የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል የማቋቋሚያ አዋጅ ማጽደቁ የሚታወስ ነው። ከዚህም ጋራ ተያይዞ ተቋሙን ለማቋቋም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
ይህም ሆኖ ተቋም መመስረት ወይም ማቋቋሚያ አዋጅ ማውጣት በራሱ ግብ አይደለም። አንድን ግብ ወይም አላማ ለማሳካት እንደ አንድ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
መሰረታዊ ጉዳይ የሚሆነው ከአዋጁ ወይም ከተቋሙ ጀርባ ያለውን ልዩነቶቻችን በማጥበብ አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያ የምትባል የበለጸገች ሰላሟ የተረጋገጠ ገናና አገር ለመገንባት በሚኖረው አስተዋጽኦ ነው።
ተደጋግሞ እንደሚገለጸው ብሄራዊ ምክክር ያስፈለገው ብሄረ መንግሥቱ የሚገነባበትን መሰረታዊ ጉዳዮች (Building Blocks) ላይ በመግባባት ቢያንስ መጪው ትውልድ የጦርነትና የድህነት ታሪክ እንዳይኖረው መሰረት መጣል ይኖርበታል።
ጥር 3/2014 በወጣው የአዲስ ዘመን እትም የመጀመሪያው ክፍል ጽሁፌ አሀዳዊም ይሁን ፌዴራላዊ የመንግሥት ስርአትን የሚከተሉ አገራት በህገ መንግሥት በሰንደቅ አላማ በጋራ ቋንቋ እና በብሄራዊ መዝሙር በመሰረታዊነት ብሄራዊ መግባባት የፈጠሩ አገራት ዘላቂና የልዩነት ምንጭ ያልሆነ ብሄረ መንግሥት ስለገነቡ ማደግና መበልጸግ እንደቻሉ ለማሳየት ተሞክሯል።
በአንጻሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የብሄረ መንግሥት የግንባታ ፕሮጀክታቸውን ያላጠናቀቁ አገሮች የልዩነት ምንጭ መሆን የማይገባቸው ጉዳዮች የልዩነት ምንጭ ሲሆኑ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በህገ መንግሥቱ ይዘትና በመንግሥት ቅርጽ ላይ ብቻ ሳይሆን በታሪካችን በሰንደቅ አላማችን እና በጋራ ቋንቋችን በሀውልቶቻችን ሳይቀር ፖለቲካዊ አጀንዳ ከመሆን አልፈው ለእርስበርስ ጦርነት ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሲሆኑ ይታያሉ።
የዚህ ጽሁፍ አላማም ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ቢያንስ መግባባት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል ከሚል ምክረ ሃሳብ በዘለለ ምን መሆን አለባቸው የሚል አቋም የለውም። ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች የብሄራዊ ምክክር አጀንዳዎች መካከል በመካተታቸው አስፈላጊነት ዙሪያ ለውይይት መነሻ ለማቅረብ ተሞክሯል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዛሬ ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና በበርካታ አገራት አሜሪካን ሳይቀር በእርስ በርስ ጦርነት ያለፉበት ታሪክ ነው። ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ችግር ካጋጠማቸው አገራት ውስጥ ጥር 03/2014 በወጣው አዲስ ዘመን ነጻ ሃሳብ አምድ ላይ ናይጀሪያ ከሶስት አመት (እ.ኤ.አ 1967-1970) የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ብሄራዊ አንድነትን (National Integration) ለመፍጠር የቀየሰችውን ፖሊሲ በግርድፉ ለማንሳት ተሞክሯል።
ይህ ፖሊሲ ከመውጣቱ በፊት በናይጀሪያ በፌዴራል መንግሥቱ እና ነጻ መንግሥት ነኝ ብሎ ባወጀው የቢያፍራ ግዛት ከ1967 እስከ 1970 እ.ኤ.አ ደም አፋሳሽ እና ለሚሊዮኖች ህልፈት ምክንያት የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት የተካሄደ ሲሆን፣ ጦርነቱን በአንድነት ሀይሎች አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላ በድህረ ጦርነት ወቅት ብሄራዊ አንድነትን ለመፍጠር በኢግቦ ጎሳዎችና በተቀረው የናይጄሪያ ህዝቦች መካከል እርቅ ለማውረድ እና መልሶ ለመገንባት ከላይ የተጠቀሰውን ፖሊሲ በወቅቱ የነበረው የናይጄሪያ መንግሥት አውጥቷል።
