቅደም ተከተል የማስቀመጡ ሂደት ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ተዋናዮች ፍላጎት ይልቅ የአገሪቱን ልዩ ሁኔታ፣ የግጭቱ ታሪክ እና ካለው የሰላም ፍላጎት አኳያ ትኩረት የሰጠ ሊሆን ይገባዋል፡ ፡ ለምሳሌ ተፈናቃዮችን ወይም ከስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡
ወይም የአገሪቱን ማህበረሰቦች የሚከፋፍላቸው ምንድን ነው ብሎ በመጠየቅ ለዚህ መፍትሄ ማፈላለግ ቅድሚያ የሚሰጠው ሊሆን ይችላል….. ይሁንና ከግጭቱ መቆም በኋላ የሰላም ግንባታውን ውጤት የሚጎዱ መቻኮሎች፣ ሴራ እና ጥርጣሬዎች፣ ስጋት፣ ስልጣንን ለማጠናከር ወይም ወደ ስልጣን ለመውጣት ከመፈለግ የሚመነጩ ማኪያቬሊያዊ ተግባራት በመስዋዕትነት እና ድካም የተፈጠረውን ሰላም እንዳያሽመደምዱት እና ወደ ኋላ እንዳይመልሱት መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ማከናወን የፖለቲካ ስልጣን ሕጋዊነትን የሚያጎናፅፍ የመሆኑን ያክል የውጥረት መንስኤ በመሆን ወደ አዲስ ግጭት እንዳያስገባ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በጥራት ምትክ ፍጥነትን በመምረጥ ወይም ያለ አስቻይ የፖለቲካ እና አመራር ሁኔታ ሥራውን መጀመር የሰላም ግንባታ ሂደቱን በመቀልበስ ግጭት እንደገና ሊቀሰቅስ የሚችል በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ 8. በድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሂደት የሚቀርቡ ትችቶች 1. የሊበራሎች ሰላም ግንባታ አቀራረብ የሚከተል በመሆኑ ለምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ነው 2. የከባብያዊ ዳይናሚክሱን የዘነጋ ነው 3. የምዕራባውያንን ዕሴቶች በሌሎች ላይ የሚጭን ነው
በጥራት ምትክ ፍጥነትን በመምረጥ ወይም ያለ አስቻይ የፖለቲካ እና አመራር ሁኔታ ሥራውን መጀመር የሰላም ግንባታ ሂደቱን በመቀልበስ ግጭት እንደገና ሊቀሰቅስ የሚችል በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡
8. በድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሂደት የሚቀርቡ ትችቶች
1. የሊበራሎች ሰላም ግንባታ አቀራረብ የሚከተል በመሆኑ ለምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ነው
2. የከባብያዊ ዳይናሚክሱን የዘነጋ ነው
3. የምዕራባውያንን ዕሴቶች በሌሎች ላይ የሚጭን ነው
ተዋናዮች በተለያዩ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ሊያከናውኑ የሚችሉ በርካታ ተዋናዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ተዋናዮች ከክልል መስተዳድር፣ ከማዕከላዊ መንግሥት፣ ከብዙኃን ማህበራት፣ መያድ እና ከግሉ ሴክተር የተውጣጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ተዋናዮች የሥራው ዕቅድ ሲዘጋጅ፣ በገቢ ማሰባሰብ ተግባር፣ ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ እና በክትትል እና ቁጥጥር ሂደት ሊሳተፉ የሚችሉ ናቸው፡፡
በድህረ ጦርነት ሰላም ግንባታ ሂደት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግጭት አፈታት እና ድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ተግባራት የሚከናወኑበት በርካታ መሣሪያዎች (ዘዴዎች) ያሉት እና አብሮ የመሥራት ልምዱ ያለው በመሆኑ ለዚህ ሥራ ቁልፍ ተዋናይ መሆኑ አይቀርም፡፡
በተጨማሪም ያደጉ አገራት፣ እምነት የሚጣልባቸው ወይም ተቀባይነት ያላቸው የአካባቢ አገራት፣ የነበሩ ወይም ወዳጅ አገራት፣ እምነት የሚጣልባቸው የጎረቤት አገራት በሰላም ግንባታው ሂደት ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡
ሕዝባዊ አደረጃጀቶች የግጭቱን መዋቅራዊ ዳይናሚክስ እና ባህላዊ መንስኤ የሚገነዘቡ በመሆናቸው ለሰላም ግንባታው ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ የግሉ ሴክተር ተዋናዮች ደግሞ በመልሶ ግንባታው ሂደት የፋይናንስ አቅም እና ጉልበቱ ስላላቸው የሰላም ግንባታ ዕድልና አጋጣሚዎችን በመፍጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡
9. ተቀናሽ ወታደሮችን (ታጣቂ ኃይሎችን) እንደገና ለማዋሀድ ውጤታማ መለኪያዎች
1. ከመጡበት ማህበረሰብ በንቃት የሚሳተፉ አባላት የሆኑ
2. የአንድ ማህበረሰብ አባል ሆነው በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ የተለየ ደረጃ (ኃላፊነት) የሌላቸው 3. የማህበረሰቡ ተራ አባል የሆኑ እና ልዩ ፍላጎት የሌላቸው
10. ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላም ግንባታ ሂደት ወቅት የሚያደርጋቸው የምርጫ ድጋፎች 1. የምርጫ ታዛቢዎችን ማዘጋጀት
2. ለብዙኃን ማህበራት ድጋፍ መስጠት
3. ለምርጫ ሥርዓቱ ምክረ ሀሳብ መስጠት
4. የምርጫ አስፈፃሚ አካላትን መደገፍ
5. የፋይናንስ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ
11. በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ግንባታ ኮሚሽን ( UN Peace Building Commision- PBS) የተባበሩት መንግሥታት ሰላም ግንባታ ኮሚሽን የመንግሥታት ውክልና ባላቸው እና የሰላም ግጭት ባስተናገዱ አገራት የሰላም ግንባታ ሂደትን የሚደግፍ አማካሪ አካል ነው፡፡ ይህ ዓለምአቀፍ ተቋም ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከፀጥታው ምክር ቤት እና በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ካውንስሎች ከተወከሉ 31 አገራት በጠቅላላ ጉባኤው አባላትን መርጦ ያካተተ ነው፡፡
በተጨማሪም ለተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚያዋጡ እና በሰላም ማስከበር ብዙ ወታደር የሚያዋጡ አገራት የኮሚሽኑ አባላት ይሆናሉ፡፡ በግጭት ሲታመሱ የነበሩ አገራት እንደራሳቸው ልዩ ሁኔታ ኮሚሽን ቢያቋቁሙ ይመረጣል፡፡
12. ትጥቅ ማስፈታት፣ ታጣቂ (ወታደር መቀነስ እና እንደገና ማዋሀድ (Disarmament,Demobilization and re-integratio (DDR ) ይህን ተግባር የበለጠ ለመገንዘብ የኮንጎ ድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሂደትን በምሳሌነት መውሰድ እንችላለን፡፡ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (DRC) ትጥቅ ማስፈታት፣ ታጣቂ (ወታደር) መቀነስ እና እንደገና ማዋሀድ (Disarmament, Demobilization and re-integration – DDR ) ሂደት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም እና መረጋጋት ተልዕኮ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (MONUSCO) የሚል ስያሜ በመያዝ በጋራ የፈፀመው ነበር፡፡
ተቋሙ ሥራውን የጀመረው እ.ኤ.አ በ2002 በምሥራቃዊ ኮንጎ ኢቱሪ በሚባለው ግዛት የማህበረሰቡን ትጥቅ በማስፈታት እና መልሶ በማቋቋም ሥራዎች (Community Disarmament and resettlement – CDR) ሂደት ነበር:: በወቅቱ ይህ ተልዕኮ በኢቱሪ ክፍለ ግዛት ተፃፃሪ ታጣቂ ሚሊሽያዎችን ትጥቅ ማስፈታት የመጀመሪያ ተግባር ነበር፡፡
በኋላ ግን ሥራው ወደ ኅብረተሰቡ ደረጃ በደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ በሌላ በኩል ይህ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ በግጭቱ ተዋናይ የነበሩ ሚሊሽያዎችን በመቀነስ የመልሶ ማቋቋሙ ተሳታፊ እንዲሆኑ አደረገ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም በኮንጎ ግጭት የተሳተፉ ተዋናዮች ባደረጉት ስምምነት መሠረት የመውጫ(Transit)፣ ሀሳብ የመቀያየሪያ(Orientation) እና እንደገና የመደራጀት (Regrouping) ማዕከላት ተፈጠሩ።
