በመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት / WHO/ የተቋቋመው እኤአ በ1948 ዓም ነው ። ድርጅቱ የፈንጣጣ/smallpox/፣ የፖሊዮና የሳንባ ነቀርሳ እና የሌሎች ወረርሽኞችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳል ።
ያልበለጸጉ አገራትን የጤና መሠረተ ልማት በማገዝ ፤ ዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ፤ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶች ሲከሰቱ ተወርውሮ በመድረስና ቅድመ ምርመራ በማድረግ ይፋ ያደርጋል ።
ከመላው ዓለም ሀብትና የሰው ኃይል ያሰባስባል ። ያቀናጃል ። ከዚህ በተጨማሪም የጤና ተቋማትን ደህንነት ይከታተላል ። ለዚህ እንዲረዳው በጤና ተቋማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የቅኝት ሥርዓት/Surveillance system for attacks on health care /(SSA) ዘርግቷል ። ለዚሁ በተዘጋጀ መተግበሪያ እኤአ ከ2018 እስከ 2020 ዓም በመላው ዓለም 2ሺህ 119 ጤና ተቋማት ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል ።
የሚያሳዝነውና የሚገርመው ባለፉት አምስት ወራት በአማራና በአፋር ክልሎች የሽብር ኃይሉ በወረራ ይዟቸው በነበሩ ከ110 በላይ ከተሞች ከ3ሺህ በላይ የጤና ተቋማት የወደሙና የተዘረፉ ቢሆንም አንዳቸውም በዚህ ድርጅት የመረጃ ቋት አልተመዘገቡም ። ይህ ድርጅቱም ሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገለልተኛ ላለመሆናቸው ጥሩ አብነት ነው ።
ይባስ ብለው የድርጅቱን ሀብትና ያላቸውን ኃላፊነት ለአሸባሪው ሕወሓት የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አቋራጭ መንገድ እንዳደረጉት በገሀድ እየታዘብን ነው ። የሽብር ኃይሉ በዘረፋቸውና ባወደማቸው የጤና ተቋማት የተነሳ የሚሊዮኖች ጤና ለአደጋ ሲጋለጥ ፤ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ነፍሰ ጡር እናቶች ፣ ህጻናት ፣ የኤችአይቪ/ኤድስ ፣ የስኳርና የሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሕሙማን መድኃኒት ፣ ክትትልና ሕክምና ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ ፤ ለከፋ የጤና ችግር ሲዳረጉና የእናቶችና የሕጻናት ክትባት ሲስተጓጎል ትንፍሽ ያላሉት ዋና ዳይሬክተር ድርጅታቸው ሕወሓት ላመጣው ቀውስ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ ሲያደርጉና የአገሪቱን ገጽታ ጥላሸት ሲቀቡ ተስተውለዋል ።
በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ አድርጓል እያሉ የፈጠራ ክስ ሲደርቱ ለትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ቀፍቃፊ ስለሆነው እፉኝቱ ሕወሓት ግን አንድም ወቀሳ ሰንዝረው አያውቁም ።
የትግራይን ሕዝብ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ እየተጠቀመ ፤ ልጁን ለጦርነት ያልሰጠ እርዳታ አያገኝም በማለት እርዳታን እንደማስገደጃ ጦር መሳሪያ ሲጠቀምበት ፤ የእርዳታ መጋዝኖችን ሲዘርፍ ፤ እርዳታን ለሠራዊቱ ቀለብ ሲያውል ፤ ለሕጻናት የተላከን አልሚ ምግብ በወታደራዊ ስንቅነት ሲጠቀምበት ፤ በአማራም ሆነ በአፋር ክልሎች የእርዳታ እህል የሚጓጓዝባቸውን መንገዶችና ድልድዮችን ሲያፈርስ ፤ የእርዳታ ማጓጓዣ መንገዶችን ሆን ብሎ በከባድ መሳሪያ በመደብደብ እንዲዘጉ ሲያደርግ ፤ እርዳታ ሊያደርሱ የተላኩ ከ1ሺህ 110 በላይ ተሽከርካሪዎችን መቐሌ አግቶ የሠራዊት ፣ የትጥቅና የስንቅ ማጓጓዧ ሲያደርጋቸው ፤ ትንፍሽ ያላሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ሰሞኑን ያለምንም ሀፍረት አይናቸውን በጥሬ ጨው ታጥበው የኢትዮጵያን መንግሥት ሲከሱ መስማት ያበግናል ። ያማል ።
