ራስን ማብቃት አገርና ትውልድ ከሚገነባባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው።ዛሬ ላይ እንደ አገር ዋጋ እያስከፈሉን ያሉ ሃሳበ አሸባሪው ሕወሓቶች ከቁስና ከአፍቅሮተ ንዋይ ባለፈ ብቃት የሌላቸው አካል ለበስ ሰውነቶች ናቸው።
ሁሉም ሰው የራስ እውነት አለው።በዚህ ግላዊ እውነት ተረማምዶ አገር ሊጠቅምም ሆነ ሊጎዳ ይችላል።በዚህ የራስ እውነት ተንጠራርቶ የራሱን ነገ ሊገነባም ሆነ ሊያፈርሰ ይችላል።
እንደዚሁ ደግሞ ሁላችንም አገርና ህዝብ የሚጠቅም የጋራ እውነት አለን።የጋራ እውነት እንደ ዜጋ፣ እንደ ነዋሪ፣ እንደ ማሕበረሰብ ለአገራችን የምናዋጣው ሕዝባዊ አስተዋጽኦ ማለት ነው። ይህ የጋራ እውነት ለአገራችን ባለን ፍቅር፣ ባለን የስራ ባህል፣ ባለን ተነሳሽነት፣ ባለን ተቆርቋሪነት፣ ባለን ማሕበራዊ ተሳትፎ የሚገለጽ ነው።ከነዚህ አገራዊ የጋራ እውነቶቻችን መካከል ራስን ማብቃት አንዱና ዋነኛው ነው።
በማሕበረሰቡ ዘንድ እንደ ዜጋ ስንኖር ለአገር የሚበጅ መልካም ተግባራትን ማከናወን የሁላችንም የውዴታ ግዴታ ነው።በምንችለው አቅም ሁሉ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለአገራችን ያለንን ፍቅር እንገልጻለን።ይሄ በሁሉም የዓለም አገራት ያለ የሁሉ ማሕበረሰብ የጋራ እውነት ነው።ዜጋ ተብለን በኢትዮጵያዊነት እስከተጠራን ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል ለጋራ ጥቅም በጋራ የመትጋት ግዴታ አለብን።
በተለይ አገርና ሕዝብ ችግር ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቆርቋሪነትን ማሳየት የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው።የጋራ እውነት የአገርን ጥቅም በማስቀደም ከፊት መቆም ነው።የጋራ እውነት ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት የሚገለጽ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው።
የጋራ እውነት ራስን በበጎ ነገር በመለወጥ አገርና ሕዝብን ለመለወጥ መትጋት ነው።ከዚህ እውነት በመነሳት ራስን ማብቃት በሕብረተሰቡ ዘንድ እንደ አንድ ችግር ፈቺ የመፍትሄ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት አገራችን ላለችበት ወቅታዊ ችግር እራስን አብቅቶ መገኘት እንደ ትልቅ የልማት ሃይል በመሆን አገርና ሕዝብ ብሎም ትውልድ የሚጠቅም የተስፋ ብርሃን ነው።
በዚህ የውጭ ሃይሎች በተነሱብን ወቅት፣ ለልማትና ለብልጽግና በተነሳንበት ዘመን ፣ ወደ ከፍታ በምንሄድበት ብርሃናማ ወቅት ላይ፣ የእኛ አብሮነት እና መነሳሳት ግድ በሚልበት በዚህ ጊዜ እራስን አብቅቶ መገኘት የለውጡ አቅም ሆኖ መገኘት ጭምር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ምድር እንዲሆን ለምንፈልገው ለማናቸውም መልካም ነገር እራስን አብቅቶ መገኘት ወሳኝ ነው።ብዙ የግል እውነት ቢኖረንም፣ በብዙ ልዩነት ውስጥ ብንሆንም አገራችን ግን የጋራ ጉዳያችን ናት።እያንዳንዱ ዜጋ ባለበት የሙያ መስክ ላይ ራሱን በማብቃት የአገሩን መጻኢ እድል መወሰን ይችላል።
እያንዳንዱ ባለሥልጣን፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ሃላፊነት ይሰማኛል የሚል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገር የሚበጅ ታማኝና አስፈላጊ ዜጋ አድርጎ ራሱን በመቅረጽ ከችግር ፈጣሪነት ወደ ታማኝ አገልጋይነት መሸጋገር ይችላል።የአገር ልዕልና ከእያንዳንዳችን የሚዋጣ የእያንዳንዳችን የብቃት ውጤት ነው።የአገር ክብር ከእያንዳንዳችን የጋራ እውነት ውስጥ የሚወጣ የአብሮነት ጥግ ነው፡፡
