ሁሉም አገር፣ ሁሉም የሰው ልጅ ትላንት ዛሬና ነገ አለው። እነኚህ የዘመን ፊት ኋላዎች ምንም እንኳን ተፈጥሮአዊ ቢሆኑም በሰው ልጅ አስተሳሰብ ስር ናቸው ።
አገር በዘመን ትሳላለች። ሕዝብ በዘመናት ሂደት ውስጥ ይፈጠራል። ይሄ ሁሉ ዓለምን የሞላው የሰው ልጅ በዘመናት ሂደት ውስጥ የተሳለ ነው። አገራችን ኢትዮጵያም በዚህ እውነት ውስጥ ያለፈች ናት። በዘመናት የተሳለች አገር ናት።
ሕዝቡም የትላንት የአስተሳሰብ ውጤት ነው። ድንቅ መሪ ድንቅ አገርና ሕዝብን ይፈጥራል በተቃራኒው እኩይ መሪ ደግሞ እኩይ አገርና ትውልድን ይፈጥራል። ይሄ ያለና የሚኖር የሰው ልጅ የጋራ እውነት ነው ፡፡
ኢትዮጵያ ትላንትና..
ለአፍታ የትላንቷን ኢትዮጵያ በአዕምሯችሁ ውስጥ ሳሏት። አገራችን የትላንት መልክ ዓለምን ያስደነቀ ገና መልክ ነበር። የአሁኑ የዓለም ስልጣኔ የኢትዮጵያን አለላ መልክ ተከትሎ የመጣ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ባለፈው ዘመን ላይ በአስተሳሰብ፣ በመሪነት ጥበብ ከዓለም ቀዳሚ ሕዝቦች ነበሩ፡፡
ለዓለም ስልጣኔ፣ ለዓለም አሁናዊ ገጽታ አሻራቸውን ካሳረፉ አገራት መካከል እኛና አገራችን ቀዳሚዎቹ ነበርን። በሀሳባቸው ድንቅ አገርና ሕዝብ የፈጠሩ፣ በእምነታቸው ለፈጣሪ የተገዙ ደጋግ ነፍሶች ነበሩን።
አክሱምና ላሊበላ የነዚያ ዘመን አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው። ዛሬ ላይ እንደ ነውር የምናያቸው ድንቅ ሥርዓቶቻችን የዛኛው ዘመን አለላ መልኮች ናቸው። በዚህ እውነት ውስጥ መኖር ደስታው ምን ያክል እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡
ዘመን በዘመን ተተክቶ ሲያልፍ ኢትዮጵያዊነት ያደበዘዘው ኢህአዲግአዊ ሥርዓት መጣ። ሌላ አገርና ትውልድ ተፈጠረ። ኢትዮጵያዊነት የተበላሸበት ትክክለኛ ቦታ የአሸባሪው ሕወሓት የሥልጣን ዘመን ነው እላለው።
አባቶቻችን አገር ለማቆም ፍቅርን ነበር የመረጡት። አባቶቻችን ትውልድ ለመፍጠር አንድነትን ነበር የተጠቀሙት። አሸባሪው ሕወሓት የፖለቲካ አስተሳሰብ ግን ኢትዮጵያዊነትን ማበላሸት ነው ። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን መርጦ የዛሬዎቹን እኛን ፈጥሯል። የዛሬዎቹ እኛ የሃያ ሰባት ዓመታት የሴራ ፖለቲካ ውጤቶች ነን።
በልባችን ውስጥ ድሮነት የለም። በነፍሳችን ውስጥ አገርና ሕዝብ መክነዋል፡፡አሸባሪው ሕወሓት ጫካ ውስጥ የተፈጠረ ቡድን ነው። እንደሚታወቀው ጫካ የአራዊት መኖሪያ እንጂ የሰው ልጅ መኖሪያ አይደለም። ሰው ኑሮውን ይመስላል እንደሚባለው የቡድኑን መነሻ አስታውሰን መድረሻውን መገመት ይከብደናል ፡፡ የሰው ልጅ አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ኃይልም ጭምር ነው፣ ሰላም ለማስፈን ጫካ መግባት ይኖርበታል ብዬ አላስብም።
