በቀደመው እትም ለመግለፅ እንደሞከርነው፣ ጤና ማለት የህመም አለመኖር ማለት ብቻ ሳይሆን ሰዎች በአካላዊ ፣ በአዕምሯዊ እና በማህበራዊ ኑሯቸው ውስጥ የሚኖራቸው ወይም የሚሰማቸው የደህንነት ስሜት ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ጤናን በዋናነት ለሦስት አበይት ክፍሎች መክፈል ይቻላል። እነዚህም አካላዊ ፣ አዕምሯዊ እና ማህበራዊ ጤናዎች ናቸው። እነዚህ የጤና ዓይነቶች አንዳቸው ከአንዳቸው የተለያዩ ቢሆኑም እንኳን፤ እርስ በርሳቸው የማይበላለጡ ወይም አንዳቸው ከአንዳቸው አንሰው የሚታዩ አይደሉም። አንዱ የጤና ዓይነት መታወክ ለሌላው የጤና ዓይነት መታወክ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለአካላዊ ጤና የሚሰጡት ግምት ከሌሎች የጤና ዓይነቶች ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው። ይህ አመለካከት ስህተት ሲሆን ፣ አዕምሯዊ እንዲሁም ማህበራዊ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩል ያልተናነሰ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የጤና ዓይነቶች ናቸው።
አካላዊ ጤና
አካላዊ ጤና ማለት በከፍተኛ ህመም አለመያዝ ማለት አይደለም። በውስጡ በርካታ ነጥቦችን ያካተተ እና ግምት ውስጥ ያስገባ የጤና ዓይነት ነው። አካላዊ ጤንነትን ከሚወስኑ ቁልፍ ነገሮች ውስጥ የአካባቢ ሁኔታ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና የዘር ሁኔታ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ለምሳሌ ያክል ተመሳሳይ ፆታ እና ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎች የተለያየ የአኗኗር ዘይቤ ሊከተሉ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ አንዳቸውን ከአንዳቸው የሚጠቁበት በሽታ ዓይነት የተለየ ነው። ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ ቢኖራቸው እንኳን ካላቸው የዘር ልዩነት የተነሳ እንዳቸው ላይ የተከሰተ የበሽታ ዓይነት ሌላኛቸው ላይ ላይከሰት ይችላል። ለዚህም የስኳር ህመምን፣ የደም ግፊትን እና አንዳንድ የካንሰር ህመም ዓይነቶች ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
እነዚህ የህመም ዓይነቶች አንዳንድ ሰዎች ጋር ፤ ለህመሙ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ሆነው ሳለ በህመሙ የማይጠቁ ሲሆን ይታያል። በአንጻሩ ደግሞ በአነስተኛ ደረጃ ለህመሙ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ግን ህመሙ ሊከሰት ይችላል።
የአካላዊ የጤና ግብዓቶች
አካላዊ ጤና/ጤንነት የአመጋገብ ሥርዓትን፣ የኗኗር ዘይቤን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ በቂ እረፍት እና እንቅልፍን የያዘ ነው። እነዚህን ያላካተተ አካላዊ ጤና ሙሉ ጤና ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። ከላይ የተጠቀሱት የአካላዊ ጤና ግብዓቶች አንዱ እንኳን ቢጎድል ወይንም በአግባቡ ባይተገበር ሙሉ ለሙሉ የጤና ሥርዓቱን ያውካል።
የአመጋገብ ሁኔታ
ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ጤንነታቸው ተጠብቆ እና በአግባቡ እንዲሰሩ የተመጣጠነ ምግብ እና ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ሁሉም የሰውነት ክፍሎች በእኩል መጠን እና ዓይነት ምግብን አይወስድም። የተመጣጠነ ምግብ ማለት ሰውነታችን ሥራውን በአግባቡ ለመስራት የሚያስፈልገውን ስድስቱን የምግብ ዓይነቶችን ያካተተ ማለት ነው።