የሕዝቦች መጻኢ እድል በእኔና በእናተ የሃላፊነት ልክ የሚወሰን ነው።ይሄ እንዲሆን ከዘልማድ ወጥቶ በምክንያት የሚኖር ዜጋ ያስፈልገናል።በምክንያት የሚኖር ማሕበረሰብ በንግግር የሚያምን፣ ከውሳኔ ይልቅ ውይይትን ያስቀደመ ነው።ከእኔነት ይልቅ እኛነትን፣ ከብቻ ይልቅ አብሮነትን ያስቀደመ ትውልድ ነው።
በጋራ ታሪክ ለመስራት የታጠቀ፣ ለአገር ክብር እስከመጨረሻው የሚሰለፍ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ መሰሪው ሕወሓት ባልተገባ ሃላፊነት ታሪካችንን አበላሽቶብናል።ግድ በሌለው አካሄድ ኢትዮጵያዊነታችንን አጠልሽቶብናል።ከወንበዴዎች ጋር እየተቧደነ በአገርና ሕዝብ ላይ ይሄ ነው የማይባል ግፍን ፈጽሟል።በከፈተብን ጦርነት ብዙ ነገራችንን አሳጥቶናል።
እኚህን ሁሉ አገራዊ ውድመቶቻችንን ለመመለስ አገር ለመስራት ትውልድ ለመፍጠር የበቃና የነቃ ማሕበረሰባዊ ሃይል ያስፈልጋል።ጠንካራ አገር በጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚገነባ ነው።አገር እምነት ትሻለች።ትውልድ ሀቅ ይፈልጋል፡፡
አንዳንዶች ከዚህ እውነት የሸሸን ነን።በጊዜያዊ ጥቅሞች ታውረን አገር ለመሸጥ የምናስማማና የምንስማማ ነን።የበግ ለምድ ለብሰን እንደ ይሁዳ ያመነንን ሕዝብና አገር አሳልፈን ለመስጠት የምንቀሳቀስ ነን።እንደ ሕወሓት ቡድን አደራ በልተን፣ እምነት አጉድለን እንደተቆርቋሪ መርዘኛ ድምጻችንን እያሰማን የቆምን ሞልተናል።አገር ውስጥና ከአገር ውጪ በሞቀ ቤት ውስጥ ሆነን ዶላር እየቆጠርን አገር ለማፍረስ በኮምፒዩተር ቁልፍ የምንጫወት አለን፡፡
አገርና ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ ለማሳነስ የምንማር፣ ትውልድ ከመፍጠር ይልቅ ለመመረዝ የምንሰራውን ቤት ይቁጠረን።አገርና ሕዝብ ከማስቀደም ይልቅ ለራሳችን ግለሰባዊ ክብርና ዝና ቅድሚያ የምንሰጥ እንዲህም ነን።የአገራችንን ወቅታዊ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ወንዝ የማያሻግር የግል ጉዳያችንን ይዘን እኔ ልቅደም አገርና ሕዝብ ይከተል የምንል ነን።ይህ እንዳይሆን ራሳችንን ማብቃት ግድ ይለናል።
ይህ እንዳይሆን የአገርንና የሕዝብን ጥቅምና ዋጋ መረዳት ይኖርብናል።ይህ እንዳይሆን የአባቶቻችንን የትናንት እውነት፣ የትናንት መልክ መመርመር አለብን፡፡ ዛሬ ላይ ከአገር ጉያ በቅሎ የአገር ጠላት የሆነው አሸባሪው ሕወሓት ይሄን ሁሉ ኪሳራ ያደረሰብን ከእኔነት ባለፈ ለአገር የሚመጥን ሥነ ልቦናል ስላልገነባ ነው።
ሕጻን ልጅ የሚደፍር፣ መለኩሴ እስከመድፈር፣ ነፍሰ ጡር እስከማሰቃየት የሚደርስ ማንነት ከሕወሓት ውጪ የማንም ሊሆን አይችልም።በድሃ ሕዝብ የተሰራን መሰረተ ልማት ማውደም የዚህ ቡድን ግብር ከመሆን ውጪ የሌላ አይሆንም።ይሄ ማንነት ነው ዛሬ ላይ አገሬን ከክብሯ ዝቅ ያደረጋት…በበቃ ሰውነት አገርና ትውልድ እንፍጠር ስል ያነሳሁትም ለዚህ ነው፡፡
ወቅቱ ከመቼውም በላይ ለአገር ክብር ዘብ የምንቆምበት ባለውለታነታችንንም የምናሰመሰክርበት ወቅት ነው።ችግር ፈጣሪ ከመሆን ወጥተን በላቀ እሳቤ ለሕዝብ የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን።ኢትዮጵያ እየጠራችን ነው…ኑ ክበቡኝ..ኑ በአንድነት በዙሪያዬ ቁሙ እያለችን ነው።ኑ እርዱኝ…በተባበረ ክንድ በፊቴ ቁሙ እያለችን ነው።ይሄ ጊዜ የአገራችንን ድምጽ የምንሰማበት ወቅት ነው።
