ከበርካታ ወራት በፊት “የአገሬ አገሯ የት ነው?” በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል። ጽሑፉ ለበርካቶች የውይይት በር የከፈተና ብዙ ሚዲያዎችም እንደተቀባበሉት ትዝ ይለኛል።
በርግጥም “አገሬ ራሷ ባለ አገር ነች ወይ?” በሚለው ሞጋች ሃሳቤ እኔው ራሴ የቆዘምኩት በወቅቱ እጅግ በርካታ ፈታኝ የሆኑ አገራዊ ክስተቶች በከፋ መልኩ ግራ ባጋቡን ሰዓት ላይ ነበር። “አገሬን አገሬን የምትል ወፍ አለች፤ እኔን እኔን መስላ ታሳዝነኛለች” በሚል የራሮት ግጥምም የጽሑፌን ሃሳብ መጠቅለሌን አልዘነጋሁትም።
የዓመቱ ዐውደ ዕለታት የተፈጥሮን ዑደት ሳያቋርጡ በጉዞ ላይ ይሁኑ እንጂ ዛሬም ቢሆን እስትንፋስ እየዘራንባት በሰውኛ ዘይቤ ይህቺን መከረኛ አገራችንን “አገርሽ የት ነው?” ብለን ብንጠይቃት በርግጠኝነት “በልብህ/በልብሽ ውስጥ!” ብላ ለመመለስ ድፍረት ኖሯት ፈጣን መልስ ትሰጣለች የሚል ግምት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።
አገሬ ብቻም ሳትሆን እኛ ዜጎች ተብዬዎችም ግራ አጋቢ የሆኑ ብዙ ጉዳዮች ዕለት በዕለት እያጋጠሙን ስለሚውሉ በስሜት ለመረጋጋትና ለመስከን እየተቸገርን ነው። የጦርነት፣ የመፈናቀልና የውድመት ዜናዎች ሰላማችንን እየገፈፉ ቆዛሚ ካደረጉን ሰንባብቷል። የውስጥ ባንዳ ሰልፈኞች፣ የውጭ ባዕዳን መንግሥታት፣ ተቋማትና ሚዲያዎች የግፈኞች ወገንተኛ በመሆን የጎን ውጋት ሆነውብን የሰላም እንቅልፋችንን ነጥቀውናል።
በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ መርዶ መስማትና ቀብርሲያስፈጽሙመዋል የጀማው የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲሆን የፈረዱብን “ጨካኝነት” የማይገልጻቸው አሸባሪ ተብዬ ጉዶች ናቸው። የንጹሐንን ደም “ደመ ከልብ” ያደረጉት እነዚህ የግፍ ከረጢቶች ፍርዳቸው ምድራዊ ብቻም ሳይሆን የፀባዖት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ጭምር ባለፉት ጽሑፎቼ አጠንክሬ አስምሬበታለሁ።
የሕወሓትና የኦነግ ሸኔን መሰል የከፋና የከረፋ ጭካኔና ግፍ “ሰይጣን ራሱ ሲተገብረው የሚደሰት አይመስለንም። ” ንጹሐን ዜጎቻችን ዛሬም በአረር ጢስ እየታፈኑ በማስነጠስ ላይ ናቸው። የመከራ ጉንፋን እየሳሉ ነው ማለት ይቀላል። በአሸባሪዎቹ የተደፈሩት ልጆቻችን፣ እህቶቻችንና እናቶቻችን የቅስማቸውና የሥነ ልቦና ስብራታቸው ተጭኗቸው የሰው ዐይን ላለማየት በስቅቅ ተኮርኩደውና ቤታቸውን በራሳቸው ላይ ዘግተው የመከራ ወስከንባይ እንደተሸከሙ ናቸው።
የተዘረፉትና በእሳት የጋዩት የግለሰቦችና የመንግሥት ተቋማት ንብረቶች የመጠናቸውና የዓይነታቸው የገንዘብ ስሌት ሙሉ ለሙሉ ሪፖርቱ በወግ ተጠናቅሮና ተሰንዶ ገና ለሕዝብ ይፋ አልሆንም። እስካሁን እየደረሰን ያለው ዜና እዚያና እዚህ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ወድሟል እየተባለ ነው።
ከቁሳቁሱ ጎን ለጎን እሳት የበላቸውና ውድመት ያነከታቸው የየተቋማቱ ሰነዶች፣ የባለጉዳዮች ፋይሎችና የተማሪዎች የትምህርት መረጃዎች ለጊዜው ዋጋቸው ቢተመንምን ያህልብር እንደሚያወጣ በገማቾችየሚወሰን ሳይሆን በፈጣሪ ሚዛን የሚለካ ነው።
