በአገር ግንባታ ላይ እጅግ ዋጋ ካላቸው ኃይሎች ውስጥ አንዱ የሀሳብ የበላይነት ነው::አብዛኞቹ የዓለማችን ስልጡን አገራት ከኢኮኖሚ የበላይነት ባለፈ ሉአላዊነታቸውን የገነቡት በዚህ የላቀ እውነታ ውስጥ በማለፍ ነው:: አሁን ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው አገራችን ይሄን መሰል ሕዝባዊ እሳቤ ያስፈልጋታል:: እንደ አገር አብዛኞቹ ችግሮቻችን ንትርክ ወለድ ናቸው::
አብዛኞቹ ዝቅታዎቻችን ከበላጭ ሀሳብ ይልቅ ለእኔነት ሀሳብ እጅ የሰጡ ናቸው:: ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ ችግሮቻችንም ከዚሁ ከላቀ ማህበራዊ እሳቤ እጥረት የመነጩ ናቸው:: እስካሁን ድረስ እየጎዱን ያሉ ነገሮች ሁሉ እያወቅናቸው ልብ ያላልናቸው ነገሮች ናቸው:: አንድን ነገር ማወቅ እና መረዳት ይለያያሉ:: ብዙዎቻችን በትምህርት፣ በልምድ በተለያየ መንገድ ብዙ ነገር የምናውቅ ነን ፤ የምናውቀውን ነገር የተረዳን ግን ጥቂቶች ነን:: አሁን ላይ አገር እየተፈተነች ያለችውም ብዙ ነገር በሚያውቁ ጥራዝ ነጠቆች ነው::
ሕዝባችን ነገሮች በድህነት ላይ ቁምጥና ሆኖበት ያለው ከአብራኩ በወጡ አዋቂ ነኝ ባዮች ናቸው:: መረዳት ስቃይ ሆኖ አያውቅም:: መረዳት አቅጣጫው ወደ መፍትሄ ነው:: የእናንተስ እውቀት ምን ዓይነት ነው? በእውቀታቸው አገርና ሕዝብ ከሚያስጨንቁት ውስጥ ናችሁ ወይስ ያወቁትን በመረዳት ለመፍትሄ ከቆሙት ውስጥ? አገር ወዳድ የሆናችሁ ሁሉ ይሄን ጥያቄ በመመለስ ለአገራችሁ ብርሃን መሆን ይቻላችኋል::
አንድን ነገር ለማወቅ ሳይሆን ለመረዳት ሆነን እንቅረበው:: አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነች ብንረዳ ኖሮ ዛሬ ላይ ይሄን ሁሉ መከራ አንፈጥርባትም ነበር::
መረዳት ከማወቅ እጅግ ይበልጣል:: ማወቅ እውቀት ሲሆን መረዳት ግን ጥበብ ነው:: ሕይወታችንን በማወቅ ሳይሆን በመረዳት እንኑረው:: መረዳት ሕይወትን ውብ የሚያደርግ የመጨረሻው የብስለት መለኪያ ነው:: አንዳንድ ሰዎች ያወቃችኋቸው ሲመስላችሁ ሌላ ሰው ሆነው ግራ አጋብተዋችሁ አያውቁም? ይሄን ሁሉ ጊዜ አብሬው ሆኜ ላውቀው አልቻልኩም ያላችሁት ሰው የለም? አለ እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ::
ጎጂ ነገሮችን ጨምሮ በሕይወታችን የምንፈልጋቸው ማናቸውም መልካም ነገሮች በእኛ አስተሳሰብ በእኛ ጭንቅላት የሚፈጠሩ ናቸው:: ራሳችንን ለመልካም ነገር ካዘጋጀነው መልካም ነገርን መውረስ እንችላለን፣ በተመሳሳይ መንገድ ራሳችንን ለክፉ ነገር ካስገባነው ያንኑ ስሜት ወደ ራሳችን እናመጣለን::
የምታስቡት ማንኛውም ነገር ነገ ላይ ሕይወታችሁ ሆኖ ወደ እናንተ ይመጣል:: የነገ ዓለማችሁ ዛሬ በምትሆኑት አሁናዊ ነገር የተዋቀረ ነው:: ነገ ላይ ለአገርና ለወገን አስፈላጊዎች እንድንሆን በዛሬ ሕይወታችን ላይ ዋጋ ወዳላቸው ነገሮች መመልከት ይጠበቅብናል:: ጎዳናችን የሚቀናው፣ ነጋችን ብሩህ የሚሆነው ዛሬ በምንሆነው ነገር ነው:: ከከሰረ ሀሳብ ውስጥ የተዋጣለት ሕይወት አይገኝም::
