ጉዳዮቻችን ሁሉ ታላቅ ከሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ በታች ናቸው። በየጊዜው እዚህና እዚያ እያነሳን የምንጫቃጨቅባቸው፣ የማያግባቡን የሚመስሉ ሀሳቦችና አመለካከቶች ሁሉ ከዚህች አገር እጅግ በጣም ያነሱ ናቸው።
ምክንያቱም ሁሉም ሀሳቦች ያሉት እስዋው ውስጥ ነው። ለስዋ ግዝፈት ብለን አሳንሰን ብናያቸው ያግባቡናል፤ ለአገር ጥንካሬና ሕልውና ስንል ተቀራርበን ብናወራባቸው እጅጉን ይቀሉናል።
ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ናት። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት። መቶ ሚሊዮኑ አንድ አይነት አቋም ሊያንፀባርቅ አይችልም፣ መቶ ሚሊዮኑም አንድ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊኖረው ከቶም አይቻለውም። መቶ ሚሊዮኑም ግን በአንድነት የሚኖርበት አንድ አገር አለው። የቁጥሩ ያህል እንኳን የተለያየ አመለካከትና እምነት ቢኖረውም አገር በሚለው እሳቤ ግን መፅናት ግድ ይለናል። ኢትዮጵያ ለእኔም ለአንተም ለእሷም አገር ናት።
በደስታችን ወቅት የቦረቅንባት አገር፤ በሀዘናችንም ጊዜ ፀንታ እንድትኖር ማድረግ ግድ ይላል። ስናኮርፍም ስንደሰትም እስዋ አገራችን ናት። በቅሬታችን ወቅት ትተናት በደስታችን ጊዜ አለሁ የምንላት እርስታችን አይደለችም። ሲከፋንም ሆነ ሲደላን አለን ብለን ለስዋ የምንቆም ልጆችዋ ነን። በልዩነታችን ውስጥም ቢሆን ስለስዋ ብለን በመቻቻል የምናድርባት አንዲትዋ የጋራ ቤታችን ናት። ኢትዮጵያ ጽኑ የሆነች አንዲት አገር በመሆንዋ ላይ ፈፅሞ የአቋም ለውጥ ሊኖረን አይገባም።
ወንድሜ ስንደሰት አገራችን እንዳልነው ሁሉ፤ በመከፋታችንም ውስጥ አገሬ ማለት ግድ ይለናል። ዳንኪራ በነፃነት እንደምንመታው ሁሉ በሀዘናችን ወግ ያለው ማልቀስ የምናለቅስበት አገር ያስፈልገናል። መከፋታችን የምንገልፅባት አገር ሊኖረንም ግድ ይላል።
ለአገር ጥቅም ፅኑ ሆኖ መቆም ሁሌም በሁሉም አይነት ስሜት ውስጥ ሆነን መሆን አለበት። የፖለቲካ አመለካከታችን ስለተለያየ እና የፖለቲከኞች ተግባር ስላልጣመን አገር የምንጠላ፤ በአንፃሩ ደግሞ ስለተመቸን ኢትዮጵያዬ የምንል ዜጎች መሆን እንዴት ይቻለናል? በመከፋትም በመደሰትም ወቅት አገር አገር ናት።
መልካም አይደለም ብለን የምናስበውን ውሳኔና ተግባር በሰከነ መልኩ እኛ ጋር ያለውና የተሻለ ነው የምንለው መፍትሄ አቅርበን መፍታት እንጂ የራስን ፅንፍ ይዞ የሌላን መገፍተር ተገቢነት የለውም።