ፖሊሲው ውጤት አምጥቷል አላመጣም የሚለው ጉዳይ የዚህ ጽሁፍ አላማ አይደለም ይልቅ የፖሊሲው ሃሳብ (Intention) ምን ነበር በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ክፍል እንዳየነው ፖሊሲው ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች መልሶ ማቋቋም (Rehabilitation) እርቅ (Reconciliation) እና መልሶ ግንባታ (Reconstruction) ሲሆኑ በጦርነቱ ወቅት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እና የማቋቋም በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ጭምር ቤቶች የጤና ተቋማት የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ መገንባት እና ዘላቂ ሰላም በማምጣት የናይጄሪያን አንድነት (United Nigeria) ለማስጠበቅ ነው።
ከላይ እንዳየነው ሁለተኛው ፖሊሲ እርቅ (Reconciliation) ሲሆን ፣ እርቅ ሰፋ ያለ ትርጉም እና ሃሳብ ያለው በውስጡ ሰፋፊ ጽንሰሃሳቦችን የያዘ ነው። እነሱም ፍትህ ፣ሰላም ፣ ይቅርባይነት ፣ እውነት ፣ሰብአዊነት ቂም መርሳት እና ካሳን ወዘተ ጭምር የሚያካትት ፅንሰ ሃሳብ (Concept) ነው።
ከዚህ በመነሳት በወቅቱ የነበረው የናይጄሪያ መንግሥት በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጄኔራል ያኩቡ ጦርነቱ በሁለት ወንድማማቾች የተካሄደ መሆኑን በጦርነቱ አሸናፊም ተሸናፊም ወይም “No Victor, No Vanquished” የሚል ውሳኔ በማሳለፍ በጦርነቱ የተሳተፉ የኢግቦ ጎሳ አባላት የአንድነት ስሜት እንዲሰማቸው በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አጥፊ ተደርገው እንዳይታዩ ወይም እንዳይገለሉ (Marginalized) በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በሲቪል ሰርቪስ እና በመከላከያ ውስጥ ሚና እና ተሳትፎ እንዲኖራቸው አጠቃላይ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ተደርጓል (General Amnesty)። ከዚህ በመቀጠል ሰንደቅ አላማ ፣ከብሔራዊ መዝሙር እና ቋንቋ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለብሄራዊ መግባባት የሚኖራቸውን ፈይዳ እንመለከታለን።
ሰንደቅ አላማ ለአገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ
ጀርመናዊው ጸሀፊ Kurt Tucholsky ‹‹ማንኛውም ሰው ጉበት ጣፊያ ሳንባ እና ባንዲራ አለው። አራቱም የሰውነት ክፍሎች ለህይወት አስፈላጊ ናቸው ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ያለ ጉበት ወይም ጣፈያ ወይም በግማሽ ሳንባ እንደሚኖሩ እንሰማለን። ሆኖም ግን ሰንደቅ አላማ የሌለው ሰው አይኖርም ››ሲል ነበር የአገር መለያ ብሄራዊ መገለጫ የሆነውን የባንዲራ አስፈላጊነትን የገለጸው።
ሰንደቅ አላማ ከከርስቶስ ልደት በፊት ከ1542 ጀምሮ ህንዶች እንደ ተግባቦት ምልክትነት ጥንታዊ ቻይናዊያን እንደ አገር መለያነት ወይም አርማነት ሲጠቀሙበት እንደነበር የታሪከ መዛግብት ያስረዳሉ። ነገር ግን ዴን ማርክ ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው የአገር ወይም ለብሄራዊ ምልክትነት ሲጠቀሙበት ነበር ።ስዊዞችም ከ1291 ዓ.ም ጀምሮ ለአገር መለያነት ጥቅም ላይ አውለውታል ።በአገራችን የሰንደቅ አላማ ታሪክ ስንመጣ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ከ1889 (በፈረንጆቹ 1897) ዓ.ም ጀምሮ ኦፊሻል ሰንደቅ አላማ ተግባራዊ ሆኗል።
በአፍሪካም እንደአገር የመጀመሪያው ኦፊሻል ሰንደቅ አላማ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ነው ።እስካሁን ድረስ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ህብር የፈጠሩበትን ሰንደቅ አላማ እየተጠቀምንበት እንገኛለን! ቀለማቱም ከጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ከታየበት ቀስተ ዳመና የተወሰደ እንደሆነ ይገመታል። በመንግሥታት መቀያየር ቀለማቱ ባይቀያየሩም በሰንደቅ አላማው መሀል
ላይ የሚገኘውን ብሄራዊ ምልክታችንን (National Emblem) በመቀያየር አንዳንድ ጊዜም መሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ልሙጥን ባንዲራ ስንጠቀም ቆተናል! የኢትዮጵያ ባንዲራ ለአለም ጥቁር ህዝቦች እና ለአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት (Flags of freedom) ተደርጎ ስለሚወሰድ ፣የጥቁር ህዝቦች መለያ ፣የፓን አፍሪካን ርእዮተአለማዊ እና አፍሪካዊ ድርጅቶችም ምልክት አድርገው ይጠቀሙበታል።
ከዚህም ባለፈ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ ቢያንስ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት አንደኛውን ቀለም በብሄራዊ ሰንደቅ አላማቸው አካተዋል። ለምሳሌ ኬንያ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ደቡብ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
በተለይ ፈር ቀዳጅ የነበሩት የእነ ጋርቬይ የጥቁር ህዝቦች እንቅስቃሴ ለምሳሌ Universal Negro Improvement Association (UNIA) ቀይ ጥቁርና አረንጓዴ ቀለማት ለአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ቀለማት እንዲሆን ወስነው እንደነበር ማስታወስ በቂ ነው። የሰንደቅ አላማ ታሪክ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።
በዘመናዊው ታሪክ በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት ወይም በነጩ ቤተ መንግሥት ወይም በአራት ኪሎው ቤተመንግሥት ሲውለበለቡ የምናያቸው ዝም ብሎ አርማ ሆነው አይደለም። ከዚያ በላይ ከሚውለበለበው ጨርቅ ጀርባ እጅግ ረቂቅ መልእከት ስላላቸው ነው።
ለዚህም ነው መከላከያ ሰራዊታችን ለሰንደቅ አላማው ሲል ክቡር ህይወቱን የሚሰጠው። ለዚህም ነው ኃይሌ ገ/ስላሴ ወይም ደራርቱ ቱሉ በአጠቃላይ አትሌቶቻችን ከድል በኋላ ባንዲራችን ወደ ላይ ከፍ ሲል ሲቃ የሚተናነቃቸው። ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር መለያ (Symbol) ከመሆን ባለፈ ከሰንደቅ አላማው ጀርባ ኢትዮጵያዊነት የሚገለጽበት የነጻነታችን ምልክት እና የሰማእታት ደም እና ስጋ የተከፈለበት የአርበኝነት ተጋድሎአችን መገለጫ ነው።
እርግጥ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ መንግሥት የጋራ ህግ የጋራ ገንዘብ የጋራ ሀውልት የጋራ ሙዚየም የጋራ አርቲስቶች ወዘተ አሉን። ነገር ግን ዘፋኙ ስለ አገር ሲዘፍን በአንድ እጁ ማይክራፎን በሌላ እጁ የሚጨብጠው ባንዲራ እንጂ የጋራ የሆነውን ህገ መንግሥት ወይንም የጋራ የሆነውን ገንዘብ አይደለም።
በምስራቅ ሶማሌውን አፋሩን በምእራብ ጋምቤላውን ቤኒሻንጉሉን በሰሜን ትግሬውን አማራውን በደቡብ ሲዳማውን ወላይታውን በጥቅሉ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ከሚያስተሳስሩት ገመዶች ቀዳሚው ስፍራ የሚወሰደው ሰንደቅ አላማ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አለም አገራት የምትለየው በባንዲራዋ ነው። በውጭ አገራት ያሉ ኤምባሲዎቻችን ከሌሎች አገራት ኤምባሲዎች የሚለዩት በሰንደቅ አላማቸው ነው። በቅርብ ጊዜ እንኳን ምእራባውያን የሚያደርሱብንን ተጽእኖ ለመቃወም በበቃ እንቅስቃሴ (#No More Movement) ከድምቀት ባለፈ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የአገራቸውን ድምጽ ያሰሙት የየአገራቸውን ባንዲራ በመያዝ ነበር ።
ስለዚህ ሰንደቅ አላማ የሌለው ህዝብ አገር የሌለው ብቻ ነው፣ በአንጻሩ የአንድ አገር ዜጎች የሌላን አገር ተቃውሞአቸውን ከሚገልጹበት አንዱ የዚያን አገር ሰንደቅ አላማ በማቃጠል ነው።ለምሳሌ ፍልስጤማውያን አሜሪካንን ወይም እስራኤልን ለመቃወም ከሚጠቀሙበት መንገድ አንዱ የአሜሪካንን ወይም የእስራኤልን ባንዲራ በማቃጠል ነው። ስለዚህ ድርጊቱ ከፍተኛ የጥላቻ ጥግን ማሳያ ምልክት ነው። ለዚህ ነው አንድ አገር የሚወከለው በሰንደቅ አላማው የሚሆነው።
