አንድ ያላነበብነው መጽሐፍ ድንገት እጃችን ቢገባ አይናችን ቀድሞ የሚያርፈው የውስጥ ገፆች ላይ ሳይሆን የፊት ወይም የኋላ ሽፋኑ ላይ ነው። እርግጥ ነው መጀመሪያ አይናችን የሚያርፈው የፊት ሽፋኑ ላይ ነው፤ ቀጥሎ ግን የጀርባ አስተያየት እናያለን። ይህ ዕይታ በሁሉም ሰውና በሁሉም መጽሐፍ ላይሆን ይችላል። ምናልባት ልማዳችን ሆኖ ይሁን ባይታወቅም አዲስ መጽሐፍ ስናገኝ ዞር ዞር አድርገን ጀርባና ፊቱን እናያለን።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በጀርባ በኩል በተሰጠው አስተያየት ታምነን ለማንበብ የምንገፋፋውና መጽሐፉን የምንገዛው። ስለዚህ የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት ጥቅሙ አንባቢን ለማንበብ መገፋፋት ወይስ መጽሐፉን ለማሻሻጥ? አንዳንዶች ‹‹ባህሪው ነው›› ይላሉ፤ ‹‹አይ! የለም ያለመጽሐፉ ይዘት በማጋነን ሰውን ማጭበርበር ነውር ነው፤ የአስተያየት ሰጪውን ክብርም ያወርዳል›› የሚሉም አልጠፉም።
የምናወራው ስለመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት(ብለርብ) ነው። ቃሉን የምናውቀው በፈረንጅኛው አጠራር ‹‹ብለርብ›› በሚለው ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች የራሳችን መጠሪያ እስከሚያወጡለት ድረስ እኛም ‹‹የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት›› እያልን እንጠቀምበታልን። ቃሉ ምንም ይባል ምን ሀሳቡ ግን ያግባባናል። አንድ መጽሐፍ ሲወጣ ስለዚያ መጽሐፍ በጀርባው በኩል የሚሰጠው አስተያየት ማለት ነው። አስተያየቱ የሚሰጠው ስለዚያ መጽሐፍ አጠር ያለ መግለጫ ማለት ነው።
አላማው መጽሐፉን አንባቢ እንዲያነበው ማስተዋወቅ ወይም ጉጉት ለመፍጠር ነው። አስተያየት እንዲሰጡ የሚመረጡት ሰዎች ብዙ ጊዜ ታዋቂና ተደናቂ የሆኑት ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፤ እነርሱ አስተያየት ሲሰጡበት መጽሐፉ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው። ዋናው ጥያቄ ግን መጽሐፉ የተሰጠውን አስተያየት ያህል ነው ወይ? የሚለው ነው። ማጋነን የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት ባህሪ ይሆን? አንባቢዎችንስ ይስብ ይሆን? ለተነሳንበት አላማ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን አነጋግረናል።
ጋዜጠኛ አብርሃም ገብሬ በርካታ መጻሕፍት አሉት። ከልጅነቱ ጀምሮ አንባቢ ነው። የገዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ የጀርባ አስተያየት እያየ የሚገዛቸው ባይሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን የጀርባ አስተያየት አይቶ ይገዛል። በተለይም አስተያየቱን የሰጠው ሰው የሚያደንቀው ደራሲ ከሆነ መጽሐፉን መግዛት እንዳለበት ያምናል፤ ዳሩ ግን አንዳንዱን እንደጠበቀው ሆኖ አያገኘውም። ‹‹ብዙ ሰው የታዋቂ ሰዎችን አስተያየት አይቶ ይገዛል›› የሚለው አብርሃም፣ እርሱም የታዋቂ ሰው አስተያየት አይቶ ገዝቷል። ስም መጥቀስ አልፈለገም።
አንድ የሚያደንቀሰው ደፋር ፀሐፊ በአንድ መጽሐፍ ላይ አስተያየት ሰጥቶ አየና መጽፉን ገዛ። መጽሐፉን ግን ጀምሮ አልጨረሰውም፤ በጀርባ የተሰጠው አስተያየት በውስጡ የለም። ‹‹እንዴት ይህን መጽሐፍ እንደዚያ ያጋንነዋል?›› ሲልም የጀርባ አስተያየት ሰጪውን እንደታዘበው ያስታውሳል። በመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት አስፈላጊነት ላይ ያምናል፤ ይስማማል።