መስጠት እንጂ የመቀበል ልምዱ የለንምና የእኔን እንካ ያንተን እንዳታመጣ የሚለው ስሌት ጋር ተጋብተናል። ይህ ግን ለአገር የሚበጅ አይደለም። የእኔ ሀሳብ መልካም ነው ያኛው ግን የሚያሻግር አይደለም ብሎ ማሰብ ልክ አይደለም። በራሴ መንገድ ልሂድ ማለት ፈፅሞ ሊያሰኬድ አይችልም። የተሻለው አቅርቦ መሞገት፤ ጥሩ የተባለውን ጥሩ ባልተባለው ለመተካት መነጋገር ፣ መወያየት፤ ስሜትን ገታ አድርጎ መመካከር ይጠይቃል።
በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነው የሚዘልቁባት፤ በመተሳሰብ እና መቻቻል የሚያድሩባት አገር ከሁሉ ጉዳዮች ከፍ ያለች ናት። ጉዳዮቻችን ተቀምጠን እንድናወራ አለመግባባታችን ተነጋግረን መቅረፍ እንድንችል ቀድመን አገር ያስፈልገናል። ስለ አገር ብለን ሁሌም አንድ ሆኖ መቆም ግድ ይለናል። የፀናች እና በሌላው የማትደፈር አገር የሚገነባው ደግሞ አንድ ሆኖ በመቆም ነው። ኢትዮጵያ የበርካታ ባህልና ማንነት መድረክ ናት።
ለዘመናት ሕዝቦችዋ አንድ ሆነው ቆመው ሉዓላዊነትዋ አስከብረው ዘልቀዋል። ዛሬ ላይ አዲስ የተፈጠረ የአመለካከት ልዩነት አልያም ደግሞ የእምነት መለያየት የለም። ባይሆን እምነትና አመለካከታችን የምንተረጉምበትና በተሳሳተ መንገድ የምንተገብርበት ሁኔታ ነው፤ የንትርካችን ሰበቡ።
ያለመግባባታችን መነሻው። ሰፊ አገር ላይ የሰፋ ሃሳብ ይዞ ቀርቦ መሞገት የተሳሳተው ማረም እንጂ የሚገባው ጉዳዮችን አጣቦ ይዞ መፍቻ መንገዶቹን መዝጋት አይገባም። ያለችን አንዲት አገር ናትና በእስዋ ጥቅምና ህልውና ፈፅሞ ልንደራደር አንችልም። ጉዳዮቻችን ከእስዋ ማነሳቸው ተረድተን ጉዳዮቻችን ሁሉ ከእስዋ ጥንካሬና መፅናት ጋር ማያያዝ ይገባል። ሁላችንም በጋራ አቅፋ የያዘች የጋራ ቤት ናት።
እንደኔ ለምን አላሰብክም አያሻግርም፤ ለምን እኔ እንደፈለኩ አትሆንም የትም አያደርስም። ብዙ ነንና አንድ አይነት አመለካከት ልንላበስና ተመሳሳይ አቋም ልናፀባርቅ አንችልም። በርካታ ነንና የበረከቱ ልዩነቶች ልናፀባርቅ እንችላለን። በፖለቲካ አቋም አልያም በእምነት ልንለያይና እንችላለን። እንደ ብዝሀነታችን አመለካከታችን ሊለያይ፤ አቋማችን ለየቅል፤ ሀሳባችን የማይጣጣም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንዲት አገር ውስጥ የምንገኝ አንድነት የምንጋራ ዜጎች ነን።
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአቋም ልዩነት ሊኖረን ልንቆጣ፣ ልናዝን፣ አልያም ደግሞ እጅጉን አምርረን ልንቃወም እንችላለን። ነገር ግን አገር ልንጠላ ወይም ለኢትዮጵያ አገራችን ያለንን ስሜት ሊለወጥ ፈፅሞ አይገባንም። አገር ስናኮርፍ የምንተዋት፤ ስንታረቅና በሀሳብ ስንግባባ አለሁልሽ ብለን የምንቆምላት አይደለችም። ስነስቅ ኢትዮጵያ እንዳልነው ሁሉ በመከፋታችን ውስጥ ከስሜታችን ከፍ ያለችው ታላቅዋን አገር አገሬ ማለት ይገባል።
መጣረሻ አጀንዳ ፈብርከው ሰጥተውን አልያም እኛ እየፈጠርን ለአገራችን ሰላም የማይበጅ ለሕዝባችን አንድነት እንቅፋት የሚፈጥር አመለካከትና ተግባር ውስጥ በተደጋጋሚ እንወድቃለን። ነገር ግን በመስከንና አገሬ በማለት እስዋን በማሰብ ከስሜታችን በመስከን ነገሮችን በስክነት መፈተሽ ደጋግሞም ማሰብ ይበጃል። በፖለቲካ ልዩነት አልያም ደግሞ በእምነት መለያየት ምክንያት ልንኳረፍ እንችላለን።
ነገር ግን በመኮራረፋችን የማንተዋት የጋራ አገር አለችን። ልዩነታችን አጥበን አልያም ደግሞ ተቻችለን የምንዘልቅባት አንድ ሆነን የምናድርባት ጎጆ አለችን። ሁሌም ልዩነት ይፈጠራል፤ ተፈጥሯዊም ነው።
ማሰብ ያለብን ልዩነቶች በምን መልክ ማቻቻል ወይም ማቀራረብና አብሮ ማስኬድ ይቻላል የሚለው ላይ ነው። በእርግጥ ይህ ልዩነትን አጥቦ መነቃቀፎችን ቀንሶ ሰላማዊ የሆነ ውይይት በማድረግ አንድ መሆን ሳይሆን አንድ አድርጎ የሚያኖር መቻቻል መላበስ ይቻላል።
ተችሎም ከ3 ሺ ዓመታት በላይ እዝች ምድር ላይ በስምምነት በጋራ እና በፍቅር ተኖሯል። ብዝሃነትን ማክበር እንደኛ ብዝሃነት በተላበሰ ማህበረሰብ ውስጥ መርህ ሊሆን ይገባል። በእርግጥም አንድ አይነት መሆን ይከብዳል። አንድ አይነት መሆንም አይቻልም። አንድ መሆን ግን ይቻላል።
የየራሳችን የፖለቲካ አቋምና እምነት ይዘን አንድ ሆኖ መኖር ይቻላል። የየግላችን እምነት ይዘንና የሌላውን አክብረን አንድ ሆኖ መኖር፤ አንድ ሆኖ እየኖሩ አንድ አይነት ሳይሆኑ መዝለቅ ይቻላል። ምክንያቱም አንድ መሆንና አንድ አይነት መሆን ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው።
እንጨት ሚስማርና ጭቃ ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው። ሁሉም ግን አንድ ላይ ሆነው ጥሩ የሆነ ቤት ሆነው ይቆማሉ። በቀላሉ የማይፈስ ጠንካራና ጥሩ ቁመና ያለው ጎጆ ሆነው በማበራቸው ይቆማሉ።
አንድ ሆነው አንድ ጠንካራ ነገር ይፈጥራሉ። አንድ አይነት ግን አይደሉም። እኛም ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ባህል ቋንቋ፣ አመለካከትና እምነት ያለን ሕዝቦች ነን። ነገር ግን አንድ ሆነን አገራችንን ለዘመናት ከጠላት ጠብቀናል።
በልዩነታችን ሳንፈተን አንድነታችን አፅንተን በፍቅር በመተሳሰብና በመቻቻል ዛሬ ላይ ደርሰናል። አንድ አይነት ሳንሆን አንድ ሆነን ከሶስት ሺህ አመታት በላይ ተሻግረናል። ከእኛ በላይ የአንድነት ጥቅም ለዓለም ያሳየ የለም።
ዓድዋ ላይ እውነትን ይዘን አንድ ሆነን ቆማን በዓለም ታሪክ ደጋግሞ የሚዘከር ገድል ፈፅመናል። በቅርቡ እንደ አገር የተጋረጠብን ታላቅ ፈተና አንድ ሆነን ቆመን ፊት ለፊት ገጥመን ድል ተቀዳጅተንበታል፤ እየተቀዳጀንበትም ነው።