አሸባሪው ሕወሓት ግን አደረገው.. ዓላማው ታሪክ ማበላሸት ነበርና ከጫካ ወጥቶ እንዳሰበው አደረገ፡፡የአባቶቻችንን ርስት አበላሸ። በውሸት ፖለቲካ ሕዝብን ለያየ። ወንድማማቾችን ደም አቀባባ። በብሔር በጎሳ ከፋፍሎ አገርና ሕዝብን አይጥና ድመት አደረገ።
ይሄ ሳይበቃው በለውጡ ዋዜማ ላይ የተለኮሰ የተስፋ ችቧችንን ሊያጠፋ ለዳግም ጥፋት የትግራይን ሕዝብ መያዣ አድርጎ መቀሌ መሽጓል። ይሄው መከራዋ ላላባራ አገራችንን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ስቃይ ሆኖናል።
የአሸባሪው ሕወሓት የስልጣን ዘመን የትላንት ፀዐዳ መልካችንን ያጣንበት፣ ከእውነት ይልቅ በሸር ፖለቲካ መከራችንን ያየንበት ነው ። የአባቶቻችንን ሀቅ ቆሽሾ፣ እምነታቸውን ንዶ በውሸት ድራማ መካን ትውልድ የፈጠረበት ዘመን ነው ። ከእውነትና ከፍትህ ይልቅ ለእሱ እንደሚመቸው አድርጎ አገርና ትውልድ የቀረጸበት የግዞት ጊዜ ነው ፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ . . . ዛሬ
ለኢትዮጵያ ሁለት መልክ አላት። አንደኛው በአሸባሪው ሕወሓት የስልጣን ዘመን የደበዘዘው መልኳ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በለውጡ መንግሥት የፈገገው ቀይ ዳማ መልኳ ነው ። ከድብዛዜ ለመውጣት የምታጣጥር አንዲት ቀይ አበባ ትታየኛለች..ፍካትየከበባት..ተስፋ የሞላት አበባ።
ይቺ አበባ ኢትዮጵያ ናት። ይቺ አበባ እኔና እናንተ ነን። ይቺ አበባ ትውልድ ናት። የዛሬው ሁኔታችን በዚች አበባ ይመሰላል። በተስፋና በፍካት ውስጥ ሆነን ወደ ፊት ለመሄድ እንቅስቃሴ ላይ ነን።
አሸባሪው ሕወሓትና የመሳሰሉ አንዳንድ እኩይ ኃይሎች ፍካታችንን ሊያደበዝዙ ቢሰለፉም ህብረት በወለደው ጽናት እያሸነፍናቸው ነው። ዛሬ ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ሕይወት ጅማሬ ነው። የአባቶቻችንን የአንድነትና የጽናት መንፈስ የምንላበስበት ሰሞነኛ ነው ፡፡ ምንም እንኳን የአሸባሪው ሕወሓትና አስተሳሰቡ በዙሪያችን ቢኖሩም፣ ለዘመናት የተበተባቸው የሴራ ፖለቲካው መንገዳችን ላይ ቢቆሙም እያሸነፍን ወደ ፊት ከመሄድ የሚያግደን የለም። መንግሥት የቡድኑን አስተሳሰብ ሰብሮ በትውልዱ ልብ ውስጥ አዲስ አስተሳሰብን ለመትከል እየሠራ ይገኛል።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተለቁበት የሰውነት ደብር ሊፈጠር ትጋት ላይ ነው። በዚህ የአንድነት ርብርብ ላይ ከእኔነት የተለቀ አገርና ሕዝብ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከመንግሥት ጎን በመቆም አጋርነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሱ የሚያቆማቸው የለም።
አሁንም በአንድነት በመቆም ከሀዲውን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡን ጭምር ታሪክ የምናደርግበት ነው ፡፡ ትላንትና ዛሬ ለእኛ ለ ኢ ት ዮ ጵ ያ ው ያ ን የተለያዩ ገጾች ናቸው። በትላንት ገጽ ላይ ገናና ታሪክ፣ ገናና አገርና ሕዝብ ነበር ያለው። ፍቅርና አብሮነት ነበር።