በዚህ መሠረት በኮንጎ ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች በእነዚህ ማዕከላት ለአምስት ቀናት ብቻ በመቆየት ሀሳብ እንዲለዋወጡ፣ ስለ ሂደቱ ግልፅነት እንዲያገኙ እና ምዝገባ ፎርማሊቲዎችን ካሟሉ በኋላ በአገሪቱ ጦር ኃይል ውስጥ እንደገና እንዲዋሀዱ አልያም በመልሶ ማቋቋሙ ሂደት የሲቪል ሕይወት እንዲመሩ ምርጫ ተሰጥቷቸው በፍላጎታቸው መሠረት ተፈፅሟል። በዚህ መሠረት ወታደር ቤት የመረጡት ወደ ማስልጠኛ ገብተው መመዘኛውን ካሟሉ የኮንጎን ጦርን ተቀላቅለዋል፡፡
በስልጠናው ያልተሳካላቸው ደግሞ ተቀናሽ ሆነው ወደ መልሶ ማቋቋም አቅጣጫ ገብተው የሲቪል ሕይወትን እንዲመሩ ተደርጓል፡፡
13. የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ዋና ዋና ተግዳሮቶች የገንዘብ ፍላጎት ወይም እጥረት፣ በዓለምአቀፍ እና ክልላዊ ተቋማት መካከል የቅንጅት ክፍተት መኖር፣ የአስተሳሰብ እና የኮሚኒኬሽን ችግሮች የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት፡- አንድ፡- የገንዘቡ እጥረት ጎልቶ የሚታየው ሰብአዊ አገልግሎት ሥራ ተጀምሮ ለተፈጠረው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ልማታዊ ሥራዎችን ለመስራት በሚጀመርበት ወቅት ነው፡፡
ሌላው ረጂ አካላት ከፍተኛ ቀውስ ለሚያስከትሉ፣ ትኩረት ለሚሹ የፖለቲካ እና ደህንነት ሥራዎች ፈንድ ለመልቀቅ አለመፈለግ ነው፡፡
ሁለተኛው፡- ሥራውን በባለቤትነት የያዘው መንግሥት ብዙ የእገሩን ተዋንያንን የማቀናጀት ድክመት ነው፡፡ በተጨማሪም ሥራውን ከሚያወሳስቡት ችግሮች መካከል ባህላዊ መሪዎች የሚጫወቱት አሉታዊ ሚና፣ ብዙኃን ማህበራት ደካማ መሆን እና በሲቪል ሰርቪሱ የማኔጅመንት እና የቅንጅት ክፍተቶች የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ዓለምአቀፍ ተዋናዮች ብዙ በሚሆኑበት ጊዜ በሰላም ግንባታ ስትራቴጂዎች ላይ አለመስማማት እና በሚና እና ሥራ ክፍፍል አለመግባባት የሚፈጠር መሆኑ ነው፡፡
ሦስተኛ፡-በድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራ ወቅት የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚያስፈልገው ሀብት የግልፅነት መጓደል፣ ትርጉም ያለው የደህንነት እና ፀጥታ ሴክተር ማሻሻያ አለመደረግ እና በተግባራዊ እንቅስቃሴው አካታች አለመሆን የሚጠቀሱ የሥራው መሰናክሎች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡
አራተኛ፡- የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ተግባርን በኃላፊነት የሚሠሩት የውጭ ኃይሎች ከሆኑ በሂደቱ የሊበራሊዝም ዓለምአቀፋዊነት ሞዴልን ስለሚከተሉ የድህረ ግጭቱን ሰላም ግንባታ ሥራ የራሳቸውን አይዲኦሎጂ ለማስረፅ እና ለመትከል ስለሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ከባቢያዊ ዳይናሚክሱን ወደ ጎን ስለሚሉት የነበረው ቀውስ የሚያገረሽበት ዕድል ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ሂደቱንም በምርጫ እና ተቋማት ሪፎርም ስም እነሱን የሚደደግፉ እና አሻንጉሊታቸው የሚሆኑ ግለሰቦችን ወደ ስልጣን በማምጣት ቀውሱን ማባባስ ላይ ይጠመዳሉ፡፡
አምስተኛ፡- ግጭትና ጦርነት ባሰቃያት አገር ውስጥ ስልጣናቸውን በቀጣይነት ለማጠናከር የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራውን ለእነሱ ዓላማ ማስፈፀሚያ ለማድረግ ተግባሩን ቴክኖክራሲያዊ፣ ቢሮክራሲያዊ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሚያደርጉ አገራት በታሪክ አጋጣሚ ታይተዋል፡፡
ከቅንነት እና ወገንተኛ አሠራር ይልቅ በስልጣን ለመቆየት ወይም ወደ ስልጣን ለመውጣት በሚፈልጉ ወገኖች የሰላም ግንባታ ሂደቱን በራሳቸው ፍላጎት አቅጣጫ ሊቀርፁት ይፈልጋሉ (Pathologisation of power)፣ በስጋት የሚያዩትን ስብስብ ለማግለል እና አንገት ለማስደፋት እና አቅም ለማሳጣት (disempowerment) ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ የግጭቱን እውነተኛ መንስኤ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ሰላማዊ መፍትሄ ከመሻት እና ሰላም ግንባታ ተግባራትን ከማከናወን ይልቅ በሴራ እና ተዓማኒነት በማይኖራቸው፣ የዓለም አቀፍ የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ስታንዳርዶችን በማያሟላ ወይም በማይከተል ዕቅድ፣ የሕግ ማዕቀፍ እና መዋቅር ተግባራዊ በማድረግ አደናቃፊ ሆነው ሊመጡ ይችላሉ፡፡
