
የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 4 ኪሎ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ አጥንቷል። ናታን ሥራ መሥራት የጀመረው ገና የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ነው። የተለያዩ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ (ቀመር) የማሰልጠን ሥራዎችን ይሠራ ነበር። በዚህም ከመመረቁ በፊት የራሱን የሥራ መስክ ዘርግቶ በመውጣት ከተመረቀ በኋላም የተለያዩ ሥራዎችን ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ይሠራል።
የኔታ ኮድ የተሰኘ ተቋምን በመመስረት ሕጻናት ልጆችን የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ሥልጠናን የሚሰጥ ሲሆን ናታን (ቢ ብሎኪንግ) የተሰኘ አፕሊኬሽን እንዲሁ በመፍጠር ልጆች ባሉበት ሆነው ይህንን ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ ችሏል። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አልጨረሰም ነበር። የዛሬው እንግዳችን ወጣት ናታን ዳምጠው ፤ የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች መሥራች ሲሆን ፤ በቅርቡ ደግሞ አሁን ካለንበት ጊዜ ጋር አብሮ የሚሄድ ሥራን በመሥራት ከራሱ አልፎ ለብዙዎች ተጨማሪ የሥራ እድል ፈጥሯል።
ናታን የመጀመሪያው የሆነውን ቢ-ብሎክ የተሰኘ ለሕጻናት የተሠራ አፕሊኬሽን ለመሥራት ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት ሕጻናትን ሊያስተምር የሚችል አፕሊኬሽን እንዲሠራለት የሚፈልግ አንድ ተቋም የሥራ ማስታወቂያ በጋዜጣ ላይ ይመለከታል። በወቅቱ ጋዜጣ የማንበብ ልምድ የነበረው ናታን የራሱን ሥራ ይዞ በመቅረብ ተቀባይነትን አግኝቷል። በዚህም ውድድሩን በማሸነፉ በሥራው ያገኘውን ክፍያ ተጠቅሞ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት ሥራውን ሊያስፋፋ ችሏል። ‹‹ በጊዜው የሰራሁት አፕሊኬሽን ሕጻናት በቀላሉ ሊማሩ የሚችሉበት ነበር። ማስታወቂያውን ያወጣው ኩባንያም የናታንን ሥራ በመውደዱ ወደ ሥራ ሲገባ በተጠቃሚዎች ዘንድም ጥሩ ተቀባይነት ነበረው። ›› ናታን የመጀመሪያ ዲግሪውን እንደጨረሰ ተማሪ በነበረበት ወቅት ይሠራ የነበረውን ሥራ ይበልጥ ማስፋፋቱን ቀጠለ።
የኮቪድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኖ የተለያዩ የሥራ እንግዶች በተጣለበት ወቅት ናታን በቤት ውስጥ ላይ ጊዜውን በማኅበራዊ ገጽ ላይ ማሳለፍ ጀመረ። የተለያዩ ማኅበራዊ ገጾችን በመጠቀም የተለያዩ አዝናኝ እና አስማሪ ጽሁፎችን በማጋራት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተወዳጅነትን ማግኘት ቻለ። በሚጽፋቸው ጽሁፎችም የሚያበረታቱትን ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። ‹‹ ብዙ ጊዜ የምጽፋቸውን ጽሁፎች የሚወዱ ሰዎች የባንክ አካውንቴን በመጠየቅ እንደግፍህ ይሉኝ ነበር። ›› ይህ አሠራር በሌሎች ሀገራት የተለመደ ሲሆን ሰዎች በማኅበራዊ ገጾች ላይ የሚመለከቷቸውን ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ፣ ትኩረታቸውን የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያደረጉ ጽሁፎችን ያጋራሉ፤ በርካታ ተከታዮችን እና ተወዳጅነትን ያገኛሉ። ያጋሯቸውን መረጃዎችም በተዘጋጀው የዲጂታል ሥርዓት አማካኝነት ጉርሻ ወይንም ክፍያን ያገኛሉ። ይህን ዲጂታል ጉርሻ ብለን ልንጠራው እንችላለን።