በተለይም በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ «በጣም ያስፈልጋል» ይላል። አብርሃም ምክንያት የሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ የመጽሐፍ ዳሰሳም ሆነ ሂስ በብቃትና በብዛት ስለማይሰራ ነው። ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ የመጽሐፉ ጀርባ ላይ እንኳን በጥቂቱም ቢሆን መረጃ ማግኘት አለባቸው። ስለዚያ መጽሐፍ አንድ ባለሙያ መመስከር አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ አንባቢ የለም እየተባለ በሚታማበት አገር ውስጥ ለማንበብ የሚያነሳሱ አስተያየቶች መሰጠት አለባቸው። ይሄ ሲባል ግን መጽሐፉ ውስጥ የሌለውን እውነት እያጋነኑና ለመጽሐፉ ማሻሻጫ መሆን እንደሌለበት ያምናል። ምንም እንኳን የጀርባ አስተያየት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ቢሆንም በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን ድክመትም መጠቀስ እንዳለበት ያምናል። «በውጭው ዓለም ይህ የተለመደ ነው፤ በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ቢደረግ ባለመጽሐፉ ሊያኮርፍ ይችላል። የባለመጽሐፉ ማኩረፍ ብቻ ሳይሆን አንባቢውም አንብቤ የራሴን ፍርድ ልስጥ አይልም።
ስለዚህ ያለውን ህፀፅ ማስቀመጥም ትክክል ላይሆን ይችላል። ያ ቢቀር ግን ቢያንስ መጽሐፉ ውስጥ የሌለ ነገር ባይሞካሽ» በማለት አስተያየቱን ይቋጫል። ጋዜጠኛ ዮሐንስ ጀማነህ ሌላ አስተያየት ሰጭ ነው። በመጽሐፍ ጀርባ ላይ የሚቀመጥ የአንድ ደራሲ ምስክርነት ጓደኛን ለማስደሰት ወይም መጽሐፉን ለማሻሻጥ ላይሆን እንደሚችል ያምናል። አስተያየቱ የዚያ ሰው እምነትና አቋም ብቻ ሊሆን ይችላል።
‹‹እኛ ስናነበው ትክክል ያልመሰለን ነገር የጀርባ አስተያየት ለሰጠው ሰው ትክክል ቢሆንስ?›› ሲል ይጠይቃል። ‹‹ምንም እንኳን ለጓደኝነትና ለመወደድ ብሎ የሚጽፍ ሊኖር ቢችልም የራሱን እምነትና አቋም የሚጽፍም አለ። በመጽሐፉ ጀርባ ላይ የተሰጠ አስተያየት ባለመጽሐፉን የሚያስደስት ላይሆንም ይችላል›› ለዚህም ማሳመኛ አንድ ምሳሌ ያነሳል።
የዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› መጽሐፍ ላይ ሃያሲ አብደላ እዝራ አስተያየት ሰጥቷል። በአስተያየቱም ‹‹የአዳም ረታ በጎ ተፅዕኖ አለበት›› ይላል። ዓለማየሁ ገላጋይ ግን ይህን ሀሳብ አይቀበልም። የአዳም ረታ ተፅዕኖ አለብኝ ብሎ አያምንም። ስለዚህ አብደላ ዕዝራ የጻፈው ዓለማየሁ ገላጋይን ለማስደሰት ሳይሆን ራሱ ስለመሰለው ነው። የየሰዎች አተያይ ይለያያል፤ በተለይም ስነ ጽሑፍ ደግሞ እንደ ሳይንስ አንድ አይነት ስምምነት ያለው አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ የጀርባ አስተያየት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ እንጂ ሒስ የሚደረግበት እንዳልሆነም ይናገራል። ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ የሚነግረን ሀሳብ ተግባራዊ ቢሆን የጀርባ አስተያየትን ገላጭ ያደርግልን ነበር። እንደ መጽሐፉ ይዘት ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ ሰው አስተያየት ቢሰጥበት የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት ነው።
የእንዳለጌታ አስተያየት። ይሄ ማለት ለምሳሌ ስለምጣኔ ሀብት የተጻፈ መጽሀፍ ከሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፤ ስለህክምና የተጻፈ ከሆነም የህክምና ሰው፤ ለልቦለድም ይሁን ለየትኛውም መጽሐፍ በዘርፉ ያለ ሰው አስተያየት ቢሰጥበት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ጥሩ ይሆናል። የመጽሐፉን ህፀፅ መናገር የ‹‹ብለርብ›› ባህሪ እንዳልሆነ ነው እንዳለጌታ የሚናገረው። ‹‹ብለርብ››፣ ‹‹ሒስ››፣ እና ‹‹ግምገማ›› ብዙ ጊዜ ይምታታል፤ ነገር ግን የተለያዩ ናቸው። ‹‹ብለርብ›› ማለት አስተያየት ጻፍልኝ የተባለው ሰው መጽሀፉ ከመታተሙ በፊት ስለመጽሐፉ ያለው አስተያየት ነው የሚጽፈው። ይሄ ሲሆን የሚመረጠው ሰው ለመጽሐፉ ይዘት የቀረበ መሆን አለበት።
የመጽሐፉን ህፀፆች ለቅሞ በጀርባው መጻፍ ስህተት ነው። እዚያ ላይ የሚሰጠው ሒስ ሳይሆን መጽፉን በአጭሩ ማስተዋወቅ ነው። ህፀፆቹን ለማውጣት ከሆነ ሌላ የሒስ ጽሑፍ በጋዜጣ ወይም መጽሔት ወይም መድረክ ላይ መሥራት እንደሚቻል ይናገራል። ያም ሆኖ ግን የጀርባ አስተያየት ሲሰጥ መጋነን እንደሌለበት ነው ደራሲ እንዳለጌታ የሚያምነው። ‹‹ማጋነን የብለርብ ባህሪም አይደለም። በጓደኝነት ወይም መጽሐፉን ለማሻሻጥ ብቻ ተብሎ የሚሰጥ ከሆነ የማንንም ሳይሆን የአስተያየት ሰጪውን ክብር ነው የሚያወርድ። ይሄ እንግዲህ ሆን ብሎ ዋሽቶም ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም የሰውየው የመረዳት አቅምም ሊሆን ይችላል›› ስም መጥቀስ አልፈለገም እንጂ ደራሲ እንዳለጌታም አንድ ገጠመኝ አለው። አንድ የሚያከብረው ሰው በአንድ የግጥም መጽሐፍ ላይ አስተያየት ሰጠ፤ ሰውየው ገጣሚ ነው።
በጣም የሚገርም አድርጎ የገለጸውን መጽሐፍ በጣም ጓጉቶ ገዛው፤ ይሁን እንጅ መጽሐፉን እንደጠበቀው አላገኘውም። ‹‹ምነው ምን ሆነህ ነው ጋሼ እገሌ?›› ሲልም ጠየቀው። ሰውየው በሰጠው መልስ ግን ገጣሚዋን ያወዳደራት እንደ ግጥም ሳይሆን ከመሰሎቿ ጋር ነው። ልጅቱ ተዋናይ ናት፤ ያወዳደራት ከተዋናዮች ጋር ነበር። ይሄ ነገር አከራካሪም ሊሆን ይችላል። ጥበብ መለካት ያለበት እንደ ጥበብ ነው፤ የልጅቷ ግጥም በግጥምነቱ ይለካ እንጂ ከተናዋይ ወይም ከዘፋኝ ጋር እየተነጻጸረ መሆን የለበትም። ምናልባትም ያሳተመችው ግጥም ነው ብላ እንጂ ለተዋናይ ወይም ለዚህ ሙያ የተዘጋጀ አይደለም።
ስለዚህ አስተያየት ሰጭው በግጥምነቱ ብቻ መለካት ነበረበት። ምናልባትም አስተያየት ሰጪውን እንዳለጌታ ሲጠይቀው የሚናገረው ጠፍቶትም ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መፅሐፉ ውስጥ ያለ ህፀፅ በተዘዋዋሪም ሊነገር ይችላል። እንዳለጌታ ይህን ምሳሌ ያነሳል። ‹‹ይህንን መጽሐፍ ለቃላት ውበት ሳይጠነቀቅ ታሪካዊ እውነቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ለሚያነብ ሰው ብዙ የመረጃ ምንጮችን ማግኘት ይችላል…›› በሚል መንገድ ይገለጻል። ይሄ ማለት እንግዲህ መጽሐፉ የቃላት ውበት የለውም ማለት ነው።
በእርግጥ መጽሐፉ ሳይንሳዊ ወይም ፖለቲካዊ ከሆነ ለስነ ጽሑፍ ውበት አይገደድ ይሆናል። ቢሆንም ግን ስነ ጽሑፋዊ ውበት ለልቦለድ ብቻም መሆን የለበትም። ታሪክም፣ ፖለቲካም ሆነ ሳይንስ የቃላት ውበት ቢኖረው ለአንባቢም ጥሩ ነው። በመጽሃፍ ጀርባ ላይ ራሱ ደራሲውም መጻፍ ይችላል። የመጽሐፉን ይዘት የሚናገሩበት አጋጣሚም ብዙ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከመጽሐፉ ውስጥ ቀንጭበው በማውጣት ያስቀምጣሉ፤ ‹‹ከመጽሐፉ የተወሰደ›› ይሉታል። ይሄም እንደ ‹‹ብለርብ እንደሚቆጠር ነው›› እንዳለጌታ የሚገልጸው። ይህን የሚያደርጉት ያ የመረጡት ጽሑፍ መጽሐፉን ይገልጽልናል ብለው ስለሚያስቡ ነው፤ ወይም ደግሞ አስተያየት ጻፉልን ላለማለትና ባዶ እንዳይሆን ብለውም ሊሆን ይችላል። ጋዜጠኛ አብርሃም ገብሬ እና ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ አንድ የጋራ አስተያየት አላቸው።
በመጽሐፍ ጀርባ ላይ ማን አስተያየት ሰጠ? ማለት ብቻ ሳይሆን አሳታሚም እየታየ ነው። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የሚያሳትማቸው መጻሕፍት ከሆኑ የራሳቸው ባህሪ አላቸው። እርሱ ነው ያሳተመው ሲባል ሰዎችን የመሳብ አቅም አለው። ምናልባት እርሱ በሚያሳትማቸው መጻሕፍት የማይስማማ ካለም የመጽፉን ይዘት ከአሳታሚው አንጻር ተነስቶ ሊገመግም ይችላል።
ስለዚህ አሳታሚም የራሱ የሆነ ባህሪ አለው ማለት ነው። የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት እንደ ኢትዮጵያ የንባብ ባህል ደካማነት አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም የምናየው ነገር ነው። በሰው ጠቋሚነት የሚያነብ ወጣት ነው ያለን። እርግጥ ነው በጀርባ አስተያየት በማታለል አንባቢ መፍጠር አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ተገፋፍተው የጀመሩ አንባቢዎች በሂደት ወደ ጥልቅ አንባቢነት ይቀየራሉ ብሎ ማሰብ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አሁን አንባቢና ጸሐፊ የሆኑት በዚህ መንገድ ተገፍተው ወይም ተስበው የገቡም ይኖራሉ። ይሄ ሲባል ግን በመጽሐፉ ውስጥ የሌለ ነገር ተጋኖ መቅረብ የለበትም።
አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። በመጽሐፍ ጀርባ ላይ የተጋነነ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች እውነት አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ነው? አንባቢ ትውልድ ማለትስ ሰው ስላደነቀው የሚያደንቅ ነው? ብሎ መጠየቅና ለዚህም ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል። እንዲያውም ይሄ ነገር መጥፎነቱም ለጀማሪ አንባቢ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ምርጥ መጽሐፍ ማለት በመፅሀፉ ጀርባ ላይ እንደተገለፀው አይነት ብቻ ሊመስለው ይችላል።
ይችኛዋ ነገር ግን ትኩረት ቢደረግባት። ‹‹የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት ሲሰጥ ለጽሑፉ ይዘት የሚቀርብ ሰው ቢሆን!›› እርግጥ ነው ከፖለቲካና ልቦለድ ውጭ በተለያዩ ሳይንሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጻሕፍት እምብዛም የሉንም። ለእነዚያውም ቢሆን ግን የሚመለከተው ሰው አስተያየቱን ቢሰጥ የተሻለ ነው፤ አስተያየቱን የሚሰጠው ሰውም ትክክለኛ የገባውን እንጂ ለማሻሻጥ ተብሎ ባይፅፍ መልካም ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በዋለልኝ አየለ