በዚህ ሁሉ አንድነት ውስጥ የምንለያይባቸው ዘርፈ ብዙ አመለካከቶች፣ እምነትና አቋሞች ነበሩን አሉንም። ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ አንድነታችንን አልፈተኑንም። ምክንያቱም አገር ከሚለያዩን ጉዳዮች በፊት መኖር ስላለባት አንድ ሆነን ቆመን አሳይተናታል።
አንድ ሆነን ቆመን አንድ አድርጋ ያኖረችን አገራችን እንድትፀና መስራት ይገባናል። አለያይቶ በተለያየ አቋም ላይ የሚያቆመን ሀሳባችን በውይይት መልክ እንዲያቀራርቡን መስራት እንጂ አንዳችን በሌላቸውን ማኩረፍና መኮራረፍ የመፍትሄ ሀሳቦች ያርቅብን ይሆናል እንጂ ፈፅሞ ወደ መፍትሄ አያቃርበንም።
ከጉዳዮቻችን ሁሉ የምትልቀዋ አገራችን ጉዳዮቻችን በእስዋ መነፅር እንመልከታቸው። ያኔ በእስዋ ግዝፈት ምክንያት የምንጣረስባቸው ሁሉ ያንሱብናል። ወገን ኩርፊያ ሆነ ድጋፋችን ኢትዮጵያን ብቻ ብለን ከሆነ ዙሪያችን ለዛ ያለ ይሆናል።
ምክንያቱም ማኩረፋችን የእስዋ ክፉ ነገር ማራቅ ፈልገን ነውና። ድጋፋችንም እስዋን አስበን ከሆነ ድጋፋችን የተቀደሰ ነው።
ጋን በጠጠር ይደገፋልና የእስዋ ቀና ማለት የእያንዳንዳችን ተናጥሏዊ ጥረት ብሎም ያበረ አንድነት ወሳኝ ነው። እጅግ በጣም የበዛን ቁጥራችን ከመቶ አስር ሚሊዮን የተሻገርን አይነት ብዙ እምነት የተሰበጣጠረ ባህልና ወግ ያለን ነን። አንድ አይነት አስተሳሰብ ይኑርህ ወደ አንድ አይነት ቀለምና ቋንቋ ተለወጥ ሊባል አይችልምና የምንግባባቸው መንገዶች ማስፋት የሚያቃርቡን ስልቶች መንደፍ ለዚህ ወሳኙ ተግባራችን ነው። ዛሬ እንደ አገር ጠንክረን መቆማችን የማይፈልግ በርክቷል አፍሪካ ውስጥ ያለንን ተሰሚነት የማይወድ ተበራክቷል።
እንደ ሕዝብ አንድ ሆነን መቆማችን የሚጎረብጠው በየቦታው አለ። ታላቅ የመሆን ህልማችን የማይጥመው እንደ አገር አንድ ሆነን መቆማችን የማይፈልገው ሁሉ ይበልጥ አንድ ሆነን ተስፋ ልናስቆርጠው ይገባል።
እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ የምንሰማውና የምናየው ሁሉ የሚያስደስትን ነገር ብቻ ሊሆን አይችልም። አንዳንዴ ቅሬታ ሊፈጥርብን የሚችል አገራዊ ጉዳይ ሊኖር ይችላል።
ቅሬታችን ስናንፀባርቅ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ሊሆን አይገባውም። የመደሰታችን ያህል ያስከፋን ስሜት ከአገር አይበልጥምና ሰክነን መመርመር ስለስዋ ብለን መከፋታችንን መቻል እስዋንም የሚያፀናትና የሚያጠነክራት መፍትሄ ማቅረብ ይኖርብናል።
የየግል የፖለቲካ አመለካከት አቋምና እምነት አለን። አገር ማለት ግን ከምናንፀባርቀው ስሜት ባሻገር ሌላ ሀሳብና አመለካከት በጋራ የሚኖርባት የብዙኋን መድረክ ናት። ስለዚህም አንድ አይነት ሳይሆን አንድ ሆነን አንዲት አገራችንን እናፅና። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014