በአሁን ገጽ ላይ ደግሞ አሸባሪው ሕወሓትና እኩይ አስተሳሰቡ አሉ ። የቡድኑ የስልጣን ዘመን ለኢትዮጵያውያን የጭንቅ ዘመናት ነበሩ። አንዳንዴ አፈ ታሪክ እንጂ በእውነት የሆነ ሁሉ አይመስልም። ምክንያቱም እንደዛ አይነት በደልና ግፍ፣ እንደዛ አይነት ጭካኔ፣ እንደዛ አይነት የመግደልና የማሰቃየት ሱስ፣ እንደዛ አይነት ራስ ወዳድነት በየትኛውም አገርና ሕዝብ ላይ ደርሶ አያውቅም ።
በአባቶቻችን ጠንካራ አስተሳሰብ የቆመችን አገር ለመናድ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ደክሟል። አባቶቻችን አገር ለማጽናት፣ ሕዝብ ለማነጽ ደክመው ነበር። አባቶቻችን ታሪክ ለመሥራት፣ ባህል ለማቆየት ሞተውና ቆስለው ነበር። አሸባሪው ሕወሓት በተቃራኒው በአባቶቻችን ሥርዓት የጸናችን አገር ለማፈራረስ በጽናት ተንቀሳቅሷል።
በሃያ ሰባት ዓመት የተንኮል ፖለቲካ ውስጥ የአሁኗን የተጎሳቆለች ኢትዮጵያ ፈጥሯል። ምን አገኘ? ምንም። ራሱን በታሪክ ተወቃሽ ከማድረግና ለትውልዱ ነውር ከማውረስ ባለፈ የጠቀመው ምንም የለም። አሁን ድረስ በአሸባሪው ሕወሓት አስተሳሰብ በተዛባች አገር ውስጥ ነን። ቡድኑ ለአገር እንድንመች ሳይሆን ለራሱ እንድንመች አድርጎ ነው የቀረጸን።
ሕዝብ እንድናገለግል ሳይሆን እሱንና ፖለቲካውን እንድናገለግል አድርጎ ነው የሠራን። ተምረን እንድንለወጥ ሳይሆን፣ ሠርተን ለአገራችን ምርጡን እንድናደርግ ሳይሆን በሁሉም እንቅስቃሴያችን ውስጥ ባሪያው ሆነን እንድንኖር አድርጎ ነው ያበጀን። ይሄን ወንዝ የማያሻግር የሴራ ፖለቲካ ለመበጣጠስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን በጽናት ልንነሳ ይገባል።
ስለ አገር የሚጨነቁ ልቦች የታማኝነት አብራክ ናቸው። በአባቶቻችን ነፍስ ውስጥ እንጂ በአሸባሪው ሕወሓት ነፍስ ውስጥ እኚህ ሁሉ የሉም። እጆቹ ለአገር ሠርተው ስለማያውቁ በእንጀራ ጠርዝ የሚደሙ ናቸው። በጭንቅላቱ ውስጥ እኔነት እንጂ አገርና ሕዝብ የለም። ልቡም የክፋት ዋሻ ነው። ለአገር መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው።
ለአገር መሥራት መብት የሚመስለን ሞልተናል ግን አይደለም። አገር እኔና እናንተ ናት። አገር የእኔና የእናንተ ሀሳብ፣ ምኞት፣ ህልም፣ ስኬት መነሻና መድረሻ ናት። አገር የእኔና የእናንተ መልክ፣ ታሪክ፣ ማንነት ሌላም ሌላም ናት። የእኔና የእናንተ ሰውነት በአገራችን በኩል የሚንጸባረቅ ነው።
ለአገርና ሕዝብ መሥራት የሰው ልጅ ሁሉ ግዴታ ነው።ይሄ እውነት ያልገባው አሸባሪው ሕወሓት ብቻ ነው። ብልሆች በሥልጣን ዘመናቸው አገራቸውን ሲለውጡ ሕወሓት ግን በስልጣን ዘመኑ ራሱን ብቻ ነው የለወጠው።
የአሜሪካ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ካለፈ ዘመን የለውም ዛሬም ድረስ ግን የአሜሪካውያን አባት እየተባለ ነው የሚጠራው። ሰው በሠራው ሥራ ልክ ነው የሚታወሰው።