በአጭሩ የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራ ዓለምአቀፋዊ መለኪያዎችን የሚያሟላ ካልሆነ እና በአገራት ልዩ ሁኔታ ካልተቀረፀ የቆየውን ግጭት የማባባስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም እውነተኛ መፍትሄዎችን ከማፈላለግ እና ተጨባጭ ሰላም ከማረጋገጥ ይልቅ በማስፈራራት፣ በተንኮል፣ በማዋከብ፣ በመግደል ወይም በማግለል፣ በሴራ እና አሻጥር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንቀሳቀስ የለብንም፡፡
ሁሉንም ዓይነት ተገቢ ያልሆኑ እና ሰላምን የማያረጋግጡ ተግባራትን በሰላም ግንባታ ስም የሚፈፀሙ ከሆነ ሂደቱ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ መዋቅር እና ተቋም ስንመሰረት ማዕከል መሆን ያለበት ሪፎርም፣ በብቃት ላይ የተመሠረተ ምልመላ፣ ምድባ እና ዕድገት፣ ፍትሀዊ በጀት ምደባ እና ልማት በማረጋገጥ የሰላም ጥረቱን ማበረታታት ይገባል፡፡
ስድስተኛ፡- ግጭት ባመሰቃቀለው አገር ሕዝቡ ባጠቃላይ፣ ሕዝባዊ ማህበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ መንግሥት እና ተፃራሪ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላምን በማምጣት ሆነ ድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ኃይሎች ሰላም እንዲመጣ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ከሆነ፣ ግጭቱን ለራሳቸው ፖለቲካዊ ስልጣን መወጣጫ እና ዓላማ የሚያውሉት ከሆነ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ የሚከተሉ ከሆኑ፣ ግጭቱን በማስቀጠል ለሚፈፅሙ ወንጀሎች እንዲሁም የአገር ሀብት ዘርፎ መደበቂያ ወይም መሸሸጊያ የሚያውሉት ከሆነ፣ ግጭትን የሚያባብስ አስተሳሰብ እና ተግባር ከያዙ፣ ዋልታ ረገጥ ብሔረተኞች ከሆኑ፣ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን የሚሉ ከሆነ፣ ስልጣን ይሰጠኝ አልያም አገር ትፍረስ የሚሉ ከሆነ፣ በግጭት ውስጥ ካሉ ተዋናዮች መካከል አንዱን በመደገፍ ሌላውን የሚያገሉ ከሆነ ሰላም ሊመጣ ይቅርና ግጭቱ ተባብሶ አገርሽቶ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
በተጨማሪም ሰላም በመፍጠር ሂደቱ ስልጣንን ለማጠናከር ወይም ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚደረጉ ማናቸውም የሴራ ድርጊቶች እንዳይኖሩ መስራት ይጠበቃል።
የፍትህ ሥርዓቱ ግጭቱ የፈጠረውን ጠባሳ ለማረም እንዲቻል የተለያዩ የአገሪቱ ሕጎችን ተከትሎ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የሕዝብ ቅሬታን እና የቆዩ የመከፋፈል ችግሮችን እንዳያባብስ በጥበብ እና ጥንቃቄ በመምራት የሰላም ግንባታ እና የመግባባት ሂደቱን ተአማኒ እንዲሆን ሚናው የላቀ ነው።
የሰላም ሂደቱን ውጤት ከሚሸረሽሩ ማናቸውም ተቀባይነት የሌላቸውን ጉድለቶች ባለመፈፀም የሰላም ግንባታ ተግባሩን በመግባባት ላይ ተመስርቶ ግቡን እንዲመታ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ሰባተኛ፡- ከግጭቱ በኋላ የመንግሥት ሆነ ግል ሚዲያዎች በገለልተኝነት እና ሀቅ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ መረጃ ባለመስጠት ማደናገር አንዱ ተግዳሮት ነው። የሚዲያው ሚና እና የኮሚኒዩኬሽን ሥርዓቱ ልፍስፍስ መሆን መሠረታዊ የድህረ ግጭት ሥራ ተግዳሮት ነው፡፡ ሜንስትሪም እና ማህበራዊ ሚዲያ ሰላም እንዲመጣ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰላም እንዳይረጋገጥ አፍራሽ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በመሆኑም