በሀገራችን መሰል ሙያ እና ችሎታ ያላቸው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም የሚጠቀማቸው ድህረ-ገጸ በሌላ ሀገር የተሠሩ እና የክፍያ ሥርዓታችን ከእነዚህ ድህረገጾች ጋር የተሳሰረ ባለመሆኑ ሰዎች እነዚህን ድኅረገጾች ተጠቅመው እውቅናን ያተርፉበታል፣ ካላቸው ሙያ ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር ትውውቅ ለመፍጠርና በሀገር ውስጥ ላሉ ተጨማሪ የሥራ እድሎች ይጠቀሙበታል። የማኅበራዊ ገጾች ትልቁ ዓላማቸው ሰፊውን ዓለም በቀላሉ ማስተሳሰር መቻል ሲሆን ጊዜው በተቀየረ ቁጥር ደግሞ እንደዚህ ያሉ ተጨማሪ የክፍያ መንገድ መሆን የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ይተዋወቁበታል።
ታዲያ ናታን ይህንን ሥርዓት በውጭው ዓለም ስለመኖሩ ቢያውቅም በአድናቂዎቹ ሀሳብ ሰጪነት ግን የሚወደውንና ትርፍ ሰዓቱን የሚያሳልፍበትን ችሎታውን ተጨማሪ ገቢ ለምን ወደ ገንዘብ አልቀይረውም የሚል ሀሳብ አዕምሮው ሹክ አለው። ይህንን ሲስተም መዘርጋት በእጁ ያለ ሙያ ነበር። ‹‹ሌሎች ሰዎች የተለያዩ ጽሁፎችን ሲጽፉ የሚከፍሉ ዌብሳይቶች አሉ ግን የሚጠይቁት የራሳቸው መመዘኛ ወይም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ጽሁፎችን ማስገባት ይጠይቃሉ። ›› ይላል።
ናታን ግን ጽሁፍን እንደ አንድ መዝናኛው አድርጎ የሚቆጥረው ሲሆን በፈለገበት ጊዜ የራሱን ጽሁፍ የሚያጋራ በመሆኑ፤ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያገኝበትን ሥርዓት እንዲዘረጋ ልዩ ሀሳብ ሆኖለታል። ይህ የዲጀታል ጉርሻ ሲስተም በሀገራችን ያልተለመደ ይሁን እንጂ በሌሎች ሀገራት በተለያዩ የበይነ መረብ ሥርዓቶች ሰዎች እንደ ምርጫቸው በይነመረብን ተጠቅመው በመረጧቸው ዘርፎች ላይ የራሳቸውን ሀሳብ በሚያስተላልፉበት፣ ሙያቸውን በሚያጋሩበት፣ ሳይንሳዊ እና ልቦለዳዊ ጽሁፎች እንዲሁም አዝናኝ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በሚያጋሩበት ጊዜ በአድናቆት መልክ ክፍያ የሚያገኙበት ሲስተም አለ። እነዚህን ዓለምአቀፍ ድህረገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ ይስሩ እንጂ እነዚህን ክፍያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ራሱን የቻለ ዓለም አቀፍ የክፍያ አካውንት ለሚከፍለውም ሰው ያስፈልጋል።
በሀገራችን የዲጂታል ሥርዓት አጠቃቀም አሁን ላይ በስፋት እየተዋወቀ የመጣ ሲሆን የክፍያ ሥርዓቶቻችንን በዲጂታል መልኩ የማስኬድ መልካም ጅማሮዎች ይታያሉ። ይህም የሰዎችን ሕይወት የሚያቀል እና አሠራርን ቀልጣፋ የሚያደርጉ ናቸው። እንደ ናታን ያሉ የኮምፒውተር ቀመር ላይ ልምድ ያላቸው እና በዚህ ውስጥ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችም ሆኑ ባለሙያዎች በዚህ ባለንበት የዲጂታል ዘመን ይበልጡኑ ተፈላጊ ናቸው። እንደ ናታን የበረቱ ወጣቶች ደግሞ ሙያቸው ላይ ፈጠራ በማከል እና ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም አዳዲስ ፈጠራዎችን ያስተዋውቃሉ።
ናታን ከእርሱ ልምድ በመነሳት በዲጂታል ጉርሻ ሰዎች ከመዝናናት ባለፈ ጊዜያቸውን በሚያሳልፉባቸው ማኅበራዊ ገጾች ላይ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ ፈጥሯል። ይህ የክፍያ ሲስተም ከለማ በኋላ ናታን ተጨማሪ ገቢ ሊያገኝ ችሏል። ሲስተሙ ብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘ ሲሆን ብዙዎች ጋር ደርሶ ልክ እንደ ናታን ያሉ የማኅበራዊ ገጽ ላይ ፈጠራዎቻቸውን የሚያጋሩ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ግን ተጨማሪ ገንዘብ እና ኢንቨስት የሚያደርጉ ተቋማት ያስፈልጉ ነበር። ታዲያ ናታን ገንዘብን ከማፍሰስ እና የሥራ ባልደረባነትን ከመፍጠር ባሻገር ዘመኑን በዋጀ መልኩ እነዚህን የክፍያ ሥርዓት ለተለያዩ ተቋማት ከሚዘረጋው አሪፍ ፔይ የተሰኘ ተቋም ጋር አብሮ ለመሥራት ቻለ።