ይሄ ጊዜ የአባቶቻችንን የአደራ ቃል የምንፈጽምበት ሰሞን ነው። በጋራ እውነታችን ውስጥ የጋራችንን ስዕል እንሳል።አላዋቂነት ይበቃናል።ብዙዎች የራሳቸውን አገር እየገነቡ የእኛን አገር ለማፍረስ እየነቀነቁ ነው።ቤታቸው ቁጭ ብለው በእኛ አላዋቂነት ቁማር እየተጫወቱ ነው።የእኛን አላዋቂነት እየተጠቀሙ እየጎዱን ነው።
በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ከእውነት የጎደለ ስር የሰደደ የእውቀት ማነስ አለ።አገርን የመክዳት፣ ታሪክን የመርሳት፣ ከሕዝባዊነት ይልቅ ለግለሰባዊነት ቅድሚያ የመስጠት የእውቀት ውስንነት አለ።የጥላቻ፣ የመለያየት ጎደሎነት አለ።
ራሳችንን እናንቃ።ራሳችንን በጋራ እውነት እንገንባ።እንደ ሕወሓት ወንበዴዎች የእውቀት ማነስ ማየት ያለብንን እንዳናይ፣ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገር ቅድሚያ እንዳንሰጥ የሚያደርግ ማሕበራዊ እንቅፋ ነው።
ራስ ወዳድነት የእውቀት ማነስ በጊዜአዊ ጥቅም ነገን የሚሰውር አይነጥላ ነው።የእውቀት ማነስ ታሪክ የሚያበላሽ፣ ሕዝብ የሚነጣጥል የፍቅር ጠላት ነው።ከዚህ እንቅፋት በመውጣት ራሳችንን ማብቃት ይኖርብናል።
ሳንበቃና ሳንነቃ የምንፈጥረው አገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ሥልጣኔ የለም።ሳንበቃና ሳንነቃ በጋራ የምንጽፈው የጋራ ታሪክ የለንም።ሳንበቃና ሳንነቃ የምንገነባው አዲስ ሰማይና ምድር የለም።ሁሉም ነገር ያለው በንቃታችን ውስጥ ነው።ሰላማችን፣ ብልጽግናችን ያለው በንቃተ ህሊናችን ጓዳ ውስጥ ነው።አሁን እየሄድንበት ባለው ውስንነት የምናተርፈው ትርፍ የለም።
የእውቀት ማነስ ልክ እያስመሰለ ስህተት የሚያሰራ የጉዳቶች ቁንጮ ነው።እስካሁን ድረስ በራሳችንም ሆነ በሌላው ላይ የፈጸምናቸው ልክ የሚመስሉ ስህተቶች ባልበቃ ጭንቅላት የፈጠርናቸው ናቸው።
ግለሰባዊ ዋጋችን ያለው በንቃታችን ውስጥ ነው።አገራዊ ትርፋችን ያለው በመዋደዳችን ውስጥ ነው።ብዙ ብርሃናማ ነገዎችን የምናየው ከድንግዝግዝ ሕይወት ወጥተን አርቀን ማየት ስንችል ነው። እዚህ ዓለም ላይ ዋጋ ያላቸው ጠቃሚ ነገሮች በእውቀት የተሰሩ ናቸው።ይሄ አለም ውብ ሆኖ የምናየው በብዙ እውቀቶች ውስጥ አልፎ ነው።
ራሳችንን የምንፈጥረው፣ ራሳችንን ወደ ፊት የምናራምደው የበቃ አእምሮአዊ ንቃት ሲኖረን ነው።ችግሮቻችን የዶግ አመድ የሚሆኑት በእውቀት ስንራመድ ነው።አሁናዊም ሆነ ትናንትናዊ የአገራችን አብዛኛው ችግር በእኛ የንቃት ማነስ የመጣ ነው።ወይም ደግሞ እንደ ሕወሓት ባሉ እያወቁ በሚስቱ አጥፊዎች የተባባሰ ነው፡፡
እዚች አገር ላይ ብዙ እውቀት አለ ሁሉም እውቀት ግን በራስ ወዳድነት ቁጥጥር ስር ነው።እዚች አገር ላይ ብዙ የተማሩ አሉ… ሁሉም የተመሩ ሰዎች ግን ችግር ፈጣሪዎች፣ ሕዝብ አስጨናቂዎች ናቸው ፤ ለዛም ነው ራስን በማብቃት አገር እናሻግር ፤ ለዛም ነው በዳግማዊ ለውጥ ከህዝብ ጎን እንቁም የምለው፡፡ አገር የጋራ እውነታችን ናት… የመጨረሻውን መስዋእት መክፈል ካለብን ለአገራችን ነው።የመጨረሻውን መስዋዕት መክፈል ካለብን ለሕዝባችን ነው።
አገራችን ለእያንዳንዳችን ምድር ላይ ያለች መንግሥተ ሰማያታችን ናት።ክፉም ለመሆን፣ ደግም ለመሆን እንደፈለገን የምንሆንባት አገር ታስፈልገናለች።ለዚህም የክህደት ጥርስ አብቅለው ሊቦጫጭቁን ከተነሱ ሕወሓትና ሕወሓት ወለድ ቡድኖች ልንጠብቃት ይገባል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014