የተጠቂዎቹ፣ የሟቾቹና የተጎጂዎቹ እምባ በምን መስፈሪያ ሊለካ እንደሚችል ተረጋግተን እናስብ ብንል ተግባሩ ሳይሆን ሃሳቡ ራሱ ኅሊናችንን አቁስሎ በእምባ ላይ ሌላ እምባ እንድናክል ግድ ይለናል። ከተሞችንና ገጠሮችን የሞሉት ፍርስራሾችም ገና ተነስተውና ጸድተው አልተጠናቀቁም።
ሙሉ ለሙሉ ተጠርገውና ተስተካክለው መቼና እንዴት የአመድ ክምሮቹ እንደሚጸዱ ጊዜ ወስኖ ለማቀድ አዳጋች ብቻም ሳይሆን አተገባበሩን ራሱን ማሰቡ እንደ መርግ ይከብዳል። በእንዲህ ዓይነቱ ዐውድ ውስጥ ካለነው ዜጎች አንደበት አፈትልከው እየወጡ ካሉት ተደጋጋሚ የምሬት ቃላት መካከል “ለምን?” የሚለው በአጋኖ የታጀበ ጥያቄ ሰሞኑን ሪከርድ የሰበረ የሚመስለውም በዚሁ ምክንያት ነው።
ከሕጻናት እስከ ታዳጊዎች፣ ከወጣቶች እስከ አዛውንቶች፣ ከመንግሥት ሹመኞች እስከ የሩቅ ተመልካቾች “ለምን?” ብለው ሳይጠይቁ ፀሐይ ወጥታ አትጠልቅም። ለምን እንዲህ ዓይነት ግፍ የግዜያችን መታወቂያ ሆነ? ለምን ይሄን ሁሉ ግፍ የሚፈጽሙ ጨካኞችን ፈጣሪ ታገሳቸው? ለምን መንግሥት እንዲህና እንዲያ ለማድረግ ተሳነው? ለምንስ አቅሙ የተልፈሰፈሰ መሰለ? ለምን እንደዚያ ሊያደርግ ተዳፈረ? ለምን ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ፊቱን አዙሮ ጠላት ሆነባት? ለምን የፍትሕ ዓይኗ በጥቁር እራፊ ታብቶ ሕጉ ጉልበት ሊያጣ ቻለ? ሀገርን ክፉ “በላ” በገጠማት ወቅት ለምን ወገን በወገን ላይ ይጨክናል? ጊዜ ያነሳቸውና “በቅል” የሚመሰሉ አንዳንድ የመንግሥት ሹመኞችና ጥቂት ነጋዴዎች ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው ለምን መከራ እንደ ድንጋይ ያጠጠራቸውን ዜጎች ሊሰባብሩ ጨከኑ? (ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል የሚለውን ሀገራዊ ብሂል ያስታውሷል። ) እነኚህን መሰል ጨፍጋጋ ርዕሰ ነገሮች እየፈለቀቅን፣ እየዳመጥንና እያባዘትን ከአንድ ነገር አዋቂ ብልህ የቅርብ ወዳጄ ጋር ስንወያይ እንዲህ ነበር ያለኝ። “የሰሞኑ የጉንፋን ወረርሽኝና ‹ለምን?› የሚሉት የእንቆቅልሾቻችን “ድፍን ዕንቁላሎች” አንደኛው በሣልና በትኩሳት፣ ሌላኛው በማሕበራዊና በስሜት ቀውስ እያንገላቱ ለከፋ ህመም ዳርገውናል።
ለጉንፋናችን ትኩስ ትኩሱን ለእንቆቅልሻችን ግራ መጋባት ደግሞ የስሜት መቀዛቀዙን ካልመረጥን በስተቀር ጉንፋኑም ለአልጋ፣ ‹ለምን› እያልን የምንሟገትባቸው እንቆቅልሾቻችንም ወደ ሀገራዊ መከፋፋት ደረጃ እንዳያደርሱን ቆም ብለን ልንሰክን ይገባል።
” ነበር ያለኝ። አመሰግናለሁ ወዳጄ ሆይ! ለምን? ለምን? ለምን? … ኢትዮጵያ በራሷ አንደበት፤ ሕዝቡም በተባበረ ድምፁ “ለምን?” እያለ የሚጠይቃቸው እንቆቅልሾቻችን መልካቸውም ሆነ ዓይነታቸው ዝንጉርጉር ስለሆነና ተዘርዝሮ ስለማያልቅ እዚሁ ላይ መግታቱ የተሻለ ይሆናል። ይልቅዬ የሚያዋጣው በዚህ መሰሉ ወቅት ሀገሬ ጥበብን፤ ዜጎቿም ማስተዋልን ተጎናጽፈን እየተመካከርን ይህንን ክፉ ቀን በትዕግስት ለማለፍ ሞሞከሩ ብልህነት ነው።
ጥቅሉን ሃሳብ ጥቂት እናፍታታው። ሀገራችንንና ሕዝባችንን እየተገዳደሩ ያሉት መልከ ብዙ ተግዳሮቶች ካሁን ቀደም ካየናቸው ክፉ ድርጊቶች ይበልጥ ከፍተውና ገፍተው መከራችንን እንዳያወሳስቡ አማኞች በእምነታቸው፣ ጠቢባን በአስተውሎታቸው፣ አዋቂዎች በብልሃታቸው፣ አዛውንቶች በምክራቸው፣ ሹመኞች በትዕግስታቸው፣ ወጣቶች በስክነታቸው፣ ፖለቲከኞች በእርጋታቸው፣ አክቲቪስቶች በማስተዋላቸው ሀገርን ከክፉ መከራ ሊታደጉ ይገባል።
ወደ አዘቅት ተንደርድረን እንዳናሽቆለቁልም ጽኑ ድጋፍ ሆነው ሊያግዙን ይገባል።
አገራዊ ምክክር እንደ መፍትሔ፤
“ለምን?” በሚሉ ቃለ አጋኖዎች የሚጠየቁ በርካታ ጥየቄዎች የሕዝቡ ዕለታዊ የእንጉርጉሮ ቅኝት ሆነው የስሜት ጭጋግ በተጫጫነን ወቅት “ሁሉን አቀፍ የምክክር ኮሚሽን” እንደሚቋቋም “ከኢትዮጵያ አፍ” ሰምተናል።
ምክክሩ በማንና በማን መካከል? የሚል ተጨማሪ “ለምን” እንድናመነዥግም ሰሞኑን አጀንዳ ቀርቦልናል።
ብዙዎች የዚህን ኮሚሽን መቋቋም እንደ በጎና እንደ መልካም መፍትሔ ሲያደንቁት አንዳንዶች ግን የኮሚሽኑ መቋቋምም ሆነ አጀንዳው ጊዜው አይደለም በማለት ሙግቱ ተጧጡፏል። ድጋፍና ተቃውሞውም በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከዓለም ዳር እስከ ዳር እያስተጋባ “ኢትዮጵያን ሻምፒዎን” በማድረግና ባለማድረግ እየተፎካከሩ መጓተቱ በርትቷል።
ይህ ጸሐፊ ዘርዘር ያሉ ጥያቄዎችን በግሉ ለመሰንዘር የአንባቢያንን በጎ ፈቃድ ይጠይቃል። ለመሆኑ በምክክር ዙሪያ እንደ አዲስ ፈጠራ ነገሮችን አክርረን ለምን እንኪያ ሰላንትያውን እናጋግላለን? መመካከር ባህላችን አይደለም ወይ? ከመመካከር ውጭስ ችግሮች በሌላ በምን ዘዴ ሊፈቱ ይችላሉ? ግፈኞች ላፈሰሱት የንጹሐን ደም በፍትሕ መዳኘታቸው አግባብ ነው።
በግፈኞች የወደሙ ንብረቶችን መተካትና መልሶ ማቋቋምም የመንግሥትና የሕዝብ ጣምራ ግዴታ መሆኑ ይታወቃል፤ ውጤቱም በሚያኮራ ሕዝባዊ ርብርብ እየተተገበረ እንደሚገኝ እያስተዋልን ስለሆነ ክብርና ሞገስ ለተቀዳንበት ባህልና ማኅበረሰብ ይሁን።
ከዚህ በተረፈ ግን በአገር ጉዳይ ተቀራርበን እንወያይ ማለቱ ምን ክፋት ይኖረዋል? እርግጥ ነው ምክክሩ የሚደረገው በምን አጀንዳ፣ እነማን በሚካፈሉበትና በሚመሩት ሸንጎና በምን ሁኔታ ነው? ብሎ መጠየቅ የማንኛውም ዜጋ መብት ነው።
ከዚህ በተረፈ ግን መንግሥት ምክክሩን የሚያደርግ ከሆነ “እኛን አያድርገን፤ እሱንም አያድርገን!” እያሉ መብከንከኑ ምን ዋጋና እርባና ይኖረዋል። ለርዕስነት የተመረጠው አገራዊ ብሂል የሚያስተምረን እውነታም ይህንኑ ነው። አንድ ቤት ማገር ከሌለው አይጸናም አይሰነብትምም።
በጡብና በድንጋይ ቢሰራ እንኳን የሕንጻው ግንባታ ጥበብ መቀነቻ እንዲኖረው የግድያዛል። አገርምእንደዚሁ ያለምክክር አገር ለመሰኘት “አጥንት” አይኖራትም።
እንኳን አገር አንድቤተሰብየጋራ ኑሮውን የሚመራው በምክክር እንጂ በአባት ወይንም በእናት በጎ ፈቃድና ውሳኔ ብቻ አይደለም።
የልጆችን ፍላጎት ለማሟላትና “የቱ ከየቱ ይቅደም” የሚሉ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የጋራ ምክክር የግድ ይላል።
“መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ ዓመት አይነግሥ!” የሚለው አባባልም ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። የፖለቲካ፣ የፖለቲከኞችንና የማኅበራዊ አንቂዎችን ንግግር ብቻ እየሰሙ ውሎ ማደር እንደሚሰለች ይታወቃል።
ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ የሆኑ ዜጎቿ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሃይማኖት ቤተሰቦች በሆኑባት አገር አልፎ አልፎ ከቅዱሳት መጻሕፍት ታሪኮችን ማጣቀሱ አግባብ እንደሆነ ጸሐፊው ስለሚያምን አንድ አስደናቂ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማስታወስን ይወዳል።
ከታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ከሰሎሞን ህልፈት በኋላ ቅድመ ልደት ክርስቶስ 930 ዓ.ዓ ገደማ የነገሠው ልጁ ሮብዓም በንግሥናው ማግሥት አንድ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመዋል። ከአባቱ ከንጉሥ ሰለሞን ጋር ጠብ ኖሮት ወደ ግብጽ ሸሽቶ የነበረ አንድ ሁነኛ ሹም ሮብዓም መንገሡን ሰምቶ ወደ ሀገር ከተመለሰ በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ሰብስቦ “ሰሎሞን ፈጽሞብን ነበር” የሚላቸውን በደልና የአገዛዝ ቀንበር በአዲሱ መንግሥትም እንዳይፈጸም ቃል እንዲገባላቸው ወደ ንጉሡ ሮብዓም መልዕክተኞችን ሰደደ።
ንጉሥ ሮብዓምም መልዕክቱ እንደደረሰው በአባቱ ዘመን የነበሩ በዕድሜና በእውቀት የበለጸጉ አዛውንቶችን ለምክር ሰብስቦ ምን ማድረግ እንዳለበት መልካሙን አቅጣጫ እንዲያመላክቱት ይጠይቃቸዋል። አዛውንቶቹም በንጉሡ ተግባር እጅግ ተደስተውና ምክር ፈላጊ መሆኑን በማድነቅ ካበረታቱ በኋላ በጎ ነው የሚሉትን ምክር እንዲተገብር እንዲህ ሲሉ አሳሰቡት። “የሚያዋጣህ ለዚህ ሕዝብ በገርነትና በቅንነት መገዛትህን ማረጋገጥ ነው።
ለሕዝቡ አገልጋይነትህን በግልጽ ንገራቸው። ከስህተትም ራስህን እንደምትጠብቅ አስረግጠህ አሳውቃቸው። ” ንጉሥ ሮብዓም የጠቢባኑን ሽማግሌዎች መልካም የምክር ቃል ከመስማት ይልቅ ልቡ ከእርሱ ጋር ወደ አደጉትባልንጀሮቹበማዘንበሉ፤የሽማግሌዎቹንምክር ንቆ አብሮ አደግ ብጤዎቹ የመከሩትን ምክር እንዲህ በማለት ለሕዝቡ አሳወቀ፤ “አባቴ ቀንበር ጭኖባችኋል፤ እኔ ግን ቀንበር እጨምረባችኋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል እኔ ግን በጊንጥ አገርፋችኋለሁ።
” መልዕክቱ የደረሰው ያ ሕዝብ ይህንን የምናምንቴዎችን ምክር እንደሰማ ተሰባስቦ በወሰደው እርምጃ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲቱ ታሪካዊቷ የአይሁዶች አገር በሰሜኑ ክፍል እስራኤል እና በደቡቡ ክፍል ደግሞ ይሁዳ ተብላ ለሁለት ተሰነጠረች።
ሁለቱም መንግሥታት ለሺህ ዓመታት እርስ በእርስና ከውጭ ጠላቶች ጋር በጦርነት እየተፋለሙና በምርኮ እየተጋዙ የሁለቱም ህልውና ከጠፋ በኋላ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሰባስበው እንደገና እየተፍገመገሙ በአንድ ሕጋዊ መንግሥት ጥላ ሥር ለመሰባሰብ የበቁት እ.ኤ.አ በሜይ 14 ቀን 1948 ነበር።
በምክክር አገር ይጸናል፤ ምክክር ሲጎድልም ዘመናት የሚሻገር ችግር ሊተከል ይችላል። “ከወርቅና ብር፤ ያበለጽጋል ምክክር” የሚባለውም ስለዚሁ ነው። እኛም ለኢትዮጵያችን ሰላምና ጤንነት፣ ለሕዝባችን እረፍትና በጎነት እንዲበዛ ችግሮቻችንን በምክክር ለመፍታት ዝግጁ እንሁን። ሰላም ይሁን!
“አገር ያለ ምክር፤ ቤት ያለማገር”
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014