ወደ አገራችን ስንመጣ ብሄራዊ መግባባት ልንፍጥርባቸው ከሚገቡን ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሰንደቅ አላማ መሆን አለበት ሲባል ያለምክንያት አይደለም። እስከ ደርግ ውድቀት በትምህርት ቤቶች ወይም በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ባንዲራ በሚወጣበት እና በሚወርድበት ሰአት ሁሉም ዜጋ ባለበት በመቆም የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በልቡ ዘምሮ የመውረድ ወይም የመስቀል ስነስርአቱ ሲጠናቀቅ ነበር መንቀሳቀስ የሚጀምረው።
ነገር ግን ባለፈው ሶስት አስርተ አመታት አንዱ ዝቅጠት የታየበት ለሰንደቅ አላማችን የሰጠነው ቦታ እና ትርጉም ነው። ከላይ እንዳየነው በርካታ የአፍሪካ አገራት እና አህጉራዊ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ቀለማትን በመዋስ የሰንደቅ አላማቸው ክፍል ሲያደርጉት ተመልክተናል።
እስቲ ለመተዛዘብ በአገራችን ስንቶቹ የክልል መንግሥታት ናቸው ከፌዴራሉ ሰንደቅ አላማ ጋር ለማስተሳሰር ሙከራ ያደረጉት ፣ ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉታል እንደሚባለው ነው።
ስንቶቻችን ነን ይህን የአገር ኩራት መለያ ብሄራዊ አርማ የታሪካችን የባህላችን መገለጫ የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማችንን ቦታ የሰጠነው ? በአንጻሩ መንግሥት አገር ችግር ባጋጠማት ወቅት በባንዲራ ቅስቀሳ ያደርጋል ፣ ለአብነት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ዜጎች መከላከያን እንዲቀላቀሉ እና አገራቸውን ከወረራ እንዲከላከሉ ለመቀስቀሻነት በከፍተኛ ሁኔታ ስንጠቀምበት ነበር።
ከዚያ በኋላ በተወሰነ መልኩ የሰንደቅ አላማ አጠቃቀምን በሚመለከት አዋጅ በማውጣት በየአመቱ የሰንደቅ አላማ ቀን እንዲከበር ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን ልክ እንደ ብሄር ብሄረሰቦች በአል ፖለቲካዊ ስለነበር የምንፈለገውን የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል ብሎ መደምደም አይቻልም።
በአጠቃላይ ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር ምልክት ብቻ ሳይሆን ዜጎች የአገራቸውን ፍቅር የሚገልጹበት ማንነታቸውን የሚያደምቁበት ቋንቋ ባንዲራ… መንፈሳቸው ነው። ዜጎች ከአገራቸው ባንዲራ ጋር ስሜታዊ ቁርኝት (emotional attachment) አላቸው። ከዚህ የተነሳም የብሄራዊ ምክክሩ ወጤታማነት ከሚመዘንበት ነጥቦች አንዱ ዜጎች በጋራ በሰንደቅ አላማቸው ዙሪያ የጋራ ስምምነት (National Consensus) ላይ ሲደርሱ ነው።
ቋንቋ ለብሄራዊ መግባባት የሚኖረው ፋይዳ
አንድ አገር የጋራ ቋንቋ ያስፈልገዋልን? ቋንቋ ለአገረ መንግሥት ምስረታ አስፈላጊ ነውን? የአንድ አገር ልማት ያለ የጋራ ቋንቋ ማረጋገጥ ይቻላልን? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ቋንቋ እና ከአገረ መንግሥት ግንባታ ጋር ተያይዞ ይነሳል።
ከዚህ በፊት ግን ቋንቋ ማለት በግርድፉ በቃል በጽሁፍ ወይም በተለመዱ ምልክቶች የተግባቦት መሳሪያ ነው።
እንደ ሁሴን አዳል (2009) ቋንቋ የአንድ ህብረተሰብ የጋራ መግባቢያ ከመሆኑም በላይ በሌሎች ማህበረሰባዊና ተፈጥሮአዊ ባህሪያት ጋር ተዳምሮ የህብረተሰብ ማንነት መለያ ባህሪይ በመሆን ያገለግላል። ስለዚህ ቋንቋ ልክ እንደ አንድ አገር ሰንደቅ አላማ ፣ታሪክ ፣ባህል ቅርስ እና ወዘተ ብሄራዊ መለያ ሆኖ ያገለግላል።
ነገር ግን ቋንቋ በአገረ መንግሥት እና በብሄር ግንባታ ላይ በሚኖረው ፋይዳ በምሁራን መካከል የጋራ አቋም የለም ፣ለምሳሌ አንዳንዶቹ ቋንቋ አንድ የጋራ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ ነው ነገር ግን ፍጹም አስፈላጊ ነው ማለት ግን አይደለም ሲሉ ፤አንዳንዶቹ ደግሞ ቋንቋ ለአገረ መንግሥት ምስረታ መንፈሳዊ (Spiritual) መሳሪያ ነው ብለው ያምናሉ ።
ቋንቋ ለአገር መንግሥት ግንባታ ስላላው ጠቀሜታ ሲያስረዱ ‘There is no language—then there is no state. በማለት ይደመድማሉ ታዋቂ የታሪክ ጸሀፍት አንትሮፖሎጂስቶች የፖለቲካ ሳይንቲስቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ቢኖር ብሄራዊ ቋንቋ አገረ መንግሥቱ ለሚገነባበት ርእዮት (Ideology) ቀዳሚ መሰረት መሆኑ ላይ ነው።