ሳንንገዳገድ ወደፈለግንበት የምንሄደው ሩቅ የሚያደርስ ቀና እሳቤ በውስጣችን ሲኖር ነው:: ሀሳባችንን እንድንገዛው እንጂ እንዲገዛን አንፍቀድለት:: የሀሳቡ ባሪያ..የስሜቱ ሎሌ የሆነ ሰው ልክም መጨረሻ የለውም:: ሀሳቦቻችን መንገድ ጠራጊዎቻችንም መንገድ ዘጊዎቻችንም ናቸው::
ዛሬ ላይ በብዙ ደስታና ስኬት ከፍታ ላይ ወጥተው የምናያቸው እነሱ ትናንት ላይ መልካም ሀሳብ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ:: ዛሬ ላይ ለራሳቸውም ሆነ ለአገር ነቀርሳ ሆነው የቆሙ ግለሰቦች በአመክንዮ ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው:: ከስህተት ሁሉ ስህተት ያለ አላማ መኖር ነው:: ያለአላማ መኖር የዚህ ዓለም የመጨረሻው ስህተት ነው:: በሕይወት ጉዞ ውስጥ የምንደነቃቀፍባቸው እንቅፋቶች
ሁሉ ከዚህ አላማ አልባ ማንነት ውስጥ የወጡ ናቸው:: አላማ ራስን በግብረገብነት ውስጥ ማኖር ነው:: አላማ ራስን ጠቃሚና አስፈላጊ አድርጎ ማቆም ነው::
የአገር ፍቅርአንዱ ማሳያ ሆኖም ይቆጠራል:: ያለአላማ መሽቶ የሚነጋ ቀን አይኑራችሁ:: ሕይወት ምን ያክል ውድና እጅግ ድንቅ ተፈጥሮ እንደሆነ የምንረዳው ከከንቱነት ርቀን ራሳችንን በአላማ ስንመራው ነው:: ከትናንት እስከ ዛሬ አገራችን ላይ የደረሱ ጥፋቶች ሁሉ ከዚህ ማንነት ውስጥ የወጡ ናቸው:: ያለአላማ መኖር እንስሳዊ ባህሪ ነው::
የጭካኔና የስግብግብነት መገለጫ ነው:: ስንፈጠርም በምክንያት ነበር:: ምክንያታችን ደግሞ በታላቅ ዋጋ መኖር ነው:: ታላቅ ዋጋ ያለው ደግሞ በአላማ ውስጥ ነው::
በርካታ ጥናቶች በአላማ መኖርን የትልቅ ነገር ማሳያ እንደሆነ ነው የሚናገሩት በተቃራኒው ደግሞ ሰው ያለአላማና ያለራዕይ የሚኖር ከሆነ እንስሳዊ ባህሪን እየተላመደ በዙሪያው ላሉ ጨካኝና አስደንጋጭ መሆን ይጀምራል ይላሉ:: ይሄ ብቻ አይደለም አላማ የሌለው ሰው ለመኖር የሚያጓጓ ነገር ስለሌለው ሀሳቡ ሁሉ ጎጂና አውዳሚ በመሆኑ ለአገር ስጋት ፈጣሪ ነው በማለት ያክላሉ:: በነገራችን ላይ አላማ ያለው ሰው ስህተት አይሠራም ስህተት ቢሠራ እንኳን ለመታረምና ለመስተካከል ራሱን ያዘጋጀ ነው::
አላማ በማወቅ ተጀምሮ በመረዳት የሚጠናቀቅ ነው:: በትንሽ እውቀት ውስጥ ትልቅ አላማ የለም:: ትልቅ አላማ ያለው በትልቅ እውቀትና በትልቅ መረዳት ውስጥ ነው:: ራሳችሁን ትልቅ አድርጋችሁ ፍጠሩ:: የሕይወት ትርጉም ከምትረዱበት ቁም ነገር አንዱ ለራሳችሁ ክብርና ዋጋ በመስጠት የምትኖሩት ዛሬ ነው:: ዛሬ ላይ እኔና እናንተ በምንሆነው ነው አገር የምትፈጠረው:: የአገራችን ፈጣሪ እኔና እናንተ ነን :: ጠንካራ አገር ለመፍጠር በአላማ የተቃኘ ጠንካራ ሀሳብ ያስፈልጋል። ዛሬ ለምንገነባው ብሩህ ነገ ጥሩ ግንበኛ መሆን ይጠበቅብናል።
ዛሬ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የሀሳብ የበላይነት የምትሻበት ጊዜ ላይ ነን:: ልዩነትን የሚያጠብ የላቀ ሀሳብ ከእያንዳንዳችን ያስፈልጋል:: ፊት ተፈጥረን ኋላ የቀረነው አስታራቂ ሀሳብ ያለው ትውልድ ታጥቶ ነው ::