እነዚህ የምግብ ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸው። ስኳር (carbohydrate ) ቅባት(fat) ፣ፕሮቲን (protein) ቫይታሚን (vitamins) ሚኒራል (minerals) እና ውሃ (water) ናቸው። አንዳንድ ጊዜ Fiber የሚባለውን የምግብ ዓይነት ተጨማሪ ሆኖ ሊካተት ይችላል። ስድስቱ (የምግብ ዓይነቶች በሰውነታችን በእኩል መጠን አይወሰዱም፤ አይፈለጉም። ይህም ማለት ውስጥ የሚያስፈልገን የስኳር መጠን ፤ የፕሮቲን እና ቅባትን በከፍተኛ መጠን ሲወስዱ ሚኒራሎችን እና ቫይታሚኖች በቀን ውስጥ በጣም በዝቅተኛ መጠን ይወስዳሉ።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው የትኛውም የምግብ ዓይነት አንዱ ከአንዱ አይበልጥም። አያንስም ሁሉም ሰውነት በሚያስፈልገው መጠን መውሰድ አለበት። ቫይታሚኖች እና ሚኒራሎችን ስንወስ ዳቸው የማናውቃቸው መጠናቸውም አነስ ተኛ ቢሆንም እነሱን ያላገናዘብ የምግብ ዓይነት ባለመውሰዳችን የሚከሰተው የጤና ቀውስ ከባድ ይሆናል። አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ ነው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ስድስቱ የምግብ ዓይነቶች ከመጠን በላይ መውሰድም የራሱ የሆነ አደጋ ያለው ሲሆን፤ ስሙ እንደሚገልጸው በመጠንም ሆነ በዓይነት የተመጣጠነ መሆን አለበት።
የአኗኗር ዘይቤ
የአኗኗር ዘይቤ ማለት ሰዎች ሕይወታቸውን ከራሳቸው እና ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር አስማምተው የሚኖሩበት መንገድ /አካሄድ ማለት ነው። የአኗኗር ዘይቤ ለአካላዊ ጤና ወሳኝ እና አስፈላጊ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ይመደባል።
የአኗኗር ዘይቤ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን፣ አመጋገብና ፣ የሥራ ፀባይን፤ የአካባቢ ሁኔታን ያካተተ ነው። የኗኗር ዘይቤ ያቸው በብዛት የሚንቀሳቀስ እና የአመጋገብ ሥርዓታቸውን በሚገባ የሚቆጣጠር ነው። ሰዎች ለተላላፊ በሽታ የመጋለጥ ዕድል እንዳላቸው ያነሰ ነው። እነዚህ ሰዎች በህመም ቢጠቁ እንኳን ህመሙ ከአንድ የከፋ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ እንዳይሸጋገር ይረዳል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
ማንኛውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአካላዊ ጤና የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በቋሚነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ከአካላዊ ጤና አልፎ አዕምሯዊ ጤናማነታቸው በጣም ከፍተኛ ይሆናል። በማህበራዊ ሕይወታቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጥናቱ ያመለክታል። እንቅስቃሴ በውስጡ የሰውነት ጥንካሬ፣ የሰውነት የመተጣጠፍ አቅም እንዲሁም የሰውነት ጽናት (endurance) የምንለውን ያካተተ ነው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መተግበር የሐኪም ምክር ወይንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎችን ማማከር ተገቢ ነው። ምክንያቱም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላያስፈልግ ይችላል።
ለምሳሌ የልብ ህመም፣ የስኳር ህመም ከአካላዊ አደጋ የሚያገግሙ ሰዎች የሚሰሯቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ከሌሎች ሙሉ ጤና አላቸው ብለን ከምና ስባቸው የተለየ ነው። ስለዚህም ማንኛውም ሰው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት ሌላ ተጨማሪ ህመሞች ወይም አደጋዎች እንደሌሉ ማወቅና ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ህመሙ ወይም አደጋው ያለ እንኳን ቢሆን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል።
በቂ እንቅልፍ እና እረፍት
ለሰው ልጅ እንቅልፍ እና በቂ እረፍት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው። በቂ እረፍት እና እንቅልፍ ባለማግኘታቸው ለተለያዩ አካላዊ ለአዕምሯዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላሉ። በቂ እንቅልፍ ከዕድሜ ዕድሜ የሚለይ ነው። ለምሳሌ በህጻንነትና በጨቅላ ጊዜያት የሚኖረን የእንቅልፍ ሰዓት ረዘም ያለ ነው። ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ ይህ የእንቅልፍ ጊዜ እያነሰ ይመጣል። በወጣቶች፣ በጎልማሶች እና በአዛውንቶች በቀን 8 ሰዓት እንዲተኙ ይመከራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011