አሸባሪው ሕወሓት ስሙን በእኩይ መዝገብ ላይ ከማስፈር ባለፈ ለዚች አገር የሠራው አንዳች ነገር አለመኖሩ የሁልጊዜ አግራሞቴ ነው፡፡
አገር መልካም ልብ ትሻለች። ትውልድ ቀና ልብ ይሻል። ለአገር መድከም ዕረፍት ነው።
ለሕዝብ መልፋት ደስታ ነው። እንደ ሕወሓት ያሉ አገር ለማውደም የደከሙት ደግሞ ትውልድ በክፉ ሲያነሳቸው ይኖራል። ሁሉም መልካም ነገሮች በመልካም ሰዎች የተፈጠሩ ናቸው።
አንድ ፓርቲ መንግሥት ሆኖ ወደ ስልጣን ሲመጣ የመጀመሪያም የመጨረሻም ዓላማው አገርና ሕዝብ መሆን አለበት። በአሸባሪው ሕወሓት ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ግን እነዚህ ነገሮች አልነበሩም። መልካም አገር ሁልጊዜም መልካም መሪ ይፈልጋል።
እኛ አገር አብዛኞቻችን ራስ ወዳድ ስለሆንን ከሕዝብና ከአገር ይልቅ ራሳችንን ነው የምናስቀድመው። ሕወሓት የስልጣን ቆይታው ውስጥ አገርና ሕዝብን አስቀድሞ ቢሆን ዛሬ ላይ አገራችን በዚህ ልክ ኋላ ባልቀረች ነበር። ዛሬ ላይ በድህነትና በኋላ ቀርነት ባልማቀቅን ነበር።
ዛሬ ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው አገራችን መልካም መሪ ያስፈልጋታል። የአባቶቻችን ትላንትና ምስጢሩ መልካም ልብና መንፈስ ነበር። በመልካም ልብ አገር መምራት ልክ እንደ ሙሴ አገርና ሕዝብን ባህር ማሻገር ነው።
እኛም በመልካም ልብ አገር ልንመራ ይገባል ፡፡
ኢትዮጵያ ነገ . . .
የነገዋ ኢትዮጵያ ምን አይነት ትመስላችኋለች? የነገዋ ኢትዮጵያ በዛሬዋ እኔና እናንተ የምትፈጠር ናት። አሸባሪው ሕወሓት በትላንት አስተሳሰቡ የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንደፈጠረ ሁሉ የዛሬዎቹ እኔና እናንተ ደግሞ የነገውን አገርና ትውልድ የመፍጠር ኃይል አለን። በነጋችን ውስጥ ታላቅ ትውልድ እንድንሆን ዛሬ ላይ ታላቅ ነገር እናስብ፣ ታላቅ ነገር እናድርግ።
በነጋችን ውስጥ ፍሬ እንድናፈራ ዛሬአችን ላይ መልካም ዘር እንሁን። ጸጸትና መክሰር፣ መለያየትና መገፋፋት እንዳይኖር ዛሬን በፍቅር እንኑር። አሁንን በይቅርታ እንጀምር። ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌላውም በማሰብ የጋራችን የሆነችን ኢትዮጵያ እንፍጠር።
መንግሥት አዲስ አገርና አዲስ ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ ትጋት ላይ ይገኛል ይሄን የአንድነት መንፈስ በመቀላቀል ነገ ለምትፈጠረው መልካም አገር የበኩላችንን አስተዋጽዖ እናድርግ ። ለአገር የሚሠሩ እጆች ምንም ያክል ቢሻክሩም ፀዓዳ ናቸው።
እኛ የነጋችን ሰዓሊዎች ነን። እኛ የነገ የአገራችን ዕጣ ፋንታ ወሳኞች ነን። ዛሬ ላይ መልካም ከሆንን ነገ ላይ ይሄንኑ ነው የምናጸባርቀው። ነጋችንን ዛሬ በትጋት እንስራ፤ አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 5/2014