‹‹ አሪፍ ፔይ የኦንላይን የክፍያ ሲስተሞችን ለተቋማት የሚዘረጉ ሲሆን ከሁሉም የሀገራችን ባንኮች እንዲሁም የውጭ ሀገር ማስተር ካርዶችን በመጠቀም ክፍያ መፈጸም የሚያስችል ነው። ›› ሲል የክፍያ ሥርዓቱን ያብራራል። ጃሚ የተሰኘው ይህ ሲስተም ለስድስት ወር ያክል ጊዜ ሙከራ የተደረገበት ሲሆን ይፋ ከተደረገ በኋላም እስካሁን ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ማኅበራዊ ገጽን በመጠቀም ችሎታቸውን የሚያሳዩ ሰዎች ይህንን ሲስተም እየተጠቀሙት ይገኛሉ።
ይህም ማንኛውንም ማኅበራዊ ገጽ ላይ የተለያዩ ርዕሶችን በመያዝ መረጃዎችን የሚያጋሩ ሰዎች ይህንን አካውንት በመክፈት ከሚጠቀሟቸው ማኅበራዊ ገጾች ጋር በማጣመር መሥራት እና ይበልጥ ጊዜያቸውን ወደ ገንዘብ መቀየር እንዲችሉ ያደርጋል። ናታን ከእነዚህ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ በፈጠረው ማሰልጠኛ እና አፕሊኬሽን ድህረገጽ አማካኝነት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ60ሺህ በላይ ተማሪዎች ሊማሩ ችለዋል።
ናታን ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት ድህረገጾችን የማልማት ሥራ በጊዜያዊነት ወስዶ የሚሠራ ሲሆን በአብዛኛው እውቅና ያለው እና በርካታ ወጣቶችን የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችን እና መድረኮችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር አብሮ የሚሠራው ‹‹አዋቂ›› ድህረ-ገጽ ከመፍጠር የማኅበራዊ ገጾችን እስከማስተዳደር ሥራዎችን ይሠራል። እነዚህ ሥራዎቹ ለሌሎች ተቋማት ለሚሠራቸው የድህረገጽ ማልማት ሥራዎች እንደ ምሳሌ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ መሆናቸውንም ጠቅሷል።
በርካታ ወጣቶች በተለያየ ዘርፍ ላይ ስኬታማ መሆን በራሳቸውን መንገድ ያለሙት ቦታ ላይ መድረስ ሕልማቸው ቢሆንም ብዙዎች ግን መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን እነዚህን መሰናክሎች አልፈው ያሰቡ የሚደርሱ ጥቂቶች ናቸው። ‹‹ የእኔ ጥንካሬ ብዬ ማስበው በቢዝነስ ሥራ ወይም በሌላ መስክ ለሚገጥመን ፈተና አለመደናገጥ፤ ቶሎ ተስፋ አለመቁረጥ እና ከሁኔታዎች ጋር ራሳችንን አመለካከታችንን እየቀያየርን መቀጠል አንዱ መንገድ ይመስለኛል። ›› ሲል ምክሩን ይለግሳል።
ጃሚ የማኅበራዊ ገጽ ርዕስ ፈጣሪዎችን የዲጂታል ጉርሻ እንዲያገኙ እና ባላቸው ተከታይ እና ሥራቸውን በወደዱላቸው ሰዎች አማካኝነት ዲጂታል ጉርሻ እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን ፤ ናታን በአሁን ሰዓት በስሩ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች 15 ያክል ሰራተኞች አሉት። ይህንን ሲስተም ይበልጥ ማስፋፋት የወደፊት እቅዱ ውስጥ አንዱ ነው።
‹‹ የዲጂታል ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥም በጣም እየተስፋፋ ሲሆን ፤ በአፍሪካም ይህንን መሰል ችግሮች ያሉ ሲሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ግን ልምዱ ስላላቸው ተቀባይነትና ተወደዳሪነት ይኖረዋል። ስለዚህ የጃሚ ድህረ-ገጽን ከኢትዮጵያ ውጪ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር በማስተዋወቅ እንዲሠራ ማድረግ እፈልጋለሁ። ›› ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል።
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም