የዛሬው እንግዳችን ዶክተር እርቁ ይመር ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በወሎ ጠቅላይ ግዛት ቦረና አውራጃ ውስጥ ልዩ ሥሙ መካነ ሰላም በሚባል አካባቢ ነው። በቦረና ትምህርት ቤት እስከ አምስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ በአካባቢው መለስተኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ደሴ ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቢሮ አስተዳደር ዘርፍ ተከታትለው ዲፕሎማቸውን አገኙ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ለጥቂት ወራት ካገለገሉ በኋላ ወደ ተማሩበት ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተመልሰው በጸሐፊነት ለሁለት ዓመት ሰሩ። በመቀጠልም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ማኅበራዊ አገልግሎት በተባለ ትምህርት ክፍል ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ። በተማሩበት የሙያ ዘርፍም ቤተሰብ መምሪያ በሚባል ዓለምአቀፍ ተቋም ውስጥ ተቀጥረው ለአራት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ ሄዱ።
በማኅበረሰብ ጥናትና ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ሲሉ ግን ወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀይ ሽብር እንቅስቃሴ በመፋፋሙ እና በዚህ ምክንያትም አንዳንድ ጓደኞቻቸው ሕይወታቸው በማለፉ እዛው ለመቆየት ወሰኑ። ይሁን እንጂ የተማሪነታቸው ጊዜ በመጠናቀቁ የአሜሪካ ኢምግሬሽን መሥሪያ ቤት ‹‹ ሕገወጥ ስደተኛ›› በሚል ፍርድ ቤት አቀረባቸው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ዳኛው ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ ያውቁ ኖሮ ‹‹ዜግነትን ቀይርና ጥገኝነት እንስጥህ›› ቢሏቸውም አገር እንደመክዳት ስለቆጠሩት አሻፈረኝ አሉ። በምትኩ የስድስት ወር ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ወደ ደቡብ ሱዳን በመሄድ ጁባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ለማገለገል ይወስናሉ። ሆኖም የአምስት ዓመት ልጃቸውን ይዘው ወደ ደቡብ ሱዳን መምጣቱ ከባድ መሆኑን በመረዳታቸው ሃሳባቸውን በመቀየር አሜሪካ ይቆያሉ። ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ ታክሲ ማሽከርከር ጀመሩ። ከታክሲ ሥራቸው ጎን ለጎን በዊስኮንሲን መዲሰን ዩኒቨርሲቲ ገብተው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠሩ።
የዛሬ የዘመን እንግዳችን በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በየአገሩ ተሰደው የነበሩ ዜጎችን ለመቀበል በተቋቋመው በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበር በዋና ዳይሬክተርነት ለ32 ዓመት ያክል አገልግለዋል። በዚህ ማኅበር አማካኝነት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከመላው ዓለም የሚመጡ ስደተኞች ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው ይጠቀሳል። ማኅበሩ ለስደተኞች ስልጠና በመስጠትና የኢትዮጵያ ሙዚየም በቺካጎ እንዲቋቋም የእኚሁ እንግዳችን ሚና ከፍተኛ ነው። በእ.ኤ.አ አ2016 ዓ.ም ጡረታ ቢወጡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮንግረስ በተባለ የሲቪክ ድርጅት ውስጥ ከሌሎች አገር ወዳድ ድርጅቶች ጋር በመሆን ይንቀሳቀሱ ነበር። ኮንግረሱ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የሚሠሩበትን ምህዳር እንዲፈጠር በማድረግ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በተለይም በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ተመሳሳይ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉና ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተዋህደውና ጥምረት ፈጥረው እንዲሠሩ ኮንግረሱ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። መቀመጫቸውን አሜሪካ ካደረጉ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በትምህርትና በሰብዓዊ አገልግሎት ሽልማት በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ደጋግመው ወደ አገራቸው የመጡት እንግዳችን ባህርማዶ ሆነው ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ያከናውኑት የነበረውን ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስቀጠል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል። በተለይም እየተመናመነ የመጣውን የዜግነት አመለካከትና የአገር ፍቅር ስሜት እንዲመለስ ብሎም ራዕይ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ደፋ ቀና ማለታቸውን ተያይዘዋል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ አሜሪካ ያለውን ድርጅት በኢትዮጵያ ሕጋዊ ሰውነት ይዞ እንዲሠራ አድርገዋል። ይህንን ጥረታቸውን የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በመደገፍ አጋርነታቸውን እያሳዩአቸውም ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዚህና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንግዳ አድርጎ ይዟቸው ቀርቧል። መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ጉባኤ የተባለው የሲቪክ ድርጅታችሁ የተቋቋመበትን ዓላማና በዋናነት ይሠራቸው የነበሩ ስራዎችን በማስተዋወቅ ውይይታችንን ብንጀምር?
ዶክተር እርቁ፡- ይህ ድርጅት በዋናነት የተቋቋመበት ዓላማ በኢትዮጵያ በብሔርም ሆነ በዜግነት ፖለቲካ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች በአንድነት እንዲቆሙና በሚያግቧቧቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንዲሠሩ ለማድረግ ነው። ድርጅታችን በተቋቋመበት ዓላማ መሠረት እነዚህ ፓርቲዎች በጋራና በአንድነት እንዲቆሙ በመሥራት የሚበረታቱ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። እንዳልኩሽ የድርጅታችን ዋና ዓላማው የነበረው በአገሪቱ በርከት ያሉ ድርጅቶች ስለነበሩ የጋራ ፕሮግራሞች ላይ ተወያይተው በሚስማሙበት ጉዳይ ላይ በአንድነት እንዲቆሙ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ነው። ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ እንደሚታወሰው እኛ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ያደረግናቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ተሳትፈው 50 የሚሆኑ መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር። ይሁንና በመሐል በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት አብዛኞቹ ተበታተኑ፤ ግማሾቹ ታሰሩ፤ በተለይ የቅንጅት ሰዎች ‹‹እንገባለን፤ አንገባም›› በሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር።
እናም የሲቪክ ማኅበሩ ድርጅቶቹ ለአንድ ዓመት ያህል ሲወያይበት ቆይቶ ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ የሚባል ድርጅት ለመመስረት አሰብን። ከ13 የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አራቱ ብቻ ራሳቸውን አክስመው ለመዋሃድ መረጡ። ሌሎቹ ግን በጀመሩበት መንገድ ቀጠሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጉባኤዎችን በማካሄድ ፓርቲዎቹ የሚሳተፉበትን እድል ፈጥረናል። በተለይም ሕዝብና የፖለቲካ ድርጅቶች ይደርስ የነበረውን ጭቆና በሚመለከት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፤ ለአሜሪካና ለሌሎች አገራት መንግሥታት አቤቱታ እናቀርብ ነበር። ከሦስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በመምጣቱ እዛ ሆነን የምንሰራው ሥራ ውጤታማ አይደለም ፤ ወደ ሕዝብም አልቀረብንም በሚል ድርጅቱን እዚህም ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ተስማምተን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረግን ነው ያለነው።
በእርግጥ እዛ ሆነን የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን አካሂደናል ፤ ጥናታዊ ሥራዎችንም አሳትመናል። ይሁንና ለውጡ ሲመጣ ወደ አገር መግባት አለብን ብለን ስምንት የምንሆን የድርጅቱ አመራሮች የተለያዩ የመንግስት መሥሪያ ቤቶችን፤ ዩኒቨርሲቲዎችን አነጋግረን ኮሚቴዎችን አቋቁመን ተመለስን። ኮሚቴው ከተቋቋመ በኋላ ግን አንዳንዶቹ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚለው ስያሜ አልተመቻቸውም። አንደኛው ግለሰብ ደግሞ በራሱ ስም ሊያስመዘግበው ሲል ተያዘ። ጥቂቶችም እሱን ተከትለው ወጡ። የቀረነው ግን የማቋቋሚያ ሕግ በማዘጋጀት አገር በቀል የሆነ ድርጅት ሆኖ በቻርተር እንዲመዘገብ አደረግን። ከአለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ሕጋዊ እውቅና ኖሮት ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ድርጅት ነው የተቋቋመው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ድርጅት በአገር ውስጥ ሕጋዊ ሰውነት ካገኘ በኋላ ምን አይነት ሥራዎችን ለመሥራት ነው ያቀደው?
ዶክተር እርቁ፡- በዋናነት ትኩረቱ አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ማስረፅና የአገር ፍቅር ያለው ትውልድ ማፍራት ነው። እንደሚታወቀው የቀደሙት የዚህ ድርጅት ጠንሳሾች መካከል ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ፣ ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ፣ ከንቲባ ገብረህይወት ይገኙበታል። ይሁንና ሁለት ዓመት ያህል ከተንቀሳቀሱ በኋላ በደረሰባቸው ተፅዕኖ እና አብዛኞችም በመሞታቸው ምክንያት ሥራው የተቋረጠበት ሁኔታ ነበር። በተለይም በአገር ውስጥ ይሠራ በነበረው ሕዝብ በታኝ ፖለቲካ ምክንያት የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና እየተሸረሸረ እየተዳከመ መጥቷል። በአንፃሩ ደግሞ የጎጠኝነት ስሜቶች ጎልብተዋል። አንዳንዶቹ የጎጠኝነት ስነልቦና ያላቸው ፓርቲዎች የተመሠረቱት በተሳሳተ ትርክት ነው። ይሄ ትርክት ከቀጠለ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጋጭ፤ ብሔር ለብሔር የሚያፋጅ በመሆኑ መድኃኒቱ የዜግነት ስነልቦና መዳበርና ማደግ አለበት ከሚል ነው የተነሳነው። ያንን ደግሞ ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርፀዋል።
አንደኛው ታሪክን የሚመለከት ሲሆን ከአገረ መንግሥት አመሠራረት ጀምሮ ሌሎች ታሪካዊ ዳራዎችን የሚያንፀባርቁ እና እውነታውን የሚያሳዩ ተከታታይ ትምህርቶችን መስጠት የሚያስችሉ መርሐ ግብሮችን የሚያካትት ነው። ከዚህም ባሻገር ሕዝብ ለሕዝብ የተወራረሱ ባህል እና እሴቶችን ለሕዝብ ለማሳወቅና በአገር አንድነት፤ እኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት አስፈላጊ የሚል እምነት አለን። ያ ካልሆነ ግን አሁን ባለው ሁኔታ በክልል እና በጎሳ ፖለቲካ እርስ በርስ እየተጋጨን ነው የምንኖረው። ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች አንዱና ዋነኛው የዜግነት ስነልቦና መመንመን ነው። እናም ያንን የዜግነት ስነልቦና ለማሳደግ እና ወደነበረበት ለመመለስ በተለያዩ ፕሮግራሞች ታሪክን በማሳወቅ፤ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተካከል፤ የጋራ እሴቶችን ለሕዝብ በማስተማር የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርፀናል። ይህንንም በሚዲያ፤ በማኅበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጫ መድረኮች የምናካሄደው ነው የሚሆነው። በእድሮችና በተለያዩ ባህላዊ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ሳይቀር ለማስተማር ነው የታሰበው። በዩኒቨርሲቲዎችም የኢትዮጵያዊነት ክለብ በማቋቋም በተለይ የታሪክና ፊዞሎጂ ዲፓርትመንቶች የኢትዮጵያን ታሪክና ቋንቋ ያውቃሉ ተብሎ ስለሚገመት እነሱን የመደገፍ ሥራ እንሠራለን።
በሌላ በኩል አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን እና ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ አይመለከትንም›› ብለው የሚያምኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የተሳሳተ አመለካከት የመቀየር ስራ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራችን አንዱ ነው። በተለይም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር የሚያስተሳስራቸውን በጎ እና መልካም እሴቶችን ነቅሶ በማውጣት ግንዛቤ የመስጠት፤ እውነታውንም የማሳየት ሥራ እንሠራለን ብለን እናስባለን። በሁሉም ብሔረሰብ ውስጥ ለአገር ባለውለታ የሆኑ ጀግኖች አሉ። በተለይም በአድዋ ጦርነት ሁሉም የውጭ ወራሪውን ለመመከት ልዩነቱን ትቶ በአንድ ላይ በመቆሙ ነው ድል የተቀዳጀነው። አሁንም ቢሆን የማንግባባቸው ልዩነቶች ቢኖሩንም በአንድነት ልንቆምላት የምትገባን አገር አለችን።