ምክንያቱም ብሄራዊ ቋንቋ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ ሳይሆን በሂደት የሚገነባ (Constructed) በመሆኑ ነው። ለአገረ መንግሥት ግንባታ አገረ መንግሥቱ የሚገነባባት ርእዮተ አለማዊ መሰረቶች የሚተላለፉት ጋዜጦችን ወይም ሚዲያዎችን በመጠቀም ነው።
በዚህም ምክንያት የጋራ ወይም ብሄራዊ ቋንቋ ከሌለ የጋራ መግባባት መፍጠር አይቻልም ። ቋንቋ እና ልማት ቋንቋ እና አገረ መንግሥት ግንባታ ቋንቋ እና ብሄረ መንግሥት ምስረታ ቀጥታ ግንኙነት አላቸው በዚህ ምክንያት በበርካታ የአፍሪካ እና ኤዥያ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላ ቋንቋ ለአገረ መንግሥት ምስረታ ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል ።
ምክንያቱም ቅኝ በተገዙበት ማለትም በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የተገዙ ፍራንኮፎን ወይም የብርቲሽ ቅኝ ተገዢዎች አንግሎፎን መሆን አለበት ወይስ የራሳችን ቋንቋ (Native language) ነው ብሄራዊ ወይንም ኦፍሻል ቋንቋ ሊሆን የሚገባው የሚለው ጉዳይ አወዛጋቢ ጥያቄ ነበር። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ በኋላ በመንግሥት ፖሊሲ ደረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ብዝሀ ቋንቋን (Multi-lingual) የሚያበረታታ ማእቀፍ ብታዘጋጅም በተጨባጭ ወይም በተግባር ግን የዜጎች ብሄራዊ ጠባይ (National Character) የእንግሊዝኛ ቋንቋ (Monolingual-English character) ተጽእኖ ስር የወደቀ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በቅኝ ባልተገዙ አገራት በአገረ መንግሥቱ ምስረታ ወቅት አስኳል ወይም core የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ቋንቋ ኦፍሻል ወይም ብሄራዊ ቋንቋ ይሆናል።
የአገረ መንግሥት ምስረታው ርእዮተ አለምም የሚተላለፈው በዚሁ ቋንቋ ነው ይህ ማለት አንድ ቋንቋ ብቻ ለአገረ መንግሥት ምስረታ ወይም በብሄራዊ መለያነት ወይም በብሄራዊ ቋንቋነት ያገለግላል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአውሮፓ ወደ 73 የሚጠጉ ጎሳዎች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 47 የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው ናቸው ፤ 26 ግን የሁለት ቋንቋ (Bilingual) ተናጋሪዎች ናቸው።
አንድ የራሳቸውን እና አንድ የሌላ ቋንቋ ማለት ነው። ስለዚህ አንድ የተለየ ቋንቋ ብቻ መኖሩ የብሄራዊ ማንነት መገለጫ አይሆንም። በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ ከአንድ በላይ ቋንቋ ሊኖር ይችላልና።
በ19ኛው ወይም 20ኛው ክ.ዘ ቋንቋ ከህዝብ ብዛትና ከአገር ግዛት ጋር ተዳምሮ የአንድን አገር (Nation) ወሰን ለመከለል እና ለአገረ መንግስት ምስረታ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። እንዲሁም ጽንፈኞች (the separatisms and regionalisms) የራስን እድል በራስ የመወሰን (Self Determination) ጥያቄን ቋንቋን መሰረት አድርገው አንስተዋል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካዊ አጀንዳነቱ እና ለአገረ መንግሥት ምስረታ (State formation) አስፈላጊነት እየቀነሰ በመምጣቱ የአለም ህዝብ ወደ አንድ ቋንቋ እና ባህል (Unified language and culture) ተጽእኖ ስር እየወደቀ መምጣቱን በርካታ ምሁራን ይስማማሉ።
ለምሳሌ የሊበራል ፖለቲካ ንድፈሃሳብ (Cosmopolitanism) አራማጆች አንድ ሰው ራሱን ማየት ያለበት የአንድ አገር ዜጋ አድርጎ ሳይሆን የአለም ዜጋ ነኝ ብሎ ነው ማሰብ ያለበት፤ በአንድ አገር ሳይሆን በአለም ላይ አንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ነው እንዲፈጠር መታጋል ያለበት ብለው ይከራከራሉ።
በአጠቃላይ ቋንቋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በባህል በኢኮኖሚ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስተሳስር መሳሪያ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ስለዚህ ከኢትዮጵያ ሁኔታ አንጻር ሲቃኝ እንደ አገር ለመቀጠል አዲስ የብሄረ መንግሥት ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል።
ይህ ፍኖተ ካርታ ከባዶ የሚነሳ ሳይሆን የንጉሳዊያን ዘመን ለደረግ ዘመነ መንግስት ፣የደርግ ዘመነ መንግስት ፣ለኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ፣የኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለዘመነ ብልጽግና ሰርተው ያስተላለፉት አገረ መንግሥት አለን። የጎደለው ነገር ኢህአዴግ በደርግ ዘመን የነበረውን ሲቪክ ብሄርተኝነት ወይም ዜጋ ተኮር ሀገረ መንግስቱን ወደ ጎሳ ተኮር ብሄረ መንግስት (Ethnic nationalism) ሲቀየር የመንግስት ቅርጽ ከአሀዳዊ (Unitary) ወደ ፌዴራላዊ ቅርጸ መንግሥት በመቀየሩ ብሄራዊ ቋንቋው ከአንድ ቋንቋ ወደ ብዝሀ ቋንቋ (Multi lingual) መቀየር የግድ ነበር። ለምን አልተተገበረም ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው። ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያ ቋንቋ ለብሄረ መንግሥት ግንባታችን ፈተና መሆኑ አይቀርም። ነገር ግን የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስንት ቋንቋ የትኛው ቋንቋ በምን መስፈርት ለብሄረ መንግሥት ግንባታው አስተዋጽኦ ያድርጉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊሰጥ ይገባል ።
በአጠቃላይ ለብሄረ መንግሥት ግንባታችን ቋንቋን ብቻ አልፋ እና ኦሜጋ አድርገን ማሰብም የለብንም። ዛሬ ዛሬ የአለም ህብረተሰብ የሚግባባት እንግሊዝኛ ቋንቋ እና ሌሎች አለም አቀፍ ቋንቋዎች አስፈላጊነታቸው ዙሪያ ላይ የሚነሳ ጥያቄ የለም። ከዚህም አልፎ በኮምፒውተር ቋንቋ በምልክት ቋንቋ ሰዎች በሚግባቡበት ዘመን ቋንቋን በጎሳ ፖለቲካ መነጽር እያየን የምንመዝን ከሆን ትልቁን ራእያችንን ማሳነስ ይሆንብናል።
ብሄራዊ መዝሙር ለብሄራዊ መግባባት የሚኖረው ፋይዳ
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው የአንድ አገር ብሄራዊ ምልክት መገለጫዎች ውስጥ ብሄራዊ መዝሙርና ሰንደቅ አላማ ተጠቃሽ ናቸው።ሁለቱም ጠንካራ እና ግልጽ በሆነ መልኩ የአንድን አገር ታሪክ ፣ባህል፣ ጀግንነት ፣ነጻነት እና ማንነት ከሚተላለፍባቸው እና ከሚንጸባረቅባቸው መንገዶች ውስጥ ይጠቀሳሉ ።
ብሄራዊ መዝሙር በተለያዩ ምሁራን በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን ለምሳሌ Kellen (2003, 166) the anthem is “the words that must always be sung, that have always been sung. That is how those words and that tune seem like permanent signs. That is how they make entities like nations appear to be permanent”. ሲል ይገልጻል ።
በአጠቃላይ ብሄራዊ መዝሙር የአንድ አገር ኦፊሻል የአርበኝነት ምልክት (Partiotic Symbol) በመሆኑ ዜጎች ለጋራ ግብ ፣ልማት እና ሰላም እንዲሁም አገር በጠላት ስትደፈር አገርን ለመከላከል ዜጎችን በአንድነት የሚያስተሳስር ገመድ ነው።
ለዚህም ነው በአለም አቀፍ ስብሰባ መድረኮች በአለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች እና ፌስቲቫሎች የተሳታፊ አገሮች ብሄራዊ መዝሙር ሰንደቅ አላማን አጅቦ የሚዘመረው። የብሄራዊ መዝሙር ረዘም ያለ ታሪካዊ ዳራ ያለው ሲሆን በ1568 የተጻፈው የኔዘርላንድስ ቀደምት ብሄራዊ መዝሙር እንደሆነ ይነገራል። በአገራችን የመጀመሪያው ብሄራዊ መዝሙር በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን በ1933 ዓ.ም በአርመናዊው ኮቦርክ ናልባዲያን የተዘጋጀው ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚለው ቀዳሚ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር እንደሆነ ይገለጻል።
ይህም መዝሙር የንጉስን ድል አድራጊነት እንጂ የህዝቦችን ተጋድሎ እና አርበኝነት አያንጸባርቅም፤ ሆኖም መመዘን ያለበት በነበረው ሁኔታ ነው። ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ ይኑርልን ለክብራችን ድል አድራጊው ንጉሳችን አትፈሪም ከጠላቶችሽ ብርቱ ናቸው ተራሮችሽ አይነካም ከቶ ነጻነትሽ ተባብረዋል አርበኞችሽ በአምላክ ሀይል በንጉስሽ ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በደርግ ዘመን የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ወድቆ በወታደራዊ መንግሥት ሲተካ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ የሚለው በገጣሚ አሰፋ ገ/ማርያም ተደርሶ ሙዚቃው በዳንኤል ዮሀንስ ተቀናብሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መስከረም 2/1967 በመጀመሪያው የአብዮት በአል የተዘመረው ሲሆን የመዝሙሩም ይዘት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ በህብረተሰባዊነት አብቢ ለምልሚ ቃል ኪዳን ገብተዋል ጀግኖች ልጆችሽ ወንዞች ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ ለኢትዮጵያ አንድነት ለነጻነትሽ መስዋእት ሊሆኑ ለክብር ለዝናሽ ተራመጂ ወደፊት በጥበብ ጎዳና ታጠቂ ለስራ ላገር ብልጽግና የጀግኞች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከ1967-1983 የነበረውን መዝሙር ኢትዮጵያዊነትን ያጎላ ዜጎቿ ቀርተው ተራራው ወንዙ ሸንተረሩ ሳይቀር የኢትዮጵያን አንድነትና ነጻነትን እንደሚጠብቁ ቃል መግባታቸውን ያመላክታል።
መቼም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ ያሉት ሰዎች አብዛኞቹ በዚህ ሂደት ያለፉና ይህንን መዝሙር በየትምህርት ቤታቸው ሲዘምሩ ያደጉ በመሆናቸው የነበረንን ስሜት ወደኋላ መለስ ብሎ መመልከት ይቻላል።
በመሆኑም በአብዛኛው ልብ ውስጥ ታትሞ የቀረ መዝሙር ነው። ከ1984 እስከ አሁን ያለውን የዘመነ ኢህአዴግ መዝሙር የዜግነት ክብር የሚል ሲሆን በደረጀ መላኩ ተደርሶ በሰለሞን ሉሉ የተቀናበረ ነው። በይዘት ደረጃ ኢትዮጵያዊ በመሆናችን የተከበርን መሆናችንን ሰላም ፣ፍትህ ፣እኩልነት የሰፈነባት አገር እንደሆነችና ተፈጥሮአዊ እና ባህላዊ ሀብቶች ያለን መሆኑንም ያመላክታል ።ነገር ግን አሁን ያለውን ትውልድ የብሄር የሃይማኖት የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበው አገራዊ አንድነቱ ምን ያህል የጸና ነው የሚለው ጉዳይ ነው።
በሚያሳዝን መልኩ በብሄራዊ በአላት ሳይቀር በቴፕ የተቀረጸው ድምጽ ካልተለቀቀልን ባስተቀር በቃሉ ሙሉ መዝሙሩን ሊዘምር የሚችለው ዜጋ ምንያህሉ ነው ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፣ ለዚህም ነው ለሰንደቅ አላማችን እና ለብሄራዊ መዝሙራችን በሰጠነው ከፍታ ልክ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እናደርጋለን ሰንደቅ አላማችንና ብሄራዊ መዝሙራችን ዝቅ ባደረግን ቁጥር አገራዊ አንድነታችንንም እንሸረሽራለን።
ለሁሉም አሁን ያለን ብሄራዊ መዝሙር የዜግነት ክብር የሚለው ሲሆን ግጥሙም….. የዜግነት ክብር የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ ለሰላም ለፍትህ ለህዝቦች ነፃነት በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት መሰረተ ፅኑ ሰብዕናን ያልሻርን ህዝቦች ነን ለስራ በስራ የኖርን ድንቅ የባህል መድረክ የአኩሪ ቅርስ ባለቤት የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ህዝብ እናት እንጠብቅሻለን አለብን አደራ ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።