ለዛሬ ተለያይቶ መቆም በትውልዱ መካከል መልካም ሀሳብ መጥፋቱ የፈጠረው ክፍተት እንደሆነ አምናሁ:: አገር ከመገንባት ይልቅ በፍሬከርስኪ አገር እያወደሙ ያሉ ሞልተዋል:: በሀሳባቸው፣ በኑሯቸውም ዘቅጠው አገር ለማጥፋት ታጥቀው የተነሱ የእንግዴ ልጆች እዚያም እዚህም አሉ::
አገር የምትገነባውም የምትፈርሰውም በሀሳብ ነው :: እናም በላቀ የሀሳብ ካብ አገር ለመገንባት ዛሬውኑ አላማ ባነገበ.. በላቀ ሀሳብ አሸንፎ መውጣት ይጠበቅብናል:: ከእኛ ውጪ በእኛ ላይ ኃይል ያለው የለም::
በሰከነና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማሸነፍን እንልመድ:: ከጦርና ከጎራዴ ውጪ ያለውን ዓለም በምክንያታዊነት መሞገት፣ መቃኘት ያስፈልጋል:: ብዙዎቻችን መብቶቻችንን ለማስከበር ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከመነጋገር ይልቅ ኃይልን የምናስቀድም ነን:: ይሄ ዓይነቱ አካሄድ ለአገራችን ሲጠቅም አላየንም::
ይልቅ በእወቀትና በሰለጠነ መንገድ ለችግሮቻችን መፍትሄ በመስጠት ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን ማሳየት ይኖርብናል:: አድርገንም ማሳየት ይጠበቅብናል።
ጦርና ጎራዴ አውዳሚ ናቸው::
ጥላቻና ኃይል በወንድማማቾች መካከል ትርፍ የላቸውም:: ትርፋችን ያለው በሀሳባችን ፣ በአንድነታችን ውስጥ ነው:: እስካሁን ትርፍ ያለው እየመሰለን በማይጠቅሙን ነገሮች እየከሰርን ኖረናል:: እኛም ሳንጠቀም አገርም ሳትጠቀም ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት መቀመቅ ወርደን በድህነት ስንማቅቅ ኖረናል:: የእስካሁኑ አገራዊ ገመናችን በእኛው ተለያይቶ መቆም የተፈጠረ እንጂ በምንም የመጣ አይደለም::
የሚሠሩ እጆች፣ የሚያስቡ ጭንቅላቶች.. ለውጥ የናፈቀው መቶ ሃያ ሚሊዮን ዜጋ እያለን ለጥሩ ነገር ዕድል ሳናገኝ በድህነት እንማቅቃለን:: ለዚች ድሀ አገር እኛ እናስፈልጋለን፣ የተሻለ ሀሳብ ርቧታል።
ስለዚህ ማሸነፊያችንን ሀሳብ አድርገን እንሟገት እንጂ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ቁጭት ከንፈራችንን አንንከስ:: ሌሎችን ማድመጥ ራስን ከማድመጥ የሚመነጭ ነው:: ከአፍራሽ አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ሰለጠነ ዘመናዊ እይታ መረማመድ እጅግ ዋጋ አለው:: ማሸነፍን በመሣሪያና በጉልበት ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት እንቀበለው:: በልዩነት ውስጥ መግባባትን፣ ባለመስማማት ውስጥ መስማማትን ባህል እናድርግ::
የምንታገለው ለአንድ አገርና ሕዝብ እስከሆነ ድረስ የሚያቀያይመንና ቂም የሚያያይዘን ምንም የለም:: በአገር ስም የሚነግዱ ብዙ አድርባዮች ይኖራሉ፤ በአገር ስም ራሳቸውን ለመጥቀም የሚታገሉ ዛሬም ነገም አሉ። ይኖራሉ። አብዛኛው አለመስማማታችንም ከዚህ የመነጨ ነው::
አገር የሚለውጡ ትልልቅ ሀሳቦችን እየጣልን በትንሽ ሀሳቦች ላይ ጊዜ አችንን የምናጠፋው ለዚህ ነው:: አላማችን አንድ አገርና ሕዝብ ቢሆን ኖሮ መስማማት እንደማያቅተን አምናለሁ:: አንዳንዱ ለምንም ነገር አገሩን ያስቀድማል፣ አንዳንዱ ለምንም ነገር ራሱን ያስቀድማል።
በዚህ ቅጥ አምባሩ በጠፋ ስብዕና ሳንግባባ ኖረናል:: ይሄ ብቻ አይደለም መነሻችንም መድረሻችንም ስልጣን ስለሆነ እኔ ያልኩት ካሆነ በሚል ለጠብ ሕዝብ እናነሳሳለን:: የእኛ ሀሳብ ካልተሰማ በሚል አገር የሚያፈርስ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በማህበራዊ ሚዲያ እንለቃለን:: ምን ዓይነት ርዮት ዓለም እንዳለን አላውቅም:: ሲበዛ ራስ ውዳድና ስግብግቦች ነን::
ሰው እንዴት በቀን ሦስት ጊዜ መብላት የማይችል ሕዝብ ይዞ ላለመስማማት ይወያያል? ሰው እንዴት ከአገርና ሕዝብ ከታሪክ በላይ ራሱን ያስቀድማል? አሁን ግን መነሻችንም መድረሻችንም አገራችን መሆን ይገባዋል። ምክንያቱም ወደ ፊት ለመሄድ የአገር እውነት ከግለሰብ እውነት ይበልጣልና:: አላማውን አገር ያደረገ ዜጋ ሰላምን እንጂ ጦርነትን አያውቅም:: አላማውን ሕዝብ ያደረገ ትውልድ ለጋር ጥቅም በጋራ ይተጋል እንጂ መለያየትን እንደ ትልቅ አላማ ይዞ አይንቀሳቀስም:: እናንተ ግን ለዚች አገር በቀና ቁሙ::
እንደ አሸባሪው ሕወሓት ካሉ አረመኔ አስተሳሰቦች ራሳችሁን አርቁ:: እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ከሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ወጥታችሁ የብዙኃኑን ድምጽ የምሰሙበት ሰፊ ጆሮና ጽኑ ልብ አዳብሩ:: ከእኔነት ወጥታችሁ በላቀ ሕዝባዊ እሳቤ ከፊት የቆሙ የመጀመሪያዎቹ ሁኑ::
አገራችንን የመልካም ነገር መነሻ እናድርጋት:: አገሩን መነሻ ያደረገ ትውልድ መንገድ አይጠፋውም:: አገሩን መነሻ ያደረገ ወጣት መድረሻ አይጠፋውም:: አገሩን መነሻ ያደረገ ሀሳብ ከማሸነፍ አይጎድልም::
ባለፉት በርካታ ዓመታት ውስጥ በዚች አገር ላይ ከአገርና ሕዝብ የሀሳብ የበላይነት ርቋቸው ነበር:: ከአገር ጥቅም ይልቅ የግለሰቦች ጥቅም ሲከበር ነበር:: በውሸትና በማስመሰል እኔ አውቅልሀለሁ በሚል ማወናበድ አገርና ሕዝብ ከክብራቸው ዝቅ ብለው ነበር::
ነገር ግን የግለሰብ ጉዳይ ከአገርና ሕዝብ ጉዳይ መብለጥ የለበትም። የትናንት ስህተት ዛሬ መደገም የለበትም። ስለዚህ እውቀታችንን ለአገር ገጽታ ግንባታ እንጂ ለእኩይ አላማ ሳንጠቀም ፤ በሀሳብ የበላይነት እናሻግራት።
ይህን ካደረግን ለአገራችን በሠራንው በጎ ሥራ ልክ በትውልድ ልብ ውስጥ በመልካም እንታወሳለን:: እኛ የአገራችን አለላ መልኮች ነን እና:: አገራችንን በበጎ እንኳላት:: ከእውቀት ወደ ጥልቅ እሳቤ፣ ከጥልቅ እሳቤም ወደ ጥልቅ መረዳት እንውሰዳት:: እኛ ለአገራችን እናስፈልጋለን:: በሀሳብ ልዕልና ወደ ከፍታ እናሻግራት ዘንድ ጊዜው አሁን ነው ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014