ለዚህ ትውልድ ኢትዮጵያ የተመሠረተችው በሁሉም አስተዋፅዖ መሆኑን ማስገንዘብ ይገባናል። እርግጥ ሥር ከሰደደው ብሔርተኝነት እና ከተዘረጋው የክልል አከላለል ሥርዓት አንፃር ይህ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ወደ አንድ አስተሳሰብ የማምጣቱ ሥራ በጣም ፈታኝ እንደሚሆን አስባለሁ። ያም ቢሆን ግን የዜግነት ስነ ልቦና ማሳደግ ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ፖለቲካ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ችግር የሚፈጠረው እንጂ ብሔሮች የራሳቸውን ቋንቋ አስተዳደር በሚፈልጉት መንገድ ቢያዳብሩና ቢተዳደሩ ችግር የለውም። እና የዜግነት ስነልቦና ለዚህች አገር ወሳኝ አጀንዳ ሆኖም በስፋት ሊሠራበት ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ያሰባችሁት ይህ የዜግነት ስነልቦና የማዳበር እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በምን መልኩ ነው ልትተገብሩ ያቀዳችሁት? ከመንግሥት ጋር መሥራትና በሕግ ማዕቀፍ ለማካተት ያስባችሁት ነገር ካለ አያይዘው ይጥቀሱልኝ?
ዶክተር እርቁ፡- ቀድሜ ልገልፅልሽ እንደሞከርኩት ትውልድን መድረስ ያስችሉን ዘንዳ የተለያዩ መንገዶችን አዘጋጅተናል። የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም ቀርፀናል። አንዱ ፕሮጀክት በመደበኛ መልኩ ማለትም በሳምንት አንድ ቀን በምሑራን አማካኝነት የተለያዩ የውይይት መድረኮች የሚዘጋጁ ነው የሚሆነው። ለዚህም ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋር አብረን ለመሥራት እየተነጋገርን ነው ያለነው። ለምሳሌ ከኢሳት እና ከአርትስ ቲቪ ጋር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት እየተወያየን ነው ያለነው። ግን ከፍተኛ ወጪ የሚፈልግ በመሆኑ ስፖንሰሮችን የማፈላለግ ሥራ ይጠይቀናል። የምንሰጣቸው የግንዛቤ ትምህርቶች ከአገር ምስረታ ጀምሮ አገር በቀል እውቀቶች ድረስ የሚካተቱ ይሆናል። በተለይም በየጊዜው እየጠፉ ያሉ ቋንቋዎችንና ታሪኮችን የመታደግ ሥራ አንዱ ፕሮጀክት ነው።
ሌላው በተለያዩ ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ ጀግኖችን የማስተዋወቅ ሥራ ሲሆን የክዋኔዎች ካላንደር በማዘጋጀት በእያንዳንዱ ቀን እውቅና ያልተሰጣቸውን የአገር ባለውለታዎችን የማስታወስ ሥራ እንሠራለን። ብዙ ጊዜ እውቅና የሚሰጣቸው ከሰሜን የአገሪቱ ክፍል ሲሆን አልፎ ከኦሮሞና ጉራጌ ብሔረሰቦች የወጡ ሰዎችን እውቅና ሲሰጣቸው እናያለን። ይሁንና ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የወጡ በርካታ ሰዎች እውቅና አልተሰጣቸውም። በተለይም አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ብሔረሰቦች የወጡ ጀግኖች የሚገባቸውን ክብር አላገኙም። ስለሆነም እነዚህን ሰዎች በምናስታውስበትና እውቅና በምንሰጣቸው ጊዜ የጋራ ስሜት ይፈጥራል። ለዚህ ደግሞ ታሪካቸውን እንዲፅፉ ይበረታታሉ። ለዚህም የሚረዳንን ሶፍትዌር እያበለፀግን ነው ያለነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቀን በሚል መንግሥት አሁን ከሚያካሂደው በተለየ መንገድ የሚከበርበትም መርሐ ግብር አለን። በዚህ መርሐ ግብር የዓመቱ ምርጥ ሰው የሚሸለምበትና እውቅና የሚገኝበት ሁኔታ ይኖራል። ልዩ ልዩ የሙዚቃና መሰል ኢትዮጵያዊነትን የሚሸቱ ዝርዝር ክዋኔዎች ይኖሩናል።
አዲስ ዘመን፡- ከመንግሥትና ከሌሎች አካላት ያገኛችሁት ግብረ መልስ ምን ይመስላል?
ዶክተር እርቁ፡- ባለፈው የመጣን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ሞክረን ነበር። እናም አንድ ቀን ሳናስበው ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈልጋችኋል›› ተብለን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ተጠርተን ነበር። ይሁንና አጋጣሚ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምጣት ባይችሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከአንድ ሰዓት በላይ እኛ ልንሠራው ባቀድነው መርሐ ግብር ዙሪያ ተወያይተናል። በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀውልን ከተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር ተቀራርበን የምንሠራበትን ምቹ ሁኔታ ፈጠሩልን። በዚህም መሠረት ከሳይንስና ቴክሎጂ ሚኒስቴር፤ ከከፍተኛ ትምህርት፤ ከትምህርት ሚኒስቴር፤ ከሰላም ሚኒስቴርና ከተለያዩ የክልል ፕሬዚዳንቶች ጋር ቀጠሮ ይዘን ውይይት አድርገናል። እናም ሁሉም በሚባል ደረጃ ዓላማችንን ወደውታል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሚቴ አቋቁመን የተመለስነው። እናም አሁን ለምሳሌ ከባህል ሚኒስቴር፤ ከትምህርት ሚኒስቴር፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት እያደረግን ነው። ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ደግሞ አስቀድመን ተፈራርመናል። ከሁሉም ጋር የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል፤ በእርግጥም በርከት ያለ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። መድረኮችን በማዘጋጀትና ባሉት የመገናኛ ብዙኃኖቻቸው አማካኝነት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት እንደምንችል አምናለሁ። ወደ ዋናው ሥራ ከመግባታችን በፊት ግን ራሳችንን ለሕዝብ የምናስተዋውቅበት ይፋዊ መርሐግብር በቅርቡ ለማዘጋጀት አቅደናል።
አዲስ ዘመን፡- ለ30 ዓመታት እያንዳንዱ ሕዝብ ዘንድ የሰረፀ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ባለበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን የዜግነት አስተሳሰብ የመቅረፅና ትውልዱን በአንድነት መንፈስ የመድረሱ ሥራ በራሱ ተግዳሮት አይሆንባችሁም?