አንድ ብሄራዊ መዝሙር ለአገረ መንግሥት እና ለብሄረ መንግሥት ግንባታ የሚኖረው እና ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ በበርካታ መመዘኛዎች መመዘን ቢቻልም በመሰረታዊነት የባለፈውን ታሪክ (ወይም ትውልድ) ጀግንነት አስተዋጽኦውን በማስታወስ አሁን ያለው ትውልድ ለአገሩ ቀናኢ እንዲሆን አንድነቱን እንዲያጠናክር በሚያስተላለፈው መልእክት እና መጪው ትውልድም ያለበትን ኃላፊነትና አደራ በማስገንዘብ ደረጃው የሚመዘን ነው።
በአጠቃላይ አንድ ብሄራዊ መዝሙር አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የሁሉንም ህዝቦች ባህል እሴት የሚገልጽ አገራዊ ሉአላዊነትን የመጠበቅ ዜጎች ስላለባቸው ግዴታ ጀግንነትን እና ለአገር የተከፈለው የደም የአጥንት መስዋእትነት ነጻነት እና እኩልነትን ብሄራዊ ኩራትን ወዘተ ጉዳዮችን መያዝ ይኖርበታል።
ከዚህም ባለፈ በህዝቡ ልብ ውስጥ ልክ እንደሰንደቅ አላማ የሰረጸ ዘመን ተሻጋሪ መሆን ይኖርበታል መንግሥታት (Government) ሲቀያየሩ አገረ መንግሥቱ (State) እንደማይቀየር ሁሉ የአንድ አገር ሰንደቅ አላማ እና ብሄራዊ መዝሙር የሚቀየሩ አይደለም።
ለምሳሌ በአገረ መንግሥት እና በብሄረ መንግሥት ግንባታ የተሳካለቸው አገራት ለበርካታ አስርት አመታት መንግሥታት ሲቀያየሩ የብሄራዊ መዝሙራቸውን እና ሰንደቅ አላማቸውን ሲቀይሩ አይታዩም ። ለምሳሌ አሜሪካ ከ1931 ዩናይትድ ኪንግደም ከ1535 ጣሊያን 1946 ጀርመን ከ1922 አልባኒያ ከ1912 ካናዳ ከ1880 ጀምሮ እስካሁን ብሄራዊ መዝሙራቸውን አልቀየሩም። በበርካታ አፍሪካ እና ኤዥያ አገራት ከቅኝ ግዛት ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ለማነሳሻነት ሲጠቀሙበት የነበረውን መዝሙር ከነጻነት በኋላም ከትንሽ ማሻሻያ ባስተቀር እስካሁን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በአንጻሩ በሀአገራችን ለተከታታይ ሶስት ጊዜ መንግሥታት ሲቀያየሩ ብሄራዊ መዝሙራችንም አብሮ ተቀይሯል። ስለዚህ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ብሄራዊ መዝሙራችንና የባንዲራችን ምልክት መቀየር የለበትም።
ማጠቃለያ
የአንድ አገር ብሄረ መንግሥት ግንባታ በአንድ ጊዜ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም ትውልዶች በቅብብሎሽ የሚሰሩት ፕሮጀከት ነው። በመሆኑም በመሰረታዊ ጉዳዮች ግን ትውልድ በመጣ እና በሄደ ቁጥር የሚለዋውጣቸው ሊሆኑ አይገባም።
ስለዚህ አሁን በአገራችን ያሉትን ፖለቲከኞች በርእዮተ አለም መለየት ወይም መክፈል አስቸጋሪ ቢሆንም በብሄረ መንግሥት ግንባታ ባላቸው እይታ (perspective) ግን መለየት ይቻላል። በዚህ መሰረት ሲቪክ (Civic Nationalists) ብሄርተኞች ወይም ምእራባዊ ብሄርተኝነት እና የጎሳ ብሄርተኝነት (Ethnic Nationalism) ወይም ምስራቃዊ ብሄርተኝነት ብሎ መለየት ይቻላል።
ሲቪክ ብሄርተኝነት ሁሉንም የሚያቅፍ ዜግነት ተኮር እና የነጻነትን እሴቶች ማለትም ነጻነት መቻቻል እኩልነት፣ የግለሰቦች ነጻነት ነደ ብዝሀ ባህልን መሰረት በማድረግ አገረ መንግሥት በተለይ ብሄረ መንግሥት ግንባታን ማሳካት ይቻላል ብሎ የሚያስብና ከስሙም እንደምንረዳው አብዛኛው ምእራባዊያን አገራት አገራቸውን የሰሩበት መንገድ እንደሆነ ይገለጻል።
በአንጻሩ የጎሳ ብሄርተኝነት (Ethnic Nationalism) የቋንቋን እና የባህል ልዩነቶችን መሰረት በማድረግ አገረ መንግሥት ወይም ብሄረ መንግሥት መገንባት ይቻላል የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው።
ስለዚህ የአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ፖለቲከኞች ከእነዚህ በአንደኛው የፖለቲካ አስተሳስብ ስር የሚወድቁ ናቸው።ይህ ማለት ግን ቾቪኒስቶች የሉም ማለት አይደለም። እነዚህ አካላት ላዩን (Face Value) የአንዱን ሃሳብ ደጋፊ መስለው የሴራ ፖለቲካ የሚከውኑ ፖለቲከኛ ይኖራሉ።
በመጨረሻም የየትኛውም አስተሳሰብ አቀንቃኝ እንሁን ግን በሀሳብ የበላይነት በማመን በሚኖረው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር የድርሻችንን መወጣት ከትውልድ ተጠያቂነት ያድነናል።
(ዶ/ር እንዳለ ሀይሌ)
አዲስ ዘመን ጥር 13/2014