ሀሰተኛ መረጃ ባለማስተላለፍ፣ ከውግንና የፀዳ መረጃ በመስጠት፣ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ከተንቀሳቀሱ ሰላምን የሚያደናቀፏ ኃይሎችን በመታገል ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ዲሞክራሲን በማቀንቀን፣ አድሎኣዊ አሠራርን ባለመከተል፣ ሚዛናዊ ዘገባ በማስተላለፍ፣ ሕዝብን ሆነ ቡድኖችን ባለማንቋሸሽ ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ባለማግለል፣ አስመሳይ የሆኑ፣ የሀሰት እና ለጥቅም ተብለው የሚሠሩ ዘገባዎችን ባለማቅረብ፣ …ወዘተ ለሰላም ግንባታ ሥራው አጋዥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ማጠቃለያ፡-
አገራችን በግጭት ስትታመስ የቆየች እና አሁንም በመታመስ ላይ ያለች ናት፡፡ ግጭቱ መፍትሄ እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ እና የተባበሩት መንግሥታት ድህረ ግጭት
ሰላም ግንባታ ሥራ አቅጣጫዎች እና መለኪያዎችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የድህረ ግጭት ሥራ እቅድ ተዘጋጅቶለት ሕዝቡ ከዕቅዱ እስከ ሂደቱ እና አፈፃፀሙ የሚሳተፍበት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተቀናጀ ተግባር መፈፀም ይጠበቅበታል።
ለዚህ ሥራ ራሱን የቻለ ከሁሉም አካባቢዎች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት የሚውጣጣ ኮሚሽን እና አማካሪ ቡድን ያስፈልጋል። የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራውን ፖለቲሳይዝ ማድረግ የኢትዮጵያን ችግሮች የሚያስቀጠል ነው፡፡
ግጭቱ እንደተጠናቀቀ አገር ለማፍረስ ታጥቀው ሕዝቡን እና መንግሥትን የወጉ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው። በሂደት ሕዝቡ ውስጥ ተሰራጭቶ የሚገኝ የጦር መሣሪያ መልክ እንዲይዝ መሠራት አለበት።
ሕዝብ እና መንግሥትን ሲወጉ የነበሩ ቡድኖች ከነበሩበት የታጣቂነት ተሳትፎአቸው ተቀንሰው የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ስልጠና ወስደው ውጤታማ የሆኑት ከሚሊተሪው ወይም ከሌላው የፀጥታ ኃይል ጋር መዋሀድ ከዚህ ውጪ የሆነው ደግሞ በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም የሲቪል ሕይወት መጀመር አለባቸው፡፡
የድህረ ጦርነቱ ሥራ በእነዚህ ታጣቂዎች ላይ ትኩረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በመንግሥት ጥሪ ከአገር መከላክያ ጋር ተሰልፎ መስዋዕትነት የከፈለውን የአማራ እና አፋር ሕዝብ፣ አርሶ አደር ሚሊሽያ እና ፋኖ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና ሚሊሽያ፣ የሲዳማ፣የደቡብ፣ የቤኒሻንጉል፣የሶማሌ ልዩ ኃይሎች መካከል በፈፀሙት ጀብዱ መጠን እና ተሳትፎ መጠን የክብር ሽልማት እና እውቅና የሚገባቸው ናቸው፡፡
እውቅና እና ሽልማት ሲቪል እና ታጣቂውንም የሚመለከት ቢሆን መልካም ነው፡፡ በአዋጅ እና መመሪያ ያዘመትነውን ኃይል መስዋዕትነት ከፍሎ ከአገሪቱ መከላክያ ጎን በመሰለፍ ታሪክ እና ጀብዱ ፈፅሞ ጠላት እንዲሸነፍ እና አገር እንዳትፈርስ ያደረገውን ልዩ ኃይል ታጣቂና ሚሊሽያ እውቅና እንዲያገኝ መሥራት አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪም በተዋጊነት እና ሎጂስቲክ በማቅረብ፣ ደጀን በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረውን ሕዝብ በአሉባልታ ገና ጦርነቱ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ፣ ግጭቱን ለማስቀጠል በልሂቃን እና ሚዲያው የሚናፈሰው ወሬ ለሕዝብ አይመጥንም፡፡ ሰላም ለማውረድም አይጠቅምምም፡፡
የወደፊቱ ድህረ ግጭት ተግባር ዓለምአቀፍ ስታንዳርዱን ያሟላ፣ የተባበሩት መንግሥታት መለኪያ መስፈርቶችን እና ዘዴዎችን እንዲያካትት በማድረግ በኢትዮጵያ ልዩ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ፣ ባህል እና የሕዝብ ፍላጎት ልዩ ሁኔታ በማቀድ በየደረጃው የሚገኝ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና ምሁራን የሚሳተፉበት የድህረ ግጭት ሰላም ግንባታ ሥራ እንደሚኖር ተስፋ ይደረጋል፡፡
አገሪቱ የአንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ ወይም የተወሰኑ ብሔሮች የግል ሀብት ባለመሆኗ መላው ሕዝብ በነቂስ የሚሳተፍበት፣ የግልፀኝነት እና ተጠያቂነት አሠራር ጎልቶ የሚታይበት ሰላም ግንባታ ሂደት እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡ የግጭት አፈታት ሂደቱን ፖለቲሳይዝ በማድረግ ለፖለቲካ ዓላማ በማዋል አቅጣጫውን እንዳይስት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ግጭቱ እንደገና ካገረሸ የሚያስከትለው ውድመት ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል በጠራ ዕቅድ እና ዝግጅት፣ በዲሞክራሲያዊ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ አካታች ሆኖ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና ሕግ አግባብ ተመስርቶ እንዲሁም የሌሎች አገራትን ልምድ በመውሰድ ዘላቂ ሰላም ማውረድ ይበጀናል፡፡ ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!::
ዋቢ መጻሕፍት
Aycan Kazanç(2013). Post conflict peace building. International Relations, AÖF Timothy A. Donais(2009).Empowerment or Imposition? Dilemmas of Local Ownership in Empowerment or Imposition? Dilemmas of Local Ownership in Post-Conflict Peacebuilding Processes. Wilfrid Laurier University, tdonais@wlu.ca Reilly, B. (2013). Political parties and postconflict peacebuilding. Civil Wars, 15 (S1). pp.88-104.Mudroch University. Avilable at http:// researchrepository.murdoch.edu.au/id/eprint /20332/ Maria Kim (2004). POST-CONFLICT PEACEBUILDING REVISITED: ACHIEVE MENTS, LIMITATIONS, CHALLENGES Contents. Clarity, Coherence and Context: Three Priorities for Sustainable Peacebuilding. New York Wendy Lambourne (2004). Post-Conflict Peacebuilding: Meeting Human Needs for Justice and Reconciliation. Peace, Conflict and Development – Issue Four, April 2004. ISSN: 1742-0601 Filip Filipov (2006). Post-conflict Peacebuilding: Strategies and Lessons from Bosnia and Herzegovina, El Salvador and Sierra Leone. Some thoughts from the rights to education and health. Social Development Division.Human Rights Unit. Políticas sociales. Santiago, Chile, September, 2006 Alex Comninos (2013).The Role of Social Media and User-generated Content in Post-Conflict Peacebuilding.102 The International Bank for Reconstruction and Development / The World Bank 1818 H Street, NW Washington, DC 20433 www. tdrp.net www.worldbank.org 560. Author. (2021). My Own Observation and knowledge
ደምስ ይግዛው አየለ( እ/ዶ/ር)
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014