ዶክተር እርቁ፡- እርግጥ ነው ያነሳሽው ነገር ትልቁ ተግዳሮታችን እንደሚሆን ይታመናል። ግን ተግዳሮቱ መኖሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት የምንሄድበት መንገድ በጥቂቱ የምንጀምረው ነው የሚሆነው። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ወጣቶችን በዩኒቨርሲቲዎቻችን አማካኝነት ለመድረስ ነው የምንሞክረው። የመግባቢያ ስምምነት የምንፈራረመውም ለዚህ ነው። የኢትዮጵያዊነት ክለብ በማቋቋም በደንብ እናሰለጥናቸዋለን። በመገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ይህንን ተግዳሮት እንወጣዋለን ብለን እናስባለን። ይህ ደግሞ አሁን መጀመር አለበት። አለበለዚያ በዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ሥነልቦና መቀመቅ ሊገባ እንደሚችል መገመት ይቻላል። የተለያዩ ጽሑፎችንም እያዘጋጀን ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ የምናደርግ ይሆናል። እስካሁንም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ፤ በተለያዩ ምሑራን የተጠኑ ግብዓቶች አዘጋጅተናል። በተለይም ሥነ-ምግባሩ የተፋለሰውን ወጣት የመቅረፅ ሂደት ስኬታማ ይሆን ዘንድ የሥነ-ምግባርና የሥነዜጋ ትምህርት የሚሰጡ የተለያዩ ጽሑፎችን የምናዘጋጅ ነው የሚሆነው።
ይህም በእኛ አቅም ብቻ የሚሆን አይደለም፤ የብዙ ተቋሞችና ትብብሮች ያስፈልጋል። በተለይ የመንግሥት ተቋሞች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥት ጋር እንሠራለን በምንልበት ጊዜ የመንግሥት ጥገኛ ሆናችኋል የሚል አስተያየት ከየቦታው ይሰጠናል። ግን የጋራ ፍላጎቶች አሉን፤ እኛ በሰላም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት፤ የግለሰብ መብት በመጠበቅ፤ የዜግነት ሥነልቦና እንዲያድግ ነው የምንሠራው። ማንኛውም መንግሥት ደግሞ ቢሆን ይህንን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም ከመንግሥት ጋር አጋር ነን። እስካሁን ያነጋገርናቸው የመንግሥት አካላት በጎ የሆነ ምላሽ ነው እየሰጡን ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎችን በምን መልኩ ነው ለማሳተፍ ያቀዳችሁት፤ ምንአልባት የተቋቋሙበት ዓላማ አኳያ ሊጋጭ ይችላል ብላችሁ አላሰባችሁም?
ዶክተር እርቁ፡- እንግዲህ ከለውጡ በፊት የነበረው ሁኔታ በኢህአዴግ በኩል የነበረውን ጭቆና በመቃወም ረገድ በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይጋሩት ነበር። በዚህ ስሜት የጋራ ችግር ስላለባቸው ይመጣሉ ብለን አስበን ነው ስንሠራ የነበረው። ደግሞም ድርጅቱ ሲቋቋም ከነበሩት አባላት መካከል አብዛኞቹ የብሔር ፖለቲካ አራማጆች ነበሩ። የኢዴፓ፣ የኢህአፓና መኢሶን አባላት የወጡት በዚያ ምክንያት ነው። እነ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እነ ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ነበሩበት። በእርግጥ አሁን ላይ ፅንፈኛ አቋም የነበራቸው የብሔር ፓርቲዎች ቁጥራቸው እየተመናመነ መጥቷል። ያሉትም ቢሆን ያንን የመገንጠል አቋማቸውን ይዘው የሚቀጥሉበት ምህዳርም የለም። በአጠቃላይ የዜግነት መንፈስ እያደገ መጥቷል ባይ ነኝ። ግን እንዳልሽው ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር በአገር አንድነትና በዜግነት ሥነልቦና ላይ መሥራት ከባድ ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ የቀደመውንና ትክክለኛው የየብሔራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ በማድረግ ይህንን ፅንፍ የወጣ አስተሳሰቡን መቀየር እንችላለን የሚል ተስፋ አለን። ሕገ-መንግሥቱም ለልዩነት እውቅና የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እዚህ ላይ መሥራት ይጠይቃል። እኛም በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ ሰፊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ያሉትን ህፀፆች ነቅሶ በማውጣት የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ እጅጉን እየተመናመነ መምጣቱን ተናግረዋል። እስቲ ይህንን ሁኔታ እርስዎ ከአገር ከመውጣትዎ በፊት ከነበረው የሕዝቡ የአገር ፍቅር ስሜት ጋር እያነፃፀሩ ይንገሩኝ?