መንግሥት የእርዳታ እህሉ በአግባቡ ለሕዝብ እንደማይደርስና አሸባሪው ሕወሓት ለጡርነት እንደሚያውለው እያወቀ 70 በመቶ የሚሆነውን እርዳታ ለክልሉ ከማቅረብ ባሻገር ከክልሉ ለቆ ከወጣ በኋላም በየብስም በአየርም እርዳታ ለማድረስ ጥረት አድርጓል ። የተናጠል ተኩስ አቁሙን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም መጀመሪያ እርዳታ የሚጓጓዝበትን የወሎ መስመር ፤ ከቅርብ ጊዜ ደግሞ በአባላ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ የአፋርን መንገድ አስተጓጉሏል ። ዋና ዳይሬክተሩ ራሳቸውም ሆኑ ድርጅታቸው ሕወሓት የዚህ ሁሉ አሻጥርና ደባ አካል ሆነው እያለ መንግሥትን ይወነጅላሉ። ይህ ሁሉ ዋይታ የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት እና በጫና ብዛት ቀጥታ ዓለም አቀፍ የመቀሌ በረራ በማስጀመር የጦር መሳሪያ ለማግኘት እንጂ ፤ ሁለቱም ስለትግራይ ሕዝብ ምንም ግድና ደንታ እንደሌላቸው ባለፉት 30 ዓመታት አረጋግጠናል ። ዋና ዳይሬክተሩ የትግራይ ሕዝብ ሕይወት ግድ የሚላቸው ቢሆኑ ኖሩ ድርጅታቸው ሕወሓት ይሄን የዕብሪት ጦርነት እንዳይጀምር የበኩላቸውን ጫና ማሳደር ፤ ለሦሥት ዓመታት ለእርቅና ለሰላም ሲለመን አሻፈረኝ ሲል ባላየ ባልሰማ ማለፍን ባልመረጡ ።
በእብሪትና በተሳሳተ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስሌት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የድሀ ትግራዋይ ልጆች እንደ ቅጠል ሲረግፉ ፤ በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት የአገርና የሕዝብ ሀብት ንብረት ሲወድም እምጥ ይግቡ ስምጥ ባልጠፉ ። የያዙትን ኃላፊነት በመጠቀም ለአሸባሪው ሕወሓት የሚዲያ ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት ጦርነቱን ባላባባሱ ።
ከማይካድራ እስከ ጋሊኮማ የዘር ማጥፋት ፣ የጦር ወንጀልና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል ሲፈጸም ፤ ሕጻናት ፣ እናቶችና መነኮሳት በቡድን ሲደፈሩ ዝምታን ባልመረጡ ።
የሽብር ኃይሉ በሕዝባዊ ማዕበል ጊዜያዊ የድል በለስ ሲቀናው ፤ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ሲወጣ ፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎን፤ ደቡብ ጎንደር የተወሰኑ አካባቢዎችን ሲቆጣጠር ፤ ከሚሴን ደብረ ሲናን ሲወር ትንፍሽ ያላሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ተጠራርጎ መማጸኛ ከተማው መቐሌ ሲገባ መርጦ አልቃሹ የሕወሓት ጠበቃ በሐሰተኛ መረጃ መንግሥትን እየከሰሱና እያሳጡ ይገኛሉ ።
ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ “ የከፋ ጦርነቶች ባሉባቸው እንደነሶሪያና የመን ባሉ አገራት እንኳ ባልተገታበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ባልታየ ሁኔታ መድኃኒትና የዕለት ደራሽ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ታግዷል ።”ብለዋል ።
በምንም መስፈርት የሶሪያና የየመን ግጭት ከእኛ ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም ። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ፤ መንግሥት ወደዚህ ጦርነት ተገዶ ከገባ በኋላ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ስምንት ወራት ሲቆይ ለመልሶ ማቋቋም 100 ቢሊዮን ብር ወጭ ከማድረግ አልፎ ፤ በክልሉ 70 በመቶ ያህሉን እርዳታ ያቀረበ ሲሆን በተናጠል የተኩስ አቁም ለቆ ሲወጣም ለትግራይ ሕዝብ ሲል የእርዳታ እህል ፣ የምግብ ዘይት ፣ ዘር እና 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ትቶ ነው የወጣው ።
ምን ይሄ ብቻ መንግስት ለትግራዋይ አሽከርካሪዎች ምህረት ከማድረግ አንስቶ ከጦርነት ቀጣና ነጻ የሆነ የእርዳታ ማጓጓዣ መስመር እንዲከፈት ቅድሚያ ተነሳሽነቱን ወስዷል ። ይሄን መንግሥት ነው ዋና ዳይሬክተሩ እየከሰሱና እያሳጡ ያሉት ።
ምንም አይነት የቅስም/የሞራል/ልዕልና የሌላቸው የዓለም የጤና ድርጅት የአማራና የአፋር ሕዝቦች በሽብር ኃይሉ ያ ሁሉ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ሰቆቃ ሲፈጸም ለይምሰል እንኳ ምንም ሳይሉ ኖረው ፤ በዓለም መንበር ለመንደር እየተንዘረዘሩ ይገኛሉ ።
“በትግራይ የመድኃኒት እጦት ሰዎች በየቀኑ እንዲሞቱ እያደረገ ነው። የምግብ እጦትም በየቀኑ ሰው ይገድላል። ይህ ሁሉ ሳያንስ በየቀኑ የድሮን ጥቃት መፈጸምና ዜጎች በፍርሃት ተሰቅዘው እንዲቆዩ ማድረግ ትክክል አይደለም” ብለዋል ። ለዚህ ሁሉ አገራዊ ቀውስ ጠንሳሽ ስለሆነው ድርጅታቸው ግን ትንፍሽ አላሉም፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የዓለም ጤና ድርጅትን ሲቀላቀሉ፤“የተጣለብኝን ኃላፊነት እና የተሰጠኝን አደራ በታማኝነት ፣ በነጻነትና በንጹሕ ህሊና ፤ ልወጣና ልፈጽም ቃል እገባለሁ ።”በማለት የፈጸሙትን ቃለ መሐላ በመጣስ እምነት አጉድለዋል ።
አደራ በልተዋል ። በመላ ዓለም የሚገኙ የሰው ልጆችን ለማገልገል የተቀበሉትን ከፍተኛ ኃላፊነት አላግባብ እየተጠቀሙ ነው ። ሰውየው ላይ የመሪነት አቅምና ብቃት ጉዳይም ተደጋግሞ ይነሳባቸዋል። በአውስትራሊያ ሲዲኒ የሚገኝ ገለልተኛ ተቋም አባል የሆኑት ሳልቫቶሪ ባቦኔስ በዚያ ሰሞን”ፎሪን ፖሊሲ”መጽሔት ላይ ባስነበቡን መጣጥፍ ፤ ኮቪድ 19 በዓለማችን ላይ ላስከተለው የሚሊዮኖች ሞትና ተያይዞ ለተከሰተው ቀውስ ተጠያቂው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ደካማ አመራር ነው ሲሉ በማስረጃ ይሞግታሉ ። 110 አገራት ድርጅቱና አመራሩ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ መጠየቃቸውንም አውስተዋል ። በጥቁሩ ናዚ እጅ የወደቀው የዓለም ጤና ድርጅት WHO ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለስ ዋና ዳይሬክተሩ በድርጅቱ መንበርና ሀብት የእፉኝቱንና የአሸባሪውን አጀንዳ ለማስፈጸም በግላጭ ተንቀሳቅሰዋል ።
በድርጅቱ ሽፋን ዓለምን እየዞሩ የሕወሓት ቃል አቀባይ ፣ አምባሳደርና አግባቢ/ሎቢስት/ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል ። ኃላፊነታቸውን አላግባብ እየተጠቀሙ ነው ። ቦታው የከፈተላቸውን የግንኙነት መስመር በመጠቀም አቻ የመንግሥታቱ ድርጅትን ተቋማት ፤ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችንና ሚዲያዎችን በትግራይ ሕዝብ ሽፋን ለድርጅታቸው ሕወሓት የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ሽፋን በማስገኘት አፈር ልሶ እንዲነሳ ከማድረግ ባሻገር በፈጸማቸው ኅልቆ መሳፍርት በሌላቸው ግፎች፣ ሰቆቃዎች ፣ ዘረፋዎችና ውድመቶች ለጊዜውም ቢሆን በዓለማቀፍ ደረጃ እንዳይጠየቅ አግባብተዋል ።
ቀስቅሰዋል ። ዋና ዳይሬክተሩ በተቃራኒው የግፉና የሰቆቃው ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያና ዜጎቿ ስማቸውና ገጽታቸው በዓለም አደባባይ እንዲጠለሽና እንዲኮሰምን ከማድረግ ባሻገር የተቀነባበረና የተናበበ ጫና እንዲፈጠርባቸው የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ላይ ናቸው ። በዚህም የዓለም ጤና ድርጅትን እሴቶች ጥሰዋል ። አዎ ! ኃላፊነታቸውን በሐቀኝነት ፣ በተጠያቂነት ፣ በገለልተኝነት፣ በፍትሐዊነትና በብዝኃነት የመወጣት ኃላፊነት ቢኖርባቸውም ከዓለም መንበር ወርደው ለመንደር መታመንን መርጠዋል ። ጥቁሩን ፋሽስትና ናዚ ሕወሓት በአደባባይ ደግፈው ቆመዋል ።
መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ሲወጣ ዋና ዳይሬክተሩ በቲዊተርና በፌስቡክ ብቅ ብለው በእንግሊዘኛ “ክብር ፣ ኩራት / ፕራይድ/ ብለው ለጠፉ ፤ ጊዜያዊ የድል በለስ በቀናው አጋጣሚ እንደተለመደው በእብሪት ብቅ ይሉና”በራስ መተማመን ፣ ልበ ሙሉነት/ኮንፊደንስ/” ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ” ፍጹምነት/ ሰርቲቲውድ/” በማለት ይመጻደቁብናል ።
አሸባሪው ሕወሓት ምት ሲበዛበትና ሲቀጠቀጥ ደግሞ ያን ሁሉ ትምክህት ፣ ማንአህሎኝነት ፣ ማንአብኝነትና እብሪት ረስተው እየያቸውን ያቀልጡታል። ትግራይ ምድራዊ ገሀነም ሆነች እያሉ ያለቅሳሉ ።
መንግሥት የዘገየ ቢሆንም ሰሞኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ ግለሰቡን አስመልክቶ አቤቱታ እንዲያቀርብ ያስገደደው ይህ መረን የለቀቀ አድልዎና መድልዎ ነው ። በማመልከቻው ላይ በዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተነሳ የድርጅቱ የገለልተኝነት መርሕ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አስመዝግቧል ። ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ከወሰደ ግለሰብ የሚጠበቅ ሙያዊ ገለልተኝነት እንዳላሳዩ አመልክቶ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ግንኙነት ሳይቀር ጣልቃ መግባታቸውን አትቷል ። ከዚህም ባሻገር ዶ/ር ቴዎድሮስ አሁንም በአሸባሪነት ለተፈረጀው ሕወሓት ድጋፍ መስጠት መቀጠላቸውንና አባልም መሆናቸውን አውስቷል ።
አንዳንድ ይፋ ያልወጡ መረጃዎች ክሱን ለመመርመር እንደወሰነ እያመለከቱ ቢሆንም ፤ መንግስት ለቦርድ አባላቱ ተጨባጭ ዝርዝር ማስረጃዎችን ከማቅረብ አንስቶ በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማጀብና ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአዲስ አበባ የሚዘጋጀውን የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የዙሪያ መለስ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻው መድረክና አካል በማድረግ አጋጣሚውን በአግባቡ ይጠቀማል ተብሎ ይታመናል ።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 12/2014