ዶክተር እርቁ፡- በግሌ በዚህ ሥርዓት ምክንያት በርካታ ወዳጆቼን አጥቻለሁ። በቤተሰቤም ሆነ በጋደኞቼ ላይ በቀውስ ደረጃ የሚጠቀስ ችግር ደርሶባቸዋል። ይህ የብሔር ፖለቲካ በጣም ትልቅ በሽታ ነው። በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰርጎ የገባ ነቀርሳ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በግሌ ይህንን ልበል እንጂ በአገር ደረጃ ትልቅ ኪሳራ ነው ያመጣው። የሚታሰበው የዲሞክራሲ ሥርዓት እና የኢኮኖሚ እድገት ያለዜግነት ሥነልቦና በዜግነት ኮርቶ ተረጋግቶ ለመሥራት ጋሬጣ የሚሆንበት ሁኔታ ነው የነበረው። ይህ የአገር ፍቅር ስሜት መጥፋት ነገር እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። በአገር ላይ መከራ የጣለ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሕዝቡ ላይ የቀደመውን የአገር ፍቅር ስሜት የመፍጠሩ ነገር የሁሉም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እርግጥ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት በሚዘጋጁ መድረኮች አማካኝነት የኢትዮጵያዊነትን ሥነልቦና ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። ግን በመድረክ ተነግረው መሬት ላይ ሳይወርዱ አየር ላይ የሚቀሩበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑንም እዚህ ላይ ነው መሥራት የሚገባን ብዬ አስባለሁ። የእኛም እቅድ ይሄ ነው። እዛ ለመድረስ ተግዳሮት ብዙ ነው፤ አቅምም የሚፈታተነን ቢሆንም አብረውን ለመሥራት ለሚፈልጉ ሰዎች በራችን ክፍት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑ መንግሥት መግባባት እንዲፈጥር በሚል ታስረው የነበሩ ፖለቲከኞችን ክስ ማቋረጡ ለአገር ሰላም ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር፡- በመሠረቱ ምክክር የሚለው ሃሳብ በራሱ ከእኛ ዓላማም ጋር የሚሄድ ነው። ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተመካክረው ፤ ያለውን ችግር ተገንዝበው ለመፍትሔው በጋራ ስምምነት እንዲፈጥሩ መንግሥት ምቹ ምህዳር መፍጠሩ የሚደገፍ ነው። ይህ የምክክር ሂደት ግን ሕወሓትን ይጨምራል ብዬ አላምንም። እኛም በድርጅታችን አማካኝነት በዚህ የምክክር መድረክ 300 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ተሳትፈው 200 እጩዎችን አቅርበዋል። ሕዝቡ ያቀረባቸውን እጩዎች በሙሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምናስተላልፍ ነው የሚሆነው። በእኛ በኩልም የምንመርጣቸውን ሰዎች የምናቀርብ ይሆናል።
በመሆኑም በእኔ በኩል መድረኩ መፈጠሩ ተገቢና የሚደገፍ ነው። የእስረኞቹን መፈታት በሚመለከት ግን ልዩነት አለኝ። ይህንን ስል አይፈቱ ማለቴ ሳይሆን ይህ ውሳኔ የተወሰነበት ጊዜ ትክክል አይደለም ብዬ ስለማምን ነው። የተፈቱበት ምክንያት ከሰብዓዊ መብት አኳያ አሳማኝ ቢሆንም በግፊት የመጣ የሚመስል ነገር አለ። ያንን ለመቀበል አስጨናቂ የሆነ ነገር ያለ ይመስለኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ሊሆን የሚችለው ነገር ያሳስባል። በተለይ ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ባልተጠናቀቀበትና አሁንም በአሸባሪው ቡድን ጉዳት እየደረሰበት ያለ የኅብረተሰብ ክፍል ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለው ነገር እንደግለሰብ ያሳስበኛል። ከሁሉ በላይ የሕዝቡን ስሜት መረዳት ተገቢ ነው ባይ ነኝ። ወደፊትም ቢሆን የሚደረጉ ነገሮችን ለመንግሥት ግልፅ ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር እርቁ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲሰ ዘመን ጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም